አእምሮና ነፍስ የሚገለጡት በሥነ አካል በመሆኑ ሕሊናና መንፈሳዊ ኃይል በአብዛኛው በአካላዊ ብርታትና ችሎታ ላይ የሚተማመኑ ናቸው፡፡ አካልን የሚያሳድግና ጤናን የሚጠብቅ ማናቸውም ነገር ሁሉ የጠነከረ አእምሮ ዕድገትና በጥሩ ሁኔታ የተስተካከለ ባህሪይ እድገት ያመጣል፡፡ ያለጤንነት ማንም ሰው ቢሆን አውቆና ለይቶ ማስተዋል ወይም ለራሱና ለወገኖቹ እንዲሁም ለፈጣሪውም የሚኖርበትን ግዴታ ሙሉ ለሙሉ አስተካክሎ መፈፀም አይችልም፡፡ ስለዚህ ጤንነት በባሕሪይ ሊደረግ የሚገባውን ያክል ጥንቃቄና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ስለ አካል አሠራርና ስለንጽህና የሚኖረን ዕውቀት የትምህርት ሁሉ መሠረት ነው፡፡ EDA 216.1
ምንም እንኳን ባሁኑ ጊዜ ስለ አካል ምንነት የተገኙ ጭብጦች አጠቃላይ ግንዛቤ የተገኘባቸው ቢሆኑም የጤናን መርሆች በሚመለከት አስጊ የሆነ ቸልተኝነት ይታያል፡፡ የእነኝህ መሠረተ ሐሳቦች ዕውቀት ካላቸው ሰዎች መካከል እንኳ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሕይወት በግልጽ ተወስነው በተቀመጡና የማይለዋወጡ ሕጐች መሠረት የምትገዛ መሆኗ ቀርቶ እንዲያው በጭፍኑ በአጋጣሚ ዕድል ብቻ የምትኖር ናት የሚል ዝንባሌ አለ፡፡ EDA 216.2
ወጣቱ ትውልድ በትኩስ ኃይልነቱ ምክንያት የእነዚህን በረከቶች ዋጋ እምብዛም አይገነዘብም፡፡ ከወርቅ የበለጠ ክብር መዝገብ፣ ከትምህርት፣ ከደረጃ፣ ከሀብት ሁሉ በላይ የበለጠ ሆኖ ሳለ እንደ ቀላል ነገር በጥድፊያ ማባከን አለ፡፡ ለሐብት ወይም ለሥልጣን ሲታገሉ ጤናቸውን በመስዋዕትነት እየከፈሉ ካሰቡት የደረሱ ቢሆኑም መጨረሻቸው ያለ ረዳት መቅረት ሲሆን ሌላው ደግሞ የበለጠ ጠንካራ የአካል ብቃትን በመያዝ የተመኘውን ዋጋ የጨበጠም አለ፡፡ በተበላሸ ሁኔታ ውስጥ ገብተው የጤናን ሕጐች በመናቅ በውጤቱ ወደ መጥፎ ተግባር ተሰማርተው ለዚህ ዓለምና ለሚቀጥለውም ያላቸውን ተስፋ ሁሉ ያጡ ስንቶች ናቸው! EDA 216.3
ስለ አካል የሚደረግ ጥናት ውስጥ ተማሪው የሰውነት ኃይል ምን ዋጋ እንዳለውና እንደትስ ሊጠበቅና ሊያድግ በሕይወት ታላቅ ትግልም ውስጥ በአብዛኛው ለእድገት መስተዋጽኦ እንዲኖረው መደረግ እንዳለበት እንዲያይ መመራት አለበት፡፡ EDA 217.1
ልጆች ከህፃንነታቸው ጀምሮ መሠረታዊ የሥነ-አካልና የንጽህና ወይም ሃይጅን ትምህርት በቀላል አቀራረብና ቀለል ያሉ ትምህርቶች ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ሥራው መጀመሪያ በቤት ውስጥ በእናት አማካይነት ይጀመርና በትምህርት ቤትም በታማኝነት መቀጠል አለበት፡፡ በእድሜአቸው እያደጉ ሲሄዱ በዚህ መስመር የሚሰጠው ትምህርት ተማሪዎቹ ለሚኖሩበት ቤት መጠንቀቅ እስከሚጀምሩ ድረስ መቀጠል አለበት፡፡ የእያንዳንዱን የአካል ክፍል ከበሽታ የመከላከልን አስፈላጊነት ማስተዋል አለባቸው፡፡ የተለመዱ በሽታዎችንና አደጋዎችን እንዴት መከላከል እንደሚችሉም መማር አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የሥነ-አካልና የአጠቃላይ ንጽህና ትምህርት መስጠት አለበት፡፡ ደግሞም በተቻለ መጠን የአካልን ቅርጽ አጠቃቀሙንና ሊደረግለት የሚገባውን ጥንቃቄ የሚያሳዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ማሟላት አለበት፡፡ EDA 217.2
በሥነ-አካል ጥናት ውስጥ ብዙ ጊዜ የማይካተቱ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ለተማሪው እነኝህ ጉዳዮች በዚህ ርዕስ ሥር ከሚሰጡ ቴክኒካዊ ትምህርቶች ሁሉ የበለጠ ዋጋ ያላቸው ሆነው መታሰብ ያለባቸው ናቸው፡፡ በነዚህ መስመሮች የትምህርት ሁሉ መሠረት የሆኑትን የተፈጥሮ ሕጐች የእግዚአብሔር ሕጐች መሆናቸውን ወጣቱ መማር አለበት፡፡ የሙሴ ሕግ ወይም አሥርቱ ትዕዛዛት የተፃፉበት ሐሳብ በእርግጥ መለኮታዊ የሆኑትን ያክል እነዚህም የእግዚአብሔር ሕጐች ናቸው፡፡ የሰውነት ብልቶቻችንን የሚገዙ ሕጐች እግዚአብሐር በእያንዳንዱ ነርቦች፤ ጡንቻዎችና በአካላችን ውስጥ እንደ ጭራ ባሉ ቀጫጭን ሥሮች ላይ ሁሉ ጽፎባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ መግዴለሽነት ወይም እያወቁ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ስህተት ሁሉ የፈጣሪን ሕግ መፃረር ነው፡፡ EDA 217.3
እንግዲህ የእነዚህ ሕጐች ዝርዝር ዕውቀት ምንኛ አስፈላጊ ነው! ለምግብና ለመጠጥ፤ ስለ ሰውነት ማጐልመሻ ልምምድ፤ ለልጆች ስለሚደረግ እንክብካቤ፣ በሽተኛን ስለ ማስታመምና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ለአጠቃላይ ንጽህና መሠረታዊ ሐሳቦች በተለምዶ ከምንሰጠው የበለጠ ልዩ ትኩረት ልናደርግበት ይገባል፡፡ EDA 218.1
አእምሮ በአካል ላይ ያለው ተጽዕኖና በአፀፋውም አካል በአእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ መብራራት አለበት፡፡ በሕሊና ሥራዎች አማካይነት የሚንቀሳቀሰው የአእምሮ ኤሌክትሪካዊ ኃይል አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በዋናነት የሚቆጣጠር ሲሆን በሽታን በመከላከል ረገድም ከፍተኛ አገዜታ አለው፡፡ ይህ ግልጽ መደረግ አለበት፡፡ የመሻት ሁሉ ኃይልና ራስን የመቆጣጠር አስፈላጊነት፤ ጤንነትን በመጠበቅም ሆነ በሽታን በመፈወስ፣ በሁለቱም መንገድ በኩል፤ የቁጣ፣ የቅሬታ፣ ራስን የመውደድና፣ የልብ ንጽህና ጉድለት ውጤት የሆነው የሐዘን ስሜት ወይም ከዚያ የከፋ አጥፊ የሆነ ውጤቱና በሌላ በኩል ደግሞ ግሩም ድንቅ ሕይወት ሰጪ ኃይል በየዋህነት ራስን ባለመውደድ፤ በለጋስነት ውስጥ በመገኘት ሊታይ ይገባዋል፡፡ EDA 218.2
ስለ ሥነ አካል አንድ እውነታ አለ፡፡ ልናመዛዝነው ወይም ልናስብበት የሚገባ እውነት ይኸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ደስ ያላት ልብ መልካም መድሃኒት ናት፡፡» ምሳሌ 17፡22፡፡ EDA 219.1
ልጄ ሆይ ፣ ሕጌን አትርሳ ልብህም ትዕዛዜን ይጠብቅ፡፡ ይላል እግዚአብሔር «ለሚአገኟት ሕይወት ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና፡፡ ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃል፡፡» መጽሐፍ ቅዱስ «ያማረቃል» «ለነፍስ ጣፋጭ» መሆኑ ብቻ ሳይሆን «ለአጥንትም ጤና ነው» በማለት ይገልፀዋል፡፡ ምሳ 3፡1፡2፡፡ ምዕ 4፡22 ምዕ 16፡24 EDA 219.2
ወጣቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን «እግዚአብሔር የሕይወት ምንጭ፡፡’ (መዝ 36፡9) የመሆኑን እጅግ ጥልቅ ዕውቀት በሚገባ ሊያስተውለው ይገባል፡፡ እርሱ ሁሉን የፈጠረና ከመጀመሪያ ያመጣው ብቻ ሳይሆን አሁን በሕልውና ላይ ለሚኖረው ሁሉ ሕይወትም ነው፡፡ በፀሐይ አማካይነት የምናገኘው በንፁህ ጣፋጭ አየር፣ ሰውነታችንን በሚገነባልንና ብርታት በሚሰጠን ምግብ አማካይነት የምናገኘው የርሱን ሕይወት ነው፡፡ በሐጢአት ካልተጣመሙ በስተቀር የርሱ ሥጦታዎች ሁሉ ወደ ሕይወት ፣ ወደ ጤናና ደስታ የሚያቀኑ ናቸው፡፡ EDA 219.3
«ነገር ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጐ ሠራው» መክ 3፡11፡፡ እውነተኛ ውበት ደግሞ የእግዚአብሔርን ሥራ በማበላሸት ሳይሆን ሁሉን ነገር ወደ ፈጠረው ወደ እርሱ ሕጐች ተስማምቶ በመቅረብና በውበታቸውና በፍጹምነታቸው በሚደሰት ጌታ በእርሱ ይጠበቃሉ፡፡ EDA 219.4
የሰውነት አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚጠናበት ጊዜ የተለያዩ ብልቶች አንዱ በሌላው ላይ በመተማመን የተቀናጀና የተዋሀደ መስተጋብር መፈፀምን መቻላ ቸውና የመነሻ ምክንያቱና ውጤቱ አስገራሚነት ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፡፡ ስለዚህም የተማሪው ፍላጐት እየተነቃቃ ሲሄድና የሥነ አካል ትምህርትን አስፈላጊነት እያየ ሲመጣ ተገቢ ዕድገትና ትክክለኛ ልማዶችን እንዲጠበቁለት ለማድረግ በአስተማሪው በኩል ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ EDA 219.5
ሊታለምባቸው ከሚገባ የመጀመሪያ ነገሮች ዋነኛው በአቀማመጥም ሆነ በአነሳስ ላይ ትክክለኛውን አቋም መያዝ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን አስተካክሎ ፈጠረው እናም አካላዊዩን ብቻ ሳይሆን የሕሊናና የሞራል ጥቅሞች ባለቤት እንዲሆን ፀጋ ክብርና ራስን የመጠበቅ ድፍረትና በራስ መተማመን በእጅጉ ወደ እድገት ያዘነበለ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ መምህሩ እዚህ ነጥብ ላይ ትምህርቱን በምሳሌና በመልመጃ ይግለጥላቸው፡፡ ትክክለኛውን አቋምም ያሳያቸው ያለማቋረጥ መቀጠል እንዳለባቸውም አጥብቆ ይንገራቸው፡፡ EDA 220.1
ከአስፈላጊነቱ አንፃር በትክክለኛ አቋቋም ቀጥሎ ያለው ጉዳይ ደግሞ የአተነፋፈስና የድምጽ ትምህርት ነው፡፡ አቋቋሙና አቀማመጡ የተስተካከለ ሰው ከሌሎች የተሻለ አተነፋፈስ ይኖረዋል፡፡ መምህሩ ግን በጥልቀት አየር መሣብ ጠቃሚ መሆኑን ለተማሪዎች ሊያሳምናቸው ይገባል፡፡ የመተንፈሻ አካሎቻችንን ጤናማ አሠራር የደም ዝውውርን፣ አጠቃላይ ሥርዓቱን እንዴት እንደሚያግዝ፣ የምግብ ፍላጐትን እንደሚጨምር፣ ለምግብ መፈጨት እንዴት እንደሚረዳ፣ ድምጽን ምን ያክል እንደሚያቃና፣ ለጣፋጭ እንቅልፍ እንደሚጠቅም ያሳያቸው፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ ሰውነትን በማደስ ብቻ ሳይሆን አእምሮን በእውነት የሚያረጋጋ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በጥልቀት አየር ወደ ሳምባችን የመሳብን አስፈላጊነት በምታዩበት ጊዜ ተግባራዊ እንቅስቃሴው ለብዙ ጊዜ በመደጋገም ይቀጥል፡፡ ይኸንኑ የሚያጠናክር አካላዊ የእንቅስቃሴ ትምህርት ይሰጣቸው፡፡ ይኸንን ልምድ ማዳበራቸውን በቅርበት ተከታተሉ፡፡ EDA 220.2
ሳምባዎችን የሚያሰፋና የሚጠነክር፣ በዚህም በሽታን የሚከላከል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ድምጽን መግራት በሥነ አካል ትምህርት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ ጥሩ ንባብና ንግግር ማቅረብ መቻላችንን ለማረጋገጥ በሆድ ዕቃዎች አካባበ ያሉ ጡንቻዎቻችን ሁሉ በምንተነፍስበት ሰዓት ሙሉ ለሙሉ በጥሩ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ፣ ለመጫወት መቻላቸውን ማረጋገጥና የመተንፈሻ ብልቶቻችንም ያልተገደቡ መሆናቸውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ የሚያስቸግር ውጥረት ቢኖር በጉሮሮ አካባቢ ላይ ከሚሆን ይልቅ በሆድ ዕቃዎች አካባቢ ቢሆን ይሻላል፡፡ እንዲህ ሲሆን ከባድ ድካምና አስጊ የሆኑ የጉሮሮና የሳምባችን አካባቢ የሚኖርን ሕመምን መከላከል ይቻላል፡፡ የነጠረና የተስተካከለ ድምጽ በሚገባ የሚንቆረቆር ጥዑመ ልሳን እንዲኖረን ለማድረግ እጅግ በመቻኮል የፈጠረ ንግግር ከማድረግ መቆጠብና ጥንቃቄና ልዩ ትኩረት ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ይሀን ጤናን የሚያበረታታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተማሪውን በሥራው ተስማሚና ቀልጣፋ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ EDA 221.1
እነኝህን ትምህርቶች በማስተማር ረገድ የሞኝነትና ደካማ አኃጢአተኛ ትብትብ ሥራዎች ሌሎች ዋና እንቅስቃሴዎችን እንደሚጐዳ ለማሳየት ወርቃማ ዕድል ተሰጥቷል፡፡ ጤናማ ካልሆነ የአለባበስ ሥርዓትና በልብስ ስፌት ዓይነት የሚመጣ ማቋረጫ የሌለው ተከታታይ በሽታ ሞልቷል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ የተሞላበት መመሪያ በዚህ ነጥብ ላይ መሰጠት አለበት፡፡ ዳሌን የሚያጠብቅ ወይም በማንኛውም የአካል ብልት ላይ ጫና የሚያሳድር አለባበስ አደጋ እንደሚያስከትል ለተማሪዎች በጥብቅ አስረዷቸው፡፡ ልብሱ ሙሉ ትንፋሽ ለመዋጥና ለመመለስ እንዲያስችልና እጆችንም ያለ አንዳች ችግር ከራስ በላይ ወደ ላይ ለማንሳት እንዳያውክ ሆኖ መሰፋት አለበት፡፡ የሳምባዎች መጨማደድ እድገታቸውን የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን የምግብ መፈጨትንና የደም ዝውውርን ሂደት ያሰናክላል፡፡ እናም አካል በሙሉ ያደክማል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ሁሉ የአካልና የአእምሮን ኃይል ይቀንሳሉ፡፡ ስለዚህም የተማሪውን እድገት ያሰናክላል ስኬታማ እንዳይሆንም ይከለክለዋል፡፡ EDA 221.2
በሃይጅን ጥናት ውስጥ፣ ጥሩ መምህር የግልና የአካባቢ ፍጹም ንጹህ የመሆንን ጠቃሚነት ለማሳየት የሚችልበትን መንገድ ሁሉ ያሻሽላል፡፡ በየቀኑ ገላን መታጠብ ጤንነትን በማጐልበትና የአእምሮን ተግባር በማነቃቃት ረገድ የሚኖረውን ከፍተኛ ፋይዳ በጥብቅ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የፀሐይ ብርሃንና ንፁህ አየር ስለሚገኝበት ሁኔታ የመኝታና የማድበት ንጽህና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የተመቻቸ የመኝታ ክፍል አጠቃላይ ንጽህናው የተጠበቀና በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ ወጥቤት፣ በአይነት የተሟላና ለመመገብ የሚያስደስት ማዕድ ወይም የምግብ ጠረጴዛ ዝግጅት ከቤተሰቡ አልፎ ማንኛውም አስተዋይ የሆነ እንግዳ እጅግ ውድ ዋጋ ባላቸው እቃዎች በተሞላ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ከመዝናናት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝለት ለተማሪዎቹ ግለጥላቸው፡፡ «ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡» (ሉቃ 12፡23) የሚለው ትምህርት ከአስራ ስምንት መቶ ዓመታት በፊት በመለኮታዊዩ መምህር ሲሰጥ ከነበረው ባላነሰ ሁኔታ አሁንም ትምህርቱ ተፈላጊ ነው፡፡ EDA 222.1
አንድ የሥነ-አካል ተማሪ የጥናቱ ዓላማ ስለ አካላት እውነተኛ ጭብጦችንና የመሰረታዊ ሀሳቦችን እውቀት ለማግኘት ብቻ አለመሆኑን መማር አለበት፡፡ ይህ ብቻውን እምብዛም የሚጠቅም ነገር አይደለም፡፡ የንፁህ አየርን ዝውውር አስፈላጊነት፤ የርሱ ክፍልም በንጹህ አየር የተሞላች ትሆን ዘንድ፣ ነገር ግን ሳምባውን በንፁህ አየር ካልሞላ ትክክለኛ ባልሆነ የአየር አጠቃቀም የሚጐዳው ራሱ መሆኑን እንዲያስተውል ነው፡፡ ንፁህ የመሆን አስፈላጊነት ይስተዋል ዘንድ፤ አስፈላጊ የሆኑ መርጃ መሣሪያዎች እንዲቀርቡ ቢደረግ ይህ ሁሉ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ዋጋ የለውም፡፡ እነዚህን መርሆች በማስተማር ረገድ የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ተማሪው አስፈላጊነታቸው አምኖ ተግባራዊ እንዲአደርጋቸው እመቻላችን ላይ ነው፡፡ EDA 222.2
እጅግ በሚያምርና በሚማርክ አቋም ላይ የእግዚአብሔር ቃል አካላዊ ክፍሎቻችን ያሰበልን እና በጥሩ ሁኔታ እንድንጠቀምባቸው የጣለብንን ኃላፊነትም ያሳያል፡፡ «ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆኑ አታውቁምን?» «የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአበሔርን ቤተመቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፡፡» 1ኛ ቆሮ 6፡19፣ 3፡17፡፡ EDA 223.1
ተማሪዎቹ እግዚአብሔር አካላታችንን ለማደሪያው እንዲሆን እንደሚፈልገው፣ ንፁህ ሆኖ መጠበቅ እንዳለበት፤ የከፍተኛና ክቡር ሐሳብ ማደሪያ ስፍራ እንደሆነ አውቀው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በሥነ አካል ጥናት ውስጥ እንዳለው ሁሉ፣ በእውነቱ «በሚያስፈራና በሚያስገርም ሁኔታ መሠራታችንን» መዝሙ 139፡14 ይመልከቱ ዘንድ በጥልቅ ስሜት ይነሳሳሉ፡፡ የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራ ከማበላሸት ይልቅ፣ የፈጣሪን ግርማ ሞገስ ያለው ፕላን ለመፈፀም የተቻላቸውን ያክል የመሞከር አላማ ያድርባቸዋል፡፡ EDA 223.2
ስለዚህም መታዘዝን ራስን አንደ ማዋረድ ወይም መስዋዕት እንደ ማድረግ የሚቆጥሩት ሳይሆን ሊገመት እንደማይቻለው ጥቅምና በረከት አድርገው ያዩታል፡፡ በእርግጥም ነውና፡፡ እንደ ጤና ሕጐች አድርገው ወደ ማክበር ያዘነብላሉ፡፡ EDA 223.3