Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ምዕራፍ ፲፭—መጽሐፍ ቅዱስና የፈረንሳይ አብዮት

    ተሐድሶው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን ከፍቶ ለሕዝቡ በማድረስ በሁሉም የአውሮፓ አገራት ተቀባይነት ለማግኘት ጥረት ላይ ነበር። አንዳንድ አገሮች እንደ ሰማይ መልእክተኛ በደስታ ተቀበሉት’ በሌሎች ስፍራዎች ደግሞ ተሐድሶው እንዳይገባ በመከልከሉ ረገድ ጳጳሳዊ ስርዓቱ በአብዛኛው ተሳካለት፤ እናም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብርሐን፣ ከፍ ከፍ ከሚያደርገው ተጽዕኖው ጋር ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ተገልሎ ነበር። በአንዲት አገር ብርሃኑ መግቢያ ቢያገኝም ከጽልመቱ የተነሳ ማስተዋል አላገኘም ነበር። ለምዕተ ዓመታት እውነትና ሐሰት የበላይነትን ለመቆናጠጥ ታግለዋል። በመጨረሻም ክፋት አሸናፊ ሆኖ የሰማይ እውነት ተገፍትሮ ወጣ፤ “ብርሐንም ወደ ዓለም ስለመጣ፣ ሰዎችም ከብርሐን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው” [ዮሐ 3÷19]። ይህች አገር የመረጠችውን መንገድ ውጤት ታጭድ ዘንድ ተተወች። የሚገድበው የእግዚአብሔር መንፈስ የፀጋውን ስጦታ ካቃለለ ሕዝብ ተወሰደ። ክፋት ይጎመራ ዘንድ ፈቃድ አገኘ፤ መላው ዓለምም ብርሐንን በፈቃደኝነት እምቢ የማለት ፍሬን ተመለከተ።GCAmh 196.1

    በፈረንሳይ ለአያሌ ምዕተ ዓመታት የቀጠለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የቀጠለው ጦርነት በአብዮቱ ክስተቶች ተደመደመ። ያ በድንገት የመጣ አሰቃቂ ክስተት ሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያደረገችው ጭቆና ተገቢ ውጤት ነበር። ይህ የጳጳሳዊው መርሃ ግብር ያስከተለው መዘዝ፣ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ የሮማ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲኮተኩተው የቆየውን ዝንባሌ በተግባር ያሳየ፣ ዓለም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ካስተናገደችው ለየት ያለ ክስተት ያበረከተ ትዕይንት ነበር።GCAmh 196.2

    በጳጳሳዊው ሥርዓት የበላይነት ዘመን የነበረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚመጣው ጭቆና በነብያት ተነግሮ ነበር። ገላጩም [ክርስቶስም] “የኃጢአት ሰው” [2ኛ ተሰሎ 2÷3] በሚቆጣጠራቸው፣ በተለይም በፈረንሳይ ላይ የሚጠራቀመውን አሰቃቂ ውጤት አመልክቷል።GCAmh 196.3

    የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለ፣ “እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ…. ምስክራቸውንም ከፈፀሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፣ ያሸንፋቸውማል፣ ይገድላቸውማል። በድናቸውም በታላቋ ከተማ አደባባይ ይተኛል። እርሱም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞም ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። እነዚህም ሁለት ነብያት በምድር የሚኖሩትን ስላሰቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል። በደስታም ይኖራሉ፣ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። ከሶስት ቀን ተኩልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ። ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው።” [ራዕይ 11÷2-11]።GCAmh 196.4

    እዚህ ላይ የተጠቀሱት “አርባ ሁለት ወር” እና “ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀናት” የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በሮም እጅ የምትሰቃይበትን ዘመን የሚወክሉ አንድ አይነት ናቸው። የ1260 ዓመታቱ የጳጳሳዊ ሥርዓት የበላይነት የጀመረው ስርዓቱ ሲቋቋም ማለትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ538 ዓ.ም ሲሆን ያበቃው ደግሞ በ1798 ዓ.ም ነው። በዚያን ጊዜ የፈረንሳይ ጦር ሮም ገብቶ ሊቀ ጳጳሱን እስረኛ ካደረገው በኋላ ሊቀ ጳጳሱ በእስር እንዳለ ሞቷል። ብዙም ሳይቆይ አዲስ ሊቀ ጳጳስ ቢመረጥም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን ጳጳሳዊ መዋቅሩ በፊት የነበረውን ኃይሉን መጠቀም አልተቻለውም።GCAmh 196.5

    የቤተ ክርስቲያን ስደቱ ለ1260 ዓመታት ሁሉ አልቀጠለም ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ ካለው ምሕረት የተነሳ እንደ እሳት የሚፋጀውን ፈተና አሳጠረው። በቤተ ክርስቲያን ላይ ስለሚወድቀው “ታላቁ መከራ” አዳኙ ሲናገር፣ “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ስጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” ብሏል [ማቴዎስ 24÷22]። ከተሐድሶው ተጽዕኖ የተነሳ ስደቱ ከ1798 ዓ.ም ቀደም ብሎ ቆሞ ነበር።GCAmh 197.1

    ሁለቱን ምስክሮች በተመለከተ ነብዩ በተጨማሪ ሲናገር፣ “እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። “ሕግህ [ቃልህ/Thy Word]” አለ መዝሙረኛው፣ “ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሐን ነው” [ራዕይ 11÷4፤ መዝ 119÷105]። ሁለቱ ምስክሮች የብሉይና የአዲስ ኪዳን መፃሕፍትን የሚወክሉ ናቸው። እነዚህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ሕግ መነሻው ከየት እንደሆነና ስለዘላለማዊነቱም ጠቃሚ ምስክሮች ናቸው። ለመዳን እቅድም እንዲሁ ምስክሮች ናቸው። የብሉይ ኪዳን ጥላዎች፣ መስዋዕቱና ትንቢታቱ አዳኝ እንደሚመጣ ወደፊት ያመለክታሉ። ወንጌላቱና መልእክቶቹ ደግሞ አስቀድሞ በተነገረው በምሳሌና ጥላ፣ እንዲሁም በትንቢት በትክክል እንደተነገረው፣ እንዲሁ ስለመጣው አዳኝ ይናገራሉ።GCAmh 197.2

    “ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ” [ራዕይ 11÷3]። በዚህ ዘመን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔር ምስክሮች ተጋርደው ቆይተዋል። ጳጳሳዊ ስልጣን የእውነትን ቃል ከሕዝቡ ለመደበቅ ጥሯል፤ ምስክርነቱንም መቃረን ይቻለው ዘንድ የሐሰት ምስክሮችን አቅርቦላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በሐይማኖታዊና በዓለማዊ ስልጣን ሲወገዝ፣ ምስክርነቱ ሲጣመም፣ የሰዎች አዕምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይርቅ ዘንድ ሰዎችና አጋንንት የፈጠራ ሥራ እንዲያደርጉ የተቻለው ሁሉ ጥረት ሲደረግ፤ የያዛቸውን የከበሩ እውነቶች ያውጁ ዘንድ የደፈሩት ሲታደኑ፣ ሲካዱ፣ ሲገረፉ፣ ከመሬት በታች ባሉ ወህኒ ቤቶች ሲቀበሩ፣ ለእምነታቸው መስዋዕት ሲሆኑ፣ ወይም ማግኘት ወደሚያስቸግሩ ተራራዎች፣ ጉድጓዶችና ዋሻዎች እንዲሸሹ በተገደዱበት ጊዜ…. ያኔ ታማኝ ምስክሮች ማቅ ለብሰው ትንቢት ተናገሩ። ያም ሆኖ በ1260 ዓመታት ሁሉ ምስክርነታቸውን ቀጠሉ። በድቅድቅ ጨለማ ዘመናት ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል የሚወዱ፣ ለአምላክ ክብር የሚቀኑ ታማኝ ሰዎች ነበሩ። በዚህ ሁሉ ዘመን የእርሱን እውነት ያውጁ ዘንድ ለእነዚህ ታማኝ አገልጋዮች ጥበብ፣ ኃይልና ስልጣን ተሰጣቸው።GCAmh 197.3

    “ማንምም ሊጎዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሎጎዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል” [ራዕይ 11÷5]። ቅጣት ሳያስከትልባቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ላይ መረማመድ አይቻላቸውም። የዚህ አስፈሪ ውግዘት ትርጉም በራዕይ መጽሐፍ የመጨረሻው ምዕራፍ ተመልክቷል፦ “በዚህ መጽሐፍ የተፃፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተፃፉትን መቅሰፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተፃፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል በዚህ መጽሐፍ ከተፃፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።” [ራዕይ 22÷18፣19]።GCAmh 197.4

    የተገለፀውን ወይም የታዘዘውን በምንም አይነት ሁኔታ ከመቀየር ይቆጠቡ ዘንድ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች እኒህ አይነቶቹ ናቸው። እነዚህ ጠንካራ ውግዘቶች፣ በተጽዕኖአቸው አማካይነት ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ አቅልለው እንዲመለከቱ በሚመሩ ሁሉ ላይ የሚወርዱ ናቸው። ይህ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ታዘዝንም አልታዘዝንም የሚያመጣው መዘዝ ኢምንት ነው ብለው በንቀት የሚያውጁትን ሊያስደንግጥና ሊያርበደብድ ይገባል። የራሳቸውን ሐሳብ ከመለኮታዊ መገለጥ በላይ ከፍ የሚያደርጉ ሁሉ፣ ለራሳቸው ምቾት ይገጥም ዘንድ፣ ወይም ከዓለም ጋር ይመሳሰሉ ዘንድ፣ ግልጽ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚቀይሩ እነርሱ በራሳቸው ላይ አስፈሪ ኃላፊነትን የሚጭኑ ናቸው። የተፃፈው ቃል፣ የእግዚአብሔር ሕግ የእያንዳንዱን ሰው ባህርይ ይመዝናል። ይህ ፍፁም የማይሳሳተው መለኪያ ጎደሎ አለባቸው ያላቸውን ሁሉ ያወግዛቸዋል።GCAmh 198.1

    “ምስክርነታቸውን ከፈፀሙ በኋላ [እየፈፀሙ ሳለ]” [ራእይ 11÷7]፤ ሁለቱ ምስክሮች ማቅ ለብሰው ትንቢት የሚናገሩበት ዘመን በ1798 ዓ.ም አበቃ። ሳይስተዋሉ፣ የሥራቸውን ማቆሚያ ጊዜ እየተቃረቡ ሲሄዱ “ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ” [ራእይ 11፦7] በመባል የተገለጠው ኃይል ጦርነት ያውጅባቸው ዘንድ ነበረው። በብዙ የአውሮፓ አገሮች ቤተ ክርስቲያንንና አገርን ያስተዳድሩ የነበሩ ኃይላት ለብዙ መቶ ዓመታት በጳጳሳዊው ሥርዓት አማካኝነት በሰይጣን ቁጥጥር ስር ነበሩ። ሆኖም እዚህ ላይ አዲስ የሰይጣናዊ ኃይል መገለጥ ወደ ማስተዋል እንዲመጣ ተደርጓል።GCAmh 198.2

    ለመጽሐፍ ቅዱስ የሚገባው ክብር ነው በሚል ሰበብ በማይታወቅ ቋንቋ ተቆልፎ ከሕዝቡ የተሰወረ ይሆን ዘንድ የሮም መርሃ ግብር ነበር። በእርስዋ አገዛዝ ስር ሆነው፣ ምስክሮች “ማቅ ለብሰው” ትንቢት ተናገሩ። ሆኖም ሌላኛው ኃይል - ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ - በመነሳት፣ ግልጽ የሆነ፣ ራሱ በአደባባይ የሚመሰክረው ጦርነት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያውጅ ዘንድ ነበረው።GCAmh 198.3

    በመንገዶችዋ ላይ ምስክሮች የሚታረዱባት ሬሳቸውም የሚወድቅባት “ታላቋ ከተማ”፣ “መንፈሳዊ ግብጽ” ናት። ከሌሎቹ በላቀ ሁኔታ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ከተገለፁ አገራት መካከል የሕያው እግዚአብሔርን መኖር በድፍረት የካደች ትዕዛዙንም የተገዳደረች አገር ግብጽ ነበረች። በግልጽና በከበደች የአመጽ እጅ፣ የሰማይን ስልጣን እንደ ግብጽ ንጉሥ የተቃወመ ሌላ ንጉሠ ነገሥት የለም። መልእክቱ በእግዚአብሔር ስም በሙሴ አማካኝነት ሲመጣለት ፈርዖን በኩራት፣ “ቃሉን እሰማ ዘንድ እሥራኤልንስ እለቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማነው? እግዚአብሔርንም አላውቅም እሥራኤልንም ደግሞ አልለቅም አለ” [ዘፀዓት 5፦2]። ይህ እምነት-የለሽነት (ኤትይዝም) ነው። በግብጽ የተመሰለችው አገር ለሕያው እግዚአብሔር መጠይቅ ተመሳሳይ የክህደት ድምጽ ታሰማለች። አንድ አይነት የእምነት-አልባነትንና የመገዳደር መንፈስም ታንፀባርቃለች። “ታላቋ ከተማ”፣ “በመንፈስ” ከሰዶም ጋርም ተነፃጽራለች። የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስ ረገድ የሰዶም ብልሽት፣ በተለይም በወሲብ ልቅነት ተንፀባርቆ ነበር። የዚህን ጥቅስ አገላለጽ የምታሟላው አገር ጎልቶ የሚስተዋለው ባህርይዋም ይህ ኃጢአት ሊሆን ነበረው።GCAmh 198.4

    እንደ ነብዩ አነጋገር፣ ያን ጊዜ፣ ከ1798 ዓ.ም ትንሽ ቀደም ብሎ ምንጩና ባህርይው ከሰይጣን የሆነ አንድ ኃይል ተነስቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጦርነት ያውጃል። የሁለቱ የእግዚአብሔር ምስክሮች ምስክርነት ዝም እንዲል በሚደረግበትም ምድር የፈርዖን እግዚአብሔርን የመካድ ድርጊትና የሰዶም ልቅነት የሚንፀባረቅ ይሆናል።GCAmh 199.1

    ይህ ትንቢት በፈረንሳዩ ታሪክ አንፀባራቂና እቅጭ ፍፃሜውን አግኝቷል። በ1793ቱ አብዮት “በስልጡን ዘመን በተወለዱና በተማሩ ከስመ ጥር የአውሮፓ አገራት መካከል አንድዋ የሆነችውን አገር ለመምራት ይገባናል ባሉ ሰዎች ህብረት የሰው ነፍስ ሊቀበል የሚችለውን ታላቅ እውነት ለመካድ የተባበረ ድምጻቸውን በአንድነት ሲያሰሙና ያለ አንዳች ተቃውሞም የጌታን እምነትና አምልኮ ሲያወግዙ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ተመለከተ።”-Sir Walter Scott, Life of Napoleon, vol. 1, ch. 17። ፈረንሳይ፣ ከዓለም አገራት ተለይታ በዓለማት ፈጣሪ ላይ በአደባባይ የተቃውሞ እጆቿን የዘረጋች፣ እንዲህ በማድረጓም የማያጠራጥር መረጃ ያለባት፣ ብቸኛዋ አገር ናት። ብዙ እግዚአብሔርን የሚሳደቡ፣ ብዙ እምነት የለሾች በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በስፔንና በሌሎች ስፍራዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ፈረንሳይ ግን በሕግ አውጪ ምክር ቤትዋ አዋጅ አማካኝነት እግዚአብሔር የለም ብላ የለፈፈች፣ በዚህ አዋጅ ከመፈንደቃቸው የተነሳ መላው የከተማዋ ሕዝብ፣ እንዲሁም አብዛኞች በሌላ ስፍራ የሚኖሩ ሴቶችና ወንዶች በአንድ ላይ የጨፈሩባትና የዘፈኑባት፣ ከዓለም ለየት ያለች ብቸኛዋ አገር ናት።”-Blackwood’s Magazine, November, 1870።GCAmh 199.2

    በተጨማሪም ፈረንሳይ፣ ሰዶምን ለየት ያደረጋትን ባህርይ ታንፀባርቅ ነበረች። በአብዮቱ ጊዜ፣ በሜዳማው ከተሞች [ሰዶምና ጎመራ] ላይ ውድመት ያመጣው የስነ ምግባር ልሽቀትና ብልሽት በፈረንሳይ ይስተዋል ነበር። በትንቢቱ እንደተናገረው የታሪኩ ሰው የፈረንሳይን ከሃዲነትና ልቅነት ሲያስቀምጥ፣ “ከእነዚህ ሕግጋት ጋር ተቆራኝቶ በኃይማኖት ላይ ተጽዕኖ የፈጠረው — ሰዎች ይገነቡት ዘንድ ከሚችሉት ህብረት ሁሉ ፈጽሞ የተቀደሰ የሆነውን፣ በቋሚነት በመኖሩም ምክንያት በእርግጠኛነት ወደ ማህበረሰብ መጠናከር የሚመራውን የጋብቻ ግንኙነት፣ ሁለት ሰዎች የሚፈጽሙት ሲያሻቸውም የሚያፈርሱት የጊዜያዊነት (ቋሚ ያልሆነ) ባህርይ ወዳለው ሰብዓዊ ውል ዝቅ እንዲል ያደረገው ሂደት ነው.… የሰው ዘር ጠላቶች በትዳር (በቤት) ህይወት ውስጥ ያለን ክቡር፣ ባለፀጋ ወይም ቋሚ የሆነ ማንኛውንም ነገር ለማጥፋት ይችሉ ዘንድ ውጤታማ ዘዴ ለማግኘት ሲዶልቱ፣ አላማቸው ያደረጉት ተንኮልም፣ [ብልሽቱ] ከአንድ ትውልድ ወደሚቀጥለው ትውልድ በቀጣይነት ይተላለፍ ዘንድ እርግጠኛ ለመሆን ጋብቻን ከማቆርቆዝ የተሻለ ሌላ የተሳካ አቅድ ሊፈጥሩ አይቻላቸውም ነበር.… በቀልደኛ ንግግሮቿ ዝነኛ የነበረችው ተዋናዊቷ ሶፊ አርኖልት የፈረንሳዮቹን ሪፐብሊካኖች ጋብቻ ስትገልፀው ‘የዝሙት ሥርዓተ-ቁርባን’ ብላዋለች።”-Scott, vol. 1, ch. 17።GCAmh 199.3

    “ጌታችን የተሰቀለባት ናት።” [ራዕይ 11÷8]’ የዚህ ትንቢት የሚጠቁመው ዝርዝርም በፈረንሳይ ተፈፃሚነትን አግኝቷል። በክርስቶስ ላይ ያለው የጠላትነት መንፈስ የተንፀባረቀበት እንደዚህ አይነት ሌላ ምድር አልነበረም። እውነት መራርና ጨካኝ ተቃውሞ የተጋረጠበት እንደዚህ ያለ አገር አልነበረም። ወንጌልን በሚመሰክሩ ሆኖም በምታሳድዳቸው ደቀ መዛሙርቱ ላይ ተፈፃሚ ባደረገችው ተግባር አማካይነት ፈረንሳይ ክርስቶስን ሰቅላዋለች።GCAmh 200.1

    የቅዱሳን ደም ለተከታታይ ምዕተ ዓመታት ሲፈስ ኖሮአል። “ለእግዚአብሔር ቃልና ለየሱስ ክርስቶስ ምስክር” ሲሉ ዋልደንሶች በፒድሞንት ተራራ ላይ ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የእውነት ምስክርነት ወንድሞቻቸው በሆኑት በፈረንሳይ አልቢጄንሶችም ተተግብሯል። በተሐድሶው ዘመን፣ የተሀድሶው ደቀ መዛሙርት በዘግናኝ እንግልት ተገድለዋል። ንጉሥና ልዑላን፣ የተከበሩ ሴቶችና እምቡጥ ደናግልት፣ የሀገሪቱ ኩራትና መመኪያ የሆኑ ሁሉ የክርስቶስ ሰማዕታት ሲሰቃዩ በመመልከት የአይን ድግስ በልተዋል። የሰብአዊ ልብ እጅግ የከበረ አድርጎ ለሚቀበላቸው መብቶች በመቆም ጀግኖቹ ሂዩጉኖቶች በብዙ የጦርነት መስኮች ደማቸውን አፍስሰዋል። ፕሮቴስታንቶች ህገ-ወጥ እንደሆኑ ተቆጥረው፣ የሚይዛቸው ሰው ዋጋ እንዲከፈለው እየተደረገ፣ እንደ ዱር አራዊት ይታደኑ ነበር።GCAmh 200.2

    በ“በረሃ የነበረችዋ ቤተ ክርስቲያን” በደቡባዊው ተራራማ ስፍራዎች ተደብቀው የኖሩ፣ ከጥንታዊያን ክርስቲያናት የሆኑ ጥቂት ተወላጆች በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ የነበሩ የአባቶቻቸውን ኃይማኖት የሚከተሉ ነበሩ። በተራራ ጥግ ወይም በጥሻ ውስጥ በጨለማ ለመገናኘት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ በፈረሰኛ ወታደሮች ታድነው እየተጎተቱ ተወስደው በመርከብ ውስጥ ለእድሜ ይፍታሽ ባርነት ይሰጡ ነበር። “ንፁሃን፣ እጅግ የነጠሩትና ብልህ የነበሩ የፈረንሳይ ዜጎች በአሰቃቂ እንግልት በዘራፊዎችና በነፍሰ ገዳዮች መካከል በሰንሰለት ይታሰሩ ነበር።” የተሻለ ዕድል የገጠማቸው እነርሱ፣ ያለ መሳሪያና እረዳት-አልባ ሆነው፣ ለፀሎት በጉልበታቸው ተንበርክከው ባሉበት ያለርኅራኄ ተገደሉ [ያለ እንግልት ወዲያው መገደል እንደ ተሻለ ዕድል ይቆጠር ነበር]። በመቶ የሚቆጠሩ የእድሜ ባለፀጎች፣ ተከላካይ የሌላቸው ሴቶች፣ እንዲሁም ንፁሃን ህፃናት በተሰበሰቡበት ስፍራ ተገድለው መሬት ላይ ይተዉ ነበር። የተለመደ የመሰብሰቢያ ስፍራቸው በነበረው በተራራው ጥግ ወይም በጫካው ሲጓዙ “በየአራት እርምጃው በሰይፍ ተወግተው የሞቱ ሬሳዎችንና ዛፍ ላይ የተንጠለጠሉ በድኖችን” ማግኘት ያልተለመደ ክስተት አልነበረም። አገራቸው “በሰይፍ፣ በመጥረቢያ፣ በቃጠሎ፣ ወድሞ ወደ ሰፊ ደብዛዛ ምድረበዳነት ተለውጦ ነበረ።” እነዚህ የግፍ ድርጊቶች የተፈፀሙት በጨለማው ዘመን ሳይሆን፣ “ሳይንስ በጎለበተበት፣ ጽሁፍ በተስፋፋበት፣ የፍርድ ቤቶችና የመዲናዎች መሪዎች የተማሩና አንደበተ-ርቱዕ የሆኑ እነርሱ በትህትና እና በፍቅር ፀጋዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ባሳደሩበት፣” በዚያ ደማቅ ዘመን ነበር።-Ibid., b. 22, ch. 7።GCAmh 200.3

    በጥቁሩ የወንጀል መዝገብ ዝርዝር ውስጥ ጥላሸት የመሰለው፣ በእነዚያ አሰቃቂ ምዕተ ዓመታት ከተፈፀሙት ክፉ ተግባራት ሁሉ እጅግ አስከፊ የነበረው የቅዱስ በርተለሚዎስ እልቂት ነበር። ያንን እጅግ አስፈሪና ጨካኝ የጥቃት ትዕይንት ዛሬም ድረስ ዓለም በሚያንዘፈዝፍ ድንጋጤ ያስታውሰዋል። በሮማዊያን ቀሳውስትና ባለስልጣናት ግፊት የፈረንሳይ ንጉሥ ለዚህ አሰቃቂ ተግባር ድጋፉን ሰጥቶ ነበር። በውድቅት በዝግታ ይሰማ የነበረው የቤተ መንግሥቱ ታላቅ ደወል ለፍጅቱ አዎንታዊ ምልክት ነበር። የንጉሣቸውን የክብር ቃል ኪዳን አምነው በፀጥታ በቤታቸው ተኝተው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፕሮቴስታንቶች ያለማስጠንቀቂያ ተጎትተው እየወጡ ያለርኅራኄ ተጨፈጨፉ።GCAmh 200.4

    በሮማ አክራሪዎች ውስጥ ሆኖ አዝማቹን የሚመራው ሰይጣን ነበር። ከግብጽ ባርነት የሕዝቦቹ የማይታየው መሪ ክርስቶስ እንደነበረ ሁሉ የሰማዕታትን ቁጥር በሚጨምረው በዚህ አሰቃቂ ሥራም የባሪያዎቹ የማይታይ መሪ ሰይጣን ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት በማይታመን (ለመረዳት በሚያስቸግር) ቁጣ ቀጥሎ፣ ግድያው ለሰባት ቀናት በፓሪስ ከተማ ተፈፀመ። በዋና ከተማዋ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በንጉሡ የተለየ ትዕዛዝ አማካኝነት ፕሮቴስታንቶች ሊገኙባቸው በሚችሉ ክፍለ ሀገራትና ከተማዎች ሁሉ ተስፋፋ። እድሜም ሆነ ፆታ ዋጋ የሚሰጥበት አልነበረም። ምንም የማያውቀው ህጻንም ሆነ ሽበታሙ ሽማግሌ አልተረፉም። ባለአባትና ጭሰኛ፣ ትልቅና ትንሽ፣ እናት እና ልጅ፣ ሁሉም በአንድ ላይ ታረዱ። ፍጅቱ በመላ ፈረንሳይ ለሁለት ወራት ዘለቀ። የአገሪቱ አበባዎች የነበሩ ሰባ ሺህ ሰዎች ረገፉ።GCAmh 201.1

    “ሊቀ ጳጳሱ፣ ግሪጎሪ 13ኛ፣ የሂዩጉኖቶችን ዕጣ ፈንታ ዜና ወደር በሌለው ደስታ ተቀበለው። የልቡ መሻት ተፈፀመለት። ቻርለስ 14ኛም አሁን የሚወደው ተመራጭ ልጁ ሆነ። ሮም በሀሴት ፈነደቀች። የቅዱስ አንጀሎ ግንብ ጠመንጃዎች የደስታ ሰላምታ ሰጡ፤ ደወሎቹ ከእያንዳንዱ ህንፃ አቃጨሉ። የደመራ እሳቶች ሌሊቱን ሙሉ ሲንቀለቀሉ አደሩ’ ግሪጎሪም በቤተክህነት መሪዎችና በቀሳውስት ታጅቦ፣ የሎሪየን የቤተ ክህነት መሪ ቴ ደየም (Te Deum) የሚባለውን ዜማ ወዳዜመበት ወደ ቅዱስ ሉዊስ ቤተ ክርስቲያን ያሸበረቀ ጉዞ አደረገ። በፈረንሳይ የነበረው ሕዝብ የሞት ጣር ሲቃ፣ ለሮም ቤተ መንግሥት የለሆሳስ መዋህድ ነበር። ክብር የተላበሰውን ፍጅት ለማስታወስ ሜዳሊያ ተቀረጸ፤ በቅዱስ ባርቶሎሚዎስ የተከናወኑትን አበይት ክስተቶች የሚያሳይ ስዕል ተሳለ፤ ያ ስዕል አሁንም ድረስ በቫቲካን ይገኛል። ቻርለስ ባሳየው የታዛዥነት ባህርይ ምስጋናውን ማሳየት የፈለገው ሊቀ ጳጳሱ ለቻርለስ የወርቅ ጽጌረዳ (the Golden Rose) ላከለት፤ በሮም መድረኮችም አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪዎች፣ ቻርለስን፣ ካተራይንና ጎይሶችን አዲሶቹ የጳጳሳዊው ቤተ ክርስቲያን መሥራቾች እንደሆኑ አድርገው አሞካሹአቸው።”-Henry White, The Massacre of St. Bartholomew, ch. 14, par. 34።GCAmh 201.2

    የቅዱስ ባርቶሎሚዎስን ጭፍጨፋ ያነሳሳው ያው የበላይ መንፈስ የአብዮቱንም ገጽታዎች መርቷል። የሱስ ክርስቶስ አስመሳይ እንደነበረ ታወጀ፤ የፈረንሳይ ከሃዲዎች መፈክርም “እርጉሙን ስበሩት” የሚል ሲሆን እርሱም ክርስቶስን ማለታቸው ነበር። ሰማይን የሚገዳደር ስድብና አፀያፊ ርኩሰት እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ እጅግ የተዋረዱ፣ የጭካኔና የምግባረ ብልሹነት አውሬዎች ሆነው የተተዉ ሰዎች ያለ ልክ ከፍ ከፍ ተደረጉ። በዚህ ሁሉ ታላቁ ክብር ለሰይጣን ተበረከተ፤ ክርስቶስ ግን ከእውነት፣ ከንጽህናና ራስ ወዳድ ካልሆነ ፍቅሩ ጋር ተሰቀለ።GCAmh 201.3

    “ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፣ ያሸንፋቸውማል፣ ይገድላቸውማል።” [ራዕይ 11÷7]። በአብዮቱና በሽብር ግዛቱ ዘመን ፈረንሳይን ይገዛት የነበረው ከሃዲ ኃይል ዓለም አይቶት የማያውቀው ጦርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጆ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል በብሔራዊ ምክር ቤቱ ተከልክሎ ነበር። መተግበር የሚቻለው ንቀት ሁሉ እየተንፀባረቀባቸው መጽሐፍ ቅዱሶች(Bibles) እየተሰበሰቡ በአደባባይ ተቃጠሉ። የእግዚአብሔር ሕግ እግር ስር ተረገጠ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቋማት ፈረሱ፤ ሳምንታዊው የእረፍት ቀን ወደ ጎን ተገፍትሮ በምትኩ እያንዳንዱ አስረኛ ቀን ለፈንጠዝያና ለስድብ ተገበረ። ጥምቀትና ቅዱስ ቁርባን ተከለከሉ። ሞት ዘላለማዊ እንቅልፍ እንደሆነ የሚናገሩ ማስታወቂያዎችም በመቃብር ስፍራዎች በቀላሉ እንዲስተዋሉ ሆነው ተለጠፉ።GCAmh 201.4

    እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ መሆኑ ቀርቶ፣ ጭራሽ የጅልነት መጀመሪያ ሆነ። ከነፃነትና ሃገሪቱን ከሚመለከቱ ጉዳዮች በስተቀር ማንኛውም ኃይማኖታዊ አምልኮ ተከለከለ። “ሀገርን ወክለው ከተከናወኑ ክስተቶች ውስጥ እጅግ ንቀትና ቅሌት የተሞላበት የልግጫ ተግባር አብዛኛው እንዲፈጸም የተደረገው በፓሪስ ህገ-መንግሥታዊ ጳጳስ አማካኝነት ነበር….ከነሙሉ አጀቡ ወደፊት እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ ለብዙ ዓመታት ሲሰብከው የነበረው ሐይማኖት በታሪክም ሆነ በተቀደሰው እውነት ዘንድ ምንም መሰረት የሌለው፣ በሁሉም አቅጣጫ ሲታይ፣ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር በሚሹ ቀሳውስት የተፈጠረ እንደሆነ ለጉባኤው ተናገረ። የምርና ግልጽ በሆነ ቋንቋ፣ ያመልከው ዘንድ ተለይቶ የተቀደሰበትን፣ የአምላክን ሕያውነት (መኖር) ክዶ፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለግብረ ገብነትና ለመልካም ባህርይ ለመገዛት የወደፊት ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ። ከዚያም ጳጳሳዊ ጌጦቹን በጠረጴዛው ላይ አኖረ፤ ወንድማዊ ሰላምታም ከጉባኤው መሪ ተቸረው። ብዙ ከሃዲ ቀሳውስት የዚህን የቤተ ክህነት መሪ ፈለግ ተከተሉ።”-Scott, vol. 1, ch. 17።GCAmh 202.1

    “እነዚህም ሁለት ነብያት በምድር የሚኖሩትን ስላሰቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል፣ በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ” [ራዕይ 11÷10]። ኃይማኖት-የለሽዋ ፈረንሳይ የሚገሥፀውን የሁለቱን የእግዚአብሔር ምስክሮች ድምጽ ዝም አሰኝታለች። የእውነት ቃል ሬሳ በየመንገዶችዋ ወደቀ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ ገደብና መጠይቅ የጣሉ እነርሱ በደስታ ፈነጩ። ሰዎች በአደባባይ የሰማይን ንጉሥ ተገዳደሩ፤ እንደ ጥንታዊያኑ ሃጥአንም “እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ?” [መዝ 73÷11] ብለው ጮኹ።GCAmh 202.2

    ለማመን በሚያስቸግር፣ ስድብ በተሞላበት ድፍረት ከአዲሱ መዋቅር ቀሳውስት መካከል አንዱ “እግዚአብሔር ሆይ በእርግጥ ካለህ የቆሰለውን ስምህን ተበቀል። እገዳደርሃለሁ! ዝም ብለህ ተቀመጥ። ነጎድጓድህን ለመጀመር እንዳትሞክር! ከዚህ በኋላ በአንተ ሕያውነት የሚያምን ማን ይኖራል?” አለ።-Lacretelle, History, vol. 11, ገጽ 309; in Sir Archibald Alison, History of Europe, vol. 1, ch. 10። ይህ የፈርኦንን ጥያቄ እንዴት የሚያስተጋባ ነው! “ቃሉን እሰማ ዘንድ እግዚአብሔር ማነው?” “እግዚአብሔርን አላውቅም!” [ዘጸ 5÷2]’GCAmh 202.3

    “ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል” [መዝ 14÷1]። እውነትን ስለሚያጣምሙም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና” [2ኛ ጢሞ 3÷9]። ፈረንሳይ “ለዘላለም የሚኖር.…ከፍ ያለው ልዑል” [ኢሳ 57÷15]ን፣ የሕያው እግዚአብሔርን አምልኮ በገሃድ አልቀበልም ካለች በኋላ የአመክንዮ እንስት ጣዖት (Goddess of Reason) በምትባል ስድ በሆነች ሴት ውክልና አምላኪነት አማካኝነት ወደሚያዋርድ የጣዖት አምልኮ ማሽቆልቆልዋ የጥቂት ጊዜ ጉዳይ ነበር። ይህ ክስተት በሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት፣ በከፍተኛው የመንግሥታዊና የሕግ አውጪ ባለስልጣናት ዘንድ ተግባራዊ ሆነ! የታሪክ ፀሃፊው፦ “በዚህ የእብደት ጊዜ ከተፈፀሙት ስነስርዓቶች መካከል አንዱ በእንግዳነቱና በእግዚአብሔር ከሃዲነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ነበር። የጉባኤው በሮች ለሙዚቃ ቡድኖች ወለል ብለው ተከፈቱ፤ ከእነርሱ በፊትም ነፃነትን የሚያወድስ መዝሙር የሚዘምሩ፣ የወደፊት አምልኮአቸው ትኩረት ያደረጓትን የአመክንዮ ጣዖት ብለው የሰየሙአትን የተሸፈነች ሴት የያዙ የመዘጋጃ ቤት አባላት በታላቅ አጀብ ገቡ። የኦፔራ ተወዛዋዥ ኮረዳ እንደሆነች እየታወቀ፣ ወደ መድረክ መብራቱ ስትደርስ በአንፀባራቂ ውበት ከተገለጠች በኋላ በፕረዘዳንቱ ቀኝ ተደረገች ….ለሚያመልኩት አመክንዮ ገጣሚ ወኪል እንደሆነች አድርጎ የፈረንሳይ ብሄራዊ መማክርት ሕዝባዊ አክብሮት ለዚች ሴት አበረከተላት። ይህ አምላክን ያዋረደ፣ የሚያስቅና እርባና ቢስ ሥነ-ሥርዓት የራሱ የአፈጻፀም መልክ ነበረው፤ የዚህ የአመክንዮ ጣዖት አምልኮ ምስረታም በአገሪቱ በሞላ ከአብዮቱ ክንውኖች ጋር ራሳቸውን አኩል አድርገው ማሳየት በሚፈልጉ ነዋሪዎች ዘንድ ሁሉ ታደሰ፣ ተደገመም።”-Scott, vol. 1, ch. 17።GCAmh 202.4

    የአመክንዮ አምልኮን ያስተዋወቀው ተናጋሪ፦ “የሕግ አውጪው አክራሪነት መሰረቱን ለቋል፤ ለአመክንዮ ቦታውን ሰጥቷል፤ ቤተ መቅደሶቹን ለቀን ወጥተናል፤ እንደገናም አቆጥቁጠዋል። ዛሬ በርካታ ሕዝብ በዚያው ተመሳሳይ ጣራ ስር ተሰብስቦ ለመጀመሪያ ጊዜ የእውነትን ድምጽ እንደገና ያስተጋባል። ፈረንሳዊያን በዚያ ሥፍራ እውነተኛውን የነፃነትና የአመክንዮ አምልኮ ያከብራሉ። በዚያ ለሪፐብሊኩ ሰራዊት ብልጽግና አዳዲስ ቃል ኪዳናትን እንመሰርታለን። በዚያ ሕይወት አልባ የሆኑትን ጣኦታት አምልኮ ትተን፣ ሕይወትና ኃይል የተሞላውን ምስል፣ የፍጥረት ግሩም ውጤት የሆነውን—አመክንዮን እናመልካለን።” አለ።-M. A. Thiers, History of the French Revolution, vol. 2, ገጽ 370, 371።GCAmh 203.1

    እንስቷ ጣዖት ወደ ጉባኤው በመጣች ጊዜ ተናጋሪው እጅዋን ይዞ ወደ ጉባኤው ዘወር በማለት፦ “ሟቾች፣ የራሳችሁ ፍርሃት በፈጠረው አቅመ-ቢስ በሆነ አምላክ [እግዚአብሔር] ነጎድጓድ መንቀጥቀጣችሁን አቁሙ። ከአሁን በኋላ ለመለኮታዊነት ሳይሆን ለአመክንዮ እውቅና ስጡ። እጅግ የከበረና በንጽህናው ተወዳዳሪ የሌለውን ምስል (እንስትዋን ጣዖት) አበረክትላችኋለሁ፤ ጣዖት ይኑረን ካላችሁ ለእንደዚህ አይነቱ ብቻ መስዋዕት አድርጉ…. ግርማ ሞገስ ባለው በነጻነት ምክር ቤት፣ በአመክንዮ አይነ እርግብ ፊት ውደቁ።” አለ።GCAmh 203.2

    “ፕረዘዳንቱ በደስታ ከተቀበላት በኋላ እንስት ጣዖትዋ በተዋበ ሰረገላ ላይ ተቀምጣ የአምላክን (የእግዚአብሔርን) ቦታ ትወስድ ዘንድ ጥቅጥቅ ባለው ሕዝብ መካከል ወደ ኖትረዳም (Notre Dame) ካቴድራል ተወሰደች። ከዚያም በከፍታ ወዳለው መሰዊያ እንድትወጣ ተደረገች፤ የመላውን ሕዝብ አክብሮት አገኘች።”-Alison, vol. 1, ch. 10።GCAmh 203.3

    ይህ ክስተት ከተፈፀመ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን በአደባባይ ማቃጠል ተጀመረ። “የሙዚየሙ ማሕበረሰብም አመክንዮ ለዘላለም ይኑር (Vive La Raison— Long Live the Reason!) እያለ፣ ‘የሰው ዘር እንዲፈጽመው ያደረጉትን ሞኝነቶች ሁሉ በታላቅ እሳት ያፀዳው’ ብሎ ፕረዘዳንቱ የተናገረለትን፣ ግማሽ አካላቸው የተቃጠሉ፣ የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ጭምር፣ ብዙ መጻሕፍት በረዥም ምሰሶ ላይ በመያዝ ወደ መዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ ገባ።”-Journal of Paris, 1793, No. 318, quoted in Buchez-Roux, Collection of Parliamentary History, vol. 30, ገጽ 200, 201።GCAmh 203.4

    እምነት አልባነት እያጠናቀቀ የነበረውን ሥራ የጀመረው ጳጳሳዊ ሥርዓት ነበር። ፈረንሳይን ወደ ጥፋት እያንደረደሩዋት የነበሩትን የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሐይማኖታዊ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ያደረገው የሮም መርሃ-ግብር ነበር። አንድ ፀኃፊ ስለ አብዮቱ አሰቃቂ ክስተቶች ሲናገር፦ “በእውነቱ ከሆነ ለእነዚያ ከልክ ያለፉ ድርጊቶች ተጠያቂዎቹ ዘውዱና ቤተ-ክህነት ናቸው።” እቅጩን የሆነ ፍርድ ከተሰጠ ደግሞ ተጠያቂዋ ቤተ ክርስቲያን ናት። ተሀድሶው የዘውዱ (የመንግሥት) ጠላት፣ ለሃገሪቱ ሰላምና ስምምነት አደገኛ የሆነ ፀብ የሚያመጣ እንደሆነ አድርጎ የነገሥታትን አዕምሮ የበረዘው ጳጳሳዊው ሥርዓት ነበር። ከመንግሥት ዙፋን የመነጨውን ተወዳዳሪ የሌለውን ጭቆናና አስከፊ ጭካኔ በዚህ ዘዴ ያነሳሳው የሮም ብልሃት ነበር።GCAmh 204.1

    የነፃነት መንፈስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አብሮ የሚሄድ (የተስማማ) ነበር። ወንጌሉ ተቀባይነት ባገኘበት ስፍራ ሁሉ የሰዎች አዕምሮ ይነቃቃ ነበር፤ ጠፍሮ ይዞ ባሪያ አድርጓቸው የኖረውን የድንቁርና፣ የብልግናና የአጉል እምነት ሰንሰለት አውልቀው ይጥሉ ጀመር፤ እንደ ሰው ማሰብና መሥራት ጀመሩ። ነጉሠ ነገሥታት ይህንን ተገንዝበው ከፈላጭ ቆራጭነታቸው የተነሳ ይንቀጠቀጡ ነበር።GCAmh 204.2

    ይህንን የምቀኝነት ፍራቻቸውን ለማቀጣጠል ግን ሮም ቀርፋፋ አልነበረችም። በ1523 ዓ.ም ሊቀ-ጳጳሱ ለፈረንሳዩ እንደራሴ እንዲህ አለው፦ “ይህ እብደት [ፕሮቴስታንትነት] የሚያወድመው ኃይማኖትን ብቻ አይደለም፤ ግዛቶችን፣ ባላባትነትን፣ ሕጎችን፣ ስርዓቶችንና ደረጃዎችን ሁሉ እንጂ።”-G. de Félice, History of the Protestants of France, b. 1, ch. 2, par. 8። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የጳጳሳዊው ልዑክ ንጉሡን ሲያስጠነቅቅ፦ “የንጉሠ ነገሥትነትህን መብቶች እንዳሉ ለማስጠበቅ ከፈለግህ፣ በሥርህ የሚተዳደሩትን ግዛቶች በሰላምና በፀጥታ ይዘህ መቆየት ከፈለግህ፣ የካቶሊክን እምነት በድፍረት መጠበቅ፣ ጠላቶቹንም በክንድህ መደቆስ ይገባሃል” ብሎት ነበር።-D’Aubigné, Hiistory of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 2, ch. 36። የኃይማኖት ምሁራንም የሕዝቡን ፍርሃት በመጠቀም የፕሮቴስታንት አስተምህሮ “ሰዎችን እንግዳና ጅልነት ወደሆነ ነገር የሚገፋፋ፣ ለንጉሡም የተገዥዎቹን ጠንካራ ፍቅር የሚያሳጣ፤ ቤተ ክርስቲያንንና አገርን የሚያፈራርስ” እንደሆነ አድርገው ቅስቀሳ አካሄዱ። እንዲህም በማድረግ ፈረንሳይ ጦርዋን በተሐድሶው ላይ እንድትሰብቅ ሮም ያደረገችው ጥረት ተሳካላት። “በፈረንሳይ፣ የስደት ሰይፍ መጀመሪያ ከሰገባው የተመዘዘው ዙፋኑን ለማስከበር፣ ልዑላንን ለመጠበቅና ሕጉን ለማስቀጠል ነበር።”-Wylie, b. 13, ch. 4።GCAmh 204.3

    ይህ እድለ-ቢስ መርሃ ግብር ወደፊት የሚያስከትለውን ውጤት የምድሪቱ መሪዎች ማየት ተስኖአቸው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የአንድ አገር ብልጽግና የማዕዘን ድንጋይ የሆኑትን ፍትሃዊነትን፣ መጠንን የማወቅን፣ እውነትን፣ አለማዳላትን፣ መልካም የማድረግን መርሆዎች በሰዎች ልብና አዕምሮ ውስጥ ይተክላል። “ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች።” “ዙፋን በጽድቅ ይፀናልና” [ምሳሌ 14÷34፤ 16÷12]። “የጽድቅ ሥራ ሰላም” ውጤቱም “ለዘላለም ፀጥታና መታመን ይሆናል” [ኢሳ 32÷17]። የመለኮትን ሕግ የሚታዘዝ እርሱ በእርግጥም የአገሩን ሕግ ይታዘዛል፤ ያከብራልም። እግዚአብሔርን የሚፈራ እርሱ ፍትሃዊና ተገቢ ተግባራትን ሁሉ የሚፈጽምን ንጉሥ ያከብራል። ሆኖም ደስታ-ቢስዋ ፈረንሳይ መጽሐፍ ቅዱስን ከለከለች፤ ደቀ መዝሙሮቹንም አገደች። ያመኑበትን በአደባባይ ለመናገር ድፍረት የነበራቸው፣ በእውነትም ለመገፋት እምነት የነበራቸው፤ የመርህና የሃቀኝነት ሰዎች፣ በእውቀት ብልጽግናቸውና በስነ-ምግባር ጥንካሬያቸው የታወቁ ሰዎች፣ ምዕተ ዓመት አልፎ ምዕተ ዓመት ሲተካ፣ እነዚህ ሰዎች በመርከቦች ውስጥ ባሪያ ሆነው ሲለፉ፣ በእሳት ሲቃጠሉ፣ በምድር ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች ሲበሰብሱ ለብዙ መቶ ዓመታት ኖረዋል። እልፍ አዕላፋት ከአደጋ ለማምለጥ ተሰደዱ። ይህ ስደት፣ ተሐድሶው ከጀመረ በኋላ ለሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት ቀጠለ።GCAmh 204.4

    “በዚያ ረጅም ዘመን የወንጌሉ ደቀ መዛሙርት የአሳዳጁን የጦፈ ንዴት ፈርተው ሲሸሹ ያልተመለከተ የፈረንሳይ ትውልድ አልነበረም። እነዚህ ስደተኞች የላቁበትን የአዕምሮ ችሎታ፣ ስነ-ጥበብ፣ ትጋትና ሥነ-ሥርዓት ይዘው መጠጊያ ያገኙበትን ምድር ሊያበለጽጉ ተሰደዱ። የተሰደዱበትን አገር ባትረፈረፉት በዚያው መጠን የለቀቁበትን ምድር አራቆቱት። አሁን ተገፍቶ የወጣው ሁሉ በፈረንሳይ ቀርቶ ቢሆን ኖሮ፣ የስደተኞች የኢንዱስትሪ ሙያ ለሶስት መቶ ዓመታት መሬትዋን ቢያሳድግ ኖሮ፣ በእነዚህ ሶስት መቶ ዓመታት ጥበባቸው የምርት ግብዓቱን ቢያሻሽል ኖሮ፣ በእነዚህ ሶስት መቶ ዓመታት ውስጥ የፈጠራ ተሰጥኦአቸውና የማሰብ (የትንተና) ችሎታቸው፣ የጽሁፍ ሥራዎችዋንና ሳይንስዋን ቢያስፋፋ ኖሮ፣ ጠቢብነታቸው ለምክር ቤቶችዋ ምሪት ቢሰጡ፣ ጀግንነታቸው ጦርነትዋን ቢዋጉ፣ ከአድልኦ የፀዳ ማንነታቸው ሕጎችዋን ቢያረቅ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐይማኖታቸው የሰዎችን አዕምሮ ቢያጎለብትና ህሊናቸውን ቢገዛ ኖሮ፣ በዚህ ጊዜ ፈረንሳይን ክብር እንዴት በሞላት ነበር! ለሃገራት ምሳሌ የሆነች፣ እንዴት ያለች የበለፀገች ታላቅና ደስተኛ አገር በሆነች!GCAmh 205.1

    “ሆኖም ጭፍንና የማይቀለበስ ጠባብነት እያንዳንዱን የስነ ምግባር መምህር፣ እያንዳንዱን የሥነ-ሥርዓት ፈር ቀዳጅ፣ እያንዳንዱን እውነተኛ የዙፋን ጠባቂ ከምድርዋ እንዲባረር አደረገ፤ አገራቸውን በምድር ላይ “ዝነኛና ክቡር” ያደርጓት የነበሩትን ሰዎች ከቃጠሎና ከስደት አንዱን ምረጡ አለች፤ በመጨረሻም የአገሪቱ ውድመት እውን ሆነ። ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክሉት ህሊና/አእምሮ አልቀረም፤ ወደ ቃጠሎ የሚጎተት ኃይማኖትም አልነበረም፤ የሚጋዝ ብሔራዊነትም አልተረፈም።” እናም አብዮቱ፣ ከአሰቃቂ ክስተቶቹ ጋር፣ አስከፊው ውጤቱ ሆነ።GCAmh 205.2

    “ከሂውጎኖቶች መኮብለል በኋላ አጠቃላይ ማሽቆልቆል በፈረንሳይ ሰፈነ። በአምራችነት እየበለፀጉ የነበሩ ከተሞች መቆርቆዝ ጀመሩ፤ ብዙ አዝርዕት ማምረት የሚችሉ ለምለም ክፍለ ሃገራት ወደነበሩበት ጥሻነት ተመለሱ፤ ያልተለመደ የእመርታ ጊዜውን የአዕምሮ መደንዘዝና የስነ ምግባር ዝግጠት ተከተለው። ፓሪስ የቆሸ መንደር ሆነች፤ አብዮቱ ሲፈነዳ ከንጉሡ እጅ ምጽዋትን የሚለምኑ ሁለት መቶ ሺህ ያህል ድሆች እንደነበሩ ይገመታል። እየበሰበሰች በነበረችው አገር እየበለፀጉ የነበሩት ጀሲውይቶች ብቻ ነበሩ፤ አሰቃቂ የሆነ አምባገነናዊ አስተዳደርም በአብያተ ክርስቲያናት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በወህኒ ቤቶችና በመርከብ ጓዳዎች ላይ መስርተው ነበር።”GCAmh 205.3

    የቤተ ክህነት መሪዎችን፣ የንጉሡን እንዲሁም የሕግ አውጪዎችን ብቃት በመገዳደር ግራ ላጋቧቸው፣ በስተመጨረሻም አገሪቱን ወደ ብጥብጥና ውድመት ለመሩት ፖለቲካዊና ማህበራዊ የፈረንሳይ ችግሮች ወንጌሉ መፍትሄ ያመጣ ነበር። ነገር ግን በሮም አገዛዝ ስር የነበሩት ሕዝቦች የአዳኙን የተቀደሱ ትምህርቶች፣ ራስን መስዋዕት የማድረግና ከራስ ወዳድነት የራቀ ፍቅር፣ ጠፍተውባቸው ነበር። ለሌሎች መልካም ለማድረግ ሲባል ራስን ከመካድ ልምምድ እንዲርቁ ተመርተዋል። ሃብታሙ ድሃውን ከመጨቆን ይታቀብ ዘንድ የሚገስጽ፣ ድሃውም ከባርነትና ከማሽቆልቆል ይተርፍ ዘንድ እርዳታ የሚለግስ አልነበረም። የሃብታሞችና የጉልበተኞች ራስ ወዳድነት የበለጠ ግልጽ እየሆነና ጨቋኝነታቸውም እየበዛ መጣ። ለምዕተ ዓመታት የቀጠለው የልዑላን ስስትና አባካኝነት፣ ጪሰኛውን ወደሚደቁስ ገንዘብን በኃይልና በማስፈራራት ወደመዝረፍ ተግባር አመራ። ባለፀጋው በድኃው ላይ በደል ፈፀመ፤ ድኃውም ሃብታሙን ጠላው።GCAmh 206.1

    በብዙ ክፍለ ሃገራት የነበሩ ዕርስቶች በልዑላን የተያዙ ሆነው፤ የሰራተኛው መደብም ተከራይ ብቻ ነበር፤ እነዚህ [ጭሰኞች] በባላባቱ በጎ ፈቃድ የሚኖሩ፣ አግባብ ለሌላቸው ከልክ በላይ ለሆኑ ጥያቄዎቻቸውም እሺ እንዲሉ የሚገደዱ ነበሩ። መንግሥትንና ቤተ ክህነትን ሁለቱንም የመርዳት ሸክም፣ በመንግሥት ባለስልጣናትና በካህናት አማካኝነት ግብር በሚጣልበት የመካከለኛውና የታችኛው መደብ ላይ የተወዘፈ ነበር። “የልዑላን ቅንጦት ጠቅላይ ሕግ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ ገበሬዎችና ጪሰኞች ቢራቡ ጪቋኞቻቸው ግድ የሚሰጣቸው አልነበሩም…. የባላባቱን ፍላጎት ሳይጠይቁ ሰዎች ወለም ዘለም ማለት አይችሉም ነበር። የእርሻ ሰራተኞች ሕይወት በማያቋርጥ ሥራና በማያባራ ስቃይ የተሞላ ነበር፤ ቅሬታቸው፣ ቅሬታ ማቅረብ ከደፈሩ ማለት ነው፣ እንደ ባለጌ ንቀት ይታይ ነበር። ፍርድ ቤቶች ሁሌም ባላባትን ደግፈው፣ ጭሰኛውን በድለው ይፈርዱ ነበር፤ ዳኞች ጉቦ በመቀበል የታወቁ ነበሩ፤ ያለምክንያት በድንገት የሚለዋወጠው የገዥው መደብ ባህርይ፣ በሁሉም ሥፍራ ተቀባይነት ባገኘው የተበላሸ መዋቅር ምክንያት፣ የሕግ ድጋፍ ነበረው። በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ከምስኪኑ ዘንድ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ግማሹ እንኳ ወደ መንግሥት ወይም ወደ ቤተ ክህነት ግምጃ ቤት አይገባም ነበር። የቀረው ገንዘብ ራስን ለማርካት በሚደረግ ቅጥ ያጣ ብክነት ይጠፋ ነበር። ከዚያም የሚገዟቸውን ወገኖቻቸውን ለድህነት የዳረጉ ሰዎች ከግብር ነጻ ሲሆኑ፤ የሁሉንም የመንግሥት የቅጥር ስፍራዎች የመያዝ የሕግ ወይም የተለምዶ ድጋፍ ነበራቸው። እነዚህ የታደሉ መደቦች ቁጥራቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ የነበረ ሲሆን የእነርሱን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለተስፋ-ቢስና የተዋረደ ኑሮ ተዳርገው ነበር።GCAmh 206.2

    ቤተ መንግሥቱ ለቅንጦትና ለብክነት ተላልፎ የተሰጠ ነበር፤ በሕዝቡና በገዥዎች መካከል መተማመን አልነበረም። መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ በማታለልና በራስ ወዳድነት የተለወሱ እንደሆኑ ያህል ጥርጣሬ ሰፈነ። አብዮቱ ከመጀመሩ በፊት ከሃምሳ አመት በላይ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ሉይስ 15ኛ፣ በእንደዚያ ያለ ክፉ ዘመን እንኳ ሰነፍ፣ ፍሬ-ቢስ፣ ፍትወተኛ ንጉሥ በመሆን የታወቀ ነበር። ክፋት በተሞላበት ጨካኝ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፣ ዝቅተኛ መደብና ምስኪን ድኃ ሕዝብ ባለበት፣ መንግሥትም በገንዘብ ችግር ውስጥ ሆኖ፣ ሕዝቡም በንዴት ገንፍሎ፣ እያንዣበበ ያለ ድንገተኛ አሰቃቂ ብጥብጥ ሊከሰት እንደሚችል ለመገመት የነብይ አይን አያስፈልግም ነበር። ማስጠንቀቂያ ለሚነግሩት አማካሪዎቹ ንጉሡ እንዲህ ብሎ የመመለስ ልማድ ነበረው፦ “እኔ በሕይወት መኖር እስከምችልበት ጊዜ ድረስ ነገሮች ባሉበት እንዲቀጥሉ ለማድረግ ሞክሩ፤ ከሞትሁ በኋላ የሆነው ይሁን።” የለውጥ (የማሻሻያ) አስፈላጊነት ግፊቱ ከንቱ ድካም ነበር። መቅሰፍቶቹን አይቶአቸዋል፣ ሆኖም የመጋፈጥ ወኔም ሆነ ጉልበት አልነበረውም። ፈረንሳይን እየጠበቃት የነበረው ጥፋት ከእርሱ የስንፍናና የራስ ወዳድነት ምላሽ በተሻለ ሊገለጽ አይችልም ነበር - “ጎርፉ ከእኔ በኋላ!”GCAmh 206.3

    የነገሥታትንና የገዥ መደቦችን ቅናት በመጠቀም፣ ሕዝቡን ጠፍረው ይይዙ ዘንድ ተጽዕኖ የምታደርገው ሮም፣ በዚህ ድርጊት መንግሥት እንደሚዳከም ስታውቅ በራስዋ ባርነት ስር ሕዝቡንና መሪዎቹን ጨምድዳ ታኖር ዘንድ እቅድዋ ነበር። አርቆ አሳቢ በሆነ መርሐ ግብር ሰዎችን በተዋጣለት ሁኔታ በባርነት ስር ለማድረግ፣ ሰንሰለቱ በነፍሳቸው መጠምጠም እንዳለበት ያስተዋለች ነበረች፤ ከባርነት ቀንበር ማምለጥ የማይችሉ ይሆኑ ዘንድ እርግጠኛው መንገድ ለነፃነት ብቁ መሆን እንዳይችሉ ማድረግ ነበር። ከዘረጋችው ሥርዓት የተነሳ ከሚደርስባቸው አካላዊ ስቃይ ይልቅ አንድ ሺህ እጥፍ የበለጠ አሰቃቂ የነበረው የሥነ ምግባር ማሽቆልቆሉ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ተነፍገው፣ ለጥላቻና ለራስ ወዳድነት ትምህርት ተትተው፣ በድንቁርናና በአጉል እምነት ተጀቡነው፣ በብልግና ውስጥ ሰጥመው፣ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ማስተዳደር ወደማይችሉበት ደረጃ እንዲወርዱ ተደርገው ነበር።GCAmh 207.1

    የዚህ ሁሉ ውጤት ግን ሮም ከአቀደችው እጅግ የተለየ ነበር። ተግባርዋ፣ ሕዝቡ ቀኖናዎችዋን በጭፍን እንዲከተል በማድረግ ፈንታ፣ እምነት የለሽና አብዮተኛ እንዲሆን አደረገው። ሮማዊነት የቀሳውስት የራሳቸው ተግባር እንደሆነ አድርገው ጠሉት። የቤተ ክህነት መሪዎች የጨቋኞች ፓርቲ እንደሆኑ አድርገው ተመለከቷቸው። የሚያውቁት ብቸኛ አምላክ የሮም አምላክን ነበር፤ አስተምህሮዎችዋም ብቸኛ ሐይማኖታቸው ነበር። ስስትዋና ጭካኔዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሚመጣ ትክክለኛው ውጤት እንደሆነ በመረዳት ፈጽመው የማይፈልጉት ሆኑ።GCAmh 207.2

    ሮም፣ የእግዚአብሔር ያልሆነውን ባህርይ በሃሰት በመወከልዋና መጠይቁንም በማጣመምዋ አሁን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ የፃፈውን[ጌታን] አንቀበልም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠይቀው መስፈርት እንደሆነ አስመስላ በቀኖናዎችዋ ላይ ጭፍን እምነትን ትሻ ነበር። ለዚህ አፀፋ ቮልቴር እና ግብረ አበሮቹ የእግዚአብሔርን ቃል ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን ትተው፣ የከሃዲነትን መርዝ በሁሉም ስፍራ አሰራጩ። ሮም በብረት ተረከዝዋ ሕዝቡን ጨፍልቃ ነበር፤ አሁን ሕዝቡ ቆርቁዞና በጭካኔ በልዞ ከእርስዋ ፈላጭ ቆራጭነት በፍጥነት ለመላቀቅ ሁሉንም ገደብ አሸቀንጥሮ ጣለ። ለረዥም ጊዜ አክብሮት ሲሰጡት በነበረው አንጸባራቂ መታለል ተበሳጭተው እውነትንም ሐሰትንም በአንድ ላይ አሻፈረኝ አሉ፤ ፈቃድን (license) በስህተት እንደ ነፃነት (liberty) ቆጥረው፣ የብልግና ባሪያዎች በምናባዊ ነፃነታቸው (freedom) ጨፈሩ።GCAmh 207.3

    አብዮቱ ሲጀምር በንጉሡ ፈቃድ የልዑላንና የቤተክህነት መሪዎች አንድ ላይ ሆነው ካላቸው ተወካዮች የበለጠ ውክልና ሕዝቡ እንዲኖረው ተደረገ። በመሆኑም የኃይል ሚዛኑ በእጃቸው ገባ፤ በጥበብና በመጠን ይጠቀሙበት ዘንድ ግን የተዘጋጁ አልነበሩም። የተሰቃዩባቸውን ስህተቶች ለማረም በመጣደፍ፣ ማህበረሰብን እንደገና የማደራጀት ሥራ ለማካሄድ ወሰኑ። ለረጅም ጊዜ በአእምሮው ሰርፆ በኖረው ክፉና መራር ተግባር የተቆጣው ሰፊው ሕዝብ ይሸከመው ዘንድ አልችል ያለውን ስቃይ ፈጽሞ ለመቀየር፣ የእንግልቱ ደራሲ ናቸው ብሎ የፈረጃቸውን ለመበቀል ቆርጦ ተነሳ። የተጨቆነው ወገን በአምባገነናዊ ሥርዓት ዘመን የተማረውን ተግባራዊ በማድረግ ሲጨቁነው የነበረውን ወገን ጨቋኝ ሆነ።GCAmh 207.4

    ያልታደለችው ፈረንሳይ የዘራችውን ዘር በደም ለውሳ አጨደች። ለማያፈናፍን የሮም ግዛት ራስዋን መስጠትዋ አሰቃቂ የሆኑ ውጤቶችን አተረፈ። በሮማዊነት ተጽዕኖ ተገፍታ፣ በተሐድሶው መባቻ የመጀመሪያው የእሳት ማቃጠያ ባቋቋመችበት በዚያው ስፍራ፣ አብዮቱ የመጀመሪያውን የአንገት መቁረጫ መሳሪያ አቋቋመ። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፕሮቴስታንት እምነት የመጀመሪያ ሰማዕታት በተቃጠሉበት በዚያው ቦታ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንገታቸው ተቀላ። ፈውስ ያመጣላት የነበረውን ወንጌል አሻፈረኝ ያለችው ፈረንሳይ ለክህደትና ለውድመት በርዋን ወለል አድርጋ ከፍታለች። ገደብ የሚያበጁት የእግዚአብሔር ሕግጋት ወደ ጎን ሲገፈተሩ የፍጡራንን የነደደ የፍላጎት ማዕበል ያስቆም ዘንድ የሰው ሕግ ብቁ እንዳልሆነ ተረጋገጠ። ሃገሪቷ በአመጽና በትርምስ ተናወጠች። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጀመረው ጦርነት በዓለም ታሪክ “የሽብር ግዛት” — [“The Reign of Terror”] በመባል የሚታወቀውን ዘመን መርቆ ከፈተ። ሰላምና ደስታ ከሰዎች ልብና መጠለያ ተጠራርገው ተባረሩ። ዛሬ ድል የተቀዳጀው፣ ነገ ይጠረጠርና ይኮነን ነበር። ብጥብጥና ፍትወት ያለተቀናቃኝ ሰፈነ።GCAmh 208.1

    ንጉሡ፣ የቤተ ክህነት መሪዎችና ልዑላን በስሜት ለተዋጠና በንዴት ለነደደ ሕዝብ የጭካኔ ተግባር እጅ ለመስጠት ተገደዱ። የንጉሡ መገደል የፈየደው ነገር ቢኖር የበቀል ጥማቸውን የበለጠ ማቀጣጠል ነበር። መሞቱን ያወጁት እነርሱ ራሳቸው ወደ መታረጃው ተከተሉት። አብዮቱን ይቃወማሉ ተብለው የተጠረጠሩ በአጠቃላይ እንዲታረዱ ተወሰነ። ወሂኒ ቤቶች ተጣበቡ፤ በአንድ ጊዜ ከሁለት መቶ ሺህ እስረኞች በላይ ተይዘው ነበር። የግዛቱ ከተሞች ሁሉ በሚያስደነግጡ ትዕይንቶች ተሞልተው ነበር። አንድ አብዮታዊ አንጃ በሌላኛው አብዮተኛ ላይ እየተነሳ ፈረንሳይ በቁጣ የነደደ ስሜታቸው በሚቆጣጠራቸው፣ በሚቀናቀኑ ሕዝቦች የተሞላች ሰፊ መስክ ሆነች። በፓሪስ አንድ ብጥብጥ ሌላውን እየተከተለ ሕዝቡ የጋራ ውድመት በሚያመጡ ነገሮች ላይ የሚሰሩ በሚመስሉ በተለያዩ አንጃዎች መሃል ተከፈለ። ከጠቅላላው ስቃይ ላይ ለመጨመር፣ እረጅምና ከባድ ውድመት ባመጣ ከታላላቅ የአውሮፓ አገራት ጋር በተደረገ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ሆነች። “ሃገሪቱ ከኪሳራ አፋፍ ላይ ነበረች፤ ሰራዊቱ ያልተከፈለው ደመወዝ እንዲከፈለው እየጮኸ ነበር፤ ክፍለ ሃገራቱ እየዞሩ በሚዘርፉ ቀማኞች ወደሙ፤ በግርግርና ባልተገደበ ባህርይ ምክንያት ስልጣኔ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ ምንም አልቀረውም ነበር።”GCAmh 208.2

    ሮም በትጋት ያስተማረችውን የጭካኔና የስቅይት ትምህርት ሕዝቡ ከበቂ በላይ ተምሯል። በመጨረሻ የበቀል ቀን መጥቷል። የየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ ወህኒ ቤት የወረዱት፣ ወደማቃጠያ ስፍራ የተጎተቱት አሁን አልነበረም። ከረጅም ዘመን በፊት አልቀዋል፤ ያለዚያም ተሰደዋል። ለነገ የማትለዋ ሮም በደም በመጫዎት ደስ ይሰኙ ዘንድ ያሰለጠነቻቸውን ገዳይ ኃይላት አሁን አወቀች። “የፈረንሳይ ቤተ ክህነት መሪዎች ለረጅም ዘመናት ያንፀባረቁት (በተግባር ያሳዩት) የማሳደድ ምሳሌነት ዛሬ በሚስተዋል ብርታት ወደ እነርሱ ተገለበጠ። የማረጃው መድረክ በቀሳውስት ደም ደመቀ። በአንድ ወቅት በሂውጉኖቶች ተጨናንቀው የነበሩ የመርከብ ጓዳዎችና ወህኒ ቤቶች አሁን እነርሱን ያሳድዱ በነበሩ ተሞሉ። የሮም ካቶሊክ ካህናት፣ ከመቀመጫ ወንበሩ ጋር በሰንሰለት ታስረው፣ በመቅዘፍ ሥራ ሲማስኑ በመዋል፣ ቤተ ክርስቲያናቸው በገራገር መናፍቃን ላይ እንዳሻት ስትፈጽመው የኖረችውን ስቃይ በሙሉ ቀመሱት። ”GCAmh 208.3

    “ከዚያም በጭካኔያቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው ውሳኔዎች፤ ፈጽሞ አረመኔ በሆኑ ልዩ ፍርድ ቤቶች የሚተገበሩበት፤ ለሞት የሚያበቃ ወንጀል የመሥራት አደጋ ሳይጋረጥበት….አንድ ሰው ጎረቤቶቹን ሰላም የማይልበት ወይም የማይፀልይበት፣ ጆሮ ጠቢዎች በእያንዳንዱ መታጠፊያ ያደፈጡበት፤ አንገት የመቅያው ስፍራ (የማረጃው ቦታ) በየጠዋቱ በረጅምና በከባድ ሥራ የተጠመደበት፤ እስር ቤቶች ባሪያዎችን እንደጫነች መርከብ የተጨናነቁበት፤ አሸንዳዎች በደም አረፋ እየተኩረፈረፉ ወደ ሰይን ወንዝ የሚጎርፉበት ቀን መጣ…. የእለቱ ተጠቂዎች በሰረገላ ሞልተው በፓሪስ ጎዳናዎች ወደ መጥፊያቸው ሲያመሩ ሳለ የበላይ ኮሚቴው ወደየዲፓርትመንቱ የላካቸው አስተዳደሮች፣ በመዲናዋ እንኳ ታይቶ በማያውቅ ከመጠን ያለፈ ጭካኔ ይቦርቁ ነበር። ከፍና ዝቅ እያለ የሚቆርጠው የመሳሪያው ካሪያ ለማረድ ሥራቸው እንደሚፈልጉት አልፈጠነላቸውም። ተይዘው ረጅም ወረፋ የሚጠብቁ ታራጆች ብዙ ድቡልቡል ጥይቶች በአንድ ጊዜ በሚተፋው መድፍ በአንድነት ተረፈረፉ። ጀልባዎች ተጠቅጥቀው ተጭነው ከሥራቸው ቀዳዳ ተበጀላቸው። የሊዮንስ ከተማ ወደ ምድርበዳነት ተቀየረች። በአራስ ከተማ እንደ ምሕረት የተቆጠረው ጭካኔ የተሞላበት ፈጣን ህልፈት እንኳ ለእስረኞች ተከልክሎ ነበር። ከሳውሙር ተነስቶ ወደ ሃይቁ የሚወርደውን የሎይር ወንዝ ተከትሎ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ተጠፍረው የወደቁ ራቁት ሬሳዎችን የሚበሉ አያሌ የቁራና የጭልፊት መንጋዎች ይታዩ ነበር። ለፆታም ሆነ ለእድሜ የተንፀባረቀ አንዳች ምሕረት አልነበረም። በዚያ አስፀያፊ መንግሥት የተጨፈጨፉ በአሥራ ሰባት እድሜ የነበሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቁጥር በመቶዎች እንደሚቆጠር ይታመናል። ህፃናት [ከእናታቸው] ጡት ተመንጭቀው በ“ጃኮቢን ሹማምንት መካከል ከአንድ የመውጊያ ጦር ወደሌላው ይወረወሩ ነበር።” በአሥር ዓመት ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አለቁ።GCAmh 209.1

    ይህ ሁሉ እንደ ሰይጣን ሃሳብ ነበረ፤ ይህንን ለማሳካት ነበር ለዘመናት ሲሰራ የነበረው። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ መርሐ ግብሩ የማታለል መርሐ ግብር ነው። ጽኑ ዓላማው ሃዘንና ጉስቁልናን በሰዎች ላይ በማምጣት፣ የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራ መልክ በማሳጣትና በመበከል፣ የመለኮትን የችሮታና የፍቅር እቅድ በማወክ፣ በሰማይ ሀዘንን ማምጣት ነው። ከዚያም በማታለል ጥበቡ የሰዎችን አዕምሮ በማወር፣ ይህ ሁሉ ስቃይ የፈጣሪ እቅድ ውጤት እንደሆነ አድርጎ በማሳየት የራሱን ክፉ ተግባር የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ ቆጥረው ሰዎች አምላክን እንዲኮንኑ ይመራቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በጨካኝ ኃይሉ የቆረቆዙና የበለዙ ሁሉ ነፃነት ሲቀዳጁ፣ ከልክ እንዲያልፉና ግፍ እንዲፈጽሙ ይጎሰጉሳቸዋል። ከዚያም ይህን ልጓም የሌለውን ልቅ ባህርይ፣ አምባገነኖችና ጨቋኞች፣ ነጻነት የሚያመጣው መዘዝ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ይጠቀሙበታል።GCAmh 209.2

    በአንድ ካባ ሥር ስህተት እንዳለ ሲታወቅ፣ ሰይጣን በሌላ ሽፋን ይደብቀውና እልፍ አዕላፋት ልክ እንደመጀመሪያው አድርገው እንዲቀበሉት ያደርጋል። ሮማዊነት ማታለያ እንደሆነ ሰዎች ሲደርሱበትና በዚህ ወኪሉ አማካኝነት የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲጥሱ ማድረግ ሲሳነው፣ ሁሉም ኃይማኖቶች ማጭበርበሪያ እንደሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስም ተረት ተረት እንደሆነ እንዲቆጥሩት አበረታታቸው፤ እነርሱም መለኮታዊ ሕግጋትን ወደ ጎን ገፍትረው ለገደብ-የለሽ ኃጢአት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ።GCAmh 209.3

    ለፈረንሳይ ነዋሪዎች እንደዚህ አይነቱን ጥልቅ ሃዘን ያስከተለው አደገኛ ስህተት - እውነተኛ ነፃነት የሚገኘው በእግዚአብሔር ሕግ ገደብ ውስጥ ነው — የሚለውን አንድ ታላቅ እውነት ገሸሽ ማለታው ነው።“ትዕዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባህር ሞገድ በሆነ ነበር።” “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር። የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ስጋት ያርፋል።” [ኢሳ 48÷18፣22፤ ምሳሌ 1÷33]።GCAmh 210.1

    እምነት የለሾች፣ እግዚአብሔር የለም ባዮችና ከኃዲዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ይቃወማሉ፤ ያወግዛሉም፤ የተጽዕኖዎቻቸው ውጤት የሚያረጋግጠው ሃቅ ግን የሰው ህልውና (ደህንነት) መለኮታዊ ደንቦችን ከመታዘዝ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ነው። ትምህርቱን ከእግዚአብሔር መጽሐፍ የማያነቡ እነርሱ ከዓለም ሕዝቦች ታሪክ ያነቡት ዘንድ ተጋብዘዋል።GCAmh 210.2

    በሮም ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ሰይጣን ሰዎችን ወደ አለመታዘዝ ሲመራቸው ውክልናው ከመደበቁ የሥራውም ውጫዊ መልክ ከመቀየሩ የተነሳ የመጣው መቆርቆዝና ስቃይ የመተላለፍ (የአመጽ) ፍሬ ተደርጎ እንዳይታይ አድርጓል። አስካሁን ደረስ፣ አላማዎቹ ሁሉ ወደ ሙሉ ውጤታማነት እንዳይደረሱ፣ በእግዚአብሔር መንፈስ አሰራር አማካኝነት ኃይሉ ሲከለከል ቆይቷል። የነገሩን መንስኤ ሰዎች አልደረሱበትም፤ የስቃያቸውንም ምንጭ አላገኙትም። በአብዮቱ ጊዜ ግን በብሔራዊው መማክርት የእግዚአብሔር ሕግ በግልጽ ወደ ጎን ተገፈተረ። ከዚያ በኋላ በመጣው በፍርሃት የግዛት ዘመንም የመንስኤና ውጤት አሰራር በሁሉም ዘንድ ሊታይ ችሏል።GCAmh 210.3

    ፈረንሳይ በአደባባይ መጽሐፍ ቅዱስን ስትከለክል፣ የእግዚአብሔር ሕግ ከሚያስቀምጣቸው ገደቦች ነጻ የሆነ መንግሥት መመስረት — የረጅም ዘመን ፍላጎታቸው የነበረ እርጉም ሰዎች የጽልመት መናፍስት እቅዳቸው ተሳክቶ በማየታቸው ፈነደቁ። ክፉ ሥራን በመቃወም መተግበር የነበረበት ሕግ በፍጥነት ሥራ ላይ ባለመዋሉ (በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ ባለመፍረዱ) የሰው ልጆች ልብ “ክፉን ለመሥራት ጠነከረ።” [መክ 8÷11-13]። ፍትሃዊና ጻድቅ የሆነውን ሕግ መጣስ ግን መጨረሻው ስቃይና ውድመት መሆኑ አይቀሬ ነው። የሥራቸው ውጤት በአንድ ጊዜ ባይጎበኝም የሰዎች ኃጢአት ግን ያለጥርጥር ጥፋታቸውን እያከናወነላቸው ነበር። ለምዕተ ዓመታት የዘለቀው ክህደትና ወንጀል ለቅጣት ቀን ቁጣ እያጠራቀመ ነበር። ጽዋቸው ሲሞላ፣ በእግዚአብሔር ላይ የሚያላግጡ፣ የመለኮት ትእግስት መሟጠጥ ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ የደረሱበት ጊዜው ካለቀ በኋላ ነበር። በሰይጣን ጨካኝ ኃይል ላይ ክትር የሚያበጀው፣ የሚገታው የእግዚአብሔር መንፈስ በአብዛኛው በመነሳቱ ብቸኛ ደስታው የሰዎች ጉስቁልና የሆነው እርሱ ፈቃዱን እንዲያደርግ ተፈቀደለት። ከአሰቃቂነቱ የተነሳ ብዕር ወረቀት ላይ ያሰፍረው ዘንድ በሚከብድ ስቃይ ምድሪቱ እስክትሞላ ድረስ የአመጽን አገልግሎት የመረጡ እነርሱ መከሩን እንዲሰበስቡ ተተው። ከጠፉ ክፍለ ሃገራትና ከወደሙ ከተማዎች የሰቆቃ ዋይታ፣ የመራር ስቃይ ጩኸት ይሰማ ነበር። የመሬት መንቀጥቀጥ የመታት ያህል ፈረንሳይ ተናወጠች። ኃይማኖት፣ ሕግ፣ ማህበራዊ ሥርዓት፣ ቤተሰብ፣ አገርና ቤተ ክርስቲያን፣ ሁሉም በእግዚአብሔር ሕግ ላይ በተነሳው፣ አምላክን በሚያዋርድ እጅ ተመቱ። በትክክልም ጠቢቡ ሰው ተናግሮአል፦ “ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሰራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፣ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት ደህንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤ ለኃጥእ ግን ደህንነት የለውም” [መክ 8÷11-13]። “እውቀትን ጠልተዋልና፣ እግዚአብሔርንም መፍራት አልመረጡምና“፤ “ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ ከራሳቸውም ምክር ይጠግባሉ” [ምሳሌ 1÷29፣31]።GCAmh 210.4

    “ከጥልቁ በሚወጣው” የስድብ ኃይል የታረዱት ታማኝ የእግዚአብሔር ምስክሮች ዝም ብለው ለብዙ ጊዜ የሚቆዩ አልነበሩም። “ከሶስቱ ቀን ተኩል በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው” [ራዕይ 11÷11]። መጽሐፍ ቅዱስን የሚከለክለው አዋጅ በፈረንሳይ ጉባኤ የተላለፈው በ1793 ዓ.ም. ነበር። ከሶስት ዓመት ተኩል በኋላ አዋጁን የሚሽር ለመጽሐፍ ቅዱስም ፈቃድ የሚሰጥ ውሳኔ ያው ጉባኤ አስተላለፈ። ቅዱሳኑን መጻሕፍት አሻፈረኝ ከማለት የሚመጣውን የኃጢአት ግዝፈት ዓለም በታላቅ ድንጋጤ ተመለከተው፤ የደግነትና የግብረ ገባዊነት መሰረት በሆነው ቃሉና በእግዚአብሔር ማመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እውቅና ሰጡ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የተገዳደርከው የሰደብከውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግህበት አይንህንስ ወደ ላይ ያነሳህበት ማን ነው? በእሥራኤል ቅዱስ ላይ ነው።“[ኢሳ 37÷23]። “ስለዚህ እነሆ አስታውቃቸዋለሁ፤ በዚህች ጊዜ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደሆነ ያውቃሉ።” [ኤር 16÷21]።GCAmh 211.1

    ሁለቱን ምስክሮች በተመለከተ ነብዩ በመቀጠል ሲናገር፣ “በሰማይም ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምጽ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ ደመና ወጡ” [ራዕይ 11÷12]። ፈረንሳይ በእግዚአብሔር ምስክሮች ላይ ጦርነት ስላወጀች፣ [ምስክሮቹ] ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ከፍ ከፍ ብለዋል። በ1804 ዓ.ም የብሪታንያና የውጪ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር [British & Foreign Bible Society] ተደራጀ። ይህንን ፈለግ ተከትለው፣ አያሌ ቅርንጫፍ ያላቸው ተቋማት በመላው አውሮፓ ተቋቋሙ። በ1816 ዓ.ም የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ተቋቋመ። የእንግሊዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በተቋቋመበት ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሃምሳ ቋንቋዎች ታትሞ ተሰራጭቶ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሁለት መቶ በላይ ወደሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ማህበራት ጥረት ከ1804 ዓ.ም ጀምሮ ከ187,000,000 በላይ ቅጅዎች ተሰራጭተዋል።GCAmh 211.2

    ከዚህ ዘመን ሃምሳ ዓመት ቀደም ብሎ በ1792 ዓ.ም ለውጪ አገር ሚሲዮናዊ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ አልነበረም። አዲስ ማህበራትም አልተቋቋሙም ነበር። እምነት በሌላቸው ስፍራዎች ክርስትና እንዲስፋፋ የሚጥሩ አብያተ ክርስቲያናትም አልነበሩም ማለት ይቀላል። ነገር ግን ወደ አሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ታላቅ ለውጥ ተከሰተ። በውስጣዊ ስሜት ሳይሆን በአመክንዮ ብቻ የተመረኮዘ እምነት ባመጣው ውጤት ሰዎች ሊረኩ ተሳናቸው፤ መለኮታዊ መገለጥና በተግባር የሚገለጥ ኃይማኖት አስፈላጊነቱ ገባቸው። ለሥራው ራሱን አሳልፎ የሰጠው፣ በ1793 ዓ.ም የመጀመሪያው ወደ ህንድ የሄደ እንግሊዛዊ በመሆን ኬር በእንግሊዝ የነበረውን ሚስዮናዊ ጥረት በአዲስ መልክ አቀጣጠለው። ከሃያ አመት በኋላ በተማሪዎች ጠንካራ ፍላጎት አማካኝነት — አዶኒራም ጀድሰንን ጨምሮ፣ የአሜሪካ የውጪ አገራት ሚስዮናዊ ሥራ ቦርድ ተመሠረተ። በዚህም ጥላ ስር ጃድሰን ሚስዮናዊ ሆኖ ከአሜሪካ ወደ በርማ [አሁን ሜይንማር] ወደምትባል አገር ሄደ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የውጪ አገራት ምስዮናዊ ሥራ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ እድገት እየተቀዳጀ ሄደ።GCAmh 211.3

    በህትመት በኩል የተመዘገበው እመርታ መጽሐፍ ቅዱስን በማሰራጨት ረገድ አጋዥ ኃይል ሆኖአል። በተለያዩ አገራት መካከል ግንኙነት ይደረግ ዘንድ የሚያስችሉ መሳሪያዎች መጨመራቸው፣ እንደ አጉል ጥላቻና ብሔራዊ ግላዊነት የመሳሰሉ ጥንታዊ መሰናክሎች መገርሰሳቸው እንዲሁም የሮም ሊቀ ጳጳስ መንግሥታዊ ስልጣን መነጠቁ የእግዚአብሔር ቃል ይገባ ዘንድ በር ከፈተ።GCAmh 212.1

    ኃይማኖት የለሹ ቮልቴር በአንድ ወቅት በኩራት “የክርስትናን እምነት የጀመሩት አሥራ ሁለት ሰዎች ናቸው እያሉ ሰዎች ሲያወሩ መስማት ደከመኝ። ለመገልበጥ ግን አንድ ሰው እንደሚበቃ አረጋግጥላችኋለሁ” ብሎ ተናግሮ ነበር። እርሱ ከሞተ እነሆ አንድ መቶ ዓመት [ይህ መጽሐፍ ከተጻፈ ከሁለት መቶ ዓመት] በላይ አለፈ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠራውን ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተቀላቅለውታል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሊደመሰስ አልቻለም፤ በቮልቴር ጊዜ ቁጥሩ መቶ ያህል ነበር፤ አሁን (በእርስዋ ዘመን) አሥር ሺህ ነው፤ አዎ መቶ ሺህ የእግዚአብሔር መጽሐፍ አለ። የክርስትና ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ በአንድ ቀዳሚ ተሐድሶ አራማጅ ቃል ሲገለጽ፣ “መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መዶሻዎችን የጨረሰ መስፍ (ባለጅ የጋለ ብረት ለመቀጥቀጥ ከስር አድርጎ የሚጠቀምበት) ነው።” የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር፦ “በአንቺ ላይ የተሰራ መሳሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሳብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጅበታለሽ።” ይላል [ኢሳ 54÷17]።GCAmh 212.2

    “የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች።”፤ “ትዕዛዙ ሁሉ የታመነ ነው፤ ለዘላለምም የፀና ነው፤ በእውነትና በቅንም የተሰራ ነው።” [ኢሳ 40÷8፤ መዝ 111÷7፣8]። በሰው ስልጣን ላይ ተመርኩዞ የተሰራ ሁሉ ፈራሽ ነው፤ በማይለወጠው በእግዚአብሔር ቃል ቋጥኝ ላይ የተመሠረተው ግን ለዘላለም ፀንቶ ይኖራል።GCAmh 212.3