Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

አእምሮ፣ባሕርይና ማንነት፣ክፍል 1

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ 13—የአእምሮ ምግብ

    ጥበብ ያለበት መሻሸል ያለ አግባብ ከመጠቀም ጋር ሲነጻጸር።--እግዚአብሔር መክሊቶችን የሚሰጠን ያለ አግባብ እንድንጠቀምባቸው ሳይሆን በጥበብ እንድናሻሽላቸው ነው። ትምህርት የሕይወትን ተግባሮች በሙሉ ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን የአካል፣ የአእምሮና የሞራል ኃይሎችን ማዘጋጀት ነው። ተገቢ ያልሆነ ንባብ የውሸት ትምህርት ይሰጣል። የትዕግስት ኃይል፣ የአእምሮ ብርታትና ሥራ ጥቅም ላይ በዋሉበት ሁኔታ በመመስረት ሊጨምሩ ወይም ሊቀንሱ ይችላሉ። --4T 498 (1880). {1MCP 107.1}1MCPAmh 89.1

    ጤናማ ምግብ ለአእምሮ።--ጤናማ ምግብ ለአካል እንደሆነ ሁሉ ንጹህና ጤናማ ንባብ ለአእምሮ ነው። በዚህ ዓይነት ፈተናን ለመቋቋም፣ ትክክለኛ ልማዶችን ለመመስረት እና ትክክለኛ በሆኑ መርሆዎች ላይ ለመመስረት ጠንካራ ትሆናለህ። --RH, Dec 26, 1882. (SD 178.) {1MCP 107.2}1MCPAmh 89.2

    የነፍስን መንገዶች ጠብቁ።--ፈተናን ለመቋቋም መሥራት ያለብን ሥራ አለ። ለሰይጣን መሳሪያዎች ሰለባ መሆን የማይፈልጉ ሰዎች የነፍስን መንገዶች በደንብ መጠበቅ አለባቸው፤ ንጹህ ያልሆኑ ሀሳቦችን የሚጠቁሙ ነገሮችን ከማንበብ፣ ከማየት ወይም ከመስማት መታቀብ አለባቸው። {1MCP 107.3}1MCPAmh 89.3

    አእምሮ የነፍሳት ጠላት በሚጠቁመው በእያንዳንዱ ትምህርት ላይ በዘፈቀደ እንዲባዝን መተው የለበትም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‹‹የአእምሮአችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ቅዱሳን ሁኑ›› ይላል (1ኛ ጴጥሮስ 1፡ 13-15)። (1 Peter 1:13-15, RV). {1MCP 107.4}1MCPAmh 89.4

    ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ ‹‹በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹህ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምሥጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ›› (ፊልጵስዩስ 4፡ 8)። ይህ ልባዊ ጸሎትንና ሁል ጊዜ ነቅቶ መጠበቅን ይጠይቃል። አእምሮን ወደ ላይ በሚስብና ንጹህና ቅዱስ ነገሮችን እንዲያስብ ማደሪያው ለማድረግ በውስጥ በሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ መመራት አለብን። የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት ማጥናት አለብን። ‹‹ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። ›› ዘማሪው ‹‹አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ውስጥ ደበቅሁ›› ይላል (መዝ. 119፡ 11)። --PP 460 (1890). {1MCP 108.1}1MCPAmh 89.5

    በንባብ ምርጫ ባሕርይ ይገለጣል። አንድ ሰው ያለው ኃይማኖታዊ ልምምድ ባሕርይ የሚገለጠው በትርፍ ሰዓቱ ለማንበብ በሚመርጣቸው መጻሕፍት ባሕርይ ነው። ጤናማ የአእምሮ ቅኝትና ትክክለኛ ኃይማኖታዊ መርሆዎች እንዲኖራቸው ወጣቶች በቃሉ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት በመፍጠር መኖር አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ አማካይነት የተዘጋጀውን የድነት መንገድ በማመልክት ከፍ ወዳለውና ወደ ተሻለው መንገድ የሚመራን መሪያችን ነው። እስካሁን ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ይልቅ እጅግ ደስ የሚልና እጅግ አስተማሪ የሆነ ታሪክና የሰዎችን ሕይወት ታሪክ ይዟል። ልብ-ወለድን በማንበብ አስተሳሰባቸው ያልተዛባ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከመጻሕፍት ሁሉ ይልቅ የሚስብ ሆኖ ያገኙታል።--YI, Oct 9, 1902. (MYP 273, 274.) {1MCP 108.2}1MCPAmh 90.1

    አንዳንድ መጻሕፍት አእምሮን ግራ ያጋባሉ።--በምድር ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተከምረው ካሉት መጻሕፍት መካከል አብዛኞቹ ለግንዛቤ ጠቃሚ ከመሆን ይልቅ አእምሮን ግራ ያጋባሉ። ሆኖም ሰዎች እነዚህን መጻሕፍት ለመግዛት ብዙ ገንዘብ ወጭ ያደርጋሉ፤ በጥናታቸው ጊዜ የጥበብ መጀመሪያና መጨረሻ የሆነውን የእርሱን ቃላት የያዘውን መጽሐፍ እስኪያገኙ ድረስ አመታትን ይፈጃል። እነዚህን መጻሕፍት በማጥናት የባከነው ጊዜ እርሱን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው የተባለለትን የእርሱን እውቀት በማግኘት ባክኖ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነበር። ይህን እውቀት የሚያገኙ ብቻ በመጨረሻ ‹‹እናንተ በእርሱ ፍጹማን ናችሁ›› (ቆላ. 2፡ 10) የሚሉትን ቃላት ይሰማሉ ።--(Pamphlet) Words of Counsel, 1903. (CH 369.) {1MCP 108.3}1MCPAmh 90.2

    ግራ የተጋባ መረዳት።--ከእግዚአብሔር የሚያርቁ መጻሕፍትን ለማንበብ ሲባል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ጎን በሚተውበት ጊዜ እና እነዚህ መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር መንግስት መርሆዎች ያለውን መረዳት ግራ ሲያጋቡ፣ የሚሰጠው ትምህርት ስሙ ተዛብቶ ቀርቦአል። ተማሪው ከክህደት አመለካከት ጋር ተደባልቆ ከፍተኛ ትምህርት ተብሎ የሚጠራው ትምህርት በደንብ ተበጥሮ ንጹህ የአእምሮ ምግብን ካላገኘ በቀር እግዚአብሔርን በትክክል ማወቅ አይችልም። በድነት እቅድ ከሰማይ ጋር የሚተባበሩ ብቻ እውነተኛ ትምህርት በቀላሉ ምን እንደሆነ ያውቃሉ። --CT 15 (1913). {1MCP 109.1}1MCPAmh 90.3

    የከሃዲ ደራሲያን አምባገነን (ጨቋኝ) ኃይል (ኤንጄል እንስትራክተር ከሚል ጽሑፍ የተወሰደ)።--ሰብአዊ አእምሮዎች በሰይጣን ውሸቶች በቀላሉ ይማረካሉ፤ እነዚህ ሥራዎች ተቀባይነት ቢያገኙና አድናቆት ቢቸራቸው ለተቀባዩ የዘላለም ሕይወት የሚያረጋግጥለትን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ማሰላሰል ለዛ እንዲያጣ ያደርጋሉ። እናንተ ልማድ ያላችሁ ፍጡራን ስለሆናችሁ ጥሩ ልማዶች በራሳችሁ ባሕርይና በሌሎች ላይ ለመልካም ባላቸው ተጽእኖ በረከት መሆናቸውን ማሰብ አለባችሁ፤ ነገር ግን የስህተት ልማዶች፣ አንዴ ከተመሰረቱ፣ አምባገነን ኃይላቸውን በመጠቀም አእምሮዎችን ባሪያቸው ያደርጋሉ። በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ አንድም ቃል አንብበህ የማታውቅ ከሆነ [ከሃዲ ደራሲያን የጻፉአቸውን]፣ ከመጻሕፍት ሁሉ በላይ መጠናት ያለበትንና ከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ ብቸኛ የሆኑ ትክክለኛ ሀሳቦችን የሚሰጠውን መጽሐፍ ዛሬ ብታነብ እጅግ የተሻለ ነው። --6T 162 (1900). {1MCP 109.2}1MCPAmh 90.4

    ጥልቀት የሌለው ንባብ በሽተኛ አስተሳሰብን ይፈጥራል።--ከወጣቶቻችን መካከል እግዚአብሔር ከፍተኛ ችሎታዎችን የሰጣቸው አሉ። ከመክሊቶች ሁሉ የበለጡ መክሊቶችን ሰጥቶአቸዋል፤ ነገር ግን ታሪክን የማንበብ ፍላጎታቸውን እያሟሉ ስለቆዩ ለዓመታት ስለ እምነታችን ምክንያት ለመስጠት በጸጋና በእውቀት ምንም እድገት ስላላሳዩ ኃይሎቻቸው ደክመዋል፣ አእምሮዎቻቸው ግራ ተጋብተዋል፣ ዝለዋልም። ሰካራም ሰው የአስካሪ መጠጥን ፍላጎት ለመቆጣጠር እንደሚቸገር ሁሉ እነርሱም ለእነዚህ ጥልቀት ለሌላቸው ንባቦች ያላቸውን ፍላጎት መቆጣጠር አቅቷቸዋል። {1MCP 110.1}1MCPAmh 91.1

    እነዚህ ዛሬ ከማታሚያ ቤቶቻችን ጋር ግንኙነት ያላቸውና መጻሕፍትን ለመጠበቅ፣ ለሕትመት የሚሆኑ ቅጂዎችን ለማዘጋጀት፣ ወይም የስህተት ማጥሪያ ንባብ ለማንበብ የተዋጣላቸው ሰራተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን የአእምሮ በሽተኞች እስኪሆኑና በየትኛውም ቦታ ቢሆን በሀላፊነት ቦታ ለመሥራት ገጣሚ መሆን እስከማይችሉ ድረስ መክሊቶቻቸው ተዛብተዋል። ሀሳባቸው በሽተኛ ሆኖአል። ከተጨባጭ ውጭ የሆነ ሕይወት ይኖራሉ። ለሕይወት ተግባራዊ ሥራዎች ገጣሚዎች አይደሉም፤ እጅግ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ የሆነው ነገር ደግሞ ተአማኒነት ላለው ንባብ ሁሉ ፍላጎት ማጣታቸው ነው። {1MCP 110.2}1MCPAmh 91.2

    ‹‹የአንክል ቶም ትንሽ ክፍል›› በሚል መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን በጣም አስቂኝ ታሪኮች በሚመስል ምግብ ፍቅር ተነድፈዋል፣ ተማርከዋልም። ያ መጽሐፍ በጊዜው ስለ ባርነት ለነበሩአቸው የተሳሳቱ ሀሳቦች መነቃቃት ለፈለጉት ጥሩ ነገር አድርጎላቸዋል፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት እንደ እነዚህ ያሉ ታሪኮች በማያስፈልጉበት በዘላለማዊው ዓለም ዳርቻ ላይ ቆመናል።--5T 518, 519 (1889). {1MCP 110.3}1MCPAmh 91.3

    አእምሮን ደካማ የሚያደርጉ መጻሕፍት።--የፍቅር ታሪኮችና ከንቱና አነቃቂ የሆኑ አፈ ታሪኮች ለእያንዳንዱ አንባቢ እርግማን የሆኑ ሌሎቹ የመጻሕፍት ክፍልን ይመሰርታሉ። ደራሲው ከመጽሐፉ ጋር ጥሩ ግብረገብን ሊያያይዝና በመላው ሥራው ውስጥ ኃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ሊያስገባ ይችላል፣ ሆኖም በአብዛኞቹ ሁኔታዎች እጅግ በተሳካ ሁኔታ ለማታለልና ለማሳሳት የመልአክን ልብስ ለብሶአል። አእምሮ ከዚያ ከሚመገበው ነገር የተነሣ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል። ከንቱና አነቃቂ አፈ ታሪኮችን የሚያነቡ ሰዎች በፊታቸው እየጠበቃቸው ላለው ሥራ ገጣሚዎች አይሆኑም። ከተጨባጭ ውጭ የሆነ ሕይወት ስለሚኖሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመመርመርና ሰማያዊ መናን ለመመገብ ፍላጎት የላቸውም። አእምሮአቸው ደካማ ስለሚሆን ተግባርንና የመጨረሻ መዳረሻን በሚመለከቱ ታላላቅ ችግሮች ላይ ለማሰላሰል ኃይል ያጣል። -7T 165 (1902). {1MCP 110.4}1MCPAmh 92.1

    ልብ-ወለድና ዓለማዊ (ፍትወተኛ) ሀሳቦች።-- ልብ-ወለድ ጽሁፎችን አንባቢ የሚናፍቀው የአእምሮ ምግብ ውጤቱ በካይ ሲሆን ቆሻሻና ፍትወተኛ ወደሆኑ ሀሳቦች ይመራል። እነዚህ ነፍሳት የዘላለማዊ ሕይወት ተስፋዎቻችን ማዕከል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ እውቀት ማግኘትን ችላ በማለታቸው ምን ያህል ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደሆነ በመገንዘቤ ልባዊ የሆነ ሀዘኔታ ተሰምቶኛል። እውነተኛ መልካምነትን መማር ይችሉበት የነበረ ብዙ ሰዓት ባክኖአል። --CTBH 123, 1890. (MYP 280.) {1MCP 111.1}1MCPAmh 92.2

    አእምሮ ወደ ጅልነት ይሰምጣል (በሕመም ምክንያት ለደከመች የቤት እመቤት የተሰጡ የማስጠንቀቂያ ቃላት)።--አእምሮሽ በአለቶችና በአረሞች ተሞልቶ፣ ውኃው ወደ ጠፍ መሬት እንደሚፈስና፣ ለዓመታት እንደሚንፎለፎል ጅረት ነበር። ኃይሎችሽ ከፍ ባሉ አላማዎች ቁጥጥር ተደርጎባቸው ቢሆን ኖሮ አሁን እንደሆንሽ ደካማ (የማትረቢ) አትሆኝም ነበር። ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በሚቀያየር የምግብ ፍላጎትሽና ከመጠን ባለፈ ንባብሽ መቀጠል እንዳለብሽ ትቃዥያለሽ። {1MCP 111.2}1MCPAmh 92.3

    የሆነ ማራኪ ታሪክን እያነበብሽ በክፍልሽ ውስጥ የእኩለ ሌሊት መብራት ሲበራና ንባቡ መጀመሪያውኑ ከመጠን በላይ የተነቃቃውን አእምሮሽን የበለጠውን እያነሳሳው አየሁ። ይህ አካሄድሽ ሕይወትን የመቆጣጠር ችሎታሽን እየቀነሰ በአካል፣ በአእምሮና በግብረገብ ደካማ እያደረገሽ ነው። ሕግን አለመከተልሽ በቤትሽ ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነትን እየፈጠረ ስለሆነ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አእምሮሽ ወደ ጅልነት እንዲሰምጥ ያደርጋል። እግዚአብሔር የሰጠሽ የምህረት ጊዜ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ውሏል፣ እግዚአብሔር የሰጠሽ ጊዜ ባክኗል። --4T 498 (1880). {1MCP 111.3}1MCPAmh 92.4

    የአእምሮ ስካሮች።--የከንቱና ቀስቃሽ አፈ-ታሪኮች አንባቢዎች ለተግባራዊ ሕይወት ተግባሮች የማይገጥሙ ይሆናሉ። ተጨባጭ ባልሆነ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ። እንደዚህ ያሉ ታሪኮችን ማንበብን ልማዳቸው እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸውን ልጆች ተመልክቻለሁ። በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ እረፍት የለሾች፣ እያለሙ የሚኖሩ፣ እጅግ ተራ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ካልሆነ በስተቀር መነጋገር የማይችሉ ናቸው። ኃይማኖታዊ ሀሳብና ንግግር ሙሉ በሙሉ ለአእምሮአቸው እንግዳ ነው። ስሜትን የሚቀሰቅሱ ታሪኮችን የማንበብ ፍላጎትን ስላሳደጉ የአእምሮ ምርጫ ስለተዛባ ይህን ጎጂ ምግብ ካልተመገበ በቀር አይረካም። እንደዚህ ዓይነት ንባብ ለሚያስደስታቸው ሰዎች የአእምሮ ሰካራሞች ከሚል የተሻለ ስም ለማግኘት ማሰብ አልችልም። የምግብና የመጠጥ ፍላጎትን ያለመቆጣጠር ልማዶች በአካል ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ ሁሉ የንባብ ፍላጎትን ያለመቆጣጠር ልማድም በአእምሮ ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ ያሳድራል። --CT 134, 135 (1913). {1MCP 111.4}1MCPAmh 93.1

    ከመጠን ያለፈ ራስን ማስደሰት ኃጢአት ነው።--በመብላት፣ በመጠጣት፣ በማንቀላፋት ወይም በማየት ከመጠን በላይ ራስን ማሞላቀቅ ኃጢአት ነው። የአካልና የአእምሮ ኃይሎች የተጣጣመና ጤናማ ተግባር ደስታን ያመጣል።…የአእምሮ ኃይሎቻችን መስራት ያለባቸው ከዘላለማዊው ፍላጎቶች ጋር ግንኙነት ካላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው። ይህ ለአካልና ለአእምሮ ጤና ተስማሚ ይሆናል። --4T 417 (1880). {1MCP 112.1}1MCPAmh 93.2

    አእምሮን ከመጠን በላይ ማሰራት (ማጨናነቅ)።--የሁለት አመት ሥራን በአንድ አመት ውስጥ ለማከናወን የሚፈልግ ተማሪ ሊፈቀድለት አይገባም። ብዙዎች እንደሚያደርጉት እጥፍ ሥራን መሥራት ማለት አእምሮን ከመጠን በላይ ማሰራትና የአካል እንቅስቃሴን ችላ ማለት ነው። አእምሮ ከመጠን በላይ የሆነ የአእምሮ ምግብ ሲሰጠው መመገብ ይችላል ብሎ መገመት ተቀባይነት ያለው ሀሳብ አይደለም፤ የምግብ መፍጫ አካል ክፍሎች ላይ ጫና መፍጠር ኃጢአት እንደሆነ ሁሉ በአእምሮ ላይ ጫና መፍጠርም ኃጢአት ነው።--CT 296 (1913). {1MCP 112.2}1MCPAmh 93.3

    የንግግር ምግባችሁንም መርምሩ።--እያንዳንዷ ነፍስ እንድትመገብ እየቀረበላት ያለው የአእምሮ ምግብ ምን ዓይነት እንደሆነ በጥንቃቄ መመርመር ጥሩ ነው። ለማውራት የሚኖሩና ‹‹ዘገባ ስጠንና እኛም እንዘግባለን›› የሚሉ ወደ እናንተ ሲመጡ ይህ ንግግር መንፈሳዊ ጠቀሜታና መንፈሳዊ ቅልጥፍና እንዳለው ወይም እንደሌለው ቆም ብላችሁ አስቡ፤ ይህ የሚሆንበት ምክንያት በመንፈሳዊ ግንኙነት የእግዚአብሔርን ልጅ ሥጋ ልትበሉና ደሙን ልትጠጡ ትችላላችሁ። ‹‹በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ…›› (1 ጴጥሮስ 2፡ 4) የሚሉ እነዚህ ቃላት ብዙ ይገልጻሉ። {1MCP 112.3}1MCPAmh 93.4

    አሳባቂዎች፣ ወይም ሀሜተኞች ወይም የአሉሽ አሉሽ ወሬ አመላላሾች መሆን የለብንም፤ የሀሰት ምስክሮች መሆን የለብንም። እግዚአብሔር የማይረባ፣ ከንቱ ንግግር መናገርን፣ መቀለድን፣ ማፌዝን፣ ወይም ማናቸውንም ፍሬ-ቢስ ቃላት መናገርን ይከለክላል። ስለምንናገረው ነገር ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። ለተናጋሪውም ሆነ ለሰሚው የማይጠቅሙ የችኮላ ቃላት ለተናገርንበት በፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለን። ስለዚህ ሁላችንም የሚያንጹ ቃላትን እንናገር። በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያላችሁ እንደሆናችሁ አስታውሱ። ርካሽና ከንቱ ንግግርን አትፍቀዱ፣ ወይም የክርስትና ልምምዳችሁ ከስህተት መርሆዎች የተጠናቀረ እንዲሆን አትፍቀዱ። --MS 68, 1897. (FE 458.) {1MCP 113.1}1MCPAmh 94.1

    የምታየው ነገር ልቧን ያዛባባት ሴት።--እህት---፣ምንም እንኳን እጅግ በጣም ጥሩ የተፈጥሮ ችሎታ ቢኖራትም፣ እውነትን በማይወዱና ለእውነት ተብሎ በሚደረገው መስዋዕትነትና ራስን መካድ በማይሳተፉ፣ በማያምኑ ጓደኞቿና ዘመዶቿ ከእግዚአብሔር እንድትርቅ እየተደረገች ነው። እህት----፣ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ እንደሚመክረው፣ ከዓለም የመለየት አስፈላጊነት አልተሰማትም። ዓይኖቿ በሚያዩትና ጆሮቿ በሚሰሙት ነገር ልቧ ተዛብቷል። --4T 108 (1876). {1MCP 113.2}1MCPAmh 94.2

    ሞራልን የሚገድሉ ድምፆች፣ እይታዎችና ተጽእኖዎች።--በእያንዳንዱ እርምጃ የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ስላለባቸው ስለ ልጆቻችሁ በበኩላችሁ በጥልቀት ለመጨነቅ ምክንያት አለ። ከክፉ ጓደኞች ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ ከባድ ነው።…የሚታዩ ነገሮችን ስለሚያዩና የሚሰሙ ድምጾችን ስለሚሰሙ፣ በደንብ የተጠበቁ ካልሆኑ በስተቀር፣ ሳይታዩ ግን በእርግጠኝነት ልብን በመበከልና ባሕርይን በማጣመም፣ ሞራልን በሚገድሉ ተጽእኖች ሥር ይሆናሉ። --Pacific Health Journal, June, 1890. (AH 406.) {1MCP 113.3}1MCPAmh 94.3

    አንዳንድ ግንኙነቶች ቀስ ብሎ እንደሚገድል መርዝ ናቸው።--ድምጼ በአገሪቱ ወዳሉ ወላጆች ሁሉ መድረስ ቢችል ኖሮ፣ ጎደኞቻቸውን ወይም አብረዋቸው የሚሆኑአቸውን ልጆች በመምረጥ ሂደት፣ ለልጆቻቸው ፍላጎት እንዳይሸነፉ አስጠነቅቃቸው ነበር። ወጣቶች ከመለኮታዊ አስተያየቶች ይልቅ ጎጂ የሆኑ አስተያየቶችን በቀላሉ እንደሚቀበሉ የሚገነዘቡ ወላጆች ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ በጸጋ እንዲያድጉና በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጠው እውነት በልባቸው ውስጥ እንዲመሰረት ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እጅግ ምቹ (ተስማሚ) መሆን አለበት። {1MCP 113.4}1MCPAmh 94.4

    ልጆች ንግግራቸው ስለማይጠቅሙ ምድራዊ ነገሮች ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲሆኑ የእነርሱም አእምሮ ወደዚያ ደረጃ ይመጣል። የኃይማኖት መርሆዎች ሲጎድፉና ሰዎች እምነታችንን ሲያቃልሉ ሲሰሙ፣ እነርሱ እየሰሙ ሳለ በእውነት ላይ የሚፈጸሙ የተንኮል ተቃውሞዎች ብቅ ሲሉ፣ እነዚህ ነገሮች በአእምሮዎቻቸው ይጣበቁና ባሕርያቸውን ይቀርጻሉ። {1MCP 114.1}1MCPAmh 95.1

    አእምሮዎቻቸው በታሪኮች ከተሞሉ፣ እውነተኛም ይሁኑ ልብ-ወለድ፣ ቦታውን መያዝ ላለበት ጠቃሚ መረጃም ሆነ ለሳይንሳዊ እውቀት ቦታ የለም። ይህ ቀላል ለሆነ ንባብ ያለው ፍቅር በአእምሮ ላይ ያስከተለው እንዴት ያለ ጥፋት ነው! ለተስተካከለ ባህርይ መሰረት የሆኑትን የታማኝነትንና እውነተኛ እግዚአብሔርን የመምሰልን መርሆዎች አጥፍቷል። ይፍጠንም ይዘግይም እንጂ በአካል ውስጥ እንደተወሰደና ቀስ ብሎ መራራ ውጤቱ እንደሚገለጥ መርዝ ነው። በወጣቶች አእምሮ ውስጥ የተሳሳተ አሻራ ስተው፣ በአሸዋ ላይ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ በሚቆይ አለት ላይ ምልክት ፈጥሮ ያልፋል። --5T 544, 545 (1889). {1MCP 114.2}1MCPAmh 95.2

    ዓይኖች በክርስቶስ ላይ ተተክለው።--ክርስቶስ በራሱ ላይ ሰብአዊ ተፈጥሮን በተቀበለ ጊዜ በግለሰቡ በራሱ ምርጫ ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም ኃይል ሊበጠስ በማይችል በፍቅር ገመድ ሰብአዊነትን ከራሱ ጋር አስተሳሰረ። ይህን ገመድ እንድንበጥስና ራሳችንን ከክርስቶስ ለመለየት እንድንመርጥ ሰይጣን ባለማቋረጥ ማታለያዎቹን ያቀርብልናል። ሌላ ጌታ እንድንመርጥ ምንም ነገር እንዳያባብለን መንቃት፣ መጣር፣ መጸለይ ያለብን እዚህ ላይ ነው፤ ይህን ለማድረግ ሁል ጊዜም ነጻነት አለን። ነገር ግን ዓይኖቻችንን በክርስቶስ ላይ እንትከል፣ ይህን ካደረግን እርሱ ይጠብቀናል። ወደ ኢየሱስ ስንመለከት ከአደጋ እንጠበቃለን። ምንም ነገር ከእጁ መንጭቆ ሊያወጣን አይችልም። ያለ ማቋረጥ እርሱን ስንመለከት ‹‹በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን›› (2ኛ ቆሮ. 3፡ 18)። --SC 72 (1892). {1MCP 114.3}1MCPAmh 95.3

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents