Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
 • Results
 • Related
 • Featured
No results found for: "".
 • Weighted Relevancy
 • Content Sequence
 • Relevancy
 • Earliest First
 • Latest First
  Larger font
  Smaller font
  Copy
  Print
  Contents

  የሰይጣን ወጥመዶች

  ለስድስት ሺህ ዓመታት ገደማ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ሲካሄድ የቆየው ታላቁ ተጋድሎ በቅርቡ ሊያበቃ ደርሷል። ክፉውም ጠላት፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሚያከናውነውን ተግባር ለማደናቀፍ እና ነፍሳትን ከወጥመዱ ለማስገባት ጥረቱን አብዝቶ በማጠናከር ላይ ይገኛል። የዚህ ጠላት ዋነኛው ዓላማ፣ አዳኙ ኢየሱስ የማማለድ ሥራውን እስኪደመድምና ለኃጢአት የሚደረግ መሥዋዕት እስኪያበቃ ድረስ ሰዎችን በበደላቸው እንዳይፀፀቱ አሳውሮ በጨለማ ውስጥ ማቆየት ነው።ታተ 16.1

  በቤተክርስቲያን እንዲሁም በዓለም ዘንድ ግዴለሽነት ሲያይልና የክፉውን ኃይል ለመቋቋም የሚደረግ የተለየ ጥረት ሲጠፋ፣ ሰይጣን አንዳችም ስጋት አይገባውም። ምክንያቱም በእርሱ ፈቃድ ስር ምርኮኛ አድርጎ የሚመራቸውን እንደማያጣቸው እርግጠኛ ስለሚሆን ነው። ነገር ግን ነፍሳት ዘለዓለማዊ ወደ ሆኑ ነገሮች ትኩረታቸውን ሲያዞሩና «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» በማለት መጠየቅ ሲጀምሩ የክርስቶስን ኃይል ለመግታትና የመንፈስ ቅዱስን ግፊት ለመቀልበስ በመሻት ስራ ላይ ይሰማራል።ታተ 16.2

  መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር መላእክት በጌታ ፊት ለመቆም በመጡ ጊዜ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። (ኢዮብ 1፡6)። አመጣጡ ለዘመናት ንጉስ ለመስገድ ሳይሆን በጻድቁ ላይ የክፋት ዓላማውን ለማሳካት ነበር። ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት ዛሬም ሰዎች ለአምልኮ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እርሱም ይገኛል። ምንም እንኳን ከእይታ ቢሰወር በአምልኮ ላይ የሚገኙትን ሰዎች አእምሮ ለመቆጣጠር በትጋት ይሰራል። እንደ አንድ ብልሃተኛ የጦር መሪ እቅዶቹን በቅድሚያ ይዘረጋል። የእግዚአብሔር አገልጋይ ቃሉን ሲመረምርና ለስብከት ሲዘጋጅ ሰይጣንም ተጠግቶ ለህዝቡ ሊቀርብ ያለውን መልእክት መዝግቦ ይይዛል። ከዚያም ብልጠቱንና ብልሃቱን ሁሉ ተጠቅሞ ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ቀድሞውኑ በዚሁ ነጥብ ላይ ላሳታቸው ሰዎች ይህ መልእክት እንዳይደርሳቸው ያደርጋል። ይህ የማስጠንቀቂያ መልእክት በይበልጥ የሚያስፈልገው ግለሰብ የእርሱ መገኘት ግድ ወደሆነበት የቢዝነስ ጉዳይ እንዲሄድ ይገደዳል። ወይም ደግሞ ሌላ ምክንያት ይፈጠርና እነዚያን የህይወት ሽታ ሊሆኑለት የሚችሉትን ቃላት እንዳይሰማ ይከለከላል።ታተ 16.3

  በተጨማሪም ሰይጣን የጌታ አገልጋዮች ህዝቡን ስለከበበው መንፈሳዊ ጨለማ ሲጨነቁ ይመለከታል። በእግዚአብሔር ፀጋና ኃይል የግዴለሽነት፣ የደንታቢስነትና የስንፍና መተት እንዲሰበር ከልባቸው የሚያደርሱትንም ጸሎት ያደምጣል። ከዚያም በኋላ በአዲስ ቅንአት ተነሳስቶ የጥበብ ሥራውን ያቀላጥፋል። ሰዎችን ሆዳቸው አምላካቸው እንዲሆን በማድረግ ወይም በሌላ ሥጋቸውን በሚያረኩበት ነገር እንዲጠመዱ በመፈታተን ስሜታቸው እንዲደነዝዝ ያደርጋል። ይህም ሲሆን ማወቅ የሚገባቸውን እጅግ አስፈላጊ ነገር ሳይሰሙ ይቀራሉ።ታተ 16.4

  ጸሎትንና የቃሉን ጥናት ችላ እንዲሉ የሚያደርጋቸው ሁሉ በጥቃቱ እንደሚሸነፉ ሰይጣን ጠንቅቆ ያውቃል። እናም አእምሮን ለመማረክ የሚቻለውን ሁሉ ዘዴ ይፈጥራል። እውነትን ለማወቅ ከመጣር ይልቅ በሀሳብ ከሚቃረኑአቸው ግለሰቦች የባህሪይ እንከንን ወይም የእምነት ስህተትን መፈለግ ሥራዬ ብለው የያዙ ‹ሃይማኖተኛ ነን› ባዮች ሁሌም በመካከላችን ይገኛሉ። እንደነዚህ አይነቶቹ የሰይጣን ቀኝ እጅ ረዳቶች ናቸው። እግዚአብሔር ሲሰራና አገልጋዮቹም እውነተኛ ስግደት ሲያቀርቡለት ዘወትር ነቅተው የሚሰሩ ብዙ የወንድሞች ከሳሾች አሉ። እነዚህ፣ እውነትን ከሚወዱና ከሚታዘዙት አፍ የሚወጣውን ቃልና ተግባራቸውን የሐሰት መልክ ያስይዛሉ። ልበ ቅን፣ ራሳቸውን የካዱና ፍጹም ቀናኢ የሆኑትን የክርስቶስን አገልጋዮች የተታለሉ ወይም አታላይ እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ። የእያንዳንዱን እውነተኛና የተከበረ ተግባር መነሻ ምክንያት ማዛባት፣ ክፉ ወሬ ማሰራጨትና ልምድ በሌላቸው ግለሰቦች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬን መዝራት ስራቸው ነው። ንፁህና ጽድቅ የሆነው ነገር ርኩስና አሳሳች መስሎ እንዲታይ ለማድረግ ሊታሰብ በሚችል መንገድ ሁሉ ይጥራሉ።ታተ 16.5

  የእነዚህን አይነት ሰዎች ማንንነት በተመለከተ ማንም ሊሳሳት አይገባውም። የማን ልጆች እንደሆኑ፣ የማንን ፈለግ እንደሚከተሉና የማንን ተግባር እንደሚፈፅሙ በቀላሉ መለየት ይቻላል። «ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።» (ማቴዎስ 7፡16)። መንገዳቸው መርዘኛ፣ ስም አጥፊና «የወንድሞቻችን ከሳሽ» የሆነው የሰይጣን መንገድ ነው። (ራእይ 12፡10)።ታተ 16.6

  ታላቁ አታላይ የተገኘውን ማንኛውንም አይነት የስህተት ትምህርት በማቅረብ ነፍሳትን ለማጥመድ ዝግጁ የሆኑ አያሌ ወኪሎች አሉት። እርሱ ሊያጠፋ ካሰባቸው ሰዎች የተለያየ ፍላጎትና ችሎታ ጋር የሚስማማ የክህደት ትምህርት ያዘጋጃል። ቅንነት የጎደላቸው፣ ያልተለወጡ፣ ጥርጥርንና አለማመንን የሚያደፋፍሩ፣ ነፍሳት እንዳይለመልሙና የእግዚአብሔርም ሥራ ወደፊት እንዳይገፋ መሰናክል የሚሆኑ አባላትን ወደ ቤተክርስቲያን መጨመር እቅዱ ነው። ብዙዎች በእግዚአብሔርም ሆነ በቃሉ ላይ ተጨባጭ እምነት ሳይኖራቸው የተወሰኑ የእውነት መርሆችን ብቻ በአፍ በማመናቸው ክርስቲያን ተብለው ይቆጠራሉ። ይህም የስህተት ትምህርቶቻቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮቶች አስመስለው እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል።ታተ 16.7

  «ሰዎች የፈለገውን ነገር ቢያምኑም አምነው የሚቀበሉት ነገር ምንም ችግር የለውም» የሚለው አቋም እጅግ ውጤታማ ከሆኑት የሰይጣን ማታለያ ዘዴዎች አንዱ ነው። እውነት፣ በፍቅር ሲቀበሏት የተቀባዩን ነፍስ እንደምትቀድስ ሰይጣን ያውቃል። ስለዚህም እውነትን በሀሰት ፅንሰ ሀሳቦች፣ በተረታ ተረቶችና በሌላ ወንጌል ለመተካት ሳያቋርጥ በመስራት ላይ ይገኛል። ከጥንትም ጀምሮ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ከሀሳዊ አስተማሪዎች ጋራ ሲታገሉ ኖረዋል። እነዚህ አስተማሪዎች አረመኔና ጨካኝም ብቻ ሳይሆኑ ለነፍስ ጠንቅ የሆኑ የውሸት ትምህርቶችን በሰዎች ጭንቅላት የሚያሰርፁ ግለሰቦች ነበሩ። ኤልያስ፣ ኤርምያስና ጳውሎስ፣ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቃል የሚያርቁትን ያለ ፍርሃት በጥብቅ ተቃውመዋቸዋል። ትክክለኛውን ሃይማኖት መያዝ አላስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ የሚያይ ልል አስተሳሰብ በእነዚያ ቅዱሳን የእውነት ጠባቂዎች አእምሮ ስፍራ አላገኘም።ታተ 17.1

  በክርስትናው ዓለም የሚታዩት ግልጽ ያልሆኑና ምናባዊ የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች እንዲሁም እምነትን በተመለከተ እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ አያሌ ፅንሰ ሀሳቦች ሰዎችን በማደናገር እውነትን እንዳያስተውሉ ለመከልከል የተዘጋጁ የባላጋራችን የእጁ ሥራዎች ናቸው። በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ላለው አለመጣጣምና ክፍፍል ዋነኛው መንስኤ የራስን ፅንሰ ሀሳብ እንዲደግፍ አድርጎ ቃሉን የመጠምዘዝ ልማድ ነው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ቃሉን በትሁት ልብ ሆኖ በጥንቃቄ ከመመርመር ይልቅ ብዙዎች አዲስ ወይም ለየት ያለ ነገር ብቻ ካላገኘን ይላሉ።ታተ 17.2

  የስህተት አስተምህሮቶችን ወይም ኢ-ክርስቲያናዊ ምግባሮችን ለመደገፍ ሲሉ አንዳንዶች የተወሰነ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ከዐውደ ምንባቡ ነጥለው ይወስዳሉ። ምናልባትም የአንዱን ጥቅስ ግማሽ ብቻ ቆርሰው በማንሳት ሀሳብቸውን ለማረጋገጥ ይሞክሩ ይሆናል። የተቀረው የጥቅሱ ክፍል ጭምር ቢታይ ግን ፍጹም ተቃራኒ አንድምታ ይኖረዋል። እንደ እባብ ባለ ብልሃት ለሥጋ ምኞታቸው እንዲስማማ ታስቦ በተቀናጀ የሀሳብ ዝብርቅርቅ ራሳቸውን ለመከላከል ይሞክራሉ። በእንዲህ አይነት መልኩ ነው ብዙዎች ሆን ብለው የእግዚአብሔርን ቃል የሚያዛንፉት። ሌሎች ደግሞ በምናባቸው የማየት ችሎታቸውን ተጠቅመው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ተምሳሌቶች ከቅዠታቸው ጋራ እንዲስማሙ አድርገው ይተረጉማሉ። የእግዚአብሔር ቃል ራሱን በራሱ የሚፈታ መሆኑ ሳይገዳቸው የራሳቸውን እንግዳ አመለካከቶች እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች አድርገው ያቀርባሉ።ታተ 17.3

  የቃሉ ጥናት በፀሎት፣ በትህትና እና ለመማር ፈቃደኛ በሆነ መንፈስ ካልሆነ በስተቀር ቀላልና ግልጽ እንዲሁም እጅግ ውስብስብ የሆኑት ምንባቦች እውነተኛ ትርጉማቸውን ያጣሉ። ጳጳሳዊ መሪዎች እነኚህን በተለይም የተወሳሰቡትን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይመርጡና ለራሳቸው ጥቅም እንዲገጥሙ አድርገው በመተርጎም ለህዝቡ ያቀርቧቸዋል። እንዲህም በማድረግ ተራ ምዕመናኖች በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እውነቱን መረዳት የሚችሉበትን መብት ይነፍጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ለሰዎች ሊሰጥ ይገባል። ሰዎች የተዛባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮት ከሚቀርብላቸው ጭራሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ባይሰጣቸው የተሻለ ነው።ታተ 17.4

  መጽሐፍ ቅዱስ የፈጣሪያቸውን ፈቃድ ማወቅ ለሚሹ ሁሉ መመሪያ እንዲሆን የታቀደ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የጸና የትንቢት ቃል ሰጥቷል። መላእክትና ክርስቶስ እራሱ ለዳንኤልና ለዮሐንስ ተገልጠው ቶሎ መሆን የሚገባውን ነገር አስታወቋቸው። ድነታችንን የሚመለከቱ አስፈላጊ ጉዳዮች ምስጢር ሆነው አልቀሩም። በቅንነት እውነትን ለማወቅ የሚሹትን ግራ በሚያጋባና በሚያሳስት መልኩ አልተገለጹም። በነቢዩ ዕንባቆም አማካኝነት ጌታ እንዲህ ብሏል፤ «በቀላሉ እንዲነበብ፣ ራእዩን ጻፈው፤ በሰሌዳም ላይ ቅረጸው» (ዕንባቆም 2፡2)። የእግዚአብሔር ቃል በፀሎት ልብ ለሚያጠኑት ሁሉ ግልጽ ነው። እያንዳንዱ ቅን ነፍስ ወደ እውነት ብርሃን ይመጣል። «ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።» (መዝሙር 97፡11)። እንደተሰወረ መዝገብ እውነትን ተግተው የሚፈልጉ አባላት የሌሉባት ቤተክርስቲያን ፈጽሞ በቅድስና አታድግም።ታተ 17.5

  ባላንጣቸው ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ያለፋታ ዘወትር በመሥራት ላይ ሳለ፣ ሰዎች በለዘብተኛነት ተይዘው የሰይጣንን መሳሪያዎች ማየት ተስኗቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በሰው ግምታዊ ፈጠራዎች የመተካት ተግባሩ ሲሳካለት፣ የእግዚአብሔር ሕግ ወደ ጎን ይጣላል፤ ቤተ-ክርስቲያናትም «ነፃ ነን» እያሉ በኃጢአት ባርነት ውስጥ ይዘፈቃሉ።ታተ 17.6

  ለብዙዎች ሳይንሳዊ ምርምር እርግማን ሆኗል። በሳይንስና በስነ-ጥበብ አዳዲስ ግኝቶች እንዲኖሩ ልዩ የመረዳት ችሎታ ዓለምን እንደጎርፍ እንዲያጥለቀልቅ አምላክ ፈቀደ። ይህም ቢሆን፣ በእውቀት አንቱ የተባሉት እንኳን በሚያካሄዱት ምርምር በእግዚአብሔር ቃል ካልተመሩ፣ በሳይንስና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ያለው ዝምድና አይገባቸውም።ታተ 17.7

  ምድራዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ነገሮችን በተመለከተ ሰብዓዊ እውቀት ውስንና የተጓደለ ነው። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች የሳይንስ እውቀታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ገለፃዎች ጋር ማጣጣም ያዳግታቸዋል። ተራ ፅንሰ ሀሳቦችንና መላምቶችን እንደ ሳይንሳዊ እውነታዎች አድርገው ይቀበላሉ። የእግዚአብሔር ቃል በዚህ «በውሸት እውቀት» በተባለ አስተምህሮት መመዘን አለበት ብለውም ያስባሉ። (1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡20)። ስለ ፈጣሪና ስለ እጁ ሥራዎች መመራመር ከአእምሮአቸው በላይ ስለሆነና ይህንንም በተፈጥሮአዊ ሕግጋት መሠረት ማብራራት ስለማይቻላቸው «በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ታሪክ የማይታመን ነው» ይላሉ። እነዚህ በብሉይና በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ የተካተተውን መረጃ ተአማኒነት የሚጠራጠሩት፣ የእግዚአብሔርን ህልውና በመካድ (ባለመቀበል) ወሰን የሌለው የመለኮት ኃይል በተፈጥሮ ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የደህንነታቸውን መልህቅ ስለተዉ፤ ከክህደት ዓለት ጋር ይላተማሉ።ታተ 18.1

  ብዙዎች በእንዲህ አይነት መልኩ ከእምነት ይስታሉ፤ ለዲያብሎስም ማባበያዎች እጅ ይሰጣሉ። የሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው በላይ ጠቢባን ለመሆን ሞክረዋል። ሰብዓዊ ፍልስፍና ለዘላለም ሊገለጡ የማይቻሉ ምስጢራትን ለመፍታትና ለማብራራት ጥረት አድርጓል። ሰዎች እግዚአብሔር ስለ ራሱና ስለ ዕቅዱ/ዓላማው የገለጠላቸውን ቢመረምሩና ቢያስተውሉ፣ የይሆዋን ኃይል፣ ክብርና ግርማ በግልፅ በተመለከቱና የራሳቸውንም ትንሽነት በተገነዘቡ ነበር። ያን ጊዜ ለእነርሱና ለልጆቻቸው በተገለጠው ብቻ በረኩ ነበር።ታተ 18.2

  እግዚአብሔር ስላልገለጠውና እንድናውቀውም ስለማይሻው ነገር በመመራመርና መላምቶችን በመሰንዘር የሰውን አእምሮ ማጥመድ የተዋጣለት የሰይጣን ማታለያ ስልት ነው። ሉሲፈርም በሰማይ የነበረውን ስፍራ ያጣው በዚሁ ምክንያት ነበር። እግዚአብሔር ምስጢሩንና ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ባለማካፈሉ ቅሬታ ገባው። በተሰጠው የከፍታ ስፍራ ስለሚኖረው ሥራ የተገለጠለትን ነገር በንቀት አይን ተመለከተ። ለእርሱ በሚታዘዙት መላእክት ልብ ውስጥ ይህንኑ የቅሬታ ስሜት በማሳደር ለውድቀት ዳረጋቸው። ዛሬም የሰዎችን አእምሮ በዚሁ መንፈስ በመሙላት የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ችላ እንዲሉ ያደርጋቸዋል።ታተ 18.3

  ምንም ትርጉም የማያስፈልጋቸው ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቆችን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች፣ ከህሊና ወቀሳ የሚያሳርፍ፣ ለጆሮ የሚመች ተረት ብቻ መስማት ይፈልጋሉ። መንፈሳዊነትን፣ ራስን መካድንና መዋረድን የማይጠይቁ አስተምህሮቶች በእነርሱ ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት አላቸው። ሥጋዊ ምኞታቸውን ለማርካት ብለው አእምሮቸውን ያቆሽሻሉ። በከንቱ ትዕቢት ስለተሞሉ፣ ቃሉን በተዋረደ ልብ መመርመርና መለኮታዊ ምሪት ለመቀበል በቅንነት መፀለይ ሞኝነት ይመሳላቸዋል። ስለዚህም ከአጉል እምነት ራሳቸውን የሚከላከሉበት ጋሻ አይኖራቸውም። ሰይጣን የልብን መሻት ለማሟላት ዝግጁ ነው። ማታለያዎቹን በእውነት ፈንታ ያቀብላል። ጳጳሳዊው ሥርዓት የሰዎችን አእምሮ የመቆጣጠር ኃይል ሊያገኝ የቻለው በዚሁ ሁኔታ ነው። መስዋዕትነትን ስለሚጠይቅ ብቻ እውነትን በመካድ ፕሮቴስታንቶችም ይህንኑ መንገድ በመከተል ላይ ናቸው። ምቾታቸውን ለመጠበቅና ከዓለም ጋር ሰላም ለመፍጠር ብለው የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ጎን የሚጥሉ ሁሉ በእውነት ፈንታ እጅግ የከፋ የሃሰት አስተምሮን እንዲቀበሉ ይተዋሉ። ማንኛውም አይነት የስህተት ሀሳብ እውነትን እያወቁ በሚክዱት ዘንድ ተቀባይነትን ያገኛል። አንዱን አይነት ማታለያ ላለማመን የማይደፍር፣ ሌላኛውን በቀላሉ ይቀበላል። ሐዋሪያው ጳውሎስ ስለእንዲህ አይነት ሰዎች ሲናገር፣ «ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ … በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል» ይላል። (2ኛ ተሰሎንቄ 2፡10-12)። ይህንን የማስጠንቀቂያ ቃል በማሰብ አምነን ስለምንቀበላቸው አስተምህሮቶች መጠንቀቅ ይገባናል።ታተ 18.4

  ታላቁ አታላይ እጅግ በተሳካ መልኩ ከሚጠቀምባቸው ዋነኛ መንገዶች መካከል የሐሰት አስተምሮና፣ «ከሙታን ጋር መነጋገር ይቻላል» ብለው የሚያምኑ ሰዎች የሚሰሯቸው ተአምራቶች ይገኙበታል። የብርሃን መልአክ መስሎ መልኩን ቀይሮ በመምጣት፣ እምብዛም በማይጠረጠርበት ሥፍራ መረቡን ይጥላል። ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በፀሎት ሆነው ቢያጠኑና ቢረዱ፣ የሐሰት አስተምህሮቶችን በማይለዩበት ጨለማ አይዋጡም ነበር። እውነትንም አንቀበልም ሲሉ ለጠላት ሽንገላ በቀላሉ ይዳረጋሉ።ታተ 18.5

  ሌላው አደገኛ ስህተት የክርስቶስን ፍጹም መለኮታዊነት የመካድና ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ህልውና እንዳልነበረው የማሰብ አስተምህሮት ነው። ይህ አስተምህሮት፣ «መጽሐፍ ቅዱስን እናምናለን» በሚሉ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ አግኝቷል። ሆኖም ግን ይህ ፅንሰ ሀሳብ፣ አዳኛችን እራሱ ከአባቱ ጋራ ስላለው ቁርኝት፣ ስለ መለኮታዊ ባህሪይውና ስለህልውናው ከተናገራቸው እውነታዎች ጋር በቀጥታ ይጋጫል። ይህ አመለካከት መሠረተ ቢስ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም የሚመነጭ ነው። ሰው ስለድነት ሥራ ያለውን አመለካከት ዝቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለመሆኑ ያለውንም እምነት ይሸረሽራል። ይህ የበለጠ አደገኛ ከመሆኑም ባሻገር ሊጋፈጡት የሚከብድ ነገር እንዲሆን ያደርገዋል። የክርስቶስን መለኮታዊነት በተመለከተ የተሰጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክርነት ከማያምኑ ግለሰቦች ጋር መከራከር ከንቱና ጊዜ ማባከን ነው። ምክንያቱም ሀሳቡ የቱን ያህል አሳማኝ ቢሆንም ለእነርሱ አይዋጥላቸውም። «ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።» (1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14)። በዚህ የተሳሳተ አመለካከት የሚጓዙ ሁሉ ስለ ክርስቶስ ተልዕኮ ባህሪይ እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ድነት ስላለው ታላቅ እቅድ የተሟላ እውቀት ሊኖራቸው አይችልም።ታተ 18.6

  ሌላኛው ረቂቅ፣ ተንኮል የተሞላበትና በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘው የስህተት ትምህርት፣ ሰይጣን የራሱ የሆነ ህልውና ያለው ፍጡር አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስም “ሰይጣን” የሚለውን ቃል የሚጠቅሰው የሰዎችን ክፉ ሀሳብና ምኞት በምሳሌ ለመግለፅ ብቻ ነው የሚል እምነት ነው።ታተ 19.1

  «ሰው ሲሞት የክርስቶስ ዳግም ምጻት በዚያ ግለሰብ ይፈጸማል» የሚል አስተምህሮት ከብዙ መድረኮች በሰፊው እያተስተጋባ ይገኛል። ይህ፣ ክርስቶስ በደመና ሆኖ በሰማያት በግልጽ እንደሚመጣ ሰዎች እንዳያስተውሉና እንዲዘናጉ ለማድረግ ሆን ብሎ የተዘጋጀ ወጥመድ ነው። ሰይጣን ለዘመናት፣ «እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ … ከዚያ አለ፤ እነሆ፥ በበረሀ ነው … በእልፍኝ ነው» ሲል ከርሟል። (ማቴዎስ 24፡23-26)። ይህንን ማታለያ በማመን ብዙ ነፍሳት ጠፍተዋል።ታተ 19.2

  ምድራዊ ጥበብ፣ ፀሎት አስፈላጊ ነገር እንዳልሆነ ያስተምራል። የሳይንስ ተመራማሪዎች፣ የጸሎት ምላሽ የሚባል አንዳች ተጨባጭ ነገር እንደሌለ በእርግጠኝነት ይናገራሉ። ተአምር የሚሉት ነገር ከተፈጥሮ ሕግጋት ጋር የሚጋጭ ስለሆነ በሳይንሱ ዓለም ቦታ የለውም። ፍጥረተ ዓለማችን በማይለዋወጡ ሕግጋት እንደሚስተዳደርና እግዚአብሔር እራሱ እነዚህን ሕግጋት የሚቃረን አንዳች ነገር እንደማያደርግ ይናገራሉ። እግዚአብሔር፣ እራሱ ባጸናቸው ሕግጋት የሚገደብና የመለኮታዊ ሕግጋት አሠራር መለኮታዊ ነጻነት የሚጫን ይመስላቸዋል። ይህ አስተምህሮት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይቃረናል። ክርስቶስ እራሱ እንዲሁም ተከታዮቹ ተአምራትን ሠርተዋል። ያ ርኅሩኅ አዳኝ ዛሬም ህያው ነው። የእምነትን ጸሎት ለመስማት ዛሬም ፈቃደኛ ነው። ሰብዓዊው ከመለኮታዊው ጋር ሊተባበር ግድ ነው። እግዚአብሔር፣ ባንለምነው የማይሰጠንን ነገር፣ በእምነት ለምናደርሰው ጸሎት ምላሽ አድርጎ ሊያድለን ይፈልጋል።ታተ 19.3

  ሊቆጠሩ የማይቻሉ የተሳሳቱ አስተምህሮቶችና ምናባዊ ሀሳቦች በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነትን እያገኙ መጥተዋል። እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ከተከላቸው ጉልህ እውነቶች አንዱን እንኳን ለመንቀል መሞከር የሚያስከትለውን ክፋት መገመት ያዳግታል። ይህን ለማድረግ ከሚደፍሩት ጥቂቆቹ አንድ እውነት ብቻ እንደካዱ ያቆማሉ። አብዛኞቹ ግን የእውነትን መርሆችን አንድ በአንድ እያነሱ ወደ ጎን በመጣል ጨርሶ ሃይማኖት አልባ እስከመሆን ይደርሳሉ።ታተ 19.4

  በብዙዎች ዘንድ እውቅና ካገኘው ከስነ-መለኮታዊ ጥናት ጋር አብረው የመጡት የስህተት ትምህርቶች፣ ብዙ ነፍሳት መጽሐፍ ቅዱስን ከማመን ይልቅ ተጠራጣሪ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። አንድ ሰው ስለ ፍትህ፣ ስለ ምህረትና ስለ በጎነት ያለውን ስሜት የሚጎዱ ትምህርቶችን መቀበል አይቻለውም። በዚያ ላይ ትምህርቶቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው ተብለው ስለሚቀርቡለት እነዚህን እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጎ መቀበል ይከብደዋል።ታተ 19.5

  ሰይጣን ሊያሳካው የሚሻው ዓላማም ይኸው ነው። በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይ አመኔታ እንዲጠፋ ከማድረግ ውጭ የሚመኘው ነገር የለም። የተጠራጣሪዎች ሠራዊት ቁንጮ የሆነው ጠላት ነፍሳትን በማታለል ከራሱ ተርታ ሊያሰልፋቸው በሙሉ ኃይሉ ይሰራል። አንድን ነገር መጠራጠር ወይም ላለመቀበል ማቅማማት የጊዜው ፋሽን እየሆነ መጥቷል። የእግዚአብሔር ቃል በኃጢአታቸው ስለሚገስፃቸውና ስለሚኮንናቸው፣ እግዚአብሔርን እንዲሁም ቃሉን በጥርጣሬ አይን የሚመለከቱ ብዙ ናቸው። ቃሉ የሚያስቀምጣቸውን መስፈርቶች ለማሟላት ፈቃደኛ ስላልሆኑ የቃሉን ስልጣን ለመገርሰስ ጥረት ያደርጋሉ። ቃሉን ያነባሉ፤ ከመድረክ የሚተላለፈውንም መልዕክት ይሰማሉ። ነገር ግን ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከስብከቱ ስህተት ለመፈልግ ብቻ ሲሉ ነው። ብዙዎች ኃላፊነታቸውን ችላ ለማለታቸው ማመካኛ ሲፈልጉ ከሀዲ ሆነው ይቀራሉ። ሌሎች በትዕቢትና በስንፍና ተነሳስተው አጠያያቂ የሆኑ መርሆችን ያስተናግዳሉ። በሰዎች ዘንድ መከበር ቢመኙም፣ ይህን ለማግኘት ግን ጥረት የማድረግና ራስን የመካድ ጭንቅ ውስጥ መግባት አይፈልጉም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስን በመተቸት ጠቢብ ለመባልና ዝናን ለማትረፍ ይሞክራሉ። በመለኮታዊ ጥበብ ካልታገዘ በስተቀር ውስን የሆነው ሰብዓዊ አእምሮ ሊረዳው የማይችለው ብዙ ነገር አለ። ይህም ለትችታቸው አመቺ ሁኔታ ይፈጥራላቸዋል። በአለማመን፣ በጥርጥርና በክህደት መንገድ መሰለፍ ምግባረ ጥሩነት የሚመስላቸው ብዙ አሉ። ቅንነት የሚመስለው ውጫዊ ሽፋናቸው ቢገለጥ እውነተኛ መልካቸው በራስ መተማመንና ትዕቢት መሆኑ ያስታውቃል። ብዙዎች የሌሎችን አእምሮ ለማስጨነቅ፣ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈልፍለው ማውጣት ይቀናቸዋል። አንዳንዶች ንትርክ ስለሚወዱ ብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትችት በመሰንዝር በተሳሳተ መንገድ ይሄዳሉ። ይህን ሲያደርጉ ራሳቸውን በአዳኝ ወጥመድ ውስጥ እየተበተቡ መሆናቸውን አያስተውሉም። አንዴውኑ ክህደታቸውን በገሃድ ስላሳወቁ በያዙት አቋም መፅናት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እንዲህም ሲሆኑ ከአህዛብ ማህበር በመቀላቀል የገነትን ደጅ በራሳቸው ላይ ይዘጋሉ።ታተ 19.6

  ስለ ቃሉ መለኮታዊነት እግዚአብሔር በቂ ማስረጃ ሰጥቶናል። ድነታችንን የሚመለከቱ ታላላቅ እውነቶች ግልጽ በሆነ መልክ ቀርበዋል። ከልባቸው ለሚሹት ሁሉ እንዲሰጥ ቃል በተገባለት በመንፈስ ቅዱስ እገዛ እያንዳንዱ ሰው እነዚህን እውነቶች መረዳት ይችላል። እግዚአብሔር ለሰዎች እምነታቸውን የሚያሳርፉበት ብርቱ መሠረት ሰጥቶአቸዋል።ታተ 20.1

  ሆኖም ግን ውስን የሆነው የሰው አእምሮ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ዓላማ ሙሉ በሙሉ የማስተዋል ብቃት የለውም። የቱንም ያህል ብንመራመር እግዚአብሔርን በሙላት ልናውቀው አንችልም። አምላክ እራሱ ግርማውን የሸፈነበትን መጋርጃ በድፍረት እጅ ለመክፈት አንሞክር። ሐዋሪያው፣ «ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም» ሲል በአድናቆት ይናገራል። (ሮሜ 11፡33)። ከመለኮታዊ ኃይሉ የሚመነጨውን ወሰን የሌለውን ፍቅሩንና ምህረቱን ማስተዋል እንድንችል ብቻ እግዚአብሔር አድራጎቱንና የልቡን ሀሳብ እንድንመረምር ይፈቅድልናል። በሰማይ ያለው አባታችን ሁሉን ነገር በጥበብና በጽድቅ ያዛል። እኛም እርካታ ከማጣትና ከመጠራጠር ይልቅ በታላቅ ክብር ልንገዛለት ይገባል። ልናውቅም የሚገባንንና የሚጠቅመንን ያህል ከዓላማው ይገልጥልናል። ከዚያ ባለፈ በኃያል ክንዱና ፍቅር በተሞላ ልቡ ልንተማመን ይገባናል።ታተ 20.2

  እግዚአብሔር ለእምነት በቂ ማስረጃ የሰጠ ቢሆንም ላለማመን ምክንያት የሚሆኑ መሰናክሎችን በሙሉ ግን አያስወግድም። ራሳቸውን ለጥርጥር ፈቅደው የሚሰጡ ሁሉ መሰናከያ አያጡም። የተቃውሞ ምክንያት በሙሉ ካልተወገደና ጥርጣሬ የሚያሳድር ነገር ጨርሶ ካልጠፋ በስተቀር የእግዚአብሔርን ቃል አንቀበልም ወይም አንከተልም ባዮች ምን ጊዜም ወደ እውነት ብርሃን ሊመጡ አይችሉም።ታተ 20.3

  በእግዚአብሔር አለመተማመን፣ ካልታደሰና እርሱን ከሚጠላ ልብ የሚመነጭ ተፈጥሮአዊ ውጤት ነው። እምነት ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጥ ሲሆን ዋጋ ሲሰጡትና ሲንከባከቡት ብቻ የሚበለጽግ ስጦታ ነው። ያለ ብርቱ ጥረት ማንም ሰው እምነተ ጠንካራ ሊሆን አይችልም። አለማመን ሲያበረታቱትና ሲደግፉት ይጠነክራል። ሰዎች ለእምነታቸው ድጋፍ እንዲሆን በተሰጣቸው ማስረጃ ከመጽናት ይልቅ ማመንታትና ማማረር ሲጀምሩ ጥርጣሬአቸው ይበልጡን እየተረጋገጠላቸው ይሄዳል።ታተ 20.4

  የእግዚአብሔርን የተሰፋ ቃል የሚጠራጠሩና የፀጋውን ማረጋገጫ የማያምኑ የሚገባውን ክብር አይሰጡትም። በሰዎች ላይም የሚያሳድሩት ተጽእኖ ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ከማምጣት ይልቅ ከእርሱ እንዲርቁ ያደርጋል። እነዚህ ሰዎች፣ ሰፋፊ ቅርንጫፎቹን በመዘርጋት ከስሩ ያሉት ዕፅዋት የፀሐይ ብርሃን እንዳያገኙ ከልሎ በጥላው ቅዝቃዜ ተቆራምደው እንዲሞቱ እንደሚያደርጋቸው ፍሬ አልባ ዛፍ ናቸው። የእነዚህ ግለሰቦች የሕይወት ዘመን ሥራ ለፍርዳቸው ዘላለማዊ ምስክር ይሆናል። የጥርጣሬንና የአለማመንን ዘር በመዝራታቸው በእርግጠኛነት የሚበቅለውን አዝመራቸውን ያጭዳሉ።ታተ 20.5

  ከጥርጣሬ ነፃ ለመሆን ከልብ ለሚመኙ ሁሉ መፍትሄው አንድ ብቻ ነው። ይኸውም ስለማያስተውሉት ነገር ጥያቄ ከማብዛትና ከመማረር ይልቅ በበራላቸው ብርሃን መኖር ነው። ይህንንም ሲያደርጉ በብርሃን ላይ ብርሃን እየተጨመረላቸው ይሄዳል። ግልጽ የሆነላቸውን ተግባር በታማኝነት ቢፈጽሙ፣ ግር ያላቸውን ነገር እንዲያስተውሉና እንዲከተሉ የሚያስችላቸው ጥበብ ይሰጣቸዋል።ታተ 20.6

  ሰይጣን እውነት የሚመስል ውሸት መፍጠር ይችልበታል። ስለዚህም፣ ለሽንገላ ራሳቸውን ፈቅደው የሚሰጡ፣ ለእውነት ሲሉ ራስን መካድና መስዋዕትነትን መክፈል የማይፈልጉ በቀላሉ ይስታሉ። የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍል እውነቱን ለማወቅ ከልቡ የሚሻውን ሰው ሰይጣን በቁጥጥሩ ሥር ሊያውል አይችልም። ክርስቶስ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን» ነው። (ዮሐንስ 1፡9)። ሰዎችን ወደ እውነት ሁሉ እንዲመራቸው የእውነት መንፈስ ወደ ዓለም ተልኳል። የእግዚአብሔርም ልጅ በስልጣኑ እንዲህ ሲል አስረግጦ ተናገረ፣ «ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፣» «ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል።» (ማቴዎስ 7፡7 ፤ ዮሐንስ 7፡17)።ታተ 20.7

  የክርስቶስ ተከታዮች ሰይጣንና ሠራዊቱ እየጠነሰሱት ስላለው ሴራ ያላቸው እውቀት እምብዛም ነው። በሰማያት ዙፋን የተቀመጠው እርሱ እነዚህን የጠላት መሳሪያዎች ጥልቅ ለሆኑ ዓላማዎቹ ማስፈጸሚያ ያደርጋቸዋል። ጌታ ህዝቡ በእሳት እንዲፈተኑ ይፈቅዳል። ይህን የሚያደርገው በጭንቀታቸውና በመከራቸው ሐሴት ስለሚያደርግ ሳይሆን ይህ ሂደት ለመጨረሻው ድላቸው ወሳኝ በመሆኑ ነው። በታላቅ ግርማው ከፈተና ሊከላከላቸው ቢችልም አያደርገውም። ምክንያቱም የዚህ ፈተና ዋናው ዓላማ ህዝቡ የክፋት ወጥመዶችን ሁሉ ለመቃወም ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።ታተ 20.8

  የእግዚአብሔር ህዝቦች በተሰበረ ልብ ኃጢአታቸውን ቢናዘዙና በእምነት የተስፋውን ቃል ቢጨብጡ፣ ክፉ ሰዎችም ሆኑ ሰይጣናት እራሳቸው የእግዚአብሔርን ሥራ ሊያስተጓጉሉና በህዝቡ መካከል መገኙቱንም ሊከለክሉ አይችሉም። ማንኛውም ፈተና፣ ማንኛውም ተጽዕኖ፣ ግልጽም ይሁን ድብቅ ድል የሚደረገው «በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።» (ዘካሪያስ 4፡6)።ታተ 21.1

  «የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል … በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?» (1ኛ ጴጥሮስ 3፡12-13)። በለዓም፣ በብዙ ሀብት ተታሎ በእስራኤል ላይ አስማት ሲሞክርና ለጌታም በመሰዋት እርግማንን ለማውረድ ሲሻ፣ ሊናገር ያሰበውን ክፋት እንዳይናገር የእግዚአብሔር መንፈስ አገደው። «እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ?» «የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን» ለማለትም ተገደደ። እንደገናም መስዋዕት ከቀረበ በኋላ ክፉው ነቢይ እንዲህ አለ፣ «እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም።» «በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል። እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል።» ለሦስተኛ ጊዜ መሰዊያው ተዘረጋ፤ በለዓምም እንደገና እርግማን ለማውረድ ሞከረ። ነገር ግን ከጠማማው ነቢይ ከንፈሮች የእግዚአብሔር መንፈስ ለተመረጠው ህዝቡ ብልጽግናን አወጀ፤ የጠላቶቻቸውንም ክፋት ገሰፀ። «የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተረገመ ይሁን።» (ዘኁልቁ 23፡8፣10፣20፣21፣23 ፤ 24፡9)።ታተ 21.2

  በዚህ ወቅት የእስራኤል ህዝቦች ለእግዚአብሔር ታማኝ ነበሩ። ሕጉን በመታዘዝ ቢቀጥሉ ሊያይልባቸው የሚችል ኃይል በምድርም ሆነ በሲኦል አይገኝም ነበር። በለዓም የእግዚአብሔርን ህዝብ እንዲረግም ባይፈቀድለትም በመጨረሻ ላይ ኃጢአት እንዲሰሩ አባብሎ እርግማንን በላያቸው ላይ በማምጣት እቅዱን አሳክቷል። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በጣሱ ጊዜ ራሳቸውን ከእርሱ ለዩ፤ የአጥፊውንም ኃይል እንዲቀምሱ ሆነ።ታተ 21.3

  ለክርስቶስ የሚኖር ደካማው ነፍስ ለጨለማው ሠራዊት ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ እንደሆነ ሰይጣን ጠንቅቆ ያውቃል። ራሱን ቢያጋልጥ ብርቱ ተቃውሞ እንደሚገጥመውም ያውቃል። ስለዚህም ከምሽጋቸው ብቅ የሚሉትን ሁሉ ለማጥቃትና ለማጥፋት ከሠራዊቱ ጋር አድፍጦ ይጠብቃል። የመስቀሉን አርበኞች ከብርቱ ምሽጋቸው ሊያስለቅቃቸው ይሻል። ከጠላት መጠበቅ የምንችለው በእግዚአብሔር ላይ መሉ በሙሉ እምነታችንን ስንጥልና ትዕዛዝቱን ስንጠብቅ ብቻ ነው።ታተ 21.4

  ያለ ፀሎት ማንም ሰው ለአንድ ቀን ቀርቶ ለአንድ ሰዓት እንኳን ደህና አይሆንም። ቃሉን ማስተዋል የሚያስችለን ጥበብ እንዲሰጠን በተለየ መልኩ ጌታን ልንማፀነው ይገባናል። የፈታኝ ማታለያዎችና እርሱን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የሚቻልበት መንገድ በቃሉ ውስጥ ተገልጾዋል። ሰይጣን የራሱን የተዛነፈ ትርጓሜ ሰጥቶት መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ ወደር የለውም። በዚህም እኛን ሊያሰናክለን ይመኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በትሁት ልብ፣ በእግዚአብሔር መተማመን ሳናቆም ልናጠና ይገባል። ራሳችንን ዘወትር ከሰይጣን መሳሪያዎች እየጠበቅን በእምነት «ወደ ፈተና አታግባን» እያልን መፀለይ አለብን።ታተ 21.5

  Larger font
  Smaller font
  Copy
  Print
  Contents