Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ 3 - ንስሓ

    አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ መቆም የሚችለው እንዴት ነው? ኃጢአተኛው በምን መልኩ ነው ጻድቅ መሆን የሚችለው? ከእግዚአብሔር ጋር በቅድስና የተስማማን መሆን የምንችልበት ብቸኛው መንገድ በክርስቶስ በኩል ነው ካልን ወደዚህ አዳኝ የምንመጣው እንዴት ነው? በጴንጤቆስጤ ቀን በአንድነት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ኃጢአታቸው በታወቃቸው ጊዜ «ምን እናድርግ?» (ሐዋ. 2:37-38) ብለው በመጮኽ የጠየቁት ዓይነት ጥያቄ ብዙዎች እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ ይህን አስመልክቶ ጴጥሮስ የሰጠው ቀዳሚ ምላሽ «ንስሓ ግቡ. . . ከመንገዳችሁም ተመለሱ» (ሐዋ. 3:19) የሚል ነበር፡፡ክየመ 21.1

    ንስሓ መግባት ለሠሩት ኃጢአት ማዘንና ከኃጢአት መራቅን ያጠቃልላል፡፡ የኃጢአትን ክፉነት ካልተመለከትን በቀር ኃጢአትን ማውገዝ አንችልም:: ከልባችን ከኃጢያት እስካልራቅን ድረስ እውነተኛ መለወጥ በሕይወታችን አይኖርም፡፡ክየመ 21.2

    የንስሐን ትክክለኛ ትርጉም ባግባቡ ያልተረዱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች «ኃጢአት መሥራታችን በራሳችን ላይ መከራ ያመጣብናል» ብለው ስለሚፈሩ ላይ ላዩን ብቻ የሚታይ ለውጥ ያደርጋሉ፡፡እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አባባል ይህ ንስሓ አይደለም:: ምክንያቱም እነርሱ የሚያለቅሱት ለኃጢአታቸው ሳይሆን ይመጣብናል ብለው ለሚፈሩት መከራ ነው:: ይህ ደግሞ ኤሳው በኩርነቱ ለዘላለም እንደተወሰደበት ባየ ጊዜ የተሰማው ዓይነት ሐዘን መሆኑ ነው፡፡ በለዓም በመንገዱ ላይ ሠይፍ ይዞ የቆመውን መልአክ በተመለከተ ጊዜ ነፍሱን እንዳያጣ ፈርቶ ኃጢአቱን ያስታወቀ ቢሆንም እርሱ ይህን ያደረገው ክፉውን ተጸይፎ ከኃጢአቱ በመመለስ ትክክለኛ ንስሓ በመግባት የመለወጥ ዓላማ ኖሮት አልነበረም፡፡ የአስቆርቱ ይሁዳም ጌታውን ከካደ በኋላ «ንጹሁን ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ» (ማቴ. 27፡4) በማለት ነበር የጮኸው:: በኋለኛው የፍርድ ቀን የሚያስፈራ ኩነኔ እንደሚጠብቀው ስላወቀ ነው የበደለኝነት ስሜት ተሰምቶት መናዘዝ ግድ የሆነበት:: ይሁዳ ኋላ የሚከተለውን ስላሰበ ፍርሐት ውስጡን ናጠው እንጂ አንዳችም ነውር የሌለበትን የእግዚአብሔር ልጅ አሳልፎ በመስጠቱና የእስራኤልን ቅዱስ በመክዳቱ ልቡ አልተሰበረም ወይም የጠለቀ ሐዘን በነፍሱ ውስጥ አልተሰማውም ነበር፡፡ ፈርዖንም እንዲሁ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ሆኖ መከራ በደረሰበት ጊዜ ከሚመጣው ቅጣት ለማምለጥ ኃጢአቱን ያስታወቀ ቢሆንም ነገር ግን መቅሰፍቱ መውረዱን ባቋረጠ ጊዜ በሰማያዊው ንጉሥ ላይ መታበዩን ቀጠለ፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ኃጢአት ላመጣው ውጤት እንጂ ስለ ኃጢአታቸው አላዘኑም::ክየመ 21.3

    ነገር ግን ሰብዓዊው ልብ በእግዚአብሔር መንፈስ በተማረከ ጊዜ፤ ሕሊናው ንቁ ሆኖ በሰማይና በምድር ለመንግሥቱ መሰረት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕግ ጥልቀትና ቅድስና ለይቶ መመልከት ይችላል «ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር፡፡» ዮሐ. 1:9)፡፡ ይህ ብርሃን በምስጢራዊውና በተደበቀው ልብ ላይ የብርሃን ጨረሩን ስለሚፈነጥቅ በጨለማ የተሰወረው ሁሉ ይገለጣል፡፡ ያኔ አእምሮና ልብ በኃጢአት የተሞሉ መሆናቸውን ያምናሉ (ይቀበላሉ)፡፡ኃጢአተኛው የእግዚአብሔርን ጻድቅነት ስለሚያስተውልና ልብን ከሚመረም ረው አምላክ ፊት ለመቅረብ የኃጢአተኝነትና የመጉደፍ ስሜት ስለሚኖረው በአምላክ ፊት ለመቅረብ ፍርሃት ያድርበታል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ የቅድስናውን ውበትና ንጽህና ባስተዋለ ጊዜ ከኃጢአቱ ለመንጻትና ከሰማይ ጋር ዳግም አንድ ለመሆን ይናፍቃል፡፡ክየመ 22.1

    ዳዊት በኃጢአት ከወደቀ በኋላ የጸለየው ጸሎት የእውነተኛ ንስሓን ትርጉም ያሳያል፡፡ የእርሱ ንስሐ እውነተኛ፣ ልባዊና ጥልቅ ነበር፡፡ ዳዊት በጸሎቱ መተላለፉን ለመሸፈን ምንም ዓይነት ጥረት ካለማድረጉ ባሻገር ከአስፈሪው ፍርድ ለማምለጥም ምኞት አልነበረውም፡፡ ዳዊት የመተላለፉን ግዝፈትና የነፍሱን መርከስ በተመለከተ ጊዜ የሠራውን ኃጢአት ጠላ፡፡ እርሱ ጸሎት ያደረገው ይቅር እንዲባል ብቻ አልነበረም የልብ ንጽሕናንም ጭምር ያገኝ ዘንድ እንጂ! በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር እንደገና አንድ ሆኖ የቅድስናን ደስታ ለማግኘት ናፈቀ፤ ይህም የሕይወቱ ቋንቋ ነበር፡፡ክየመ 22.2

    «መተላለፉ ይቅር የተባለለት፧
    ኃጢአቱም የተሸፈነለት፣እንዴት ብሩክ ነው!
    እግዚአብሔር ኃጢአቱን የማይቆጥርበት፣
    በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው፣
    ክየመ 23.1

    እርሱ ብሩክ ነው::» መዝ 32:1-2

    «እግዚአብሔር ሆይ እንደ ቸርነትህ መጠን ምህረትን እድርግልኝ፤
    እንደ ርህራሄህም ብዛት፣መተላለፌን ደምስስ፡፡
    በደሌን ፈጽሞ እጠብልኝ፤
    ከኃጢአቴም አንፃኝ፡፡እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤
    ኃጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው::
    በሂሶጵ እርጨኝ እኔም እነፃለሁ፤
    እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ ..
    አምላኬ ሆይ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ፤
    ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ፡፡
    ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ፡፡
    የማዳንህንም ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ፡፡. ..
    የደህንነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤
    ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤
    አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል»
    ክየመ 23.2

    (መዝ. 51፡1-14)

    እንደዚህ አይነቱን ንስሓ ማንም ከራሱ ሊያመነጨው አይችልም። ነገር ግን ወደ ላይ ከፍ ብሎ ባረገውና ለሰዎች ስጦታን በሰጠው በክርስቶስ ብቻ ነው የሚገኘው።ክየመ 24.1

    ስለ ንስሃ ብዙዎች በትክክል ያላስተዋሉት ነገር አለ፡፡ ከዚህም የተነሳ ክርስቶስ ሊሰጣቸው የሚመኘውን እርዳታ ሳይቀበሉ ይቀራሉ፡፡ በቅድሚያ ንስሓ ካልገቡ በቀር ወደ ክርስቶስ መምጣትእንደማይችሉና ንስሓውም ለኃጢአታቸው ይቅር መባል ራሳቸውን ማዘጋጀት የሚችል እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፡፡ እርግጥ ነው በቅደም ተከተሉ መሰረት ከኃጢአት ይቅርታ በፊት ንስሓ ይቀድማል፡፡ አዳኝ እንደሚያስፈልገው የሚሰማው የተደቆሰውና የተሰበረው ልብ ብቻ ነው።ለመሆኑ ኃጢአተኛው ወደ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት አስቀድሞ ንስሓ እስኪገባ ድረስ መጠበቅ አለበት? ንስሓ አለመግባት ኃጢአተኛውና በአዳኙ መካከል ዕንቅፋት መሆን አለበትን? ክየመ 24.2

    «ኃጢተኛው የክርስቶስን ግብዣ ከመቀበሉ በፊት ንስሓ መግባት አለበት!»ብሉ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም «እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ» (ማቴ. 11:28) ከክርስቶስ የሚወጣው ኃይል ሰዎችን ወደ ትክክለኛ ንስሓ ይመራል፡፡ ጴጥሮስ ለእስራኤሎች «እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኃጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀን ከፍ ከፍ አደረገው»(ሐዋ. 5:31) ብሎ በተናገረ ጊዜ ነገሩን ግልጽ አደረገላቸው።ያለ ክርስቶስ መንፈስ ንስሃ ልንገባ አንችልም፡፡ ያለ ክርስቶስም ይቅር መባል አንችልም፡፡ክየመ 24.3

    ክርስቶስ ትክክለኛውን ነገር እንድናደርግ ለሚገፋፋን ስሜት ሁሉ ምንጭ ነው።ኃጢአትን እንድንጠላ የሚያስችለንን ኃይል በልባችን ውስጥ መትከልም የሚችለው እርሱ ብቻ ነው። በደልና መተላለፋችንን በማመን እውነትና ንጽህናን ለማግኘት ያለን መሻት የእርሱ መንፈስ በልባችን ውስጥ እየሰራ ለመሆኑ በቂ መረጃ ነው፡፡ክየመ 24.4

    «እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ» በማለት ኢየሱስ ተናግሮ ነበር ዮሐ. 12፡32)። ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት ሲል የሞተ አዳኝ መሆኑ፣ ለኃጢአተኛ ሰው ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡የእግዚአብሔርን በግ በቀራኒዮ መስቀል ላይ ስንመለከት የደህንነት ምስጢር በአዕምሮአችን እየተገለጠ ይመጣል፤የአምላክ መልካምነትም ወደ ንስሓ ይመራናል፡፡ ክርስቶስ ለኃጢአተኞች በመሞት አዕምሮ ሊያስተውል ከሚችለው በላይ የሆነ ፍቅሩን ገለጸ::ኃጢአተኛው ይህን ፍቅር በሚመለከትበት ጊዜ፣ ልቡን አለስልሶና አዕምሮውን ማርኮ ነፍሱ መንፈሳዊ ትህትና እንድታገኝ ያደርጋታል።ክየመ 24.5

    “ኃጢያተኛው የክርስቶስን ግብዣ ከመቀበሉ በፊት ንስሓ መግባት አለበት» ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም።

    በርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ወደ ክርስቶስ የሚስባቸው ኃይል እንዳለ ከማስተዋላቸው በፊት፣ በኃጢአት ስለተሞላው መንገዳቸው ሃፍረት ተሰምቷቸው ክፉ ባህርያቸውን ይተዋሉ፡፡ ነገር ግን እውነተኛና ልባዊ ከሆነ ምኞት በመነሳት ለመለወጥ ጥረት እንዲያደርጉ የሚስባቸው ኃይል የክርስቶስ ኃይል ነው:: እነርሱ ያላሰቡት ኃይል በነፍሳቸው ውስጥ አድሮ ሥራውን ይሠራል፡፡ ህሊናቸው የሚያመዛዝንና ንቁ፣ ውጪያዊ ሕይወታቸውም ያማረና የተስተካከለ ይሆናል፡፡ ኃጢአታቸው የወጋው እርሱን እንደሆነ ይመለከቱ ዘንድ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ወደ መስቀሉ እንዲመለከቱ ሲያደርጋቸው፣ ትዕዛዛቱ ወደ እሳቤያቸው ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ የሕይወታቸው ክፋትና ጠማማነት፤ እንዲሁም በነፍሳቸው ውስጥ በጥልቀት የተንሰራፋው ኃጢአት ግልጽ ሆኖ ይታያቸዋል፡፡ ስለ ክርስቶስ ጽድቅ በጥቂቱ ማስተዋል በመጀመር ራሳቸውን እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፡-«የሰውን ልጅ ለማዳን ይህን ያህል መስዋዕትነት ያስከፈለው ለመሆኑ ይህ “ኃጢአት» የሚባል ነገር ምንድነው? ይህ ሁሉ ፍቅር፣ ሥቃይና ውርደት የደረሰው እኛ እንዳንጠፋ ነገር ግን የዘላለም ሕይወት እናገኝ ዘንድ ነውን?»ክየመ 25.1

    ኃጢአተኛው ይህን የክርስቶስ ፍቅር አሻፈረኝ ብሎ ሊቃወም ይችላል፡፡ነገር ግን ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነ ክርስቶስ ወደ ራሱ ይስበዋል፡፡ በተወደደው የእግዚአብሔር ልጅ ላይ ሥቃይ እንዲደርስ ምክንያት ለሆነው ለኃጢአቱ ንስሓ ይገባ ዘንድ ዘላለማዊው የድነት እቅድ ወደ መስቀሉ ግርጌ ይመራዋል፡፡ክየመ 25.2

    በሥነ ፍጥረት ውስጥ እየሠራ ያለው ያው መለኮታዊ አዕምሮ የሰው ልጆችን ለልቦናቸው ይናገራቸዋል፡፡ ገና ያላገኙትን ነገርም ይለምኑ ዘንድ ሊገለጽ በማይቻል መልኩ የማግኘት ጉጉት በውስጣቸው ያሳድራል፡፡ በዓለም ያሉ ቁሳዊ ነገሮች የሰዎችን ፍላጎት ማርካት አይችሉም:: የቅድስና የሆነው ደስታ የክርስቶስ ጸጋ፤ ሰላምና እረፍትን ያመጣላቸው ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ይማጸናቸዋል:: እርካታ በማይገኝበት የኃጢአት ደስታ ውስጥ ተዘፍቆ የሚገኘውን ሰብዓዊ አዕምሮ አዳኛችን በሚታየውና በማይታየው አምላካዊ እጁ እየመራ ወደ ዘላለማዊ ባርኮት ለመሳብ ያለማቋረጥ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ዓለም ቀዳዳ ጉድጓዶች ውሃ ለመጠጣት በከንቱ ለሚደክሙት ሰዎች ሁሉ እንዲህ የሚል መለኮታዊ መልእክት ተልኮላቸዋል፡- «የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ» (ራእ.22:17)ክየመ 26.1

    ይህ ዓለም ከሚሰጠው ይልቅ የተሻለ ነገር ለማግኘት በልባችሁ የምትናፍቁ ከሆነ በውስጣችሁ የሚሰማችሁ ናፍቆት የእግዚአብሔር ድምፅ መሆኑን አስተውሉ፡፡ የንስሃ መንፈስ እንዲሰጣችሁና ክርስቶስም በማያልቀው ፍቅሩና ፍጹም በሆነው ንጽሕናው እንዲገለጽላችሁ ለምኑ፡፡ «ፍቅር ለእግዚአብሔር እና ፍቅር ለሰው» የተሰኙት የእግዚአብሔር ሕግ መርሆ ዎች ፍጹም ሆነው በአዳኙ ሕይወት ውስጥ ታይተዋል፡፡ ለሌሎች በጎ ማድረግና እራስን አለመውደድ የክርስቶስ ሕይወት ነበር፡፡ የገዛ ራሳችንን ልብ ኃጢአተኝነት መረዳት የምንችለው፣ ወደ እርሱ ስንመለከትና ከእርሱም የሚፈነጥቀው ብርሃን በእኛ ላይ ሲያርፍ ነው:: ኒቆዲሞስ እንዳደረገው ሁሉ «ኑሮአችንና አካሄዳችን የቀና ነው፤ ባህሪያችንም የታረመ ነው» በማለት እንደ ማንኛውም ኃጢአተኛ ልባችንን በእግዚአብሔር ፊት ማዋረድ እንደሌለብን አድርገን በማሰብ እራሳችንን እናታልል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የክርስቶስ ብርሃን በነፍሳችን ላይ በፈነጠቀ ጊዜ ምን ያህል እንደ ጎደፍን እራሳችንን በመመልከት፤ ምኞታችን ሁሉ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተመሆኑን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ጠላት እንደሆንን፣ በዚህም እያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴያችን እንደተበከለ ለይተን እንረዳለን፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ የእኛ የራሳችን ጽድቅ በእርግጥም የመርገም ጨርቅ መሆኑን በመረዳት ከዚያ በኃጢአት ከረከሰ ሕይወት ሊያነጻንና በእርሱ አምሳያ ልባችንን ሊያድሰው የሚችለው የክርስቶስ ደም ብቻ መሆኑን ለይተን እናውቃለን፡፡ክየመ 26.2

    ከእግዚአብሔር ክብር የሚወጣው ጨረርና ከክርስቶስ ንጽሕና የሚፈነጠቀው ብርሃን፤ ወደ ሰብዓዊው ነፍስ ዘልቆ በመግባትና እያንዳንዱን የርኩሰት ነቁጥ ላይቶ በማውጣት፤ በእክል የተሞላውንና የተበላሸውን ሰብዓዊ ባህሪ በገሃድ ያሳያል፡፡ ቅዱስ ያልሆነውን የሰው ምኞት፣ የልብን ክህደትና የከንፈርን መርከስ ግልጽ ያደርጋል፡፡ ኃጢአተኛው ታማኝ ባለመሆን የእግዚአብሔርን ሕግ ዋጋ ቢስ ማድረጉን በማስተዋል ኃጢአትና ጉድፍ የሌለበትን ንጹሁን የክርስቶስን ባሕርይ በሚመለከትበት ጊዜ እራሱን ይጸየፋል፤ መንፈሱ የተጎዳና የተሰቃየም ይሆናል፡፡ክየመ 27.1

    ነቢዩ ዳንኤል ወደ እርሱ ተልኮ የነበረው የሰማይ መልእክተኛ የተከበበበትን ክብር ባየ ጊዜ የራሱ ደካማነትና ፍጹም አለመሆን ታወቀው።ነቢዩ በአዕምሮው ውስጥ የቀረውን ድንቅ ስሜት ሲገልጽ «ስለዚህ ይህን ታላቅ ራእይ እያየሁ ብቻዬን ቀረሁ፤ ምንም ጉልበት አልነበረኝም፤ መልኬ እጅጉን ገረጣ፤ ኃይልም አጣሁ» (ዳን 10፡8) በማለት ነበር የተናገረው:: በዚህ መልኩ የተዳሰሰች ነፍስ በውስጧ ያለውን ራስ ወዳድነት በመጥላትና በመጸየፍ፣ በክርስቶስ ጽድቅ በኩል፣ ከእግዚአብሔር ሕግና ከክርስቶስ ባሕርይ ጋር የተስማማውን የልብ ንጽሕና ለማግኘት ትመኛለች፡፡ክየመ 27.2

    ጳውሎስ በሕግ የሚገኘውን ጽድቅ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለው«ሕግን በመፈጸም ስለሚገኝ ጽድቅ ያለ ነቀፋ ነበርኩ» (ፊሊ. 3:6)፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊ የሆነውን የሕጉን ባህርይ ባስተዋለ ጊዜ የራሱን ኃጢአተኝነት ተመለከተ፡፡ የሕጉን ፊደል አይተው ሰዎች ለውጫዊ ሕይወታቸው በሚሰጡት ደረጃ መሠረት፣ ጳውሎስ ከኃጢአት የታቀበ ሕይወት ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ወደ ጠለቀው ቅዱስ ሕግ በተመለከተ ጊዜና በእግዚአብሔር እንደታየው እርሱም ራሱን ሲያይ፣ በተዋረደ መንፈስ አጎንብሶ እንዲህ ሲል ኃጢአቱን ተናዘዘ፡- «ሕጉ ሳይኖር ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ ከመጣ በኋላ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትኩ» (ሮሜ 7፡9)፡፡ ሐዋርያው የሕጉን መንፈሳዊ ትርጉም በተመለከተ ጊዜ የኃጢአትን አስከፊነት ለማስተዋል ቻለ፡፡ በዚያን ጊዜ የሚመካበት የራሱ ክብር ከእርሱ ራቀ፡፡ክየመ 27.3

    እግዚአብሔር ለሁሉም ኃጢአት እኩል ሚዛንና ደረጃ አይሰጠውም::በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ዓይን በበደሎች መካከል የደረጃ ልዩነት አለ፡፡ሁን እንጂ፣ በሰዎች ዓይን አንዳንድ በደሎች እንደ ቀላል የሚታዩ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር ዓይኖች ግን ቀላል የሚባል ኃጢአት የለም፡፡ የሰው ፍርድ አድሎአዊና ፍጽምና የጎደለው ነው:: እግዚአብሔር ግን ነገሮችን ካሉበት ተጨባጭ ሁናቴ አኳያ ይመለከታል፡፡ የሚሰክርን ሰው ሰዎች ይንቁታል ደግሞም ይህ ኃጢአቱ ከሰማይ እንደሚያስቀረው ይነግሩታል፡፡ ይሁንና ትእቢትን፣ ራስ ወዳድነትንና የሌላውን መመኘትን ግን ሳይገስጹ ያልፉዋቸዋል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በእጅጉ የሚያስቆጡት ኃጢአቶች እነዚህ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ ባሕርይና በኃጢአት ያልተነካው ዩንቨርስ ከባቢ አየር ከሆነው ራስ ወዳድነት ከሌለበት ፍቅር ጋር ተጻራሪ ናቸውና፡፡ በእነዚህ ከባድ ኃጢአቶች ውስጥ የወደቀ ሰው ሃፍረትና ባዶነት ተሰምቶት ወደ ክርስቶስ ጸጋ መምጣት እንዳለበት ቢያስተውልም፤ክርስቶስ ለመስጠት የሚፈልገውን በረከት እንዳይቀበል ትዕቢት ልቡን ይደፍንበታል፡፡ክየመ 28.1

    «አቤቱ እኔን ኃጢአተኛውን ይቅር በለኝ» (ሉቃ. 8፡13) ብሎ ምስኪኑ ቀረጥ ሰብሳቢ በጸለየ ጊዜ የእራሱን ክፉነትና ኃጢአተኝነት መመልከት ቻለ፡፡ሌሎችም በዚሁ መልክ ያዩት ነበር፡፡ እርሱ ግን ምን እንደሚያስፈልገው ስለተሰማው ምህረትን እየለመነ ከበደል፣ ከሃፍረትና ከሸክሙ ጋር ወደ እግዚአብሔር ፊት መጣ፡፡ ልቡም ከኃጢአት ኃይል ነጻ ለሚያወጣው ለእግዚአብሔር መንፈስ ክፍት ነበር፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፣ የፈሪሳዊው በትዕቢት የተሞላና ራስን ጻድቅ ያደረገ ጸሎት መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ገብቶ እንዳይሠራ ልቡን ያደነደነ ሰው መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረው ርቀት የተነሳ ፍጹም ከሆነው መለኮታዊ ቅድስና ጋር ራሱን ስላላስተያየ ምን ያህል በኃጢአት መርከሱ ሊሰማው አልቻለም ነበር፡፡ በመሆኑም እርዳታን ማግኘት አልቻለም፡፡ክየመ 28.2

    ሰው ኃጢአተኝነቱን ማየት ከቻለ እራሱን እስኪያስተካክል ድረስ መቆየት የለበትም:: «ወደ ክርስቶስ ለመምጣት ብቁ አይደለንም» ብለው የሚያስቡ ስንቶች ናቸው? ለመሆኑ እርስዎ በራስዎ ጥረት የተሻሉ ሰው መሆን እንደሚችሉ አድርገው ያስባሉ? «ኢትዮጵያዊ መልኩን፤ ነብርስ ዥንጉርጉርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንት ክፉ ማድረግ የለመዳችሁም መልካም ማድረግ አትችሉም» (ኤር 13:23)፡፡ ለእኛ እርዳታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው:: ወደ ክርስቶስ ለመምጣት ጠንከር ያለ አሳማኝ ነገር እስክናገኝ፣ የተሻለ ዕድል እስኪገጥመን ወይም በውስጣችን ቅዱስ ስሜት እስኪሰማን ድረስ መጠበቅ የለብንም:: እኛ በራሳችን ልናደርግ የምንችለው አንዳች ነገር ባለመኖሩ፤ ከእኛ የሚጠበቀው ባለንበት ሁኔታ ወደ ክርስቶስ መምጣት ብቻ ነው።ክየመ 29.1

    ነገር ግን እግዚአብሔር ከታላቅ ፍቅሩና ምህረቱ የተነሳ የእርሱን የማዳን ጸጋ የሚቃወሙትን እንኳ ሳይቀር ያድናቸዋል በማለት ማንም ራሱን አያታል፡፡ የኃጢአት እጅግ አስከፊነት ሊለካ የሚችለው በመስቀሉ ብርሃን ብቻ ነው:: «እግዚአብሔር እጅግ መልካም ስለሆነ ኃጢአተኞችን ወደ ውጪ አይጥልም» ብለው የሚያደፋፍሩ ሁሉ ወደ ቀራኒዮ ይመልከቱ፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መስዋዕት የሆነበት ምክንያት ከዚያ ውጪ ሰዎች ከሚያረክሰው የኃጢአት ኃይል ሊድኑ የሚችሉበት፣ ከቅዱሱ ጋር ሕብረታቸው የሚታደስበትና እንደገና የመንፈሳዊ ሕይወት ተካፋይ የሚሆኑበት ሌላ መንገድ ስላልነበረ ነው:: በመሆኑም ያልታዘዘውን ሰው ኃጢአት በመውሰድ አዳኛችን በኃጢአተኛው ምትክ መከራና ሥቃይ ተቀበለ። የእግዚአብሔር ልጅ ፍቅር፣ ሥቃይና ሞት በአንድነት የኃጢአትን አስፈሪነት ከመመስከራቸው ባሻገር ከዚያ ለመውጣትና ከፍ ያለውን ሕይወት ተስፋ ለማድረግ ያለው ማምለጫ መንገድ ነፍስን ለክርስቶስ አሳልፎ መስጠት ብቻ መሆኑን በግልጽ ያስረዳሉ።ክየመ 29.2

    አንዳንድ ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው ያላዘኑና ሃፍረት ያልተሰማቸው ሰዎች፤በስም ክርስቲያን ነን ከሚሉት ጋር ራሳቸውን በማወዳደር «እነርሱ በባህሪያቸው እራሳቸውን ያልካዱ፣ ያልሰከኑ እና ጥንቃቄ የጎደላቸው በመሆናቸው ከእኔ የሚሻሉ አይደሉም:: እንደ እኔ ፌሽታና ፈንጠዝያ ይወዳሉ» በማለት የራሳቸውን ኃላፊነትና ግዴታ ወደ ጎን በመተው፤ ለትክክለኛነታቸው የሌሎችን ስህተት እንደ መረጃ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ ጌታ የሚስቱትን ሰዎች ምሳሌ አድርጎ አልሰጠንም! በመሆኑም የሌሎች ኃጢአትና ስህተት ለማንም ሰው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ነውር የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ለእኛ ምሳሌ ሆኖ ተሰጥቶናል፡፡ ውጪያዊው ክርስትና ብቻ የሚታይባቸውን ሰዎች ስለ እምነታቸው ደካማነት የሚከሱና የሚተቹ ሁሉየተሻለ ሕይወት ሊያሳዩዋቸውና የከበረ ምሳሌ ሊሆኗቸው ይገባል፡፡ አንድ ክርስቲያን እንዴት ዓይነት ሕይወት ሊኖረው እንደሚገባ ላቅ ያለ ግንዛቤ እስካላቸው ድረስ የበለጠው ኃጢአት የእነርሱ አይደለምን? ሊያደርጉ የሚገባቸውን ትክክለኛ ነገር ያውቃሉ ነገር ግን አያደርጉትም::ክየመ 30.1

    የእግዚአብሔር ልጅ ፍቅር፣ ሥቃይና ሞት በአንድነት የኃጢአትን አስፈሪነት ይመሰክራሉ፡፡

    በክርስቶስ የሚገኘውን ንጽህና በመሻት «ለነገ» ማለትን ትታችሁ ኃጢአታችሁን ሊያስተሰርይ የሚችለውን ውሳኔ ከመተግበር ወደ ኋላ አትበሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በብዙ ሺህ ሚቆጠሩ ሰዎች ለዘላለም ጥፋት የሚያደርሰውን ስህተት ፈጽመዋል፡፡ዘመኑ አጭር በሆነ ኑሮና ባልተረጋገጠ ሕይወት ለመኖር መምረጥ የለብንም፡፡ የሚማጸነንን የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ ድምፅ ለመታዘዝ መዘግየትና በኃጢአት ለመኖር መምረጥ በሚገባ ያልተስተዋለና አስፈሪ አደጋ ያለው ነው:: ለኃጢአት ምንም ያህል ትንሽ ግምት ቢሰጠውም ነገር ግን ተደጋግሞ በተደረገ ቁጥር እየገዘፈ በመሄድ አደጋው ዘላለማዊ ጥፋትን የሚያስከትል ይሆናል፡፡ እኛ ኃጢአትን ካላሸነፍን እርሱ ያሸንፈናል፤ ለዘላለም ጥፋታችንም መንስዔ ይሆናል፡፡ክየመ 30.2

    አዳምና ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ መብላትን እንደ ትንሽ ነገር በመቁጠር ራሳቸውን ባይሸነግሉ ኖሮ እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ዓይነቱ አስፈሪና አሳዛኝ ውጤት ባልተከሰተ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ትንሽ ነገር የማይለወጠውን የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ መተላለፍ ስላመጣ፣ ስብዓዊውን ፍጡር ከእግዚአብሔር ጋር አለያየው:: የሞትንም ደጃፍ በመክፈት ሊነገር የማይቻል ዋይታን በዓለማችን ላይ አመጣ፡፡ ከሰው አለመታዘዝ የተነሳ ከዘመን ወደ ዘመን የማያቋርጥ የጣር ልቅሶ ከምድራችን ሽቅብ ወደ ላይ ወጣ ኖሯል፡፡ ኃጢአት ባስከተለው ውጤት የተነሳ እነሆ ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት ሲያቃስቱና የሕመም ሥቃይ ሲደርስባቸው ይስተዋላል፡፡ ሰማይ እንኳ ሳይቀር ሰው በእግዚአብሔር ላይ ያደረገው የአመፃ ውጤት ተሰምቶታል፡፡ በዚህም ቀራንዮ መለኮታዊውን ሕግ ለተላለፉ ማስታረቂያ ይሆን ዘንድ ለተጠየቀው አስደናቂ መስዋዕት መታሰቢያ ሆኖ ይኖራል።ስለዚህ ኃጢአትን በጭራሽ እንደ ትንሽ ነገር አንቁጠረው።ክየመ 31.1

    በሰው ውስጥ የሚከሰተው እያንዳንዱ ሕግን የመተላለፍ ድርጊትና የክርስቶስን ጸጋ ችላ የማለት ወይም የመቃወም ተግባር፤ ልብን ያደነድናል፧ፈቃድንም ያዳክማል፤ አእምሮንም ብልሹ እያደረገ ማስተዋልን ያደነዝዛል፡፡ይህም አንድ ነፍስ በክርስቶስ ለመማረክ ያላትን ዝንባሌ ዝቅተኛ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሩህሩህ ለሆነው መንፈስ ተማጽኖ ራስዋን ለመስጠት ያላትን ችሎታ በእጅጉ አናሳ ያደርገዋል፡፡ክየመ 31.2

    ብዙዎች የቀረበላቸውን የምህረት ግብዣ በማቅለል የሚመርጡትን ክፉና የተሳሳተ አቅጣጫ በማንኛውም ጊዜ መለወጥ እንደሚችሉ አድርገው ያስባሉ፡፡ በዚህም የተረበሸ ህሊናቸውንና አስተሳሰባቸውን ለማረጋጋት ይሞክራሉ፡፡ ስሜታቸው ግን አሁንም ገና በዚያው ሁናቴ ውስጥ ተማርኮይገኛል፡፡ የጸጋን መንፈስ ንቀው ሁለንተናቸውን ለሰይጣን ካስገዙ በኋላ አስፈሪ ነገር በገጠማቸው ጊዜ በቅጽበት ክፉ መንገዳቸውን መለወጥ የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ግን በዋዛ የሚሆን አይደለም፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ያካበቷቸው የሕይወት ልምምዶችና ትምህርቶች ባህርያቸውን በክፉ መንገድ ስለቀረጹት የክርስቶስን ባህርይ ሕይወታቸው ለመቀበል የሚሹ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ክየመ 31.3

    አንድም ቢሆን የተሳሳተ ባህሪን ወይም የኃጢአት ምኞትን አጽንተን የምንይዝ ከሆነ፤ በውስጣችን የነበረውን የወንጌል ኃይል ቀስ በቀስ እየሸረሸ ረው ይሄዳል፡፡ እያንዳንዱ የኃጢአት ተግባር፣ ነፍስ በእግዚአብሔር ላይ ያላትን ጥላቻ ይበልጥ እያጠናከረች እንድትሄድ ያደርጋታል፡፡ ባለማመኑ የሚጸና ወይም ለመለኮታዊው እውነት አንዳችም ምላሽ የማይሰጥ ሰው ያንኑ የዘራውን ያጭዳል፡፡ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ክፉው እንደ ዋዛ መታየት እንደሌለበት ጠቢቡ ሰሎሞን የተናገረውን ያህል የሚያስፈራ ማስጠንቀቂያ የለም «ኃጥዕን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች፤ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል» ምሳ. 5:22ክየመ 32.1

    ክርስቶስ እኛን ከኃጢአት ነፃ ለማውጣት ዝግጁ ቢሆንም የእኛን ፈቃድ መጋፋት አይፈልግም:: ጽኑ በሆነ መተላለፍ ፈቃዳችን ሁሉ ለክፉው የተንበረከከ ከሆነ፣ ነጻ የመውጣት ምኞት ከሌለንና ጸጋውን ለመቀበል የማንፈልግ ከሆነ ከዚህ የበለጠ ምን ማድረግ ይቻለዋል? ፍቅሩን ለመቃወም በወሰንነው ውሳኔ ራሳችንን አጠፋን ማለት ነው:: በተወደደ ቀን ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ» (2ኛ ቆሮ. 6:2) «ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፤ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣ በዐመጽ እንዳደረጋችሁት፣ልባችሁን አታደንድኑ» (ዕብ. 3:7-8)፡፡ክየመ 32.2

    «ሰው የውጪውን ገጽታ ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል› (1ኛ ሳሙ. 16፡7)፡፡ ይህ ልብ ደስታና ሃዘን የሚፈራረቁበት፣ የሚሳሳት፣ ስሜታዊ፣ ርኩሰትና አታላይነት የተሞሉበት ልብ ነው:: እግዚአብሔር የሰውን ሃሳብ እንዲሁም ሊያደርግ ያቀደውን ሁሉ ያውቃል፡፡ በመሆኑም ባሉበት ሁናቴ ከእነ ጉድፍዎ ወደ እርሱ ይሂዱ ፤ እንደ ባለ መዝሙሩም ሁሉን ለሚያይ አምላክ ልቦናዎን ከፍተው እንዲህ ይበሉት «እግዚአብሐር ሆይ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፈትነኝ ሃሳቤንም እወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ፡፡» (መዝ. 139:23-24)ክየመ 32.3

    ብዙዎች ገና ልባቸው ሳይነጻ በአእምሮ እውቀት ላይ ብቻ የተመሰረተ ሃይማኖትና የአምልኮ መልክ ያለው ውጪያዊ ሃይማኖተኝነትን ይዘው ይኖራሉ፡፡ ጸሎትዎ እንዲህ ይሁን «አምላኬ ሆይ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ» (መዝ. 51፡10)፡፡ ከነፍስዎ ጋር በሐቀኝነት ይነጋገሩ፣ ይህ የሕይወትና የሞት ጥያቄ ስለሆነ በቆራጥነትና በጽናት ይቁሙ፤ ይህ በእርስዎና በእግዚአብሔር መካከል ዘላለማዊ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ክየመ 33.1

    የእግዚአብሔርን ቃል በጸሎት መንፈስ ያጥኑ፡፡ ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ በእግዚአብሔር ሕግና ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ የተገለጠውን ያለ ቅድስና «ማንም ጌታን ማየት አይችልም የሚለውን ታላቅ መርህ ይመለከታሉ (ዕብ. 12፡14)።የእግዚአብሔር ቃል ኃጢአተኝነታችንን እንድናምን ይረዳናል፣ የድነትንም መንገድ ግልጽና ቀጥተኛ አድርጎ ያሳየናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ለነፍስዎ ሲናገር ሳለ ተገቢውን ትኩረት ይስጡ፡ክየመ 33.2

    ኃጢአትን ካሳሸነፍን እርሱ ያሸንፈናል፣ ለዘላለም ጥፋታችንም መንስዔ ይሆናል።

    ክርስቶስ የመጣው ኃጢአተኞችን ሁሉ ሊያድን እንደመሆኑ የኃጢአትን ግዝፈትና እርስዎ የሚገኙበትን ሁናቴ በመመልከት ተስፋ አይቁረጡ: እኛ እግዚአብሔርን ከራሳችን ጋር አላስታረቅነውም ነገር ግን ድንቅ በሆነ ፍቅር እግዚአብሔር በክርስቶስ «ዓለምን ከራሱ ጋር አስታረቀ» (2ኛ ቆሮ. 5:19)፡፡የሳቱት ልጆቹን ልብ ወደ እርሱ ለመመለስ ሩህሩህ በሆነው ፍቅሩ ይለምናቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ሊያድናቸው የሚፈልገውን ሕዝቦቹን የሚታገሰውን ያህል ምድራዊ ወላጆች የልጆቻቸውን ስህተትና በደል ሊታገሱ አይችሉም:: በደለኞችን የእርሱን ያህል በርህራሄ የሚማጸን የለም::ከቀናው መንገድ ላፈነገጠው ነፍስ እንደ እርሱ ዓይነት የርህራሄ ልመና ያፈሰሰ አንዳችም ሰብዓዊ ከንፈር የለም:: እርሱ የሰጠን ተስፋና ማስጠንቀቂያ ሁሉ ሊነገር የማይችል የፍቅር እስትንፋስ ነው፡፡ክየመ 33.3

    ትልቁ ኃጢአተኛ እርስዎ መሆንዎን ሰይጣን ሊነግርዎ በመጣ ጊዜ ሽቅብ ወደ አዳኝዎ ኢየሱስ በመመልከት ስለከፈለልዎ ዋጋ ይናገሩ፡፡ ይህም ወደ እርሱ የብርሃን ጨረር እንዲመለከቱ ይረዳዎታል፡፡ ኃጢአትዎን ይመኑ፤ለጠላትም «ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ» (1ኛጢሞቴ. 1፡15) ብለው ይንገሩ፡፡ እርስዎ የሚድኑት ወደር በሌለው ፍቅሩ ነው:: ኢየሱስ ሁለት ተበዳሪዎችን አስመልክቶ ስምዖንን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- «አንድ ሰው ከጌታው ጥቂት ገንዘብ ተበደረ፧ ሌላው ደግሞ ብዙ ገንዘብ ተበደረው እናም አበዳሪያቸው ሁለቱንም ይቅር አላቸው፡፡ ታዲያ የትኛው ተበዳሪ ይበልጥ ጌታውን ይወድ ይመስልሃል?» ስምዖንም ሲመልስ «ብዙው ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል» አለው (ሉቃ. 7፡43)፡፡ የኃጢአተኞች ቁንጮ ሆነን ሳለ ይቅር እንባል ዘንድ ክርስቶስ ለእኛ ሞተ፡፡ ክርስቶስ ስለ እኛ በአብ ፊት ይታይ ዘንድ የከፈለልን መስዋዕትነት ብቁ ነው:: አብልጦ ይቅር ያላቸው ሁሉ አብልጠው ይወዱታል፡፡ ለዘላለማዊ መስዋዕቱና ለታላቅ ፍቅሩ ከዙፋኑ አጠገብ ቆመው ያወድሱታል፡፡ የእግዚአብሔርን ፍቅር በሙላት በምናስተውልበት ጊዜ የኃጢአትን አስከፊነት በሚገባ እንረዳለን፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኛ የተዘረጋውን የፍቅር ሰንሰለት ስናይ፣ ክርስቶስ ለእኛ ሲል የከፈለውን ዘላለማዊ መስዋዕትነት ስንረዳ፣ ሻክሮ የነበረው ልባችን እነሆ በፍቅሩ ይቀልጣል፡፡ክየመ 34.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents