ጥቂት የክፋት ድርጊቶች ኃይል፣ ጠባይን በመቅረጽ ሂደት የሚታዩ ትንንሽ ቸልተኝነቶች በተገቢው ሁኔታ ግምት አልተሰጣቸውም:: ከሁሉም የበለጡና እጅግ የተከበሩ መርሆዎች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ተገልጠውልናል:: እነርሱ የተሰጡን ለመልካም ነገር ያለንን እያንዳንዱን ጥረት ለማጠናከር፣ አእምሮን ለመቆጣጠርና ሚዛን ለመጠበቅ እንዲሁም ከፍ ወዳለው መስፈርት ለመድረስ እንድንጓጓ ለማድረግ ነው:: MYPAmh 26.3
በዮሴፍ፣ በዳንኤልና ጓደኞቹ ታሪክ ውስጥ ወርቃማው የእውነት ሰንሰለት ወጣቶችን ከእግዚአብሔር ዙፋን ጋር እንዴት እንደሚያስተሳስር እናያለን:: ከሀቀኝነት መንገዳቸው ወደኋላ ለመመለስ አይፈተኑም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትን በነገሥታት ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘትና ከእነርሱ ሙገሳ የበለጠ ዋጋ ስለ ሰጡ እግዚአብሔር ወደዳቸውና ጋሻውን በለያቸው ዘርግቶ ከለላቸው፡፡ ታማኝነት ላለበት ሃቀኝነታቸውና ከማንኛውም ሃይል በላይ እግዚአብሔርን ለማክበር ስለ ወሰኑ ጌታም በሰዎች ፊት በምልክት አከበራቸው:: ኃይሉ በላይ በሰማይና በታች በምድር ካሉ የእጅ ሥራዎቹ ሁሉ በላይ በሆነው በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ተከበሩ:: እነዚህ ወጣቶች ትክክለኛ ማንነታቸውን ለመግለጥ አላፈሩም ነበር:: በንጉስ ፊት እንኳን በቃላቶቻቸው፣ በልምዳቸውና በድርጊታቸው በሰማይ ጌታ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ገለጡ:: እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ለሚከለክላቸው ለማንኛውም ምድራዊ ሥልጣን መስገድ እምቢ አሉ:: ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት መግለጥ የሚችሉበትን ብርታት ከሰማይ አገኙ:: MYPAmh 26.4
የእነዚህን ክቡራን ወጣቶች ምሳሌ ለመከተል መዘጋጀት አለባችሁ:: በማንነታቸሁ በፍፁም አትፈሩ:: የራሳችሁን ቀለም ልበሱና በሰዎችና በመላእክት እይታ ፊት ዘርግታችሁ እንዲታይ አድርጉት:: ከዚህ ምክር በተቃራኒ አቅጣጫ እንድትሄዱ በሚያደርጋችሁ የውሸት ጨዋነትና ጥንቃቄ ቁጥጥር ሥር አትሁኑ:: በተመረጡ ቃላቶቻችሁና በማያቋርጥ ተግባራችሁ፣ በትክክለኛነታችሁ፣ ልባዊ በሆነ ርህራሄአችሁ ክርስቶስ በነፍስ ቤተመቅደስ ውስጥ ዙፋኑን እንዲይዝ እምነታችሁን ግለጡ፤ መክሊቶቻችሁን ሳትቆጥቡ ለእርሱ አገልግሎት እንዲውል በእግሩ ሥር አስቀምጡ:: MYPAmh 26.5