Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፰—ሉተር በጉባኤው ፊት

    አዲሱ ንጉሠ ነገሥት ቻርለስ 5ኛ ወደ ጀርመን ዙፋን ሲወጣ የሮም መልክተኞች የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክታቸውን ለመለገስ፣ ኃይሉንም ተጠቅሞ ተሐድሶውን እንዲቃወም ለማግባባት ተጣደፉ። በሌላ በኩል ደግሞ ቻርለስ ዘውድ እንዲደፋ በመርዳት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጉ ንጉሠ ነገሥቱ ከባድ ውለታ እንዳለበት እንዲሰማው ያደረገው የሳክሶኒው መራጭ፣ የመሰማት መብት ሳይሰጠው በሉተር ላይ እርምጃ እንዳይወስድ ለመነው። በዚህም ንጉሠ ነገሥቱ በታላቅ ግራ መጋባትና ሐፍረት ውስጥ ወደቀ። ጳጳሳውያኑን ሊያረካ የሚችለው ሉተር ሞት እንዲፈረድበት የሚያዝ መንግሥታዊ አዋጅ ብቻ ነው። መራጩ ደግሞ “ግርማዊነቱ ወይም ማንም ሰው የተሐድሶ አራማጁ ጽሁፎች ስህተት እንደሆኑ አረጋግጦ ሊያሳየው የቻለ እንደሌለ” አስረግጦ በመናገር “በፍርድ ቤት፣ በተማሩ፣ ሐይማኖተኛና አድልኦ በማያደርጉ ዳኞች ፊት ቀርቦ ራሱ መልስ መስጠት ይችል ዘንድ ዶክተር ማርቲን ንጉሣዊ ጥበቃ ያለው የይለፍ ፈቃድ እንዲሰጠው” ጠየቀ።-D’Aubigné, b. 6, ch. 11።GCAmh 109.1

    አሁን ቻርለስ ወደ ስልጣን እንደወጣ ወደተደረገው፣ በዎርምስ ወደተጠራው የመላው ጀርመን ግዛቶች ጉባኤ የሁሉም ቡድኖች ቀልብ ተሳበ። በዚህ ብሔራዊ ጉባኤ የሚጤኑ ጠቃሚ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ጠቃሚ ነገሮች ነበሩ። አስፈላጊ የሆኑ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶችን ለመመርመር በተጠራው በዚህ ጉባኤ የጀርመን ልዑላን ወጣት ንጉሠ ነገሥታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገናኙት ነበር። ከሁሉም የአባት አገር ዳርቻዎች የመጡ የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ነበሩ። በዘር ላገኙት መብት ቅንዓት ያላቸው ትውልደ-ልዑላን፣ ኃያላንና መንግሥታዊ ሹሞች፤ በስልጣን እርከንና በኃይል እንደሚበልጡ ማወቃቸው ያፈካቸው ኃይማኖታዊ ልዑላን፤ የተከበሩ የቀድሞ የጦር አርበኞች ከታጠቁ አገልጋዮቻቸው ጋር፤ ከውጪና ከሩቅ አገር የመጡ አምባሳደሮች ሁሉ በዎርምስ ተሰበሰቡ። ሆኖም የዚያን ግዙፍ ጉባኤ ትኩረት በተለየ ሁኔታ የሳበው የሳክሰኑ ተሐድሶ አራማጅ ጉዳይ ነበር።GCAmh 109.2

    ቀደም ብሎ ሉተርን ወደ ጉባኤው ይዞት እንዲመጣ፣ ጥበቃ እንደሚደረግለት፣ አወዛጋቢዎቹ ጥያቄዎች ብቁ ከሆኑ ሰዎች ጋር ነፃ ውይይት እንዲደረግባቸው ቻርለስ ለመራጩ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ሉተር በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ለመቅረብ ተሸበረ። በዚህ ጊዜ ጤናውም ብዙ የሚያወላዳ አልነበረም፤ ሆኖም ለመራጩ ሲጽፍ፦ “በብቁ ጤንነት ወደ ዎርምስ የሚደርገውን ጉዞ ማድረግ ካልቻልኩ፣ ተጭኜም ቢሆን እንደታመምሁ ወደዚያ እወሰዳለሁ። ያዘዘኝ ራሱ ንጉሠ ነገሥቱ ስለሆነ የራሱ የእግዚአብሔር ጥሪ እንደሆነ አልጠራጠርም። በፊታቸው እንድቀርብ የፈለጉበት ምክንያት ከእኔ አንዳች መረጃ ለማግኘት እንዳልሆነ እርግጥ በመሆኑ፣ እንደሚገመተው ሁከት ሊፈጥሩብኝ ካሰቡም፣ ይህንን ጉዳይ ለጌታ እጆች አሳልፌ እሰጣለሁ። በእቶኑ እሳት ውስጥ ሶስቱን እሥራኤላውያን የጠበቀ እርሱ አሁንም ሕያው ነው፤ ይገዛልም። ያድነኝ ዘንድ ፈቃዱ ባይሆን፣ የእኔ ሕይወት የሚያስገኘው ፋይዳ ኢምንት ነው። ብቻ ወንጌሉ እግዚአብሔርን በማይመስሉ ሰዎች ዘንድ ለማላገጫነት እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ እናድርግ፤ እንዲያሸንፉ ከምንፈቅድላቸው ይልቅ ለእርሱ [ለወንጌሉ] በመቆም ደማችንን እናፍስስ። ለወንድሞቼ ድነት ብልጫ ያለውን አስተዋፅኦ የሚያደርገው ሕይወቴ ይሁን ሞቴ ማን ያውቃል?” “አንዳች ነገር ከእኔ ብትጠብቁ እንኳ፣ ሽሽት ወይም ክህደት ይፈጽማል ብላችሁ እንዳትጠብቁ፤ መሸሽ አልችልም፣ የማምነውን መካድማ እንዲያውም ጭራሽ የማይሞከር ነው።”-Ibid, b. 7, ch. 1።GCAmh 109.3

    ሉተር በጉባኤው ፊት የመቅረቡ ወሬ በዎርምስ ሲናፈስ አጠቃላይ ግርግር ሆነ። ይህ ጉዳይ በተለየ ሁኔታ ኃላፊነት የተሰጠውን የሊቀ-ጳጳሱን ልዑክ አሊያንደርን አሳሰበው፤ አበሳጨውም። ውጤቱ ለጳጳሳዊው ሥርዓትዓላማአጥፊ እንደሚሆን ተረዳ። ሊቀ-ጳጳሱ አስቀድሞ የጥፋተኝነት ፍርድ ያሳረፈበትን ጉዳይ እንደገና ወደ ምርመራ ማምጣት የሉዓላዊ ሊቀ-ጳጳሱን ስልጣን መናቅ ይሆናል። በተጨማሪም የአንደበተ ርቱዕው ኃይለኛ የመከራከሪያ ነጥቦች ብዙ ልዑላን ከጳጳሳዊ ሥርዓት ፊታቸውን እንዲመልሱ እንደሚያደርጋቸውም በማመን ፈርቷል። በመሆኑም ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ሉተር በጉባኤው ፊት መቅረቡን በመቃወም ከቻርልስ ጋር ተከራከረ። በዚሁ ጊዜ ሉተር ከቤተ ክርስቲያን እንዲገለል የሚያዘው አዋጅ ይፋ ሆነ፤ ይህና የልዑኩ ውትወታ ንጉሠ ነገሥቱ እንዲሸነፍ ገፋፋው። ንጉሠ ነገሥቱ ለመራጩ ደብዳቤ በመፃፍ ሉተር ተሳስቼ ነበር ለማለት ካልሆነ በስተቀር በዊተርበርግ እንዲቆይ አዘዘው።GCAmh 110.1

    በዚህ ድሉ ባለመርካት፣ አሊያንደር የነበረውን ኃይልና ብልጠት ሁሉ በመጠቀም የሉተርን ውግዘት ለማግኘት ጣረ። ለተሻለ ግብ ቢውል መልካም በነበረ የዓላማ ጽናት፣ ሕዝብን በማሳመጽ፣ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ በማስነሳት፣ በኃይማኖተ-ቢስነትና እግዚአብሔርን በመስደብ ጥፋት የተሐድሶ አራማጁን በመወንጀል የልዑላንን፣ የቤተ ክህነት ሰዎችንና የሌሎች የጉባኤ አባላትን ትኩረት ለመሳብ ያላሰለሰ ጥረት አደረገ። ነገር ግን በልዑኩ የተንፀባረቀው የሃይለኝነትና የስሜታዊነት መንፈስ፣ የሚገፋፋው መንፈስ የትኛው እንደሆነ በግልጽ ያሳየ ነበር። “እርሱ ይህን እንዲያደርግ የሚገፉት ምክንያቶቹ ለኃይማኖት ያለው ትክክለኛ ቅንዓት ሳይሆን” አለ፣ አንድ ጳጳሳዊ ፀሃፊ፣ “የጥላቻና የበቀል ጥማት ነው።”-Ibid, b. 7, ch. 1። አብዛኛው ጉባኤ ከምን ጊዜውም የበለጠ የሉተርን ዓላማ በአዎንታ ወደ መመልከቱ አዘነበለ።GCAmh 110.2

    በእጥፍ ጥረት፣ አሊያንደር፣ ንጉሠ ነገሥቱ የሊቀ-ጳጳሱን አዋጆች የማስፈጸም ኃላፊነት እንዳለበት በመናገር ሊገፋፋው ሞከረ፤ ሆኖም በጀርመን ሕግ መሰረት ያለ ልዑላኑ ስምምነት ይህ ተግባራዊ የሚሆን ባለመሆኑ በመጨረሻ በልዑኩ የማያቋርጥ ንዝነዛ ተሸንፎ ጉዳዩን በጉባኤው እንዲያቀርብ ፈቀደለት። “ለልዑኩ የኩራት ቀን ነበር። ጉባኤው ታላቅ ነበር፣ ተልዕኮው ደግሞ ከዚያ በላይ። አሊያንደር የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እናትና እመቤት ለሆነችው ሮም ጥያቄ ሊያቀርብ ነበር። በተሰበሰቡ የክርስትና ግዛት መሪዎች ፊት የጴጥሮስን ልዑልነት ሊያረጋግጥ [ተዘጋጅቶ] ነበር። የመናገር ተሰጥኦ ነበረው፤ ታላቁን ዕድል ይጠቀምበት ዘንድ ተነሳ። ሮም፣ ከመወገዝዋ በፊት፣ እጅግ በተከበረው ልዩ ፍርድ ቤት ፊት ምርጥ ከሚባሉ ተናጋሪዎችዋ መካከል በቀንደኛው አማካኝነት ቀርባ መጠይቅዋን(መከራከሪያዋን) ታቀርብ ዘንድ የመለኮታዊ እጅ አቅዶት ነበር።”-Wylie, b. 6, ch. 4። የተጠራጠሩ የተሐድሶ አራማጁ ደጋፊዎች የአሊያንደር ንግግር ምን ውጤት እንደሚያስከትል ይጠባበቁ ነበር። የሳክሶኒ መራጭ በዚያ አልተገኘም ነበር፤ የጳጳሱ ልዑክ መልእክት ይዘት ምን እንደሚመስል ይመረምሩ ዘንድ ግን አንዳንድ የኮሚቴ አባላቱ እንዲገኙ አዞ ነበር።GCAmh 110.3

    በተማረው የእውቀት ኃይልና በንግግር ጥዑምነቱ አሊያንደር እውነትን ይገለብጥ ዘንድ ጀመረ። ሉተር የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት፣ በሕይወት ያሉትና የሞቱት፣ የመሪዎችና የተራው ምዕመን፣ የምክር ቤቶችና የግል ክርቲስያኖች ሁሉ ጠላት እንደሆነ በማሳየት በክስ ላይ ክስ ደራረበበት። “በሉተር ስህተቶች ውስጥ”፣ አለ፣ “አንድ መቶ ሺህ መናፍቃን እንዲቃጠሉ ማድረግ የሚችል በቂ ምክንያት አለ።”GCAmh 111.1

    በማጠቃለያው፣ በተሐድሶው አማኞች ላይ ያለውን ንቀት ለማንፀባረቅ ሞከረ፦ “እነዚህ ሉተራዊያን ሁሉ ምንድን ናቸው? በስህተት ከመሩት አእምሮውን ካጣመሙት ሕዝብ ጋር የቆሙ፣ ረባሽና ባለጌ፣ የቃላት ፍቺ ፈልፋዮች፤ የተዋረደ ሕይወት የሚመሩ መነኮሳት፣ ገልቱ የሕግ ሰዎችና የቆረቆዙ መሳፍንት ጥርቅም ናቸው። የካቶሊክ ጉባኤ በቁጥር በእውቀትና በኃይል እንዴት እጅግ አብላጫ ያለው ነው! አንድ ድምጽ የሆነ የዚህ የተመሰከረለት ጉባኤ አዋጅ የተራውን (እውቀት የሌለውን) ሰው አይን ይከፍታል፣ ላልጠረጠረው አደጋውን ያመላክተዋል፤ የሚንገዳገደው እንዲፀና፣ ደካማ ልብ ያለው እንዲጠነክር ያደርጋል።” አለ።-D’Aubigné, b. 7, ch. 3።GCAmh 111.2

    በእንደዚህ አይነት መሳሪያዎች የእውነት ጠበቃዎች በየዘመናቱ ሲጠቁ ኖረዋል። መሰረት የጣሉትን ስህተቶች በመቃወም ግልጽና ቀጥተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ትምህርቶች ለማቅረብ በደፈሩት ላይ ዛሬም እነዚያው መከራከሪያዎች በተቃርኖ እየተሰነዘሩባቸው ነው። “እነዚህ አዲስ አስተምህሮ የሚሰብኩ እነማን ናቸው?” ይላሉ ተወዳጅ የሆነ ኃይማኖት አፍቃሪዎች። “ያልተማሩ፣ በቁጥር አናሳና ከዝቅተኛ መደብም ናቸው። ሆኖም እውነትን እንደያዙና የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሆኑ ይናገራሉ፤ ገልቱና የተታለሉ ናቸው። ቤተ ክርስቲያናችን በብዛትና ተጽዕኖ በማሳደር እንዴት ታላቅ ናት! ስንት የተማሩና ታላላቅ ሰዎች በመካከላችን ናቸው! ከጎናችን ያለው እንዴት ያለ የበለጠ ኃይል ነው!” እነዚህ መከራከሪያዎች በዓለም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያላቸው ናቸው፤ እውነትነታቸውን ለማረጋገጥ ግን ከተሐድሶ አራማጁ ዘመን በተሻለ ዛሬ መረጃ ሊቀርብላቸው የሚችሉ አይደሉም።GCAmh 111.3

    ብዙዎች እንዳሰቡት ተሐድሶው በሉተር አላበቃም። የዚህ ዓለም ታሪክ እስኪዘጋ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። ሉተር በእርሱ ላይ ያበራ ዘንድ እግዚአብሔር የፈቀደለትን ብርሐን ለሌሎች የማንፀባረቅ ታላቅ ኃላፊነት ነበረበት። ዓለም ይቀበል ዘንድ የተገባውን ብርሐን ሁሉ ግን እርሱ አልተቀበለም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አዲስ ብርሐን በቀጣይነት እያረፈ ነው፤ አዳዲስ እውነቶችም በቀጣይነት እየተገለጡ ናቸው።GCAmh 111.4

    የልዑኩ መልእክት በጉባኤው ዘንድ ጥልቅ አሻራ አሳረፈ። ግልጽና አሳማኝ የሆኑትን የእግዚአብሔርን ቃል እውነቶች ይዞ የጳጳሱን ተጋዳይ ብትንትኑን ያወጣ ዘንድ ሉተር በዚያ አልነበረም። የተሐድሶ አራማጁን ለመደገፍ የተደረገ አንዳች ሙከራ አልነበረም። የነበረው አጠቃላይ አንደምታ እርሱንና ያስተማራቸውን አስተምህሮዎቹን ለማውገዝ ብቻ ሳይሆን፣ ከተቻለ ኑፋቄውንም ከስሩ የመመንገል ስሜት ነበር። ሮም አላማዋን ለማፅናት ተወዳዳሪ የሌለው ተስማሚ ዕድል አግኝታለች። ራስዋን ከበደል ነፃ ለማድረግ ማለት ያለባት ሁሉ ተብሏል። ነገር ግን ግልጽ የሆነው ድል የሽንፈት ምልክት ነበር። ጦርነቱ በግልጽ ሜዳ ላይ ስለሚካሄድ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በእውነትና በሃሰት መካከል ያለው ልዩነት የበለጠ እየጎላ ይመጣል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሮም እንደቀድሞው ደህንነቷ በአስተማማኝ ተጠብቆ ትቆይ ዘንድ ፈፅማ አትችልም።GCAmh 111.5

    አብዛኛዎቹ የጉባኤው አባላት ሉተር ለሮም የበቀል እርምጃ ተላልፎ እንዲሰጥ ባያመነቱም በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋውን የስነ-ምግባር ማሽቆልቆል ተመልክተው ብዙዎቹ እጅግ ያወግዙት ስለነበር [በቤተ ክርስቲያን]ስልጣን መዋቅሩ ብልሹነትና አልጠግብ ባይነት ምክንያት በጀርመን ሕዝብ ላይ የወደቀው ስቃይና እንግልት እንዲገታ ፍላጎት ነበራቸው። ልዑኩ የጳጳሳዊው ሥርዓት አስተዳደር እጅግ መልካም እንደሆነ አድርጎ ነበር ያቀረበው። የጳጳሳዊው አምባገነናዊ አስተዳደር ያስከተለውን ውጤት በትክክል ይተነትን ዘንድ እግዚአብሔር ከጉባኤ አባላቱ መካከል አንድ ሰው አስነሳ። በተከበረ ልበ ሙሉነት የሳክሶኒው መስፍን ጊዮርጊስ በታላቁ ጉባኤ ቆሞ የጳጳሳዊውን ሥርዓት ማጭበርበሪያዎችና ነውሮች፣ ያስከተሉትንም አስከፊ ውጤት በሚዘገንን ሁኔታ ልቅም አድርጎ፣ በነቂስ ተናገረ። ሲያጠቃልልም እንዲህ አለ፦GCAmh 112.1

    “እነዚህ የተጠቀሱት ጉዳቶች ልታስተካክላቸው ከሚገቡ፣ ሮምን በመቃወም ከሚነሱ ጉዳዮች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ሁሉም ሀፍረት ወደ ጎን ተገፍትሮ፣ ያለማቋረጥ የሚሳደደው አንድ ዓላማ ብቻ ነው፤ ገንዘብ! ሁሌም ተጨማሪ ገንዘብ! እውነቱን ለማስተማር ኃላፊነት የተጣለባቸው እነርሱ ከሀሰት በቀር ሌላ እንዳይናገሩ ሆነዋል፤ የሚያደርጉትን ያለገደብ እንዲቀጥሉበት መተዋቸው ብቻ ሳይሆን ወሮታም ተሰጥቷቸዋል። ምክንያቱም ውሸታቸው በበዛ መጠን ትርፋቸውም ይጨምራልና ነው። ይህ ብዙ የጠነቡ ጅረቶች የሚፈልቁበትና ወደ ሁሉም ስፍራ የሚፈሱበት የተበከለው ምንጭ ነው። ልቅ የሆነ የገንዘብ አባካኝነትና ንፉግነት አንድ ላይ የሚሄዱ ናቸው።” “ወይኔ! በቤተክህነት ሰዎች የሚፈፀም ድርጊት ነው አያሌ ድሃ ነፍሳትን ወደ ዘላለም ጥፋት የሚማግደው። ፍጹም የሆነ (ልቅም ያለ) ተሐድሶ ተግባራዊ መሆን ይገባዋል።”-Ibid, b. 7, ch. 4።GCAmh 112.2

    ከዚህ የተሻለ ጠንካራና አሳማኝ፣ የጳጳሳዊውን ሥርዓት ጥፋቶች የሚያወግዝ ንግግር በሉተር በራሱ እንኳ ሊቀርብ የሚችል አልነበረም። ይህንን የተናገው ሰው የተሐድሶ አራማጁ የለየለት ጠላት መሆኑ ደግሞ ለተናገረው ንግግር ተጨማሪ ክብደት ሰጥቶት ነበር።GCAmh 112.3

    የጉባኤው አይኖች ቢከፈቱ ኖሮ የእግዚአብሔር መላዕክት በመካከላቸው ቆመው፣ በስህተት ፅልመት ላይ ከዳር እስከዳር የብርሐን ጮራ ሲለቁ፣ እውነትን ይቀበሉ ዘንድ አእምሮዎችንና ልቦችን ሲከፍቱ በተመለከቱ ነበር። የተሐድሶውን ተቃዋሚዎች ሳይቀር በመቆጣጠር ሊከናወን ላለው ታላቅ ሥራ መንገድ ያመቻቸው የእውነትና የጥበብ አምላክ ኃይል ነበር። ማርቲን ሉተር በዚያ አልነበረም፤ ከሉተር የሚበልጠው የእርሱ [የጌታ] ድምጽ ግን በዚያ ጉባኤ ውስጥ ተሰምቶ ነበር።GCAmh 112.4

    በጀርመን ሕዝብ ላይ ከባድ ቀንበር የጫነው ጳጳሳዊ ጭቆና በዝርዝር ተጣርቶ ይቀርብ ዘንድ ጉባኤው ወዲያውኑ ኮሚቴ አቋቋመ። ይህ መቶ አንድ የተብራሩ ዝርዝሮችን የያዘው መዝገብ፣ እነዚህን ጥፋቶች ለማረም ወዲያውኑ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ከሚለምን መጠይቅ ጋር ለንጉሠ ነገስቱ ቀረበለት። “ምን ያህል የክርስቲያን ነፍስ ጥፋት ነው” አሉ ጠያቂዎቹ “ምን አይነት የፍርድ መጓደል፣ ምን አይነት የኃይል ዘረፋ ነው የእነዚህ የክርስትናው ዓለም መንፈሳዊ መሪ ድጋፍ የሚሰጣቸው አሳፋሪ ድርጊቶች የየዕለት ፍሬዎች። የአገራችን ክፋትና ውርደት መቀልበስ አለበት። እናም በታላቅ ትህትና ሆኖም በአስቸኳይ አጠቃላይ ተሐድሶ እንዲደረግ እንዲያዙ፣ ሥራው እንዲጀምርና እንዲከናወን ፈቃድዎ ይሆን ዘንድ እንለምንዎታለን።”-Ibid, b. 7, ch. 4።GCAmh 112.5

    በዚህ ጊዜ ጉባኤው ተሐድሶ አድራጊው እንዲቀርብ ጠየቀ። የአሊያንደር ልመና፣ ተቃውሞና ማስፈራሪያ ቢቀጥልም ንጉሠ ነገሥቱ በመጨረሻ ተስማምቶ በጉባኤው ፊት ይቀርብ ዘንድ ለሉተር መጥሪያ ወጣ። ከመጥሪያው ጋር ደህንነቱ ወደሚጠበቅበት ሥፍራ በደህና እንደሚመለስ የሚያረጋግጥለት የይለፍ ተዘጋጅቶለት ነበር። ወደ ዎርምስ ይዞት እንዲመጣ ኃላፊነት በተሰጠው ህጋዊ መልክተኛ አማካኝነት መጥሪያውና የይለፍ ፈቃዱ ወደ ዊተንበርግ ተላከ።GCAmh 113.1

    የሉተር ጓደኞች በድንጋጤ ተዋጡ፤ ተጨነቁም። በእርሱ ላይ የተቀሰረው፣ ሚዛናዊነት የጎደለው ጥላቻና ጠላትነት ምን እንደሆነ ስለሚያውቁ፣ የይለፍ ወረቀቱ እንኳ እንደማይከበር በመስጋት ሕይወቱን አደጋ ላይ እንዳይጥል ለመኑት። ሲመልስም፦ “ጳጳሳዊያኑ የእኔን መኮነንና መሞት ይመኛሉ እንጂ በዎርምስ እኔን የማየት ፍላጎት የላቸውም። ምንም እርባና የለውም። ለእኔ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቃል ፀልዩ…. እነዚህን የሰይጣን አገልጋዮች ድል እነሳ ዘንድ ክርስቶስ መንፈሱን ይሰጠኛል። በሕይወት እስካለሁ ድረስ እጠላቸዋለሁ፤ በሞቴም አሸንፋቸዋለሁ። እምነቴን እንድክድ ለማስገደድ በዎርምስ በሥራ ላይ ተጠምደዋል። የአቋም ለውጤ የሚሆነው ይህ ነው፦ ሊቀ-ጳጳሱ የክርስቶስ ወኪል እንደሆነ ከአሁን በፊት ተናግሬ ነበር፤ አሁን ደግሞ እላለሁ፣ እርሱ የጌታ ባላንጋራ፣ የሰይጣን ሐዋርያ ነው።”-Ibid, b. 7, ch. 6።GCAmh 113.2

    ሉተር አደገኛ የሆነውን ጉዞውን ብቻውን ሊጓዝ አልነበረም። ከንጉሠ ነገስቱ መልዕክተኛ በተጨማሪ ሶስት በጣም የሚቀርቡት ጓደኞቹ አብረውት ለመሄድ ወሰኑ። ሜላክቶን ከልቡ ሊቀላቀላቸው ፈለገ። ልቡ ከሉተር ልብ ጋር ተቆራኝታ ነበረችና አስፈላጊ ከሆነም ወደ ወህኒ ቤት ወይም ወደ ሞት አብሮት ለመሄድ ፅኑ መሻት ነበረው። ልመናው ግን ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ምናልባት ሉተር የሚገደል ከሆነ የተሐድሶው ተስፋ የሚያርፈው በዚህ የሥራ ባልደረባው ወጣት ላይ ነው። ከሜላንክተን ጋር ሲሰናበት ሉተር እንዲህ አለ፦ “የማልመለስ ከሆነ፣ ጠላቶቼም የሚገድሉኝ ከሆነ፣ ማስተማርህን ቀጥል። ሳትነቃነቅ እውነትን ጠብቀህ ቁም፤ በኔ ቦታ ተተክተህ ጣር…. አንተ የምትተርፍ ከሆነ የእኔ ሕይወት ቢጠፋ ምንም አይደል።”-Ibid, b. 7, ch. 7። የሉተርን መሄድ ለማየት የተሰበሰቡ የአገሬው ሰዎችና ተማሪዎች እጅግ አዘኑ። በወንጌሉ ልባቸው የተነካ አዕላፋት በሉተር መሄድ ልባቸው ተሰብሮ በለቅሶ ሸኑት። ከዚያም የተሐድሶ አራማጁና ጓደኞቹ ከዊተንበርግ ተነስተው ጉዟቸውን ቀጠሉ።GCAmh 113.3

    በጉዞአቸው የሰዎች አእምሮ መጥፎ ነገር ይከሰታል በሚል ሃሳብ ተውጦ ተመለከቱ። በአንዳንድ ከተሞችም ምንም አይነት አክብሮት አልተቸራቸውም ነበር። ሌሊቱን ለማሳለፍ ሲያርፉ አንድ ወዳጅ የሆነ ቄስ በኢጣሊያ የሰማዕትነት ዕጣ የገጠመውን የአንድ ተሐድሶ አራማጅ ስዕል በሉተር ፊት አምጥቶ ያለውን ፍራቻ ገለፀለት። በሚቀጥለው ቀን የሉተር ጽሁፎች በዎርምስ እንደተወገዙ ተረዱ። ንጉሣዊ መልክተኞች የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ እየለፈፉ የተወገዙትን መጻሕፍት ወደ አጥቢያ ዳኞች እንዲያመጡ ለሕዝቡ ጥሪ ያደርጉ ነበር። በጉባኤው ፊት ለሚኖረው የሉተር ደህንነት በመስጋት እንዲሁም የሉተር አቋም ተናውጦ ይሆናል ብሎ በማሰብ መንግሥታዊ መልዕክተኛው አሁንም መንገዱን መቀጠል ይፈልግ እንደ ሆነ ጠየቀ። ሉተር እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በእያንዳንዱ ከተማ እግድ ቢጣልብኝ እንኳ ጉዞዬን እቀጥላለሁ።” አለ።-Ibid, b. 7, ch. 7።GCAmh 113.4

    በኤርፈርት ሉተር የክብር አቀባበል ተደረገለት። የልመና ኮሮጆውን ይዞ ሲመላለስባቸው በነበሩት የከተማ መንገዶች መሃል በሚያሞጋግሰው ሕዝብ ተከቦ አለፈ። የምንኩስና ዘመን መኖሪያ ክፍሉን ጎበኘ፤ አሁን መላ ጀርመንን እያጥለቀለቀ ያለው ብርሐን ወደ ሕይወቱ የመጣበትን ያንን የትንቅንቅ ዘመን አስታወሰ። ለመስበክ ተነሳሳ፤ ይህንን እንዳያደርግ ተከልክሏል፤ ሆኖም በመንግሥታዊ መልክተኛው ፈቃድ በአንድ ወቅት የመነኩሴዎች መኖሪያ፣ የገዳም አገልጋይ አሁን ወደ መድረክ ወጣ።GCAmh 114.1

    ጥቅጥቅ ብሎ ለተሰበሰበው ሕዝብ ከክርስቶስ ቃላት ተናገረ፣ “ሰላም ለላንት ይሁን“[ዮሐ 20÷21]። “ፈላስፎች፣ ዶክተሮችና ፀሐፊያን” አለ፣ “የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን መንገድ ለሰዎች ለማስተማር ሲደክሙ ኖረዋል፤ ውጤታማ ግን አልሆኑም። አሁን እኔ እነግራችኋሁ።” “ሞትን ይደመስስ ዘንድ፣ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ፣ የሲኦልንም በሮች ይዘጋ ዘንድ እግዚአብሔር አንድን ሰው፣ ጌታ የሱስ ክርስቶስን ከሞት አስነሳ። ይህ የድነት ክንዋኔ ነው። ክርስቶስ ድል ነሳ! ደስ የሚያሰኘው የምሥራች ይህ ነው! የዳንነውም እርሱ በሰራው እንጂ በራሳችን ሥራ አይደለም….ጌታችን የሱስ ክርስቶስ ሲናገር፦ “ሰላም ለናንት ይሁን! እጆቼን….እዩ [ሉቃ 24÷39] ሲል እንዲህ ማለቱ ነው፤ ኦህ ሰው ሆይ! እነሆ ተመልከት፤ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህን የወሰድኩ የተቤዤሁህም እኔ ብቻ ነኝ እያለ ነው፤ እናም ጌታ ተናገረ….አሁን ሰላም አለህ።”GCAmh 114.2

    እውነተኛ እምነት በቅዱስ ሕይወት እንደሚገለጽ በማሳየት ቀጠለ። “እግዚአብሔር አድኖናልና ደስ ይሰኝባቸው ዘንድ ሥራዎቻችን በመልክ እናድርግ። ሐብታሞች ናችሁ? ሐብታችሁ ለባልንጀራችሁ ድህነት የሚለገስ ይሁን። ድሆች ናችሁ? አገልግሎታችሁ ለሃብታሞች ይመስክር። ልፋታችሁ ለራሳችሁ ብቻ ከሆነ ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት አገልግሎት አስመሳይነትን ብቻ ነው።”GCAmh 114.3

    በድግምት እንደተያዙ ያህል ሕዝቡ [አፋቸውን ከፍተው] አዳመጡ። ለተራቡ ነፍሳት የሕይወት እንጀራ ተቆረሰላቸው። ክርስቶስ ከሊቀ-ጳጳሳት፣ ከቤተክህነት መሪዎች፣ ከንጉሠ ነገሥታትና ከነገሥታት በላይ ከፍ ከፍ ብሎ በፊታቸው ተመለከቱ። የራሱ ሁኔታ አስጊ ደረጃ ውስጥ እንደሆነ ሉተር ምንም የጠቀሰው ነገር አልነበረም። የሐሳብ ወይም የከንፈር መጠጣ ኢላማ ይሆን ዘንድ አልፈለገም። በክርስቶስ ሐሳብ ውስጥ ተመስጦ ራሱን መመልከት ረስቶ ነበር። የኃጢአተኛውን ይቅር ባይ የሱስን ብቻ ለመወከል በመሻት በቀራንዮ ሰው ኋላ ራሱን ሰወረ።GCAmh 114.4

    የተሐድሶ አራማጁ ባለፈበት ሁሉ ታላቅ ትኩረት ይስብ ነበር። ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ይሰበሰብ ነበር። ወዳጃዊ ድምጾችም ስለ ሮማዊያኑ እቅድ ያስጠነቅቁት ነበር። “በሕይወት እያለህ ትቃጠላለህ” አሉት “እንደ ጆን ኸስ አካልህ ወደ አመድ ይለወጣል።” ሉተርም ሲመልስ፣ “ነበልባሉ ሰማይ የሚደርስ እሳት ከዎርምስ እስከ ዊተንበርግ ቢያቀጣጥሉ እንኳ በጌታ ስም በመካከሉ አልፋለሁ፤ በፊታቸውም እቆማለሁ፤ ወደዚህም ግዙፍ አራዊት (ጉማሬ) [እዮብ 40÷15] መንጋጋ ገብቼ ጌታ የሱስ ክርስቶስን እየመሰከርሁ ጥርሶቹን እሰብራለሁ።”አለ።-Ibid, b. 7, ch. 7።GCAmh 114.5

    ወደ ዎርምስ የመቃረቡ ወሬ ታላቅ ሽብር ፈጠረ። ወዳጆቹ ስለደህንነቱ ሲንቀጠቀጡ ጠላቶቹ ደግሞ የአላማቸው መሳካት ጉዳይ አስፈርቷቸው ነበር። ወደ ከተማዋ እንዳይገባ ለማግባባት እልህ አስጨራሽ ጥረት ተደርጎ ነበር። ሁሉም ነገር በሰላም እንደሚፈታ በማተት በጳጳሳውያኑ አነሳሽነት ወዳጅ በሆነ በአንድ ባለማዕረግ የጦር ሰው እልፍኝ እንዲያርፍ ተገፋፋ። ወዳጆቹ የተጋረጡበትን አደጋዎች በመዘርዘር ፍርሃት በውስጡ እንዲነሳሳ ጣሩ። ልፋታቸው ሁሉ ግን ከንቱ ሆነ፤ ምንም ሳይናወጥ ሉተር፦ “በከተማዋ ያሉትን የጣራ ሸክላዎች ቁጥር ያክል ብዛት ያላቸው ዲያብሎሶች በዎርምስ ቢኖሩ እንኳ፣ ወደርስዋ እገባለሁ” በማለት ተናገረ።-Ibid, b. 7, ch. 7።GCAmh 115.1

    በዎርምስ እንደደረሰ፣ እንኳን ደህና መጣህ ይለው ዘንድ ብዙ ሕዝብ ወደ በሩ ጎረፈ። እንደዚህ ብዛት ያለው ሕዝብ ንጉሠ ነገሥቱን እንኳ ለመገናኘት ወጥቶ አያውቅም። ብርቱ ስሜታዊነት ይንፀባረቅ ነበር፤ በሕዝቡ መሃልም ጆሮን በሚበጥስ አሳዛኝ ጩኸት፣ ሉተርን የሚጠብቀው ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማስጠንቀቅ፣ የቀብር ሙሾ የሚያወርድ ድምጽ ይሰማ ነበር። “እግዚአብሔር ምሽጌ ይሆናል” አለ ከፈረስ ጋሪው እየወረደ። ጳጳሳውያኑ በእርግጥ ሉተር ደፍሮ በዎርምስ ብቅ ይላል የሚል እምነት በጭራሽ አልነበራቸውም፤ የእርሱ እዚያ መድረስ በድንጋጤ ሞላቸው። ንጉሠ ነገሥቱ ወዲያውኑ አማካሪዎቹን ሰብስቦ ምን መደረግ እንዳለበት ምክክር ጀመረ። ጳጳሳዊ ሥርዓትን በግትርነት ከሚደግፉ መካከል አንዱ ጳጳስ፦ “በዚህ ጉዳይ ላይ ከተመካከርንበት ብዙ ቆይተናል፤ ግርማዊነትዎ ይህንን ሰው ባስቸኳይ ያስወግዱት። ሲጂስመንድ ጆን ኸስን ወደ ማቃጠያ ስፍራው አላመጣውም እንዴ? ለመናፍቅ የይለፍ ትዕዛዝ ለመስጠት ወይም የተሰጠውን ለማክበር የምንገደድበት ምንም ምክንያት የለም” አለ፤ “እንደዚያ አይሆንም” አለ ንጉሠ ነገሥቱ፦ “ቃላችንን ማክበር ይገባናል፤” ስለዚህም የተሐድሶ አራማጁ ቃል እንዲሰማ ተወሰነ።GCAmh 115.2

    ይህንን ልዩ ሰው ለማየት ከተማዋ በሞላ ጓጉታ ነበረች፣ ጎብኚዎችም ወዲያው ማደሪያ ስፍራውን ሞሉት። ሉተር በቅርቡ ካመመው በሽታ አላገገመም ነበር፤ ሁለት ሳምንት ሙሉ ከወሰደው ጉዞው የተነሳ እጅግ ደክሞ ነበር፤ በሚቀጥለው ቀን ለሚካሄደው በጣም አስፈላጊ ክንውን መዘጋጀት አለበት፤ ለዚህም ፀጥታና እረፍት ያስፈልገው ነበር። እርሱን ለማየት ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ፣ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ እንዳረፈ የተከበሩ ሰዎች፣ የጦር አርበኞች፣ ቀሳውስትና የአገሬው ሰዎች በዙሪያው ተሰበሰቡ። ከእነዚህ ከተሰበሰቡት መካከል ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽመው ጎጂ ድርጊት ተሐድሶ እንደሚያስፈልገው ንጉሠ ነገሥቱን በድፍረት የጠየቁ፣ ሉተር “በወንጌሉ ነፃ የወጡ” የሚላቸው ልዑላን ይገኙበት ነበር።-Martyn, ገጽ 393። ጠላቶቹም ሆኑ ወዳጆቹ አይሸበሬውን መነኩሴ ለመመልከት መጡ፣ በማይናወጥ እርጋታ ተቀበላቸው፣ ለሁሉም በአክብሮትና በጥበብ ይመልስላቸው ነበር። አቋሙ ደፋርና ጽኑ ነበረ። የልፋትና የህመም ምልክት የሚታይበት የገረጣው ቀጭን ፊቱ ቸርነትን፣ እንዲያውም ደስታን የሚያንፀባርቅ ነበረ። የንግግሩ ክብደትና ጥልቅ ቅንነት ጠላቶቹ እንኳ ሙሉ ለሙሉ ሊቋቋሙት ያልቻሉት ኃይል ለገሰው። ወዳጆችና ጠላቶች በአንድነት በመገረም ተሞሉ። አንዳንዶች መለኮታዊ ተፅዕኖ እንዳለበት አመኑ። ሌሎች ደግሞ ልክ ፈሪሳውያን ክርስቶስ እንዳሉት፣ “ጋኔን አለበት” አሉ [ማቴ 11÷18]።GCAmh 115.3

    በሚቀጥለው ቀን በጉባኤው ፊት እንዲቀርብ ለሉተር ተነገረው። ወደ ሕዝባዊ አዳራሹ ይወስደው ዘንድ ንጉሠ ነገሥታዊ ሹም ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ወደ ቦታው የደረሰው ግን በመከራ ነበር። ሁሉም ስፍራ የሊቀ-ጳጳሳሱን ስልጣን ለመገዳደር የደፈረውን መነኩሴ ለማየት በመጣ ተመልካች ተጥለቅልቆ ነበር።GCAmh 116.1

    ወደ ፈራጆቹ ፊት ሊገባ ሲል አንድ በብዙ ጦርነቶች ላይ ጀብዱ የፈፀመ ታዋቂ፣ በእድሜ የገፋ ጀነራል በትህትና እንዲህ አለው፦ “ምስኪን መነኩሴ! ምስኪን መነኩሴ! እኔም ሆንሁ ሌሎች የጦር መሪዎች እጅግ ደም አፍሳሽ በተባለው ጦርነት እንኳ ፈጽሞ ያልቀመስነው ሰልፍና ትግል ይጠብቅሃል ነገር ግን ትክክለኛ አላማ ካለህ፣ አንተም እርግጠኛ ከሆንክበት፣ በእግዚአብሔር ስም ወደፊት ገስግስ፣ አንዳች ነገር አትፍራ! እርሱ አይጥልህም።”GCAmh 116.2

    በመጨረሻ ሉተር በጉባኤው ፊት ቆመ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። በግዛቱ ሁሉ ተወዳዳሪ በሌላቸው ገናና እና የተከበሩ ሰዎች ተከቦ ነበር። ማርቲን ሉተር ለእምነቱ ለመመስከር እንደቆመበት አይነት ያለ ግርማ ሞገስ የነበረው ጉባኤ ከዚያ ጊዜ በፊት ተሰብስቦ አያውቅም። “እንዲህ አይነት መልክ ያለው ጉባኤ መሰብሰቡ በራሱ በጳጳሳዊ ሥርዓት ላይ የተገኘ ድል ነበር። ሊቀ-ጳጳሱ አስቀድሞ ፈርዶበታል፤ ጉዳዩ እንደገና ይመረመር ዘንድ ሉተር በተለየው ፍርድ ቤት መቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱ ከሊቀ-ጳጳሱ በላይ መሆኑን አሳየ። ሊቀ ጳጳሱ በእግድ ስር አድርጎት፣ ከማንኛውም ሰብዓዊ አብሮነት እንዲገለል ቢያደርገውም ሉተር ግን ክብሩን በጠበቀ ቋንቋ መጥሪያ ደርሶት በዓለም ተወዳዳሪ በማይገኝለት ጉባኤ ፊት ተቀባይነት አገኘ። ሊቀ-ጳጳሱ ለዘላለም ዝም እንዲል የፈረደበት ቢሆንም አሁን ግን ክርስትና ከሚያካልላቸው ሩቅ ሃገራት ጭምር ለመጡ በሺዎች ለሚቆጠሩ በፀጥታ ለሚያዳምጡ ሰዎች ሊናገር ጀመረ። በሉተር መሳሪያነት አማካኝነት ታላቅ አብዮት ተግባራዊ ሆነ። ሮም ከዙፋንዋ እየወረደች ነበረች፣ የዚህ ውርደት ምክንያትም የአንድ መነኩሴ ድምጽ ነበረ።”-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 116.3

    በዚያ ኃያልና ስመ-ጥር ጉባኤ ፊት ከተራ ቤተሰብ የተገኘው የተሐድሶ አራማጁ የፈራና ሃፍረት የያዘው መሰለ። ውስጣዊ ስሜቱን በመገንዘብ ብዙዎቹ ልዑላን ወደርሱ መጡ፤ ከመካከላቸውም አንዱ በሹክሹክታ፦ “አካልን እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍራቸው።” አለው። ሌላኛው ደግሞ፦ “ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም በምትወሰድበት ጊዜ በአባትህ መንፈስ የምትናገረው ይሰጥሃል።” እንዲህም የክርስቶስ ቃላት በዓለማችን ታላላቅ ሰዎች አማካኝነት ባርያው በፈተናው ሰዓት ይጠነክር ዘንድ ተነገሩ።GCAmh 116.4

    ሉተር በቀጥታ የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ፊት ለፊት ወዳለ ስፍራ ተመራ፤ ጥቅጥቅ ብሎ የሞላው ጉባኤ ፀጥ ረጭ አለ። ከዚያም አንድ ንጉሣዊ ሹም ተነስቶ ወደ ሉተር ጽሁፎች ስብስብ እያመለከተ የተሐድሶ አራማጁ ሁለት ጥያቄዎችን እንዲመልስ ጠየቀ፦ የእርሱ ጽሁፎች መሆን አለመሆናቸውን እንዲያረጋግጥ፣ በጽሁፎቹ ያሰፈራቸውን አመለካከቶች ለመካድ (ስህተት እንደሆኑ ለማመን) ወይም ላለመካድ ያለው ሃሳብ ምን እንደሆነ ጠየቀው። የመጻሕፍቱ ርዕሶች ከተነበቡ በኋላ፣ ለመጀመሪያው ጥያቄ ሉተር የእርሱ እንደሆኑ አመነ። “ሁለተኛው” አለ፣ “ጥያቄ የሚመለከተው እምነትን፣ የነፍሳትን ድነት እንዲሁም በሰማይም ሆነ በምድር አቻ የሌለውን የተከበረውንና ታላቁን ቅርስ የእግዚአብሔርን ቃል በመሆኑ በደንብ በጥንቃቄ ሳላስብበት መልስ መስጠቴ ችኩልና አደገኛም ነው። ሁኔታዎቹ ከሚፈልጉብኝ በታች አዎንታዊ መልስ ወይም እውነት ከሚጠይቀው በላይ ልሰጥ እችላለሁ። በሁለቱም አካሄድ ቢሆን በክርስቶስ ፍርድ ሥር መሆን ይኖርብኛል፦ “በሰው ፊትም የሚክደኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” [ማቴ 10÷33] በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃወም ጥፋት ሳልሠራ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠኝ ግርማዊነትዎን በፍጹም ትህትና እለምናለሁ” አለ።-D’ Aubigné, b. 7, ch. 8።GCAmh 116.5

    ይህንን ጥያቄ በማቅረቡ ሉተር ጥበብ የተሞላበት አካሄድ አደረገ። አካሄዱም የሚያደርገው ነገር ስሜታዊነት ወይም የልብ ትርታን የተከተለ እንዳልሆነ ጉባኤውን ማሳመን ቻለ። በድፍረት፣ ወደ ኋላ ባለማለት የሚታወቀው ሉተር ባልተጠበቀ ሁኔታ የተረጋጋና ራሱን የተቆጣጠረ እንደሆነ ማሳየቱ ተጽዕኖውን ከፍ አደረገለት፣ በኋላም መልሱን በጥንቃቄ፣ ባለማወላወል፣ በጥበብና በክብር በማቅረብ፣ ጠላቶቹን ማስገረምና ቅር ማሰኘት፤ ብልግናቸውንና እብሪታቸውን መገሰጽ አስቻለው።GCAmh 117.1

    በሚቀጥለው ቀን የመጨረሻ መልሱን ለመስጠት መቅረብ ነበረበት። እውነትን ለመቃወም ያበሩትን ኃይላት ሲያስብ ለአፍታ ልቡ ቀለጠች። እምነቱ ደከመ፤ ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ወደቀበት፤ ታላቅ ድንጋጤ አሸነፈው። አደጋዎች በፊቱ ተበራከቱ፤ ጠላቶቹ ሊያሸንፉ፣ የጨለማ ኃይላትም ድል ሊነሱ የተቃረቡ መሰለ። ደመናዎች በዙሪያው ተሰባሰቡ፣ ከእግዚአብሔር የሚለዩትም መሰሉ። የሰራዊት ጌታ ከእርሱ ጋር እንደሚሆን ማረጋገጫ ያገኝ ዘንድ ተመኘ። እጅግ በተጨነቀ መንፈስ በፊቱ ተደፍቶ መሬት ላይ ወደቀና ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ሙሉ ለሙሉ መረዳት የማይችላቸውን ስቅታ የቆራረጣቸው፣ ልብን የሚተረትሩ ዋይታዎች አሰማ።GCAmh 117.2

    “እግዚአብሔር ሆይ” ለመነ፦ “ሁሉን የምትችል ዘላለማዊ እግዚአብሔር ሆይ! ዓለም እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይውጠኝ ዘንድ እንዴት አፉን እንደከፈተ ባንተም ላይ ያለኝ እምነት እንዴት ኢምንት እንደሆነ ተመልከት!…. ይህ ዓለም ባለው አንዳች ጉልበት የምደገፍ ከሆነ በቃ አከተመልኝ…. ደወሉ ተደውሎአል…. ውሳኔም ተላልፎአል…. አንተ የእኔ አምላክ ሆይ የዚህን ዓለም ጥበብ ተቃውሜ ፀንቼ እቆም ዘንድ እርዳኝ። በራስህ ኃያል ጉልበት ይህንን ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሥራው የእኔ አይደለም፤ የራስህ እንጂ። እዚህ ምንም ጉዳይ የለኝም…. ከዓለም ታላላቅ ሰዎች ጋር የምከራከርበት እኔ ምንም ጉዳይ የለኝም…. ጉዳዩ ያንተ ነው፤…. ፃድቅና ዘላለማዊም ነው…. ታማኝና የማትለወጠው እግዚአብሔር ሆይ! እኔ በሰው ላይ አልደገፍም…. ከሰው የሆነ ነገር ሁሉ ይንገዳገዳል፤ ከእርሱ የሚወጣው ሁሉ መውደቁ እርግጥ ነው…. ለዚህ ሥራ የመረጥከኝ አንተው ነህ…. ስለዚህ ኦ ጌታ ሆይ የራስህን ፈቃድ ፈጽም፤ ምሽጌ፣ ጋሻዬና መሰረቴ ስለሆነው ስለተወደደው ልጅህ የሱስ ክርስቶስ ስትል አትተወኝ።”-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 117.3

    በራሱ ኃይል እንዳይተማመንና አቅሙን በውል ሳያውቅ ወደ አደጋ በጥድፊያ እንዳይገባ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ ሉተር የተጋረጠበትን አደገኛ ሁኔታ እንዲረዳ ፈቀደ። በፍርሃት እንዲሸነፍ ያደረገው ወዲያውኑ የሚፈጸም የሚመስለው የራሱ የስቃይ ፍርሃት፣ የግርፋት ወይም የሞት ስጋት አልነበረም። ወደ ችግሩ መጥቷል፤ የመጋፈጥ ብቁነት ግን ሊሰማው አልቻለም። በእርሱ ድክመት ምክንያት እውነት ኪሳራ ሊደርስበት ይችላል። ለራሱ ደህንነት ሳይሆን ለወንጌሉ አሸናፊነት ሲል ከእግዚአብሔር ጋር ታገለ። የነፍሱ ስቃይና ፍጭት ፀጥ ረጭ ባለው ጅረት አጠገብ በሌሊት እንደታገለው እንደ እሥራኤል [ያዕቆብ] ነበር። እንደ እሥራኤል ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎ አሸነፈ። ፈጽሞ እረዳት አልባ በሆነበት ጊዜ እምነቱ በሃያሉ አዳኝ በክርስቶስ ላይ ተጣበቀ። በጉባኤው ፊት ብቻውን እንደማይቀርብ በተሰጠው ማረጋገጫ ተበረታታ። ሰላም ወደ ነፍሱ ተመለሰች፤ በአገሪቱ መሪዎች ፊት የእግዚአብሔርን ቃል ከፍ ከፍ ያደርግ ዘንድ ዕድል ስላገኘ እጅግ ሀሴት አደረገ።GCAmh 118.1

    አዕምሮው በእግዚአብሔር ፀንቶ ሉተር በፊቱ ላለው ትግል ይዘጋጅ ጀመር። ስለሚመልሰው መልስ እቅድ አሰላሰለ፤ የፃፋቸውን ጽሁፎች አገላበጠ፤ አቋሙን የሚደግፉ ገጣሚ ጥቅሶችን በማስረጃነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ወሰደ። ከዚያም ግራ እጁን በፊቱ በተከፈተው ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ጭኖ፣ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሳና፦ “ምስክርነቱን በደም ለማተም ቢጠራ እንኳ ከወንጌሉ ጋራ በቋሚነት ሊጣበቅ፣ እምነቱንም በነጻነት ሊመሰክር ቃል ገባ።”-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 118.2

    በጉባኤው ፊት እንደገና ለመቅረብ ወደዚያ ሲመራ ፊቱ የፍርሃት ወይም የሃፍረት አንዳች ምልክት አይታይበትም ነበር። አደብ የገዛና ሰላማዊ፣ ሆኖም እጅግ ደፋርና የተከበረ ሆኖ፣ በታላላቅ የምድር ሰዎች መካከል የእግዚአብሔር ምስክር ሆኖ ቆመ። ሉተር አስተምህሮዎቹን ይክድ እንደሆነ ውሳኔውን እንዲያሳውቅ መንግሥታዊ ሹሙ ጠየቀ። ሁከትና ጠንካራ ስሜት ሳያንፀባርቅ ሉተር ለሰስ ባለ ትሁት ቃና መለሰ፤ ገጽታው የተለየና አክብሮት የተሞላበት ነበረ፤ ሆኖም ጉባኤውን ያስደነቀ መተማመንና ደስታ ይንፀባረቅበት ነበር።GCAmh 118.3

    “እጅግ ደርባባ የሆኑት ንጉሠ ነገሥት፤ የተከበራችሁ ልዑላን፣ የተወደዳችሁ ጌቶች” አለ ሉተር፣ “በትእዛዛችሁ መሰረት ዛሬ በፊታችሁ በትህትና ተገኝቻለሁ። እውነትና ትክክል እንደሆነ በጣም እርግጠኛ የሆንኩበትን ጉዳይ ደግፌ ስናገር በእግዚአብሔር ቸርነት በአዎንታ ታዳምጡኝ ዘንድ ግርማዊነትዎንና የተከበሩትን ልዑላን እማፀናለሁ። በምመልስበት ጊዜ ትክክለኛውን የፍርድ ቤት ሥነ-ሥርዓት ያልተከተልኩ እንደሆነ ስለ አጠቃቀሙ ብዙም ልምድ ስለሌለኝ ይቅርታ እንዲደረግልኝ እጠይቃለሁ። እኔ ድሃ መነኩሴ፣ የገዳም ልጅ፣ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ ስተጋ የኖርሁ ሰው ነኝ።”-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 118.4

    ከዚያም ወደ ጥያቄው በማምራት የታተሙት ሥራዎቹ ባህርይ ተመሳሳይ እንዳልሆነ አመለከተ። በተወሰኑት ጽሁፎች ስለ እምነትና ሥራ ያተተ ሲሆን ጉዳት የሌለባቸው ብቻ ሳይሆኑ አትራፊም እንደሆኑ ጠላቶቹ ሳይቀር ተናግረዋል። እነዚህን መካድ ማለት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የመሰከሩላቸውን እውነቶች ማውገዝ ነው። ሁለተኛው የጽሁፍ ክፍል የጳጳሳዊውን ሥርዓት ብልሹነቶችና አግባብነት የሌለው ምግባር የሚያጋልጡ ጽሁፎችን ያካተተ ነበር። እነዚህን ሥራዎች መግታት የሮምን ፈላጭ ቆራጭነት በማበረታታት ለበርካታ፣ ታላላቅ፣ እግዚአብሔርን መሰልነት ለሌለባቸው ነገሮች በር በሰፊው የሚከፍት ይሆናል። ሶስተኛ ደረጃ ያሉ ጽሁፎች ደግሞ በጊዜው የነበሩትን ክፋቶች የሚደግፉትን ግለሰቦች የሚተቹ ነበሩ። እነዚህን ሰዎች በተመለከተ ከሚገባው በላይ ጨከን ያለ እንደነበረ በነጻነት ተናገረ። ከስህተት ነፃ እንደሆነ አልተናገረም። ቢሆንም [ስለነዚህ ክፉ ሰዎች የሚዘረዝሩትን] መጻሕፍት እንኳ ሊወገዱ ይገባል አላለም፤ ምክንያቱም እንደዛ አይነት አካሄድ ለእውነት ጠላቶች የልብ ልብ የሚሰጥ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም የእግዚአብሔርን ሰዎች በበለጠ ጭካኔ ለመደቆስ እንዲመቻቸው የሚያደርግ ስለሆነ ነው።GCAmh 118.5

    “ነገር ግን እኔ ተራ ሰው እንጂ እግዚአብሔር ስላልሆንኩ” ቀጠለ፣ “ክርስቶስ እንዳደረገው እኔም ራሴን ለመከላከል ‘ክፉ ተናግሬ እንደሆንሁ ስለ ክፉ ምስክር’ [ዮሐ 18÷23] በማለት እናገራለሁ። ግርማዊነትዎ፣ ወይም ማንም ሰው ቢሆን የሚቻለው ከሆነ ስህተተኛ እንደሆንሁ ከነብያትና ከሐዋርያት ጽሁፎች ውስጥ ማስረጃ በመጥቀስ ታረጋግጥሉኝ ዘንድ በእግዚአብሔር ቸርነት እለምናችኋለሁ። ስህተተኛ እንደሆንኩ ባመንኩበት ቅጽበት እፀፀታለሁ፤ መጽሐፎቼንም ወደ እሳት ለመወርወር የመጀመሪያው እሆናለሁ። ራሴን እያጋለጥኩ ያለሁባቸውን አደጋዎች እንዳሰብኳቸውና እንደመዘንኳቸው አሁን የተናገርኩት የሚያመለክት ነው። ነገር ግን አደጋዎቹ አንዳች ሳያስጨንቁኝ ይልቁንም እንደጥንቱ ዛሬም ወንጌሉ የችግር፣ የክርክርና የጥል ምክንያት ሆኖ ማየቴ እጅግ ያስደስተኛል። የእግዚአብሔር ቃል ባህርይና መዳረሻ ይህ ነው። ክርስቶስ አለ፦ “ሰይፍ እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።” [ማቴ 10÷34]። እግዚአብሔር በምክሩ ግሩምና ኃያል ነው። አለመግባባትን ለማስቆም በምንለፋበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ስንዋጋ እንዳንገኝ፣ በራሳችን ላይም ልንወጣው የማንችለው አስፈሪ የአደጋ መዓት፣ ወቅታዊ እልቂትና ዘላለማዊ ውድመት እንዳናመጣ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል…. ከእግዚአብሔር መጻሕፍት ምሳሌዎችን ልጠቅስ እችላለሁ። በእይታ ጥንቁቅና አርቆ አሳቢ ይመስሉ ስለነበሩት፣ መንግሥታቸውንም እያፀኑ ይመስላቸው ስለነበሩት፣ ነገር ግን የጥፋታቸውን ማገዶ እየቆሰቆሱ ስለነበሩት ፈርዖኖች፣ የባቢሎን ወይም የእሥራኤል ነገሥታት መናገር እችላለሁ። እግዚአብሔር ‘ተራሮችን ይነቅላል አያውቁትም።’” [ኢዮኤ 9÷5] አለ።-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 119.1

    ሉተር የተናገረው በጀርመንኛ ነበር፤ አሁን ደግሞ ያንኑ የተናገረውን በላቲንኛ እንዲደግመው ተጠየቀ። እስካሁን ባከናወነው ሥራው እጅግ ደክሞ የነበረ ቢሆንም ለመድገም በመስማማት እንደመጀመሪያው ሁሉ ጥርት ባለና ኃይል በተሞላበት ሁኔታ ንግግሩን አደረገ። የእግዚአብሔር ምሪት ይህንን ጉዳይ አስተባበረ። የብዙዎች ልዑላን አዕምሮ በስህተትና አጉል እምነት የታወረ ስለነበር በመጀመሪያው ንግግሩ ሉተር የሰጠው የሚያሳምን ምክንያት ጥንካሬ አልታያቸውም ነበር። መደገሙ የቀረቡትን ነጥቦች በተሻለ ግልጽነት እንዲረዱ አስቻላቸው።GCAmh 119.2

    ለብርሃኑ ዓይናቸውን በግትርነት የጨፈኑ በእውነቱም ላለመረታት የወሰኑ እነርሱ በሉተር ቃላት ኃያልነት እጅግ ተበሳጩ። መናገሩን ሲጨርስ የጉባኤው አፈ-ጉባኤ በቁጣ፦ “ጥያቄውን አልመለስክም። ግልጽና የተብራራ መልስ ነው የሚፈለገው። አቋምህን ትለውጣለህ ወይስ አትለውጥም?” አለውGCAmh 119.3

    የተሐድሶ አራማጁ መለሰ፦ “ግርማዊነትዎ እንዲሁም ልዑላን፣ የምትፈልጉት ቀላል፣ ግልጽና ቀጥተኛ መልስ ስለሆነ እመልስላችኋለሁ ይኸውም፦ እምነቴን ለሊቀ-ጳጳሱ ወይም ለመማክርቱ አሳልፌ አልሰጥም፤ ምክንያቱም በተደጋጋሚ ወደ ስህተት እንደወደቁ፣ ይባስ ብሎም የራሳቸውን አቋም መከተል ተስኖአቸው ፍንትው ባለ መዋዠቅ ውስጥ እንዳሉ፣ እንደ ቀትር ፀሐይ ግልጽ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ በማስረጃ ወይም በአጥጋቢ ምክንያቶች እንዳምን ካልተደረግሁ፤ በጠቀስኳቸው በእነዚሁ ጽሁፎች ካልረካሁና አቋሜም በዚህ አኳኋን በእግዚአብሔር ቃል የማይገዛ ካልሆነ በስተቀር ምንም ነገር አልክድም፤ ልክድም አይቻለኝም፤ ህሊናውን የሚቃረን ነገር ይናገር ዘንድ ለአንድ ክርስቲያን ተገቢ አይደለም። ይህ አቋሜ ነው፤ ሌላ ነገር አደርግ ዘንድ አይቻለኝም። እግዚአብሔር እረዳቴ ይሁን! አሜን።”-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 119.4

    በዚህም ሁኔታ ይህ ጻድቅ ሰው እርግጥ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ላይ ቆመ። ሰማያዊ ብርሐን ፊቱን አፈካው። የስህተትን ኃይል ተቃውሞ ቃሉን ሲሰጥ፣ ታላቅነቱና የባህርይ ንጽህናው፣ የልቡ ደስታና ሰላሙ ለሁሉም በግልጽ ይታዩ ነበር፣ ዓለምን ስለሚያሸንፈው እምነት የበላይነትም ምስክር ሆኑ።GCAmh 120.1

    ጉባኤው በሞላ ለተወሰነ ጊዜ በግርምት ፀጥ ረጭ አለ። በመጀመሪያ መልሱ ሉተር በለሆሳስ፣ በአክብሮት፣ እንዲያውም እጅ የመስጠት በሚመስል ቅላጼ ንግግሩን አድርጎ ስለነበር ሮማውያኑ ይህን ምልክት የጥንካሬው መሸርሸር ጅማሮ እንደሆነ አድርገው ተረድተውት ነበር። ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ስህተቱን ለማመን ያቀረበው መንደርደሪያ ነው ብለውም ገምተው ነበር። ቻርለስ ራሱ በከፊል ንቀትም ቢሆን የመነኩሴውን ያለቀ ሰውነት፣ ያልተዋበና ቀላል የሆነ አለባበሱን በመመልከት “ይህ ሰው እኔን እንደመናፍቅማ ሊያስቆጥረኝ ፈጽሞ አይችልም” በማለት ተናግሮ ነበር። “አሁን ያሳየው ጀግንነትና ጥንካሬ የምክንያቱ ግልጽነትና ኃይል ሁሉንም መደቦች ያስደመመ ሆነ። ንጉሠ ነገሥቱ በታላቅ አክብሮት “መነኩሴው ፍርሃት በሌለው ልብ በማይናወጥም ጉብዝና ይናገራል” በማለት በመደነቅ ተናገረ። ይህንን አገራቸውን የወከለውን ሰው የጀርመን ልዑላን በኩራትና በደስታ ተመለከቱት።GCAmh 120.2

    የሮም ደጋፊዎች ድል ተነሱ። አላማቸው ፈፅሞ ተቀባይነት በሌለው (አዎንታዊ ባልሆነ) ብርሐን ታየ። ስልጣናቸውን ሊያስጠብቁ የሞከሩት፣ የሮም የማያበቃ መከራከሪያ በሆነው የማስፈራራት ተግባራቸው እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ አልነበረም። የጉባኤው አፈ-ጉባኤ እንዲህ አለ፦ “የማትክድ ከሆነ ንጉሠ ነገሥቱና የግዛቱ ሃገራት እንዲህ ዓይነቱን ግትር መናፍቅ እንዴት መቅጣት እንዳለባቸው ምክራቸውን ይቀጥላሉ።”GCAmh 120.3

    ግሩም የመከራከሪያ ንግግሩን በታላቅ ደስታ ሲያዳምጡ የነበሩት የሉተር ወዳጆች እነዚህን ቃላት ሲሰሙ በፍርሃት ተርበደበዱ ። ዶክተሩ ግን እንዲህ በተረጋጋ መንፈስ “አንዳች ነገር አልክድምና እግዚአብሔር ረዳቴ ይሁን!” አለ።-Ibid, b. 7, ch. 8።GCAmh 120.4

    ልዑላን ሲመካከሩ ሳለ ከጉባኤው እንዲሄድ ታዘዘ። ታላቅ ቀውስ እንደመጣ በሁሉም ዘንድ ታውቆ ነበር። የሉተር የአልቀበልም ባይነቱ፣ የማይናወጥ አቋሙ፣ ለወደፊቱ በሚሆነው የቤተ ክርስቲያን የዘመናት ታሪክ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ሃሳቡን ይቀይር ዘንድ አንድ ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጠው ተወሰነ። ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ጉባኤው እንዲመጣ ተደረገ። አስተምህሮው ስህተት መሆኑን ይናገር እንደሆነ ተብሎ ጥያቄው እንደገና ቀረበለት። “ከሰጠሁት መልስ ሌላ”፣ አለ፣ “የተለየ የምሰጠው መልስ የለኝም።” በማባበልም ሆነ በማስፈራራት ለሮም ትዕዛዝ እንደማይንበረከክ ግልጽ ሆነ።GCAmh 120.5

    ነገሥታትንና ልዑላንን ያንቀጠቀጠው ኃይላቸው በአንድ ተራ መነኩሴ ከምንም አለመቆጠሩ ለጳጳሳዊያኑ መሪዎች ውርደት ሆነባቸው። አሰቃይተው በመግደል ቁጣቸው እንዲሰማው ቢያደርጉ ተመኙ። ሉተር ግን የተጋረጠበትን አደጋ በማስተዋል ለሁሉም የተናገረው በክርስቲያናዊ ክብርና መረጋጋት ነበር። ቃላቱ ከእብሪት፣ ከስሜታዊነትና የሃሰት ገለጻ ነጻ ነበሩ። ራሱንና በዙሪያው ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ረስቶ ከሊቀ-ጳጳሳት፣ ከቤተክህነት መሪዎች፣ ከነገሥታትና ከንጉሰ-ነገሥታት ለዘላለም የሚልቀው አምላክ ፊት ብቻ እንደቆመ ይሰማው ነበር። በመደነቅና በመገረም ጓደኞቹንም ሆነ ጠላቶቹን ያነሳሳ ኃያልና ታላቅ ምስክርነት ክርስቶስ በሉተር በኩል ተናገረ። የግዛቱን ባለስልጣናት ልብ የሚነካ ሥራ እየሰራ የእግዚአብሔር መንፈስ በዚያ ጉባኤ መካከል ነበር። ብዙ ልዑላን የሉተር አቋም ትክክል እንደሆነ በድፍረት እውቅና ሰጡ። ብዙዎች እውነቱ አሳማኝ ሆኖ አገኙት፤ በአንዳንዶች ዘንድ ግን እነዚያ የእውነት አሻራዎች ብዙም በውስጣቸው ሳይቆዩ ቀሩ። በዚያን ሰዓት እምነታቸውን ያልገለፁ፣ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ራሳቸው መርምረው በኋላ የተሐድሶው ፍርሃት-የለሽ ደጋፊ የሆኑ ሌሎች ነበሩ።GCAmh 121.1

    መራጩ ፍሬደሪክ የሉተርን በጉባኤው ፊት መቅረብ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር፤ ንግግሩንም በጥልቅ ስሜት ተከታተለ። በደስታና በኩራት ስለ ዶክተሩ ጉብዝና፣ አይበገሬነትና ራስን የመቆጣጠር ችሎታ በመመስከር በተሻለ ቆራጥነት ከጎኑ ለመቆም ወሰነ። ተቃርኖ ውስጥ ከነበሩት ወገኖች (ፓርቲዎች) የተለየ አቋም ያዘ፤ የሊቀ-ጳጳሳት፣ የነገሥታትና የቤተ-ክህነት መሪዎች ጥበብ በእውነት ኃይል አማካይነት መና እንደሆነ ተመለከተ። ጳጳሳዊ ስርዓቱ ሁሉም አገራት ለዘላለም የማይረሱት ሽንፈት ተከናነበ።GCAmh 121.2

    የሉተር ንግግር ያስገኘውን ውጤት ልዑኩ ሲገነዘብ ከምን ጊዜውም በላይ ለሮም ስልጣን ደህንነት ሃሳብ ገባው፤ ማድረግ የሚችለውንም ሁሉ ተጠቅሞ ተሐድሶ አራማጁን ይገለብጥ ዘንድ ቆርጦ ተነሳ። በማያሻማ ሁኔታ የታወቀበትን የንግግርና የማግባባት (የዲፕሎማሲያዊ) ችሎታውን ተጠቅሞ ለአንድ እርባና-ቢስ መነኩሴ ጉዳይ ብሎ የገናናዋን የሮም መንበረ ሥልጣን ወዳጅነትና ድጋፍ የማጣትን ስህተትና አደጋ ለወጣቱ ንጉሠ ነገሥት ገለፀ።GCAmh 121.3

    ንግግሩም ፍሬ አልባ አልነበረም። ሉተር መልሱን ከሰጠበት ቀጥሎ ባለው ቀን ቻርለስ ለጉባኤው የሚቀርብ መልእክት ላከ፤ ይዘቱም፣ ከእርሱ በፊት የነበሩትን ዱካ የሚከተል አቋም እንዳለው በመግለጽ የካቶሊክን ኃይማኖት ለማስቀጠልና ለመጠበቅ ያለውን መርሃ ግብር አሳወቀ። ሉተር ስህተቱን አምኖ ለመመለስ ፈቃደኛ ስላልሆነ በእርሱና ባስተማራቸው ኑፋቄዎች ላይ እጅግ ጠንካራ እርምጃ መወሰድ አለበት። “በራሱ እብደት የተመራ አንድ፣ ብቸኛ መነኩሴ የክርስትናውን ዓለም እምነት ተገዳድሮ ቆሟል። የዚህን እምነት-የለሽነት መስፋፋት ለማስቆም መንግሥቴን፣ ኃይሌን፣ ወዳጆቼን፣ ኃብቴን፣ አካሌንና ደሜን፣ ኃሳቤንና ሕይወቴን እሰዋለሁ። በሕዝቡ ዘንድ ምንም ብጥብጥ እንዳያስነሳ እየከለከልኩት አውገስቲን ሉተርን አሰናብተዋለሁ። በእርሱና በደጋፊዎቹ ላይ፣ እንደ መናፍቅነታቸው አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ሁሉ እወስዳለሁ። እንደ ታማኝ ክርስቲያኖች ይሆኑ ዘንድ ለሁሉም ግዛቶች አባላት ጥሪ አቀርባለሁ።”አለ፤ የሉተር የይለፍ ትዕዛዝ ግን መከበር እንዳለበት በማወጅ እርምጃ መወሰድ ከመጀመሩ በፊት ሉተር ወደ ሃገሩ በሰላም መመለስ እንዳለበት ተናገረ።GCAmh 121.4

    ሁለት የማይጣጣሙ ሃሳቦች በጉባኤው መንሸራሸር ጀመሩ። የሊቀ-ጳጳሱ መልዕክተኞችና ተወካዮች የተሐድሶ አራማጁ የይለፍ ፍቃድ መከበር እንደሌለበት ተከራከሩ። “የራይን [ወንዝ]” አሉ “ከመቶ ዓመት በፊት የጆን ኸስን አመድ እንደወሰደ ሁሉ የእርሱንም አመድ ይቀበል።” የጀርመን ልዑላን የጳጳሳዊ ሥርዓት ደጋፊዎችና የሉተር ቀንደኛ ጠላቶች ቢሆኑም የሕዝብን እምነት የሚሸረሽረውን፣ በአገሪቱ ክብር ላይም ነቁጥ የሚያሳርፈውን ድርጊት ለመፈፀም አልተስማሙም። የኸስን ሞት ተከትሎ የመጣውን እልቂት በማስታወስ በጀርመን አገርና በወጣቱ መሪያቸው ላይ እነዚያን አሰቃቂ ክፋቶች ለመድገም እንደማይደፍሩ ተናገሩ።GCAmh 122.1

    ቻርለስ ራሱም ለቀረበው ግብረ-ገብነት ለሌለው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እምነት በምድር እንዲጠፋ ቢደረግ እንኳ በልዑላን መካከል መጠጊያ ማግኘት እንዳለበት ተናገረ። አሁንም ግን በሉተር ቀንደኛ ጳጳሳዊ ጠላቶች ዘንድ ግፊቱ በመቀጠል ሲጅስመንድ በኸስ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በተሐድሶ አራማጁ ላይ እንዲያደርግበት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተላልፎ እንዲሰጥ እንዲያደርግ ተጨማሪ ጫና ተደረገበት። ኸስ ሕዝብ በተሰበሰበበት ወደ ታሰረበት ሰንሰለት እያመለከተ ንጉሠ-ነገሥቱ የገባውን የእምነት ቃል ሲያስታውሰው የነበረበትን ትዕይንት በማስታወስ ቻርለስ 5ኛ “እንደ ሲጅስመንድ በውርደት ፊቴ እንዲቀላ አልፈልግም።” አለ።-Lenfant, vol. 1, ገጽ 422።GCAmh 122.2

    ያም ሆኖ ቻርለስ በሉተር የቀረቡትን እውነቶች ሆን ብሎ አልቀበልም ብሏል። “የቅድመ አያቶቼን ዱካ ተከትዬ ለመራመድ ቁርጥ ሃሳቤ ነው።” አለ ንጉሠ ነገሥቱ ሲጽፍ።-D’Aubigné, b. 7, ch. 9። በእውነትና በፅድቅ መንገድ ለመራመድ ሲል እንኳ ቢሆን ከልማድ መንገድ ፈቀቅ ላለማለት ወስኖ ነበር። አባቶች እንደዛ ስላደረጉ፣ ከጭካኔውና ከብልሹነቱ ጋር ጳጳሳዊውን ሥርዓት ደገፈ። በመሆኑም አቋም ወሰደ፤ አባቶቹ ከተቀበሉት የበለጠ አንዳች ብርሐን ለመቀበል፣ ወይም እነርሱ ያልተገበሩትን ማንኛውንም ኃላፊነት ለመፈጸም እምቢ አለ።GCAmh 122.3

    ዛሬም በዚህ ዘመን ከአባቶቻቸው ወግና ባህል ጋር ተጣብቀው ያሉ ብዙዎች ናቸው። ጌታ ተጨማሪ ብርሐን ሲልክላቸው፣ ይህ ብርሐን ለአባቶቻቸው ያልተሰጠ ስለነበር፣ አባቶቻቸው አላገኙትምና እነርሱም ለመቀበል አሻፈረኝ ይላሉ። አባቶቻችን በነበሩበት አይደለም ያለነው፤ በመሆኑም ልንሰራቸው የሚገባን ሥራዎችና ኃላፊነቶቻችን ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ አይደሉም። የእውነትን ቃል ራሳችን መመርመር ሲገባን ሳለ፣ ኃላፊነቶቻችን ምን እንደሆኑ ለመገንዘብ የአባቶቻችንን ምሳሌ መመልከታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አያስገኝልንም። የኛ ኃላፊነት አያቶቻችን ከነበረባቸው ኃላፊነት የበለጠ ነው። እነርሱ ለተቀበሉት፣ እንደ ውርስ ሆኖም ወደ እኛ ለተላለፈው ብርሐን ተጠያቂዎች ነን፤ ከእግዚአብሔር ቃል ዘንድ አሁን ወደ እኛ ለሚመጣው ተጨማሪ የብርሐን ጮራም እንዲሁ ተጠያቂዎች ነን።GCAmh 122.4

    ስለማያምኑ አይሁዳውያን ክርስቶስ እንዲህ አለ፦ “እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር። አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም” [ዮሐ 15÷22]። በሉተር በኩል ለንጉሠ ነገሥቱና ለጀርመን ልዑላን የተናገረው ያው መለኮታዊ ኃይል ነበር። ከቃሉ ብርሐን ፈንጥቆ ሳለ፣ መንፈሱ በዚያ ጉባኤ የነበሩትን ብዙዎችን ለመጨረሻ ጊዜ ለመናቸው። ከመቶዎች ዓመታት በፊት ኩራትና ተወዳጅነት በዓለም አዳኝ ላይ ልቡን እንዲደፍኑበት እንደፈቀደው ጲላጦስ፤ ይንቀጠቀጥ የነበረው ፊሊክስ የእውነትን መልዕክተኛ፦ “አሁንስ ሂድ፣ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ” [የሐዋ ሥራ 24÷25]፣ “በጥቂት ቀረህ ክርስቲያን ልታደርገኝ” [የሐዋ ሥራ 26÷28] እንዳለው ኩሩው አግሪጳ - ነገር ግን እነርሱ ሁሉ ከሰማይ ለተላከው መልእክት ፊታቸውን እንዳዞሩ ሁሉ - ቻርለስ 5ኛም ለዓለማዊ ክብርና መርሃ-ግብር እጁን በመስጠት የእውነትን ብርሐን ላለመቀበል ወሰነ።GCAmh 123.1

    ለሉተር የታቀደለት ነገር ወሬ በስፋት ሲሰራጭ በመላ ከተማዋ ታላቅ ግርግር ተቀሰቀሰ። ሉተር፣ ብልሽትዋን ለማጋለጥ የደፈሩትን ሁሉ ሮም የሚሰብቅ ጭካኔ እንደምትፈጽምባቸው የገባቸው፣ መስዋዕት መሆን እንደሌለበት የወሰኑ ብዙ ጓደኞች አፍርቶ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ መሳፍንት ይጠብቁት ዘንድ ለራሳቸው ቃል ገቡ። የንጉሣዊው መልእክት ለማያፈናፍነው የሮም ኃይል የተንበረከከ፣ ደካማ እጅ መስጠትን በግልጽ ያሳየ እንደሆነ በግላጭ የኮነኑ ጥቂቶች አልነበሩም። ሉተርን የሚኮንኑና የሚደግፉ መፈክሮች በአደባባዮችና በሰዎች መኖሪያ በሮች ላይ ተለጥፈው ነበር። ከእነዚህ መካከል የጠቢቡ ሰው ታዋቂ ንግግሮች ተጽፈው ነበር፦ “ንጉሥሽ ህፃን የሆነ….አንቺ አገር ሆይ ወዮልሽ!” [መክ 10÷16]። በመላው የጀርመን አገር የተንፀባረቀው፣ ሉተርን በመደገፍ የታየው ሕዝባዊ ስሜት በእርሱ ላይ የተጓደለ ፍርድ መበየን የግዛቱን ሰላም ብሎም የመንበረ መንግሥቱን ፅናት አደጋ ላይ እንደሚጥለው ንጉሠ ነገሥቱና ጉባኤው አምነውበት ነበር።GCAmh 123.2

    የሳክሶኒው ፍሬደሪክ የተጠና ተአቅቦ አድርጎ፣ ለተሐድሶ አድራጊው ያለውን ትክክለኛ ስሜት በመደበቅ፣ በማይዝል ንቃት የሉተርንና የጠላቶቹን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመከታተል በትጋት ይጠብቀው ነበር። ለሉተር ያላቸውን ኃዘኔታ ለመደበቅ ያልሞከሩ ግን ብዙዎች ነበሩ። በልዑላን፣ በሹሞች፣ በአገረ ገዥዎችና ከተራው ሕዝብና ከቤተ ክህነት በመጡ ታዋቂ ሰዎች ጭምር ይጎበኝ ነበር። “የዶክተሩ ትንሽ ክፍል” አለ ስፓላቲን ሲጽፍ፦ “የሚመጣውን ሁሉ ለማስተናገድ አልበቃችም።”-Martyn, vol. 1, ገጽ 404። ከሰው የላቀ አስመስሎ ሕዝቡ አትኩሮ ይመለከተው ነበር። አስተምህሮውን የማይቀበሉት እንኳ ህሊናውን ከሚጥስ ይልቅ ሞትን መጋፈጥ ያስመረጠውን አያሌ ሐቀኝነቱን ከማድነቅ በቀር ሌላ የሚሉት አልነበራቸውም።GCAmh 123.3

    ሉተር ከሮም ጋር ወደሚያስታርቅ የድርድር ሃሳብ እንዲገባ ልባዊ ጥረት ተደረገ። ፍርዱን በራሱ ላይ እንዲፀና በማድረግ ቤተ ክርስቲያኑንና ጉባኤዎቹን ተቃውሞ ከቀጠለ በቅርቡ ከግዛቱ እንደሚወሰድና መከላከያም እንደማይኖረው የተከበሩ ሰዎችና ልዑላን አስረዱት። ለዚህ ጥያቄ ሉተር ሲመልስ፦ “ያለ ፀብ የክርስቶስን ወንጌል መስበክ ፈጽሞ የማይቻል ነው። ታዲያ የአደጋ ፍርሃት ብቸኛ እውነት ከሆነው ከመለኮታዊው ቃልና ከጌታ ይለየኝን? አይደረግም፤ አካሌን ደሜንና ሕይወቴን መስጠትን እመርጣለሁ።” አለ።-D’Aubigné, b. 7, ch. 10።GCAmh 123.4

    አሁንም እንደገና ለንጉሠ ነገሥቱ ብይን እንዲገዛ፣ ከዚያም የሚስፈራው ነገር እንደማይኖር ተነገረው። ሲመልስም፦ “ንጉሠ ነገሥቱ፣ ልዑላኑ፣ እንዲሁም ተራው ክርስቲያን ጭምር ጽሁፎቼን እንዲመረምሩና እንዲፈርዱ በሙሉ ልቤ እስማማለሁ፤ ይህንን የማደርገው ግን የእግዚአብሔርን ቃል መሪያቸው ያደረጉ እንደሆነ ብቻ ነው። ሰዎች ማድረግ የሚገባቸው ለዚያ መታዘዝ ብቻ ነው። የእኔ ህሊና በዚያ ቃል ላይ የተመረኮዘ ነው፤ በስልጣኑም የታሰርኩ አገልጋይ ነኝ።”-Ibid, b. 7, ch. 10።GCAmh 124.1

    ለሌላ ተማፅኖ ሲመልስ፣ “ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ እኔነቴንና ሕይወቴን ለመስጠት፣ የይለፍ ፈቃዴንም ለመተው ዝግጁ ነኝ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተመለከተ ግን ፈጽሞ አላደርገውም!”-Ibid, b. 7, ch. 10። ጉባኤው ውሳኔውን ሲሰጥ መፅሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርጎ የሚወስን ከሆነ ብቻ ለጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ለመገዛት ተስማማ። “በእግዚአብሔር ቃልና በእምነቱ ዙሪያ” አለ ሲጨምር፣ “ሊቀ-ጳጳሱ በአንድ ሚሊዮን ጉባኤዎች ቢደገፍ እንኳ፣ ሊቀ-ጳጳሱ መስጠት የሚችለውን ፍርድ እያንዳንዱ ክርስቲያን የመስጠት ብቃት አለው።”-Martyn, vol. 1, ገጽ410። ለማስታረቅ የሚደረግ ተጨማሪ ጥረት ፍሬ ቢስ እንደሆነ ወዳጆቹም ሆኑ ጠላቶቹ ያመኑት ጉዳይ ሆነ።GCAmh 124.2

    የተሐድሶ አድራጊው ለአንዲት ነጥብ እንኳ እጅ ሰጥቶ ቢሆን ሰይጣንና ሰራዊቱ ድል በተቀዳጁ ነበር። የማይዋዥቀው አቋሙ ቤተ ክርስቲያንን ነፃ ለማውጣት መሳሪያ ለመሆን ለአዲስና የተሻለ ዘመን መጀመሪያ ነበር። ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ራሱ ሊያስብና ሊተገብር የደፈረው የዚህ ሰው ተፅዕኖ በእርሱ ጊዜ የነበረውን ዓለምና ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የሚነካ ነበር። እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ በተመሳሳይ ተሞክሮ ለሚያልፉ ሁሉ ጽናቱና ታማኝነቱ ጉልበት ይሆናቸው ዘንድ ነበረው። የእግዚአብሔር ኃይልና ግርማዊነት ከሰው ምክር በላይ፣ ከኃይለኛው የሰይጣን ጉልበት በላይ ሆነ።GCAmh 124.3

    ሉተር ወዲያውኑ ወደ ቤቱ እንዲመለስ በንጉሠ ነገሥቱ ስልጣን ታዘዘ፤ ይህን ትዕዛዝ ተከትሎ የሚኮነንበት ፍርድ ተግባራዊነት በፍጥነት እንደሚተገበር አውቋል። የሚያስፈራሩ ደመናዎች በመንገዱ ቢያንዣብቡም እርሱ ግን ከዎርምስ ሲወጣ ሳለ ልቡ በደስታና በምስጋና ተሞልቶ ነበር። “ሰይጣን ራሱ” አለ፣ “የሊቀ-ጳጳሱን ቅጥር (ቤተ-መንግሥት) ይጠብቅ ነበር፤ ሆኖም ክርስቶስ በሰፊው ደረመሰው፤ ክርስቶስ ከእርሱ በላይ ኃያል እንደሆነ ዲያብሎስ ለመመስከር ተገደደ።”-D’Aubigné, b. 7, ch. 11። ከዚያ ስፍራ ከሄደም በኋላ በአቋሙ መጽናቱ እንደ አመጽ ተደርጎ በተሳሳተ አስተያየት እንዳይተረጎም ግልጽ ለማድረግ ከነበረው ፍላጎት የተነሳ ለንጉሠ-ነገሥቱ ደብዳቤ ጻፈ። “ሃሳብን የሚያውቀው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው” አለ፣ “ሰው ይኖርበት ዘንድ ከሚገባው ከእግዚአብሔር ቃል በቀር፣ በመልካምም ሆነ በክፉ ወሬ፣ በሕይወትም ሆነ በሞት፣ በሁሉም ነገር ግርማዊነትዎን በሙሉ ልቤ ለመታዘዝ ዝግጁ ነኝ። በዚህ ዓለም ሕይወት በሁሉም ጉዳዮች ታማኝነቴ የማይነቃነቅ ጽኑ ነው፤ ምክንያቱም በዓለማዊ ጉዳዮች ማትረፍ ወይም መክሰር ከድነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የዘላለም ሕይወት በሆነው ጉዳይ ላይ ግን ሰው በሰው እዝ ስር ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፃረር ነው። ለመንፈሳዊ አገልግሎት መገዛት እውነተኛ አምልኮ ነው፤ የሚገባውም ለፈጣሪ ብቻ ነው።”-Ibid, b. 7, ch. 11።GCAmh 124.4

    ከዎርምስ ሲመለስ በጉዞው ላይ የነበረው ተቀባይነት ወደ ዎርምስ ሲሄድ ከነበረው የበለጠ ነበር። የተከበሩ የቤተ ክህነት ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን የተገለለውን መነኩሴ እንኳን ደህና መጣህ አሉት፤ ንጉሠ ነገሥቱ የኮነነውን መንግሥታዊ ባለስልጣናት አከበሩት፤ ይሰብክ ዘንድ ግፊት ተደረገበት፣ የንጉሠ ነገሥቱ እግድ ቢከለክለውም ወደ መድረክ ወጣ። “የእግዚአብሔርን ቃል እለጉም ዘንድ ለራሴ ፈጽሞ ቃል አልገባሁም” አለ “ወደፊትም አላደርገውም።”-Martyn, vol. 1, ገጽ 420።GCAmh 125.1

    ከዎርምስ ከሄደ ብዙም ሳይቆይ ጳጳሳውያኑ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ሰልጥነው በሉተር ላይ አዋጅ እንዲያውጅ አደረጉት። በዚህ አዋጅ ሉተር “በመነኩሴ ካባ ተሸፍኖ የሰው አምሳል የያዘ ራሱ ሰይጣን” እንደሆነ ተደርጎ ተወገዘ።-D’Aubigné, b. 7, ch. 11። የይለፍ ፈቃዱ ጊዜ እንዳበቃ፣ ሥራውን ለማስቆም እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ትዕዛዝ ተላለፈ። ማንም ሰው እንዳያስጠጋው፣ ምግብ ወይም ውሃ እንዳይሰጠው፣ በቃልም ሆነ በተግባር በግልጽም ሆነ በስውር እንዳይረዳው ወይም እንዳያደፋፍረው ተከለከለ። በተገኘበት ተይዞ ለባለስልጣናት እንዲሰጥ ተወሰነ። ደጋፊዎቹም እንዲያዙና እንዲታሰሩ፤ ንብረታቸውም እንዲወረስ ታዘዘ። ጽሁፎቹ እንዲወድሙ ከታዘዘ በኋላ በመጨረሻም ይህንን አዋጅ ለመገዳደር የደፈረ ሁሉ በኩነኔው እንደሚካተት ተወሰነ። የሳክሶኒው መራጭና ሉተርን በጣም የሚቀርቡት ልዑላን እርሱ እንደሄደ ዎርምስን ለቀው ስለነበር የንጉሠ ነገሥቱ አዋጅ በተቀረው ጉባኤ ፀደቀ። አሁን ሮማውያኑ በድል ደስታ ተዋጡ። የተሐድሶው ዕጣ ፈንታ የተደመደመ ጉዳይ እንደሆነ አሰቡ።GCAmh 125.2

    በዚህ የአደጋ ሰዓት እግዚአብሔር ለባሪያው ማምለጫ መንገድ አዘጋጅቶ ነበር። የማያንቀላፋ አይን የሉተርን እንቅስቃሴ ይከታተል ነበር፤ እውነተኛና ክቡር የሆነ ልብ እርሱን ለማትረፍ ወስኖ ነበር። ከሉተር ሞት ያነሰ ቅጣት ሮምን እንደማያረካት ግልጽ ነበር፤ ከአንበሳው መንጋጋ ሊተርፍ የሚችለው በመደበቅ ብቻ ነበር። የተሐድሶ አራማጁ በሕይወት ይቆይ ዘንድ መላ እንዲያበጅ እግዚአብሔር ለሳክሶኒው ፍሬዴሪክ ጥበብ ሰጠ። በልባዊ ጓደኞች ትብብር የመራጩ እቅድ ተግባራዊ ሆነ፤ ሉተርም ከወዳጆቹና ከጠላቶቹ ተሰወረ። ወደ ቤቱ ለመመለስ በጉዞ ላይ እያለ ተይዞ፣ አብረውት ከነበሩት ሰዎች ተነጥሎ፣ ጫካ ለጫካ ወደ ዋርትበርግ ግንብ፣ ነጠል ወዳለ የተራራ መጠለያ ምሽግ ተወሰደ። የተያዘበትና የተደበቀበት አኳኋን እጅግ ምስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ራሱ ፍሬዴሪክ እንኳ ለረዥም ጊዜ ሉተር የት እንደተወሰደ አያውቅም ነበር። ይህ ደግሞ ታስቦበት የተደረገ ነው። መራጩ ሉተር የት እንዳለ እስካላወቀ ድረስ ሊሰጥ የሚችለው ፍንጭ የለም። መራጩም የተሐድሶ አድራጊው ከአደጋ ነፃ እንደሆነ መረዳቱ አረካው፣ ይህንን ማወቁ በቂው ነበር።GCAmh 125.3

    ፀደይ፣ በጋና መከር አልፈው ክረምቱ ሲመጣ ሉተር አሁንም እስረኛ ነበር። የወንጌሉ ብርሐን ሊዳፈን የተቃረበ በመምሰሉ አሊያንደርና ደጋፊዎቹ ይፈነጥዙ ጀመር። በዚህ ፈንታ ግን የተሐድሶ አራማጁ ከእውነት ግምጃ ቤት ፋኖሱን እየሞላ ነበር፤ ብርሃኑም የተሻለ ጮራ ያንፀባርቅ ዘንድ ነበረው።GCAmh 125.4

    በዋርትበርግ የወዳጅነት ከለላ ስር ሆኖ ከጦርነት አመጽና ትኩሳት ስለራቀ ለተወሰነ ጊዜ ደስተኛ ነበር። በፀጥታና በእረፍት ውስጥ ግን እርካታን ያገኝ ዘንድ አልቻለም። ሥራና የከረረ ተጋድሎ የለመደው ሉተር ዝምታን እረፍትን ይቋቋም ዘንድ አልተቻለውም። በብቸኝነት ቀናቶቹ የቤተ ክርስቲያንዋ ሁኔታ በፊቱ ድቅን አለበት፤ በተስፋ መቁረጥም፣ “ወይኔ! በዚህ በኋለኛው [የጌታ] የቁጣው ሰዓት፣ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ግንብ የሚቆምና እሥራኤልን የሚያድን አንድ ስንኳ የለም!” በማለት ጮኸ።-Ibid, b. 9, ch. 2። እንደገና ወደ አእምሮው ሲመለስ ከውድድሩ የወጣው ፈርቶ ነው እባላለሁ ብሎ በማሰብ ፈራ። ከዚያም ስለ ስንፍናውና ስለ ራስ ወዳድነቱ ራሱን ይወቅስ ጀመር። እንደዛም ሆኖ አንድ ሰው ያከናውነዋል ብሎ ከሚታሰበው በላይ በየቀኑ ያከናውን ነበር። ብዕሩ ፈጽሞ እረፍት አልነበረውም። ዝም እንዳሰኙት በማሰብ ጠላቶቹ ራሳቸውን ቢያታልሉም አሁንም በሥራ ላይ እንዳለ በተግባር የሚያረጋግጥላቸውን መረጃ ሲያገኙ ግርምትና ግራ መጋባት ያዛቸው። በብዕሩ የተፃፉ በርካታ በራሪ ጽሑፎች በመላው የጀርመን አገር ይሰራጩ ነበር። የአዲስ ኪዳንን መፃሕፍት ወደ ጀርመንኛ ቋንቋም በመተርጎም ዋጋ ሊተመንለት የማይችለውን እጅግ አስፈላጊ አገልግሎት ለአገሩ ሰዎች አበረከተ። ከድንጋያማዋ ፍጥሞ ለአንድ ዓመት ለሚቃረብ ጊዜ ያህል ወንጌሉን ማወጁን፣ የዘመኑን ኃጢአትና ስህተት ማውገዙን ቀጠለ።GCAmh 125.5

    ነገር ግን እግዚአብሔር አገልጋዩን ከሕዝብ መድረክ ያራቀበት ምክንያት ሉተርን ከጠላቶቹ ቁጣ ለማዳን ወይም ለሚሰራው አስፈላጊ ሥራ የፀጥታ ጊዜ ሊሰጠው ፈልጎ አልነበረም። ከዚህ በላይ ውድ የሆኑ ግብዓቶች ይገኙ ዘንድ ነበራቸው። ተደብቆ በብቸኝነት በነበረበት የተራራ ምሽግ ሉተር ከምድራዊ እርዳታ ተገልሎ፣ ከሰው ሙገሳም ርቆ ነበር። በመሆኑም ስኬት በተገኘ ጊዜ ከሚመጡት፣ ከኩራትና በራስ ከመደገፍ ጥፋቶች ተረፈ። በመሰቃየቱና በመዋረዱ በድንገት ከፍ ከፍ ባለበት እጅግ አስፈላጊ ከፍታ ላይ አደጋ ሳይኖርበት እንደገና መራመድ ይችል ዘንድ አዘጋጀው።GCAmh 126.1

    እውነት ካመጣላቸው ነፃነት የተነሳ ሰዎች ሃሴት ሲያደርጉ፣ የአጉል አምልኮና የስህተትን ሰንሰለት ይበጥሱ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀመጣቸውን አገልጋዮች የማሞገስ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ሰዎች [ለእግዚአብሔር የተገባውን] ሃሳባቸውንና ፍቅራቸውን ከጌታ ላይ አንስተው ወኪል በሆኑ ፍጡራን ላይ ያሳርፉ ዘንድ ሰይጣን ጥረት ያደርጋል። የክንውኖቹን አቅርቦት የሚያቀነባብረውን እጅ ቸል በማለት በመሳሪያነት ብቻ የሚጠቀምባቸውን [ባሪያዎቹን] ያከብሩ ዘንድ ዲያብሎስ ይመራቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ሁኔታ የሚሞገሱና የሚከበሩ ሐይማኖታዊ መሪዎች በእግዚአብሔር መደገፋቸውን ረስተው በራሳቸው እንዲተማመኑ ይመራሉ። ከዚህም የተነሳ ወደ እግዚአብሔር ቃል በመመልከት ፈንታ ለምሪት ወደነርሱ እንዲመለከቱ የተዘጋጁ ሰዎችን አእምሮና ንቃተ ህሊና ሊቆጣጠሩ ይፈልጋሉ። በደጋፊዎቹ በሚበረታታው በዚህ መንፈስ ምክንያት የተሐድሶ ሥራ ሁል ጊዜ ወደ ኋላ ይጎተታል። ከዚህ አደጋ የተሐድሶውን ተልዕኮ ይጠብቀው ዘንድ እግዚአብሔር ነበረው። ያ ሥራ የእግዚአብሔር አሻራ እንጂ የሰው ማህተም እንዳይኖረው ፍላጎቱ ነበር። እውነትን ወዳብራራው ወደ ሉተር የሁሉም አይኖች ዞረው ነበር፤ አይኖች ሁሉ ወደ ዘላለማዊው የእውነት ፀሐፊ ይመለከቱ ዘንድ ሉተር ፈቀቅ ተደረገ።GCAmh 126.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents