Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ 7 - የደቀመዝሙርነት መፈተኛ

    ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፋል እነሆ፣ ሁሉም አዲስ ሆኗል፡፡» (2ኛ ቆሮ. 5:17)ክየመ 53.1

    አንድ ሰው የተለወጠበትን ትክክለኛ ጊዜ ወይም ቦታ ወይም መለወጡ ሂደት ውስጥ የነበሩ አጠቃላይ ሁናቴዎችን አያይዞ አንድ በአንድ መናገር አይችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ መናገር አልቻለም ማለት አለመለወጡን ያሳያል ማለት አይደለም፡፡ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቁጥር 8 ላይ እንዲህ ብሎት ነበር «ንፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፣ድምጹንም ትሰማለህ፣ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉም እንዲሁ ነው::» ንፋስ በዓይን አይታይም፤ ይሁን እንጂ ንፋሱ ያስከተለው ውጤት ይታያል፣ ይሰማል፡፡ ልክ እንደ ንፋሱ የእግዚአብሔር መንፈስም በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚሠራው ሥራ በጉልህ ከመታየቱና ከመሰማቱ ውጭ መንፈሱ በዓይን አይታይም:: ያ የሰው ዓይን የማያየው ውስጣችንን ዳግም የሚያድሰው ኃይል በነፍሳችን ውስጥ አዲስ ሕይወትን ይዘራል፤ በእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን አዲስ ማንነትን ይፈጥራል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ፀጥ ያለና ሲሠራ የማይታይ ቢሆንም ውጤቱ ግን ይታያል፡፡ ልባችን እግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ከታደሰና ከተለወጠ፤ ሕይወታችን እውነትን ይመሰክራል፡፡ በራሳችን ልባችንን መለወጥም ሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ራሳችንን ማስማማት አንችልም፡፡ በመሆኑም በራሳችንም ሆነ በመልካም ሥራችን ላይ ሙሉ ለሙሉ መታመናችንን ስናቆም፤ ያኔ የእግዚአብሔር ጸጋ በውስጣችን ማደሩን ህይወታችን ይገልጻል፡፡ ይህን ተከትሎ በባህሪያችንና በልማዳዊ ድርጊቶቻችን ለውጥ መስተዋል ይጀምራል፡፡ በእነዚህ በሁለት የተለያዩ ነገሮች መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ስለሚሆን በቀድሞው ሁናቴና በአሁኑ መሃል ያለው ልዩነት ምን እንደ ሆነ ለይቶ ለማወቅና ለመወሰን ይቻላል፡፡ባህርይ የሚገለጸው አልፎ አልፎ በሚደረጉ ጥሩ ወይም መጥፎ ሥራዎች ሳይሆን አዘውትረው በሚነገሩ ቃላትና ድርጊቶች ነው።ክየመ 53.2

    እርግጥ ነው፤ ያለ ክርስቶስ ለዋጭ ኃይል ውጫዊ የባህርይ መልካምነት ሊኖር እንደሚችል አይካድም፡፡ በሌሎች ለመታየትና ለመወደስ ያለን ፍላጎት የተስተካከለ ሕይወት የምንለውን እንድንቀዳጅ ሊያተጋን ይችላል፡፡ ለራሳችን ያለን አክብሮት የክፋት መገለጫ እንዳንሆን ሊያግዘን ይችል ይሆናል፡፡ምናልባትም እራስ ወዳድ ልብ ለሌሎች መልካምን ነገር ሊያደርግ ይችል ይሆናል፡፡ ታዲያ ከማን ወገን እንደሆንን የሚወሰነው በምን መንገድ ነው? አዕምሯችንን የተቆጣጠረው ማን ነው? ሃሳባችን ከማን ጋር ነው? ማውራት ደስ የሚለን ስለማን ነው? የሞቀ ፍቅራችንን እና ከፍተኛውን አቅማችንን ለማን እያዋልነው ነው? የክርስቶስ ከሆንን ሃሳባችን ሁሉ ከእርሱ ጋር ነው።ጣፋጭ አስተሳሰባችን ሁሉ ስለ እርሱ ነው፡፡ እንዲሁም እኛ ያለንንና የእኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ለእርሱ ብቻ እንቀድሳለን፡፡ እርሱን ለመምሰል፣መንፈሱን ለመተንፈስና ፈቃዱን ለማድረግ በሁሉም ነገራችን እርሱን ለማስደሰት እንናፍቃለን፡፡ክየመ 54.1

    በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት የሆኑ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ያፈራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ ምዕራፍ 5 ቁጥር 22 እና 23 ላይ ስለመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ሲናገር «የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ሰላም፣ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋህነት፣ እራስን መግዛት ነው»ይላል፡፡ እነዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት የሆኑ ሰዎች በቀድሞው የሥጋ ፍላጎታቸው መነዳት ያቆሙና በእግዚአብሔር ልጅ በሚገኝ እምነት ምክንያት የእርሱን ዱካ ይከተላሉ፣ የእርሱን ባህሪ ያንፀባርቃሉ፤ እርሱ ንፁህ እንደሆነ እራሳቸውን ያጠራሉ፡፡ ቀድሞ ይጠሏቸው የነበሩ ነገሮችን አሁን ይወዳሉ፤ ቀድሞ ይወዷቸው የነበሩ ነገሮችን አሁን ይጠላሉ፡፡በራሳቸው ብቻ የሚታመኑ ልበ ደንዳኖች የነበሩ ትሁትና የተሰበረ ልብ ባለቤት ይሆናሉ:: ግብዝነትና ልታይ ባይነት በእውነተኛነት እና በጭምትነት ይተካል፡፡ የመጠጥ ሱሰኛው ከነበረበት የመጠጥ ሱስ ይላቀቃል፣ አባካኞች ከማባከን ይታቀባሉ፡፡ የዓለም የግብዝነት ልማዶች እና ፋሽኖች ወልቀው ይጣላሉ፡፡ ክርስቲያን «ውጫዊ ጌጥን» መፈለግ በማቆም «ነገር ግን . . .የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው» ይሆን ዘንድ (1ኛ ጴጥ. 3:3-4) ይፈልጋል፡፡ክየመ 54.2

    በሕይወት ላይ የሚታይ ለውጥን የማያመጣ ንስሃ እውነተኛ ንስሃ አይደለም። አንድ ሰው ቃል ኪዳኑን ካፀና፣ ዘርፎ የነበረውን ሲመልስ፣ኃጢአቱን ከተናዘዘ እንዲሁም እግዚአብሔርንና በአጠገቡ ያሉ ሰዎችን ከወደደ ይህ ኃጢአተኛ የነበረ ሰው ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገሩን እርግጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡ክየመ 55.1

    በደለኞችና በኃጢአት የረከስን መሆናችንን አምነን ወደ ክርስቶስ በመቅረብ የፀጋ ምህረቱ ተቋዳሾች ስንሆን ፍቅር ከልባችን ይፈልቃል፡፡ የክርስቶስ ቀንበር ቀላል ከመሆኑ የተነሳ አንድ ሰው በእርሱ ሲሆን ሸክሙ ሁሉ ይቀለዋል፡፡ በጨለማ የተዋጠ ይመስል የነበረው መንገድ በፅድቅ ብርሃን ወገግታ ፍንትው ብሎ ይበራል፡፡ክየመ 55.2

    የክርስቶስ የአፍቃሪነት ባሕርይ በተከታዮቹ ላይም ይታያል፡፡ የእርሱ ደስታ የእግዚአብሔር አብን ፈቃድ ማድረግ ነበር። የአዳኛችንን ሕይወት የተቆጣጠረው ኃይል የአብ ፍቅርና ለአብ ክብር ማምጣት ነበር፡፡ የክርስቶስ ሥራዎች ሁሉ ያማሩና የከበሩ የሆኑት በፍቅር ስለተሠሩ ነው::እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፤ ፍቅርም ከእግዚአብሔር ነው:: በንስሓ ያልታደሰ ልብ ንፁሕ ፍቅር ሊያፈልቅ አይችልም፡፡ ይህ ንፁሕ ፍቅር ሊገኝ የሚችለው ኢየሱስ ከነገሠበት ልብ ብቻ ነው:: «አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንዋደዳለን፡፡»(1ኛ ዮሐ 4፡19)፡፡ ልባችን በመለኮታዊ ፀጋ ከታደሰ፤ የድርጊቶች ሁሉ መሠረት የሆነው ፍቅር ባህርያችንን ይለውጣል፤ አስተሳሰባችንን ይመራል፤ምኞታችንን ይቆጣጠራል፤ ጥላቻችንን ያስወግዳል፤ መንፈሳችንን ይቀድሳል፡፡ይህንን ፍቅር ዘወትር ስንለማመደው፤ ሕይወታችን ይጣፍጣል እንዲሁም በአካባቢያችን ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እናሳድራለን፡፡ክየመ 55.3

    የእግዚአብሔር ልጆች በተለይም ጌታን በቅርቡ የግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉ ሊርቋቸው የሚገቡ ሁለት ስህተቶች አሉ፡- የመጀመሪያው እና ከዚህ በፊት የጠቀስነው «በራሳችን መልካም ስራና ተግባር ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት እንችላለን» የሚለው እምነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በራሱ ጥረት ሕግን በመጠበቅ ቅዱስ ለመሆን የሚጥር ማንኛውም ሰው የማይቻል ነገር እየሞከረ ነው:: ምክንያቱም አንድ ሰው ከክርስቶስ ውጪ የሚያደርገው ነገር ሁሉ በእራስ ወዳድነትና በኃጢአት በተበከለ ማንነት የሚያደርገው ነው:: ምክንያቱም ቅዱስ የሚያደርገን በእምነት የምንቀበለው የክርስቶስ ፀጋ ብቻ ነውና፡፡ክየመ 56.1

    ከዚህ ተቀራኒውና ቀላል የማይባለው አደገኛ ስህተት ደግሞ የክርስቶስ ጸጋ ተካፋዮች የምንሆነው በእምነት በመሆኑና የእኛ መልካም ሥራዎች ከመዳናችን ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌላቸው ክርስቶስ ሰዎችን የእግዚአብሔርን ሕግ ከመጠበቅ ነጻ አውጥቶአቸዋል» የሚለው እምነት ነው::ክየመ 56.2

    ድነት በእምነት ብቻ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ስለሆነ፣ በመታዘዛችን ብዛት ልናገኘው አንችልም፡፡

    እዚህም ጋር አብሮ መታሰብ ያለበት ነገር ታዛዥነት ማለት ዝም ብሎ ሕጉን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አገልግሎት መሆኑን ነው። የእግዚአብሔር ሕግ የራሱ የእግዚአብሔር፣ የማንነቱ መገለጫ ነው፤ ሕጉ የፍቅርን ባሕርይ ያቀፈ ከመሆኑ የተነሳ በሰማይና በምድር የመንግሥቱ መሠረት ነው:: ሕይወታችን በእግዚአብሔር አምሳል ከተለወጠ፤መለኮታዊው ፍቅርም በልባችን ውስጥ ከሰረጸ እግዚአብሔርን ሕግ ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ የፍቅር መርሆ በልባችን ውስጥ ሲሰርጽ እኛም የፈጠረንን አምላክ አምሳል ስንይዝ «ሕጌን በልቦናቸው አኖራለሁ በልባቸውም የምንቀበለው እጽፈዋለሁ. . .» (ዕብ. 10፡16) የሚለው የአዲሱ ኪዳን ተስፋ ቃል ይፈጸማል፡፡ ሕግም በልባችን ውስጥ ሲጻፍ ሕይወታችን በእርሱ ይመራል፡፡ በፍቅር እና ታማኝ አገልግሎት የተመሰረተው ታዛዥነት እውነተኛ የደቀ መዝሙርነት ምልክት ነው:: በዚህ ምክንያት ነው መጽሐፍ ቅዱስ «ትዕዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና» (1ኛ ዮሐ 5፡3)፡፡ «የእግዚአብሔርን) አውቄዋለሁ የሚል ትዕዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም፡፡»(1ኛ ዮሐ 2:4) በማለት የሚነግረን፡፡ እምነት እኛን ከታዛዥነት ነፃ ከማውጣት ይልቅ የክርስቶስ ጸጋ ተካፋይ እንድንሆንና እንድንታዘዝ የሚያደርገን ያው እምነት ብቻ ነው፡፡ክየመ 56.3

    ድነት በእምነት ብቻ የምንቀበለው የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ስለሆነ፣ በመታዘዛችን ብዛት ልናገኘው አንችልም:: ነገር ግን መታዘዝ የእምነት ፍሬ ነው:: «እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደተገለጠ ታውቃላችሁ፣ በእርሱም ኃጢአት የለም፡፡ በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም» (ዮሐ. 3:5-6፡፡ እዚህ ላይ ነው እውነተኛው ፈተና ያለው። በክርስቶስ የምንኖር ከሆነ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን ካለ፤ የእኛ ስሜት፣ አስተሳሰብ፣ ዓላማና ድርጊት ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ እንደተጠቀሰው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይጣጣማል፡፡ «ልጆች ሆይ፡ ማንም አያስታችሁ፤እርሱም ፃድቅ እንደሆነ ፅድቅን የሚያደርግ ፃድቅ ነው፡፡› (1ኛ ዮሐ. 3:7)፡፡ «ጽድቅ» የሚለው ቃል የሚመዘነው በእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ ነው:: ይህም ሕግ በሲና ተራራ በተሰጡት አስር ሕጎች ተገልጾአል፡፡ክየመ 57.1

    «በክርስቶስ ማመን ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ነፃ ያወጣል» የሚለው አስተሳሰብ «እምነት» ሳይሆን፣ እምነት የሚመስል ስህተት ነው፡፡ በርግጥ «ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና፡፡» ይላል (ኤፌ.2፡8)፡፡ ነገር ግን «እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡» (ያዕ. 2:17) ይላል፡፡ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለራሱ እንዲህ ብሎ ነበር፡- «አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ» (መዝ. 40፡8)፡፡ ተመልሶ ወደ አባቱ ቀኝ ከማረጉም በፊት «እኔ የአባቴን ትዕዛዝ እንደጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ፡፡» (ዮሐ. 15:10) በማለት ተናግሮአል፡፡ እንደዚሁ መጽሐፍ ቅዱስ በ1ኛ ዮሐ. 3:6 እና በ1ኛ ጴጥ. 2:21 «በእርሱ የሚኖር ኃጢአትን አያደርግም ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም» «ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን ልትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏልና» ይላል፡፡ «ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው» (1ኛ ጴጥ. 2:21)፡፡ክየመ 57.2

    ይህ የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት የሚጠየቀው መስፈርት አሁንም ሆነ ጥንት ወላጆቻችን በገነት ውስጥ በኃጢአት ከመውደቃቸው በፊት ተመሳሳይ ነው:: ይኼውም ለእግዚአብሔር ሕግ በፍጽምና መገዛትና የጽድቅ ህይወትን መኖር ነው፡፡ የዘለዓለም ሕይወት ከእነዚህ ውጪ የሚሰጥ ቢሆን ኖሮ የመላው ፍጥረት ደስታ አደጋ ላይ በወደቀ ነበር፡፡ ይህ ቢሆን ኑሮ፤የኃጢአት መንገድ ከነግሳንግሱና ሰቆቃው፣ ዋይታውና ምሬቱ ጋር ለዘላለም በተከፈተ ነበር፡፡ክየመ 58.1

    አዳም በኃጢአት ከመውደቁ በፊት ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ ፃድቅ ባሕርይን ማሳየት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ ይህን ስላላደረገና ከእርሱም ውድቀት የተነሳ የእኛ ተፈጥሮ በኃጢአት ስለ ጎደፈ እራሳችንን ልናጸድቅ አልቻልንም:: ኃጢአተኞች ፣ ቅድስና የጎደለንና በኃጢአት የረከስን እንደመሆናችን፣ ቅዱሱን ሕግ በፍጹምነት ልንታዘዘው አንችልም፡ የእግዚአብሔር ሕግ የሚጠይቀውን ለማሟላት የራሳችን የሆነ ጽድቅ ባይኖረንም ክርስቶስ ግን የማምለጫውን መንገድ አዘጋጀልን፡፡ እርሱ በኖረው ምድራዊ ህይወቱ እኛ በምናልፍበት ፈተናና መከራ ውስጥ አልፏል፡፡ይሁንና ኃጢአት የሌለበትን ሕይወት ኖረ፡፡ ስለዚህም ስለኛ ሞቶ ኃጢአታችንን ለመውሰድ እራሱን በመስጠት ጽድቁን አወረሰን፡፡ እራሳችሁንለእርሱ ብትሰጡና እንደ አዳኛችሁ ብትቀበሉት የፈለገውን ያህል ኃጢአተኛ የነበራችሁ ቢመስላችሁም፤ ስለ ራሱ ሲል እንደ ጻድቅ ይቆጥራችኋል፡፡የክርስቶስ ባሕርይ በእናንተ ምትክ ተቆጥሮ በእግዚአብሔር አብ ፊት ምንምኃጢአት እንዳልሠራ ሰው ሆናችሁ እንድትታዩ ያደርጋችኋል፡፡ክየመ 58.2

    ከዚህ በተጨማሪም ክርስቶስ ልባችሁን ይቀይራል፤ በእምነትም በልባችሁ ውስጥ ይኖራል፡፡ ታዲያ ይህንን ከክርስቶስ ጋር ያለ ግንኙነት በእምነት እየጠበቃችሁ ፈቃዳችሁን ያለ ማቋረጥ ለእርሱ እየሰጣችሁ እስከኖራችሁ ድረስ እርሱም መልካም ፈቃዱን የመፈለግ እና የማድረግን ነገር በእናንተ ውስጥ ይሠራል፡፡ ስለዚህ እናንተም «ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም፧ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል:: አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝ እና ስለእኔ እራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው፡፡» (ገላ. 2:20) ትላላችሁ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ «በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና» (ማቴ. 10:20) ብሏቸዋል፡፡ በእናንተ በሚሠራው ክርስቶስ ምክንያት የእርሱን አይነት መንፈስ ትገልጻላችሁ፤እንደ እርሱም መልካም ሥራን ታደርጋላችሁ፡፡ ሥራዎቹም የፅድቅና የመታዘዝ ናቸው፡፡ክየመ 58.3

    ስለዚህ የምንኩራራበት የራሳችን የሆነ ምንም ነገር የለንም:: እራሳችንን ከፍ አድርገን የምናይበት ምንም መሠረት የለንም:: ብቸኛው የተስፋችን መሠረት ለእኛ የተቆጠረልን የክርስቶስ ጽድቅና በእኛ ውስጥ እንዲሁም በእኛ በኩል በመሥራት ለውጥ የሚያመጣው የእርሱ መንፈስ ብቻ ነው::ስለ እምነት በምንናገርበት ጊዜ መዘንጋት የሌለብን ነገር አለ፡፡ ከእውነተኛው እምነት ፍጹም የተለየ የእምነት አይነት አለ፡፡ የእግዚአብሔር ሕልውናና ኃያልነት እንዲሁም የቃሉ እውነትነት ሰይጣንና ጭፍሮቹ እንኳ በልባቸው ሊክዱት የማይችሉት ተጨባጭ እውነታ ነው:: ለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ በያዕ. 2:19 ላይ፡- «እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ መልካም ታደርጋለህ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡» ይላል፡፡ ስለዚህ ይህ አይነት እምነት እውነተኛ እምነት አይደለም፡፡ እውነተኛ እምነት በእግዚአብሔር ቃል ማመን ብቻ ሳይሆን፤ ፈቃዳችንን ለእርሱ ማስገዛትንም ይጨምራል፡፡ አንድ ሰው ልቡን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሲያስገዛ፤ በዚያ ሰው ልብ ውስጥ ነፍስን የሚያነጻ በፍቅር የሚሠራ እምነት አለ ማለት ነው፡፡ክየመ 59.1

    በዚህም እምነት አማካኝነት ነው ልባችን በእግዚአብሔር አምሳል የሚታደሰው:: ያልታደሰ ልብ ለቅዱሱ የእግዚአብሔር ሕግ በተግባርም ሆነ በፍላጎት ሊገዛ አይችልም፡፡ የተለወጠ ልብ ያለው ሰው ግን በቅዱሱ የእግዚአብሔር ሕግ በመደሰት ከመዝሙረኛው ጋር፡- «አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፡፡» (መዝ. 119:97)፣«እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ» የሕግ ፅድቅ ይፈጸማል በማለት ይናገራል (ሮሜ 8:3)፡፡ክየመ 59.2

    የክርስቶስን ይቅር ባይ ፍቅር የሚያውቁና በእርግጥም የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ሰዎች ባሕርያቸው ፍጽምና የጎደለው፣ ህይወታቸውም እንከን ያለው መሆኑን ስለሚረዱ ልባቸው በመንፈስ ቅዱስ መታደሱን ይጠራጠራሉ:: እነዚህን ሰዎች «ተስፋ በመቁረጥ ወደ ኋላ አታፈግፍጉ!» ማለት እፈልጋለሁ፡፡ እኛ በተደጋጋሚ በኢየሱስ እግር ስር በመውደቅ ስለ ጉድለታችንና ኃጢአታችን ማንባት ቢኖርብንም ተስፋ መቁረጥ ግን አይገባንም፡፡ ምንም እንኳ በጠላት ብንሸነፍም፤ በእግዚአብሔር የተረሳን፣ የተጣልን እና የተተውን አይደለንም፡፡እርሱ ከቶ አይተወንም፡፡ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ስለ እኛ ይማልድልናል፡፡ የተወደደው ሐዋርያ ዮሐንስ በ1ኛ ዮሐ. ምዕ. 2 ቁጥር 1 «ልጆች ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህንን ጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::» ብሏል፡፡ «አብ እራሱ ወድዷችኋል፡፡» ዮሐ. 16:27 ያለውን የክርስቶስን ቃል አትርሱ:: እርሱ በእናንተ ውስጥ ተሃድሶ በማድረግ በውስጣችሁ የሚንጸባረቀውን የራሱን ንጽህናና ቅዱስነት ለማየት ይመኛል፡፡እናንተም ይህ እንዲሆን የምትፈልጉ እና እራሳችሁን ለእርሱ የምትሰጡ ከሆነ በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ ይፈጽመዋል፡፡ በትጋት ጸልዩ፤ በሙላትም እመኑ፡፡ በእራስ መታመናችንን በመተው በዋጀን ኃይል እንታመን፡፡ ይህን ስናደርግ በገጽታችን ላይ ጤነኛ ስሜት እንዲነበብ ላደረገ ለእርሱ ምስጋና እንሰዋለን፡፡ክየመ 60.1

    ወደ ኢየሱስ የበለጠ በተጠጋችሁ ቁጥር እይታችሁ እየበራ ስለሚመጣ ራሳችሁን ከእርሱ ፍጹም ባሕርይ ጋር ስታነጻጽሩት የእናንተን ኃጢአተኝነት በሰፊውና በግልጽ ታያላችሁ፡፡ ይህ ሲሆን የበለጠ ኃጢአተኛ መሆናችሁን በራሳችሁ ዓይኖች ትመለከታላችሁ፡፡ ይህም የሰይጣን ማታለያዎች ኃይል የማጣታቸው ምስክር ሲሆን በእናንተ ውስጥ ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ስራውን መጀመሩን ያሳያል፡፡ክየመ 60.2

    የራሱን ኃጢአተኛነት በግልጽ ባልተገነዘበ ልብ ውስጥ ጥልቅ የሆነው የኢየሱስ ፍቅር ሊኖር አይችልም፡፡ በክርስቶስ ፀጋ የተለወጠ ነፍስ የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ያደንቃል፡፡ የራሳችንን የባህሪ መበላሸት ማየት ከተሳነን የክርስቶስን ውበትና ልዕቀት በሚገባ አላስተዋልንም ማለት ነው።ክየመ 61.1

    በእራሳችን መመካታችንን ባሳነስን መጠን ወሰን በሌለው የአዳኛችን ንጽሕናና ውበት ላይ መመካታችን ይጨምራል፡፡ ኃጢአተኛነታችንን ማመናችን ይቅር ሊል ወደሚችለው ወደ እርሱ እንድናይ ይገፋፋናል፡፡ረዳተ ቢስነታችንን አስተውለን ወደ ክርስቶስ ስንቀርብ፣ እርሱ ራሱን ከነሙሉ ኃይሉ ይገልጥልናል፡፡ የጎዶሎነት ስሜታችን ወደ እግዚአብሔርና ወደ እግዚአብሔር ቃል አብዝቶ ባስጠጋን ቁጥር ስለ እርሱ ባሕርይ ላቅ ያለ አመለካከት ይኖረናል፡፡ የእርሱንም አምሳል በተሻለ ሙላት እናንጸባርቃለን፡፡ ክየመ 61.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents