Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፵፪—ተጋድሎው አበቃ

    በአንድ ሺው ዓመት መጨረሻ ክርስቶስ ወደ ምድር ተመለሰ። የተዋጁት ሰራዊትና የመላእክት አጃቢዎች ይከተሉታል። በታላቅ ክብር ሲወርድ ሳለ የሞቱት ኃጥአን ፍርዳቸውን ይቀበሉ ዘንድ እንዲነሱ አዘዛቸው። እጅግ ታላቅ ሰራዊት፣ እንደ ባህር አሸዋ የማይቆጠሩ ሆነው ወጡ። በመጀመሪያው ትንሳኤ ከተነሱት ጋር ሲነፃፀር እንዴት ያለ ልዩነት ነው! ፃድቃን የማይሞት ወጣትነትና ውበት ተላብሰው ነበር። ኃጥአን ግን የህመምና የሞት ምልክቶችን ተሸክመዋል።GCAmh 476.1

    የእግዚአብሔርን ልጅ ክብር ያይ ዘንድ፣ በዚያ እልፍ አዕላፋት ውስጥ ያለ የእያንዳንዱ አይን ዞረ። የኃጥአን ሰራዊት በአንድ ድምጽ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” ብለው ጮኹ። ይህንን ጩኸት የሚያነሳሳው ለየሱስ ያለው ፍቅር አይደለም። የእውነት ኃይል፣ ቃላቱ፣ ፈቃደኛ ካልሆኑ ከንፈሮች ፈንቅለው ይወጡ ዘንድ ገፋቸው። ኃጥአን ወደ መቃብር ሲወርዱ እንደነበሩት፣ ለክርስቶስ በነበራቸው በተመሳሳይ ጠላትነት፣ በዛው ተመሳሳይ የአመጽ መንፈስ ሆነው ከመቃብር ወጡ። ያለፈውን የሕይወታቸውን ግድፈት ያርሙ ዘንድ የሚያስችላቸው አዲስ የምሕረት ጊዜ አይሰጣቸውም። በዚህ የሚተረፍ አንዳች ነገር የለም። የእድሜ ልክ መተላለፍ ልባቸውን አላለሰለሰውም። ሁለተኛ የምሕረት ጊዜ ቢሰጥ ኖሮ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ የእግዚአብሔርን መጠይቆች ገሸሽ በማለትና እርሱንም በመቃወም አመጽ በማነሳሳት ጥቅም ላይ ይውል ነበር።GCAmh 476.2

    ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ባረገበት፣ መላእክትም የመመለሱን ተስፋ በደገሙበት በደብረዘይት ተራራ ላይ ወረደ። ነብዩ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም አምላኬ ይመጣል ቅዱሳኑም ሁሉ ካንተ ጋራ።”፤ “በዚያም ቀን እግሮቹ በየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ… እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል።” “እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ይነግሳል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ ይሆናል፣ ስሙም አንድ (there shall be one Lord, and his name one)” [ዘካ 14÷5፣4፣9]። አዲሲቱ የሩሳሌም፣ በሚያስገርም ውበትዋ ከሰማይ ስትወርድ ፀድቶና ተዘጋጅቶ በሚቀበላት ስፍራ አረፈች፤ ከዚያም ክርስቶስ ከሕዝቦቹና ከመላእክቱ ጋር ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ገቡ።GCAmh 476.3

    አሁን ሰይጣን ለመጨረሻው ታላቅ የበላይነት ግብግብ ይዘጋጃል። ኃይሉ የተወሰደበት፣ ከማታለል ሥራውም ተገልሎ የክፋት ልዑል ጎስቋላና ኃዘንተኛ ሆኖአል፤ ሆኖሞ የሞቱት ኃጥአን ሲነሱና እልፍ አዕላፋት በእሱ ጎን ሆነው ሲያይ ተስፋው አንሰራራ፤ እናም ታላቁን ተጋድሎ ላለመሸነፍ ቆረጠ። የጠፉትን የጦር ሰራዊት በባንዲራው ስር አሰልፎ በመምራት፣ በእነርሱ አማካኝነት እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራል። ኃጥአን የሰይጣን ምርኮኞች ናቸው። ክርስቶስን ባለመቀበላቸው የአማፂውን መሪ አስተዳደር ተቀብለዋል። የሚያቀርባቸውን ኃሳቦች ለመቀበል ትዕዛዛቱንም ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው። ሆኖም ልክ እንደመጀመሪያው አታላይነቱ እሱ ራሱ ሰይጣን እንደሆነ እውቅና አይሰጥም። የተገባው የዓለም ባለቤት፣ ርስቱም ያለአግባብ የተወሰደበት ልዑል እንደሆነ ይናገራል። ለተሞኙት ተገዥዎቹ ራሱን አዳኝ አድርጎ በማቅረብ ኃይሉ ከመቃብር እንዳስነሳቸው፣ እጅግ ጨካኝ ከሆነው አንባገነንም ሊያድናቸው እንደሆነ ይነግራቸዋል። የክርስቶስ መገኘት ከዚያ ስለተወገደ፣ ንግግሩን ለመደገፍ ሰይጣን ተዓምራትን ያደርጋል። ደካማውን አጠንክሮ፣ ሁሉንም በራሱ መንፈስና ኃይል ያነሳሳቸዋል። የቅዱሳንን ሰፈር ለማጥቃት ሊመራቸው፣ የእግዚአብሔርንም ከተማ ለመያዝ ኃሳብ ያቀርባል። በዲያብሎሳዊ ትዕቢት ተሞልቶ ከሞት ወደ ተነሱት የማይቆጠሩ ሚሊዮኖች በመጠቆም መሪያቸው እንደመሆኑ ከተማዋን ለመገልበጥ በእርግጥ የሚቻለውና ዙፋኑንና መንግሥቱን እንደገና ለመያዝ የሚችል መሆኑን ያውጃል።GCAmh 476.4

    በዚያ ሰፊ መንጋ ውስጥ ከውኃ ጥፋት በፊት የነበሩ፣ እረጅም እድሜ ይኖሩ የነበሩ እልፍ አዕላፋት አሉ። ለወደቁ መላእክት እጅ ሰጥተው ጥበባቸውንና እውቀታቸውን ሁሉ ለራሳቸው ከፍ ከፍ ማለት ያዋሉ በአካል የገዘፉና በእውቀት የመጠቁ ሰዎች፤ አስደናቂ የጥበብ ሥራቸውና ተሰጥዖአቸው ዓለም ምጡቅነታቸውን እንዲያመልክ የመራ፣ ነገር ግን ጭካኔያቸውና የክፋት ፈጠራዎቻቸው ምድርን ያረከሰ፣ የእግዚአብሔርን መልክ ያጠፋ፣ ከፍጥረቱ ቆርጦ እንዲጥላቸው ያደረጉት ሰዎች በዚያ አሉ። አገራትን የወረሩ ነገስታትና የጦር መኮንኖች፣ በጦር ግንባር ተሸንፈው የማያውቁ፣ ደፋር፣ ኩሩ፣ ዜዴያቸው መንግሥታትን ያንቀጠቀጠ፣ ጉጉት ያላቸው ጦረኞች አሉ። በመሞታቸው ምክንያት ለውጥ አልተለማመዱም። ከመቃብራቸው ሲወጡ የኃሳብ ፍሰታቸውን ልክ ከቆሙበት እንደገና አስቀጠሉት። ሲወድቁ ተቆጣጥሯቸው በነበረው በዚያው የመውረር ጥማት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።GCAmh 477.1

    ሰይጣን ከመላእክቱ ጋር፣ ከዚያም ከእነዚህ ነገስታት፣ ወራሪዎችና ኃያላን ሰዎች ጋር ተመካከረ። ከጎናቸው የተሰለፉትን ጥንካሬና የቁጥር ብዛት አዩ፤ እናም በከተማዋ ውስጥ ያለው ጦር ከእነርሱ ጋር ሲነፃፀር ትንሽ በመሆኑ መሸነፍ እንደሚችል ተናገሩ። የአዲሲቱን የሩሳሌምን ኃብትና ክብር ለመውረስ እቅዳቸውን አወጡ። ሁሉም ወዲያውኑ ለጦርነት መዘጋጀት ጀመረ። ጥበበኞች የጦር መሳሪያዎችን ሰሩ፤ በስኬታቸው ስመ-ጥር የሆኑ የጦር መሪዎች ለጦርነት ያሾሩ ሰዎችን በጦር ሻምበልና ብርጌድ ከፋፈሏቸው።GCAmh 477.2

    በመጨረሻም ወደፊት የመንቀሳቀስ ትዕዛዝ ተሰጠ — በምድራዊ ወራሪዎች ዘንድ ተደራጅቶ የማያውቅ፣ ጦርነት በምድር ላይ ከተጀመረ ጀምሮ፣ በዘመናት ሁሉ የነበሩት ኃይላት አንድ ላይ ቢሰለፉ፣ ፈጽመው የማይተካከሉት ጦር — የማይቆጠረው ሰራዊት ተንቀሳቀሰ። ከጦረኞች ሁሉ ይልቅ ኃያል የሆነው ሰይጣን ሰራዊቱን እየመራ መላእክቱም በዚህ የመጨረሻ ፍልሚያ ኃይላቸውን አስተባበሩ። ነገሥታትና ጦረኞች በእርሱ ስር ሆነው እልፍ አዕላፋትም በየተመደቡበት ብርጌድ በየመሪዎቻቸው ስር ሆነው ተከታተሉ። ዝንፍ በማይል ወታደራዊ ሰልፍ የተሰደሩት ተዋረዶች በተሰባበረውና በወጣ ገባው ምድር ላይ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ገሰገሱ። በየሱስ ትዕዛዝ የአዲሲቱ የሩሳሌም በሮች ተዘጉ፤ የሰይጣን ሰራዊትም ከተማዋን ከበው ለጥቃት ዝግጁ ሆኑ።GCAmh 477.3

    አሁን፣ ክርስቶስ እንደገና ጠላቶቹ እንዲያዩት ሆነ። በከተማይቱ በላይ ራቅ ብሎ በተወለወለ ወርቅ መሰረት ላይ ዙፋኑ ከፍ ብሎ አለ። በዚህ ዙፋን ላይ የእግዚአብሔር ልጅ ተቀምጦአል፤ በዙሪያውም የመንግሥቱ ተገዥዎች አሉ። የክርስቶስን ኃይልና ግርማ የትኛውም ቋንቋ ሊገልፀው፣ ብዕር ሊስለው አይችልም። የዘላለማዊው አባት ክብር ልጁን ከቧል። የመገኘቱ ብርሃን የእግዚአብሔርን ከተማ ሞልቷታል፤ በበሮችዋም ወደ ውጪ እየፈሰሰ ነፀብራቁ ምድርን አጥለቀለቃት።GCAmh 477.4

    ከዙፋኑ ቀጥሎ ያሉት በአንድ ወቅት በሰይጣን ዓላማ ቅንዓት የነበራቸው፣ ነገር ግን ከእሳት የተነጠቁ ትንታጎች አዳኛቸውን በጥልቅ፣ ኃያል መሰጠት የተከተሉ ናቸው። ከእነርሱ ቀጥለው ደግሞ በሐሰትና በክህደት መካከል ተከበው ሳለ የክርስቲያን ባህርይን ወደ ፍጽምና ያሳደጉ፣ የክርስትናው ዓለም እንደቀረ ያወጀውን የእግዚአብሔርን ሕግ ያከበሩና በዘመናት ሁሉ የነበሩ ለእምነታቸው የተሰው ሚሊዮኖች ይገኛሉ። ከዚያም ቀጥሎ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ፣ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ፣ እጅግ ብዙ ሰዎች” “ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው፣ በዙፋኑና በበጉ ፊት” [ራዕይ 7÷9] ነበሩ። ጦርነታቸው አብቅቷል፤ ውድድሩን ሩጠው፣ ወደ ሽልማቱ ደርሰዋል። በእጃቸው ያለው የዘንባባ ዝንጣፊ የድላቸው ምልክት ነው፤ ነጩ መጎናፀፊያ ደግሞ አሁን የእነርሱ የሆነው ነቁጣ የሌለበት የክርስቶስ ጽድቅ አርማ ነው።GCAmh 478.1

    በሰማይ ጣሪያዎች እየተመላለሰ የሚያስተጋባ የምስጋና መዝሙር የተዋጁት ዘመሩ። “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” መላእክትና ሱራፌሎች በአምልኮ ድምፃቸውን አዋሃዱ። የተዋጁት የሰይጣንን ኃይልና ተንኮል ስላዩ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ ከክርስቶስ በቀር ሌላ ኃይል አሸናፊዎች ሊያደርጋቸው እንደማይችል አስተውለዋል። በዚያ በሚያንፀባርቀው ሕዝብ መኃል በራሳቸው ኃይልና መልካምነት እንዳሸነፉ አድርገው ድነትን እንዳገኙ የሚቆጥሩ አንዳች የሉም። ስለሰሩት ወይም ስለተሰቃዩት ነገር አንዳች የሚባል የለም፤ የእያንዳንዱ መዝሙር ሸክም፣ የእያንዳንዱ ዜማ ዋና ሃሳብ “ማዳን ለአምላካችንና ለበጉ” የሚል ነው።GCAmh 478.2

    በተሰበሰቡት የምድርና የሰማይ ነዋሪዎች ፊት የእግዚአብሔር ልጅ የመጨረሻው ንግስና (ሥርዓት-ዘውድ) ተከናወነ። እናም አሁን ማንም በማይተካከለው ግርማና ኃይል ተላብሶ የነገሥታት ንጉሥ በመንግሥቱ ላይ ባመፁት ላይ ፍርድ በማወጅ ሕጉን በተላለፉትና ሕዝቦቹን በጨቆኑት ላይ ፍርድን አወጀ። የእግዚአብሔር ነብይ እንዲህ ይላል፦ “ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፣ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ። መጽሐፍትም ተከፈቱ፣ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው። ሙታንም በመጽሐፍ ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።” [ራእይ 20÷11፣12]።GCAmh 478.3

    የመዝገብ መጻሕፍት እንደተከፈቱ፣ የክርስቶስም ዓይን በኃጥአን ላይ ሲያርፍ፣ የሰሩትን እያንዳንዱን ኃጢአት አስታወሱ። ከንጽህናና ከቅድስና መንገድ እግሮቻቸው የት ላይ እንዳፈነገጡ፣ ኩራትና ዓመጽ የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስ ምን ያህል እርቀት እንደወሰዷቸው አዩ። ኃጢአትን በማጣጣም ያበረታቷቸው የሚገፋፉ ፈተናዎች፣ እንዲጣመሙ የተደረጉ በረከቶች፣ የተጠሉ የእግዚአብሄር መልዕክተኞች፣ ችላ የተባሉ ማስጠንቀቂያዎች፣ ግትርና ፀፀት የለሽ በሆነ ልብ እየተመታ የሚመለሰው የምሕረት ማዕበል—እነዚህ ሁሉ በእሳት እንደተፃፋ ፊደላት ሆነው ታዩ።GCAmh 478.4

    ከዙፋኑ በላይ መስቀሉ ተገለጠ። ትዕይንቶችን ዳር እስከ ዳር በሚያሳይ መልኩ የአዳም ፈተናና ውድቀት፣ ከዚያም በተከታታይ የመጡት የታላቁ የማዳን እቅድ ክስተቶች ታዩ። የአዳኙ የተዋረደ መወለድ፣ የህፃንነቱ ቀላልና የመታዘዝ ሕይወት፣ በዮርዳኖስ ጥምቀቱ፣ ፆሙና የምድረበዳ ፈተናው፣ ተወዳዳሪ የሌለውን የሰማይን በረከት ለሰዎች የገለጠበት ሕዝባዊ አገልግሎቱ፣ በፍቅርና በምሕረት አድራጎት የተጨናነቁት ቀናት፣ የሌሊት ፀሎቶችና ፀጥ ባሉት ተራሮች መቆየት፣ ለመልካም አድራጎቱ የተከፈሉት የቅንዓት፣ የጥላቻና የምቀኝነት ደባዎች፣ በሚያደቀው በዓለሙ ሁሉ ኃጢአት ጭነት በታች የደረሰበት አሰቃቂና ምስጢራዊ የጌቴሰማኒ ስቃይ፣ ለገዳዩ ሕዝብ እጅ ተላልፎ የተሰጠበት ክህደት፣ ያላንገራገረው እስረኛ፣ ከሌላው በልጠው በተወደዱት ደቀመዛሙርቱ ተትቶ፣ ትህትና በሌለው አኳኋን በየሩሳሌም ጎዳናዎች የተጣደፈበት፣ የዚያ አሰቃቂ ሌሊት አስፈሪ ክስተቶች፤ ፈሪውና ጨካኙ ሄሮድስ አፊዞበት፣ ሰድቦትና ገርፎት ሞት ከመፍረዱ በፊት በጲላጦስ የፍርድ አዳራሽ የእግዚአብሔር ልጅ፣ በሊቀ ካህኑ መኖሪያ፣ ተጊጦ፣ በአሸናፊነት ስሜት በሐና ፊት እንዲታይ የተደረገበት—ይህ ሁሉ በግልጽ ታየ።GCAmh 478.5

    አሁን በሚረግደው ሕዝብ ፊት የመጨረሻዎቹ ትዕይንቶች ተገለጡ — ታጋሹ ተሰቃይ ወደ ቀራንዮ በሚወስደው መንገድ ላይ ሲራመድ፣ የሰማይ ልዑል በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ ኩራተኛ ካህናትና በፌዝ የሚያሽካካው ጀሌ የሞቱን ስቃይ ሲሳለቅበት ከተፈጥሮ ኃይል በላይ የሆነው ጽልመት፣ የተንቀጠቀጠው ምድር፣ የተሰነጠቁ ቋጥኞች፣ የተከፈቱ መቃብሮች፣ የዓለም አዳኝ ነፍሱን ሲሰጥ ያመለከቱት ክስተቶች ተገለጡ።GCAmh 479.1

    ይህ አሰቃቂ ትዕይንት ልክ ሲከናወን እንደነበረው ነው። ሰይጣን፣ መላእክቱና ተገዥዎቹ የራሳቸው ሥራ ከሆነው ስዕል ዘወር የማለት ኃይል የላቸውም። እያንዳንዱ ተዋናኝ የተጫወተውን ክፍል ያስተውላል። የእሥራኤልን ንጉሥ ያጠፋ ዘንድ የቤተልሄምን ንፁህ ህፃናት ያረደው ሔሮድስ፣ የመጥምቁ ዮሐንስ ደም በኃጥዑ ነፍሷ ላይ ያረፈባት ሔሮድያዳ፤ ደካማው፣ ጊዜ ገፊው፣ ጲላጦስ፤ አላጋጮቹ ወታደሮች፤ ካህናትና አለቆች፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብሎ የጮኸው በቁጣ የሰከረው ሕዝብ — ሁሉም የኩነኔያቸውን ግዝፈት ተመለከቱ። የፀሐይን ክብር ከሚበልጠው፣ ከፊቱ መለኮታዊ ግርማ ለመሸሸግ በከንቱ ሲጥሩ፣ በአንፃሩ የዳኑት ዘውዶቻቸውን በአዳኙ እግሮች በማኖር፣ “ሞተልኝ ለእኔ!” ብለው ጮኹ።GCAmh 479.2

    ከተዋጀው ሕዝብ መሐል የክርስቶስ ሐዋርያት፣ ጀግናው ጳውሎስ፣ ጽኑው ጴጥሮስ፣ ተወዳጁና አፍቃሪው ዮሐንስ፣ እንዲሁም ሐቀኛ ልብ ያላቸው ወንድሞቻቸው፣ አብሯቸውም የሰማዕታት ሰራዊት ሲኖር፣ ከቅጥሮቹ ውጭ ደግሞ ከክፋትና ከአፀያፊ ነገር ሁሉ ጋር በውስጥ ያሉትን ያሳደዱ፣ ያሰሩና ያረዱ ይገኛሉ። በአንድ ወቅት ያሰቃያቸውን በማይመዘን ስቃያቸውም ሰይጣናዊ እርካታ ያገኝ የነበረው ኔሮ፣ ደስታቸውንና ከፍ ከፍ ማለታቸውን እያየ እዚያ አለ። ለራስዋ የሥራ ውጤት ምስክር ትሆን ዘንድ እናቱም እዚያው አለች፤ ወደ ልጅዋ የተላለፈው የባህርይ የክፋት ማህተም፣ በእርሷ ተጽዕኖና ምሳሌነት የተበረታቱትንና የጎበለቱት ፍላጎቶች፣ ዓለምን ያንቀጠቀጠ የወንጀል ፍሬ ያፈሩትን ታይ ዘንድ እዚያ አለች።GCAmh 479.3

    የክርስቶስ አምባሳደሮች ነን ያሉ ነገር ግን የሕዝቦቹን ንቃተ ህሊና ለመቆጣጠር መስቀያ ስፍራ፣ ወህኒ ቤትና ማቃጠያ ስፍራ የተጠቀሙ ጳጳሳዊ ካህናትና የኃይማኖት መሪዎች እዚያው አሉ። ራሳቸውን ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ ከፍ ያደረጉ፣ የታላቁንም አምላክ ሕግ ለመለወጥ የደፈሩ፣ ኩሩ ሊቃነ-ጳጳሳት አሉ። እነዚያ አስመሳይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ይቅርታ ቢደረግላቸው እጅግ ደስ የሚሰኙበት፣ ለእግዚአብሔር መመለስ ያለባቸው ሂሳብ አላቸው። ሁሉን የሚያየው እርሱ ለሕጉ ቀናተኛ እንደሆነ፣ ባለኩነኔውንም በምንም ዓይነት የማያነፃ መሆኑን ጊዜ ካለፈ በኋላ እንዲያዩ ተደረጉ። ክርስቶስ የሚወግነው (ፍላጎቱን አንድ የሚያደርገው) ከሚሰቃዩ ሕዝቦቹ ጋር እንደሆነ አሁን ተማሩ፤ የራሱ ቃላት ጉልበትም ተሰማቸው፦ “ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” [ማቴ 25÷40]።GCAmh 479.4

    መላው የኃጥዑ ዓለም፣ በሰማይ መንግሥት ላይ ከፍተኛ የመክዳት (የባንዳነት) ኃጢአት በመፈፀም ተከሶ በእግዚአብሔር ፍርድ ሸንጎ ፊት ቆሞአል። ይግባኝ የሚሉበት [ጥፋተኛ አይደለንም ብለው የሚከራከሩበት] አንዳች ነገር የላቸውም፤ ማሳበቢያ አልባ ናቸው፤ የዘላለም ሞት ቅጣትም ተበየነባቸው።GCAmh 480.1

    የኃጢአት ዋጋ የከበረ ነፃነትና ዘላለማዊ ሕይወት ሳይሆን ባርነት፣ ውድመትና ሞት እንደሆነ አሁን ለሁሉም ግልጽ ሆነ። በዓመጽ ሕይወታቸው ምክንያት ምን እንደቀረባቸው ኃጥአን ተመለከቱ። እጅግ የሚበልጠውና ዘላለምን የሚመዝን ክብር ሲበረከትላቸው ችላ ተባለ፤ አሁን እንዴት ተፈላጊ ሆኖ ታየ። “ይህ ሁሉ” በማለት ጮኸ የጠፋው ነፍስ፦ “ሊኖረኝ ይችል ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ከእኔ ለማራቅ መረጥሁ፤ ኦ እንግዳ፣ ቅጥ ያጣ ፍላጎት! ሰላምን፣ ደስታንና ክብርን ለራቁትነት፣ ለክፉ ስም፣ ለተስፋ መቁረጥ ለወጥኩ”። ከሰማይ መገለላቸው ፍትሃዊ እንደሆነ ሁሉም አስተዋሉ። በሕይወታቸው “ይህ የሱስ እንዲገዛን አንፈቅድም” ብለው ተናግረዋልና።GCAmh 480.2

    በአስማት እንደተያዙ ዓይነት ሆነው ኃጥአን የእግዚአብሔርን ልጅ ሥርዓተ ዘውድ ተመልክተዋል። ቸል ያሉትንና የተላለፉንት ሥርዓት፣ የመለኮታዊውን ሕግ ገበታዎች (ጽላቶች) በእጁ አዩ። ከዳኑት የሚመነጨውን ግርምት፣ ሐሴትና አድናቆት ተመለከቱ። የጥዑመ-ዜማው ማእበል ከከተማዋ ውጪ ባሉት እልፍ አዕላፋት ላይ እያለፈ ሲያስተጋባ፣ ሁሉም በአንድ ድምጽ “ጌታ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ፃድቅና እውነተኛ ነው” [ራዕይ 15÷3] እያሉ ወድቀው በመስገድ የሕይወትን ልዑል አመለኩት።GCAmh 480.3

    የክርስቶስን ክብርና ግርማ ሲመለከት ሳለ ሰይጣን ሽባ የሆነ መሰለ። በአንድ ወቅት የሚሸፍን (የሚጋርድ) ኪሩቤል የነበረው እርሱ የወደቀበትን ሥፍራ አስታወሰ። ያ የሚያንፀባርቅ ሱራፌል፣ “የንጋት ልጅ፤” እንዴት ተለውጧል፣ እንዴት ቆርቁዟል! በአንድ ወቅት ከተከበረበት መማክርት ለዘላለም ተለይቷል። በአብ አጠገብ፣ ክብሩን ከልሎ፣ አሁን ሌላ መልአክ ቆሞ ተመለከተ። ግዙፍ አካልና ግርማን በተላበሰ መልአክ ዘውዱ በክርስቶስ ራስ ላይ ሲደረግ አይቶአል፤ ይህ ከፍ ከፍ ያለው የዚህ መልአክ ደረጃ የእርሱ ይሆን እንደነበር ያውቃል።GCAmh 480.4

    በእግዚአብሔር ላይ በማጉረምረም ክርስቶስንም በመመቅኘት ሐሳብ እስኪያዝ ድረስ የእርሱ የነበሩት ሰላምና እርካታ፣ የየዋህነቱና የንጽህናው [ዘመን] ቤቱ ትውስታ ውል አለበት። የመላእክትን ድጋፍና ኃዘኔታ ለማግኘት ያደረገው ማታለል፣ ክሱ፣ አመፁ፣ እግዚአብሔር ይቅርታ በሚያደርግበት ጊዜ ራሱን ለማደስ ምንም ጥረት ያላደረገበት መንቻካ ጽናቱ — ሁሉ ጥርት ብለው በፊቱ ቀረቡ። በሰዎች መካከል የሰራው ሥራና ውጤቱን ከለሰ — የሰው ጠላትነት ለባልንጀራው ሰው፣ አሰቃቂው የሕይወት ውድመት፣ የነገሥታት መነሳትና መውደቅ፣ የዙፋኖች መገልበጥ፣ ለረጅም ጊዜ በተከታታይ የተከሰቱ ሕዝባዊ ኹከቶችና ብጥብጦች፣ ጥልና አብዮቶች። የክርስቶስን ሥራ ለመቃወም ሰውንም ቁልቁል ለማስመጥ ያደርጋቸው የነበሩትን የማያባሩ ጥረቶች አስታወሰ። እምነታቸውን በየሱስ ያደረጉትን ያጠፋ ዘንድ ሲኦላዊ ደባዎቹ ኃይል አልባ እንደነበሩ አየ። የልፋቱ ፍሬ የሆነችውን መንግሥቱን ሲመለከት፣ የሚያየው ውድቀትና ውድመትን ብቻ ሆነ። የእግዚአብሔር ከተማ ቀላል ኢላማ እንደሆነች እልፍ አዕላፋትን አሳምኖአል፤ ይህ ሐሰት እንደሆነ ግን ያውቀዋል። በታላቁ ተጋድሎ ሂደት በተደጋጋሚ ተሸንፏል፤ እጅ እንዲሰጥም ተገዷል። የዘላለማዊውን [የጌታን] ኃይልና ግርማም ጠንቅቆ ያውቃል።GCAmh 480.5

    ራሱን ፃድቅ ለማድረግና አመፁ የመለኮታዊው አስተዳደር ኃላፊነት መሆኑን ለማረጋገጥ የታላቁ አማጺ የሁልጊዜም አላማ ነበር። ይህንንም ለማሳካት የግዙፍ ክህሎቱን ኃይል ሁሉ አፍስሷል። አቅዶበት፣ በብልሃት ሰርቷል፤ ለረጅም ጊዜ የተካሄደውን፣ ለታላቁ ተጋድሎ እርሱ ራሱ የሰጠውን ትርጉም እልፍ አዕላፋት እንዲቀበሉት በመምራት አንፀባራቂ ድልን ተቀዳጅቷል። ይህ የሴራ አለቃ ለበርካታ ሺህ ዓመታት በማታለል ኃሰት እውነት እንዲመስል አድርጓል። ነገር ግን አመፁ በስተመጨረሻ የሚሸነፍበት፣ የሰይጣን ታሪክና ባህርይ የሚጋለጥበት ጊዜ አሁን ደርሶአል። ክርስቶስን ከዙፋኑ ለማውረድ፣ ሕዝቦቹን ለማጥፋትና የእግዚአብሔርን ከተማ ለመውሰድ ባደረገው የመጨረሻ ጥረት ቀንደኛ አታላዩ ሙሉ በሙሉ ተጋልጦአል። ከእርሱ ጋር የተባበሩ እነርሱ የእቅዱን ሙሉ ለሙሉ መንኮታኮት አስተዋሉ። በእግዚአብሔር አስተዳደር ላይ የሰነዘረውን የተንኮል ሴራ ልክ፣ የክርስቶስ ተከታዮችና ታማኝ መላዕክቱ በሙላት አዩ። የዓለም አቀፋዊ ጥላቻ ኢላማም ሆነ።GCAmh 481.1

    በፈቃዱ ያደረገው አመጽ ለሰማይ ገጣሚ እንዳይሆን እንዳደረገው ሰይጣን አየ። ከእግዚአብሔር ጋር ይዋጋ ዘንድ ክህሎቶቹን አሰልጥኖአል፤ ለእርሱ የሰማይ ንጽህና፣ ሰላምና ስምሙነት ተወዳዳሪ የሌለው ስቃይ ይሆንበታል። በእግዚአብሔር ምሕረትና ፍርድ ላይ ያነሳቸው ክሶች አሁን ፀጥ ተደረጉ። በያህዌ ላይ ለማሳረፍ ሲጥር የነበረው ነቀፋ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ አረፈ። አሁን ሰይጣን አጎንብሶ የቅጣቱን ፍትሃዊነት መሰከረ።GCAmh 481.2

    “ጌታ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና የጽድቅህም ሥራ ስለተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ” [ራዕይ 15÷4]። ለረጅም ጊዜ በነበረው ተጋድሎ የተነሳው እያንዳንዱ የእውነትና የስህተት ጥያቄ አሁን ግልጽ ተደርጓል። የአመጽ ውጤቶች፣ የመለኮትን መመሪያዎች ወደጎን የመገፍተር ፍሬዎች ለፍጡራን ሁሉ [ላልወደቁ አለማት ጭምር] ይታዩ ዘንድ ተከፍተዋል። የሰይጣን ሥራ ውጤት፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር በንጽጽር ለመላው አለም (ዩኒቨርስ) ቀርቦለታል። የገዛ ራሱ ሥራዎች ሰይጣንን ኮነኑት። የእግዚአብሔር ጥበብ፣ ፍትሃዊነቱና መልካምነቱ ከክስ ነፃ ሆኑ። በታላቁ ተጋድሎ ያደረገው ሁሉ ለሕዝቦቹ ዘላለማዊ ጥቅም፣ እንዲሁም ለፈጠራቸው አለማት ሁሉ ጥቅም ይሆን ዘንድ የተከናወነ እንደሆነ ታየ። “አቤቱ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል” [መዝ 145÷10]። የእግዚአብሔር ሕግ ነዋሪነት ከፈጠራቸው ፍጡራን ደስታ ጋር የተቆራኘ ለመሆኑ ምስክር ይሆን ዘንድ የኃጢአት ታሪክ ለዘላለም ይኖራል። የታላቁ ተጋድሎ እውነቶች በእይታቸው ውስጥ ሆኖ፣ ታማኙና አማፂው፣ መላው ዓለም፣ በአንድ ላይ “የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ፃድቅና እውነተኛ ነው” በማለት አወጀ።GCAmh 481.3

    ስለ ሰው በአብና በወልድ የተደረገው ታላቅ መስዋዕት ለዓለም በግልጽ ቀርቧል። ክርስቶስ የሚገባውን ስፍራ ሊይዝ፣ ከአለቆችና ከስልጣናት እንዲሁም ከተሰጠ ስም ሁሉ በላይ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ መጥቷል። መስቀሉን ችሎ፣ ሃፍረቱን ወስዶ ያለፈው በፊቱ ላለው ደስታ - በርካታ ልጆችንም ወደ ክብር ያመጣ - ዘንድ ነበር ። ኃዘኑና ውርደቱ ሊታሰብ የማይችል ታላቅ የነበረ ቢሆንም ቅሉ ደስታውና ክብሩ ደግሞ ከዚያ የላቀ ነው። የተዋጁትን፣ ወደራሱ አምሳል ተለውጠው፣ እያንዳንዱ ልብ የመለኮትን ፍፁም ማህተም ተሸክሞ፣ እያንዳንዱ የፊት ገጽታ የንጉሣቸውን አምሳያ እያንፀባረቀ፣ ተመለከታቸው። የነፍሱን ጭንቀት ውጤት በእነርሱ ውስጥ አየ፣ እረካም። ከዚያም ወደ ተሰባሰቡት እልፍ አዕላፋት ፃድቃንና ኃጢአን በሚደርስ ድምጽ እንዲህ አለ፦ “እነሆ በደሜ የተገዙ ከእኔ ጋር ለዘላለም ይኖሩ ዘንድ ለእነዚህ ተሰቃየሁ፤ ለእነዚህ ሞትሁ”። የምስጋና መዝሙርም በዙፋኑ ዙሪያ ባሉ፣ ነጭ ከለበሱ ወጣ፣ “የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።” [ራዕይ 5÷12]።GCAmh 482.1

    ለእግዚአብሔር ፍትህ እውቅና እንዲሰጥና ለክርስቶስም የበላይነት እንዲያጎነብስ የተገታ ቢሆንም ቅሉ የሰይጣን ባህርይ አሁንም አልለወጠም። የአመጽ መንፈስ፣ ልክ እንደ ኃይለኛ ዶፍ (ጎርፍ) ወደፊት ይፈነዳል። በታላቅ ስሜት ለታላቁ ተጋድሎ እጅ ላለመስጠት ወሰነ። የሰማይን ንጉሥ በመቃወም የመጨረሻውን ተስፋ አስቆራጭ ትግል የሚያደርግበት ሰዓቱ ደርሶአል። ወደ ተገዥዎቹ መኃል ገስግሶ በመግባት በራሱ ቁጣ ሊያበረታታቸው፣ ወዲያው ወደ ጦርነት እንዲገቡም ሊያነስነሳቸው ጣረ። ሆኖም ወደ አመጽ ካታለላቸው የማይቆጠሩ ሚሊዮኖች ውስጥ አንድም ለበላይነቱ እውቅና የሚሰጥ አልተገኘም። ኃይሉ ማብቂያው ላይ ነው። ኃጥአን፣ ሰይጣንን በሚያነሳሳው በዚያው ተመሳሳይ እግዚአብሔርን የመጥላት ስሜት ተሞልተዋል፤ ሆኖም ጉዳያቸው ተስፋ-ቢስ እንደሆነ፣ እግዚአብሔርንም ማሸነፍ እንደማይችሉ አስተዋሉ። በሰይጣንና በማታለል በተባበሩት ወኪሎቹ ላይ ቁጣቸው ፈነዳ፤ በአጋንንት ቁጣም ተነሱባቸው።GCAmh 482.2

    ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ልብህን እንደ እግዚአብሔር [ልብ] አድርገሃልና ስለዚህ እነሆ የሌላ አገር ሰዎችን የአሕዛብን ጨካኞች አመጣብሃለሁ፤ ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዛሉ፣ ክብርህንም ያረክሳሉ። ወደ ጉድጓድ ያወርዱሃል።” “የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፣ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ [አጠፋሃለሁ/I will destroy thee]….በምድር ላይ ጣልሁህ [እጥልሃለሁ/I will cast you]….ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ [እሰጥሃለሁ/I will lay thee]….በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ [አደርግሃለሁ]….አንተም ለድንጋጤ ሆነሃል [ትሆናለህ/thou shall be a terror]፤ እስከ ዘላለምም አትገኝም።” [ሕዝ 28÷6-8፤ 16-19]።GCAmh 482.3

    “ተዋጎች በጦርነት ሲፋጁ፣ በደምም የተለቀለቀ ልብስ ሁሉ ለማቃጠል ይሆናል፤ እሳትም ይበላዋል፤ “የእግዚአብሔር ቁጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፤ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው።” “ወጥመድ በኃጥአን ላይ ያዘንባል። እሳትና ዲን አውሎ ነፋስም የጽዋቸው ዕድል ፈንታ ነው [እርሱ በክፉዎች ላይ የሚቀጣጠል ፍምን፣ እሳትን፣ ዲንን፣ ከባድንም ውሽንፍር ያዘንባል፡ የጽዋቸው እድል ፈንታም ይህ ይሆናል/upon the wicked he shall rain quick burning coals, fire and brimstone, and a horrible tempest: this shall be the portion of their cup]” [ኢሳ 9÷5፤ 34÷2፤ መዝ 11÷6]። እሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ ወረደ። ምድር ተሰባበረች፤ በውስጥዋ የተደበቁት መሳሪያዎች ወደ ላይ ወጡ። የሚፋጁ ነበልባሎች ከእያንዳንዱ ከተከፈተ የምድር ገደል ወጡ። ቋጥኞቹ ራሳቸው ተቃጠሉ። እንደ ምድጃ እሳት የሚያቃጥለው ቀን ደርሶአል። የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ቀለጠ፤ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ተቃጠለ [ሚል 4÷1፤ 2ኛ ጴጥ 3÷10]። የምድር ፊት አንድ የቀለጠ ግዙፍ አካል መሰለ — ሰፊ የሚፈላ የእሳት ሐይቅ። የፍርድ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን የማይመስሉ ሰዎች መጥፊያ ሰዓት ነው — “የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፣ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት አመት ነው።” [ኢሳ 34÷8]።GCAmh 482.4

    ኃጢአተኞች ፍዳቸውን በምድር ተቀበሉ [ምሳሌ 11÷31]። “ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል…ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” [ሚል 4÷1]። አንዳንዶች በቅጽበት ሲጠፉ ሳለ ሌሎች ለብዙ ለቀናት ተሰቃዩ። “እንደ ሥራ[ቸ]ው መጠን” ሁሉም ተቀጡ። የፃድቃን ኃጢአት ወደ ሰይጣን ተላለፈና ስለራሱ አመጽ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንዲሠሩት ባደረገበት ኃጢአት ሁሉ ልክ እንዲሰቃይ ተደረገ። የእርሱ ቅጣት፣ ካሳታቸው ይልቅ እጅግ የበዛ ይሆናል። ያታለላቸው ሁሉ ከጠፉ በኋላ፣ እርሱ በሕይወት ሆኖ ይሰቃይ ዘንድ አለው። በስተመጨረሻ፣ ኃጥአን፣ ሥርና ቅርንጫፍ፣ በሚያፀዳው ነበልባል ጠፉ - ስሩ ሰይጣን፣ ቅርንጫፎቹ ተከታዮቹ። የሕጉ ሙሉ ቅጣት ተጎብኝቷል፤ የፍርድ መጠይቁም ተማልቷል፤ ሰማይና ምድርም፣ እያዩ፣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አወጁ።GCAmh 483.1

    የሰይጣን የውድመት ሥራ ለዘላለም አበቃ። ለስድስት ሺህ አመት ፈቃዱን ሲያደርግ፣ ምድርን በኃዘን ሲሞላ በዓለማት በሙሉ እንዲቆዝም ሲያደርግ ቆይቷል። ፍጥረት ሁሉ በአንድነት በህመም ሲያቃስትና ሲከፋ ቆይቷል። አሁን የእግዚአብሔር ፍጥረታት ከእርሱ [ከሰይጣን] መገኘትና ከፈተናው ለዘላለም ነፃ ወጥተዋል። “ምድርም ሁሉ አርፋ በፀጥታ ተቀምጣለች፤ እርፍም ብላለች። እነርሱም [ፃድቃን] ይዘምራሉ” [ኢሳ 14÷9]። የምስጋናና የድል ጩኸት ከታማኙ ዓለም በሞላ ወደ ላይ ይወጣል። “የብዙ ሕዝብ ድምጽ” “እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምጽ እንደ ብርቱም ነጎድጓድ ድምጽ” ያለ ተሰማ እንዲህ ሲል፦ “ሃሌሉያ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሶአልና።” [ራዕይ 19÷6]።GCAmh 483.2

    ምድር በአጥፊው እሳት ተጀቡና ሳለ፣ ፃድቃን ግን በቅድስቲቱ ከተማ በደህና ኖረዋል። በመጀመሪያው ትንሳኤ እድል ፈንታ ባላቸው ላይ ሁለተኛው ሞት ኃይል የለውም [ራዕይ 20÷6]። እግዚአብሔር ለኃጥአን የሚፋጅ እሳት ሆኖ ሳለ ለሕዝቦቹ ግን ብርሃንና ጋሻ ነው። [መዝ 84÷11]።GCAmh 483.3

    “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ የፊተኛው ሰማይና የፊተኛው ምድር አልፈዋልና” [ራዕይ 21÷1]። ኃጥአንን የሚበላው እሳት ምድርን አንጽቷታል። እያንዳንዱ የእርግማን ምልክት ተጠርጓል። የሚያስፈራውን የኃጢአትን ውጤት ያሳይ ዘንድ በተዋጁት ፊት ለዘላለም የሚቃጠል ሲኦል አይኖርም።GCAmh 483.4

    አንድ ማስታወሻ ብቻ ይቀራል፦ አዳኛችን ለዘላለም የስቅላቱን ጠባሳ እንደያዘ ይኖራል። በቆሰለው ራሱ፣ በጎኑ፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ብቻ ኃጢአት ያመጣው ጨካኝ ሥራ ምልክት ይቀራል። ክርስቶስን በክብሩ ሲመለከት ሳለ ነብዩ እንዲህ አለ፦ “ፀዳሉ እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል” [እንባ 3÷4]። ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀው ቀዩ ጅረት የወጣበት ያ የቆሰለ ጎን — የአዳኙ ክብር እዚያ ነው። “ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል።” “ለማዳን የበረታ”ው [ኢሳ 63፥1]፤ በመዋጀት መስዋዕት አማካኝነት የእግዚአብሔርን ምሕረት ባቃለሉት ላይ ፍርድን ይተገብር ዘንድ ብርቱ ሆነ። የመዋረዱ ምልክቶችም የእርሱ የክብሩ ከፍታ ጥግ ናቸው፤ ወደፊት ባሉት የዘላለም ዘመናት የቀራንዮ ቁስሎች ምስጋናውን ይገልጣሉ፤ ኃይሉንም ያውጃሉ።GCAmh 483.5

    “አንተ የመንጋ ግንብ ሆይ፣ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ ወደ አንተ ትመጣለች፤ የቀደመችው ግዛት” [ሚክ 4÷8]። “የዋጃትን ገንዘብ (the redemption of the purchased possession)” [የሚወስድበትን] ጊዜ — የሚንበለበለው ሰይፍ የመጀመሪያዎቹን ጥንዶች ከኤደን ከከለከለ ጀምሮ ቅዱሳን ሰዎች በናፍቆት ሲጠብቁት የኖሩት ሰዓት መጥቷል [ኤፌ 1÷14]። ግዛቱ ትሆን ዘንድ ለሰው መጀመሪያ (ከጥንት) የተሰጠችው ምድር በሰይጣን እጅ ተላልፋ ተሰጥታ ኖራ በታላቁ የማዳን እቅድ ተመልሳለች። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል… ምድርን የሰራና ያደረገ ያፀናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት” [ኢሳ 45÷18]። የተዋጁት የዘላለም መኖሪያ ስትሆን እግዚአብሔር መጀመሪያ ምድርን የፈጠረበት አላማ ይፈፀማል። “ፃድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” [መዝ 37÷29]።GCAmh 484.1

    የወደፊቱ ውርስ ከሚገባው በላይ ቁሳዊ ሆኖ እንዳይታይ ያለው ስጋት፣ የራሳችን ቤት እንደሆነ አድርገን እንድንናፍቀው ከሚያደርጉን እውነቶች እንዲሸሹ ብዙዎችን መርቶአል [የሰማይ ቤታችን የተገለጸበት አውድ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው (ምሳሌያዊ የሆነ) እንጂ እንደተብራራው በትክክል እንደዚያው አይነት አይደለም ብለው እንዲያስቡ መርቷቸዋል]። በአባቱ ቤት እልፍኞችን ሊያዘጋጅላቸው እንደሄደ ደቀ-መዛሙርቱ እርግጠኛ እንዲሆኑ ክርስቶስ ነግሯቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል አስተምህሮ የሚቀበሉ ሁሉ በሰማይ ስላለው ቤት ሙሉ በሙሉ እውቀት የሌላቸው አይሆኑም። ሆኖም “አይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” ነው[1ኛ ቆሮ 2÷9]። ፃድቃን የሚወርሱትን ሽልማት የሰው ቋንቋ ይገልጸው ዘንድ ይሳነዋል። የሚያዩት ብቻ የሚያስተውሉት ይሆናል። ይህ ውስን የሆነ አእምሮ የእግዚአብሔርን ገነት ክብርና ግርማ ሞገስ ይረዳው ዘንድ አይችልም።GCAmh 484.2

    የዳኑት ውርስ በመጽሐፍ ቅዱስ አገር ተብሎ ይጠራል [ዕብ 11÷14-16]። በዚያ ቦታ ሰማያዊው እረኛ መንጋውን ወደ ሕያው ምንጮች ይመራቸዋል። የሕይወት ዛፍ በየወሩ ፍሬ ትሰጣለች፤ ቅጠሎችዋም ለአሕዛብ አገልግሎት ይውላሉ። ሳያቋርጡ የሚፈሱ እንደ መስታወት ድንጋይ የነጹ ጅረቶች፣ ባጠገባቸው ቅጠላቸውን የሚያውለበልቡ ጥላቸውን ለዳኑት ባዘጋጀው መንገድ ላይ የሚያሳርፉ ዛፎችም አሉ። ወደ ውብ ኮረብታማ ስፍራዎች የሚለወጡ የተነጣጠሉ ሜዳዎች አሉበት፤ የእግዚአብሔር ተራራዎችም ግዙፍ ቁንደዶአቸውን አምጥቀው ገዝፈው ይታያሉ። በነዚያ ፀጥታ በሰፈነባቸው ሜዳዎች በሕያው ምንጮች አፋፍ ለረዥም ጊዜ ተጓዥና ተቅበዝባዥ የነበሩት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቤታቸውን ያገኛሉ።GCAmh 484.3

    “ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በፀጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል”። “ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፣ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን፣ በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ”። “ቤቶችንም ይሰራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሰሩም፤ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም….እኔም የመረጥኳቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።” [ኢሳ 32÷18፤ 60÷18፤ 65÷21፣22]።GCAmh 484.4

    በዚያ፣ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሃውም ሐሴት ያደርጋል፤ እንደ ጽጌረዳም ያብባል”። “በእሾህም ፋንታ ጥድ፣ በኩርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል” [ኢሳ 35÷1፤ 55÷13]። “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፤ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል”.... ታናሽ ልጅ ይመራቸዋል”። “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም” [ኢሳ 11÷6፣9] ይላል እግዚአብሔር።GCAmh 485.1

    በሰማይ ከባቢ አየር ህማም ይኖር ዘንድ አይችልም። እንባ፣ የቀብር ስደራ [የቀብር መኪኖች ሰልፍ] ወይም የመርዶ አርማ እዚያ አይኖርም። “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ኃዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” [ራዕይ 21÷4]። “በዚያም የሚቀመጥ፣ ታምሜያለሁ አይልም፤ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።” [ኢሳ 33÷24]።GCAmh 485.2

    የከበረችው የአዲሲቱ ምድር ዋና ከተማ አዲሲቷ የሩሳሌም “በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ” ሆና አለች [ኢሳ 62÷3]። “ብርሃንዋም እጅግ እንደከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበር።” “አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገስታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ”[ራዕይ 21÷11፣24]። እግዚአብሔርም አለ፦ “እኔም በየሩሳሌም ሐሴት አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል” [ኢሳ 65÷19]። “እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።” [ራዕይ 21÷3]።GCAmh 485.3

    በእግዚአብሔር ከተማ “ሌሊት አይኖርም”፤ እረፍት የሚሻ፣ የሚያስፈልገውም የለም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረግም ሆነ ለስሙ ምስጋና በመስጠት መድከም አይኖርም። ሁልጊዜም የጧት ትኩስነት (አዲስነት) ይሰማናል፤ ከማብቂያውም ፈጽሞ የራቅን እንሆናለን። “አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራባቸዋልና የመብራት [የኩራዝ/ሻማ] ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም” [ራዕይ 22÷5]። የፀሐይ ብርሃን በደማቅ ጨረር፣ ሆኖም በማያሳምም ፀዳል፣ ከእኛ የቀትር ብርሃን በሚበልጥ፣ መለካት በማይችል ነፀብራቅ ይተካል። የእግዚአብሔርና የበጉ ክብር ቅድስቲቱን ከተማ በማይደበዝዝ ብርሃን ያጥለቀልቃታል። የዳኑት በፀሐይ-አልባ ዘላለማዊ ቀን ይመላለሳሉ።GCAmh 485.4

    “ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም” [ራእይ 21÷22]። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከአብና ከልጁ ጋር ያልተገደበ የአብሮነት ዕድል ይኖራቸዋል። አሁን “በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን” [1ኛ ቆሮ 13÷12]። የእግዚአብሔር ምሳሌ በመስታወት እንደተንፀባረቀ ያህል ሆኖ በተፈጥሮ ሥራና ከሰዎች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት በኩል እናያለን። ነገር ግን የሚያደበዝዘው መጋረጃ በመካከላችን ሳይኖር ፊት ለፊት እናያለን። በመገኘቱ እንቆማለን፣ የፊቱንም ክብር እናያለን።GCAmh 485.5

    እዚያ የዳኑት “ያውቃሉ እነርሱ ደግሞ እንደታወቁ”፤ እግዚአብሔር ራሱ የተከለው በነፍስ ውስጥ ያለው ፍቅርና ርኅራኄ እዚያ ፍጹም እውነተኛና ጣፋጭ ልምምድ ያገኛል። ከቅዱስ ፍጡራን ጋር ያለው አብሮነት፤ ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ነጭ ካደረጉ፤ ለዘመናት ከነበሩ ታማኞችና ከተባረኩ መላዕክት ጋር ያለው ማህበራዊ ኑሮ “የሰማይና የምድር ጥምር ቤተሰብ” [ኤፌ 3÷15]”ን ሁሉ የሚያቆራኘው ቅዱስ ትስስር — እነዚህ ሁሉ የተዋጁትን ደስታ ለመጨመር የሚያግዙ ናቸው።GCAmh 486.1

    እዚያ የማይሞቱ አዕምሮዎች የመፍጠር ኃይልን ተዓምራት፣ የሚያድነውን ፍቅር ምስጢራት፣ በማይከስም ሐሴት ያሰላስላሉ። እግዚአብሔርን ይረሱ ዘንድ የሚፈትናቸው፣ የሚያታልለው ጨካኙ ባላንጣ እዚያ የለም። እዚያ ሁሉም ጉልበት ይጠነክራል፤ እያንዳንዱ ችሎታ ይጨምራል። እውቀትን መቅሰም አእምሮን አያዝለውም፣ የአካላዊና የአእምሮአዊ ኃይላትንም አያደክምም። ታላላቅ የሥራ እቅዶች ይተገበራሉ፤ የገዘፉ ምኞቶች ወደ ፍፃሜ ይመጣሉ፤ የመጠቁት ጉጉቶች እውን ይሆናሉ። ሆኖም አሁንም እንደገና መወጣት ያለባቸው አዳዲስ ከፍታዎች፣ የሚያስደምሙ አዳዲስ ድንቃድንቆች፣ ማስተዋል የሚጠይቁ አዳዲስ እውነቶች፣ የአካልን የአእምሮንና የነፍስን ኃይላት የሚጋብዙ አዳዲስ ጉዳዮች ብቅ ይላሉ።GCAmh 486.2

    በስነ-ፍጥረት ውስጥ በዓለማት ያሉት እምቅ መዛግብት ሁሉ የተዋጁት ያጠኑዋቸው ዘንድ የተከፈቱ ይሆናሉ። በሞት እግር-ብረት ሳይገደቡ ከሰው ልጅ መከራ የተነሳ በሃዘን ይሸበሩ፣ እዳዋ በተከፈለላት ነፍስ ምክንያት ደግሞ የደስታ መዝሙር ይዘምሩ ወደ ነበሩ ወደ እነዚያ ሩቅ ዓለማት በማይደክመው ክንፋቸው ይበራሉ። ሊነገር በማይችል ደስታ የምድር ልጆች ወዳልወደቁት ተድላና ጥበብ ይገባሉ። ለዘመን፣ ለዘመናትም በእግዚአብሔር የእጅ ሥራ ላይ ሲደረግ ከነበረው ጥናት የተከማቸ እውቀትና መረዳት ተካፋይ ይሆናሉ። ባልደበዘዘ እይታ የፍጥረትን ክብር ያያሉ፤ ፀሐዮችና ከዋከብት በግሩም የአሠራር ቅንጅታቸው ሁሉም በተሰጣቸው የሃላፊነት ሥነ-ሥርዓት የመለኮትን ዙፋን ከበው ሲዞሩ ይመለከታሉ። በጥቃቅንና ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ላይ የፈጣሪ ሥም ተጽፎባቸዋል፤ በሁሉም ላይ የኃይሉ ጥልቀት ይገለጽባቸዋል።GCAmh 486.3

    የዘላለም ዓመታት እየተጠቀለሉ ሲያልፉ ሳለ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ክርስቶስ ጥልቅ፣ ብሎም የበለጠ ግሩም ድንቅ መገለጦችን ያመጣሉ። እውቀት እየጨመረ እንደሚሄድ ሁሉ ፍቅርም፣ አክብሮትም፣ ደስታም ይጨምራሉ። ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የበለጠ እየተማሩ ሲሄዱ ለባህርይው ያላቸው አድናቆት የላቀ ይሆናል። የሱስ የድነትን ባለጠግነት በፊታቸው ሲገልጽላቸው፣ ከሰይጣንም ጋር በነበረው ታላቁ ተጋድሎ የተቀዳጃቸውን አንፀባራቂ ስኬቶች ሲያሳያቸው የተዋጁት ልቦች በበለጠ መሰጠት ይፈነድቃሉ። በሚያፍነከንክ ደስታም የወርቅ በገናዎችን ይደረድራሉ። አሥር ሺህ ጊዜ አሥር ሺህ፣ ሺህ በሺህ የሆኑ ድምፆች ኃያሉን የምስጋና መዝሙር ያደምቁ ዘንድ አንድ ይሆናሉ።GCAmh 486.4

    “በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባህርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፣ በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።” [ራዕይ 5÷13]።GCAmh 486.5

    ታላቁ ተጋድሎ (ተቃርኖ) አብቅቷል። ኃጢአትና ኃጢአተኞች ከእንግዲህ የሉም። መላው ዩኒቨርስ ንፁህ ነው። አንድ የመስማማትና የደስታ ትርታ በሰፊው ፍጥረት ሁሉ ይመታል። ወሰን በሌለው ህዋ ዳርቻዎች ሁሉ ሕይወት፣ ብርሃንና ደስታ ሁሉን ከፈጠረ ከእርሱ ዘንድ ይፈሳሉ። እጅግ ደቃቅ ከሆነችው ክፍለ-ቁስ (atom) እስከ ግዙፉ ዓለም፣ ሕይወት ያለውም ሆነ ሕይወት የሌለው፣ ባልደበዘዘ ውበታቸውና ፍፁም ደስታቸው፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ብለው ያውጃሉ።GCAmh 487.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents