Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፳፩—ተቀባይነት ያጣው ማስጠንቀቂያ

    የዳግም ምፅዓቱን አስተምህሮ በመስበክ ዊሊያም ሚለርና ግብረ አበሮቹ የለፉበት ብቸኛው አላማ ለፍርዱ ይዘጋጁ ዘንድ ሰዎችን መቀስቀስ ነበር። የኃይማኖት ሰዎች ነን ባዮች ለቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ ተስፋና ለሚያስፈልጋቸው ጠለቅ ያለ የክርስቲያንነት ልምምድ እንዲነቃቁ መሻታቸው ነበር፤ ያልተለወጡትም ተነሳስተው አፋጣኝ ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይለፉ ነበር። “ሰዎች ወደ አንድ የኃይማኖት ልዩ ወገን ወይም ቡድን እንዲቀየሩ በፍፁም አልሞከሩም። በመሆኑም በአደረጃጀታቸውና በስርዓታቸው ጣልቃ ሳይገቡ በሁሉም የኃይማኖት ወገኖችና ቡድኖች መካከል ለፉ።”GCAmh 273.1

    “በሁሉም ጥረቶቼ” አለ ሚለር “አሁን ካሉት ኃይማኖቶች የተነጠለ ሌላ ኃይማኖት የመመስረት ወይም አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የመጉዳት ፍላጎትም ሆነ ሐሳብ ኖሮኝ አያውቅም፤ ሐሳቤ ሁሉንም መጥቀም ነበር። ሁሉም ክርስቲያኖች በክርስቶስ መምጣት ደስ ይሰኛሉ፤ እኔ እንደሚታየኝ ያላዩ ሰዎች ደግሞ አስተምህሮውን የተቀበሉትን ከቀድሞው ያነሰ ፍቅር ያሳዩአቸዋል ብዬ ስላላሰብኩ፣ ከሌላው የተነጠለ ስብሰባ ሊያስፈልግ ይችላል ብዬ በውስጤ ፀንሸው በጭራሽ አላውቅም። አጠቃላይ አላማዬ የነበረው ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር ማምጣት፣ ስለሚመጣው ፍርድ ዓለምን ማሳወቅ፣ ባልንጀሮቼ እግዚአብሔርን በሰላም ለመገናኘት የሚያስችላቸው የልብ መዘጋጀት እንዲያደርጉ መርዳት ነበር። በእኔ ጥረት የተለወጡት አብዛኛዎቹ ከወዲሁ ተመስርተው ከነበሩት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ህብረት ፈጥረው ነበር።”-Bliss, ገጽ 328።GCAmh 273.2

    ጥረቱ አብያተ ክርስቲያናትን መገንባት ስለነበረ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በአዎንታ ታይቶ ነበር። ሆኖም አገልጋዮችና የኃይማኖት መሪዎች የአድቬንትን (የዳግም ምፅዓትን) አስተምህሮ ላለመቀበል በመወሰናቸው፣ የጉዳዩንም ቅስቀሳ ለመጨቆን ፍላጎት ስለነበራቸው በመድረክ ከመቃወም አልፈው፣ አባሎቻቸው ስለዳግም ምፅዓቱ በሚደረጉ ስብከቶች ላይ እንዳይገኙ መብታቸውን በመገደብ፣ ይባስ ብሎም በቤተ ክርስቲያን በሚደረጉ በማህበራዊ ስብሰባቸው ላይ እንኳ ስለሰነቁት ተስፋ እንዳይናገሩ ከለከሉአቸው። በመሆኑም አማኞች በታላቅ ፈተናና ግራ መጋባት ውስጥ ወደቁ። አብያተ ክርስቲያኖቻቸውን ይወዱ ነበርና የመለየት ፍላጎት አልነበራቸውም፤ የእግዚአብሔር ምስክርነት ሲጨቆን፣ ትንቢታትን የመመርመር መብታቸው ሲነፈግ ሲያዩ ግን እጅ እንዳይሰጡ ለእግዚአብሔር ያላቸው ታማኝነት እንደሚከለክላቸው ተሰማቸው። የእግዚአብሔርን ቃል ምስክርነት ለማፈን የሚጥሩ እነርሱ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አካል፣ “የእውነት መሰረትና ምሰሶ” እንዳልሆኑ አድርገው ማየት ጀመሩ። በመሆኑም ቀድሞ ከነበራቸው ቁርኝት መለያየት ተገቢ እንደሆነ አመኑበት። በ1844 ዓ.ም በጋ ወራት ሃምሳ ሺህ ያህል የሚሆኑ ሰዎች ከአብያተ ክርስቲያናቱ ተነጥለው ወጡ።GCAmh 273.3

    በዚሁ ጊዜ አካባቢ በመላው አሜሪካ በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በቀላሉ የሚስተዋል ለውጥ ታይቶ ነበር። ለብዙ ዓመታት ዝግ ያለ፣ ነገር ግን ቀጣይነት የነበረውና እየጨመረ የሚሄድ ወደ ዓለማዊነት ተግባራት የማዘንበል፣ ከወግና ባህል ጋር የመመሳሰል አዝማሚያ ይታይ ነበር፤ በዚያውም መጠን ትክክለኛ መንፈሳዊ ሕይወት እያሽቆለቆለ ነበር። በዚያ ዓመት ግን በምድሪቱ በነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ለየት ያለና ድንገተኛ የሞራል መላሸቅ እንደነበር ጠቋሚ መረጃዎች ነበሩ። መንስኤው ምን እንደሆነ ማንም ይኸ ነው ማለት ባይችልም የነገሩ እውነታነት ግን በስፋት ተስተውሎ በህትመትና በመድረክ ሃሳብ ተሰጥቶበታል።GCAmh 273.4

    በፊላደልፊያ በነበረው የፕረስባይቴሪ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ላይ፣ በስፋት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ማብራሪያ (commentary) የፃፈው አቶ ባርነስ፣ በከተማዋ ከነበሩ ቁጥር አንድ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የአንዱ መሪ ሲሆን “እርሱ እንደተናገረው ለአለፉት ሃያ ዓመታት በአገልግሎት የነበረ ሲሆን የመጨረሻውን የቁርባን ሥርዓት እስኪያካሂድ ድረስ፣ ይብዛም ይነስም፣ አዲስ ነፍስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳይቀላቀል ሥነ ሥርዓቱ የተፈጸመበት ጊዜ አልነበረም። አሁን ግን ምንም መነቃቃት፣ መለወጥ የለም፤ በአማኞች ዘንድ የሚታይ የፀጋ እድገት የለም፤ ስለነፍሳቸው መዳን ይወያዩ ዘንድ ወደሚያዘጋጀው ጥናት የሚመጣ የለም። ከንግድ ሥራ መጨመር ጋር ተያይዞ እየታየ ካለው የንግድ ልውውጥና የማምረት ብሩህ የወደፊት ሁኔታ ጋር ተዳምሮ፣ የዓለማዊነት አስተሳሰብ ጨምሯል። በሁሉም የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁ ተመሳሳይ ነበር።”-Congregational Journal, May 23, 1844።GCAmh 274.1

    በዚያው ዓመት በየካቲት ወር ከኦበርሊን ኮሌጅ የነበሩት ፕሮፌሰር ፊኒ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በአጠቃላይ የአገራችን የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት በዘመኑ ለሚካሄዱት የግብረ ገብነት ተሐድሶዎች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ምንም ፍላጎት ያልነበራቸው ወይም ተቃዋሚዎች እንደሆኑ ማስረጃዎቹን ፊት ለፊት የምናያቸው ናቸው። ከዚህ የተለዩ ከፊላዊ ልዩነት ያላቸው አሉ፤ ሆኖም እነዚያ የተለዩት አብዛኛው እንዲህ እንደሆነ ከመናገር የሚያስቆጥቡ አይደሉም። ይህንን ጉዳይ (ዝንባሌ) የሚደግፈው ሌላው እውነት ደግሞ ዓለምአቀፋዊ በሚባል ሁኔታ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የመነቃቃት ተጽዕኖ አለመኖሩ ነው። የመንፈሳዊነት ፍላጎት ማጣት በሁሉም ስፍራ የተንሰራፋ ነው ማለት ይቻላል፤ በአስፈሪ ሁኔታ ጥልቅ ነው። ይህንንም በምድሪቱ በሞላ ኃይማኖታዊ ህትመት የሚመሰክረው ነው። የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በስፋት ለፋሽን የተሰጡ ሆነዋል፤ እግዚአብሔርን ከማይመስሉ ሰዎች ጋር በፌሽታ ፓርቲዎች፣ በእስክስታዎችና በክብረ በዓላት ጨዋታዎች አብረዋል። ይህንን የሚያም ርዕሰ ጉዳይ ግን ልናሰፋው አይገባንም። በአጠቃላይ አብያተ ክርስቲያናት በሚያሳዝን ሁኔታ እያሽቆለቆሉ መሆናቸውን እንድናሳይ መረጃው በላያችን ላይ እየተጠቀለለና እየወፈረ ነው ማለት በቂ ይሆናል። ከጌታ እጅግ እርቀው ሄደዋል፤ እርሱም ከእነርሱ ራሱን አግልሏል።”GCAmh 274.2

    የሪሊጂየስ ቴሌስኮፕ (Religious Telescope) ፀኃፊ የነበረ አንድ ሰው ሲመሰክርም፦ እንደ “አሁኑ ያለ አጠቃላይ ማሽቆልቆል አጋጥሞን አያውቅም። በእውነት ቤተ ክርስቲያን ነቅታ የዚህ ደዌ መንስኤው ምን እንደሆነ መመርመር ያስፈልጋታል። ጽዮንን የሚወድ ማንም ሰው መቅሰፍቱን ማየት አለበት። የእውነተኛ መለወጥ ጉዳዮች ምን ያህል አናሳና የተራራቁ መሆናቸውን ስናሰላስል፣ የኃጢአተኞችንም ወደር የሌለው ግትርነትና አለመፀፀት ስናይ፣ ሳናስበው እግዚአብሔር ደግ መሆኑን እረሳን እንዴ ወይስ የምሕረት ደጅ ተዘጋ? ብለን ልንጮህ ምንም አይቀረንም” ብሏል።GCAmh 274.3

    በቤተ ክርስቲያን በራስዋ ውስጥ መንስኤ ሳይኖር እንደዚህ አይነቱ ሁኔታ በፍፁም አይከሰትም። በአገራት፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በግለሰቦች ላይ የሚወድቀው መንፈሳዊ ጽልመት፣ መለኮታዊ ፀጋን በመለገስ ረገድ በእግዚአብሔር በኩል የሚደረግ ድንገተኛ ማቋረጥ ሳይሆን በሰዎች በኩል የሚደረገው መለኮታዊ ብርሐንን ቸል ማለት ወይም አለመቀበል ነው። የዚህ እውነት አንፀባራቂ ማስረጃ የሚሆነው በክርስቶስ ዘመን የነበሩት የአይሁዳዊያን ታሪክ ነው። ለዓለም በመሰጠታቸውና እግዚአብሔርንና ቃሉን በመርሳታቸው ማስተዋላቸው ደበዘዘ፤ ልባቸው ምድራዊና ስሜትን በማርካት ላይ ያተኮረ ሆነ። በመሆኑም የመሲሁን መምጣት በተመለከተ እውቀቱ አልነበራቸውም፤ በኩራታቸውና በአለማመናቸውም አዳኙን ሳይቀበሉ ቀሩ። እንዲህም ሆኖ እንኳ እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከድነት በረከቶች እውቀት ወይም በዚህ በረከት ውስጥ ከመሳተፍ አላገለላቸውም ነበር። እውነትን አሻፈረኝ ያሉ እነርሱ ግን ለሰማይ ስጦታ ያላቸውን ፍላጎት ሁሉ አጡ። በውስጣቸው የነበረው ብርሐን ወደ ጨለማነት እስኪለወጥ ድረስ “ጨለማውን ብርሐን፣ ብርሃኑን ጨለማ” [ኢሳ 5÷20] አሉ። ያ ጨለማ እንዴት ታላቅ ነበረ!GCAmh 275.1

    ህያው የሆነ እግዚአብሔርን የመምሰል መንፈስ እስካልኖረ ድረስ ሰዎች የኃይማኖት መልክ ይዘው ቢቀጥሉ የሰይጣንን መርሃ ግብር የሚገጥም ነው። የእግዚአብሔር መገኘት በመካከላቸው መታየት እንዳቆመ ራሳቸው የማይክዱት እውነታ ሆኖ ሳለ ወንጌሉን አንቀበልም ካሉ በኋላ አይሁዳዊያን የጥንቱን የአምልኮ ሥርዓት በቅንዓት ቀጠሉበት፤ ብሄራዊ ብቸኝነታቸውን በጥንቃቄ ጠበቁ። የዳንኤል ትንቢት የመሲሁን የመምጣት ጊዜ በትክክል ስላመለከተ፣ መሞቱንም በቀጥታ ስለተነበየ እንዳይጠና ግፊት አደረጉ፤ በመጨረሻም ረቢዎች ዘመኑን ለማስላት በሞከሩ ሁሉ ላይ መርገም አወጁ። ከፀጋው ለሆነላቸው የድነት ስጦታ ቁብ ሳይሰጡ፣ የወንጌሉን በረከቶች ሳያስተውሉ፣ ከሰማይ የሚመጣን ብርሐን አሻፈረኝ ማለት ለሚያመጣው አደጋ ከባድና አስፈሪ ማስጠንቀቂያውን ቸል ብለው፣ በእውርነትና በአለመፀፀት፣ የእሥራኤል ሕዝቦች ለአንድ ሺህ ስምንት መቶ አመት [ለተከታታይ ምዕተ ዓመታት] ቆመዋል።GCAmh 275.2

    [የአንድ ነገር] ምንጭ (መንስኤ) ባለበት ሁሉ፣ ተመሳሳይ ውጤቶች ይከተላሉ። ከዝንባሌዎቹ ጋር ስለሚጋጭ ለሃላፊነቱ ያለውን መሰጠት ሆን ብሎ የሚገድብ እርሱ በስተመጨረሻ በእውነትና በስህተት መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት የሚያስችለውን ኃይል ያጣል። ማስተዋሉ ይጨልማል፣ ህሊናው ይደንዛል፣ ልቡ ይደነድናል፣ ነፍሱም ከእግዚአብሔር ትለያለች። መለኮታዊ የእውነት መልእክት ተቀባይነት ባጣበት ወይም በቀለለበት በዚያ ስፍራ ቤተ ክርስቲያን በጨለማ ትጀቦናለች፤ እምነትና ፍቅር ይቀዘቅዛሉ፤ መቃቃርና አለመግባባት ይከተላል። የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መሻቶቻቸውንና ኃይላቸውን ዓለማዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ማእከል ያደርጋሉ፤ ኃጢአተኞችም በአልፀፀት ባይነታቸው ይደነድናሉ።GCAmh 275.3

    የእግዚአብሔርን የፍርድ ሰዓት በማወጅ ሰዎች እንዲፈሩትና እንዲያመልኩት የሚጠራው በራእይ 14 የሚገኘው የመጀመሪያው መልአክ መልእክት የእግዚአብሔርን ታማኝ ሕዝቦች ከሚያበላሸው ከዓለም ተጽዕኖዎች ለመለየት እንዲሁም የዓለማዊነታቸውንና ወደ ኋላ የማፈግፈጋቸውን ትክክለኛ ሁኔታ እንዲያዩ ታቅዶ የተሰጠ ነበር። ቢቀበሉት ኖሮ እግዚአብሔር በሰጣቸው በዚህ መልእክት ውስጥ ከእርሱ እየለዩአቸው ያሉትን እርኩሰቶች ማስተካከል ይችሉ ነበር። የመጣውን መልእክት በመቀበል በጌታ ፊት ልባቸውን ቢያዋርዱ፣ በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ከልባቸውም ለመዘጋጀት ቢሹ ኖሮ፣ የእግዚአብሔር መንፈስና ኃይል በመካከላቸው በተገለጠ ነበር። ቤተ ክርስቲያንም በሐዋርያት ዘመን እንደነበረችበት እንደገና በተባረከ ህብረት፣ እምነትና ፍቅር፣ ያመኑትም “አንድ ልብ አንድም ነፍስ” እንደነበሯቸው “የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ” እንደተናገሩ “ጌታም የሚድነቱን እለት እለት በእነርሱ ላይ ይጨምር” እንደነበረበት ጊዜ በሆነች ነበር [የሐዋ ሥራ 4÷32፣31፤ 2÷47]።GCAmh 275.4

    የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች [ነን ባዮች] ከቃሉ የሚያንፀባርቀው ብርሐን በላያቸው ሲያበራ ቢቀበሉ ክርስቶስ ለለመነው፣ ሐዋርያውም “የመንፈስንም አንድነት በሰላም ማሰሪያ” በማለት ለገለጸው ለዚያ ህብረት መድረስ ይችላሉ። ሲናገርም፣ “በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ” ይላል፣ “አንድ ጌታ አንድ ኃይማኖት አንዲት ጥምቀት።” [ኤፌ 4÷3-5]።GCAmh 276.1

    የአድቬንትን መልእክት የተቀበሉት ሰዎች የተለማመዱዋቸው የተባረኩ ፍሬዎች እንደዚህ አይነት ነበሩ። “ከተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት የመጡ ነበሩ፤ ከተለያዩ ተቋማት ስም ልዩነት የተነሳ የነበሩባቸው ግድግዳዎች ወደ መሬት ተወረወሩ፤ የሚጋጩ አመለካከቶች እንደ ብናኝ ተበተኑ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው የአንድ ሺህ ዓመት ምድራዊ መንግሥት ተስፋ ተተወ፤ የዳግም ምፅዓቱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ተስተካከሉ፤ ኩራትና ከዓለም ጋር መመሳሰል ተጠራርገው ተወገዱ፤ ስህተቶች ታረሙ፤ እጅግ በሚማርክ ህብረት ልቦች አንድ ሆኑ፤ ፍቅርና ደስታ የበላይ ገዥ ሆኑ። ይህ አስተምህሮ ለተቀበሉት ጥቂቶች እንዲህ ካደረገ፣ ሁሉም ቢቀበሉት ኖሮ እንዲሁ ባደረገላቸው ነበር።”GCAmh 276.2

    ነገር ግን በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት ማስጠንቀቂያውን ሳይቀበሉ ቀሩ፤ አገልጋዮቻቸው “የእሥራኤል ቤት ጠባቂ” እንደመሆናቸው [ሕዝ 3÷17] የየሱስን ምፅዓት ምልክቶች በማወቅ ረገድ የመጀመሪያዎቹ መሆን ሲገባቸው፣ ከነብያት ምስክርነትም ሆነ ከዘመኑ ምልክቶች እውነቱን መገንዘብ ተሳናቸው። ዓለማዊ ተስፋዎችና ምኞቶች ልብን በመሙላታቸው፣ ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር፣ በቃሉ ላይም የነበረው እምነት ቀዘቀዘ። የአድቬንት አስተምህሮ በተሰጠበት ጊዜ ማድረግ የቻለው መጥሌአቸውንና አለማመናቸውን ማነቃቃት ብቻ ነበር። መልእክቱ የተሰበከው በአብዛኛው ባልተማሩ (በተራ) ሰዎች መሆኑ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ የመከራከሪያ ምክንያት ሆነ። እንደ ጥንቱ ሁሉ ግልጽ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ምስክርነት “ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳዊያን በእርሱ ያመነ አለን?” [ዮሐ 7÷48] የሚል ጥያቄ ተሰነዘረበት። ከትንቢታዊ ዘመናት የተገኙትን መረጃዎች ትክክል እንዳልሆኑ ማረጋገጫ የማቅረብ ሥራ እጅግ ፈታኝ እንደሆነ በመረዳት፣ የትንቢት መጻሕፍት የታተሙ (የተዘጉ) በመሆናቸው፣ ልንረዳቸው የማይገባን ናቸው እያሉ በማስተማር ትንቢታት እንዳይጠኑ ብዙዎችን ያሳንፉ ነበር። እልፍ አእላፋት፣ ፓስተሮቻቸውን ያለምንም ጥርጣሬ በማመን ማስጠንቀቂያውን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ እውነት መሆኑን ቢያምኑም “ከምኩራብ እንዳያስወጡአቸው” [ዮሐ 12÷43] በመስጋት ማመናቸውን መመስከር አልደፈሩም። ለቤተ ክርስቲያን መፈተኛና መንፃት እግዚአብሔር የሰጠው መልእክት፣ ፍላጎቶቻቸውን በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዚህ ዓለም ላይ ያደረጉ ምን ያህል ብዛት እንዳላቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር። ከምድር ጋር ያቆራኟቸው ገመዶች ወደ ሰማይ ከሚጎትቱ ስበቶች የጠነከሩ ነበሩ። የዓለማዊ ጥበብን ድምጽ ለመስማት መርጠው ልብን ከሚመረምረው የእውነት መልእክት ዘወር አሉ። የመጀመሪያውን መልአክ ማስጠንቀቂያ አንቀበልም በማለት ለመታደሳቸው ምክንያት ይሆን ዘንድ ሰማይ የሰጠውን አቅርቦት አንፈልግም አሉ። ከእግዚአብሔር የለዩአቸውን እርኩሰቶች የሚያስተካክልላቸውን መልካሙን መልዕክተኛ በዘለፋ አባረሩ፤ ከበፊቱ በጠለቀ ፍላጎትም የዓለምን ዝምድና ለመሻት ተመለሱ። በ1844 ዓ.ም በአብያተ ክርስቲያናት የነበረው አስፈሪ የዓለማዊነት ሁኔታ፣ ወደ ኋላ የማፈግፈግና የመንፈሳዊ ሞት መንስኤ ይህ ነበር።GCAmh 276.3

    በራዕይ 14 የመጀመሪያውን መልአክ ተከትሎ የመጣ፣ “አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቁጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች” [ራእይ 14÷8] ብሎ የሚያውጅ ሁለተኛ መልአክ አለ። ባቢሎን የሚለው ቃል ባቤል ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ድንግርግር (confusion) ማለት ነው። የተለያዩ የሐሰት ወይም የክህደት ኃይማኖታዊ ስርዓቶችን በመወከል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅም ላይ ውሏል። በራዕይ 17 ባቢሎን በሴት ተመስላ ቀርባለች፤ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ተደርጎ የተቀመጠ ሲሆን መልካም ባህርይ ያላት ሴት ንጽህት ቤተ ክርስቲያንን ስትወክል፣ ምግባረ ብልሹዋ ሴት ደግሞ ከሃዲዋን ቤተ ክርስቲያን ትወክላለች።GCAmh 277.1

    በመጽሐፍ ቅዱስ፣ የተቀደሰውና ዘላቂ የሆነ ባህርይ ያለው በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል የሚኖረው ግንኙነት በጋብቻ ጥምረት ምሳሌ የተወከለ ነው። በእውነተኛ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ከራሱ ጋር አቆራኝቷቸዋል፤ እርሱ አምላካቸው ሊሆን ቃል ገብቶ፣ እነርሱም የእርሱና የእርሱ ብቻ ሊሆኑ ቃል ገብተዋል። እንዲህ ይላል፦ “ለእኔም ለዘላለም አጭሻለሁ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በርኅራኄም አጭሻለሁ” [ሆሴ 2÷19]። እንደገናም “እኔ ባላችሁ ነኝ” [ኤር 3÷14] ይላል። ጳውሎስም ተመሳሳዩን ተምሳሌት በአዲስ ኪዳን እንዲህ ሲል ይጠቀመዋል፣ “እንደ ንጽህት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና።” [2ኛ ቆሮ 11÷2]።GCAmh 277.2

    መታመንዋና ፍቅርዋ ከእርሱ ፈቀቅ እንዲል በመፍቀድ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ላይ እምነት አጉዳይ መሆንዋ፣ የዓለማዊ ነገሮችም ፍቅር ነፍስን እንዲወር እሺ ማለትዋ፣ የጋብቻን ቃል ኪዳን ከመጣስ ጋር ተመሳስሎ ቀርቦአል። ከጌታ በመራቅ እሥራኤል የሰራችው ኃጢአት በዚህ ምሳሌነት ቀርቦአል። የረገጡት የእግዚአብሔር ግሩም ፍቅርም እንዲሁ በዚህ መልክ ልብን በሚነካ መንገድ ተስሏል። “ማልሁልሽም ካንችም ጋራ ቃል ኪዳን አደረግሁ አለ እግዚአብሔር አምላክ ለእኔም ሆንሽ።” “እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ፤ ባንች ላይ ካኖርኳት ከክብሬ የተነሳ ውበትሽ ፍፁም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ.…በውበትሽም ታምነሽ ስለስምሽም አመነዘርሽ” “በባልዋ ፈንታ እንደምታመነዝር ሴት የእሥራኤል ቤት ሆይ እንዲሁ በእኔ ላይ አደረጋችሁ ይላል እግዚአብሔር።” [“በባልዋ ፈንታ እንግዶችን እንደምታስገባ ምንዝር እንደምትፈጽም ሚስት”]፤ “ሚስት ባልዋን እንደምታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ” [ሕዝ 16÷8፣ 13-15፣ 32፤ ኤር 3÷20]።GCAmh 277.3

    በአዲስ ኪዳንም ከእግዚአብሔር ሞገስ ይልቅ የዓለምን ጓደኝነት ስለሚሹ ክርስቲያኖች [ነን ባዮች] በተመሳሳይ ቋንቋ የተፃፈ መልእክት ቀርቦላቸዋል። ሐዋርያው ያዕቆብ ሲናገር፦ “እላንት አመንዝሮች፣ አመንዝራይቶችም አታውቁምን የዓለም ፍቅር በእግዚአብሔር ላይ ፀላትነት እንደሆነች? የዓለም ወዳጅ መሆን የሚወድ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖ ተገኘ።” [ያዕ 4÷4]።GCAmh 277.4

    ሴቲቱ፣ የራዕይ 17 ባቢሎን ስትገለጽ “በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ” በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቁዎችም ተሸልማ ነበር። በእጅዋም የሚያፀይፍ ነገር፣ የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ያዘች። … በግንባርዋም ምስጢር የሆነ ስም ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞቶችና የምድር ርኩሰት እናት ተብሎ ተፃፈ” ይላል ነብዩ። “ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት።” [ራዕይ 17÷4-6]። በተጨማሪም ባቢሎን “በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግስ ታላቂቱ ከተማ” እንደሆነች ተነግሮአል [ራዕይ 17÷18]። ለብዙ መቶ ዓመታት በክርስቲያን ነገሥታት ላይ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ አገዛዝ መስርቶ ቀፍድዶ ያኖራቸው ሮም ነው። ቀይና ሐምራዊ ቀለም፣ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች እንዲሁም ዕንቁዎች በግልጽ የሚያመለክተው አንፀባራቂውን፣ ከነገሥታት በላይ የሆነውን፣ በእብሪተኛው ሮም መንበረ-መንግሥት የተደገፈውን ልታይ ልታይ ባይነትን ነው። “በቅዱሳን ደም ሰክራ” ተብላ በትክክል የተነገረባት፣ የክርስቶስን ተከታዮች በጭካኔ ካሳደደችው ቤተ ክርስቲያን በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም። ባቢሎን “ከምድር ነገሥታት” ጋር ህገ-ወጥ ቁርኝት በማድረግ ኃጢአትም ትከሰሳለች። ከጌታ ተለይታ ከአሕዛብ ጋር ህብረት በመፍጠርዋ ነበር የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን ጋለሞታ የሆነችው፤ ሮምም የምድራዊ ኃይላትን እገዛ በመሻት በተመሳሳይ ሁኔታ ራስዋን ስላበላሸች፣ ተመሳሳይ ኩነኔ ትቀበላለች።GCAmh 278.1

    ባቢሎን “የጋለሞቶች እናት” ተብላለች። ሴት ልጆችዋ ሊወክሉ የሚችሉት ደግሞ አስተምህሮችዋንና ባህልዋን አጥብቀው የያዙ፣ ከዓለም ጋር ህገ-ወጥ ህብረት ትመሰርት ዘንድ እውነትንና የእግዚአብሔርን ይሁንታ የምትሰዋበትን እርስዋ የሄደችበትን መንገድ የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያናትን ነው። የባቢሎንን መውደቅ የሚያውጀው የራእይ 14 መልእክት፣ በአንድ ወቅት ንፁህ የነበሩትን ሆኖም የተበላሹትን ኃይማኖታዊ ተቋማት የሚመለከት መሆን አለበት። ይህ መልእክት የፍርዱን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የሚመጣ በመሆኑ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት መሰጠት ያለበት ነው። ስለዚህ የሮም ቤተ ክርስቲያን በውድቀት ውስጥ ሆና ለብዙ መቶ ዓመታት ስለቆየች ይህ መልእክት እርስዋን የሚመለከት አይደለም። በተጨማሪም በራእይ በአሥራ ስምንተኛው ምዕራፍ ገና ወደፊት ሊመጣ ስላለው መልእክት፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከባቢሎን እንዲወጡ ተጠርተዋል። እናም በየትኞቹ የኃይማኖት ተቋማት ነው አብዛኛዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች የሚገኙት? ያለምንም ጥርጥር የፕሮቴስታንትን እምነት በሚመሰክሩ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ነው። በተነሱበት ዘመን፣ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ለእግዚአብሔርና ለእውነት ክቡር አቋም ያዙ፤ በረከቱም አብሯቸው ነበረ። የማያምነው ዓለም እንኳ የወንጌሉን መርህ ከመቀበል ጋር ተያይዘው የመጡትን ጠቃሚ ውጤቶች እውቅና ለመስጠት ተገዶ ነበር። ለእሥራኤል በተነገሩት የነብዩ ቃላት፣ “የውበትሽም ወሬ [ዝና] በአሕዛብ ተሰማ፣ ፍፁም ነበረና ባንቺ ላይ ባኖርኋት በክብሬ ይላል እግዚአብሔር አምላክ” [ሕዝ 16÷14]። ነገር ግን የእሥራኤል እርግማንና ውድመት በነበረው ማለትም እግዚአብሔርን የማይመስሉትን ሕዝቦች ተግባራት መቅዳትና ከእነርሱም ጋር ወዳጅነት ለመፍጠር የማባበል ጽኑ ፍላጎት፣ እነርሱም በዚሁ ተመሳሳይ ፍላጎት ወደቁ። “በውበትሽም ታመንሽ ስለስምሽም አመነዘርሽ።” [ሕዝ 16÷15]።GCAmh 278.2

    ብዛት ያላቸው የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት “ከምድር ነገሥታት ጋር” ኃጢአት የተሞላበት ግንኙነት የነበራትን የሮምን ተምሳሌት እየተከተሉ ናቸው - በመንግሥት የሚደገፉ አብያተ ክርስቲያናት ኃይማኖታዊ ካልሆኑ መንግሥታትና ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ እንዲሁም ከሌሎች የኃይማኖት ተቋማት ደግሞ የዓለምን ተቀባይነት ለማግኘት በመጣር፣ እንዲህ ያደርጋሉ። ባቢሎን - ድንግርግር - የሚለው ቃል ለእነዚህ ተቋማት ገጣሚ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም አስተምህሮአቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ የወሰዷቸው መሆኑን ሲናገሩ ሳለ፣ መቆጠር በማይቻል ብዛት ተከፋፍለው፣ በስፋት የሚጣረሱ እምነቶችንና ንድፈ-ሐሳቦችን የሚያራምዱ ናቸው።GCAmh 279.1

    ኃጢአት የሞላበት ሕብረት ከዓለም ጋር ከማድርጋቸው ባሻገር፣ ከሮም የተነጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ የእርስዋን ሌሎች ባህርያትም ያሳያሉ።GCAmh 279.2

    ካቶሊክ ክርስቲያን ኢንስተረክትድ/Catholic Christian Instructed የሚለው የሮም ሥራ ውጤት የሆነው ሲከራከር፦ “ከቅዱሳን ጋር በተገናኘ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጣዖት አምላኪነትዋ በደለኛ ከነበረች፣ ቀድሳ ለለየችው አንድ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ ቀድሳ የለየቻቸው አሥር የማርያም አብያተ ክርስቲያናት ያሏት፣ ሴት ልጅዋ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የዚያው ኃጢአት ጥፋተኛ ናት።”-Richard Challoner, The Catholic Christian Instructed, Preface, ገጽ 21, 22።GCAmh 279.3

    አቶ ሆፕኪንስ በሚሊኒየም/Millennium ላይ ሲተነትን እንዲህ ይላል፦ “የክርስቲያን ተቃዋሚ መንፈስና ተግባራት አሁን የሮማ ቤተ ክርስቲያን ብለን በምንጠራው ስፍራ ብቻ ነው የሚገኘው ብሎ ለማሰብ ምክንያት የለም። የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትም በአብዛኛው ኢ-ክርስቲያንነት በውስጣቸው አለ፤ ከብልሽትና ከርኩሰት ሙሉ ለሙሉ ከመታደስ እጅግ የራቁ ናቸው።”-Samuel Hopkins, Works, vol.2, ገጽ 328።GCAmh 279.4

    የፕረስባይቴሪያኖች ቤተ ክርስቲያን ከሮም መነጠልዋን በተመለከተ ዶክተር ጉትሪ ሲጽፍ፦ “ከሶስት መቶ ዓመት በፊት የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ አርማዋ ላይ አድርጋ ‘መጽሐፍ ቅዱስን መርምሩ’ የሚል መፈክር አንግባ ቤተ ክርስቲያናችን ከሮም ግቢ ወጣች”፤ ከዚያም አስፈላጊ ጥያቄ ይጠይቃል፤ “ከባቢሎን ፀድተው ወጥተዋል?”GCAmh 279.5

    “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን” አለ ስፐርጂዮን “በሳክራመንታሪያኒዝም (የቅዱስ ቁርባንን ሥርዓት እውንነት የማይቀበል) ውስጥ ውስጡን ተቦርቡራ ተበልታለች። ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ አለመስማማት (አለመመሳሰል) እራሱ በፍልስፍና እምነተ-ቢስነት የተበሳሰከ ይመስላል። የተሻለ ነገር የጠበቅንባቸው ሁሉ አንድ በአንድ ከእምነቱ መሰረታዊ መርሆዎች እያፈነገጡ ናቸው። አሁንም ወደ መድረክ ወጥቶ ራሱን ክርስቲያን ብሎ ለመጥራት በሚደፍር፣ ሊኮነን በሚገባው እምነት አጉዳይነት፣ የእንግሊዝ ልብ፣ ውስጥ ውስጡን እንደተበሳሳ አምናለሁ።”GCAmh 279.6

    የታላቁ ክህደት ምንጭ ምን ነበር? ቤተ ክርስቲያን ግልጽነት ከተላበሰው (ካልተወሳሰበው) ወንጌል መጀመሪያ እንዴት ፈቀቅ አለች? አሕዛብ ክርስትናን ይቀበሉ ዘንድ ለማቀላጠፍ ስትል የጣዖት አምልኮ ተግባራትን ስለተከተለች ነበር። በእርሱ ዘመን እንኳ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የአመጽ ምስጢር አሁን ይሰራልና” [2ኛ ተሰሎ 2÷7]። በሐዋርያቱ የሕይወት ዘመን ቤተ ክርስቲያን በአንፃራዊ ንጽህና እንደሆነች ነበረች። “በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ግን አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት አዲስ መልክ ያዙ፤ መጀመሪያ የነበረው ግልጽነት ጠፋ፤ ታላላቆቹ ደቀ መዛሙርት ወደ መቃብራቸው ከወረዱ በኋላ፣ አስተዋይነት በጎደለው ሁኔታ ልጆቻቸው ከአዲስ የእምነቱ ተቀባዮች ጋር በመሆን….ወደ ፊት በመምጣት ይህንን አላማ አዲስ ቅርጸ-አካል አበጁለት።”[Robinson, in History of Baptism]። አዲስ አባላት ለማግኘት ሲባል ከፍ ብሎ የነበረው የክርስትና እምነት ደረጃ ዝቅ ተደረገ፤ በዚህም የተነሳ “ባህልና ወጉን፣ ስነ ስርዓቱንና ጣዖቶቹን ይዞ፣ የጣዖት አምልኮ ጎርፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጥለቅልቆ ገባ።” [Gavazzi’s Lectures, ገጽ 290]። የክርስትና እምነት የመንግሥታዊ ገዥዎችን ይሁንታና ድጋፍ ማግኘት ሲችሉ፣ በስም ብቻ ቢሆንም እልፍ አዕላፋት ተቀበሉት፤ ሆኖም የክርስቲያን መልክ ቢይዙም፣ ብዙዎች “በተለይም በድብቅ ጣኦቶቻቸውን እያመለኩ በተግባር ኃይማኖት-የለሾች እንደሆኑ ነበሩ።” [Gavazzi’s Lectures, ገጽ290]GCAmh 279.7

    ይህ ተመሳሳይ ሂደት ራሱን ፕሮቴስታንት ብሎ በሚጠራ በሁሉም ቤተ ክርስቲያን ማለት ይቻላል፣ አልተደገመም? እውነተኛ የመታደስ መንፈስ የነበራቸው መሥራቾች ሲሞቱ ትውልዶቻቸው ተረክበው “አላማውን አዲስ መልክ አስያዙት።” የአባቶቻቸውን እምነት የሙጥኝ ብለው በጭፍንነት በመያዝ ቀደምቶች ካስተዋሉት እውነት በተጨማሪ ሌላ አንቀበልም ብለው ሳለ የተሐድሶ መሪዎች በምሳሌነት ካሳዩት ራስን ዝቅ ማድረግን፣ ራስን መካድንና ዓለም-በቃኝ ማለትን በስፋት ትተውት ነበር። በመሆኑም “የመጀመሪያው ግልጽነት ይጠፋል።” ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጎርፍ ዓለማዊ የውኃ ሙላት “ወግና ባህሉን፣ ምግባሩንና ጣኦቱን” አብሮ ይዞ ይገባል።GCAmh 280.1

    እግዚኦ፣ “ለእግዚአብሔር ጥል” የሆነው ዓለምን መውደድ በክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ዘንድ የሚፈቀርበት መጠን እንዴት አስፈሪ ነው! በክርስትናው ዓለም ያሉ ሕዝባዊ አብያተ ክርስቲያናት የመጽሐፍ ቅዱስ ደረጃ ከሆነው ራስን ዝቅ ከማድረግ፣ ራስን ከመካድ፣ ውስብስብ ካለመሆንና ከእግዚአብሔር መሰልነት ምን ያህል ርቀው ተለይተዋል! ስለ ትክክለኛ የገንዘብ አጠቃቀም ጆን ዌስሊ ሲናገር፦ “እንዲሁ አይን ያየውን ለማርካት፣ ከመጠን በላይ የሆነና በጣም ውድ ልብስ፣ ወይም አላስፈላጊ ጌጣጌጥ በመግዛት ምንም ገንዘብ መጥፋት የለበትም። ልዩ በሆነ ጌጥ ቤታችሁን በማስዋብ፣ ከመጠን ባለፈ ወይም በውድ ቁሳቁስ፣ ውድ ፎቶዎች፣ ስዕሎች፣ በወርቅ ለተለበጡ እቃዎች ምንም ገንዘብ አታባክኑ” ይላል። “የሰዎችን አድናቆት ወይም ሙገሳ ለማትረፍ፣ የሕይወትን የክብር ጥማት ለማርካት ምንም ነገር አታውጡ።” “‘ለራስህ መልካም እስካደረግህ ድረስ ሰዎች ስለአንተ ጥሩ ይናገራሉ’፤ ‘እጅግ ውድ በሆነ ኃምራዊና ጥሩ በፍታ በየቀኑ እስከለበስህ ድረስ’ በድንቅ ምርጫህ ብዙዎች ያጨበጭቡልሃል፣ በለጋስነትህና በመስተንግዶህ ብዙዎች እንደሚያጨበጭቡልህ ጥርጥር የለውም። አድናቆታቸውን ግን በውድ አትግዛው፣ ከእግዚአብሔር ከሚመጣው ክብር የረካህ ብትሆን ይሻላል።” በዘመናችን ባሉ አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ግን እንደዚህ አይነቱ ትምህርት ተትቷል።GCAmh 280.2

    ኃይማኖተኛነት በዓለም ተወዳጅ ሆኖአል። የማህበረሰብን ክብርና አመኔታ ለማግኘት እንዲሁም የራሳቸውን ዓለማዊ ፍላጎቶች ለማሳካት ሲሉ ገዥዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሕግ ሰዎች፣ ዶክተሮች፣ ነጋዴዎች ቤተ ክርስቲያንን ይቀላቀላሉ። እንደዚህም በማድረግ ፃድቅነት የጎደላቸውን ግብይቶቻቸውን በክርስትና እምነት ተከታይነት ስም ስር ለመደበቅ ይጥራሉ። የተለያዩ ኃይማኖታዊ አካላት፣ በእነዚህ በተጠመቁ ዓለማዊያን ኃብትና ተጽዕኖ እየተበራቱ ለላቀ ዝነኛነትና ስልጣን ይኳትናሉ። እጅግ የተዋቡ አብያተ ክርስቲያናት፣ እጅግ ከመጠን ያለፈ ብክነት በሚታይበት ሁኔታ ተንቆጥቁጠው ዝነኛ በሆኑ አካባቢዎች ይቆረቆራሉ። አምላኪዎቹም እጅግ ውድና ወቅታዊ (ፋሽን) በሆኑ ልብሶች ራሳቸውን ያስጌጣሉ። ሰዎችን ለሚያዝናና እና ለሚስብ፣ ተሰጥኦ ላለው አገልጋይ ከፍተኛ ደመወዝ ይከፈላል። ስብከቶቹ የተለመዱ (በአብዛኛው ሕዝብ የሚፈፀሙ) ኃጢአቶችን መንካት የለበትም፤ ለስላሳና ለወቅቱ ጆሮዎች ደስ የሚያሰኝ መሆን አለባቸው። እናም ዘመናዊ ኃጢአተኞች በቤተ ክርስቲያን መዛግብት ይመዘገባሉ፤ ዘመናዊ ኃጢአቶችም በአስመሳይ እግዚአብሔርን መሰልነት ስር ይደበቃሉ።GCAmh 281.1

    ታማኝ የእግዚአብሔር ሕዝቦች [ነን ባዮች] ለዓለም ያላቸውን ወቅታዊ አስተያየት አስመልክቶ አንድ የታወቀ ኃይማኖታዊ ያልሆነ መጽሔት ሲናገር “ቤተ ክርስቲያንዋ በቸልተኛነት ለዘመኑ መንፈስ እጅ ሰጥታለች፣ የአምልኮ ስርዓቷም ዘመናዊነት ከሚጠይቀው ጋር እንዲስማማ አድርጋለች።” “በእርግጥ ኃይማኖትን ተወዳጅ የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ አሁን ቤተ ክርስቲያን እንደ መሳሪያ ትጠቀምበታለች።” በኒውዮርክ ኢንዲፐንደንት [New York Independent] ፀኃፊ የሆነ ስለ ሜተዲዝም ምንነት ያለውን ሁኔታ በግልጽ ሲናገር፦ “በእግዚአብሔርን መሰሎችና ኃይማኖት በሌላቸው መካከል ያለው መለያ መስመር እንደ ደብዛዛ ጥላ እየከሰመ ነው፤ በሁለቱም በኩል ያሉ ጉጉ ሰዎች በሥራቸውና በመዝናኛቸው አተገባበር መካከል ያለውን ሁሉንም ልዩነት ለማፈራረስ ተግተው እየሰሩ ናቸው።” “የኃይማኖት ተወዳጅነት በአብዛኛው አባል በመሆን ጥቅምን የሚያገኙ እንጂ ኃላፊነትን የማይወስዱ ሰዎችን ቁጥር የማብዛት ዝንባሌ አለው።”GCAmh 281.2

    ሆዋርድ ክሮስቢ እንዲህ ይላል፦ “ዛሬ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ዓለምን እየተዳራች ነው። አባላቶችዋ እግዚአብሔርን ወደማይመስሉ ሰዎች ደረጃ ዝቅ ሊያደርጓት እየሞከሩ ነው። ኳሱ፣ ትያትሩ፣ እርቃኑንና ሃፍረተ-ቢስ የሆነው ጥበብ፣ ልክስክስ ስነ-ምግባር ያላቸው ማህበራዊ ቅንጦቶች ሁሉ ወደ ተቀደሰው የቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ጥሰው እየገቡ ናቸው። ለዚህ ሁሉ ዓለማዊነት እርካታ ሲባል ክርስቲያኖች የሁዳዴ ፆምን፣ ፋሲካንና ቤተ ክርስቲያንን የማስጌጥ ተግባር አንዳች ታላቅ ክስተት አድርገው ይቆጥሩታል። የሰይጣን የጥንት ማታለያ ነው። የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን በዚያ ቋጥኝ ላይ ተመታ፣ የሮም ቤተ ክርስቲያን በዚያው ቋጥኝ ተንኮታኮተ፤ ፕሮቴስታንትነትም ወደዚያው ጥፋት በፍጥነት እየደረሰ ነው።”GCAmh 281.3

    በዚህ ዓለማዊነትና የቡረቃ ጥማት ማዕበል ውስጥ ስለ ክርስቶስ የሚደረገው ራስን መካድና ራስን ለመስዋዕትነት ማቅረብ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፉ ምንም አልቀራቸውም። “አሁን በአብያተ ክርስቲያናችን የሚንቀሳቀሱ በሕይወት ያሉ የተወሰኑት ሴቶችና ወንዶች፣ በልጅነታቸው ጊዜ ለክርስቶስ ለመለገስ ወይም አንዳች ነገር ለማድረግ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ የተማሩ ነበሩ።” ሆኖም “አሁን ገንዘብ ቢፈለግ…. ማንም እንዲሰጥ መጠየቅ የለበትም። ኦህ አይሆንም! ቲአትር ማየት፣ በማይንቀሳቀሱ ሞዴሎች የሚቀርቡ ትይንቶችን መመልከት፣ እውነት የሚመስሉ የውሸት ሸንጎዎችን ማየት፣ ታሪካዊ የሆነ እራት ወይም የሆነ የሚበላ ነገር መውሰድ፣ ሰዎችን የሚያዝናና ማንኛውም ነገር ማድረግ ይመረጣል።”-The Healthy Christian, an Appeal to the Church ገጽ 141, 142’GCAmh 281.4

    በዊስኮንሲን ውስጥ የሚገኘው የዋሽበርን አስተዳዳሪ በአመታዊ መልእክቱ “የቤተ ክርስቲያን ትርኢቶች፣ ለበጎ አድራጎት የሚውሉ ውድድሮች፣ ለበጎ አድራጎትና ሌሎች አላማዎች የሚውሉ የሙዚቃ ትርኢቶች፣ ሎተሪዎች፣ የሽልማት ጥቅሎች፣ ‘ዕድልን መሰረት ያደረጉ ግዥዎች’፤ በቲኬት አማካኝነት የሚገኙ የሰንበት ትምህርትና ሌሎች ኃይማኖታዊ እድሎች፣ እነዚህ ሁሉ የወንጀል ችግኝ ማፍያ ናቸው፤ ከባዶ ነገር የሆነ ነገር ለማስገኘት ተስፋ የሚሰጡ ከመሆናቸው የተነሳ የዕድል ጨዋታዎች፣ በእርግጥም ቁማሮች ናቸው። ጎጂ የሆነው የቁማርተኝነት መንፈስ በእነዚህ አስፈፃሚዎች አማካኝነት እንዲስፋፋ፣ እንዲበረታታና ቀጣይ እንዲሆን ይደረጋል፤ ሆኖም ይህ ድርጊታቸው በጥሩ ዜጎች ዘንድ አይታወቅም በማለት ይናገራል። እንደ እነርሱማ ባይሆን ኖሮ ቁማርን የሚኮንኑ የተለመዱ ሕጎች በቀላሉ አይጣሱም ነበር፤ በተሻለ ሁኔታ በቀላሉም ተግባራዊ ይሆኑ ነበር። እነዚህ ተግባራት ከአሁን ወዲያ የወጣቱን ስነ-ምግባር እንዲያበላሹ ሊፈቀድላቸው አይገባም በማለት ይናገራል።”GCAmh 282.1

    ከዓለማዊ ጋር የመጣጣም መንፈስ በክርስትናው ዓለም ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ እየወረረ ነው። ሮበርት አትኪንስ በለንደን በሰጠው ስብከት በእንግሊዝ ተስፋፍቶ ስላለው መንፈሳዊ ማሽቆልቆል መልካም ያልሆነ ሁኔታ ሲገልጽ፦ “እውነተኛ ፃድቃን በምድር ላይ አንሰዋል፤ አንድም ሰው ልብ አይለውም። በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ያሉት የዘመኑ ኃይማኖተኛ ነን ባዮች የዓለም አፍቃሪዎች፣ የዓለም ተከታዮች፣ የፍጡር-ምቾት አፍቃሪዎችና ክብር ለማግኘት የሚኳትኑ ናቸው። ከክርስቶስ ጋር ይሰቃዩ ዘንድ ተጠሩ፤ እነርሱ ግን ነቀፋ ሲደርስባቸው እንኳ ይሸማቀቃሉ።” ክህደት፣ ክህደት፣ ክህደት፣ በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ግንባር ላይ ተቀርጿል(ታትሟል)፤ ቢያውቁት፣ ቢሰማቸው ኖሮ ተስፋ ይኖር ነበር፤ እግዚኦ! ‘ሃብታም ነንና ባለጠጋ ሆነናል አንድም ስንኳ አያስፈልገንም’ [ራዕይ 3÷17] ብለው ይጮሃሉ።”-Second Advent Library Tract No. 39’GCAmh 282.2

    ባቢሎን የተከሰሰችበት ታላቁ ኃጢአት፣ “አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ እንዲጠጡ” ማድረጓ ነበር [ራዕይ 18÷3]። ይህ ለዓለም የምታቀርበው የስካርዋ ጽዋ፣ ከዓለም ኃያላን ጋር ከአደረገችው ህገ-ወጥ ንክኪ የተነሳ የተቀበለቻቸውን ሐሰተኛ አስተምህሮዎችን የሚወክል ነው። ከዓለም ጋር መወዳጀት እምነትዋን ያበላሻል፤ እርስዋም በበኩልዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ምንም በማያሻማ ሁኔታ የተፃፉትን ትዕዛዛት የሚቃረኑ አስተምህሮዎችን በማስተማር የሚያበላሽ ተጽዕኖ በዓለም ላይ ታሳድራለች።GCAmh 282.3

    ሮም ሕዝቡን መጽሐፍ ቅዱስ ከልክላ በምትኩም ሁሉም ሰው የእርስዋን ትምህርት ይቀበሉ ዘንድ ፈለገችባቸው። ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያገኙ ማድረግ የተሐድሶው ተግባር ነበር። ነገር ግን በዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰዎች የእምነታቸው መሰረት ያደርጉት ዘንድ የሚማሩት የራሳቸውን መሰረተ-እምነትና ቤተ ክርስቲያናቸው የምታስተምራቸውን እንጂ መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም ብንል ማጋነን ይሆናልን? ቻርለስ ቢቸር ስለ ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሲናገር:- ” እነዚያ ቅዱስ አባቶች የተባሉት እያስፋፉት በነበረውና እያደገ በመጣው ለቅዱሳንና ለሰማዕታት በሚሰጠው አክብሮት ላይ የሚያቃልል ቃል ቢነገር ይሸማቀቁ እንደነበር ሁሉ በተለያዩ እምነቶች ላይ ማንኛውም ክብር የሌለው ቃል ሲነገር እነርሱም በተመሳሳይ ይጨማተራሉ….የፕሮቴስታንት ወንጌላዊት (evangelical) ኃይማኖታዊ ተቋማት እጅ ለእጅ ተጠላልፈው ከመያያዛቸው የተነሳ፣ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንድ ሰው ሰባኪ ሊሆን ከፈለገ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ/በተጨማሪ የሚቀበለው አንድ መጽሐፍ መኖሩ የግድ ነው.…የእምነት ኃይል፣ በእርግጥ ሮም እንዳደረገችው ሁሉ፣ አሁን የበለጠ ጮሌ በሆነ መንገድ ቢሆንም፣ መጽሐፍ ቅዱስን መከልከል እየጀመረ ነው የሚለው አባባል ምናባዊ አይደለም።”GCAmh 282.4

    ታማኝ አስተማሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገሩ፣ በዚያው ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ እንደገባቸው የሚናገሩ ምሁራንና አገልጋዮች ተነሳስተው ትክክለኛውን አስተምህሮ እንደ ኑፋቄ በማውገዝ እውነትን የሚፈልጉትን ያባርራሉ። ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ዓለም በባቢሎን ወይን ባይሰክር ኖሮ፣ ግልጽ በሆኑት፣ በሚሰነጥቁት የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች እልፍ አዕላፋት በተመለሱ ነበር። ነገር ግን ኃይማኖታዊ እምነት የተደነጋገረና የሚጋጭ መስሎ ከመታየቱ የተነሳ ሰዎች እውነት ነው ብለው የሚያምኑት ምን እንደሆነ አያውቁም። የዓለም ንስሐ ያለመግባት ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን በራፍ ላይ ተጋድሞአል።GCAmh 283.1

    የራዕይ 14 የሁለተኛው መልአክ መልዕት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበከው በ1844 ዓ.ም በጋ ወቅት ነበር፤ የበለጠ ቀጥተኛ ተፈፃሚነቱም የፍርዱ ማስጠንቀቂያ በስፋት በታወጀበት፣ በአብዛኛው ተቀባይነት ባጣበትና የአብያተ ክርስቲያናት ማሽቆልቆል እጅግ ፈጣን በነበረበት በአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ነበር። ነገር ግን የሁለተኛው መልአክ መልዕት በ1844 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ፍፃሜ ላይ አልደረሰም ነበር። የአድቬንትን መልእክት በአለመቀበላቸው ምክንያት በዚያን ጊዜ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት በግብረ ገብነት ውድቀት ውስጥ ነበሩ፤ ውድቀቱ ግን ገና አልተጠናቀቀም ነበር። ለዚህ ጊዜ የሚያስፈልጉትን የተለዩ እውነቶችን እምቢ ማለታቸውን ሲቀጥሉበት ወደ ታች እየወደቁ፣ እየወረዱ መጡ። ነገር ግን “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና” ማለት የሚቻልበት ጊዜ ገና ነው። አሕዛብ ሁሉ ይህን እንዲያደርጉ ገና አላደረገቻቸውም። ከዓለም ጋር የመመሳሰልና ለፈታኞቹ የዘመናችን እውነቶች ግድ የለሽ መሆን ያለ ሲሆን፣ በክርስትናው ዓለም ባሉ ሁሉም አገራት በሚገኙ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ስር እየሰደደ መጥቷል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናትም ጠንካራና ከባድ በሆነው የሁለተኛው መልአክ ውግዘት ውስጥ ተካትተዋል። የክህደት ሥራ ግን ገና መደምደሚያው ላይ አልደረሰም።GCAmh 283.2

    መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከጌታ መምጣት በፊት “በኃይል ሁሉ በምልክትም በሐሰትም ተዓምራት” ሰይጣን እንደሚሰራ ሰዎችም “ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ” “ሐሰትን ያምኑ ዘንድ የስህተት መንፈስ” ይቀበሉ ዘንድ ይተዋሉ። ይህ ቅድመ ሁኔታ ሳይደርስ፣ በክርስትናው ዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያናት የዓለም ህብረት ሙሉ ለሙሉ ሳይሳካ የባቢሎን ውድቀት ሙሉ አይሆንም (ፍፃሜ አያገኝም)። ለውጡ ተራማጅነት ያለው ነው፤ የራዕይ 14÷8 ሙሉ የሆነ መፈፀሚያ ገና ወደፊት ነው።GCAmh 283.3

    ባቢሎን በሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የመንፈሳዊ ጽልመትና ከእግዚአብሔር ጋር ፀብ ቢኖርም ብዙ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በአባልነት የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ለዚህ ጊዜ የተሰጡትን የተለዩ እውነቶች በጭራሽ አይተው የማያውቁ ብዙዎች አሉ። አሁን ባሉበት ወቅታዊ ሁኔታቸው ያልረኩ፣ የተሻለ፣ ግልጽ ያለ ብርሐን በመናፈቅ ላይ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም። በተቆራኟቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የክርስቶስን መልክ ለማየት በከንቱ ያማትራሉ። እነዚህ አካላት[አብያተ ክርስቲያናት] ከእውነት የበለጠ እየራቁ፣ እየራቁ ሲሄዱና ቁርኝታቸውን ከዓለም ጋር የበለጠ እያጠናከሩ ሲሄዱ፣ በሁለቱ መደቦች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሄዶ በመጨረሻም በመለያየት ይደመደማል። እግዚአብሔርን ከሁሉም በላይ አስበልጠው የሚወዱ፣ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፣ የአምልኮ መልክ አላቸው ሃይሉን ግን ክደዋል” [2ኛ ጢሞ 3÷4፣5] ከተባሉት ጋር ተቆራኝተው መቆየት የማይችሉበት ጊዜ ይመጣል።GCAmh 284.1

    በራዕይ 14÷6-12 ያለውን ሶስት እጥፍ ማስጠንቀቂያ ካለመቀበልዋ የተነሳ ቤተ ክርስቲያንዋ በሁለተኛው መልአክ የተነገረው ቅድመ ሁኔታ ላይ ሙሉ በሙሉ የምትደርስበት፣ አሁንም በባቢሎን ያሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከህብረትዋ እንዲነጠሉ የሚጠሩበት ጊዜ መቼ እንደሆነ ራዕይ 18 ይጠቁማል። ይህ ለዓለም የሚሰጥ የመጨረሻው መልእክት ነው፤ ሥራውንም ይፈጽማል። “በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በአመጽ ደስ ይላቸው የነበሩ” [2ኛ ተሰ 2÷12] የስህተትን አሰራር እንዲቀበሉና ሐሰትን እንዲያምኑ በሚተውበት ጊዜ እውነትን ይቀበሉ ዘንድ ልባቸውን ክፍት በሚያደርጉ ሁሉ ላይ የእውነት ብርሐን ያንፀባርቃል፤ በባቢሎን የቀሩት የእግዚአብሔር ልጆች “ሕዝቤ ሆይ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” [ራዕይ 18÷4] የሚለውን ድምጽ ይሰማሉ።GCAmh 284.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents