Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፴፱—“የመከራ ዘመን”

    “በዚያን ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።” [ዳን 12÷1]።GCAmh 443.1

    የሶስተኛው መልአክ መልእክት ሲጠናቀቅ ለኃጢአተኞቹ የምድር ነዋሪዎች ምሕረት መማፀንዋን ታቆማለች። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሥራቸውን ከግብ አድርሰዋል። “ከጌታ ፊት መጽናናት”ን፣ “የኋለኛውን ዝናብ” ተቀብለዋል፤ በፊታቸው ላለው ፈታኝ ሰዓትም ተዘጋጅተዋል። መላዕክት ከሰማይ ወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ናቸው። ከምድር የተመለሰ መልአክ ሥራው እንደተጠናቀቀ አወጀ። የመጨረሻው መፈተኛ በዓለም ላይ መጥቷል፤ ለመለኮታዊ መመሪያ ታማኝ መሆናቸውን ያስመሰከሩት ሁሉ “የሕያው አምላክን ማህተም” ተቀብለዋል [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 13ን ይመልከቱ]። ያኔ ክርስቶስ በላይ ባለው ቤተ መቅደስ አማላጅነቱን አቆመ። እጆቹን አንስቶ በታላቅ ድምጽ “ተፈፀመ” አለ። ይህንን ክቡር መግለጫ ሲያስተላልፍ የመላእክት ሰራዊት ሁሉ ዘውዳቸውን አወረዱ፦ “አመፀኛው ወደፊት ያምጽ፣ እርኩሱም ወደፊት ይርከስ፣ ፃድቁም ወደፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ” [ራዕይ 22÷11]። እያንዳንዱ ጉዳይ ለሕይወት ወይም ለሞት ተወስኖአዋል። ክርስቶስ ለሕዝቦቹ ስርየት አድርጎ ኃጢአታቸውን አስወግዷል። የእርሱ ተገዥዎች ቁጥር ታውቋል። “መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት “[ዳን 7÷25] ለድነት ወራሾች ሊሰጥ፣ የሱስም የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ ሆኖ ሊነግስ ነው።GCAmh 443.2

    የሱስ ቤተ መቅደሱን በሚለቅበት ጊዜ የምድርን ነዋሪዎች ጽልመት ይሸፍናቸዋል። በዚያ አስፈሪ ጊዜ፣ ፃድቃን በቅዱስ አምላክ እይታ ፊት ያለ አማላጅ መቆም ይኖርባቸዋል። በክፉዎች ላይ የነበረው ገደብ ተነስቶ ሰይጣን በመጨረሻ ንስሐ ያልገቡትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠራቸው። የእግዚአብሔር ትዕግስት አልቋል፤ ዓለም ምህረቱን እምቢ ብሏል፤ ፍቅሩን ጠልቷል፤ ሕጉንም ረግጧል። ኃጥአን የምሕረት ጊዜ ወሰናቸውን (ገደባቸውን) አልፈዋል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ፣ ባላሰለሰ ተቃውሞ ምክንያት በመጨረሻ ተወስዶአል። በመለኮት ፀጋ ስላልተከለሉ ከክፉው [ከሰይጣን የሚከልላቸው] ጥበቃ የላቸውም። ከዚያም ሰይጣን የምድርን ነዋሪዎች ወደ አንድ የመጨረሻ ታላቅ መከራ ይዘፍቃቸዋል። የእግዚአብሔር መላእክት የሰውን ጥልቅ የስሜት ሞገድ ከማገድ ሲያቆሙ የጥላቻ ባህርያት ሁሉ ልቅ ይሆናሉ። በጥንታዊት የሩሳሌም ላይ ከመጣው ጥፋት እጅግ በከፋ ሁኔታ መላው ዓለም ውድመት ውስጥ ይገባል።GCAmh 443.3

    የግብፃውያንን የበኩር ልጆች በማጥፋት ምድሪቱን በኃዘን የሞላት አንድ መልአክ ነበር። ሕዝቡን በመቁጠር ዳዊት እግዚአብሔርን በበደለ ጊዜ ኃጢአቱ የተቀጣበትን አሰቃቂ ውድመት ያመጣው አንድ መልአክ ነበር። እግዚአብሔር ሲያዝ ሥራ ላይ የሚውለው የቅዱሳን መላእክት አውዳሚ ኃይል፣ ያው ተመሳሳሳይ ኃይል፣ እርሱ ሲፈቅድ በርኩስ መላእክት ዘንድ የሚተገበር ይሆናል። በሁሉም ስፍራ ውድመት ለማሰራጨት መለኮታዊ ፈቃድ ብቻ እየጠበቁ፣ አሁን በተጠንቀቅ የቆሙ ኃይላት አሉ።GCAmh 443.4

    የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጠብቁ እነርሱ በዓለም ላይ ለሚወርደው ፍርድ ምክንያት እንደሆኑ ተደርገው ሲከሰሱ ቆይተዋል፤ የተፈጥሮ መናወጥ፣ ምድርን በሰቆቃ እየሞላው ያለው በሰዎች መካከል ላለው ጥላቻና ደም መፋሰስ ምክንያት ተደርገው ይፈረጃሉ። የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ ያጀበው ኃይል አማፂያንን አስቆጥቷቸዋል፤ መልእክቱን በተቀበሉ ሁሉ ላይ ንዴታቸው ይቀጣጠላል፤ የጥላቻንና የስደትን መንፈስ፣ ሰይጣን፣ ከነበረው በላይ እንዲጠነክር ያነሳሳል።GCAmh 444.1

    የእግዚአብሔር መገኘት በመጨረሻ ከአይሁድ ምድር ሲወሰድ ካህናትና ሕዝቡ አላወቁትም። በሰይጣን ቁጥጥር ስር ሆነው እጅግ ዘግናኝና አረመኔ በሆነ ምኞት ቢማረኩም፤ አሁንም የእግዚአብሔር ምርጥ እንደሆኑ ያስቡ ነበር። የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ቀጠለ፤ በተበከሉት መሰዊያዎች መስዋዕት ይቀርብ ነበር፤ አገልጋዮቹንና ሐዋርያቱን ለማረድ በሚሻ፣ የእግዚአብሔር ውድ ልጅ ደም ኩነኔ ባለበት ሕዝብ ላይ መለኮታዊ በረከት ይወርድ ዘንድ በየቀኑ ምልጃ ይቀርብ ነበር። የማይቀለበሰው የቤተ መቅደሱ ውሳኔ በሚታወጅበት ጊዜ የዓለም መጨረሻም ለዘላለም በሚወሰንበት ጊዜ የምድር ነዋሪዎች እንዲሁ አያውቁትም። የእግዚአብሔር መንፈስ በስተመጨረሻ ከሕዝቡ ከተወሰደ በኋላም የኃይማኖት ስርዓቱ የሚቀጥል ይሆናል። የክፋት ልዑል አረመኔ ንድፉን ያሳካ ዘንድ እነርሱን የሚያነሳሳበት ሰይጣናዊ ቅንዓት፣ ለእግዚአብሔር ያለውን ቅንዓት መልክ ይይዛል።GCAmh 444.2

    ሰንበት በክርስቲያኑ ዓለም ሁሉ የተቃርኖ ልዩ ነጥብ እየሆነ ሲመጣና ኃይማኖታዊና መንግሥታዊ ስልጣናት ኃይላቸውን አስተባብረው የእሁድን መከበር አስገዳጅ ሲያደርጉ፣ ለሕዝባዊ መጠይቅ እጅ ይሰጡ ዘንድ ባለማወላወል እምቢ የሚሉትን በቁጥር ጥቂት የሆኑ አናሳዎችን የዓለም አቀፋዊ ውግዘት ኢላማ ያደርጋቸዋል። የቤተ ክርስቲያንን ተቋም፣ የመንግሥትንም ሕግ ተቃውመው የሚቆሙትን መታገስ እንደማያስፈልግ፣ አገራት በሞላ ወደ ድንግርግሮሽና ሥርዓት አልበኝነት ከሚወድቁ እነርሱ ቢሰቃዩ ይሻላል የሚለው ኃሳብ ይኮተኮታል። ይህ ተመሳሳይ መከራከሪያ ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ዓመት (አሁን ከሁለት ሺህ ዓመት ገደማ) በሕዝብ ገዥዎች አማካኝነት በክርስቶስ ላይ ቀርቦበት ነበር። “ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ” አለ ጮሌው ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን አላቸው” [ዮሐ 11÷50]። ይህ መከራከሪያ ወሳኝ መስሎ ይቀርባል። አራተኛውን ትዕዛዝ ሰንበት በሚቀድሱት ላይም በስተመጨረሻ አዋጅ ይወጣል፤ ተወዳዳሪ የሌለው ቅጣት እንደሚገባቸው አድርጎ በማውገዝ፣ በሞት ይቀጡ ዘንድ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለሕዝቡ ነፃነት ይለግሳል። ሮማዊነት በአሮጌው ዓለም፣ እንዲሁም ፕሮቴስታንትነት በአዲሱ ዓለም፣ መለኮታዊ መመሪያዎችን በሚያከብሩ ላይ ተመሳሳይ መንገድን ይከተላሉ።GCAmh 444.3

    ከዚያም በነብዩ የያዕቆብ መከራ ተብሎ ወደተገለፀው የመከራና የጭንቀት ትዕይንት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይዘፈቃሉ። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና:- የሚያስፈራ ድምጽ ሰምተናል የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም።” “ፊት ሁሉ ወደ ጥቁረት [መገርጣት] ተቀየረ [All faces are turned into paleness]። ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፤ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል።” [ኤር 30÷5-7]።GCAmh 444.4

    ከኤሳው እጅ ይድን ዘንድ በፀሎት የታገለበት የያዕቆብ የጭንቀት ሌሊት [ዘፍ 32÷24-30] በመከራ ዘመን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ተሞክሮ የሚወክል ነው። ለኤሳው የተባለውን በረከት ለማግኘት በተከናወነው የማታለል ተግባር፣ በወንድሙ አደገኛ ዛቻዎች ተደናግጦ ያዕቆብ ሕይወቱን ለማትረፍ ኮበለለ፤ ከብዙ ዓመታት ስደት በኋላ፣ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ከሚስቶቹ፣ ከልጆቹና ከመንጋው ጋር ወደ ትውልድ አገሩ ይመለስ ዘንድ ጉዞ ጀመረ። በምድሩ ደንበር አቅራቢያ ሲደርስ፣ የጦረኛ ቡድን መሪ ሆኖ፣ ያለምንም ጥርጥር ለበቀል ተዘጋጅቶ እየቀረበ ስላለው ኤሳው ወሬ ሲደርሰው በፍርሃት ተሞላ። ያልታጠቀውና መከላከያ የሌለው የያዕቆብ ቡድን የጥልና የፍጅት ተጠቂ መሆኑ አይቀሬ መሰለ። ከድንጋጤና ከፍርሃት ሸክም በተጨማሪ፣ ራስን የመኮነን የሚደቁስ ክብደት ተሰማው፤ ይህንን አደጋ ያመጣው የራሱ ኃጢአት ነበረና። ብቸኛ ተስፋው የእግዚአብሔር ምሕረት ነበር፤ ብቸኛው ቅጥሩ ፀሎት መሆን አለበት። ያም ሆኖ የመጣውን አደጋ ይቀለብስ ዘንድ፣ በወንድሙ ላይ ላጠፋው ጥፋት መሻሪያ ይሆን ዘንድ፣ በእርሱ በኩል መደረግ ከሚገባው ያላደረገው ነገር አልነበረም። የእግዚአብሔር ሕዝቦችም ወደ መከራ ዘመን በተቃረቡ ጊዜ፣ መላምትን ትጥቅ ያስፈቱ ዘንድ፣ የህሊና ነፃነትንም አደጋ ላይ ከጣለው ክስተት ለማትረፍ ራሳቸውን በትክክለኛው ብርሐን ያደርጉ ዘንድ ሁሉንም ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።GCAmh 445.1

    ጭንቀቱን እንዳያዩ ቤተሰቡን ከሰደደ በኋላ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ይማለድ ዘንድ ያዕቆብ ብቻውን ቀረ። ኃጢአቱን ተናዘዘ፤ እግዚአብሔር ላሳየው ምሕረት በምስጋና እውቅና ሰጠ፤ በጥልቅ ራስን ማዋረድ ለአባቶቹ ስለገባው ቃል ኪዳን፣ ለራሱ ስለተሰጠው በቤቴል ሌሊትና በስደት ምድር ስላየው ራዕይ ተስፋዎች ተማፀነ። በሕይወቱ ላይ መከራ መጥቶአል፤ ሁሉም ነገር አደጋ ላይ ነው። በጨለመውና ፀጥታ በሰነፈነበት፣ በእግዚአብሔር ፊት መፀለዩንና ራሱን ዝቅ ማድረጉን ቀጠለ። በድንገት አንድ እጅ በትክሻው ላይ አረፈበት። ሕይወቱን የሚሻ ጠላት መሰለውና ተስፋ በቆረጠ ኃይል ከአጥቂው ጋር ታገለ። ጎህ መቅደድ ሲጀምር እንግዳው ከሰው በላይ የሆነውን ኃይሉን ተጠቀመ፤ በተነካ ጊዜ ኃያሉ ሰው የሰለለ መስሎ፣ በሲቃ እየለመነ እረዳተ-ቢስ ሆኖ በምስጢራዊ ተፎካካሪው አንገት ላይ ወደቀ። ያዕቆብ ከቃል ኪዳኑ መልአክ ጋር ሲታገል እንደነበረ አሁን አወቀ። ምንም እንኳን የአካል ጉዳተኛ የሆነና እጅግ ከባድ የህመም ስሜት ውስጥ የነበረ ቢሆንም አላማውን ግን አልተወም። በኃጢአቱ ግራ መጋባትን፣ ፀፀትንና ችግርን ለረጅም ጊዜ አስተናግዷል። አሁን ይቅር እንደተባለ ማረጋገጫ ማግኘት አለበት። መለኮታዊው ጎብኝ መሄድ የፈለገ መሰለ፤ ያዕቆብ ግን በረከትን በመለመን እንደያዘው ቀረ። መልአኩም “ሊነጋ አቅላልቶአልና ልቀቀኝ ልሂድ” አለው። ሆኖም የኃይማኖቱ አባት “ካልባረከኝ አልለቅህም” አለው። ምን አይነት መተማመን (ልበ ሙሉነት)፣ ምን አይነት አልነቃነቅ ባይነትና ጽናት ነው እዚህ ላይ የተንፀባረቀው! ይህ የትእቢትና በራስ የመተማመን መጠይቅ ቢሆን ኖሮ ያዕቆብ በቅጽበት በጠፋ ነበር፤ የእርሱ ተማጽዕኖ ግን ደካማነቱንና ዋጋ-ቢስነቱን የሚናዘዝ፣ ሆኖም ቃል-ኪዳን ጠባቂ በሆነ አምላክ ላይ የሚተማመን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር።GCAmh 445.2

    “መልአኩንም አሸነፈ፣ በረታም/He had power over the Angel, and prevailed” [ሆሴዕ 12÷4]። ራስን በማዋረድ፣ በፀፀትና ራስን በማስረከብ ይህ ኃጢአተኛ፣ ስህተትን የሚያደርግ ሟች፣ የሰማይን ግርማዊነት አሸነፈ። የሚንቀጠቀጥ እጁን በእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ አጣበቀ፤ መጠን-የለሽ የፍቅር ልብም የኃጢአተኛውን ተማጽዕኖ መልሶ ይሰድ ዘንድ አልተቻለውም። ለድሉ እንደማረጋገጫ፣ ሌሎችም የእርሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ለማበረታታት የኃጢአቱ ማስታወሻ የነበረው ስሙ ወደ ድሉ መታሰቢያነት ተቀየረ። ያዕቆብ እግዚአብሔርን ማሸነፍ የመቻሉ ጭብጥ ሰዎችንም ማሸነፍ እንደሚችል ማረጋገጫ ነበር። ጌታ የእርሱ ከለላ ነበርና፣ የወንድሙን ቁጣ ይገናኝ ዘንድ ከዚያ ወዲያ ፍርሃት አልነበረበትም።GCAmh 445.3

    በኃጢአቱ ምክንያት ያጠፋው ዘንድ መብት እንዳለው በመናገር ሰይጣን ያዕቆብን በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ከሶት ነበር፤ ይዘምትበት ዘንድም በኤሳው ላይ ተንቀሳቅሶ ነበር፤ በኃይማኖት አባቱ ረጅም የትግል ሌሊትም፣ ተስፋ ሊያስቆርጠውና እግዚአብሔርን የጨበጠበትን ሊያስለቅቀው ይቻለው ዘንድ ጥፋተኛ እንደሆነ እንዲሰማው ለማድረግ ሰይጣን በኃይል ይጥር ነበር። ያዕቆብ ተስፋ ወደ መቁረጥ አፋፍ ተጠግቶ ነበር፤ ሆኖም ያለሰማይ እርዳታ መጥፋቱ አይቀሬ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ታላቁን ኃጢአቱን ከልቡ ተፀፅቶአል፤ ለእግዚአብሔር ምሕረትም ተማፀነ። ከዓላማው ንቅንቅ የሚል አልነበረም፤ መልአኩን ግጥም አድርጎ ያዘ፤ እስሚሳካለትም ድረስ ልባዊ በሆነና ሲቃ በተሞላበት ጩኸት ጥያቄውን ገፋበት።GCAmh 446.1

    በያዕቆብ ላይ ይነሳ ዘንድ በኤሳው ተጽዕኖ ያሳደረው ሰይጣን በመከራው ዘመንም የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ያጠፏቸው ዘንድ ኃጥአንን ያነሳሳል። ያዕቆብንም እንደከሰሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይም ክሱን ይሰነዝራል። የእርሱ ተገዥ እንደሆነ አድርጎ ዓለምን ይቆጥራል፤ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቀው ትንሽ መንጋ ግን የበላይነቱን እየተቋቋው ነው። እነርሱን ከምድር ገጽ ማጥፋት ከቻለ ድሉ ሙሉ ይሆንለታል። ቅዱሳን መላእክት ሲጠብቁአቸው ያያል፤ ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸው መሆን አለበት ብሎም ይደመድማል፤ በላይኛው መቅደስ ጉዳያቸው እንደተወሰነ ግን አያውቅም። ያደርጓቸው ዘንድ የፈተነባቸውን ኃጢአቶች ልቅም አድርጎ ያውቃቸዋል፤ እነዚህንም ኃጢአቶች አጋኖ በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ፣ ልክ እንደ እርሱ ሁሉ እነዚህ ሰዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማጣት የሚገባቸው እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባቸዋል። ትክክለኛ ፍርድ የሚፈርድ ከሆነ ጌታ እርሱንና መልአክቱን አጥፍቶ የእነርሱን (የሕዝቡን) ኃጢአት ይቅር ማለት እንደማይችል ይናገራል። የእርሱ ግዳይ እንደሆኑ አስረግጦ በመናገር ያጠፋቸው ዘንድ ለእጁ ተላልፈው እንዲሰጡ ይጠይቃል።GCAmh 446.2

    ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በኃጢአታቸው ምክንያት ሲከሳቸው፣ ጥግ ድረስ እንዲፈትናቸው ጌታ ይፈቅዳል። በእግዚአብሔር ያላቸው መተማመን፣ እምነታቸውና ጽናታቸው በጥብቅ ይፈተናል። ያለፈውን ሲከልሱ ሳለ፣ ተስፋቸው ይሟሽሻል፤ በሕይወታቸው ሁሉ የሚያዩት መናኛ መልካምነት ነውና። ደካማነታቸውንና ጥቅመ-ቢስነታቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጉዳዮቻቸው ተስፋ-ቢስ እንደሆኑ፣ የቆሻሻነታቸው እድፍ ፈጽሞ ሊታጠብ የማይችል እንደሆነ በሚያደርግ ኃሳብ ሊያስበረግጋቸው ሰይጣን ይጥራል። በእንደዚህም ሁኔታ እምነታቸውን አውድሞ ለፈተናዎቹ እጅ እንዲሰጡ፣ ከእግዚአብሔር ጎራ ከመቆም ፈቀቅ እንዲሉ ተስፋ ያደርጋል።GCAmh 446.3

    ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ያጠፏቸው ዘንድ በቆረጡ ጠላቶቻቸው የሚከበቡ ቢሆንም የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸው [የሚሰቃዩበት ስቃይ] ግን ለእውነት ሲሉ በሚደርስባቸው የስደት ፍራቻ አይደለም። እያንዳንዱ ኃጢአታቸው ንስሐ አልተገባበትም ብለው ይፈራሉ፤ በራሳቸው ባለው አንዳንድ ድክመቶችም “በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ” [ራዕይ 3÷10] የሚለውን የአዳኙን ተስፋ ማስተዋል ይሳናቸዋል። ይቅር እንደተባሉ ማረጋገጫው ቢኖራቸው ከግርፋት ወይም ከሞት አያፈገፍጉም፤ ነገር ግን የተገባቸው አለመሆናቸውን ካረጋገጡ፣ በራሳቸው የባህርይ ግድፈት ምክንያት ሕይወታቸውን ቢያጡ፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ ስም ይነቀፋል።GCAmh 446.4

    በሁሉም አቅጣጫ የክህደት ሴራዎች ይሰማሉ፤ የዓመጽንም ሕያው ሥራ ይመለከታሉ። ከዚያም ይህ ታላቅ ክህደት ያበቃ ዘንድ፣ የክፉዎችም ኃጢአት መቋጫ ያገኝ ዘንድ ጠንካራ ፍላጎት፣ ልባዊ የሆነ የነፍስ መሻት በውስጣቸው ይነሳሳል። የአመጽን ሥራ ይቋቋሙ ዘንድ እግዚአብሔርን ሲማፀኑ ሳለ የክፋትን ኃይለኛ ማዕበል ለመቋቋምና ለመግፋት የቀራቸው ኃይል እንደሌላቸው ሲያዩ ራሳቸውን በጽኑ ይወቅሳሉ። ያላቸውን ኃይል ሁሉ ክርስቶስን ለማገልገል ቢጠቀሙበት ኖሮ፣ ከብርታት ወደ ብርታት እየተሸጋገሩ፣ ድል ያደርጓቸው ዘንድ የሰይጣን ኃይላት አቅም ከእነርሱ ይልቅ አናሳ ይሆን ነበር ብለው ያስባሉ።GCAmh 447.1

    “ጉልበቴን ይያዝ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ” [ኢሳ 27÷5] እያሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ነፍሳቸውን በማሰቃየት ባለፈው ንስሐ ስለገቡባቸው በርካታ ኃጢአቶች እያመለከቱ የአዳኙን ተስፋ ይማፀናሉ። ፀሎታቸው ወዲያውኑ ስላልተመለሰ እምነታቸው አይደክምም። እጅግ ከባዱን ድንጋጤ፣ ፍርሃትና ጭንቀት ቢያስተናግዱም ምልጃቸውን አያቋርጡም። ያዕቆብ መልአኩን እንደተጠማጠመ ሁሉ እነርሱም የእግዚአብሔርን ብርታት ይጠማጠማሉ፤ የነፍሳቸው ቋንቋም “ካልባረከኝ አልለቅህም” ይሆናል።GCAmh 447.2

    ያዕቆብ ብኩርናውን ያገኘበትን የማጭበርበር ኃጢአት ከአሁን ቀደም ባይናዘዝ ኖሮ እግዚአብሔር ፀሎቱን ባልሰማው፣ ሕይወቱንም ባልጠበቀለት ነበር። እንደዚሁም በፍርሃትና በስቃይ እየተገረፉ ሳለ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በፊታቸው ያለ፣ ያልተናዘዙት ኃጢአት ቢኖርባቸው ኖሮ ተሸናፊ በሆኑ ነበር፤ ተስፋ መቁረጥ እምነታቸውን ይበጥሰዋል፤ ይቤዣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ለመማፀን መተማመን አይኖራቸውም። ነገር ግን ያልተገባቸው የመሆናቸው ጥልቅ ስሜት ቢኖርም፣ የሚገለጥ፣ የተደበቀ ጥፋት አይኖርባቸውም። ኃጢአቶቻቸው ከወዲሁ ለፍርድ ቀርቦ ተወግደዋል፤ ወደ ማስታወስ ያመጧቸው ዘንድም አይቻላቸውም።GCAmh 447.3

    ተራ በሆኑ የሕይወት ጉዳዮች ላይ አለመታመናቸውን እግዚአብሔር እንዳላየ እንደሚያልፈው ያምኑ ዘንድ ሰይጣን ብዙዎችን ይመራቸዋል፤ ጌታ ያዕቆብን ያስተናገደበት ሁኔታ ግን ክፋትን በምንም አይነት እንደማያፀድቅ ያሳያል። ለኃጢአታቸው ምክንያት ለመፈለግ የሚደክሙ በሰማይ መጽሐፍትም ተመዝግበው (ኑዛዜ ሳይደረግባቸውና ይቅር ሳይባሉ) እንዲቀሩ የሚፈቅዱ እነርሱ በሰይጣን ይሸነፋሉ። ሙያቸው የበለጠ ከፍ ከፍ ያለ፣ የያዙት ስፍራም የበለጠ የተከበረ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር እይታ አካሄዳቸው የበለጠ ከባድ (አሳዛኝ) ይሆናል፣ የታላቁ ጠላታቸው ድልም በዚያው መጠን የበለጠ እርግጠኛ ይሆናል። ለእግዚአብሔር ቀን ለመዘጋጀት የሚዘገዩ እነርሱ ያንን ዕድል በመከራ ዘመን ወይም በቀጣይ ጊዜያት ያገኙት ዘንድ አይችሉም። የእንደዚህ ያሉት ሁሉ ጉዳይ ተስፋ-ቢስ ነው።GCAmh 447.4

    ሳይዘጋጁ ወደዚያ የሚያስፈራ የጦርነት ጊዜ የሚደርሱ ታማኝ [ነን ባይ] ክርስቲያኖች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው በሚለበልቡ፣ በሚሳቀዩ ቃላት ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ፣ ኃጥአን በጭንቀታቸው ሐሴት ያደርጋሉ። እነዚህ ኑዛዜዎች የኤሳው ወይም የይሁዳ አይነት ባህርይ ያላቸው ናቸው። እነዚህን ፀፀቶች የሚያደርጉ እነርሱ መተላለፍ በሚያስከትለው ውጤት ያዝናሉ እንጂ በበደሉ አይደለም [የሚያለቅሱት ከበደላቸው የተነሳ ሳይሆን መተላለፋቸው የሚያመጣባቸውን ቅጣት በመፍራት ነው]። እውነተኛ ፀፀት፣ ክፋትንም መፀየፍ አይሰማቸውም። ቅጣትን በመፍራት ለኃጢአታቸው እውቅና ይሰጣሉ። ሆኖም እንደ ጥንቱ ፈርኦን፣ ፍርድ ቢቀር ሰማይን ወደ መገዳደር ማንነታቸው ይመለሳሉ።GCAmh 448.1

    በተጨማሪም የተታለሉትን፣ የተፈተኑትንና ለኃጢአት ተላልፈው የተሰጡትን፣ ሆኖም በእውነተኛ ንስሐ ወደ እርሱ የተመለሱትን እግዚአብሔር እንደማይጥል የያዕቆብ ታሪክ ማረጋገጫ ነው። ይህንን መደብ ሰይጣን ለማውደም ሲጥር ሳለ፣ በአደጋ ጊዜ ያጽናኑአቸውና ይጠብቋቸው ዘንድ እግዚአብሔር መልአክቱን ይልካል። የሰይጣን ጥቃቶች ጽኑና የማያወላውሉ ማምታቻዎቹም አስከፊ ናቸው። የእግዚአብሔር አይን ግን በሕዝቦቹ ላይ ነው። ጆሮውም ጩኸታቸውን ይሰማል። ስቃያቸው ታላቅ ነው፤ የእቶኑ እሳት ነበልባል ሊበላቸው የተቃረበ ይመስላል። አንጥረኛው ጌታ ግን በእሳት የተፈተነ ወርቅ አድርጎ ያወጣቸዋል። እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ ተወዳዳሪ በሌለው የፈተናቸው ሰዓት የሚያሳየው ፍቀር እጅግ ብሩህ እንደሆነው የስኬት ዘመናቸው ጠንካራና ለስላሳ ነው። ሆኖም በእቶኑ እሳት ውስጥ መግባታቸው አስፈላጊ ነው። የክርስቶስ መልክ በፍጽምና ይንፀባረቅ ዘንድ ምድራዊነታቸው ተቃጥሎ መበላት አለበት።GCAmh 448.2

    በፊታችን ያለው የጭንቀትና የስቃይ ወቅት፣ ድካምን፣ መዘግየትንና ረሃብን መቋቋም የሚችል፣ በእጅጉ ቢፈተንም የማይደክም (የማይጠፋ) እምነትን የሚጠይቅ ነው። የምሕረት ጊዜ ለሁሉም የተሰጠው ለዚያ ጊዜ እንዲዘጋጁበት ነው። ያዕቆብ ትጉህና ቆራጥ ስለነበረ አሸነፈ። የእርሱ ድል ያለማያቋረጥ የሚነዘንዝ ፀሎት ኃይል ማስረጃ ነው። እርሱ እንዳደረገ ሁሉ የእግዚአብሔርን ተስፋ የሚጨብጡ እንደ እርሱም ልባዊና ጽኑ የሚሆኑ እነርሱ፣ ያዕቆብ እንደተሳካለት ይሳካላቸዋል። ራሳቸውን ለመካድ፣ በእግዚአብሔር ፊት ለመቃተት፣ ለባርኮቱም ለረጅም ጊዜ ከልብ ለመፀለይ ፈቃደኛ ያልሆኑ አያገኙትም። ከእግዚአብሔር ጋር መታገል - ምን እንደሆነ የሚያውቁት እንዴት ጥቂቶች ናቸው! በኃይለኛ ፍላጎት፣ እያንዳንዱ ጉልበት እስኪሟጠጥ ድረስ እግዚአብሔርን በመፈለግ ነፍሳቸውን የሚያገረጡ እንዴት ጥቂቶች ናቸው። ቋንቋ ሊገልፀው የማይችል የተስፋ መቁረጥ ማዕበል በሚለምነው ላይ ባለፈ ጊዜ፣ ፍንክች በማይል እምነት ከእግዚአብሔር ተስፋዎች ጋር የሚጣበቁ እንዴት ጥቂቶች ናቸው።GCAmh 448.3

    አሁን አለ ለማለት የሚከብድ እምነት የሚለማመዱ እነርሱ በሰይጣናዊ ማታለያዎችና ሕሊናን ለማስገደድ በሚወጣ ከባድ ኃይል ቁጥጥር ስር የመሆን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ፈተናውን መቋቋም ቢችሉ እንኳ በእግዚአብሔር መታመንን ልምዳቸው አላደረጉትምና በመከራ ዘመን ወደ ባሰ ጥልቅ ጭንቀትና ስቃይ ይዘፈቃሉ። ቸል ያሏቸውን የእምነት ትምህርቶች በከባድ የተስፋ መቁረጥ ግፊት ስር ሆነው ሊማሩ ይገደዳሉ።GCAmh 448.4

    ተስፋዎቹ እርግጥ እንደሆኑ እያረጋገጥን አሁን ከእግዚአብሔር ጋራ ራሳችንን ማለማመድ አለብን። ታማኝና ልባዊ የሆነን እያንዳንዱን ፀሎት መላእክት ይመዘግቡታል። ከእግዚአብሔር ጋራ ያለንን ግንኙነት ቸል ከምንል ይልቅ ራስ-ወዳድ ርካታዎቻችንን ብንተው ይበጀናል። የእርሱ ይሁንታ ያለው ስር የሰደደ ድህነትና ተወዳዳሪ የሌለው ራስን መካድ፣ ያለእርሱ እሽታ ከሚገኝ ሐብት፣ ክብር፣ ምቾትና ጓደኝነት ይልቅ ይሻላል። ለመፀለይ ጊዜ መውሰድ አለብን። በምድራዊ ፍላጎቶች አዕምሮዎቻችን እንዲወሰዱ ከፈቀድን፣ የወርቅ፣ የቤት ወይም የለም መሬት ጣኦቶቻችን ከእኛ በመውሰድ እግዚአብሔር ጊዜ ሊሰጠን ይችላል።GCAmh 449.1

    የእግዚአብሔርን በረከት መጠየቅ የሚችሉበት ካልሆነ በስተቀር፣ ወደየትኛውም መስመር ለመግባት እምቢ የሚሉ ከሆነ፣ ወጣቶች ኃጢአት ይሰሩ ዘንድ አይወሰወሱም። የመጨረሻውን ክቡር (ከባድ) ማስጠንቀቂያ ለዓለም የሚያደርሱ መልዕክተኞች በቀዘቀዘ፣ በተልፈሰፈሰና ስንፍና በሚያሳይ ሁኔታ ሳይሆን፣ ያዕቆብ እንዳደረገው በጥልቅ ፍላጎትና እምነት እግዚአብሔር ይባርካቸው ዘንድ ቢፀልዩ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፣ ሰውነቴም ድና ቀረች” [ዘፍ 32÷30] የሚሉበት ብዙ ስፍራ (ገጠመኞች) ያገኛሉ። እግዚአብሔርንም ሰውንም ለማሸነፍ ኃይል ያላቸው ተብለው በሰማይ እንደ ልዑላን ይቆጠራሉ።GCAmh 449.2

    “እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን” በቅርቡ በፊታችን ይከፈታል፤ አሁን የሌለንና ያገኙትም ዘንድ ብዙዎች እጅግ ሰነፎች የሆኑበት፣ ልምምድ የሚያስፈልገን ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ መከራ፣ በተግባር ከሚሆነው ይልቅ ሲያስቡት የበለጠ የገዘፈ ነው። ይህ [አገላለጽ] ግን በፊታችን ላለው ችግር ትክክል አይደለም። እጅግ እውነት አስመስሎ የሚያቀርብ ተወዳዳሪ የሌለው ገለፃ እንኳ የአበሳውን ዲካ ሊነካው አይችልም። በዚያ የመከራ ጊዜ፣ እያንዳንዱ ነፍስ በእግዚአብሔር ፊት ለራሱ መቆም ይኖርበታል። “[ኖህ፣ ዳንኤልና እዮብ በምድሪቱ ቢኖሩም] እኔ ሕያው ነኝና በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶችን ልጆቻቸውን አያድኑም ይላል ጌታ እግዚአብሔር” [ሕዝ 14÷20]።GCAmh 449.3

    አሁን፣ ሊቀ ካህናችን ስርየት እያደረገልን ሳለ በክርስቶስ ፍፁማን እንሆን ዘንድ መጣር ይገባናል። አዳኛችን በአንዲት ሃሳብ እንኳ ለፈተና ኃይል እጅ እንዲሰጥ መደረግ አልቻለም። በሰው ልብ ውስጥ ሰይጣን የሚንጠላጠልበት፣ እግሩን ማሳረፊያ አንዳች ነጥብ ያገኛል፤ የሆነ የኃጢአት ፍላጎት ይበረታታል፤ በዚህም አማካኝነት ፈተናዎቹ ኃይላቸውን ይገልጣሉ። ክርስቶስ ግን ስለራሱ ሲናገር፦ “የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም” [ዮሐ 14÷30] ይላል። ድል ይቀዳጅበት ዘንድ ሰይጣን በእግዚአብሔር ልጅ ዘንድ ማግኘት የቻለው አንዳች ነገር አልነበረም። የአባቱን ትዕዛዛት ጠብቋል፤ ሰይጣን ለራሱ ጥቅም ሊያውለው የሚችል ኃጢአት በእርሱ ዘንድ አልነበረም። በመከራ ዘመን የሚቆሙ እነርሱ ሊገኙበት የሚገባቸው ሁኔታ ይህ ነው።GCAmh 449.4

    በሚያስተሰርየው የክርስቶስ ደም በማመን ራሳችንን ከኃጢአት መለየት ያለብን በዚህ ሕይወት ነው [በምድር ነው]። ራሳችንን ከእርሱ ጋር እንድናቆራኝ፣ ድክመታችንን ከእርሱ ብርታት ጋር፣ ድንቁርናችንን ከእርሱ ጥበብ ጋር፣ ያልተገባን መሆናችንን የተገባው ከሆነው ከእርሱ ሥራ ጋር እንድናዋህድ ውዱ አዳኛችን ይጋብዘናል። የእግዚአብሔር አቅርቦት የየሱስን የዋህነትና ትህትና የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው። እኛ የምንመርጠውን፣ የበለጠ ቀላልና አስደሳች የሚመስለውን ሳይሆን የሕይወትን እውነተኛ አላማዎች ሁልጊዜ ጌታ በፊታችን ያደርግልናል። ባህርያቶቻችን ከመለኮት ምሳሌ ጋር አንድ ይሆኑ ዘንድ በሚሰራው ሥራ ላይ ሰማይ ከሚቀጥራቸው ወኪሎች ጋር መተባበር የእኛ ፈንታ ነው። ማንም ይህንን ሥራ ቸል የሚል ወይም በኋላ ይደርሳል የሚል፣ ሕይወቱን እጅግ አስፈሪ በሆነ አደጋ ውስጥ ከመክተት አያመልጥም።GCAmh 449.5

    ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይ አንድ ታላቅ ድምጽ እንዲህ ሲል ሰማ፦ “በምድርና በባህር ለምትኖሩ ግን ወዮላችሁ። ዲያቢሎስ ወርዶባችኋልና በእርሱም ታላቅ ቁጣ አለበት ጥቂት ዘመን እንደቀረለት ያውቃልና” [ራዕይ 12÷12]። ከሰማያዊው ድምጽ ይህንን ጩኸት የሚጋብዙ ትዕይንቶች አስፈሪዎች ናቸው። የቀረው ጊዜ እያጠረ በሄደ መጠን የሰይጣን ቁጣ እየጨመረ ይሄዳል፤ የማታለልና የማውደም ሥራውም በመከራው ዘመን የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳል።GCAmh 450.1

    የተዓምር-ሰሪ አጋንንትን ኃይል የሚገልጡ፣ ከሰው ኃይል በላይ የሆነ ባህርይ ያላቸው አስፈሪ ትዕይንቶች በቅርቡ በሰማያት ይገለጣሉ። በማታለል አጥብቀው ይይዟቸው ዘንድ፣ የሰማይንም አስተዳደር ይቃወሙ ዘንድ በሚደረገው የመጨረሻ ትግል ከሰይጣን ጋር እንዲተባበሩ ይገፋፏቸው ዘንድ የአጋንንት መናፍስት ወደ ምድር ነገሥታትና ወደ ዓለም ሁሉ ይሄዳሉ። በእነዚህ ወኪሎች አማካኝነት ገዥዎችና ተገዥዎች፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ይታለላሉ። ለዓለም አዳኝ የሚገባውን ማዕረግና አምልኮ ይገባናል የሚሉ፣ ክርስቶስን ራሱን የሚያስመስሉ ሰዎች ይነሳሉ። ግሩም የሆኑ የመፈወስ ተዓምራት ያደርጋሉ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርን የሚቃረኑ፣ ከሰማይ የመጡ መገለጦች እንዳሏቸውም ይናገራሉ።GCAmh 450.2

    በሚመጣው የማጠቃለያ የማታለል ትወና፣ ሰይጣን ራሱ ክርስቶስን መስሎ ይቀርባል። የተስፋዋ መደምደሚያ አድርጋ ወደ መሲሁ መምጣት እንደምታንጋጥጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ መስክራለች። አሁን ታላቁ አታላይ ክርስቶስ እንደመጣ ያስመስላል። ሰይጣን፣ በራእይ መጽሐፍ በዮሐንስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ልጅ ባህርያት ተመስሎ በሚያስደንቅ ብርሐን ወይም ነፀብራቅ ግርማ ሞገስ ተላብሶ በተለያዩ የምድሪቱ ክፍሎች በሰዎች ዘንድ ራሱን ይገልጣል [ራእይ 1÷13-15]። የሚከበው ክብር የፍጡር አይኖች እስካሁን ካዩአቸው በላይ የሚልቅ ነው። የድል ድምጽ በህዋው ያስተጋባል፤ “ክርስቶስ መጥቷል! ክርስቶስ መጥቷል!።” በምድር ሳለ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በባረከበት አኳኋን፣ እጆቹን አንስቶ ሲባረካቸው ሳለ ሕዝቡ በፊቱ በመስገድ ያመልኩታል። ድምፁ ለስላሳና ገራም ነው፤ ሆኖም ጥዑመ ዜማ ያለው ነው። በለሆሳስና ርኅራኄ በሚያስተጋቡ ቃናዎች፣ አዳኙ የተናገራቸውን፣ የተወሰኑ ተመሳሳይ፣ የተከበሩ ሰማያዊ እውነቶችን ያቀርባል። የሕዝቡን ደዌ ይፈውሳል፤ በተላበሰው የክርስቶስ ባህርይም ሰንበትን ወደ እሁድ እንደቀየረ በመናገር የባረከውን ቀን እንዲቀድሱ ሁሉንም ያዛቸዋል። ሰባተኛውን ቀን በቅድስና በመጠበቅ የሚፀኑ እነርሱ፣ በብርሐንና በእውነት ወደ እነርሱ የተላኩትን መላዕክት አንሰማም በማለት ስሙን እንደሚያረክሱ ይናገራል። ይህ ጠንካራው፣ ድል ሊነሳ ምንም የማይቀረው ማሳሳቻ ነው። ልክ በስምኦን ማጉስ እንደተታለሉት ሰማርያዊያን ሁሉ፣ ከታናናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ፣ እልፍ አዕላፋት፦ ይህ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ነው” እያሉ ለእነዚህ አስማቶች ጆሮ ይሰጣሉ [የሐዋ ሥራ 8÷10]።GCAmh 450.3

    የእግዚአብሔር ሕዝቦች ግን አይሳሳቱም። የዚህ የሐሰተኛ ክርስቶስ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መሰረት አይደሉም። የሚባርካቸው አውሬውንና ምልክቱን የሚያመልኩቱን ነው፤ እነዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ያልተቀላቀለ ቁጣ የሚወርድባቸው፣ እነዚያው ህዝቦች፣ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።GCAmh 451.1

    በተጨማሪም የክርስቶስን ዳግም ምፅዓት ሁናቴ ሰይጣን አስመስሎ እንዲያሳይ አይፈቀድለትም። በዚህ ነጥብ ላይ ስላለው ማታለል አዳኙ ሕዝቦቹን አስጠንቅቋል፤ የዳግም ምፅዓቱን ክስተትም አስቀድሞ በግልጽ ተናግሯል። “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነብያት ይነሳሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ… እንግዲህ እነሆ በበረሃ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፣ እነሆ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ አትመኑ። መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና” [ማቴ 24÷24-27፣31፤ 25÷31፤ ራዕይ 1÷7፤ 1ኛ ተሰሎ 4÷16፣17]። ይህ ምፅዓት ተመሳስሎ ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ የለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ — በመላው ዓለም የሚታይ ይሆናል።GCAmh 451.2

    የመጽሐፍ ቅዱስ ትጉህ ተማሪዎች የሆኑ፣ የእውነትንም ፍቅር የተቀበሉ እነርሱ ብቻ ዓለምን በምርኮ ከሚይዘው ኃይለኛ ማታለያ የሚከለሉ ይሆናሉ። አታላዩ መልኩን ለውጦ ሌላ ቢመስልም በመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት አማካይነት፣ እነዚህ፣ የሚለዩት ይሆናሉ። ፈታኙ ሰዓት ለሁሉም ይመጣል፤ በፈተና ወንፊት ተነፍቶ እውነተኛው ክርስቲያን ይለያል። የስሜት ህዋሳቶቻቸው ለሚያቀርቡላቸው መረጃዎች እጅ ላለመስጠት እስኪችሉ ድረስ፣ አሁን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቃሉ በጥብቅ ተመስርተዋልን? እንደዚህ ባለ የችግር ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ብቻ ይጣበቃሉን? ሰይጣን፣ የሚቻለው ከሆነ፣ በዚያ ቀን ለመቆም የሚያስችላቸው ዝግጅት ከማድረግ ይገድባቸዋል። መንገዶቻቸውን ለማጠር ነገሮችን በማደራጀት፣ በምድራዊ ኃብት ይተበትባቸዋል፣ ልባቸው በዚህ ምድር ሕይወት ጣጣ ጢም ይል ዘንድ ከባድና አድካሚ ሸክም እንዲሸከሙ ያደርጋቸዋል፤ የፈተና ቀንም እንደሌባ ይደርስባቸዋል።GCAmh 451.3

    ትዕዛዛቱን የሚጠብቁትን በመቃወም በክርስትናው ዓለም ከተለያዩ መሪዎች የሚወጡ አዋጆች፣ ከመንግሥት የሚያገኙትን ጥበቃ በማስቀረት፣ ሊያጠፏቸው ለሚፈልጉ ሰዎች በሚተውበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከከተማዎችና ከመንደሮች ሸሽተው፣ አንድ ላይ በመሰባሰብ እጅግ ምድረበዳና ጭር ባሉ ቦታዎች መኖር ይጀምራሉ። በተራራ ምሽጎች ብዙዎች ከለላ ያገኛሉ። ልክ እንደ ፒድሞንት ሸለቆ ክርስቲያኖች፣ መኖሪያዎቻቸውን የምድር ታላላቅ ስፍራዎችን ያደርጋሉ። ለ “ጠንካራ አምባ”ም (“munitions of rocks”) እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ [ኢሳ 33÷16]። ነገር ግን በሁሉም አገራት ያሉ ብዙዎች፣ በሁሉም መደብ ያሉ፣ በከፍታም በዝቅታም ያሉ፣ ሃብታሞችና ድሆች፣ ጥቁሮችና ነጮች ፍርደ-ገምድል ወደሆነና ጨካኔ ወደተሞላበት ባርነት ይጣላሉ። በሰንሰለት ተጠፍረው፣ በእስር ቤት አጥር ተዘግተው፣ ሞት ተፈርዶባቸው፣ አንዳንዶቹም ጨለማና ቀፋፊ ወህኒ ቤቶች በረሃብ እንዲሞቱ ተትተው፣ የእግዚአብሔር ውዶች አድካሚ ቀናቸውን ይገፋሉ። ማቃሰታቸውን ይሰማ ዘንድ የሚከፈት የሰብአዊ ፍጡር ጀሮ የለም፤ ይረዳቸው ዘንድ የተዘጋጀ የሰብአዊ ፍጡር እጅ የለም።GCAmh 451.4

    በዚህ ፈታኝ ሰዓት እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ይረሳልን? በውኃ ጥፋት ዘመን በነበረው ዓለም ላይ ፍርድ በጎበኘ ጊዜ ታማኙን ኖህን ረሳውን? የደልዳላ ስፍራውን ከተሞች ያጠፋ ዘንድ እሳት ከሰማይ በወረደ ጊዜ ሎጥን ረሳውን? በግብጽ በጣዖት አምላኪዎች ተከቦ የነበረውን ዮሴፍን ረሳውን? ወይስ ዕጣ ፈንታው እንደ በአል ነብያት እንደሚሆን ኤልዛቤል በማለችበት ጊዜ ኤልያስን ረሳውን? በጨለማና በሚያንገሸግሽ የእስር ቤት ጉድጓድ በነበረበት ጊዜ ኤርምያስን ረሳውን? ሶስቱንም ጀግኖች በእቶን እሳት ውስጥ፣ ወይስ ዳንኤልን በአናብስት ጉድጓድ ረሳቸውን? “ጽዮንም አለች፦ እግዚአብሔር ጣለኝ፣ ጌታዬም ረሳኝ፤ በውኑ ሴት ከማህፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን እርስዋ ትረሳ ይሆናል፤ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ እኔ በእጄ መዳፍ ቀርጨሻለሁ” [ኢሳ 49÷14-16]። የሰራዊት ጌታ አለ፦ “የሚነካችሁ የአይኔን ብሌን የሚነካ ነው።” [ዘካ 2÷8]።GCAmh 452.1

    ጠላቶች ወደ እስር ቤት ቢወረውሯቸውም፣ የወህኒ ቤቱ ግድግዳዎች በነፍሳቸውና በክርስቶስ ያለውን ግንኙነት ይቆርጡት ዘንድ አይችሉም። እያንዳንዱን ድክመታቸውን የሚያይ፣ እያንዳንዱን ፈተና የሚያውቅ እርሱ ከምድራዊ ኃይላት ሁሉ በላይ ነው፤ ከሰማይ ብርሐንና ሰላም ይዘው መላእክት ወደ ተገለሉ የእስር ቤት ክፍሎቻቸው ይመጣሉ። የእምነት ባለፀጎች እዚያ ይኖራሉና እስር ቤት እንደ ቤተ መንግሥት ይሆናል። በፊልጵስዩስ ወህኒ ቤት ጳውሎስና ሲላስ በእኩለ ሌሊት ሲፀልዩና የምስጋና መዝሙር ሲያቀርቡ እንደሆነው ሁሉ የደበዘዙ ቀፋፊ ግድግዳዎች በሰማያዊ ብርሐን ይፈካሉ።GCAmh 452.2

    ሕዝቦቹን ለመጨቆንና ለማጥፋት በሚሹ ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ ይጎበኛል። ለኃጥአን የሚያሳየው ረጅም ትዕግስት ሰዎች [ሕግን] በመተላለፍ ውስጥ የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ሆኖም ለረጅም ጊዜ እንዲዘገይ የተደረገ ነውና ቅጣታቸው እርግጥና አሰቃቂ ነው። “እግዚአብሔር ይነሳልና በጵራፂም ተራራ እንደነበረ፣ በገባኦን ወንዝ እንደነበረ ይቆጣል። ሥራውን ያደርግ ዘንድ፣ እንግዳ ሥራውን፣ አደራረጉን ያደርስ ዘንድ ያልታወቀውን አደራረግ” [ኢሳ 28÷21]። ለመሐሪው አምላካችን የቅጣት ድርጊት እንግዳ አድራጎት ነው። “እኔ ሕያው ነኝ ይላል እግዚአብሔር አምላክ፣ የኃጢአተኛውን ሞት አልሻም” [ሕዝ 33÷11]። እግዚአብሔር “መሐሪ፣ ፀጋ ያለው፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ባለታላቅ ቸርነትና እውነት”፤ “ጠማማነትንና መተላለፍን፣ ኃጢአትንም የሚሰረይ”፤ “በደለኛውንም ከቶ የማያነፃ” “እግዚአብሔር ታጋሽ፣ ኃይሉም ታላቅ ነው፤ ኃጢአተኛውንም ንፁህ ነህ አይልም” [ዘፀ 34÷6፣7፤ ናሆም 1÷3]። በጽድቅ በሚፈጸሙ አስፈሪ ድርጊቶቹ የተረገጠውን የሕጉን ስልጣን ያስመሰክራል። ተላላፊውን የሚጠብቀው ቅጣት ክብደት፣ ጌታ ፍርድን ለመፈፀም በሚዘገይበት [ጊዜ] መጠን ሊመዘን ይችላል። በእግዚአብሔር መዝገብ ያለውን የኃጢአት መስፈሪያ እስኪሞላ ድረስ የማይመታው፣ ለረጅም ጊዜ የታገሰው ሕዝብ (አገር)፣ በስተመጨረሻ ከምሕረት ጋር ያልተቀላቀለውን የቁጣ ጽዋ ይጠጣል።GCAmh 452.3

    ክርስቶስ በቤተ መቅደሱ የማማለድ ሥራውን ሲያቆም፣ አውሬውንና ምስሉን የሚያመልኩትን ምልክቱንም የሚቀበሉትን እንደሚያገኝ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት ያልተቀላቀለው ቁጣ [ራዕይ 14÷9፣10] ይወርዳል። እሥራኤልን ነፃ ሊያወጣ በነበረበት ጊዜ በግብጽ ላይ የወረዱት መቅሰፍቶች፣ ልክ ከእግዚአብሔር ሕዝቦች መዳን በፊት በዓለም ላይ ከሚወርዱት፣ የበለጠ አሰቃቂና ሰፊ ከሆኑት፣ ቅጣቶች ጋር የባህርይ ተመሳሳይነት አላቸው። ስለእነዚህ ዘግናኝ ስቃዮች ገላጩ [የሱስ] ሲናገር፦ “የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው። ባህሩ “እንደሞተም ሰው ደም ሆነ፤ በባህርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ”፤ “በፈሳሽ ውኃ፣ በውኃውም ምንጭ ሁሉ ላይ ደም ሆነ” [ራዕይ 16÷2-6]። እነዚህ ጥቃቶች አሰቃቂ ቢሆኑም የእግዚአብሔር ፍርድ ግን ሙሉ በሙሉ ትክክል መሆኑ ይረጋገጣል። የጌታ መልአክ ይናገራል፦ “አንተ ፃድቅ ነህ አቤቱ….በዚህ ፈርደሃልና። የቅዱሳንና የነብያትን ደም አፍሰዋልና ደምንም ሰጠኃቸው ይጠጡ ዘንድ ይገባቸዋልና” [ራዕይ 16÷2-6]። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሞት ኩነኔ በማሳረፋቸው፣ ደሙን በራሳቸው እጅ የማፍሰሳቸውን ያህል የደማቸውን ኩነኔ በራሳቸው ላይ አምጥተዋል። ከአቤል ዘመን ጀምሮ ለፈሰሰው የቅዱሳን ደም ሁሉ፣ ጥፋተኛ እንደሆኑ አድርጎ በእርሱ ዘመን የነበሩትን አይሁዳዊያን ክርስቶስ ተናገራቸው፤ ምክንያቱም ከእነዚህ የነብያት አራጆች ጋር ተመሳሳይ መንፈስ የነበራቸው፣ ያንኑ ተመሳሳይ ሥራም ለመፈፀም የሚሹ፣ ስለሆኑ ነበር።GCAmh 452.4

    በሚቀጥለው መቅሰፍት፣ ፀሐይም ኃይል ተሰጣት “ሰውንም በእሳት ታቃጥል ዘንድ። ሰዎችም ታላቅ መቃጠል ተቃጠሉ” [ራዕይ 16÷8፣9]። በዚህ አስፈሪ ሰዓት የምድርን ሁኔታ ነብያት እንዲህ ይገልፁታል፦ “ምድር አለቀሰች፤ እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአልና የምድር ዛፎች ሁሉ ደረቁ፤ ደስታ ከሰው ልጆች ረግፎአልና።” “ዘሩ ከምድር በታች በሰበሰ፤ ጎተሮች ፈረሱ።” “እንስሶች ስለምን አለቀሱ! የላሙ መንጋ መሰማሪያ የለውምና ጮኹ….የውኃው ፈሳሽ ሁሉ ደርቋልና እሳትም የምድረበዳውን መሰማሪያ በላች።” “የመቅደሱ የምስጋናው ዜማ ወደ ዋይታ ይለወጣል ይላል እግዚአብሔር አምላክ። የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፤ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል” [ኢዮኤ 1÷10-12፣17-20፤ አሞጽ 8÷3]።GCAmh 453.1

    እነዚህ መቅሰፍቶች ዓለም አቀፋዊ አይደሉም፤ እንዲያማ ቢሆን የምድር ነዋሪዎች ሁሉ በጠፉ ነበር። ሆኖም ፍጡር ከሚያውቃቸው መቅሰፍቶች ሁሉ ይልቅ እጅግ የከፉት ይሆናሉ። ከምሕረት ጊዜ መደምደሚያ በፊት ባሉ ሰዎች ላይ የወረዱ መዓቶች ሁሉ በምሕረት የተቀላቀሉ ናቸው። የሚማፀነው የክርስቶስ ደም ኃጢአተኛው የበደሉን ሙሉ ስፍር ከመቀበል ከልሎታል፤ በመጨረሻው ፍርድ ግን የሚወርደው ቁጣ ከምሕረት ጋር ያልተቀላቀለ ነው።GCAmh 453.2

    በዚያ ቀን ለረጅም ዘመን ያቃለሉትን የእግዚአብሔር ምሕረት ከለላ እልፍ አዕላፋት ይፈልጉታል። “እነሆ በምድር ላይ ረሃብን የምሰድበት ዘመን ይመጣል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። ከባህር እስከ ባህር ድረስ፣ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ። የእግዚአብሔርን ቃል በመሻት ይሯሯጣሉ፤ አያገኙትምም።” [አሞጽ 8÷11-12]።GCAmh 453.3

    የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከስቃይ ነፃ አይሆኑም። ቢሳደዱና ቢጨነቁ፣ በድህነት ቢያልፉ፣ ምግብ በማጣትም ቢቸገሩ፣ እንዲጠፉ ግን አይተውም። ለኤልያስ የተጠነቀቀ ያ እግዚአብሔር ራሳቸውን መስዋዕት ከሚያደርጉ ልጆቹ መካከል አንዱን እንኳ ዝም ብሎ አያልፈውም። የራስ ፀጉራቸውን ቁጥር የሚያውቅ ይጠነቀቅላቸዋል፤ በረሃብ ጊዜም ይጠግባሉ። ኃጢአን በረሃብና በቸነፈር ሲሞቱ ሳለ፣ መላእክት ፃድቃንን ይከልሏቸዋል፤ የሚያስፍለጋቸውንም ያቀርቡላቸዋል። “በጽድቅ ለሚራመድ ለእርሱ” የተሰጠው ተስፋ “እንጀራም ይሰጠዋል፤ ውኃውም የታመነች ትሆናለች”፤ ” ድሆችና ችግረኞች ውኃ ይሻሉ አይገኝምም፤ ምላሳቸውም በጽማት ደረቀ። እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፤ እኔ የእሥራኤል አምላክ አልጥላቸውም።” [ኢሳ 33÷16፤ 41÷17]።GCAmh 453.4

    “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይን ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎች ከጋጥ ቢጠፉ፣ ላሞችም ከበረት ውስጥ ባይገኙ”ም የሚፈሩት ግን “በአምላክ ደስ” ይሰኛሉ፤ በመድኃኒታቸውም አምላክ ሐሴት ያደርጋሉ [እንባ 3÷17-18]።GCAmh 454.1

    “እግዚአብሔር ጠባቂህ ነው፤ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ ጥላህ ነው። ፀሐይ በቀን ጨረቃም በሌት አይመታህም። እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ነፍስህንም ይጠብቃታል።” “እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፣ ያድንሃልና ከሚያጠፋም ቸነፈር። ፊትህን በላቦቹ ይሰውርሃል፤ ከክንፎቹም በታች ትጠጋለህ፤ እውነቱም ጋሻና ምግብ ትሆንልሃለች። ከሌሊት ግርማ አትፈራም፤ በቀን ከሚበረውም ፍላፃ። በጨለማም ከሚሄድ ቸነፈር፣ በቀትርም ከሚያጠፋ በሽታ። ባጠገብህ ሺህ፣ በቀኝህም እልፍ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይደርስም፤ ብቻ በአይንህ ትመለከተዋለህ። የኃጥአንንም ብድራት ታያለህ። አንተ እግዚአብሔርን መታመኛዬ ነህ፣ ብለሃልና ልዑልንም ለመኖሪያህ አደረግህ። ክፉ ነገር አያገኝህም፣ መቅሰፍትም ወደ ድንኳህ አይቀርብም።” [መዝ 121÷5-7፤ 91÷3-10]።GCAmh 454.2

    ሆኖም ለሰብአዊ ፍጡር እይታ የእግዚአብሔር ሕዝቦች፣ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት ሰማዕታት፣ በቅርቡ ምስክርነታቸውን በደማቸው ለማተም የሚገደዱ ይመስላል። በጠላቶቻቸው እጅ ይወድቁ ዘንድ እግዚአብሔር እንደተዋቸው አድርገው ራሳቸው መፍራት ይጀምራሉ። ጊዜው አስፈሪ የስቃይ ጊዜ ነው። ይቤዣቸው ዘንድ ቀንና ሌት ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ። ኃጥአን ይፈነድቃሉ፤ የፌዝ ጩኸታቸውም ይሰማል። “አሁን እምነታችሁ የታለ? በእርግጥ የእርሱ ሕዝቦች ከሆናችሁ እግዚአብሔር ከእጃችን ለምን አላዳናችሁም?” የሚጠባበቁት ግን፣ የሱስ በቀራንዮ መስቀል በሞት አፋፍ ላይ ሳለ የካህናት አለቆችና ገዥዎች በማላገጥ “ሌሎችን አዳነ፣ ራሱን ማዳን አይችልም፤ የእሥራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን” [ማቴ 27÷42] ሲሉ የተናገሩትን ያስታውሳሉ። ልክ እንደ ያዕቆብ ሁሉም ከእግዚአብሔር ጋር እየታገሉ ናቸው። ገጽታቸው የውስጥ ትግላቸውን ይገልፃል። ፊታቸው ገርጥቶአል። ሆኖም ልባዊ ምልጃቸውን አያቋርጡም።GCAmh 454.3

    ሰዎች፣ በሰማያዊ እይታ ማየት ቢችሉ ኖሮ፣ በኃይል የላቁ የመላእክት ቡድኖች የክርስቶስን የትዕግስት ቃል በጠበቁት ዙሪያ ሰፍረው ይመለከቱ ነበር። ኃዘኔታ ባለው ትህትና መላእክት ጭንቀታቸውን አይተዋል፤ ፀሎታቸውንም ሰምተዋል። ከጥፋት ይነጥቋቸው ዘንድ የመሪያቸውን ቃል በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ትንሽ ጊዜ ግን መቆየት አለባቸው። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጽዋውን መጠጣት፣ በጥምቀትም መጠመቅ አለባቸው። ህመም የሆነው ያ መዘግየት ራሱ የጥያቄዎቻቸው ሁነኛው መልስ ነው። ጌታ እንደሚሰራ አምነው ለመቆየት ሲታገሉ ሳለ፣ በኃይማኖታዊ ልምምዳቸው ጊዜ በተግባር ያልተለማመዷቸውን እምነትን፣ተስፋንና ትዕግስትን እንዲለማመዱ ይመራሉ። ሆኖም ስለ ተመረጡት ሲባል የመከራው ጊዜ እንዲያጥር ይሆናል። “እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሳቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል” [ሉቃስ 18÷7፣8]። ሰዎች ከሚጠብቁት ይልቅ ፈጥኖ መጨረሻው ይመጣል። ለእግዚአብሔር ጎተራ ስንዴው ተሰብስቦ ነዶው ይታሰራል፤ እንክርዳዱም ተቃጥሎ ይጠፋ ዘንድ ለማገዶነት ይታሰራል።GCAmh 454.4

    ሰማያዊ ዘቦች፣ ለአደራቸው ታማኝ ሆነው፣ ጥበቃቸውን ይቀጥላሉ። ትዕዛዛት ጠባቂዎች የሚገደሉበትን ጊዜ የሚወስን አጠቃላይ አዋጅ ቢነገርም፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ጠላቶቻቸው አዋጁ እንደቀረበ በመገመት፣ ከታቀደው ጊዜ በፊት፣ ሊገድሏቸው ጥረት ያደርጋሉ። ነገር ግን በእያንዳንዱ ታማኝ ነፍስ ዙሪያ የሰፈሩትን ኃያል ጠባቂዎች ማንም ሊጥስ አይቻለውም። ከከተሞችና ከመንደሮች ሲሳደዱ አንዳንዶች ይጠቃሉ፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ የተቀሰረው ሰይፍ እንደ ገለባ ኃይል አልባ ሆኖ ተሰባብሮ ይወድቃል። ሌሎች ደግሞ የጦር ሰዎችን ምስል በያዙ መላእክት ይጠበቃሉ።GCAmh 455.1

    በዘመናት ሁሉ፣ በቅዱሳን መላእክት በኩል ሕዝቦቹን ለመርዳትና ለማዳን እግዚአብሔር ሰርቷል። ሰማያዊ ፍጡራን በሰዎች ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል። እንደ መብረቅ በሚያንፀባርቅ ልብስ ሆነው ታይተዋል፤ የተጓዥ ልብስ ለብሰው፣ እንደ መንገደኛ ሰዎች ሆነው፣ መጥተዋል። መላእክት የሰው ቅርጽ ይዘው ለእግዚአብሔር ሰዎች ተገልጠዋል። እንደደከማቸው አይነት ሆነው በቀትር በዋርካ ዛፍ ስር አርፈዋል። የሰዎችን ቤት መስተንግዶ ተቀብለዋል። በጨለማ ለተዋጡ ተጓዦች እንደ መንገድ መሪ ሆነዋል። በራሳቸው እጅ የመሰዊያውን እሳት አቃጥለዋል። የእስር ቤት በሮችን ከፍተዋል፤ የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ነፃ አውጥተዋል። በሰማይ አልባሳት አጊጠው ከአዳኙ መቃብር ድንጋዮችን ለማንከባለል መጥተዋል።GCAmh 455.2

    የሰው ግዝም ይዘው፣ መላእክት፣ ፃድቃን በተሰበሰቡበት ሁልጊዜ ይገኛሉ፤ የእግዚአብሔርን ትዕግስት ወሰን ማለፋቸውን አለማለፋቸውን ለመወሰን፣ ሥራቸውን ይመዘግቡ ዘንድ፣ ልክ ወደ ሰዶም እንደሄዱ፣ መላእክት የኃጥአንን ስብሰባዎች ይጎበኛሉ። ጌታ በምሕረት ደስ ይለዋል፤ በእርግጥ ለሚያገለግሉት ለጥቂቶች ሲል፣ መቅሰፍቶችን ይገድብና፣ የሰዎችን ሰላምና ፀጥታ ያራዝማል። እግዚአብሔርን የሚበድሉ ኃጢአተኞች፣ ለራሳቸው ሕይወት ለሚያገኙት ደህንነት፣ ሲሳለቁባቸውና ሲጨቁኑዋቸው ደስ ለሚላቸው፣ ለጥቂት ታማኞች ምን ያህል ባለእዳ እንደሆኑ አያስተውሉም።GCAmh 455.3

    የዚህ ዓለም ገዥዎች ባያውቁትም፣ አብዛኛውን ጊዜ በመማክርቶቻቸው፣ መላእክት ቃል አቀባዮች ናቸው። የሰብአዊ ፍጡር አይን ተመልክቶአቸዋል፤ ልመናቸውን የሰው ጀሮ ሰምቶአል፤ የሰው ከናፍርት ያቀረቡትን ኃሳብ ተቃውመዋል፤ ምክራቸውንም ተሳልቆበታል፤ የሰው እጆች በስድብና ባልተገባ ተግባር ተገናኝቷቸዋል። በምክር ቤት አዳራሾችና በፍርድ ሸንጎዎች እነዚህ ሰማያዊ መልዕክተኞች፣ ከሰው ታሪክ ጋር ቅርበት ያለው ትውውቅ እንዳላቸው አሳይተዋል። ተወዳዳሪ ከሌላቸው፣ አንደበተ ርቱዕ ተከራካሪዎች ይልቅ የጭቁኖችን ጉዳዮች ይግባኝ በማለት የተሻሉ እንደሆኑ አረጋግጠዋል። የእግዚአብሔርን ሥራ አዝጋሚ ሊያደርጉ፣ በሕዝቦቹም ላይ ታላቅ ስቃይ ሊያመጡ ይችሉ የነበሩትን ውጥኖች አክሽፈዋል፤ ክፋቶችን አምክነዋል። በአደጋና በጭንቀት ሰዓት “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” [መዝ 34÷7]።GCAmh 455.4

    በልባዊ ናፍቆት የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚመጣውን ንጉሳቸውን ምልክቶች ይጠባበቃሉ። ጉበኞች ጠበቅ ተደርገው እንደተጠየቁት፣ “ሌሊቱ ምን ያህል ነው?” መልሱም ያለማወላወል ተሰጠ፦ “‘ይነጋል ደግሞም ይመሻል’ [ኢሳ 21÷11፣12]። ከተራሮች ቁንደዶ በላይ፣ በደመናዎች ላይ ብርሐን እያንፀባረቀ ነው። በቅርቡ የክብሩ መገለጥ ይሆናል። የጽድቅ የፀሐይ ብርሐን ሊያንፀባርቅ ተቃርቦአል። ለፃድቃን ማብቂያ የሌለው ቀን የሚጀምርበት፣ ለኃጥአን ደግሞ ዘላለማዊ ጨለማ የሚሰፍንበት — ጠዋቱና ማታው በደጅ ናቸው።”GCAmh 456.1

    የሚታገሉት እነርሱ አቤቱታቸውን በእግዚአብሔር ፊት ሲማፀኑ ሳለ ከማይታየው የጋረዳቸው መጋረጃ ሊገለጥ ምንም ያልቀረው ይመስላል። በዘላለማዊ ቀን ንጋት ወገግታ ሰማያት ይፈካሉ፤ እንደ መላእክት ጥዑመ ዜማም ቃላቱ ወደ ጆሮ ይገባል “ታማኝ ለሆናችሁለት ፀንታችሁ ቁሙ፤ እርዳታ እየመጣ ነው።” ክርስቶስ፣ ሁሉን በሁሉ የሆነው አሸናፊ ለደከሙ ወታደሮቹ የዘላለም ክብር ዘውድ እጁን ዘርግቶ ይዟል፤ ገርበብ ካሉት በሮችም ድምጹ ይመጣል፦ “እዩ፣ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፣ አትፍሩ። ኃዘናችሁን አውቃለሁ፤ ኃዘናችሁን ተሸክሜያለሁ። እየተዋጋችሁ ያላችሁት ያልተሞከሩ ጠላቶችን አይደለም፤ በእናንተ ፈንታ ጦርነቱን ተዋግቻለሁ፣ በስሜም ከአሸናፊዎች በላይ ናችሁ።”GCAmh 456.2

    ውዱ አዳኝ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ እርዳታ ይልካል። ወደ ሰማይ የሚወስደው ጎዳና በእርሱ ዱካ የተቀደሰ ነው። እግራችንን የሚወጋን እያንዳንዱ እሾህ እርሱንም ወግቶታል። እንሸከመው ዘንድ የተጠራንለት እያንዳንዱ መስቀል፣ ከእኛ በፊት እርሱ ተሸክሞታል። ነፍስን ለሰላም ያዘጋጅ ዘንድ እግዚአብሔር ግጭትን ይፈቅዳል። የመከራው ዘመን ለእግዚአብሔር ሕዝቦች አስፈሪ የመከራ ገፈት ነው፤ ነገር ግን የተስፋ ቀስተ-ደመና ዙሪያውን እንደከበበው በእምነት ያዩ ዘንድ እያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ወደ ላይ የሚያንጋጥጥበት ጊዜ ነው።GCAmh 456.3

    “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታና ተድላን ያገኛሉ። ኃዘንና ልቅሶም ይሸሻል። የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ? ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ረሳህ….ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ [ሊያጠፋ የተዘጋጀ እንደሆነ አድርገህ/as if he were ready to destroy] ከአስጨናቂው ቁጣ የተነሳ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቁጣ የታለ እኔም እግዚአብሔር አምላክህ ባህርን የማውክ፣ ሞገዱም ይተማል። [ነገር ግን ሞገዱ የሚደነፋውን ባህር የከፈልኩ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ/But I am the Lord thy God, that divided the sea, whose waves roared]። ስሙ እግዚአብሔር የሰራዊት ጌታ ነው። ነገሬንም ባፍኽ አደረግሁ በእጄም ጽላ ጋረድሁህ።”[ኢሳ 51÷11-16]።GCAmh 456.4

    “ስለዚህ ስሚ አንቺ ችጋረኛ የሰከርሽም ከፀጅም አይደለም። ስለወገኑ የሚሟገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ የሚያንገደግድን ጽዋ የቁጣየንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። ባስጨነቁሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ሰውነትሽን ዝቅ አድርጊ እንሻገር ዘንድ ባሉሽ። ገላሽንም እንደ ትቢያ እንደ መንገድም አደረግሽ ላላፎች [በላይሽ ለሚያልፉ]” [ኢሳ 51÷21-23]። ምድራዊ ኃይላት ይቃወሟቸው ዘንድ በሚሰለፉበት ጊዜ ሕዝቦቹ በሚገጥማቸው ችግር ላይ ዘመናትን አቆልቁሎ የሚያየው የእግዚአብሔር አይን አተኩሮ ነበር። እንደ ፈለሰ ምርኮኛ፣ በረሃብም ይሁን በጥል የሚመጣን ሞት የሚፈሩ ይሆናሉ። ነገር ግን በእሥራኤል ፊት ባህሩን የከፈለ ቅዱስ ጌታ፣ ኃያሉን ጉልበቱን ይገልጣል፤ ምርኮኝነታቸውንም ይለውጣል። “እኔ በምሰራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፤ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር እንዲሁ እምራቸዋለሁ” [ሚል 3÷17]። በዚህ ጊዜ የክርስቶስ ታማኝ ምስክሮች ደም ቢፈስ፣ ልክ እንደ ሰማዕቱ ደም፣ ለእግዚአብሔር መከር የሚያመጣ ዘር አይሆንም። ደንዳናው (ለመለወጥ እምቢ ያለው) ልባቸው በስተመጨረሻ እስከማይመለስበት ድረስ የምሕረትን ሞገድ ወደኋላ ሲመልስ ቆይቷልና የንፁሃን ታማኝነት ሌሎችን ስለ እውነቱ ሊያሳምናቸው ምስክር አይሆንም። አሁን ፃድቃን በጠላቶቻቸው ፊት ታድነው የሚወድቁ ከሆነ ለጽልመት ልዑል ታላቅ ድል ይሆናል። መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ “በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ይሰውረኛልና፤ በድንኳኑም መሸሸጊያ ይሸሸግኛልና [መዝ 27÷5]። ክርስቶስ ተናግሯል፦ “ሕዝቤ ሆይ ና ወደ ቤትህ ግባ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ያመጣባቸው ዘንድ እነሆ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል” [ኢሳ 26÷20፣21]። ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ የሰፈረ፣ ለመምጣቱም በትዕግስት የጠበቁ የእነርሱ ነፃ መውጣት አንፀባራቂ ይሆናል።GCAmh 456.5

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents