Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
 • Results
 • Related
 • Featured
No results found for: "".
 • Weighted Relevancy
 • Content Sequence
 • Relevancy
 • Earliest First
 • Latest First
  Larger font
  Smaller font
  Copy
  Print
  Contents

  የተጋድሎው ፍጻሜ

  በሺው ዘመን ፍጻሜ ክርስቶስ በተዋጁት ሠራዊት ተከቦ፣ በታዛቢ አእላፍ መላዕክት ታጅቦ ዳግም ወደ ምድር ይመለሳል። በሚያስፈራው ግርማው ወደ ምድር ሲመጣ በመቃብር ያሉትን ኃጢአንን ዋጋቸውን እንዲቀበሉ ያስነሳቸዋል። እነሱም እንደ ባህር አሸዋ የማይቆጠሩ ታላቅ ሰራዊት ሆነው ከመቃብር ይወጣሉ። በመጀመሪያው ትንሳኤ ከተነሱት ጋር ሲነጻጸሩ ልዩነታቸው ጉልህ ሆኖ ይታያል፡፡ ጻድቃን የማይሞተውን የጎልማሳ ውበት ልብስ ተላብሰዋል። ኃጢአን ግን የበሽታ እና የሞት ጠባሳ ይታይባቸዋል።ታተ 83.1

  የእልፍ አእላፍ አይን ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጅ ክብር ለመመልከት ዘወር አለ። ኃጢአን በአንድ ድምጽ «በጌታ ስም የሚመጣው ብሩክ ነው» ብለው አወጁ። ይህንን አባባል ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር አልነበረም የቀሰቀሰው። የእውነት ኃይል እምቢተኛውን ከንፈር እኚህን ቃላቶች እንዲናገሩ ያስገድዳል። ኃጢአን ወደ መቃብር ሲገቡ ለክርስቶስ በነበራቸው ጠላትነት እና በተመሳሳይ የአመጻ መንፈስ ነው ከመቃብራቸው የሚወጡት። ያለፈውን የተጣመመ የቀድሞ ህይወታቸውን የሚያርሙበት አዲስ የምህረት ጊዜ አይኖራቸውም። በሕይወት ዘመናቸው ያደረጉት ኃጢአት ልባቸውን አላለሰለሰም። ሕይወታቸውን የመለወጥ ዳግም እድል ቢሰጣቸውም እንደቀድሞው በተመሳሳይ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመቃወም እና በርሱ ላይ አመጽን በማነሳሳት ይጠቀሙበት ነበር።ታተ 83.2

  ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ባረገበት እና መላዕክት የዳግም ምፅአቱን ተስፋ በተናገሩበት በዚያው በደብረ ዘይት ተራራ ይመጣል። ነብዩ እንዲህ ብሏል፤ «አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ይመጣል» «በዚያን ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምስራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ ደብረ ዘይት ተራራም በመካከል ወደ ምስራቅ እና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፤ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል። ... እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሳል፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር አንድ ስሙም አንድ ይሆናል።» (ዘካሪያስ 14፡5፣4፣9)፡፡ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም አሰደናቂ ውበቷን ተጎናጽፋ እየተገለጠች እያለ፣ በተቀደሰ እና በተዘጋጀላት ስፍራ ታርፋለች፣ ክርስቶስም ከህዝቡ እና ከመላዕክቱ ጋር ሆኖ ወደ ቅድስት ከተማ ይገባል።ታተ 83.3

  በዚያን ጊዜ ሰይጣን የበላይ ሆኖ ለመገኘት ለመጨረሻው ታላቅ ጦርነት ይዘጋጃል። ኃይሉን በመነጠቁ፣ የማሳሳት ተግባሩንም በመታደጉ ምክንያት የእርኩሳን አለቃ መመሰቃቀል እና ቁጡነት ይታይበታል፡፡ ዳሩ ግን ሞተው የነበሩትን እልፍ አእላፍ ኃጢአንን ከሞት ተነስተው ከጎኑ ሲመለከት ተስፋው ይታድሳል፤ እርሱም በታላቁ ተጋድሎ እጅ ላለመስጠት ይወስናል። የጠፉትን ሠራዊት ሁሉ በዓላማው ስር በማሰለፍ እቅዱን ለማስፈጸም ያግባባቸዋል። ኃጢአን የሰይጣን ምርኮኞች ናቸው። ክርስቶስን እምቢ በማለታቸው የአመጸኛውን ገዢ አገዛዝ ተቀብለዋል። የእርሱን ትዕዛዝ በመቀበል በእርሱ ለመመራት ዝግጁዎች ናቸው። እንደ ቀድሞው ተንኮሉ አሁንም ሰይጣን መሆኑን አይገልጥም። የምድር ባለቤት ራሱ እንደሆነ በማቅረብ ‹መብቱን› (ባለቤትነቱን) ያላግባብ እንደተነፈገ ልዑል ያስመስላል። በራሱ ኃይል ከመቃብር ያወጣቸው አዳኝ እርሱ እንደሆነና አሁንም ከጨካኙ ገዥ ሊያድናቸው የሚችል አዳኛቸው እንደሆነ አድርጎ ራሱን ለተከተሉት ተከታዮቹ ያቀርባል። ክርስቶስ ዞር ሲል የሚናገረው ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሰይጣን ተዓምራትን ይሰራል። ደካሞችን እንዲጠነክሩ ያደርጋቸዋል፣ ሌሎቹንም ሁሉ በመንፈሱ እና በኃይሉ ያነቃቃቸዋል። የእግዚአብሔርን ከተማ ለመውረስ በቅዱሳን ጉባኤ ላይ እንዲዘምቱ እቅዱን ያቀርብላቸዋል። ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ሚሊዮን ወደሚሆን ከሙታን ወደተነሱት ኃጢአኖች በመጠቆም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ከተማዋን በመገልበጥ መንግስቱን ሊያስመልስ እንደሚችል በጭካኔና በትዕቢት ይናገራል።ታተ 83.4

  በእነዚህ ሕዝቦች መካከል በኖህ ዘመን በነበረው ከጥፋት ውኃ በፊት ለረጅም ዘመን የኖሩ የሰው ዘሮች፣ ግዙፍ አካል እና ማስተዋል የነበራቸው ሰዎች፣ በወደቁት መላዕክት ቁጥጥር ስር ሆነው ዕውቀታቸውንና ጥበባቸውን ራሳቸውን ከፍ ከፍ ያደርጉ የነበሩ ሰዎች፣ በአስደናቂው ክህሎታቸው ዓለም እንደጣኦት ያመልካቸው የነበሩ ነገር ግን ክፉው ግኝታዊ ተግባራቸው እና ጭካኔያቸው ዓለምን ያረከሰ እና የመለኮትን ተምሳሌት ያበላሸ፣ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ከምድር ገጽ ላይ እንዲያጠፋቸው ምክንያት የሆኑ ሰዎች ነበሩ። መንግስታትን ድል የነሱ ንጉሶች እና የጦር አዛዦች፣ በጦር ሜዳ ሽንፈትን ያልቀመሱ፣ ትዕቢተኞች እና የጦርነት ጉጉታቸው ነገስታትን የሚያስፈራ ነበሩ። በመቃብር ውስጥ ምንም አይነት ለውጥ አላሳዩም። ከመቃብር በሚወጡበት ጊዜ አስተሳሰባቸው ያን ጊዜ ሲሞቱ ከቆመበት ቦታ ነው የሚቀጥለው። ያኔ ይገዛቸው የነበረውን ገዢ የመገርሰስ ተመሳሳይ ፍላጎት ይዘው ነው የሚነሱት።ታተ 83.5

  ሰይጣን ከመላዕክቶቹ ጋር፣ እንዲሁም ከእነኚህ ነገስታት፣ ተዋጊዎች እና ከኃያላን ሰዎች ጋር ይወያያል። እነሱም በዙሪያቸው ያሉትን ኃያላን እና የቁጥራቸውን ብዛት ሲመለከቱ በከተማይቱ ያሉት ቁጥር አናሳ በመሆኑ ድል መንሳት አይሳነንም ብለው ያውጃሉ። የአዲሲቷን ኢየሩሳሌም ሃብት እና ክብሯን ለመውረስ ዕቅድ ያወጣሉ። ወዲያውኑ ሁሉም በአንድነት ለጦርነት ይዘጋጃሉ። የተካኑ ጥበበኞች የጦር ስልቶችን ይወጥናሉ። በስኬታቸው የታወቁ የጦር መሪዎች የጦር ሰራዊቱን በየብርጌዱና በየሻለቃው ያሰልፋሉ።ታተ 84.1

  በመጨረሻም «ወደፊት!» የሚል ትዕዛዝ ተላለፈ፤ ጦርነት ከተጀመረበት ዘመን ሁሉ አንስቶ በዓለም ተሰልፎ የማያውቅ ቁጥር የሌለው ሠራዊት፣ ከዘመናት ሁሉ የተውጣጣ እና ማንም ሊመጥነው የማይችል ኃይል ወጣ። የተዋጊዎቹ አውራ የሆነውም ሰይጣን ክተቱን ሲመራ መላዕክቶቹ ለዚህ ለመጨረሻው ተጋድሎ ኃይላቸውን አስተባበሩ። ነገስታት እና ጦረኞች፣ በቡድን የተከፋፈሉ እጅግ ብዙ ሠራዊት ከነአዛዦቻቸው በእርሱ መሪነት ተከተሉት። የተሰለፉቱ ሠራዊት በወታደራዊ ጥንቃቄ በተመሰቃቀለችው መሬት ላይ እየተራመዱ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ተጠጉ። በኢየሱስ ትዕዛዝ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ደጆች ተዘጉ፤ የሰይጣን ሠራዊትም ከተማይቱን ከበው ለማጥቃት ተዘጋጁ።ታተ 84.2

  በዚያን ጊዜ እንደገና ክርስቶስ ለጠላቶቹ ተገለጠ። ከከተማይቱ በላይ በሚያብረቀርቀው በወርቁ መሠረት ላይ ዙፋኑ ወደላይ ከፍ ብሎ ታየ። በዚህ ዙፋን ላይ የእግዚአብሔር ልጅ ተቀምጧል፥ በዙሪያውም የመንግስቱ ግዛቶች ይገኛሉ። የክርስቶስን ኃይል እና ሞገስ ምንም ቋንቋ ሊገልጸው፣ ምንም አይነት ቀለም ሊጽፈው አይችልም። የዘላለማዊው የአባት ክብር ልጁን ከብቦታል። የመገኘቱ አንጸባራቂ ብርሃን የእግዚአብሔርን ከተማ ሞልቷል፣ ከከተማይቱም ደጅ ይፈነጥቃል፣ ምድርም ሁሉ በክብሩ ብርሃን ተሞልታለች።ታተ 84.3

  ከዙፋኑ አጠገብ በአንድ ወቅት በሰይጣን ጉዳዮች ልባቸው የቀና፣ ነገር ግን ከእሳት እንደ ተነጠቀ ትርኳሾ (ትንታግ) በትጋት እና በጉጉት አዳኛቸውን የተከተሉት ይገኛሉ። ከእነርሱም ቀጥለው ውሸት እና አለመታዘዝ በበዛበት መካከል ፍጹም የክርስትና ባህሪን የተተለማመዱት፣ የክርስትናው ዓለም ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢተውትም እንኳ፤ እነርሱ ግን ያከብሩ የነበሩ በዘመናት ሁሉ ለእምነታቸው ሲሉ የተሰው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቆመዋል። ከነሱ ባሻገርም «አንድም እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከህዝብ እና ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፥ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባ ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ» (ራዕይ 7፡9)፡፡ ጦርነታቸው ተጠናቅቋል፣ ድልንም ተቀዳጅተዋል። ሩጫቸውን ጨርሰዋል፣ ዋጋቸውን ሊያገኙ ተዘጋጅተዋል። በእጃቸው የያዙት የዘንባባ ዝንጣፊ የድል ነሺነታቸው ምልክት ነው፣ የለበሱት ነጭ ልብስ ደግሞ አሁን የለበሱት አንድም እድፍ እንኳን የሌለው የክርስቶስ ጽድቅ ነው።ታተ 84.4

  የተዋጁት ሁሉ ድምጻቸው ደግሞ ደጋግሞ በሰማያት እስኪያስተጋባ ድረስ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ «በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ መዳን ሆኗል» እያሉ ዘመሩ (ቁጥር 10)፡፡ ሱራፌል እና ሌሎች መላዕክት በውዳሴ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አጀቧቸው። የተዋጁት የሰይጣንን የክፋት ኃይል በሚመለከቱበት ጊዜ ከማንኛውም ጊዜ ይልቅ ከክርስቶስ ኃይል በስተቀር ማንም አሸናፊ ሊያደርጋቸው እንደማይችል ተገነዘቡ። ከነዚያ ከሚያበሩ ህዝብ ሁሉ መካከል «መዳን ይገባኛል» ወይም «በራሴ ኃይል እና መልካምነት ድልን ማግኘት ቻልኩ» የሚል ከቶ አልተገኘም። ስለ ሰሩት መልካም ሥራ ወይም ስለተሰቃዩት ስቃይ አንዳች የተባለ ነገር አልነበረም፤ የእያንዳንዱ ሰው ዝማሬ፣ የእያንዳንዱ የዜማ ቅላጼ «ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ሆኗል» የሚል ነበር።ታተ 84.5

  በምድር እና በሰማይ ውስጥ በሚኖሩት ነዋሪዎች ጉባኤ ፊት የእግዚአብሔር ልጅ አክሊሉን ተጎናጸፈ። በታላቅ ግርማ እና ኃይል የተሞላው የነገስታት ንጉስ በመንግስቱ ላይ አምፀው በነበሩት ላይ እንዲሁም ሕጉን በተላለፉት እና ህዝቦቹን በጨቆኑት ላይ ፍትሃዊ ፍርዱን አወጀ። የእግዚአብሔር ነብይ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- «ታላቅ እና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ ምድር እና ሰማይ ከርሱ ሸሹ፥ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾች እና ታላላቆች በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻህፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፡ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው። ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።» (ራዕይ 20፡11 እና 12)ታተ 84.6

  መጻሕፍት በተከፈቱ ጊዜ የክርስቶስ ዓይን ወደ ኃጢአን ሲመለከት፤ ያን ጊዜ የፈጸሙትን ኃጢአት ሁሉ ያስታውሳሉ። እግራቸው እንዴት ከንጽህና እና ቅድስና ጎዳና እንደተንሸራተተ ያስታውሳሉ፣ ትዕቢት እና አመጻ እንዴት በእግዚአብሔር ሕግ ላይ ወደ ማመፅ እንደመራቸው ይመለከታሉ። ኃጢአታቸውን ያስተባበሉበት ጊዜ፣ በረከቱን ያጣመሙበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን መልዕክተኞች የናቁበት ጊዜ፣ ማስጠንቀቂያውንም እምቢ ያሉበት ጊዜ፣ የምህረትን ጥሪ በግትርነታቸው እና ንስኃ በሌለው ልብ የተሳለቁበት ጊዜ፣ እነዚህ ሁሉ በእሳት እንደተጻፈ ፊደል ሆነው በግልፅ ያነቧቸዋል።ታተ 84.7

  ከዙፋኑ በላይ መስቀሉ ይታያል፡፡ የአዳም ፈተና እና ውድቀት፣ በተከታታይ የተወሰደው የድነት የእቅድ እርምጃ ሁሉ ልክ እንደ ፊልም ጎልቶ ይታያል። የአዳኙ ራስን ዝቅ ያደረገ መወለድ፣ በለጋነት የእደሜ ዘመኑ ያሳየው የቀናነት እና የመታዘዝ ሕይወት፣ የዮርዳኖስ ጥምቀቱ፣ ጾሙ እና የምድረ በዳ ፈተናው፣ የሰማይን አስደናቂ በረከት ለሰው የገለጸበት የአደባባይ አገልግሎቱ፣ በፍቅር እና በምህረት የተሞላው የዕለት ተግባሩ፣ ፀጥታ በሰፈነበት ተራራ ላይ የነበረው የሌሊት የጸሎት ትጋት፣ ሰዎች በእርሱ ላይ የነበራቸው ቅናት፣ ብቀላ እና የጥላቻ ዱለታ፣ በዓለም አድካሚ የኃጢአት ሸክም ክብደት ምክንያት የነበረው አሳዛኝና ምስጢራዊ የጌተሰማኔ ስቃይ፣ ለጨካኙ ገዳይ እጅ ተላልፎ መሰጠቱ፣ በዚያች ሌሊት የነበረው የሚያስፈራራ ክስተት፣ እምቢታን የማያውቅ እስረኛ በሚወዳቸው ወዳጆቹ የመተው ሁኔታ፣ በኢየሩሳሌም ጎዳና እየተገፈተረ መወሰዱ፥ የኃያሉ እግዚአብሔር ልጅ በሊቀ ካህናት ቦታ በተሾመው በሃና ፊት መቅረቡ፥ በጲላጦስ የፍርድ ዙፋን ፊት መቆሙ፣ ከጨካኙ እና ከሞኙ ሄሮድስ ፊት መቆሙ፣ የተሳለቁበት፣ የተሰደበው ስድብ፣ የተገረፈው ግርፊያ፣ እንዲሞት የተፈረደበት ፍርድ፣ ሁሉም እንደ ትዕይንት በግልጽ ይታያሉ።ታተ 85.1

  በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ላሉት አህዛብ የክርስቶስ የምድር ሕይወት የመጨረሻዎቹ ሰዓታት እንደ ፊልም ይታያቸዋል፡፡ የቀራንዮን ስቃይ የታገሰው ትዕግስተኛው አዳኝ፣ በመስቀል የተሰቀለው የሰማዩ ልዑል፣ የስቃይ ጣሩን ሲመለከቱ የነበሩት ትዕቢተኞቹ ካህናት እና ሲጮህ የነበረው ጉባኤ፣ ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የተከሰተው ጨለማ፣ የመሬት መናወጡ፣ የመሬት መሰንጠቁ፣ የመቃብር መከፈቱ፣ እነኚህ ሁሉ የዓለም መድህን ህይወቱን መስጠቱን አመላክተዋል።ታተ 85.2

  ይህ አስደንጋጭ ትዕይንት ልክ በተከሰተበት ቅደም ተከተል እንደገና ታየ። ሰይጣን፣ መላዕክቶቹ እና ተከታዮቹ የሰሩትን ሥራ ከማየት ፊታቸውን ሊያዞሩ ኃይል አልነበራቸውም። እያንዳንዱ ተዋናይ በዛን ወቅት የተውኔቱ ድርሻ ምን እንደነበረ በግልጽ ያስታውሳል። የእሥራኤልን ንጉሥ ለማጥፋት ሲል የቤተልሔም ንጹህ ህጻናትን ያረደው ሄሮድስ፣ የመጥምቁ ዮሐንስ ንጹህ ደም በደል ያረፈባት ሄሮዲያ፣ አቋም የለሹና ደካማው ጲላጦስ፣ ዘላፊዎቹ ወታደሮች፣ የካህናት እና ሊቃውንት እንዲሁም በእብደት እንደሰከሩ ሆነው «ደሙ በእኛ እና በልጆቻችን ይሁን» ብለው የጮሁ ካህናት፣ መሪዎች እና ያበዱት ህዝቦች፤ ሁሉም በአንድነት የበደላቸውን ግዙፍነት ይመለከታሉ። የዳኑቱ አክሊላቸውን ከአዳኛቸው እግር ስር ጥለው «እርሱ ለእኔ ሞተልኝ ሲሉ»፤ እነዚያ ግን ከጸሐይ በላይ ከሚያብረቀርቀው ከመለኮታዊው ግርማ ፊት ለመሸሸግ በከንቱ ይጥራሉ።ታተ 85.3

  ከተዋጁቱ መካከል የክርስቶስ ሐዋሪያት አሉ፤ የኃይማኖት አርበኛው ጳውሎስ፣ ችኩሉ ጴጥሮስ፣ ተወዳጁ እና ወዳጁ ዮሐንስ፣ እውነተኛ የልብ ወዳጅ የሆኑት ወንድሞች፣ ከእነርሱም ጋር ስለ ኃይማኖታቸው ሲሉ የተሰው አዕላፋት ሠራዊት ሲቆሙ፤ ከቅጥሯ ውጭ ግን እርኩስ እና አስጸያፊ ነገሮች በማድረግ እነዚህን ቅዱሳን ያሳድዱ፣ ያስሩ እና ያርዱ የነበሩ ሁሉ ይገኛሉ። የጭካኔ እና የእርኩሰት አውራ የነበረው ኔሮም ከዚያ ውስጥ ሆኖ በአንድ ወቅት ያሰቃያቸው እና ከመጠን ባለፈው ስቃያቸው ሰይጣናዊ ደስታ ያገኝባቸው የነበሩትን አሁን ግን በላቀ ደስታ ሲፈነድቁ ይመለከታቸዋል። የእርሱም እናት የሥራዋን ውጤት ለመመስከርና እንዴት አድርጋ ክፉ ባህርይን ለልጇ እንዳወረሰችው፣ በእርሷ ተፅዕኖና ምሳሌያዊነት ልጇ እንዴት ዓለምን የሚያናውጥ የወንጀል ፍሬን እንዳፈራ እዚያው ሆና ትመለከተዋለች።ታተ 85.4

  «የክርስቶስ አምባሳደር ነን» የሚሉ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ህሊና ለማገድ የማሰቃያ ቦታዎችን፣ እስር ቤቶችን እና የማቃጠያ ስፍራዎችን ያበጁ የነበሩ የጳጳሳዊው ስርዓት ካህናት እና ሊቃውንት ከዚያው ከደጅ ቆመዋል። «ከእግዚአብሔር በላይ ነን» በማለት የኃያሉን አምላክ ሕግ ለመቀየር ያስቡ የነበሩት ትዕቢተኞቹ ሊቀ-ጳጳሳትም እንዲሁ ቆመዋል። እነኚህ «የቤተክርስቲያን አባቶች ነን» የሚሉ ሁሉ ይቅርታ የሌለው ምላሽ በክርስቶስ ፊት ይሰጣሉ። ሁሉን አዋቂ የሆነው አምላክ በሕጉ ላይ ቅንዓት እንዳለው እና በምንም አይነት በደለኛውን ሳይቀጣ እንደማያልፍ አሁን እድሉ ካመለጣቸው በኋላ ይገነዘባሉ። የሚሰቃየው ህዝቡ ጉዳይ ክርስቶስን ግድ እንደሚለው እና የእነርሱ ጉዳይ ከእርሱ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ያኔ ይገነዘባሉ። «ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነኚህ ወንድሞቼ ላንዱ እንኳ ያደረጋችሁት፣ ለኔ አደረጋችሁት» የሚለው የገዛ ራሱን ቃላት ጥልቅ ትርጉምም ያኔ ይረዳሉ። (ማቴዎስ 25:40)ታተ 85.5

  ክፉዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ቅጥር ዙሪያ ከበው በሰማይ መንግስት ላይ በማደማቸው ፍርዳቸውን ይጠባበቃሉ። ለጉዳያቸው የሚከራከርላቸው ማንም አልተገኘም። በቂ ምክንያትም የላቸውም። የዘላለም ሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል።ታተ 85.6

  የኃጢአት ዋጋ ነጻነትና የዘላለም ሕይወት ሳይሆን ባርነት፣ ጥፋትና ሞት መሆኑ በዚያን ጊዜ ይረጋገጣል። ኃጢአተኞች የአመጸኛ ህይወታቸው ውጤት ምን እንደሆነ ይመለከታሉ። ከሁሉም የሚበልጠውን ዘላለማዊውን የክብር ግርማ ግብዣ ንቀዋል፡፡ አሁን ግን ይህንን ክብር ለማግኘት ፍላጎት ያላቸው ይመስላል። «ይህ ሁሉ የእኔ መሆን ይችል ነበር፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ ከራሴ ማራቅን መረጥኩኝ፤ ኦ! ምን አይነት እውርነት ነው! ሰላም፣ደስታ እና ክብርን በእርግማን፣ ኃፍረት እና ተስፋ መቁረጥ ለወጥኩት።» በማለት የሚጠፉቱ ይጮሃሉ። ሁሉም ወደ መንግስተ ሰማይ መግባት መከልከላቸው ፍትሃዊ መሆኑን ይስማሙበታል። ምክንያቱም በምድር ህይወታቸው «ይህ ሰው [ክርስቶስ] በእኛ ላይ እንዲነግስ አንፈቅድም» ብለው አውጀው ነበርና፡፡ታተ 85.7

  ልክ ህልም እንደሚያልም ሰው ኃጥአን የእግዚአብሔር ልጅ አክሊል ሲጫንለት ተመለከቱት። በእጁም ላይ እነርሱ የናቁትንና የተላለፉትን ትዕዛዛቱ ያሉበትን የመለኮታዊውን ሕግ ጽላቶች ተመለከቱ። የተዋጁት የሚያስደንቀውን የደስታ ፈንጠዝያ እና ውዳሴ፣ «ሁሉን የምትገዛ ጌታ ሆይ ሥራህ ታላቅ እና ድንቅ ነው የአህዛብ ንጉሥ ሆይ» (ራዕይ 15፡3) የሚለውን የዜማ ሞገድ ከቅጥሩ ውጭ ባሉት አእላፍ ጆሮ እስኪሰማ ድረስ ሁሉም በአንድ ድምጽ ካስተጋቡ በኋላ በግንባራቸው ተደፍተው ለሕይወት ልዑል ሰገዱለት።ታተ 86.1

  በዚያን ጊዜ ሰይጣን የክርስቶስን ግርማ ሞገስና ክብር ሲመለከት ደንዝዞ ቆመ። አንድ ወቅት ላይ የሚጋርድ ኪሩቤል የነበረው መልአክ ከየት እንደወደቀ አስታወሰ። ያ የሚያበራ ሱራፌል፣ «የንጋት ኮከብ» ምንኛ ተቀይሯል! ምንኛ ተዋርዷል! በአንድ ወቅት ተከብሮ ከነበረበት ጉባኤ አሁን ለዘላለም ተባርሯል። በእርሱ ቦታ በአባት አጠገብ ቆሞ ክብሩን የሚጋርደውን መልአክ ተመለከተ። ግርማ ሞገስ በነበረውና ልዩ አካል በነበረው መልአክ አማካኝነት በክርስቶስ ራስ ላይ አክሊል ሲጫን ተመለከተ፡፡ የዚህ ልዩ ሥልጣን የነበረው መልአክ ቦታ የእርሱ መሆን ይችል እንደነበረ ተገነዘበ።ታተ 86.2

  ያኔ ታማኝና ንፁህ በነበረበት ወቅት ይኖርበት የነበረውን ቤት፣ በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረምን ሳያስብ እንዲሁም በክርስቶስ ላይ ቅናት ሳይቀሰቀስበት በፊት የእርሱ የነበሩትን ሰላም እና ባለጸግነትን ሁሉ አስታወሰ፡፡ ክሶቹ፣ አድማው፣ የመላዕክቶችን ድጋፍና ሃዘኔታ ለማግኘት ሲል የጠነሰሰው የማታለል ሴራ፣ እግዚአብሔር ይቅር ሊለው በመፈለግ ከዚህ ጥፋት እንዲመለስ ጥሪ ሲያቀርብለት የነበረው ግትርነትና እምቢተኝነት እነዚህ ሁሉ አሁን እንደሚታይ ፊልም ይታዩት ነበር፡፡ በሰዎች መካከል የፈጸማቸውን ሥራዎችና ውጤታቸውንም ተመለከተ፡- ሰው ለሰው የነበረው ጠላትነት፣ አሰቃቂ የነፍስ ማጥፋት ሥራዎች፣ የነገሥታት መነሳት እና መውደቅ፣ የመንግሥታት መገልበጥ፣ ያልተቋረጠ የህዝብ አመጽ፣ ጦርነትና አብዮት፤ ሁሉም ተራ በተራ ድቅን አሉበት። ባልተቋረጠ ጥረት የክርስቶስን የወንጌል ሥራ በመቃወም ሰዎችን ለውድቀት እንዲዳረጉ ያደረገውን የአመፃ ሥራ ሁሉ አስታወሰ። ሰይጣናዊ ዱለታው በኢየሱስ ላይ ሙሉ እምነታቸውን የጣሉትን ለማጥፋት የሚያስችል ኃይል እንደሌለው ተመለከተ። ሰይጣን ተከታዮቹንና ግዛቱን ሲመለከት፤ የልፋቱ ፍሬ ውድቀትና ጥፋት ብቻ መሆኑን ተገነዘበ። ይህ ሊሆን እንደማይችል በትክክል ቢያውቅም የእግዚአብሔርን ከተማ በቀላሉ መውረር እንደሚቻል ከእርሱ ጋር የተሰበሰቡትን እልፍ አእላፍ አሳመነ፡፡ በታላቁ ተጋድሎ ፍልሚያ ውስጥ በተደጋጋሚ ሽንፈትን አስተናግዷል። የዘላለማዊውን አምላክ ግርማ እና ኃይልም ጠንቅቆ ያውቃል።ታተ 86.3

  ራሱን እውነተኛ ማድረግ እና መለኮታዊውን መንግስት [እግዚአብሔርን] ለአመጻው ተጠያቂ ማድረግ የታላቁ አመፀኛ ዓላማ ነበር። እስከ መጨረሻው ድረስ የነበረውን አስደናቂ ጥበብ ሁሉ ለዚህ ዓላማው አውሎታል። በጥንቃቄ፣ በዘዴና በሚያስደንቅ ስኬት የታላቁንና ለረጅም ጊዜ የቆየውን ተጋድሎውን ሂደት እልፍ አእላፍ የሆኑት ፍጡሮች እንዲቀበሉት ለዘመናት ሲያሳምን ቆይቷል። ይህ አውራ አድመኛ ለብዙ ሺህ ዘመናት ውሸትን በእውነት ቦታ ተክቷል። ነገር ግን አመጻው የሚሸነፍበት ጊዜ እንዲሁም የሰይጣን ታሪክ እና ባህሪ በገሃድ የሚጋለጥበት ጊዜ እነሆ አሁን መጣ። የክርስቶስን መንግስት ለመገልበጥ፣ ህዝቦቹንም ለማጥፋት፣ እና የእግዚአብሔርን ከተማ ለመውረስ በሚያደርገው በዚህ የመጨረሻ ጥረት የዚህ ሊቀ-አታላይ ባህርይ ይገለጣል። ከእርሱ ጋር የተባበሩት ሁሉ ጉዳዩ ያለቀለት መሆኑን ይረዳሉ። የክርስቶስ ተከታዮች እና ታማኝ መላዕክቶች አሁን ሰይጣናዊ ዱለታውንና ምስጢራዊ አድማውን በሙላት ይመለከታሉ። ሰይጣንም በመላው ዩኒቨርስ ሁሉ የተጠላ ይሆናል።ታተ 86.4

  ሰይጣን በፈቃደኝነት (በነጻ ምርጫ) ላይ የተመሰረተው አመጻው ለሰማይ ገጣሚ እንዳይሆን እንዳደረገው ይመለከታል። ኃይሉን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት ነበር ያሰለጠነው፡፡ በመንግስተ ሰማይ ውስጥ ያለው ንጽህና፣ ሰላም እና አንድነት ለእርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ስቃይ ነው። በእግዚአብሔር ምህረት እና ፍትህ ላይ የነበረው ክስ አሁን ጸጥ ተሰኘ። በእግዚአብሔር ላይ ይነዛ የነበረው የጥላቻ ዘመቻ አሁን ወደ ራሱ ተመለሰ። አሁን ሰይጣን ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ደፍቶ ስለ ፍርዱ ፍትኃዊነት መሰከረ።ታተ 86.5

  «ጌታ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና የጽድቅም ሥራህ ስለተገለጠ አህዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ።» (ራእይ 15፡4)፡፡ ዘመናትን ያስቆጠረው የእውነት እና የውሸት ተጋድሎ፣ እያንዳንዱ ጥያቄ አሁን መልስ አገኘ። የአመጽ ውጤት፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ወደ ጎን የመተው ፍሬ በሚያስተውሉ ፍጥረታት ዘንድ በግልጽ ታየ። የሰይጣን አገዛዝ ውጤት ከእግዚአብሔር መንግስት ጋር ተነጻጽሮ ለዩኒቨርስ ሁሉ ታየ። ሰይጣንን የገዛ እራሱ ተግባር ኮነነው። የእግዚአብሔር ጥበብ፣ ፍትኃዊነቱ፣ መልካምነቱ ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ። በታላቁ ተጋድሎ ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር አሰራር የህዝቡን እና እርሱ የፈጠራቸውን ዓለማት ሁሉ ዘላለማዊ ጥቅም ማዕከል ያደረገ አካሄድ መሆኑ ያን ጊዜ ይገለፃል። «አቤቱ ሥራህ ያመሰግኑሃል፣ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል» (መዝሙር 145:10)፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ እርሱ ለፈጠራቸው ፍጡራን ደስታን የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኃጢአት ታሪክ ለዘላለም ምስክር ሆኖ ፀንቶ ይቆያል። የታላቁን ተጋድሎ መጨረሻ በመመልከት በዩኒቨርስ የሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ፤ ታማኞችም ሆኑ አመጸኞች በሙሉ በአንድ ድምጽ «አቤቱ የቅዱሳን አምላክ ሆይ፣ መንገድህ እውነት እና ትክክለኛ ነው» በማለት ያውጃሉ።ታተ 86.6

  አባት እና ልጅ በሰው ምትክ ያደረጉት መስዋዕትነት በዩኒቨርስ ሁሉ ፊት በግልጽ ታየ። ክርስቶስ የሚገባውን ስልጣን የሚያገኝበት፣ ከሥልጣናት እና ከኃያላን እንዲሁም ከሌሎች ሥሞች ሁሉ በላይ ሆኖ የሚከብርበት ጊዜ አሁን ደረሰ። «ብዙዎቹን ልጆቹን ወደ ክብር በማምጣት ለሚያገኘው ደስታ» ሲል መስቀልን እና ሃፍረትን ሁሉ ቻለ። ስቃዩና ሃፍረቱ ከአቅም በላይ ቢሆኑም ደስታው እና ክብሩ ግን ከዚያ የበለጠ ታላቅ ነው። ጌታ እንደ እርሱ ምሳሌ ሆነው የተለወጡትን ፃድቃን፣ የእያንዳንዱ ልብ በፍፁም መለኮታዊነት ተማርኮ፣ የእያንዳንዳቸው ፊት ንጉሳቸውን ሲያንጸባርቁ ይመለከታል። በእነርሱ ውስጥ የነፍሱን ድካም ውጤት ተመልከቶ ይረካል። ከዚያም ሁሉም፣ ጻድቃንም ሆኑ ኃጢአን በሚሰሙት ድምጽ «እነሆ በደሜ የተዋጁት! ለእነርሱ ተሰቃይቻለሁ፣ ለእነርሱ ሞቼአለሁ፣ ለዘላለም እኔ ባለሁበት እነርሱም ይሆኑ ዘንድ» በማለት ያውጃል። ከዚያም ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑ ዙሪያ የነበሩት በታላቅ ድምጽ «የታረደው በግ ኃይል እና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም፣ ክብርም፣ ምስጋናም፣ በረከትም ሊቀበል ይገባዋል» የሚል መዝሙር ዘመሩ (ራዕይ 5:12)ታተ 87.1

  ሰይጣን የእግዚአብሔርን ቅን ፈራጅነት እንዲቀበል እና ለክርስቶስ ስልጣን ዝቅ እንዲል ቢገደድም ቅሉ ባህሪው ግን ከቶ አልተለወጠም። የአመጽ መንፈስ ልክ እንደ ታላቅ ማዕበል በውስጡ ይናወጣል። በቁጣ ተሞልቶ ታላቁ ተጋድሎን ላለመሸነፍ ወሰነ። ከሰማያዊው ንጉሥ ጋር የመጨረሻው ወሳኝ ፍልሚያ እንደ ደረሰ አሁን ተገነዘበ። ወደ ተከታዮቹ በመሮጥ በቁጣ መንፈስ በማነቃቃት ለወሳኙ ፍልሚያ ሊያነሳሳቸው ሞከረ። ነገር ግን ቁጥር ስፍር ከሌላቸው እርሱ አሳስቶ ወደዚህ አመጻ ካመጣቸው ውስጥ አሁን የእርሱን ስልጣን ማንም የተቀበለ አልነበረም። ኃይሉ አሁን አልቆለታል። ቢሆንም ኃጢአተኞች ልክ እንደ ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ በተመሳሳይ የጥላቻ ስሜት ተሞልተዋል፤ ነገር ግን ሁኔታው ተስፋ ቢስ እንደሆነና ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እንደማያሸንፉት ሲረዱ በሰይጣንና በማታለያ መሳሪያዎቹ ላይ ቁጣቸው ነደደ፤ ከዚያም በዲያብሎሳዊ ቁጣ በእርሱ ላይ ተነሱ።ታተ 87.2

  ጌታ እንዲህ ይላል «ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና፤ ስለዚህ እነሆ የሌላ አገር ሰዎችን የህዝብን ጨካኞች አመጣብሃለሁ። ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዛሉ፤ ክብርህንም ያረክሳሉ። ወደ ጉድጓድ ያወርዱሃል» … «ስለዚህ አረከስኩህ ከእግዚአብሔር ተራራ አሳደድኩህ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ ከእሳት ድንጋይ መካከል አጠፋሁህ፤ እኔ በምድር ጣልኩህ በነግስታት ፊት ያዩህ ዘንድ ሰጠሁህ፣ ... በምድር ላይ አመድ አደረግሁህ፣ በሚያዩህ ሁሉ ፊት ... ለድንጋጤም ትሆናለህ፣ ለዘላለምም አትገኝም» (ሕዝቅኤል 28:6-8, 16-19)ታተ 87.3

  «የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ በደም የተለወሰ ይሆናል፤ (የእርሱ ግን) በማቃጠል እና በእሳት ይሆናል» «የእግዚአብሔር ቁጣ በአህዛብ ላይ ነው፣መዓቱም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው። ፈጽሞ አጠፋቸው፣ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው።» «ወጥመድን በኃጢአን ላይ ያዘንባል እሳት እና ዲን ዓውሎ ነፋስም የጽዋቸው ዕድል ፋንታ ነው።» (ኢሳይያስ 9:5፣ 34:2 ፤ መዝ 11:6)፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳት መጣ፣ ምድርም ተከፈተች፣ የተደበቁ የጦር መሳሪያዎች ተመዘዙ፣ የሚበላ እሳትም ከየቦታው ብቅ ብቅ አለ፣ ድንጋዮች በእሳት ተያያዙ፣ «እንደ ምድጃ የሚያቃጥል ዘመን» መጣ፣ ቁሶች በሙሉ ምድርም ጭምር በግለቱ እንደ ገለባ ሆኑ፣ «ምድርም በእርሷ ያለውም ሁሉ ይቃጠላል»፣ «የሰማይ ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ቀለጠ» (ሚልክ. 4:1 ፤ 2 ጴጥ 3:10)፡፡ የምድር ዳርቻ ሁሉ እንደ ቀለጠ ነገር፣ እንደ ትልቅ የእሳት ባህር መሰለ። እነሆ የፍርድ ሰዓት ነው፣ ኃጢአን የሚጠፉበት፣ «የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው» (ኢሳ. 34:8)ታተ 87.4

  ኃጢአተኞች ብድራታቸውን በምድር ይቀበላሉ (ምሳሌ 11፡31)፡፡ እነርሱም «እንደ ገለባ ይሆናሉ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል። ይላል የሰራዊት ጌታ።» (ሚል 4፡1)፡፡ አንዳንዶቹ በቅጽበት ይሞታሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ለብዙ ቀናት ተሰቃይተው ይሞታሉ» ሁሉም «እንደ ሥራቸው ቅጣታቸውን ያገኛሉ»። የጻድቃን ኃጢአት ሁሉ ወደ ሰይጣን ይዛወራል፡፡ እርሱ የሚሰቃየው ስቃይ ስለ ራሱ አመጽ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጆች ኃጢአትን እንዲሰሩ ላደረገባቸው ኃጥአቶችም ጭምር ነው። የቅጣቱ አይነት እርሱ ካሳሳታቸው እጅግ የላቀ ነው። በእርሱ አማካኝነት የሳቱት ሁሉ ከጠፉ በኋላ እርሱ ቀጥሎ በስቃይ ይቆያል። በሚያነጻው የእሳት ወላፈን ኃጢአተኞች ይጠፋሉ፡፡ ሥር እና ቅርንጫፎች፡- ሰይጣን ሥር ሲሆን ተከታዮቹ ደግሞ ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ እነርሱ በመጨረሻ ይጠፋሉ። ህጉ የሚጠይቀውን ዋጋ መከፈሉን እና የፍትህ ፍላጎት መሟላቱን ሰማይና ምድር ይመለከታሉ፤ የጀሆባንም ፃድቅ ፈራጅነት ያውጃሉ፡፡ታተ 87.5

  የሰይጣን የጥፋት ሥራ ለዘላለም አከተመ። ለስድስት ሺህ ዘመናት ዓለምን በዋይታ በመሙላትና ዩኒቨርስን በሃዘን በማጥለቅለቅ ፈቃዱን ሲፈጽም ቆይቶ ነበር። ፍጥረት በሙሉ በአንድነት እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተት እና በምጥ ላይ ነበር። አሁን ግን የእግዚአብሔር ፍጡሮች ከሰይጣን መኖር እና ከፈተናው ለዘላለም አርነት ወጥተዋል። «ምድር ሁሉ አርፋ በጸጥታ ትቀመጣለች፣ [ቅዱሳንም] እልል ይላሉ::» (ኢሳ 14፡7) ታማኝ ከነበሩት የዩኒቨርስ ነዋሪዎች የምስጋና እና የድል ጩኸት ያስተጋባል። «እንደ ብዙ ህዝብም ድምጽ» «እንደ ብዙ ውኆችም ድምጽ፣ እንደ ብዙ ነጎድጓድም ድምጽ ያለ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል ‹ሃሌ ሉያ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሷልና»› (ራዕ 19፡6)ታተ 88.1

  ዓለም በአጥፊው እሳት ተከባ ሳለች ጻድቃን ግን በቅድስቲቱ ከተማ ከክፉ ተጠብቀው ይቆያሉ። በመጀመሪያው ትንሳኤ ዕድል ባገኙት ላይ ሁለተኛው ሞት ሥልጣን የለውም። ለኃጢአተኞች የሚባላ እሳት የሆነው እግዚአብሔር ለህዝቦቹ ግን የፀሐይ ብርሃን እና ጋሻቸው ነው። (ራዕ 20:6 ፤ መዝ 84:11)ታተ 88.2

  «አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና...» (ራዕ 21፡1) ኃጢአተኞችን የሚበላው እሳት ምድርን ያነጻታል። የእርግማን ጠባሳ ሁሉ ይጸዳል። ስለ ኃጢአት አስቀያሚ ውጤት ፃድቃንን እያስታወሳቸው የሚኖረው ለዘላለም የሚቃጠለው የሲኦል እሳት አይደለም ።ታተ 88.3

  አንድ መታሰቢያ ብቻ ይኖራል፤ አዳኛችን የመሰቀሉን ምልክት ለዘላለም ይሸከመዋል። በቆሰለው ራሱ ላይ፣ በተወጋው ጎኑ፣ እጁና እግሩ ላይ ብቻ ያሉት ኃጢአት ያስከተላቸው የጭካኔ ምልክቶች ናቸው ለመታሰቢያነት የሚቆዩት። ክርስቶስን በታላቅ ክብሩ የተመለከተው ነብይ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- «ጸዳሉም እንደ ብርሃን ነው ጨረር ከእጁ ወጥቶዋል ኃይሉም በዚያ ተሰውሯል» (ዕምባ 3፡4)፡፡ ከዚያ ከተወጋው ጎኑ የፈሰሰው ደም ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቋል፤ከዚያ የጌታ ክብር አለ፤ «ከዚያ ኃይሉም ተሰውሮዋል»። ሰዎችን ለማዳን በከፈለው መስዋዕትነት አማካኝነት «ሊያድን የሚችል ኃያል» ስለሆነ እርሱ የእግዚአብሔርን ምህረት በናቁት ላይ ሁሉ ሊፈርድ ይችላል። የመዋረዱ ምልክቶች ለእርሱ ታላቅ ክብሩ ሆኑለት፤ በመሆኑም የቀራንዮ ቁስል ከዘላለም እስከ ዘላለም የእርሱን ምስጋና እና ኃይሉን ያበስራል።ታተ 88.4

  «አንተ የመንጋ ግንብ ሆይ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ፥ ወዳንተ ትመጣለች የቀደመችው ግዛት የኢየሩሳለም ሴት ልጅ መንግስት ትደርሳለች።» (ሚክያስ 4፡8)፡፡ የመጀመሪዎቹ ጥንዶች በሚንቦገቦገው ሰይፍ ከኤደን ገነት ከተባረሩበት ዕለት ጀምሮ ጻድቃን ሰዎች በከፍተኛ ጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የመዳን ቀን፡- «ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ» የተባለለት ቀን አሁን ደረሰ (ኤፌ 1፡14)፡፡ በመጀመሪያ ለሰው ልጅ ግዛቱ እንዲሆን የተሰጠው ምድር በኋላም በሰይጣን እጅ የተወረሰው እስካሁንም በታላቁ ጠላት እጅ የነበረው፣ በታላቁ የድነት ዕቅድ አሁን ተመለሰ። በኃጢአት ምክንያት ተቀምቶ የነበረው አሁን እንደገና ተመለሰ። «ምድርን የሰራና ያደረገ ያጸናትም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- መኖሪያ ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠረ» (ኢሳ 45፡18)፡፡ ዓለም የጻድቃን መኖሪያ እንድትሆን እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር የነበረው የመጀመሪያ እቅዱ አሁን ተሳካ። «ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ ለዘላለምም ይኖራሉ» (መዝ 37:29)ታተ 88.5

  እንደምንወርስ ተሰፋ የተገባልንን የሰማይ መኖሪያ ቤት ቁሳዊነትን ብቻ በማጉላት፣ ብዙዎች የዚህን እውነት መንፈሳዊ ይዘት በማጣት እውነተኛ ቤታችን መሆኑን እንዲዘነጉት አድርጓል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በአባቱ ቤት መኖሪያ ሊያዘጋጅላቸው እንደሚሄድ አረጋግጦላቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል ትምህርት የሚቀበሉ ሁሉ ስለ ሰማያዊው ቤት እንዳላዋቂ አይሆኑም። ሐዋሪያው ጳውሎስ «አይን ያላየው ጆሮም ያልሰማው በሰው ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቷል» (1ኛ ቆሮ 2፡9) በማለት ተናግሯል፡፡ የጻድቃንን ሽልማት ሰብአዊ ቋንቋ በበቂ ሁኔታ አይገልጸውም። የሚያዩት ብቻ ናቸው ሊገልፁት የሚችሉት። አላፊ የሆነ ሰው (ሟች ሰው) አእምሮ የእግዚአብሔርን ገነት ክብር ሊያስተውለው አይችልም።ታተ 88.6

  የጻድቃ ውርስ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ሃገር» ተብሎ ይጠራል (ዕብ 11:14-16)፡፡ በዚያም ሰማያዊው እረኛ መንጋውን ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራል። የሕይወት ዛፍ በየወሩ ፍሬውን ይሰጣል፣ የዛፉም ቅጠሎች ህዝቡን ያገለግላሉ። ወንዞችም እንደ ብርጭቆ የነጹ ሆነው ያለማቋረጥ ይፈሳሉ፡፡ በእነርሱ ዳርም ለጌታ ለተዋጁት መንገዳቸው ላይ ጥላቸውን የዘረጉ የሚወዛወዙ ዛፎች ይገኛሉ። ለጥ ያሉ ሜዳዎች በሚያምር ሁኔታ ወደ ተዋቡ ኮረብቶች ያብጣሉ። የእግዚአብሔር ተራሮችም በእነኚህ ኮረብቶች ታጅበዋል። በእነኚያ ከሕይወት ውኃ ምንጭ አጠገብ ባሉት ሰላማዊ ሜዳዎች በመናኝ እና በጉዞ ላይ የነበሩ የእግዚአብሔር ህዝቦች አሁን ማረፊያ ያገኛሉ።ታተ 88.7

  «ህዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።» «ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፣ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልና ቅጥቃጤ አይሰማም፣ ቅጥርሽን መዳን፣ በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ።» «ቤቶችንም ይሰራሉ፣ ይቀመጡባቸዋል፣ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሰሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፣... እኔም የመረጥኳቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።» (ኢሳ 32፡18 ፤ 60፡18 ፤ 65፡21 እና 22)ታተ 88.8

  በዚያ «ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይለዋል። በረሃውም ሐሴት ያደርጋል፣ እንደ ጽጌረዳም ያብባል።» «በእሾህም ፋንታ ጥድ በኩርንችትም ፋንታ ባርሰነት (ጽጌረዳ) ይበቅላል። ለእግዚአብሔርም መታሰቢያና ለዘላለም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።» «ተኩላም ከበግ ጋር ይቀመጣል ነብርም ከፍየል ጋር ያርፋል‹ ... ታናሽ ብላቴናም ይነዳቸዋል። (ኢሳ 35፡1፣ 55፡13፣ 11፡6 እና 9)ታተ 89.1

  በሰማይ መኖሪያ ቤት ስቃይ አይኖርም። እምባም ከቶ አይኖርም፣ የቀብር ስነ ስርአትም፣ የሃዘን ምልክትም አይኖርም። «ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሃዘንም ቢሆን ወይም ጩኽት ... የቀድሞው ሥርዓት አልፏልና» «በዚያ የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም፣ በዚያ የሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል» (ራዕ 21፡4፣ ኢሳ 33፡24)ታተ 89.2

  የከበረችው የአዲስቷ ምድር ዋና ከተማ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም በዚያ ትሆናለች፡፡ «በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግስት ዘውድ ትሆኛለሽ።» «ብርሃኗ እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ እያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ» «አህዛብም በብርሃኗ ይመላለሳሉ፣ የምድርም ነግስታት ክብራቸውን ወደርሷ ያመጣሉ።» ይላል ጌታ፡፡ «በኢየሩሳሌም ደስ ይለኛል፣ በህዝቤም ሐሴት አደርጋለሁ» «እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፣ ከእነርሱ ጋርም ያድራል፣ እነርሱም ህዝቡ ይሆናሉ፣ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።» (ኢሳ 62:3፣ ራዕ 21:11,24፣ ኢሳ 65:19፣ ራዕ 21:3)ታተ 89.3

  በእግዚአብሔር ከተማ «ሌሊት ከቶ አይኖርም»፡፡ ማረፍ የሚፈልግ ወይም የሚመኝ ማንም አይኖርም፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸምም ሆነ ውዳሴን ለእርሱ ለማቅረብ «ደከመኝ» የሚል አይገኝም። የማያቋርጥ የመታደስ ስሜት ይሰማናል፡፡ ይህ ስሜት ከእኛ መቼም አይርቅም። «የመብራት ብርሃን፣ የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ጌታ አምላክ በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና።» (ራዕ 22፡5)፡፡ ከፀሐይ በሚመነጨው ሃይለኛ ጨረር እንዳንጎዳ ከለላ ይደረጋል፣ ይህ ከለላ ቢኖርም ከፀሐይ የምናገኘው የብርሃን ኃይል ከቀትር ፀሐይ እጅግ የሚበልጥ ይሆናል። የእግዚአብሔር እና የበጉ ክብር በማይደበዝዝ ብርሃን ቅድስቲቷን ከተማ ያጥለቀልቃሉ። ጻድቃን ፀሐይ-አልባ በሆነው ዘላለማዊ ቀን ክብር ይረማመዳሉ።ታተ 89.4

  «ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ እና በጉ መቅደሷ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም» (ራዕ፡ 21-22)፡፡ የእግዚአብሔር ህዝቦች ከአብ እና ወልድ ጋር ፊት ለፊት የመነጋገር ዕድል ያገኛሉ። «ዛሬ በመስታወት በድንግዝግዝ እናያለን» (1ኛ ቆሮ 13፡12)፡፡ ዛሬ የእግዚአብሔርን ምስል በመስታወት እንደሚንፀባረቅ፣ በተፈጥሮ ውስጥ እና እርሱ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት አማካኝነት እናያለን፡፡ በዚያን ጊዜ ግን ድንግዝግዝ ሳይጋርደን ፊት ለፊት እናየዋለን። በእርሱ ፊት ቆመን የፊቱን ክብር እንመለከታለን።ታተ 89.5

  በዚያ ቦታ የተዋጁት እራሳቸው እንደሚታወቁ ሁሉ እርሱን ያውቁታል። እግዚአብሔር ራሱ በልባቸው ውስጥ የተከለው ፍቅር እና ርህራሄ በዚያ ቦታ እውነተኛውንና ጣፋጩን ልምምድ ያገኛል። ከቅዱሳን ፍጥረታት ጋር የሚኖራቸው ቅዱስ ግንኙነት፣ ከብሩካን መላዕክት እና በበጉ ደም ልብሳቸውን ታጥበው ካነጹት የዘመናት ታማኞች ጋር የሚኖራቸው ፍጹም ህብረት «ከሰማይ እና ከምድር ቤተሰቦች ጋር» (ኤፌ 3፡15) የሚያስተሳስራቸው የተቀደሰ ገመድ እነዚህ ናቸው የጻድቃን የደስታ ምንጭ መሰረቶች።ታተ 89.6

  በዚያ ሥፍራ የማይሞት አዕምሮን የያዙ ሁሉ በዘላለማዊ ተድላ ውስጥ ሆነው የፈጣሪን ኃይል፣ ተአምርና የማዳንን ፍቅር ሚስጢር ይመረምራሉ። በዚያ ቦታ እግዚአብሔርን እንድንረሳ የሚያደርገን ጨካኝና አታላይ ጠላት አይኖርም። እያንዳንዱ የአእምሮ ክፍል ያድጋል፣ እያንዳንዱ ብቃትም እየጨመረ ይሄዳል። በየእለቱ የሚገኘው አዲስ እውቀት አእምሮን አያደክምም ኃይልንም አያዝልም። በዚያ የምንሰራቸው ማንኛውም አይነት ሥራዎች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ የምናቅዳቸው ግዙፍ እቅዶች ሁሉ ይፈፀማሉ፡፡ የምንመኛቸው ምኞቶችም ይሟላሉ፡፡ ይህንን ሁሉ ማድረግ ቢቻልም፣ ሁልጊዜ አዳዲስ ግኝቶችን እናገኛለን፣ አዳዲስ ተአምራቶችን እናደንቃለን፣ አዳዲስ እውነቶችን እንማራለን፣ አዳዲስ ነገሮች የአእምሮአችንን፣ የአካላችንንና የነፍሳችንን ኃይል ያጎለብታሉ፡፡ታተ 89.7

  በዩኒቨርስ የሚገኙትን መዝገቦች ሁሉ የእግዚአብሔር ጻድቃን እንዲያጠኑት በሩ ክፍት ይደረግላቸዋል። ከሟች አካል እስራት ነፃ ሆነው በማይደክም በረራ በክንፋቸው በመብረር በሰው ፍጥረት ውድቀት የሃዘን እሮሮ ምክንያት አዝነው ለነበሩትና በተዋጁት ነፍሳት መልካም ዜና ምክንያት የደስታ ዜማ ወዳ ሰሙት ወደ እሩቅ ዓለማት ይበራሉ። በቃላት ሊገለጽ በማይቻል ደስታ ከምድር የተዋጁት የእግዚአብሔር ልጆች በኃጢአት ካልወደቁት ፍጥረታት ደስታ እና ጥበብ ጋር ይቀላቀላሉ። እነዚህ በኃጢአት ያልወደቁት ፍጥረታት የእግዚአብሔርን ታላላቅ ሥራዎች በማድነቅ ለዘመናት በሕይወታቸው ስላገኙት እውቀትና ማስተዋል ጻድቃን ይመለከታሉ። ባልደበዘዘ መገለጥ የፍጥረታትን ክብር ይመለከታሉ፡፡ ፀሐዮች ከዋክብትና ፕላኔቶች በሙሉ በተመደበላቸው ስርዓት ሳይዛነፉ በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ ሲሽከረከሩ ይመለከታሉ። ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ ባሉ ነገሮች ሁሉ ላይ የፈጣሪ ስም ተጽፏል፣ በሁሉም ነገሮች ላይ የኃይሉ ብዛት ተገልጿል ።ታተ 89.8

  የተጀመሩት ዘላለማዊ ዓመታት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ክርስቶስ የበለጸገ እና የከበረ መገለጥን ያበስሩልናል። እውቀት እለት በእለት እያደገ ሲሄድ፤ ፍቅር፣ አክብሮትና ደስታ እያደር ይጨምራሉ። ሰዎች እግዚአብሔርን የበለጠ ባወቁ ቁጥር ለባህሪው ያላቸው አድናቆት የዚያኑን ያህል ያድጋል። ጌታ ኢየሱስ ስለ ድነት፣ ባለጠግነትና ከሰይጣን ጋር በተደረገው አስደናቂ ተጋድሎ ስለተገኘው ድል የበለጠ ግልጽ ባደረገላቸው መጠን የተዋጁት ጻድቃን ልባቸው በአድናቆት እና በታላቅ ደስታ ተሞልቶ የወርቅ በገናቸውን በእልልታ ይመታሉ። እልፍ አእላፋት ድምጾችም የውዳሴ መዝሙርን በማሰማት ህብረቱን ይቀላቀላሉ።ታተ 90.1

  «በሰማይና በምድርም፣ ከምድርም በታች በባህርም ላይ ያለ ፍጥረትም ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያሉ ሁሉ፣ በረከት እና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉ ይሁን ሲሉ ሰማሁ።» (ራዕይ 5:13)ታተ 90.2

  ታላቁ ተጋድሎ አሁን ተጠናቀቀ። ኃጢአት እና ኃጢአተኞች ከእንግዲህ ወዲህ የሉም። ዩኒቨርስ በሙሉ ጸድቷል። አንድነት እና ደስታ እጅግ ሰፊ በሆነው ፍጥረት ውስጥ ሰልጥነዋል። ሁሉን ከፈጠረው አምላክ ከእርሱ ሕይወት፣ ብርሃንና ደስታ ወሰን በሌለው ዩኒቨርስ ሁሉ ላይ ይፈሳሉ። ከአንዷ ደቃቅ አቶም ጀምሮ እስከ ታላቁ ዓለም ድረስ፣ ሕይወት ያላቸውም ሆነ ሕይወት የሌላቸው ሁሉ፣ ያልተጋረደው ውበታቸውንና ፍፁም ደስታን ተጎናጽፈው እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ ይገልፃሉ።ታተ 90.3

  Larger font
  Smaller font
  Copy
  Print
  Contents