በጌታ ድፍረት
በቅርቡ በሌሊት ወቅት ጌታ በቶሎ ይመጣል ብለን እኛ እንደምናምነው በፍጥነት የሚመጣ ከሆነ እውነትን በሰዎች ፊት ለማቅረብ ከዚህ በፊት በነበሩት አመታት ከነበረን የበለጠ መሥራት እንዳለብን መንፈስ ቅዱስ ለአእምሮዬ ተናግሯል፡፡Amh2SM 402.3
ከዚህ ጋር በተገናኘ ሁኔታ በ1843 እና በ1844 ዓ.ም የዳግም ምጻት አማኞች ያደርጉት ወደነበረው ተግባር አእምሮዬ ተመልሶ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙ ከቤት ለቤት ጉብኝት ነበር፣ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለተነገሩ ነገሮች ሰዎችን ለማስጠንቀቅ መሰልቸት የሌለባቸው ጥረቶች ተደርገው ነበር፡፡ የመጀመሪያውን መልአክ መልእክት በታማኝነት ያወጁት ሰዎች ካደረጉት ጥረት እጅግ የበለጠ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በፍጥነት ወደ ምድር ታሪክ መጨረሻ እየተቃረብን ነን፤ ኢየሱስ በርግጥ በቅርብ እንደሚመጣ ስንገነዘብ ከዚህ በፊት አድርገን ከምናውቀው በበለጠ ሁኔታ ለመስራት እንነሳሳለን፡፡ ለሕዝብ የማስጠንቀቂያ ደወል እንድናሰማ ታዘናል፡፡ በራሳችን ሕይወት ውስጥ የእውነትንና የጽድቅን ኃይል ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ ዓለም የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ በተመለከተ በቅርቡ ታላቁን ሕግ ሰጭ ሊገናኝ ነው፡፡ ምህረትን እና ሰላምን ተስፋ ማድረግ የሚችሉት ከመተላለፍ ወደ መታዘዝ የሚመለሱት ብቻ ናቸው፡፡Amh2SM 402.4
«የእግዚአብሔርን ትዕዛዛትና የኢየሱስን ኃይማኖት” የሚል ጽሁፍ ያለበትን አርማ ማንሳት አለብን፡፡ ትልቁ ጉዳይ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባላትን እና ስለ እምነታቸው ምንም የማይናገሩትን ሰዎች የሰማይ ሕግ የሚፈልግባቸውን ነገር እንዲያዩና እንዲታዘዙ ለማነሳሳት ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ይህን ሕግ ማጉላትና የተከበረ ማድረግ አለብን፡፡ Amh2SM 403.1
የእውነትን ዘር እንድንዘራና በዚህች ምድር ታሪክ መዝጊያ ላይ በሚኖሩ ሰዎች ሊሰራ ያለውን ሥራ አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ሕዝባችንን እንድናነሳሳቸው ክርስቶስ ሥራ ሰጥቶናል፡፡ የእውነት ቃላት በአውራ ጎዳናዎችና በመንገድ መተላለፊያዎች ሲታወጁ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ መገለጥ በሰብዓዊ ልቦች ውስጥ ይሆናል፡፡Amh2SM 403.2
እውነት፣ የሕይወት ቃል፣ ያላቸው ሰዎች እውነት የሌላቸው ሰዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ ቢሰሩ ኖሮ ምን ያህል ጥሩ ሥራ ይሰራ ነበር! በሳምራዊቷ ሴት ጥሪ ሳምራውያን ወደ ክርስቶስ በመጡ ጊዜ እነርሱን በተመለከተ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ መከሩ ዝግጁ መሆኑን ነገራቸው፡፡ እንዲህ ነበር ያላቸው፡- «እናንተ ገና አራት ወር ቀርቷል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፣ ዓይናችሁን አንሱ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ” (ዮሐ. 4፡35)፡፡ ሳምራውያን እውነትን ለመስማት ተርበው ስለነበር ከእነርሱ ጋር ለሁለት ቀናት አብሮ ቆየ፡፡ እነዚያ ቀናት እንዴት ሥራ የበዛባቸው ቀናት ነበሩ! በእነዚያ ቀናት ከተሰራው ሥራ የተነሳ «ስለ ቃሉም ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ” (ዮሐ. 4፡ 41)፡፡ ምስክርነታቸውም ይህ ነበር፡- «እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን» (ዮሐ. 4፡ 42)፡፡Amh2SM 403.3
የእግዚአብሔር ሕዝብ ነን ከሚሉት መካከል ይህንን ቅዱስ ሥራ የሚቀበል እና እውቀት ከማጣት የተነሳ እየጠፉ ላሉት ነፍሳት የሚሰራ ማን ነው? ዓለም ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ራስን ቀድሶ መስጠት፣ ታማኝነት እና መሰልቸት የሌለበት ጥረት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ቦታዎች ተጠቁመውልኝ ነበር፡፡ በታላላቅ ከተማዎቻችን ውስጥ ክርስቶስ የብዙዎችን አእምሮና ልብ እየከፈተ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እውነቶች ይፈልጋሉ፤ ከክርስቶስ ጋር የተቀደሰ ቅርርብ የምንፈጥር እና ወደ እነዚህ ሕዝቦች ለመቅረብ የምንሻ ከሆንን መልካም ተጽኖዎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ መንቃት እና ከክርስቶስና እኛን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር ስምምነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ትንንሽና ትላልቅ ከተማዎች፣ በቅርብና በሩቅ ያሉ ቦታዎች ሊሰራባቸው የሚገቡ ቦታዎች ስለሆኑ በጥበብ ሊሰራባቸው ይገባል፡፡ ወደ ኋላ አታፈግፍጉ፡፡ ከጌታ መንፈስ ጋር የምንሰራ ከሆንን እርሱ ትክክለኛ የሆኑ አሻራዎችን በሰዎች ልብ ያሳርፋል፡፡ Amh2SM 403.4
ወንድሞቼ ሆይ፣ ለእናንተ የማስተላልፋቸው የማደፋፈሪያ ቃላቶች አሉኝ፡፡ ከእግዚአብሔር ትልልቅ ነገሮችን በመጠበቅ በእምነትና በተስፋ ወደ ፊት መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ጠላት በተለያየ መንገድ እውነት ወደ ፊት እንዲቀጥል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለማደናቀፍ ይሻል፣ ነገር ግን በጌታ ብርታት ስኬትን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ Amh2SM 404.1
ተስፋ የሚያስቆርጡ ቃላት አይነገሩ፣ ነገር ግን መነገር ያለባቸው ቃላት እንደ እናንተ ያሉትን ሰራተኞች የሚያበረታቱና የሚያቆሙ ናቸው፡፡Amh2SM 404.2