Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ 9 - ሥራ አና ሕይወት

    እኔ ግዚአብሔር ለዓለማት ሁሉ የሕይወት፣ የብርሃንና የደስታ ምንጭ ነው፡፡ የብርሃን ጨረር ከጸሐይ እንደሚፈነጥቅ፣ የወንዝ ውሃም ከምንጭ ፈልቆ እንደሚጐርፍ እግዚአብሔርም በረከቱን ለፍጥረቱ ሁሉ አብዝቶ ይሰጣል፡፡ መለኮታዊ ሕይወት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሲኖር ከዚያ ሰው ልብ ለሌሎች ሰዎች የሚሆን ፍቅርና በረከት ይፈልቃሉ፡፡ክየመ 71.1

    የአዳኛችን ደስታ በኃጢአት የወደቀውን ሰው ማንሳትና ማዳን ነበር፡፡ ለዚህም ነው ለሕይወቱ ሳይሳሳ ነገር ግን መስቀሉን ታግሶ፣ ነውርንም ንቆ ያለፈው፡፡ መላእክትም እንዲሁ ሌሎች ፍጡራንን ደስ ለማሰኘት ሁልጊዜ ይሰራሉ:: ይህም ለእነርሱ ደስታቸው ነው:: ራስ ወዳዶችና ትእቢተኞች የሚንቁት፣ ድሆችንና የተዋረዱትን፣ በማእረግም ዝቅ ያሉትን የማገልገል ሥራ በኃጢአት ያልወደቁት መላእክት በደስታ ይሰሩታል፡፡ የክርስቶስ እራሱን መስዋት አድርጎ የመስጠት የፍቅር መንፈስ የመንግስተ ሰማይ መመሪያ ነው፡፡ ይህም እውነተኛ ደስታን ለማግኘትም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ የክርስቶስ ተከታዮችም ተመሳሳይ መንፈስን በመጋራት፣ ተመሳሳይ ሥራን ይሰራሉ፡፡ክየመ 71.2

    የክርስቶስ ፍቅር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሲኖር ልክ ጣፋጭ ማዕዛ እንዳለው እጣን ሊሸሽግ አይችልም፡፡ የዚህን ፍቅር ቅዱስ ኃይል የምናገኛ ቸው ሰዎች ሁሉ ያዩታል:: በአንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚኖረው የክርስቶስ መንፈስ የደረቀውን ሁሉ እንደሚያረሰርስ፣ ሊሞቱ የቀረቡትንም በፍጥነት ወደ ሕይወት ውሀ እንዲመጡ እንደሚያደርግ በበረሀ ውስጥ እንዳለ የውሀ ምንጭ ነው:: ኢየሱስን መውደዳችን የሚገለጸው እርሱ ይሰራ እንደነበረው ሰዎችን የማበረታታትና ለሰዎች በረከት የሚጠቅም ስራ ስንሰራ ነው። የክርስቶስ ፍቅር የሰማዩ አባታችን የሚያስብላቸውን ፍጥረታት ሁሉ እንድንወድ፣ እንድንራራላቸው፣ ችግራቸውንም እንድንካፈልላቸው ወደ መልካም ሃሳብ ይመራናል፡፡ክየመ 71.3

    የአዳኛችን የምድር ሕይወት የምቾትና ራስን የመውደድ ሕይወት አልነበረም፡፡ የጠፋውን የሰው ዘር ለማዳን ደከመኝ ሳይል በቅንነት ያለማቋረጥ ለፋ፡፡ ከበረት ጀምሮ እስከ ቀራንዮ ድረስ «ስራው ከበደኝ፣ ጉዞው ሰለቸኝ፣አቅም አጣሁ» ሳይል ራስን የመካድን ጉዞ ተጓዘ፡፡ ስለራሱ ሲናገር እንዲህ አለ፡ «የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጐ ለመስጠት መጥቶአልና» (ማቴ. 20:28)፡፡ በምድር ሳለ የነበረው ዋና ዓላማ ይህ ነበር፡፡ ሌላው ሁሉ ሁለተኛና ከዚህ በታች የሚመጣ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግና ስራውን መፈጸም የእርሱ መብልና መጠጥ ነበር፡፡ ራስንና የራስን ጥቅም መውደድ በስራው ውስጥ ቦታ የላቸውም ነበር፡፡ክየመ 72.1

    የክርስቶስ ጸጋ ተካፋዮች የሆኑ ሁሉ ይህንን የሰማይ ስጦታ ሌሎች ክርስቶስ የሞተላቸው ሰዎችም እንዲያገኙ ማንኛውንም አገልግሎትና መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ይሆናሉ፡፡ በዓለማችን ላይ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ እንደዚህ ያለ መንፈስ ከልብ ወደ ጌታዋ የተመለሰች ነፍስ ፍሬ ነው::ክየመ 72.2

    የክርስቶስ ፍቅር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሲኖር፣ ልክ ጣፋጭ ማዕዛ እንዳለው እጣን ሲሸሸግ አይችልም፡፡

    አንድ ሰው በርግጥ ወደ ክርስቶስ ለመመለሱ ማረጋገጫው፤ እርሱ ስላገኘው የከበረ ወዳጅ ስለ ኢየሱስ ለሌሎች ለመመስከር ፍላጎት ሲያድርበት ነው:: ይህንን የሚያድንና የሚቀድስ እውነት ለራሱ ብቻ ይዞ መቀመጥ አይችልም፡፡ የክርስቶስን ጽድቅ ከለበስንና በልባችን በሚኖረው የመንፈሱ ደስታ ከተሞላን ዝም ልንል አንችልም:: ጌታ ቸር እንደሆነ ከቀመስንና ካየን የምንናገረው ነገር ይኖረናል፡፡ እንደ ፊሊጶስ እኛም መድኅንን ካገኘን በኋላ ሌሎችን ወደ እርሱ እንጋብዛለን፡፡ ስለ ክርስቶስ የማዳን ኃይል እንዲሁም አሁን በዓይን ስለማይታየው ነገር ግን ስለሚመጣው የጌታ መንግስት እውነታ ለእነርሱ ለመንገር እንጓጓለን፡፡ ኢየሱስ የሄደበትን ፍለጋ ለመከተል ጥልቅ ፍላጎት ያድርብናል፡፡ በዙሪያችን ያሉት ሰዎችም «የዓለምን ኃጢአት ሁሉ የሚያስወግደውን የእግዚአብሔርን በግ» ዮሐ. 1፡ 29) እንዲመለከቱ የጋለ መሻት ይኖረናል፡፡ክየመ 72.3

    ሌሎች ሰዎች እንዲባረኩ የሚጥር ሰው ራሱ በረከትን ይቀበላል፡፡ በድነት ስራ ላይ እንድንተባበር እግዚአብሔር ሲጋብዘን ዓላማው ይህ ነበር፡፡ በፀጋው የመለኮታዊው ኃይል ተካፋዮች እንድንሆን አድርጎናል፤ በምላሹም እኛ የተሰጠንን በረከት ለሌሎች ሰዎች እንድናካፍል ይፈልጋል። እግዚአብሔር ይህንን በረከት ለሰዎች መስጠቱ ትልቅ ደስታና ክብር ነው:: በፍቅር አገልግሎት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ ወደ ፈጣሪያቸው ይበልጥ እየተጠጉ ይመጣሉ::ክየመ 73.1

    ወንጌልን የማሰራጨት ኃላፊነትንና የፍቅር አገልግሎት ማበርከትን እግዚአብሔር ለመላእክቱ መስጠት ይችል ነበር፡፡ ዓላማውን ለማከናወን ሌላ መንገድ መቀየስም ይችል ነበር፡፡ ቢሆንም ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ከእርሱ፣ከክርስቶስና ከመላእክቱ ጋር ተባብረን በመስራት በዚያ ውስጥ የሚገኘውን በረከት፣ ደስታ እና መንፈሳዊ እርካታ እንድንካፈል ፈለገ፡፡ክየመ 73.2

    የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች ስንሆን የእርሱን ርህራጌ ጭምር እንጋራለን፡፡ራስን መስዋዕት በማድረግ የሚከናወን በጎ አድራጎት፣ በድርጊት ፈጻሚው ልብ ውስጥ የለጋስነትን ስሜት የሚያጠናክር ሲሆን «በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ» (2 ቆሮ. 8፡ 9) ከሆነው የዓለም አዳኝ ጋር ይበልጥ ያቀራርበዋል:: አምላክ ለእኛ ያለውን ዓላማ በእርግጠኝነት ስንከተል ሕይወታችን ለሌሎች በረከት ይሆናል፡፡ክየመ 73.3

    ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ በነደፈው እቅድ መሠረት ብትሰሩና ነፍሳትን ወደ እርሱ ብትማርኩ፣ መለኮታዊውን ነገር በጥልቀት ለመለማመድና ጠንቅቆ ለማወቅ የሚኖራችሁ ፍላጎት ይጨምራል፤ ጽድቅንም የምትራቡና የምትጠሙ ትሆናላችሁ:: እግዚአብሔርን የሙጥኝ ትላላችሁ፤እምነታችሁም ይጠነክራል፤ ነፍሳችሁም ከድነት የውሃ ጉድጓድ ጠለቅ አድርጋ መቅዳትና መጠጣት ትችላለች፡፡ክየመ 73.4

    ራስን ብቻ የመውደድ መንፈስ የሌለበት አገልግሎት ከአስመሳይነት ይጠብቀናል፣ ጥንካሬንና ፍቅርን ያስገኝልናል፣ ሰላምንና ደስታም ይሰጠናል፡፡መንፈሳዊነታችንም ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም ስንፍናና እራስን ብቻ መውደድ በእኛ ዘንድ ስፍራ አይኖራቸውም:: በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታ ዎች የሚያገለግል ሰው በእግዚአብሔር እየበረታና እየጠነከረ ይሄዳል፣ ንጹህ መንፈሳዊ እውቀትን ያገኛል፣ በእምነትና በጸሎት ኃይልም ይጸናል (ይበረታል)፡፡ እግዚአብሔርን በመተዋወቁ ምክንያት መንፈስ ቅዱስ የአማኙን ልብ ከሰማይ አባት ጋር ቅዱስ ስምምነት እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ለሌሎች መልካም እንዲሆንላቸው ራስን ብቻ መውደድ በሌለበት ጥረት እራሳቸውን ለሌሎች ቀድሰው የሚሰጡ ሁሉ ለራሳቸው ደህንነት እጅግ ጠንክረው በመስራት ላይ ናቸው::ክየመ 74.1

    በክርስቶስ ጸጋ የምናድገው የራሳችንን ጥቅም ብቻ ሳንፈልግ ክርስቶስ ለኛ የሰጠውን ስራ ስናደርግና በተቻለን ኃይል የእኛ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስንደርስ ብቻ ነው:: ኃይል በስራ ልምምድ ነው የሚገኘው፡፡ ስራ ደግሞ ለሕይወት ዋና ነገር ነው:: ለክርስቶስ አንዳች ነገር ሳይሰሩ ከጸጋው የሚገኘውን በረከት በመቀበል ብቻ የክርስቶስን ሕይወት ለማግኘት የሚጥሩ ሁሉ ሳይደከሙና ሳይጥሩ መብላትን የሚፈልጉትን ይመስላሉ፡፡ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ በመንፈሳዊም ሆነ በስጋዊ ሕይወት ውርደትንና ጥፋትን ያመጣል፡፡ አካሉን ስራ ከማስለመድ እንቢ የሚል ሰው ሰውነቱን ማንቀሳቀስ እስኪሳነው ድረስ በቶሎ ኃይል ያጣል፡፡ እግዚአብሔር በሰጠው ስጦታ የማያገለግል ክርስቲያንም እንዲሁ በክርስቶስ ማደግ ካለመቻሉ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የሰበሰበውን ኃይል ሁሉ ያጣል፡፡ክየመ 74.2

    እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የመረጣት ሰውን ለማዳን እንድትሰማራ በማሰብ ነው:: የጥሪዋም ዋና ዓላማ ወንጌልን ለዓለም ማዳረስ ነው::እያንዳንዱ ክርስቲያን በተሰጠው ስጦታ እና አጋጣሚ የአዳኙን ትእዛዝ እንዲፈጽም ታዟል፡፡ ለእኛ የተገለጸው የክርስቶስ ፍቅር ላልሰሙትና ለማያውቁት እንድንነግር ባለእዳ ያደርገናል:: እግዚአብሔር ብርሃኑን የሰጠን ለኛ ብቻ እንዲሆን አይደለም ለሌሎችም እንዲበራላቸው ጭምር እንጂ፡፡ክየመ 74.3

    የክርስቶስ ተከታዮች ይህንን ስራ ለመስራት ከልባቸው ቢፈልጉ ኖሮ ዛሬ አንድ ሰው ብቻ ባለበት ስፍራ አንድ ሺህ ወንጌልን የሚያሰራጩ ሰዎች በተገኙ ነበር:: አንድ ሰው ወንጌልን እርሱ ራሱ ማሰራጨት ባይችልም እንኳን ቢያንስ በገንዘቡ፣ በበጎ ፈቃዱ እና በጸሎቱ ሊያግዝ ይገባዋል፡፡ እንዲህ ቢሆን ከአሁኑ አዳኛችን የበለጠ የነፍሳት ማዳን ስራ በክርስቲያን አገሮች ድጋፍ አማካኝነት በተካሄደ ነበር፡፡ክየመ 75.1

    አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን ናዝሬት በሚገኘው አነስተኛ የአናጢ ቤት ነበር ሲሰራ የቆየው፡፡

    ክርስቶስን ለማገልገል ወደ ሩቅ አገሮች መሄድ ወይም ደግሞ አገራችንን ለቀን መሄድ እንኳን አያስፈልገን ይሆናል፡፡ በቤታችን፣ቤተክርስቲያናችን፣ከወዳጆቻችንና በሥራ ቦታችን ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር መልካሙን የምስራች መካፈል እንችላለን፡፡ አዳኛችን አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን ናዝሬት በሚገኘው አነስተኛ የአናጢ ቤት ነበር ሲሰራ የቆየው:: የሕይወት ታ ከገበሬዎችና ከወዛደሮች ጋር ጐን ለጐን ሆኖ ሲሰራ እነርሱ ባያስተውሉትም እንኳን የሚያገለግሉት መላእክቱ ዙሪያውን ከበውት ነበር፡፡የእጅ ሙያ ስራ ይሁን፣ በሽተኞችን መፈወስ፣ ወይም በገሊላ ባህር ላይ መራመድ፣ ኢየሱስ የትኛውንም አገልግሎቱን በታማኝነት ይፈጽም ነበር፡፡እንዲሁም እኛም የተሰጠንን ኃላፊነት ትንሽም ብትሆን እንኳን ከኢየሱስ ጋር በመሆን ማከናወን ይገባናል፡፡ክየመ 75.2

    ሐዋርያው ጳውሎስ ሲጽፍ እንዲህ አለ «ወንድሞች ሆይ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር» (1 ቆሮ. 7:24)፡፡ ነጋዴው በታማኝነት ሲነግድ ጌታውን በሚያስከብር መንገድ እየሰራ ነው ማለት ነው:: እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ ከሆነ በሚያደርገው ነገር ሁሉ ኃይማኖቱን ያሳያል ፣ የክርስቶስንም መንፈስ ለሰዎች ይገልጻል፡፡ክየመ 75.3

    የእጅ ሙያ ያለው ደግሞ በታታሪነቱና በታማኝነቱ በገሊላ ተራ ስራ ሲሰራ የነበረውን የኢየሱስን ባህሪይ ያንጸባርቃል፡፡ እያንዳንዱ የክርስቶስን ስም የሚጠራ ሁሉ ሌሎች መልካም ስራውን በማየት የእርሱን ፈጣሪና አዳኝ ያከብሩ ዘንድ ስራውን በታማኝነት መስራት አለበት::ክየመ 76.1

    «ከእኔ ይልቅ ሌሎች የተሻለ ችሎታና የተመቻቸ ሁኔታ አላቸው» የሚል ምክንያት በመስጠት ብዙዎች ስጦታቸውን ለክርስቶስ አገልግሎት ለማዋል ፈቃደኞች አይደሉም:: «ልዩ ስጦታ ያላቸው ብቻ ናቸው የእግዚአብሔርን ስራ መስራት የሚችሉት» የሚለው አስተሳሰብም የመጣው ከእንደዚህ አይነቱ አቋም ነው፡፡ እንዲያውም «ለጥቂቶች ብቻ ነው ስጦታ የተሰጠው፤የቀሩቱ ግዴታ የለባቸውም፧ ሽልማትም አይሰጣቸውም» ብለው የሚያስተውሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ኢየሱስ ግን ለአገልጋዮቹ ስራ ስላከፋፈላቸውአንድ ጌታ በተናገረው ምሳሌ ላይ ከቶ እንዲህ አላለም:: ምሳሌው «ጌታውአገልጋዮቹን ስበስቦ ለእያንዳንዱ ስራን ሰጥቷቸው ሄደ» ነው የሚለው::ክየመ 76.2

    በሰው አይነት አነስተኛ ግምት የሚሰጠው አገልግሎትም ቢሆን «ለጌታ እንደምናደርገው» (ቆላ. 3፡ 23) በማሰብ በደስታ መንፈስ እናገልግል፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ውስጥ ካለ በሕይወታችን ይገለጣል፡፡ የክርስቶስ መልካም ማዕዛ ዙሪያችንን ይከበናል፤ በሌሎች ላይ የምናሳድ ረው ተጽእኖም ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጋቸውና የሚባርካቸው ይሆናል።ክየመ 76.3

    ለእግዚአብሔር ለመስራት ትልቅ አጋጣሚ እስኪከሰት ድረስ ወይም ደግሞ ልዩ ችሎታ እስኪኖረን ድረስ አንጠብቅ:: ሌሎች ስለእኛ ስለሚያስቡትም ሆነ ስለሚናገሩት ልባችን አይጨነቅ፤ በየዕለቱ ሕይወታችን የምናሳየው በንጽህናና በሀቀኝነት የተሞላው እምነታችን ምስክር ከሆነ እንዲሁ ሌሎች ሰዎች በሙሉ ልባችን ልንረዳቸው እንደምንፈልግሲያስተውሉ ልፋታችን ከንቱ እንዳልሆነ እንወቅ፡፡ክየመ 76.4

    ትሁትና ምስኪን የሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለሌሎች ሰዎች በረከት ይሆናሉ:: እነርሱ ምናልባት መልካም ነገር እያደረጉ መሆናቸው አይታወቃቸው ይሆናል:: ቢሆንም ከእነርሱ ውስጥ ኃይለኛ የበረከት ምንጭ ይፈልቃል፡፡ የአገልግሎታቸውም ፍሬ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ለሁሉም ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡ ትልቅ ነገር ማድረጋቸው አይታወቃቸውም፣ስለጥረታቸውም ውጤታማነት አይጨነቁም፡፡ ስራቸውን ያለማወላወልይሰራሉ፣ እግዚአብሔር እንደባለጥበብነቱ የሰጣቸውን ኃላፊነት (ስራ)በታማኝነት ያከናውናሉ፡፡ በመሆኑም ሕይወታቸው እንዲሁ ከንቱ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ክርስቶስን እየመሰሉ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ተባብረው በመስራት ወደፊት ለሚጠብቃቸው ኃላፊነትእንዲሁም በዘላለም ሕይወት ለሚያገኙት ፍጹም ደስታ የተዘጋጁ ይሆናሉ፡፡ክየመ 77.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents