Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ 5 - ቅድስና

    እግዚአብሔር የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቶናል «እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ» (ኤር.29:13)።ክየመ 40.1

    ሰብዓዊው ልብ ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር እስካልተማረከ ድረስ፣ በአምላካዊው አምሳል እየተቀረጽንና እርሱን እየመሰልን መሄድ አንችልም፡፡እኛ በተፈጥሯችን ከእግዚአብሔር ተነጥለናል፡፡ እኛ የምንገኝበትን ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ እንደሚከተለው ይገልጸዋል:- «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ» (ኤፌ. 2:1) «ራስ ሁሉ ለሕመም፤ ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል» (ኢሳ. 1፡5)፡፡ «በዲያብሎስ ወጥመድ» አጥብቀን ተይዘናል (2ኛጢሞ. 2:26)፡፡ እግዚአብሔር እኛን ለመፈወስና ነጻ ለማውጣት በብርቱ ይመኛል፡፡ ነገር ግን ይህ ሙሉ ለሙሉ መለወጥንና የተፈጥሮአችንን መታደስ የሚጠይቅ እስከሆነ ድረስ መላው እኛነታችንን ለእርሱ ማስረከብ ይኖርብናል፡፡ክየመ 40.2

    ከጦርነቶች ሁሉ የላቀው ጦርነት ከራስ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ነው።እኔነት መላው ፈቃዱን ለእግዚአብሔር በማስገዛት እጁን በምርኮ ይሰጥ ዘንድ ብርቱ ፍልሚያ ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም አንዲት ነፍስ ከመታደሷና ከመቀደሷ አስቀድሞ እራሷን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ማስገዛቷ የግድ ነው::ክየመ 40.3

    የእግዚአብሔር መንግሥት ሰይጣን አስመስሎ ሊያቀርብ እንደሚሞክረው በጭፍን መገዛት እና ምክንያታዊነት የሌለበት ኢፍትሐዊ የባርነት ሥርዓት አይደለም፡፡ በተቃራኒው እግዚአብሔር ወደ አዕምሮአችንና ህሊናችን በመምጣት «ኑና እንዋቀስ» (ኢሳ. 1:18) በማለት ለፍጡሩ ሁሉ የፍቅር ግብዣውን ያቀርባል፡፡ እግዚአብሔር ፍጡራኑን አስገድዶ ፈቃዱን የሚያደርግ አምላክ ባለመሆኑ በፈቃደኝነትና በማስተዋል ላይ ያልተመሰረተን አምልኮ መቀበል አይችልም፡፡ በግዳጅነት የተመሰረተ እራስን መስጠት እውነተኛውን የአዕምሮአዊ ዕድገትና የባህሪ መጎልበት በማገድ ሰብዓዊውን ፍጡር ከአንድ ግዑዝ ማሽን ያልተለየ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የፈጣሪ ዓላማ አይደለም:: እርሱ የሚመኘው የፍጥረት ሥራው አክሊል የሆነው ሰብዓዊው ፍጡር ዘወትር እያደገ በመሄድ ሊደርስ ወደ ሚችለው ከፍ ያለ ማዕረግ ላይ እንዲደርስ ነው:: እርሱ በጸጋው ወደ ራሱ ሊያመጣን በመመኘት የተትረፈረፈ ባርኮቱን ከፊት ለፊታችን በመዘርጋት ሥራውን በእኛ ውስጥ መሥራት ይቻለው ዘንድ እራሳችንን ለእርሱ እንድናስረክብ ይጋብዘናል፡፡ ከኃጢአት እሥራት ተፈትተን የእግዚአብሔር ልጆች የሚያገኙትን በክብር የተሞላ ነጻነት እንካፈል ዘንድ እነሆ ምርጫውን ለእኛ ትቶአል፡፡ እራሳችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ስንሰጥ፤ ከእርሱ የሚለዩንን ነገሮች ሁሉ ፍጹም መተው ይኖርብናል፡፡ ይህን አስመልክቶ አዳኙ እንዲህ ይላል «እንደዚሁም ከእናንተ ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም» (ሉቃ. 14፡33)፡፡ ልባችንን ከእግዚአብሔር የሚያርቀውን ነገር ሁሉ መተው ይገባናል፡፡ ለሐብት ቅድሚያ መስጠት የብዙዎች ጣዖት ነው:: የንዋይ ፍቅርና የተትረፈረፈ ሐብት የማግኘት አባዜ ለሰይጣን ጠፍንጎ የሚሰጥ የወርቅ ሰንሰለት ነው:: መልካም ስም ማግኘትና ዓለማዊ ክብርን መጎናጸፍ የብዙዎች ጣኦት ሲሆን፤ በንፉግነት የታጠረ የምቾት ኑሮ እየኖሩ ሌሎችን በመርዳት የሚገባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣት እንዲሁ ሌላው ጣዖት ነው:: በመሆኑም ሙሉ በሙሉ ካልሆነ በስተቀር በከፊል የእግዚአብሔር ልጆች መሆን አንችልም::ክየመ 40.4

    የእግዚአብሔርን ሕግ ለመታዘዝ፣ ትክክለኛውን ባህሪ በውስጣቸው ለመፍጠርና ድነትን ለማግኘት በራሳቸው ጥረት ብቻ እየተመኩ እግዚአብሔርን እያገለገሉ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ አሉ፡፡ ልባቸው ጥልቅ በሆነው የክርስቶስ ፍቅር ያልተነካ፣ «አንድ ክርስቲያን ወደ ሰማይ ለመግባት በሕይወቱ መፈጸም አለበት» ብለው የሚያምኗቸውን ተግባራት ሁሉ ለማከናወን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ኃይማኖት ከንቱ ነው:: ክርስቶስ በልብ ውስጥ ሲያድር ያቺ ነፍስ ከእርሱ ጋር በሚኖራት ግንኙነት አብልጣ በፍቅሩ ትሞላለች፣ ከእርሱ ጋር ትጣበቃለች እንዲሁም እርሱን ብቻ በማሰላሰል እኔነትን ትዘነጋለች፡፡ ለክርስቶስ የሚኖረን ፍቅር ለታላቅ ሥራ የሚያነሳሳ ኃይል ይሆነናል፡፡ የእግዚአብሔርን ብርቱና ግድ የሚል ፍቅር የሚለማመዱ ሁሉ «የእግዚአብሔርን መጠይቅ አሟላ ዘንድ አሳልፌ መስጠት ያለብኝ አነስተኛው ነገር ምን ይሆን?» ብለው አይጠይቁም፡፡ ከልብ በሆነ መሻት ሁሉንም ለእርሱ በማስገዛት ለዚያ ዋጋ ላለው ነገር ያላቸውን ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ የክርስቶስን ጥልቅ ፍቅር ሳይረዱና ሳያስተውሉ እርሱን አገለግለዋለሁ ማለት ከባዶ ወሬና ከደረቅ ሥርዓት እንዲሁም ከአድካሚ ተግባር የዘለለ አይሆንም::ክየመ 41.1

    ያለንን ነገር ሁሉ ለክርስቶስ መስዋዕት አድርገን መስጠታችንን እንደ ትልቅ ነገር እንቆጥረው ይሆን? «ክርስቶስ ለእኔ የሰጠው ስጦታ ምንድን ነው?» ብላችሁ እስቲ እራሳችሁን ጠይቁ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መላ ሕይወቱንና ፍቅሩን በመስጠት ለእኛ ድነት ሥቃይ ተቀበለ፡፡ ይህ ታላቅ ፍቅር የማይገባን ሆኖ ሳለ እንዲህ ላደረገልን ጌታ ልባችንን መንፈግ ይቻ ለናል? የሕይወታችን እያንዳንዱ ደቂቃ የጸጋው ባርኮት ተካፋይ መሆኑን ከልብ ስለማናስተውል፤ የዳንነው ከእንዴት ያለ የከፋ አለማወቅና ሥቃይ አዘቅት ውስጥ እንደሆነ ብዙ ጊዜ እንዘነጋለን፡፡ ኃጢአታችን ወደ ወጋው ጌታ በመመልከት ስለ ፍቅሩና ስለ ከፈለው መስዋዕትነት ስንል ማድረግ የሚገባንን ለመሥራት ፈቃደኞች ነን? የክብር ጌታ ላይ ከደረሰው ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ ከማይችል መጠነ ሰፊ ውርደት አኳያ ወደ ዘላለም ህይወት የምንገባው በትግልና እራስን ዝቅ በማድረግ ብቻ በመሆኑ ልናጉረመርም ይገባል?ክየመ 42.1

    ብዙዎች ልባቸው የታበየ «እግዚአብሔር የሚቀበለኝ መሆኑን እርግጠኛ ሳልሆን ለምን ብዬ ነው ራሴን የማዋርደው?» ሲሉ ይጠይቃሉ:: እስቲ ወደ ክርስቶስ እንመልከት፣ እርሱ ኃጢአት የሌለበት ብቻ ሳይሆን የሰማይ ልዑልም ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለሰብዓዊው ዘር ሲል ኃጢአት ሆነ «ከክፉ አድራጊዎችም ጋር በመቆጠሩ፣ የብዙዎችን ኃጢአት ተሸከመ፤ ስለ አመጸኞችም ማለደ» (ኢሳ. 53:12)፡፡ክየመ 42.2

    ሁሉን ለእርሱ ስናስረክብ የትኛውን ነው ለራሳችን የምናስቀረው? ኢየሱስ በኃጢአት የተበከለውን ልብ በደሙ ሲያነጻ፣ ሲያጠራና ወደር በሌለው ፍቅሩ ሲያድን፤ ሰብአዊ ፍጡር ግን ሁለንተናውን ለእርሱ ማስረከቡ አስቸጋሪ እንደሆነ አድርጎ ሲያስብ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሲነገር ስሰማም ሆነ ስጽፈው ያሳፍረኛል!ክየመ 43.1

    እግዚአብሔር አስፈላጊያችን የሆነውን ማንኛውንም ነገር እንተው ዘንድ አይጠይቀንም:: እርሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ለልጆቹ ደህንነት የሚበጀውን ነው:: ክርስቶስን ያልመረጡት ነፍሳት ሁሉ ለራሳቸው ጥቅም ከሚሹት ነገር ሁሉ በእጅጉ የላቀውን እርሱ ሊሰጣቸው የሚችል መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሲያስብና ሲያደርግ ታላቅ ጉዳትና ኢፍትሐዊነት በገዛ ነፍሱ ላይ ያደርጋል፡፡ ለፍጡሮቹ የበለጠውን የሚያውቀውና የሚያቅደው አምላክ በከለከለው ጎዳና ላይ ምንም ዓይነት እውነተኛ ደስታ ሊገኝ አይችልም፡፡ የኃጢአት ጎዳና የሥቃይና የጥፋት መንገድ ነው::ክየመ 43.2

    የተሰጠንን የመምረጥ ኃይል በመለማመድ በሕይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

    የሰው ልጅ ደስ ይሰኝ ዘንድ የሰማይ ሁሉ ፍላጎት እንደመሆኑ፤ እግዚአብሔር ልጆቹ ሲሰቃዩ በማየት ይደሰታል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ሰማያዊው አባታችን በማንኛውም ፍጡር ላይ የደስታን ጎዳና አይዘጋም፡፡መለኮት ለእኛ የሚያቀርበው ጥሪ፣ ደስታን ከእኛ አርቀው ሥቃይና ተስፋ መቁረጥን በማምጣት ሰማያዊውን ደጃፍ ከሚያዘጉብን ኃጢአቶች እንድንርቅ ነው:: የዓለም አዳኝ የሆነው አምላክ ሰዎችን ከነመሻታቸው፣ከነጉድለታቸውና ከነድካማቸው በመቀበል ኃጢአታቸውን በደሙ በማንጻት ይቅርታን ማሰጠት ብቻ ሳይሆን ቀንበሩን ሊሸከም የሚናፍቀውን ልብ ሁሉ ያረካዋል፡፡ የሕይወት እንጀራን ፈልገው ወደ እርሱ ለሚመጡ ሁሉ ሰላምና እረፍት ሊያካፍላቸው ፈቃደኛ ነው:: እኛ እናከናውነው ዘንድ የሚጠይቀን ተግባር ሰው በራሱ ጥረት ሊደርስበት ወደ ማይችለው፣ ከፍ ያለ ደስታ ወደምናገኝበት ደረጃ እንድንወጣ ነው:: ሕይወት በእውነተኛ ደስታ የተሞላ የሚሆነው የክብር ተስፋ የሆነው ክርስቶስ በዚያች ነፍስ ውስጥ ሲኖር ብቻ ነው::ክየመ 43.3

    ብዙዎች «እንዴት አድርጌ ራሴን ለእግዚአብሔር ማስገዛት እችላለሁ?» ብለው ሲጠይቁ ይደመጣሉ፡፡ ራስዎን ለእርሱ ለመስጠት ቢመኙም ነገር ግን ያን ለማድረግ ወኔ ቢስና የጥርጣሬ ባሪያ በመሆንዎ በሚሠሯቸው ልማዳዊ ኃጢአቶች ቁጥጥር ስር ውለው ይሆናል፡፡ የእርስዎ ቃል ኪዳንና ቆራጥነት እንደ አሸዋ ገመድ ሊሆንም ይችላል፡፡ አጉል ሃሳብና ምኞትዎን በመቆጣጠር መሻትዎን መግዛት አልሆነልዎትም ይሆናል፡፡ ያፈረሱት ቃል ኪዳን በራስዎ ላይ ሊኖርዎ የሚገባውን ከልብ የመነጨ መተማመን ስለሚያዳክምብዎ እግዚአብሔር አይቀበለኝም የሚል ስሜት ሊሰማዎም ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ተስፋ ሳይቆርጡ የፈቃድን ኃይል የተሰጠንን የመምረጥ ኃይል) ምንነት ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ይህ ኃይል ሰብዓዊውን ተፈጥሮ የሚገዛ፣ ውሳኔውን ወይም ምርጫውን የሚቆጣጠር ነው:: እያንዳንዱ ነገር ፈቃዳችንን ተመርኩዘን በምንወስደው እርምጃ ይወሰናል፡እግዚአብሔር የመምረጥን ኃይል ለሰዎች ስለሰጠ፣ ስጦታውን መለማመድ ደግሞ የሰዎች ድርሻ ይሆናል፡፡ ልብዎን ሊለውጡም ሆነ በልብዎ ውስጥ ያለውን ፍቅር ለእግዚአብሔር መስጠት አይችሉም:: ነገር ግን እርሱን ለማገልገል ምርጫ ዎ በማድረግ ፈቃድዎን ለእርሱ ማስገዛት ይችላሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሳለ ፈቃዱን በእርስዎ ውስጥ የሚያደርገው አምላክ እርሱ እንደሚወድና እንደሚፈቅድ መሥራት ይጀምራል፡፡ በውጤቱም መላው ተፈጥሮዎ በክርስቶስ መንፈስ ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ በልብዎ ውስጥ ለሚኖረው ፍቅር እርሱ ማዕከል በመሆን ከሃሳብዎ ጋር ውህደት ይፈጥራል፡፡ክየመ 44.1

    መልካሙን መመኘትና ቅድስናን መሻት ተገቢ ቢሆንም፤ ነገር ግን በምኞት ብቻ መቅረቱ ከንቱ ነው:: ብዙዎች እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን ተስፋ ሲያደርጉና ሲመኙ ጠፍተው ይቀራሉ፡፡ ለዚህ መንስዔው እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ወደሚያስረክቡበት መንገድ ለመምጣት ባለመምረጣቸው ነው::ክየመ 44.2

    የተሰጠንን የመምረጥ ኃይል በመለማመድ በሕይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል:: ፈቃድዎን ለክርስቶስ በማስገዛት ከአለቆችና ከኃይላት በላይ ከሆነው ኃያል ጋር ራስዎን ተባባሪ ያድርጉ፡፡ ታማኝና የማይለወጥ ሆነው ሲቆሙ፤ ብርታትን ከላይ ያገኛሉ፡፡ ያለማቋረጥ ራስዎን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሲሰጡ አዲስ ሕይወት መኖር ይጀምራሉ ያውም የእምነት ህይወት::ክየመ 45.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents