Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፩—የየሩሳሌም ውድመት

    “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከአይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኩሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም የመጎብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” [ሉቃ 19÷42-44]።GCAmh 17.1

    በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ የሱስ የሩሳሌምን ተመለከተ። የሚያየው ሁሉ መልካምና ሰላም የሰፈነበት ነበር። የፋሲካ ወቅት ነበርና የያዕቆብ ልጆች ታላቁን በዓላቸውን ለማክበር ከየአቅጣጫው በመምጣት ተሰብስበው ነበር። በአትክልት ቦታው፣ በወይን ስፍራውና የእምነት ተጓዦች በተከሏቸው ድንኳች በተጌጡት በአረንጓዴ ደፋታማ ቦታዎች መካከል፣ እርከን የተሰራባቸው ኮረብታዎች፣ አስተዳደራዊ ቤተ መንግሥቶችና የእሥራኤል ዋና ከተማ ቅጥሮች ወደ ሰማይ ወጣ ወጣ ብለው ይታዩ ነበር። የጽዮን ልጅ በኩራት “ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ… ሃዘንም ከቶ አላይም” [ራዕይ 18÷7] የምትል ትመስል ነበር። በቀድሞ ዘመን ንጉሣዊ አቀንቃኙ እንደዘመረው “በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው” እንዳለው “የታላቁ ንጉሥ ከተማ” [መዝ 48÷2] የቀድሞ ውበትዋን እንደተላበሰች በእግዚአብሔር የተመረጠችበትን [ያንን የድሮ ወርቃማ] ዘመን ትመስል ነበር። የቤተ መቅደሱ ህንጻዎች ቁልጭ ብለው ይታዩ ነበር። አጫ በረዶ በሚመስሉት የእብነበረድ ግድግዳዎቹ ላይ ያረፈው የፀሐይ ግባት ጮራ ነጸብራቅ ነጭነቱን የበለጠ አጉልቶታል፤ ከወርቅ በሮቹና ከጉልላቱ ተንፀባርቆ የሚፈካ ብርሐን ይታይ ነበር፤ የአይሁድ ሕዝብ ኩራት “የውበት ፍጻሜ” [መዝ 50÷2] ቆሞ ይታይ ነበር። ይህንን ትዕይንት የሚመለከት የእሥራኤል ልጅ የሆነ፣ ማን ደስታና አድናቆት የማይሰማው ይገኛል! የክርስቶስን አእምሮ የያዘው ግን ፈጽሞ ከዚህ የራቀ ሃሳብ ነበር። “ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት” [ሉቃ 19÷41]። ወደ የሩሳሌም በሚገባበት ጊዜ፣ በድል ከሚገባው ሕዝብ ላይ ከሚንፀባረቀው ደስታ መሃል፣ የዘንባባ ዝንጣፊዎች ወዲያ ወዲህ ሲውለበለቡ፣ በደስታ የፈነደቁት የሆሳዕናዎች ድምጽ ኮረብታውን ሲቀሰቅሰው ሳለ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጉሥነቱን ሲያውጁለት ሳለ፣ የዓለም መድሃኒት ግን ድንገተኛና ሚስጢራዊ በሆነ፣ ሊሸከመው ባቃተው ሃዘን ተውጦ ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእሥራኤል ተስፋ፣ ሞትን ድል ነስቶ በሲኦል ግዞት ስር የነበሩትን ከመቃብር የጠራ እርሱ እንባ በእንባ ሆነ፤ ተራ ሃዘንም አልነበረም፣ እጅግ ከባድ በሆነ፣ ሊያበርደው በማይችል ሰቆቃ ውስጥ ነበር።GCAmh 17.2

    እግሮቹ የሚያመሩት ወደየት እንደሆነ ጠንቅቆ ቢያውቅም፣ ወደ ሞት እንደሚያመራ ቢገባውም፣ የሚያወርደው እንባ ግን ለራሱ አልነበረም። በፍጥነት እየደረሰ ያለው፣ የሰቆቃው ምድረ-ትዕይንት የሆነው ጌቴሰማኒ በፊቱ ነበር። “ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት” [ኢሳ 53÷7] የሚሆንበት፣ ለእርሱም በቅርብ የሚከፈተው፣ ለብዙ መቶ ዓመታት በመስዋዕትነት ይታረዱ ዘንድ የሚነዱበት የበጎች በርም እይታው ውስጥ ነበር። የስቅላት ቦታው ቀራንዮም ከዚያ ሩቅ አልነበረም። በቅርቡ ክርስቶስ በሚራመድበት መንገድ ላይ ታላቅ የሰቆቃ ጽልመት ይወድቃል፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት ይሰጣልና። ሆኖም በዚህ የደስታ ሰዓት የሃዘን ጥላ የጣለበት እነዚህን በርሱ ላይ የሚመጡትን ትእይንቶች ማሰላሰሉ አልነበረም። ሰው ከሚችለው በላይ የሆነው ስቃዩ በውል ቢገባውም ቅሉ ያንን ራስ ወዳድነት የሌለበትን መንፈሱን ግን አላደበዘዘበትም ነበር። የሚያለቅሰው፣ ሊያድናቸውና ሊባርካቸው ለመጣላቸው፣ በእውርነታቸውና ንሰሐ መግባትን እምቢ በማለታቸው ምክንያት ለሚጠፉት በሺዎች ለሚቆጠሩ የሩሳሌማውያን ነበር።GCAmh 17.3

    ለተመረጡት ሕዝቦች ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ እግዚአብሔር ያደረገው የተለየ እንክብካቤና ጥበቃ በየሱስ እይታ ውስጥ ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ መስዋዕትነት ተምሳሌት የነበረው የተስፋው ልጅ፣ ያለ ማንገራገር ሊሰዋ ወደ መሰውያው የቀረበበት የሞርያ ተራራም በዚያ ነበር [ዘፍ 22÷9]። በዚያ ስፍራ የበረከት ቃልኪዳን የከበረው መሲሃዊ ተስፋ ለአማኞች አባት ቃል ተገብቶ ነበር [ዘፍ 22÷16-18]። በዚያ ስፍራ ከኦርና አውድማ ወደ ሰማይ ይወጣ የነበረው የመስዋዕቱ ነበልባል የአጥፊው መልአክ ሰይፍ ወደ ሰገባው እንዲመለስ አድርጎ ነበር [1ኛ ዜና 21]። ይህም ለበደለኛው የሰው ዘር የከፈለውን መስዋዕትነትና ምልጃ በትክክል የሚወክል ነበር። በምድር ካሉ ነገሥታት ሁሉ የሩሳሌም በእግዚአብሔር ፊት የከበረች ነበረች። እግዚአብሔር “ጽዮንን መርጦአታልና” “ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ወድዶአታልና” [መዝ 132÷13]። እዚያ ስፍራ ነብያት ለዘመናት የማስጠንቀቂያ ድምጻቸውን አሰምተዋል፤ በዚያ ቦታ የሕዝቡን ፀሎት ይዞ ወደ እግዚአብሔር የሚወጣውን፣ የዕጣን ጭስ የሚያፈልቀውን ጥና ካህናት አወዛውዘውበት ነበር። እዚያ ወደ እግዚአብሔር በግ የሚያመላክተው፣ በጎች በየቀኑ ታርደው ደማቸው በመስዋዕትነት የሚቀርብበት ሥርዓት ይፈጸም ነበር። በዚያ ስፍራ በስርየት መክደኛው በላይ በክብር ደመና ያህዌ መገኘቱን ገልጾአል። ከምንም ነገር በላይ ቅዱስ ወደ ሆነው ስፍራ ለዓለም መንገድ የከፈተው፣ መላእክት ወደ ላይና ወደታች ይረማመዱበት የነበረው፣ ሰማይንና ምድርን ያገናኘው መንፈሳዊ መሰላል መሰረቱ ያረፈው በዚህ ስፍራ ነበር [ዘፍ 28÷1፤ ዮሐ 1÷51]። እሥራኤል እንደ ሕዝብ ከሰማይ ጋር ያላትን አንድነት ጠብቃ ቢሆን ኖሮ የእግዚአብሔር ምርጥ ሆና ለዘላለም በቆመች ነበር [ኤር 17÷21-25]። የዚያ የተመረጠ ሕዝብ ታሪክ ግን ወደ ኋላ የማፈግፈግና የአመጽ መዝገብ ነበር። የሰማይን ጸጋ እምቢ አሉ፤ መታደላቸውን ተረማመዱበት፤ እድላቸውን ከመናኛ ቆጠሩት።GCAmh 18.1

    እሥራኤላውያን “በእግዚአብሔር መልዕክተኞች ይሳለቁ፤ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ” [2ኛ ዜና 36÷15-16] የነበረ ቢሆንም “እግዚአብሔር መሃሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለብዙ ቸርነትና እውነት” [ዘፀአት 34÷6] ነውና ራሱን ለእነርሱ ከመግለጽ ፈጽሞ አልተቆጠበም ነበር። አሻፈረኝ ባይነታቸው በተደጋጋሚ ቢተገበርም ምህረቱ ግን ተማፅኖዋን አላቋረጠችም ነበር። አባት ለልጁ ከሚያሳየው ርኅራኄ ባለፈ ፍቅር “የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነስቶ በመልክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር” [2ኛ ዜና 36÷15-16]። ተቃውሞው፣ ልመናውና ተግሳጹ ፍሬ አልባ ሲሆንበት፣ ወደር የማይገኝለትን የሰማይን ምርጥ ስጦታ ላከላቸው፤ ኦ አይደለም! ሰማይን በሙሉ በአንዱ ስጦታው አፈሰሰላቸው።GCAmh 18.2

    ንሰሐ አልገባም ያለችውን ከተማ ይለምን (ያባብል) ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ራሱ በአካል ተላከ። እንደ ግዙፍ የወይን ዛፍ [ተሸክሞና ተንከባክቦ] እሥራኤልን ከግብጽ ያወጣው ክርስቶስ ነበር። [መዝ 80÷8]። የራሱ እጅ ባዕድ አምላኪ ሕዝብን ከፊቱ አስወጣ፤ “በፍሬአማው ኮረብታ” ላይም [ኢሳ 5÷1-4] ተከለው። ጥበቃው ዙሪያውን ከልሎት ነበር፤ይንከባከቡትም ዘንድ ባርያዎቹ ተልከው ነበር። “ለወይኔ ያላደረግሁለት” ጠየቀ፦ “ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው?” [ኢሳ 5÷1-4]፤ ፍሬ ይሰጣል ብሎ በመተማመን ቢጠብቅም፣ “ወይን ያፈራል” ብሎ ተስፋ ያደረገው ተክሉ “ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ” [ኢሳ 5÷1-4]። ሆኖም አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ ምናልባት ከጥፋት ይተርፍ፣ ፍሬም ይሰጥ እንደሆነ ተስፋ ሰንቆ ወደ ወይን ስፍራው በአካል መጣ። ዙሪያውን ኮተኮተው፣ ገረዘው፣ ተንከባከበው። ራሱ የተከለውን ወይን ያተርፈው ዘንድ ሳይታክት ለፋ።GCAmh 18.3

    የክብር ጌታ፣ የብርሐን ንጉሥ ለሶስት ዓመት ያህል በሕዝቡ መካከል ተመላለሰ። “መልካም እያደረገ”፣ “ለዲያቢሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ” [የሐዋ ሥራ 10÷38፤ ሉቃ 4÷18፤ ማቴ 11÷5]፣ ያዘኑትን እያጽናና፣ የታሰሩትን ነጻ እያወጣ፣ ወንጌልን ለድሆች እየሰበከ በመካከላቸው ኖረ። [የሐዋ ሥራ 10÷38፣ ሉቃ 4÷18፣ ማቴ 11÷11]። የርኅራኄ ጥሪው ለሁሉም መደቦች አስተጋባ፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” [ማቴ 11÷28]።GCAmh 19.1

    ለመልካምነቱ ክፋት፣ ለፍቅሩም ጥላቻ ቢመለስለትም [መዝ 109÷5] የምሕረት ተልዕኮውን በጽናት አከናወነ። ፀጋውን የፈለገ ማንም በባዶ የተሸኘ አልነበረም። ቤት-የለሽ፣ ተቅበዥባዥ፣ ነቀፋና ስር የሰደደ ድህነት የእለት ዕጣው የነበረው ጌታ የሰዎችን ፍላጎት ሊያሟላ፣ መከራቸውን ሊያቃልል፣ የሕይወትን የነጻ ስጦታ ይቀበሉ ዘንድ ሊለምን በመካከላቸው አደረ። በደነደነ ልብ እየተገፈተረ የሚባረረው የምሕረት ማዕበል በሩኅሩኅና ሊገለጽ በማይችል ፍቅር እንደገና ተጠናክሮ ይመለስ ነበር። እሥራኤል ግን ተወዳዳሪ ከሌለው ጓደኛዋ፣ ከብቸኛው ረዳትዋ ፊትዋን አዞረች። የፍቅር ተማፅኖ ጥላቻን አተረፈ፤ ምክሩ ተቀባይነት አጣ፤ ማስጠንቀቂያውም መሳለቂያ ሆነ።GCAmh 19.2

    የተስፋና የምሕረት ጊዜ በፍጥነት እያለፈ ነበር፤ ለረጅም ጊዜ ሲገታ የነበረው የእግዚአብሔር የቁጣ ጽዋ ሊሞላ ምንም አልቀረውም ነበር። በአመጽና በክህደት ለዘመናት ሲጠራቀም የኖረው ደመና አሁን በመሪር ሃዘን ጠቁሮ በኃጢአተኛው ሕዝብ ላይ ሊፈስ አንዣቦ ነበር። ሊመጣባቸው ካለው ዕጣቸው የሚያተርፋቸው ብቸኛው ጌታ እንደ ምናምንቴ ተቆጥሮ፣ ተሰድቦና ተንቆ ይባስ ብሎም በቅርቡ ሊሰቀል ነበረ። ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ሲሰቀል እሥራኤል በእግዚአብሔር የተመረጠችና የተባረከች የመሆንዋ ዘመን ያበቃል። የአንድ ነፍስ እንኳ መጥፋት፣ ሊመዘን በማይችል ክብደት፣ የአንድን ዓለም ሀብትና ትርፍ ሁሉ የሚበልጥ መቅሰፍት ነው። ክርስቶስ የሩሳሌምን ሲመለከት ግን የአንድ ሙሉ ከተማ፣ የአንድ ሀገር ሕዝብ እልቂት በፊቱ ድቅን አለበት። ያ ሕዝብ፣ ያቺ ከተማ፣ በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር ምርጥ፣ የተለየች ቅርሱ ነበረች።GCAmh 19.3

    ኃጢአታቸው በመጎብኘቱ ስለወረደባቸው አሰቃቂ እልቂት፣ በእሥራኤል ክህደት ምክንያት ስለመጣው ጥፋት ነብያት ሲያነቡ ኖረዋል። ተወግተው ስለሞቱ ስለ ሕዝቡ ሴት ልጆች፣ ተማርኮ ስለተወሰደው የእግዚአብሔር መንጋ፣ ቀንና ሌት ያለማቋረጥ ያነባ ዘንድ አይኑ የእንባ ምንጭ ይሆንለት ዘንድ ኤርምያስ ተመኝቶ ነበር። [ኤር 9÷1፣ 13÷17]። ታዲያ ትንቢታዊ ጨረፍታውን ለዓመታት ሳይሆን ለዘመናት የተመለከተው የእርሱ ሃዘን ምን ነበር! የያህዌ የረጅም ጊዜ ማደሪያ በነበረችው ከተማ ላይ አጥፊው መልአክ ሰይፉን ወደ ላይ ቀስሮ ተመለከተ። ከጊዜ በኋላ በቲቶና በሰራዊቱ በተያዘው የደብረ ዘይት ተራራ ጫፍ ቆሞ፣ በሸለቆው ማዶ አሻግሮ የተቀደሱትን አደባባዮችና ሰገነቶች ሲቃኝ፣ ቅጥሮችዋ በእንግዳ ሰራዊት የተመሸገበትን አሳዛኝ ትዕይንት ሲመለከት አስለቅሶት፣ የዕንብ ውሐ አይኑን ጋርዶት፣ በደብዛዛው አይኑ ተመለከታቸው። ወደ ሰልፍ የሚሄድ ሰራዊት ኮቴ ሰማ። ከተከበበችው ከተማ ውስጥ እናቶችና ህጻናት እንጀራ ፈልገው በጩኸት ሲማጸኑ ሰማ። የተቀደሰውና የሚያምረው ቤትዋ፣ ቤተ-መንግሥቶችዋና ታላላቅ ህንጻዎችዋ በእሳት ነበልባል ሲንቀለቀሉ፣ ቆመውበት በነበረው በዚያው ስፍራ የከሰል አርባጫ ተቆልሎ ተመለከተ።GCAmh 19.4

    ዘመናትን ወደፊት አቆልቁሎ ሲመለከት “በበረኃ የባህር ዳርቻ እንደተልከሰከሰ” ስብርባሪ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ በምድሪቱ ተበትኖ አየ። በዚህ በልጆችዋ ሊወርድ ባለው፣ በዚህ ዓለም በምትቀበለው፣ በተገባት ቅጣት ውስጥ፣ በመጨረሻው ቀን በፍርድ ሰዓት ጭላጭ ሳታስቀር ግጥም አድርጋ የምትጠጣውን የቁጣ ጽዋ የመጀመሪያ ገፈት ተመለከተ። መለኮታዊ ሃዘኔታ፣ የሙጥኝ ባይ ፍቅር፣ በአሳዛኝ የእንጉርጉሮ ቃላት አንደበት አገኘ፦ “የሩሳሌም የሩሳሌም ሆይ፣ ነብያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩትዎችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።” [ማቴ 23÷37]። ኦ! አንቺ፣ አዎ አንቺ በምድር ካሉ ነገሥታት ሁሉ የተመረጥሽ ሆይ፣ የመጎብኘትሽን ወራት፣ ለሰላምሽ የሚሆነውን ብታውቂ! የፍርድን መልአክ ገረገርሁ፤ ወደ ንስሐም ጠራሁሽ፤ አልሰማሽኝም። የጠላሽው፣ አልቀበልም ያልሽው፣ አገልጋዮችን፣ መልእክተኞችንና ነብያትን ብቻ ሳይሆን የተቤዠሽን፣ የእሥራኤልን ቅዱስ አዳኝሽን ጭምር ነው። ብትጠፊ ለውድመትሽ ተጠያቂዋ ራስሽ ነሽ፤ ምክንያቱም “ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” [ዮሐ 5÷40]።GCAmh 20.1

    ክርስቶስ በየሩሳሌም ውስጥ፣ በአለማመንና በአመጽ የደነደነውን፣ የተገባውን የእግዚአብሔር ቅጣት ለመገናኘት የሚገሰግሰውን ዓለም አምሳያ ተመለከተ። የወደቀው የሰው ዘር ሰቆቃ ነፍሱን በሃዘን ሲደቁሰው መሪር ለቅሶ እንዲያሰማ አስገደደው። በሰው ስቃይ፣ እንባና ደም የተኮለኮለውን የኃጢአትን ታሪክ ዱካ ተመለከተ፤ በምድር ስላሉት፣ ስለተሰቃዩና ስለተጎዱ ሁሉ በዘላለማዊ ርኅራኄ አንጀቱ ተላወሰ፤ ሁሉንም ከስቃያቸው ሊገላግላቸውም ተመኘ። ሆኖም የሚግተለተለውን የሰው ልጅ የሰቆቃ ማዕበል የእርሱ እጅ እንኳ አይመልሰው ይሆናል፤ የብቸኛውን ረዳታቸውን እገዛ የሚጠይቁ ብዙ አልነበሩምና። ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ እንኳ ድነትን መጨበጥ ቢችሉ ያደርገው ዘንድ ሙሉ ፈቃደኛ ነበር። ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ ወደ እርሱ የሚመጡት ግን ከቁጥር የሚገቡ አልነበሩም።GCAmh 20.2

    የሰማይ ግርማ ሞገስ እንባ በእንባ ሆነ! የዘላለማዊው አምላክ ልጅ በመንፈስ ታውኮ በጭንቀት አጎነበሰ! ትዕይንቱ ሰማይን በግርምት ሞላው። ይህ ክስተት የኃጢአትን አስከፊነት የሚገልጽልን ነው። የእግዚአብሔርን ሕግ ከመተላለፍ ከሚመጣው መዘዝ ኃጢአተኛውን ለማዳን ችሎታው ወሰን ለሌለው ዘላለማዊ ኃይል እንኳ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይህ ምስክር ነው። የሱስ ወደ መጨረሻው ትውልድ አቆልቁሎ ሲመለከት፣ ዓለም፣ለየሩሳሌም ጥፋት ምክንያት በሆነው ተመሳሳይ መታለል ውስጥ ሆኖ አየ። የአይሁዳውያን ታላቁ ኃጢአት ክርስቶስን አለመቀበላቸው ነበር፤ የክርስትናው ዓለም ታላቅ ኃጢአት የሚሆነው ደግሞ በሰማይና በምድር የመንግሥቱ መሰረት የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ አሻፈረኝ ማለቱ ነው። የያህዌ መመሪያዎች በንቀት እንደምናምንቴ (ዋጋ ቢስ ሆነው) ይቆጠራሉ። የሰይጣን ባርያዎች፣ የኃጢአት ግዞተኞች ሆነው፣ ሁለተኛው ሞት ዕጣ ፈንታቸው ቢሆንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግን በመጎብኘታቸው ዘመን የእውነትን ቃል ያደምጡ ዘንድ አሻፈረኝ የሚሉ ይሆናሉ። አስከፊ እውርነት! እንግዳ የመጃጃል አባዜ!GCAmh 20.3

    የአይሁድ መሪዎችን ግብዝነት አውግዞ ለመጨረሻ ጊዜ ከመቅደሱ ከወጣ በኋላ ፋሲካ ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ደብረ ዘይት ተራራ በመሄድ በከተማዋ ትይዩ በእሳራማው አቀበት ላይ አብሮአቸው ተቀመጠ። ዛሬም እንደገና ቅጥሮችዋን፣ ህንጻዎችዋንና ቤተ መንግሥቶችዋን ተመለከተ። የተቀደሰው ተራራ የውበት ዘውድ የሆነውን፣ የእጹብ ድንቅ ግርማ ባለቤት የሆነውን ቤተ መቅደስ ተመለከተ።GCAmh 21.1

    እግዚአብሔር ለእሥራኤል ስለሰጠው ሞገስ፣ መኖሪያው ስላደረጋት የተቀደሰች ቤቱ፣ መዝሙረኛው ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት አጉልቶ አሳይቶ ነበር፦ “ስፍራው በሳሌም ማደሪያውም በጽዮን ነው።” [መዝ 76÷2]። እርሱ “የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፤ የወደደውን የጽዮንን ተራራ። መቅደሱን እንደ አርያም ሰራ።” [መዝ 78÷68፣69]። የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ የተሰራው በእሥራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ ስኬታማ በተባለው ዘመን ነበር። ብዛት ያለው የሀብት ክምችት ለዚህ አላማ በንጉሥ ዳዊት ተሰብስቦ አሰራሩ ደግሞ በመለኮት ምሪት የተከናወነ ነበር። [1ኛ ዜና 28÷12፣19]። ከእሥራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ጥበበኛ የነበረው ሰለሞን ግንባታውን አጠናቀቀ። ይህ ቤተ መቅደስ ዓለም አይቶት የማያውቅ እጅግ አስደናቂ ህንፃ ነበር። ስለ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ በነብዩ ሐጌ ጌታ ሲናገር ግን፦ “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል” አለ። “አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም እቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” [ሐጌ 2÷9፣7]።GCAmh 21.2

    መቅደሱ በናቡከደነፆር ከወደመና ለረጅም ዘመን በባርነት ከቆዩ በኋላ ወደ ተራቆተና መካን ለመሆን ወደ ተቃረበ አገር በተመለሱ ሰዎች ክርስቶስ ከመወለዱ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት [ሁለተኛው መቅደስ] እንደገና ተሰራ። ሰለሞን የሰራውን ቤተ መቅደስ ውበት ያዩ፣ ከፊተኛው መቅደስ ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ የተረዱ፣ በመሰረቱ ላይ በሃዘን ያነቡ ከሰራተኞቹ መካከል በእድሜ የገፉ ሰዎች ነበሩ። ይንጸባረቅ የነበረው ስሜት ምን አይነት እንደነበር በጥሩ ሁኔታ በነብዩ ተገልጾአል፦ “በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህንን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምናምን አይደለምን?” [ሐጌ 2÷3]። ያም ሆኖ የዚህ የሁለተኛው መቅደስ ክብር ከቀድሞው እንደሚልቅ ተስፋ ተሰጥቶ ነበር።GCAmh 21.3

    ነገር ግን ሁለተኛው የመጀመሪያውን መቅደስ ግርማ ሞገስ አልተስተካከለም፤ የመለኮትን መገኘት በሚያረጋግጡት በግልጽ በሚታዩ ምልክቶችም እንደፊተኛው አልተባረከም ነበር። በምርቃቱ ጊዜ መለኮታዊ ኃይል አልተገለጸም ነበር። በአዲስ የቆመውን ቤተ መቅደስ ይሞላ ዘንድ የክብር ደመና አልታየም ነበር። በመሰዊያው የተቀመጠውን መስዋዕት ይበላ ዘንድ እሳት ከሰማይ አልወረደም ነበር። በቅድስተ ቅዱሳኑ፣ በኪሩቤሎች መካከል የእግዚአብሔር የመገኘቱ ብርሐን አልነበረም። ታቦቱ፣ የስርየት መክደኛው፣ የምስክሩ ገበታም አልነበሩም። የያህዌን ፈቃድ ያውቁ ዘንድ ለሚጠይቁ ካህናት ከሰማይ የመጣ ድምጽ አልነበረም። በሐጌ የተሰጠው የእግዚአብሔር ተስፋ የት እንደተፈጸመ ለማሳየት አይሁዶች ለዘመናት በከንቱ ሲደክሙ ኖረዋል። ሆኖም እብሪትና እምነት-የለሽነት የነብዩን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም እንዳያስተውሉ አእምሮአቸውን ሸፍነውባቸው ነበር። ሁለተኛው መቅደስ በእግዚአብሔር የክብር ደመና ባይከብርም፣ በስጋ መገለጥ ራሱ እግዚአብሔር በሆነ፣ የእግዚአብሔር አብ ሙላት በሕያው አካል በተገለጸበት፣ በእርሱ መገኘት ከበረ። የናዝሬቱ ሰው በተቀደሱት አደባባዮች ሲያስተምርና ሲፈውስ ሳለ በእርግጥም “በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠው/the desire of all nations” [ሐጌ 2÷7] እርሱ ወደ መቅደሱ መጥቶ ነበር። በክርስቶስ መገኘትና፣ በመገኘቱ ብቻ የሁለተኛው መቅደስ ክብር ከመጀመሪያው በለጠ። እሥራኤል ግን ከሰማይ የተገለጸውን ስጦታ አልተቀበለችም። ራሱን ያዋረደው መምህር ከወርቃማ በሮችዋ የወጣ እለት፣ ያኔ ክብር ለዘላለም ከመቅደሱ ተለየ። የመሲሁ ቃላት ከወዲሁ ፍጻሜ አግኝተው ነበር፦ “እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” [ማቴ 23÷38]።GCAmh 21.4

    ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ የክርስቶስን ትንቢት ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱ አክብሮት በተላበሰ ፍርሃትና ግርምት ውስጥ ተውጠው የንግግሩን ትርጉም የበለጠ መረዳት ፈለጉ። ቤተ መቅደሱ የተዋበ ይሆን ዘንድ ከአርባ አመት በላይ ሃብት፣ ጉልበትና የምህንድስና ጥበብ በገፍ ፈሶበታል። ታላቁ ሄሮድስ የሮማንና የአይሁድን ጥሪት አፍስሶበታል፤ የዓለም ንጉሠ ነገሥት ሳይቀር በስጦታው አበልጽጎታል። ክብደታቸውና መጠናቸው ያስደነቁ፣ ነጫጭ እምነበረዶች ከሮማ እንዲመጡ ተደርገው የህንጻው አካል ሆነው ነበር። ለዚህም ነበር ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ትኩረት ለመሳብ በማሰብ፦ “እንዴት ያሉ ድንጋዮችና እንዴት ያሉ ህንጻዎች እንደሆኑ እይ!” [ማር 13÷1] ያሉት።GCAmh 22.1

    ለእነዚህ ቃላት የሱስ ከባድና አስገራሚ መልስ ሰጠ፦ “እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።” [ማቴ 24÷2]።GCAmh 22.2

    ክርስቶስ፣ በአካል፣ በምድራዊ ክብር መጥቶ ዓለም አቀፍ መንበረ መንግሥቱን የሚወርስበትን፣ ንሰሐ አንገባም ያሉትን አይሁዳውያን የሚቀጣበትና ከሮማ ቀንበር አገሩን ነጻ የሚያወጣበትን ክስተት ደቀ መዛሙርቱ ከየሩሳሌም ጥፋት ጋር አያይዘውት ነበር [ክርስቶስ ስልጣኑን ሲቆናጠጥ የሚፈጽመው ድርጊት ነው ብለው ያስቡ ነበር]። ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ እንደሚመጣ ጌታ ከዚህ በፊት ነግሮአቸው ነበር። እናም አሁን ፍርድ በየሩሳሌም ላይ እንደሚመጣ ሲነግራቸው አዕምሮአቸው ወደዚያ ሁለተኛ መምጣት ተመራና አዳኙን ከበው በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጠው ሳለ ጠየቁት፦ “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” [ማቴ 24÷3] አሉት።GCAmh 22.3

    የወደፊቱ ክስተት በምሕረት መጋረጃ ከደቀ መዛሙርቱ ተሸፍኖ ነበር። እነዚያን ሊሆኑ ያላቸውን ሁለቱን ክስትቶች፤ የመሲህን መሰቃየትና መሞት፣ እንዲሁም የከተማቸውንና የቤተ መቅደሳቸውን ውድመት ሙሉ በሙሉ ቢረዷቸው ኖሮ በታላቅ ድንጋጤ በተሸነፉ ነበር። ዘመን ከመፈጸሙ በፊት የሚከናወኑትን ክስተቶች ቅደም ተከተል ክርስቶስ ገለጸላቸው። ንግግሮቹ ያኔ ሙሉ በሙሉ መረዳትን አላገኙም ነበር። በውስጡ ያዘሉትን መመሪያዎች ሕዝቦቹ በሚፈልጉበት ሰዓት ግን ትርጉማቸው ይገለጽ ዘንድ ነበረው። የተናገረው ትንቢት ሁለት ትርጉም የያዘ ነበር፦ ስለየሩሳሌም መጥፋት ሲያመለክት ሳለ ስለመጨረሻው ዘመን መከራም የሚገልጽ ነበር።GCAmh 22.4

    የሱስ፣ ለሚያደምጡት ደቀ መዛሙርት በከሃዲዋ እሥራኤል ላይ የሚወርደውን ፍርድ፣ በተለይም ደግሞ መሲህን አንቀበልም ብለው በመስቀላቸው የሚመጣውን፣ የሚገባቸውን የበቀል ቅጣት ነገራቸው። ይህንን አሳዛኝ መደምደሚያ የሚቀድሙ ግልጽ ምልክቶች ይፈጸማሉ። አስፈሪው ሰዓት በድንገትና በቅጽበት ይመጣል። አዳኙ ተከታዮቹን አስጠንቅቋል፦ “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።” [ማቴ 24÷15፣16፤ ሉቃ 21÷20]። አሁን ከከተማዋ ትንሽ ራቅ ብሎ የሚታየው የሮማውያን የጣዖት አምልኮ ሥርዓት በተቀደሰው ስፍራ ሲቆም የክርስቶስ ተከታዮች በመሸሽ ከአደጋ ማምለጥ ነበረባቸው። የማስጠንቀቂያ ምልክቱ በሚታይበት ጊዜ የሚያመልጡ ሁሉ መዘግየት አይገባቸውም። በይሁዳ አገር ሁሉ፣ እንዲሁም በራስዋ በየሩሳሌም የሽሽት ትዕዛዙ ወዲያውኑ አዎንታ ማግኘት ይኖርበታል። የቤቱ ጣራ ላይ ያለ ቢኖር እጅግ የከበረውን ቅርሱን እንኳ ለመያዝ ወደ ቤቱ መግባት አይኖርበትም። በመስኩ ወይም በአትክልት ስፍራው የሚሰሩ እነርሱ፣ በቀኑ ሃሩር ሲለፉ ሳለ በእርሻቸው ድንበር ላይ ያስቀመጡትን ልብስ ሊያነሱ መመለስ የለባቸውም። የውድመቱ አካል እንዳይሆኑ ለአፍታም እንኳ ማቅማማት አይኖርባቸውም።GCAmh 23.1

    በሄሮድስ ግዛት ዘመን እጅግ መዋብ ብቻ ሳይሆን ህንጻዎች፣ ቅጥሮችና ምሽጎች ተሰርተውባት፣ ተፈጥሮአዊ አቀማመጧ ካደላት አቅም ጋር ተዳምሮ የሩሳሌምን ፈጽሞ የማትደፈር አስመስሎአት ነበር። ስለ መጥፋትዋ በአደባባይ በዚህ ጊዜ የሚናገር እርሱ፣ ልክ በኖህ ዘመን እንደተደረገው፣ መዓት ጠሪ፣ እብድ መባሉ አይቀሬ ነበር። ክርስቶስ ግን ተናግሮ ነበር፦ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።” [ማቴ 24÷35]። በኃጢአትዋ ምክንያት በየሩሳሌም ላይ ቁጣ ታውጆባት ነበር፤ ግትርነት ያሸነፈው እምነት-የለሽነቷ ውድመትዋን እርግጠኛ አደረገው።GCAmh 23.2

    ጌታ በነቢዩ ሚክያስ ተናግሮ ነበር፦ “ፍርድን የምትጠሉ፣ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንት የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእሥራኤል ቤት ገዦች ሆይ፣ እባካችሁ ይህን ስሙ። ጽዮንን በደም የሩሳሌምንም በኃጢአት ይሰራሉ። አለቆችም በጉቦ ይፈርዳሉ፣ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፤ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።” [ሚክ 3÷9-11]።GCAmh 23.3

    እነዚህ ቃላት ብልሹና ተመጻዳቂ የነበሩትን የሩሳሌማውያንን በትክክል ገልጸዋቸዋል። የሕጉን ትእዛዛት በግትርነት ጠብቀናል ሲሉ ሳለ መመሪያዎቹን ግን ጥሰው ነበር። ንጽህናውና ቅድስናው ኃጢአታቸውን ራቁት ስላስቀረው ክርስቶስን ጠሉት፤ በኃጢአታቸው ምክንያት ለመጣባቸው ችግር ሁሉ መንስኤው እርሱ እንደሆነ አድርገው ወነጀሉት። ኃጢአት አልባ እንደሆነ ቢያውቁም ለሕዝባቸው ደህንነት ሲባል፣ እንደ ሉአላዊ አገር ይቀጥሉ ዘንድ፣ የእርሱ መሞት የግድ መሆኑን አወጁ። “እንዲህ ብንተወው” አሉ የአይሁድ መሪዎች፣ “ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ።” [ዮሐ 11÷48]። ክርስቶስ ከተሰዋ እንደገና ጠንካራና አንድ ሕዝብ ሊሆኑ ይችላሉ፤ እንደዚህም አመካኙ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፉ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ቢሞት ይሻላል በሚለው በሊቀ ካህናቸው ሃሳብ ተስማሙ።GCAmh 23.4

    እንዲህም አድርገው የአይሁድ መሪዎች “ጽዮንን በደም፤ የሩሳሌምንም በኃጢአት” [ሚክ 3÷10] ገነቡአት። በኃጢአታቸው ስለገሰፃቸው መሲህን መግደላቸው አልበቃ ብሎ ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው፣ በእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች እንደሆኑ ቆጥረው፣ አምላካቸው ከጠላቶቻቸው እጅ እንዲያስመልጣቸው ይጠብቁበት ነበር። “ስለዚህ” ቀጠለ ነቢዩ፣ “በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤ የሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፤ የቤቱም ተራራ እንደዱር ከፍታ ይሆናል።” [ሚክ 3÷12]GCAmh 24.1

    የየሩሳሌም ጥፋት በክርስቶስ በራሱ ከተነገረ ከአርባ ዓመት በኋላ ጌታ ፍርዱን በከተማዋ እና በሕዝቡ ላይ አዘገየ። ወንጌሉን ላልተቀበሉትና አንድያ ልጁን ለገደሉ ያሳየው ታጋሽነት የሚያስደንቅ ነበር። ፍሬ ያልሰጠው ተክል ምሳሌ እግዚአብሔር ከአይሁድ ሕዝብ ጋር የነበረውን ግንኙነት የሚወክል ነበር፤ “ቁረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች” የሚለው ትእዛዝ ተላልፎ ነበር [ሉቃ 13÷7]። አሁንም ግን መለኮታዊ ምሕረት ለጥቂት ጊዜ ታግሶአት ነበር። የክርስቶስን ባህርይና የፈጸመውን ተግባር ያላስተዋሉ ብዙዎች አሁንም በአይሁድ መካከል ነበሩ። ወላጆቻቸው ያቃለሉትን ብርሐን፣ የተሰጣቸውንም ዕድል ልጆቻቸው አላገኙም ነበር። በሐዋርያቱና አብረዋቸው ይሰሩ በነበሩ ሰዎች አማካኝነት እግዚአብሔር ብርሐን ይፈነጥቅላቸዋል። በመወለዱና በሕይወቱ ብቻ ሳይሆን በሞቱና በመነሳቱ ትንቢት እንዴት እንደተፈጸመ ይረዱ ዘንድ ይፈቅድላቸዋል። በአባቶቻቸው ኃጢአት ምክንያት በልጆቹ ላይ መርገም አልመጣም (አልተኮነኑም) ነበር። ነገር ግን ለወላጆቻቸው ስለተሰጠው ብርሐን ከነበራቸው ግንዛቤ በተጨማሪ ለራሳቸው የተቸራቸውን ብርሐን ባለመቀበላቸው፣ በወላጆቻቸው ኃጢአት እነርሱም ተሳታፊ (ተባባሪ) ሆነው የበደላቸውን ጽዋ ሞሉ።GCAmh 24.2

    እግዚአብሔር ለየሩሳሌም ያሳየው ትዕግስት ያረጋገጠው ነገር ቢኖር የአይሁድን በአመጽ የመቀጠል ግትርነት ነበር። ለየሱስ ደቀ መዛሙርት ከነበራቸው ጥላቻና ጭካኔ የተነሳ የመጨረሻውን የምሕረት ስጦታ አንቀበልም አሉ። ከዚያም እግዚአብሔር ጥበቃውን ከእነርሱ አነሳ፤ ሰይጣንንና መላእክቱን የገደበውን ሃይሉን መለሰ፣ ያችም ሃገር ያስተዳድራት ዘንድ ለመረጠችው መሪዋ [ለዲያብሎስ] ተተወች። የክፋት ትርታቸውን የሚያንበረክከውን የክርስቶስን ጸጋ ልጆችዋ እምቢ አሉ፤ እነዚህም ሃሳቦቻቸው በቁጥጥራቸው ስር አደረጓቸው። ሰይጣን እጅግ ጠንካራውንና ፈጽሞ የተዋረደውን የነፍስ ስሜት ቀሰቀሰ። ሰዎች ማገናዘብ ተሳናቸው፤ ከምክንያት አልፈው በስሜትና በእውር ቁጣ ቁጥጥር ስር ሆኑ። በጭካኔያቸውም ወደ ሰይጣንነት ተለወጡ። በቤተሰቡ፣ በሕዝቡ፣ በላይኛውና በታችኛው መደብ በሞላ፣ መላምት፣ ቅንዓት፣ ጥላቻ፣ ጸብ፣ አመጽና ነፍሰ ገዳይነት ተንሰራፍቶ ነበር። አደጋ የሌለበት ስፍራ አልነበረም። ጓደኛሞችና ዘመዳሞች ይከዳዱ ነበር። ወላጆች ልጆቻቸውን ገደሉ፤ ልጆችም ወላጆቻቸውን። የሕዝቡ አስተዳዳሪዎች ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም አልነበራቸውም። ገደብ የለሽ ፍላጎቶቻቸው ጨካኝና አምባገነን አድርጓቸው ነበር። ጥፋት በሌለበት በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አይሁዳውያን የሃሰት ምስክርነትን ተቀብለዋል። አሁን ደግሞ የሐሰት ውንጀላዎች የራሳቸውን ሕይወት አልጨበጥ ባይ አደረገባቸው። በድርጊታቸውም ለረጅም ጊዜ “የእሥራኤልን ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ” [ኢሳ 30÷11] ሲሉ ቆይተዋል። አሁን ፍላጎታቸው ተቸራቸው። ፍርሃተ-እግዚአብሔር ውስጣቸውን መረበሽ አቆመ። የሕዝቡ ራስ ሰይጣን ሆኖ፣ የሕዝባዊና የሐይማኖታዊ ከፍተኛ የስልጣን ስፍራዎች ጭምር በእርሱ እዝ ስር ነበሩ።GCAmh 24.3

    የተቀናቃኝ አንጃ መሪዎች አንዳንድ ጊዜ የተጎሳቆሉ ተጠቂዎችን ይዘርፉና ያሰቃዩ ዘንድ ይተባበሩ ነበር፤ እንደገናም እርስ በርሳቸው ይጣሉና ያለ ምሕረት ይተራረዱ ነበር። አሰቃቂውን ጭካኔአቸውን የቤተ መቅደሱ ክቡርነት እንኳ አላስቀረውም ነበር። የሚያመልኩ ሰዎች ከመሰዊያው ስር ይገደሉ ነበር፤ የሞቱትም ሬሳ ቤተ መቅደሱን በክሎት ነበር። ሆኖም በጭፍንና በስድብ አዘል አይን ያወጣ አስተሳሰባቸው፣ የዚህ አሰቃቂ ሥራ አነሳሽዎች፣ የሩሳሌም የእግዚአብሔር የራሱ ከተማ ስለሆነች ትጠፋለች የሚል ምንም አይነት ፍርሃት እንደሌለባቸው በአደባባይ ይለፈልፉ ነበር። ስልጣናቸውን የበለጠ ለማደላደል ሲሉ፣ የሮማ ክፍለ ጦር መቅደሱን እየከበበ ባለበት ሰዓት እንኳ ለሐሰተኛ ነብያት ጉቦ ከፍለው ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ማዳን ዝም ብሎ መጠበቅ እንዳለበት ያስለፍፉ ነበር። ጠላቶቻቸውን ያሸንፉ ዘንድ ታላቁ ንጉሥ(አምላክ) ጣልቃ እንደሚገባ ብዙዎች እስከመጨረሻዋ ሰዓት እምነት ጥለው ነበር። እሥራኤል ግን መለኮታዊ ጥበቃን አሻፈረኝ ብላለችና አሁን የሚያድናት የለም። ደስታ-ቢስዋ የሩሳሌም! የሰው አገር ሰራዊት ቅጥሮችዋን ሲደረማምሱና የጦር ሰዎችን ሲያርዱ ሳለ፣ በውስጥ አለመግባባት ተከፋፍላ፣ ልጆችዋ እርስ በርስ ተገዳድለው በጃቸው ጎዳናዎችዋን በደም ያቀልሙት ነበር።GCAmh 25.1

    ስለየሩሳሌም መጥፋት በክርስቶስ የተነገረው ሁሉ አንድዋም ፊደል ሳትቀር ተፈጸመች። የማስጠንቀቂያ ቃላቱን እውነትነት አይሁዳውያን በተግባር አረጋገጡ፣ “በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።” [ማቴ 7÷2]።GCAmh 25.2

    ጥፋትንና ውድመትን የሚጠቁሙ ምልክቶችና አስገራሚ ክስተቶች መታየት ጀመሩ፤ በእኩለ ሌሊት እንግዳ መብራት በቤተ መቅደሱና በመሰዊያው ላይ አንጸባረቀ። በፀሐይ ግባት ጊዜ ሰረገላዎችና የጦር ሰዎች ለሰልፉ ሲዘጋጁ ደመናዎች ላይ ተስለው ታዩ። በቤተ መቅደሱ በሌሊት የሚያገለግሉ ካህናት ከሚሰሙት ምስጢራዊ (እንግዳ) ድምጽ የተነሳ በፍርሃት ተዋጡ። ምድር ተሸበረች፤ የብዙ ሕዝብ ድምጽ ” በፍጥነት እንሂድ” ብሎ ሲጮህ ተሰማ። ከክብደቱ የተነሳ በብዙ ሰዎች ጥረት የሚዘጋው፣ በድንጋይ መሃል ተጣብቀው በጥልቀት ወደ ታች ገብተው በቆሙት ከባባድ የብረት ዘንጎች ታግዞ የቆመው ታላቁ የምሥራቅ በር ማን እንደከፈተው ሳይታይ በእኩለ ሌሊት ተከፈተ። - Milman, The History of the Jews, book 13.GCAmh 25.3

    ለሰባት ዓመታት በየሩሳሌም ጎዳናዎች እየተመላለሰ የሚወርድባትን መከራ የሚያውጅ አንድ ሰው ነበር። በቀንና በሌሊት ዋይታውን ያሰማ ነበር፦ “ድምጽ ከምሥራቅ፣ ድምጽ ከምዕራብ፣ ድምጽ ከአራቱም ነፋሳት፣ ስለየሩሳሌምና ስለመቅደሱ ጥፋት የሚናገር ድምጽ፣ ስለ ሙሽራውና ስለ ሙሽራይቱ ጥፋት ስለ ሕዝቡም ሁሉ ጥፋት የሚናገር ድምጽ።” ይህ እንግዳ ፍጡር ታስሮ ተገረፈ፣ የምሬት ድምጽ ግን ፈጽሞ ከከንፈሩ አልወጣም። ለደረሰበት ስድብና ጉስቁልና የሚመልሰው “ወዮ ለየሩሳሌም ወዮ፣ ወዮ በርስዋ ለሚኖሩ ሁሉ!” ብቻ ነበር። እንደሚመጣ በተናገረው፣ በከበበው ጦር እስኪገደል ድረስ የማስጠንቀቂያ ጩኸቱን አላቋረጠም ነበር። በየሩሳሌም ጥፋት አንድስ እንኳ ክርስቲያን አልሞተም። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። ቃሉን ያመኑ ሁሉ፣ ተስፋ የተገባለትን ምልክት ይጠባበቁ ነበር። “የሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ” አለ የሱስ፣ “በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ።” [ሉቃ 21÷20፣21]። በሴስቲየስ የሚመሩት ሮማውያን ከተማዋን ከከበቡ በኋላ፣ ወዲያውኑ ለማጥቃት ሁኔታዎች ሁሉ የተመቻቹ መስለው እያሉ ሳይታሰብ ከተማዋን ትተው አፈገፈጉ። የተከበበውና ተስፋ ወደ መቁረጥ የተቃረበው [የአይሁድ] ሰራዊት እጁን ሊሰጥ በተቃረበበት ጊዜ ምንም አይነት ሊብራራ የሚችል ምክንያት ሳይኖር የሮም አዛዥ ጦሩን መለሰ። ምሕረት የተሞላበት የእግዚአብሔር ጥንቃቄ ለራሱ ሕዝቦች ደህንነት ሲል የሚፈጸሙትን ነገሮች ይመራ ነበር። ይጠብቁ ለነበሩት ክርስቲያኖች ቃል የተገባው ተስፋ ተሰጠ፤ የአዳኙን ማስጠንቀቂያ ለሚሰሙና ለሚታዘዙ ሁሉ አሁን ዕድል ተበረከተ። ክስተቶች ሁሉ ተገለባብጠው ምስቅልቅላቸው ወጥቶ ስለነበር ሮማውያንም ሆኑ አይሁዳውያን የሚሸሹትን ክርስቲያኖች ያስቀሩ ዘንድ እንዳይችሉ ተደርገው ነበር። ሴስቲየስ ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ አይሁዳወያኑ ከምሽጎቻቸው እየወጡ ይከተሏቸው ጀመር። ሁለቱም ተቃራኒ ኃይሎች በከባድ ውጊያ ተጠምደው ሳለ ከተማዋን ለቀው ይሸሹ ዘንድ ለክርስቲያኖች ዕድል ተከፈተ። የገጠሩ ክፍልም ሊይዟቸው ጥረት ከሚያደርጉት ጠላቶች ጸድቶ ነበር። ከተማዋ በተከበበች ጊዜ አይሁድ ሁሉ ለዳስ በዓል በየሩሳሌም ተሰብስበው ነበር። በመሆኑም በምድሪቱ የነበሩ ክርስቲያኖች ሳይረበሹ ማምለጥ ቻሉ። ሳይዘገዩም አደጋ ወደሌለበት ስፍራ፣ ከዮርዳኖስ ባሻገር በፐሪያ ምድር ወደምትገኝ ከተማ ወደ ፔላ ሸሹ።GCAmh 25.4

    የአይሁድ ሰራዊት ሴስቲየስንና ሰራዊቱን ተከትሎ ከኋላቸው እጅግ ጠንካራ በሆነ ሰልፍ በመውጋት ሙሉ ለሙሉ ሊደመስሱት ምንም አልቀራቸውም ነበር። ከከባዱ ውጊያ የተነሳ የሮም ሰራዊት የማፈግፈግ ውሳኔውን የተገበረው በጭንቅ ነበር። አይሁዳውያን ብዙም ጉዳት ሳይደርስባቸው አመለጡ፤ ከምርኮአቸውም ጋራ በድል ወደ የሩሳሌም ተመለሱ። ሆኖም ይህ ግልጽ ስኬት ያመጣላቸው ጉዳትን ብቻ ነበር። ይህ የተፈጠረው ሁኔታ ኃይለኛ የመከላከል መንፈሳቸውን የበለጠ አነቃቅቶ ሮማዊያንን እንዲቋቋሙ ሲያነሳሳቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሮማዊያኑ ለውድመት በተሰጠችው ከተማ ላይ ሊነገር የማይችል ሰቆቃ በፍጥነት ያመጡባት ዘንድ ዘመቱ።GCAmh 26.1

    ቲቶ እንደገና ሲከባት ዘግናኝ ውድመት በከተማዋ ላይ መጣ። ከተማዋ የተከበበችው በፋሲካ በዓል ወቅት ስለነበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በቅጥሮችዋ ውስጥ ነበሩ። በሥነ ሥርዓት ቢጠበቁ ኖሮ ነዋሪዎችዋን ለዓመታት መመገብ ይችሉ የነበሩት የእህል ጎተራዎችዋ፣ በሚቀናቀኑ ቡድኖች ቅንአትና በቀል ወድመው፣ የሩሳሌም በረሃብ ሰደድ እሳት ተንቀለቀለች። አንድ የስንዴ መስፈሪያ በአንድ ታለንት ተሸጠ። የረሃቡ ስሜት ከሚችሉት በላይ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች የቀበቶአቸውን ቆዳ፣ የነጠላ ጫማቸውንና የጋሻቸውን ልባስ መቆርጠም ጀመሩ። ከከተማዋ ቅጥሮች ውጪ የበቀሉትን የዱር እጽዋት ለመሰብሰብ አያሌ ሰዎች በሌሊት ተደብቀው ይወጡ ነበር። አብዛኛዎቹ ተይዘው በአሰቃቂ ግርፋት ሲገደሉ፣ አምልጠው የተመለሱት ደግሞ ብንሞትም እንሙት ብለው ያመጡትን በሌሎች ይዘረፉ ነበር። ከሁሉም በላይ ኢ-ሰብአዊ የሆነውን ድርጊት የፈጸሙት በስልጣን ላይ ያሉት ነበሩ። የደበቁት ትርፍራፊ፣ አንዳች የሚቀመስ ነገር ሸሽገው ይሆናል በማለት ችግር ያበለዛቸውን ረሃብተኞች ይገርፏቸው ነበር። በደንብ ጠግበው የሚያድሩቱ [የሚበሉት ከሌላቸው ቀምተው] በመውሰድ የወደፊት ስንቅ ይሆናቸው ዘንድ በጎተራ ማከማቸት የሚፈልጉ ሰዎች እነዚህን የጭካኔ ተግባራት ደጋግመው ይፈጸሙ ነበር።GCAmh 26.2

    በሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብና በቸነፈር እረገፉ። ተፈጥሮአዊ መልካምነት የጠፉ መሰለ። ባሎች ሚስቶቻቸውን፣ ሚስቶችም ባሎቻቸውን ዘረፉ። ልጆች በእድሜ ከገፉ ወላጆቻቸው አፍ ምግብ ሲነጥቁ ይታዩ ነበር። “በውኑ ሴት ህጻንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን?” [ኢሳ 49÷15] የሚለው የነቢዩ ጥያቄ በዚያች በተረገመች ከተማ ውስጥ መልስ አገኘ። “የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻቸውን ቀቅለዋል፤ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኑአቸው።” [ሰቆ ኤር 4÷10]። እንደገናም ከአንድ ሺህ አራት መቶ አመት በፊት የተነገረው የማስጠንቀቂያ ትንቢት ተፈጸመ፦ “በአንተ ዘንድ ያለችው የተለሳለሰችና በቅምጥልነት ሁል ጊዜ ትኖር የነበረችው፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፣ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፣ በወንድና በሴት ልጅዋም፣ በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅ፣ በምትወልዳቸውም ልጆች ትቀናለች፤ በደጆችህም ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች።” [ዘዳ 28÷56፣57]።GCAmh 27.1

    ሮማዊያን መሪዎች በአይሁድ ላይ ታላቅ ፍርሃት በመንዛት እጅ እንዲሰጡ ብዙ ጣሩ። ሲወሰዱ ያንገራገሩ ምርኮኞች ተሰቃዩ፤ ተገረፉ፤ በከተማይቱ ቅጥር ትይዩም ተሰቀሉ። በዚህ አኳኋን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጉ ነበር። ከዮሳፍጥ ሸለቆ ጀምሮ እስከ ቀራንዮ፣ እጅግ ብዛት ያላቸው መስቀያ እንጨቶች ተጠጋግተው ተተክለው፣ በመካከላቸው መተላለፍ እስኪያቅት ድረስ ኢ-ሰብአዊው ድርጊት ቀጥሎ ነበር። በጲላጦስ የፍርድ ወንበር ፊት ይወርድ ዘንድ የተለመነው ያ አሳዛኝ እርግማን በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈጻሚ ሆነ፦ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን።” [ማቴ 27÷25]።GCAmh 27.2

    ቲቶ በፈቃዱ አስፈሪውን ትዕይንት ሊያስቆመው፣ የሩሳሌምንም ከሞላው ጽዋዋ መዓት ሊያተርፋት ይችል ነበር። በሸለቆዎቹ የተጣሉትን የሬሳዎች ክምር ሲመለከት በታላቅ ድንጋጤ ተዋጠ። በደብረ ዘይት ተራራ ጫፍ ሆኖ የሚያምረውን መቅደስ በተመስጦ ተመለከተ፤ አንድስ እንኳ ድንጋይ እንዳይነካ ትዕዛዝ ሰጠ። ይህንን ስፍራ በቁጥጥሩ ስር ከማድረጉ በፊት፣ የከበረውን ስፍራ በደም ያረክሰው ዘንድ እንዳያስገድዱት ለአይሁድ መሪዎች ልባዊ ልመና አቀረበ። ወደ ውጪ ወጥተው [ከመቅደሱ ርቀው] በሌላ ስፍራ የሚዋጉ ከሆነ፣ ማንም ሮማዊ መቅደሱን አያረክስም። ዮሴፈስ ራሱ ልብን በሚነካ ንግግር እጃቸውን በመስጠት ራሳቸውን፣ ከተማቸውንና የማምለኪያ ስፍራቸውን ያተርፉ ዘንድ ተማጸናቸው። ለንግግሩ ያገኘው ምላሽ ግን መሪር እርግማን ነበር። የመጨረሻው ሰብዓዊ አስታራቂ ቆሞ ሲለምናቸው ሳለ የቀስት ናዳ አወረዱበት። አይሁዳውያን የእግዚአብሔርን ልጅ ተማፅኖዎች አልተቀበሉም ነበር፤ እናም አሁን በምሬት ሀሳባቸውን ለማስተው [ዮሴፈስ] የሚያደርገው ልመና፣ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ በተቃውሞ እንዲቀጥሉ የባሰ አደነደናቸው። መቅደሱን ለማትረፍ ያደረገው የቲቶ ጥረት መና ቀረ። ድንጋይ በድንጋይ ላይ በዚያ እንደማይቀር ከእርሱ የሚበልጠው ጌታ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።GCAmh 27.3

    የአይሁድ መሪዎች ጭፍን ግትርነት፣ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ሲፈጸሙ የነበሩ አስከፊ ወንጀሎች፣ የሮማውያንን ጥላቻና ንዴት ቀስቅሶ፣ ቲቶ መቅደሱን በኃይል ለመማረክ ወሰነ። ከተቻለ ከውድመት እንዲተርፍ ግን አሁንም ወስኖ ነበር። ሆኖም ትዕዛዙ አልተከበረለትም። ሌሊት በድንኳኑ ተኝቶ ሳለ አይሁዳውያን ከመቅደሱ እየወጡ ቅጥሩ ውጪ የነበሩትን ወታደሮቹን ማጥቃት ጀመሩ። በትግሉ መሃል በበረንዳው በኩል ባለ ቀዳዳ የሳት ችቦ በአንድ ወታደር ተወርውሮ በዝግባ የተዋበው ቅዱሱ ስፍራ ወዲያውኑ ተቀጣጠለ። ቲቶ ወደ ቦታው ሲሮጥ ደረሰ፣ ሹማምንቱና አለቆችም ደረሱ፤ እሳቱንም ያጠፉ ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ። ማንም ግን የሰማው አልነበረም። ይልቁንም በንዴት የተቃጠሉት ወታደሮቹ ትንታጎችን ከመቅደሱ ተያይዘው ባሉ ክፍሎች እየወረወሩ በዚያ ተጠግተው የነበሩትን አያሌ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሰይፍ ረፈረፏቸው። በመቅደሱ ደረጃዎችም ደም እንደ ውሃ ጎረፈ። እልፍ አእላፋት አይሁዳዊያን ሕይወታቸው አለፈ። ከሰልፉ ሩምታ ልቀው የሚሰሙ የጩኸት ድምጾች ነበሩ፦ “ኢካቦድ!” - ክብር [ከእሥራኤል] ሸሸ።GCAmh 27.4

    “የሰራዊቱን ቁጣ ይመልስ ዘንድ ቲቶ አልተቻለውም፤ የተቀደሰውን ቤት ከሹማምንቱ ጋር ሆኖ ቃኘው፤ ውበቱ በግርምት ሞላቸው፤ ነበልባሉ ገና ወደ ቅዱሱ ስፍራ ስላልደረሰ ወደ ፊት ተንደርድሮ በመሄድ የሚገሰግሰውን ነበልባል ያቆሙት ዘንድ ወታደሮቹን በመገሰጽ ያተርፈው ዘንድ ወደደ። የመቶ አለቃው ላይቤራሊስ ትዕዛዙ በወታደሮቹ አዎንታ ያገኝ ዘንድ ጣረ። ሆኖም ለንጉሠ ነገስቱ የነበረው ክብር እንኳ በአይሁዳውያን ላይ ለነበረው ጥልቅ ጥላቻ፣ በጦፈ ጦርነት ውስጥ ለሚነሳሳው የጋለ ስሜት እንዲሁም ለዘረፋ ስግብግብነት ቦታ ለቀቀ። በሚንቀለቀለው ነበልባል ውስጥ፣ በዙሪያቸው በፍካት የሚንጸባረቀውን ወርቅ ተመልክተዋል። በመቅደሱ ውስጥ ቁጥር ስፍር የሌለው የወርቅ ክምችት ያለ መሰላቸው። አንድ ወታደር በስውር፣ የተቀጣጠለ ችቦ በበሩ ማጠፊያዎች መካከል ወደ ውስጥ ሲወረውር ህንጻው በሙሉ በእሳት ተያያዘ። አይን የሚያሳውረው ጭስና እሳት ሹማምንቱ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ሲያስገድዳቸው የተከበረው ቤት ለአይቀሬው ዕጣ ፈንታው ተተወ።”GCAmh 28.1

    “ትዕይንቱ ለሮማውያን የሚሰቀጥጥ ነበር፤ ለአይሁዳውያኑ እንዴት ይሆን? ከተማዋ የተመሠረተችበት ኮረብታ ቁንጮ እንደ እሳተ-ገሞራ በእሳት ተንቀለቀለ። ህንጻ በህንጻ ላይ በታላቅ ኃይል ሲወድቅ እየተፈረካከሰ በእቶኑ እሳት ይዋጥ ነበር። የዝግባ ጣራዎች እሳት እንደያዛቸው ወረቀቶች ሆኑ። በወርቅ ቅጠል የተለበጡት የጣራዎቹ ቁንጮዎች እንደ ቀይ ብርሀን ያንጸባርቁ ነበር። ከበሮቹ መሰሶዎች የሚንቀለቀል እሳትና ጭስ ወደ ላይ ይወጣ ነበር። በአቅራቢያው ያሉ ኮረብታዎች በብርሐን ተሞሉ፣ በጥልቅ ሃዘን ውስጥ የሆኑ ሰዎች በአንድነት የውድመቱን ሂደት በታላቅ ድንጋጤ ሲከታተሉ ይታዩ ነበር። በቅጥርዋና በከፍታማው የከተማዋ ክፍል የነበሩ አንዳንዶች በተስፋ መቁረጥ ስቃይ ፊታቸው ገርጥቶ፣ ሌሎቹ ሊተገበር በማይችል የበቀል ስሜት ነደው ይታዩ ነበር። ወዲያ ወዲህ የሚራወጡት የሮም ወታደሮች ጩኸት፣ በነበልባሉ ውስጥ የሚያልቁት የተዋጊዎች ማንቋረር፣ እንደ መብረቅ እየተከሰከሰ ከሚያጉራራው አጠና እና ከሚንቀለቀለው ነበልባል ድምጽ ጋር ተዋህዶ ነበር። የተራሮቹ ማሚቶ በየከፍታው ቆመው የሚጮሁትን ሰዎች ድምጽ እያስተጋባ ወዲያ ወዲህ ያመላልሰው ነበር። በቅጥሮቹ ዙሪያ ሁሉ የሰዎች ዋይታና ጩኸት ያስተጋባ ነበር። በረሃብ አጽማቸው የቀረ፣ በሞት አፋፍ የነበሩ ሁሉ ከመጠን የዘለለ ስቃያቸውንና ምድረ-በዳነታቸውን ይገልጹ ዘንድ የቀራቸውን ጭላጭ ጉልበት አጠራቅመው አፋቸውን ከፈቱ።GCAmh 28.2

    “በቅጥሮቹ ውስጥ የተፈጸመው ግድያ ውጪ ካለው ትዕይንት እጅግ የባሰ ነበር። ወንዶችና ሴቶች፣ ታላላቆችና ታናናሾች፣ አማጽያንና ካህናት፣ የተዋጉትም ሆኑ ምሕረት ይደረግላቸው ዘንድ የለመኑ፣ ሁሉም በአንድ ላይ በአሰቃቂ እልቂት ተመልምለው እረገፉ። የታረዱት ቁጥር ከአራጆቹ በለጠ። የሮማ ወታደሮች የዘር ማጥፋት ግድያቸውን ይቀጥሉ ዘንድ በሬሳ ቁልል ላይ ይረማመዱ ነበር።”- Milman, The History of the Jews, book 16.GCAmh 29.1

    ከቤተ መቅደሱ ውድመት በኋላ ከተማዋ በሮማ እጅ ወደቀች። የአይሁድ መሪዎች አይደፈሬ ቅጥራቸውን ጥለው ለብቻቸው ሆነው ቲቶ አገኛቸው። በመገረም ተመለከታቸው፤ እግዚአብሔር በእጁ አሳልፎ እንደሰጣቸውም ተናገረ፤ ባይሆንማ ኖሮ እነዚያን አስደናቂ ቅጥሮች ይደመሰስ ዘንድ የሚቻለው ኃይል ባልኖረ ነበር። ከተማዋም ሆነ ቤተ መቅደሱ እስከ መሰረታቸው ድረስ ፈጽመው ወደሙ። ቤተ መቅደሱ ቆሞበት የነበረው መሬት “እንደ እርሻ” ታረሰ [ኤር 26÷18]። በከበበውና ተከትሎም በመጣው እልቂት ከሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። የተረፉትም በምርኮ ተይዘው ተወሰዱ፤ በባርነት ተሸጡ፤ የወራሪውን አንጸባራቂ ድል ያደምቁ ዘንድ ወደ ሮም እየተጎተቱ ተወሰዱ፤ በትያትር ማሳያ ቤቶች ለአራዊት ተወረወሩ፤ የቀሩትም ያለ መጠለያ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ተበተኑ።GCAmh 29.2

    አይሁዳውያን የራሳቸውን ሰንሰለት አበጁ፤ የበቀል ጽዋቸውን ራሳቸው ሞሉ። እንደ አገር የደረሰባቸው ከባድ ውድመት፣ ከተበተኑም በኋላ ያገኛቸው መከራ የራሳቸው እጅ የዘራውን ሰብል እየሰበሰበ ነበር። ነብዩ ይላል፦ “እሥራኤል ሆይ ጥፋትህ ከራስህ ነው።” “በኃጢአትህ ወድቀሃልና።” [ሆሴ 13÷9፤14÷1]። ስቃዮቻቸው በእግዚአብሔር ቀጥተኛ አዋጅ የመጣባቸው ቅጣት እንደሆነ ተደርገው ብዙ ጊዜ ይታያሉ። እንዲህ በማድረግ ታላቁ አሳሳች የራሱን ሥራ ይደብቃል። መለኮታዊ ፍቅርን አንቀበልም ብለው በመደንደናቸው የእግዚአብሔር ጥበቃ ከእነርሱ እንዲሄድ አደረጉ፤ ሰይጣንም እንደራሱ ፈቃድ ያስተዳድራቸው ዘንድ ተፈቅዶለት ነበር። በየሩሳሌም ጥፋት የተፈጸሙት አሰቃቂ ጭካኔዎች፣ ሰይጣን ይነግስባቸው ዘንድ ለቁጥጥሩ ራሳቸውን አሳልፈው በሰጡ ላይ የሚያሳየውን የበቀል ኃይል በተግባር የሚያሳይ ነው።GCAmh 29.3

    እያጣጣምነው ላለው ሰላምና ጥበቃ፣ ለክርስቶስ ምን ያህል ባለእዳዎች እንደሆንን በውል እናውቀው ዘንድ አይቻለንም። የሰው ልጅ ሙሉ ለሙሉ በሰይጣን ቁጥጥር ስር እንዳያልፍ የሚያደርገው፣ ወሰኑን የሚገድበው የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ጨካኝና አረመኔውን ኃይል በማስቆሙ፣ ለእግዚአብሔር ምሕረትና ታጋሽነት ምስጋና ያቀርቡ ዘንድ ለአመጸኞችና ለምስጋና-ቢሶች ከበቂ በላይ ምክንያት አለ። ሆኖም ሰዎች የመለኮታዊውን ትዕግስት ገደብ ሲያልፉ፣ ያ ገደብ ይነሳል። በመተላለፍ ምክንያት የሚመጣውን ቅጣት ያስፈጽም ዘንድ እግዚአብሔር በኃጢአተኛው ፊት አይቆምም። የምህረቱን እምቢ ባዮች ግን የዘሩትን ያጭዱ ዘንድ ለራሳቸው ይተዋቸዋል። እያንዳንዱ የተተወ ብርሐን፣ እያንዳንዱ የተናቀ ወይም ያልተሰማ ማስጠንቀቂያ፣ እያንዳንዱ የተተገበረ ፍላጎት፣ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ሕግ ጥሰት፤ ፍሬ ሳያፈራ የማይቀር፣ የሚበተን ዘር ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ በተደጋጋሚ (በቋሚነት) እምቢ ሲባል በመጨረሻ ከኃጢአተኛው ይወሰዳል፤ የነፍስን ክፉ ምኞት የሚከላከል ኃይልም አይኖርም፤ ከሰይጣን ጠላትነትና ክፉ ሥራም መከለያ አይገኝም። የየሩሳሌም ጥፋት፣ የመለኮትን ጸጋ ስጦታ ለሚያቃልሉ፣ የመለኮትንም የምሕረት ተማፅኖ እምቢ ለሚሉ ከባድና አስፈሪ ማስጠንቀቂያ ነው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ስላለው የመረረ ጥላቻ ምስክር ይሆን ዘንድ በተላላፊውም ላይ ስለሚመጣው እርግጠኛ ቅጣት ማሳያ ይሆን ዘንድ ከዚያ የተሻለ ማረጋገጫ አልነበረም።GCAmh 29.4

    የሩሳሌም ስለምትጎበኝበት ፍርድ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት፣ ያን በእሥራኤል ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ውድመት እንደ ምንም በሚያስቆጥር አኳኋን፣ ገና ወደፊት ተፈጻሚነት ያገኛል። በተመረጠችው ከተማ ዕጣ ፈንታ ውስጥ የእግዚአብሔርን ምሕረት አልቀበልም ያለን፣ በሕጉም ላይ የተረማመደን ዓለም የወደፊት ጥፋት ማየት እንችላለን። በረጅም የወንጀል ዘመናት ዓለም ያስተናገደችው የሰው ስቃይ መዝገብ ጥላሸት መስሎአል። ሲያስቡት ልብ ያሳምማል፤ አእምሮን ወደ መሳት ያደርሳል። የሰማይን ስልጣን (ትዕዛዝ) እምቢ ማለት አሰቃቂ ውጤትን አምጥቷል። ካለፈው የባሰ የጠቆረ ክስተት በወደፊቱ ራዕይ ተቀምጧል። ያለፈው ታሪክ መዝገብ፣ የረብሻ፣ የጥልና የአብዮቶች ግርግር “ተዋጎች በጦርነት ሲፋጁ በደምም የተለቀለቀ ልብስ” [ኢሳያስ 9÷5] ሁሉ፤ የሰብአዊውን ፍጡር የሚገነፍል ፍላጎትና የሰይጣንን የሚፋጅ ቁጣ የሚከላከለው የእግዚአብሔር መንፈስ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአተኞች ሲወሰድ፣ ከሚኖረው ጋር ሲወዳደሩ እስካሁን የሆኑት ምንድን ናቸው? ከዚያን ጊዜ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ ዓለም የሰይጣንን አስተዳደር ውጤት ይመለከታል።GCAmh 30.1

    ሆኖም በየሩሳሌም ጥፋት እንደሆነው ሁሉ በዚያን ቀንም እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ይታደጋቸዋል። “ለሕይወት የተጻፈ ሁሉ”/በሕያዋን መካከል ተፅፎ የሚገኝ ሁሉ (everyone that shall be found written among the living)” [ኢሳ 4÷3] ይድናል። ታማኞቹን ወደርሱ ይሰበስብ ዘንድ ዳግም እንደሚመጣ ክርስቶስ ተናግሯል፦ “በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል። መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምጽ ጋር ይልካቸዋል ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።” [ማቴ 24÷30፣31]። ወንጌሉንም አንቀበልም ያሉ ከአፉ በሚወጣው መንፈስ ያልቃሉ፤ በመገለጡም ብርሐን ይጠፋሉ [2ኛ ተሰሎ 2÷8]። እንደ ጥንትዋ እሥራኤል ሁሉ ኃጥአን ጥፋትን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ በበደላቸውም ይወድቃሉ። ከኃጢአተኝነት ሕይወት የተነሳ ከእግዚአብሔር መስማማት ውጪ ራሳቸውን አስቀምጠዋልና ተፈጥሮአቸው በክፋት እጅግ ስለዘቀጠ የክብሩ መገለጽ እንደሚያቃጥል እሳት ይሆንባቸዋል።GCAmh 30.2

    ክርስቶስ በተናገራቸው ቃላት የተላለፉትን ትምህርቶች ቸል ከማለት ይቆጠቡ ዘንድ ሰዎች ይጠንቀቁ። ማምለጫቸውን ያዘጋጁ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን ስለ የሩሳሌም ጥፋት እንዳስጠነቀቀ፣ ስለሚመጣው ጥፋት ምልክት እንደሰጠ ሁሉ፣ ስለመጨረሻው ጥፋትም ዓለምን አስጠንቅቋል። ከሚመጣው ቁጣ ሁሉም ያመልጡ ዘንድ የመቃረቡን ምልክቶች ነግሮአቸዋል። የሱስ እንዲህ ይላል፦ “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድርም ላይ የአሕዛብ ጭንቀት።” [ሉቃ 21÷25፣ ማቴ 24÷29፣ ማር 13÷24-26፣ ራዕይ 6÷12-17]። መምጣቱትን የሚያውጁትን እነዚህን ምልክቶች የሚያስተውሉ ሁሉ “በደጅ እንደቀረበ” ያውቃሉ [ማቴ 24÷33]፤ “አሁንም ትጉ” [ማር 13÷35] ይላሉ የእርሱ የምክር ቃላት። ማስጠንቀቂያውን የሚሰሙ ሁሉ ያ ቀን በድንገት ይይዛቸው ዘንድ በጨለማ ውስጥ አይተዉም። አጥብቀው ለማይጠብቁት ግን ያ ቀን “የጌታ ቀን ሌባ እንደሚመጣ” በድንገት ይይዛቸዋል [1ኛ ተሰሎ 5÷2-5]።GCAmh 30.3

    የሩሳሌምን በተመለከተ መሲሁ የተናገረውን ማስጠንቀቂያ ለመቀበል አይሁዳውያኑ ከነበራቸው ዝግጁነት ጋር ሲነጻጸር፣ የአሁኑን ዘመን መልእክት ዋጋ ይሰጠው ዘንድ ዓለም ከድሮው የተሻለ ፍላጎት አይታይበትም። ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ለከኃዲያን የእግዚአብሔር ቀን በድንገት ይመጣባቸዋል። ሕይወት በእለት ተእለት በተመሳሳይ ድግግሞሹ ሲቀጥል ሳለ፤ ሰዎች በተድላ፣ በንግድ ሥራ፣ በህገ-ወጥ ዝውውር፣ ገንዘብ በመሰብሰብ ተጠምደው ሳለ፣ የኃይማኖት መሪዎች የዓለምን እድገትና የእውቀት ምጥቀት ሲያጋንኑ፤ ሕዝቡም በሐሰት ዋስትና ሲነሆልል ሳለ፤ በጥንቃቄ ወዳልጠበቀው ቤት ሌባ በውድቅት ገብቶ እንዲሰርቅ እንዲሁ ጥፋት በዋዘኞችና በከሃዲዎች ላይ በድንገት ይወርዳል፤ “አያመልጡምም።” [1ኛ ተሰሎ 5÷2-5]።GCAmh 31.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents