Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፫—ክህደት - የመንፈሳዊ ጽልመት ዘመን

    ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤው ለጳጳሳዊ ኃይል መመስረት ምክንያት ስለሚሆነው ታላቅ ክህደት ተንብዮ ነበር። “ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የኃጢአት ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ አይደርስምና። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ” የክርስቶስ ቀን እንደማይመጣ ተናግሯል። በተጨማሪም “የአመጽ ምስጢር አሁን ይሰራልና” [2ኛ ተሰሎ 2÷3፣4፣7] በማለት ሐዋርያው ወንድሞቹን አስጠንቅቋል። በዚያ ቀደምት ጊዜ እንኳ ጳጳሳዊው ሥርዓት ይጠነሰስ ዘንድ መንገድ የሚያመቻቹ ስህተቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየተሳቡ ሲገቡ ተመልክቶ ነበር።GCAmh 39.1

    ጥቂት በጥቂት፣ መጀመሪያ በስውርና በዝምታ፣ ከዚያም ጉልበት ሲያገኝና የሰዎችን አእምሮ መቆጣጠር ሲችል በገሃድ፣ የኃጢአት ምስጢር፣ የማታለልና የስድብ ሥራውን ወደ ፊት ገፋበት። ለማስተዋል ከባድ በሆነ አኳኋን የዓረማዊያን ልማድ ወደ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን መግባት ቻለ። በጣዖት አምልኮ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በደረሰባት ከባድ ስደት ምክንያት የመቻቻልና የመመሳሰል መንፈስ ለተወሰነ ጊዜ ተገትቶ ነበር። ስደት ሲቆምና ክርስትና ወደ ነገሥታት ሰገነቶችና ቤተ-መንግሥታት ሲገባ ግን የክርስቶስንና የሐዋርያቱን ትሁት የሆነ ተራ ሕይወት ወደ ጎን ገፍትራ፣ በጣዖት አምላኪ ካህናትና ገዢዎች ኩራትና አንጸባራቂ ታይታ ተካችው። በእግዚአብሔር መጠይቆች(መስፈርቶች) ፈንታም የሰውን ጽንሰ ሃሳብና ወግ ተካች። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የቆስጠንጢኖስ ወደ የይስሙላ ክርስትና መለወጥ ታላቅ ፈንጠዝያን በመቀስቀስ፣ ዓለም ከነዓለማዊነቱ አስመሳይ የጽድቅ ካባ ደርቦ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰተት ብሎ ገባ። አሁን የብልሽት ሥራ በፍጥነት ይስፋፋ ጀመር። ጣዖት አምላኪነት የጠፋች መስላ፣ አሸናፊ ሆነች። መንፈስዋ ቤተ ክርስቲያንን በቁጥጥርዋ ስር አደረገ። አስተምህሮዎችዋ፣ ክብረ በዓላቶችዋ፣ እንዲሁም መላምቶችዋ (አጉል አምልኮዎችዋ) ከክርስቶስ ተከታዮች አምልኮና እምነት ጋር ተዋሃዱ።GCAmh 39.2

    በጣዖት አምልኮ እና በክርስትና መካከል የተደረገው የአስታራቂ ሃሳብ ተግባራዊነት (ድርድር) አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት፣ ተቃዋሚውና ራሱን ከፈጣሪ በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርገው “የኃጢአት ሰው” እንዲነሳ ምክንያት ሆነ። ያ ግዙፉ ሐሰተኛ የኃይማኖት ሥርዓት፣ የሰይጣን ኃይል ድንቅ ጥበብ ውጤት ነው - ምድርን እንደ ፈቃዱ ይመራት ዘንድ ራሱን መንበረ መንግሥት ላይ ለማስቀመጥ ያደረገው ጥረቱ መታሰቢያ ኃውልት።GCAmh 39.3

    በአንድ ወቅት ሰይጣን ከክርስቶስ ጋር ለመደራደር ጥረት አድርጎ ነበር። በምድረ በዳ ሊፈትነው ወደ እግዚአብሔር ልጅ በመጣ ጊዜ የዓለምን መንግሥታት፣ ክብራቸውንም ካሳየው በኋላ ለጨለማ ልዑል የበላይነት እውቅና ቢሰጥ ሁሉንም ሊሰጠው እንደሚችል ነግሮት ነበር። ክርስቶስም ልኩን የማያውቀውን ፈታኝ ከገሰጸው በኋላ አባረረው። እነዚህን ተመሳሳይ ፈተናዎች ለሰዎች ሲያቀርብ ግን ሰይጣን የተሻለ ውጤታማ ነው። ዓለማዊ ብልጽግናንና ክብርን ለማግኘት ስትል ቤተ ክርስቲያን የዓለም ታላላቅ ሰዎችን አዎንታና እርዳታ ወደ መሻት ተመራች፤ በዚህም ተግባርዋ ክርስቶስን አሻፈረኝ ብላ፣ የዲያቢሎስ ወኪል ለሆነው ለሮማ ጳጳስ ታማኝነትዋን ትሰጥ ዘንድ ተግባባች።GCAmh 39.4

    ሊቀ-ጳጳሱ በአካል (በገሃድ) የሚታይ የዓለም-አቀፋዊትዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሆነና በምድር ዳርቻ ሁሉ ባሉ ጳጳሳትና ፖስተሮች ላይ ጠቅላይ ስልጣን እንዳለው የሚናገረው ቀኖናቸው፣ ከግንባርቀደምየሮማዊነት አስተምህሮዎች ውስጥ አንዱ ነው። ይባስ ብሎም ሊቀ-ጳጳሱ የአምላክ የሆኑትን እነዚያኑ ስያሜዎች ለራሱ ወስዷል። ራሱን “ጌታ እግዚአብሔር ሊቀ-ጳጳስ/Lord God the Pope” አድርጓል፣ ስህተት መሥራት የማይቻለው የመሆን ሥፍራ ይዟል፤ የሰው ዘር ሁሉ ክብር እንዲሰጡት ይጠይቃል። ስለዚህ በምድረ በዳው ፈተና ሰይጣን ያቀረበውን መጠይቅ ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ በሮም ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት እያቀረበው ነው፤ አያሌ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ክብር ሊሰጡት የተዘጋጁ ሆነዋል።GCAmh 40.1

    እግዚአብሔርን የሚፈሩና ክብርም የሚሰጡት ግን ሰማይን ተገዳዳሪ የሆኑትን እነዚህን አስተሳሰቦች፣ የተጠበበው አታላዩ ጠላት ላቀረባቸው ማባበያዎች ክርስቶስ በመለሰበት አኳኋን በመገናኘት እንዲህ ይመልሳሉ፦ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ።” [ሉቃ 4÷8]። የቤተ ክርስቲያኑ ራስ ይሆን ዘንድ አንድን ሰው እንደሾመ እግዚአብሔር በቃሉ የሰጠው ምንም ዓይነት ፍንጭ የለም። የጳጳሳዊው ጠቅላይ ስልጣን አስተምህሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው። በስልጣን ንጥቂያ ካልሆነ በስተቀር ሊቀ-ጳጳሱ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የገዥነት ኃይል ሊኖረው አይችልም።GCAmh 40.2

    ሮማውያኑ፣ ፕሮቴስታንቶችን በኑፋቄ ወንጀል በመፈረጅ፣ እንዲሁም ከእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ሆን ብለው ተገንጥለዋል በማለት የሚያቀርቡባቸውን ውንጀላ አጠናክረው ቀጥለውበታል። ይህ ክስ ተግባራዊ መሆን ያለበት ግን በእነርሱ በራሳቸው ላይ ነው። የክርስቶስን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው፣ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ኃይማኖት” [ይሁዳ 3] ከተባለለት እምነት የተለዩት እነርሱ ናቸውና።GCAmh 40.3

    ማታለያዎቹን ያውቁ ዘንድ፣ ብሎም ሃይሉን ይቋቋሙ ዘንድ የሚያስችላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ሰይጣን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። የዓለም መድሃኒት እንኳ ጥቃቱን የተቋቋመው በቃሉ ነበር። “ተጽፏል” በማለት እያንዳንዱን ጥቃት በዘላለማዊው እውነት ጋሻ ይመክት ነበር። ጠላት ለሚያቀርበው እያንዳንዱ ሃሳብ ተቃውሞውን የሚመልሰው በቃሉ ጥበብ ኃይል ነበር። በሰዎች ላይ ያለውን ተጽእኖና የመቆጣጠር ኃይል ጠብቆ ለማቆየት፣ ብሎም የነጣቂውን የጳጳሳዊውን ስልጣን ለማደላደል ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ገልቱ ሆነው እንዲቀሩ የግድ ማድረግ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ውስን ሰብአዊ ፍጡራንንም በትክክለኛ ስፍራቸው ያስቀምጣቸዋል። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የተቀደሱ እውነቶች መደበቅና መጨቆን ይኖርባቸዋል። ይህ አስተሳሰብ በሮማ ቤተ ክርስቲያን ተተግብሯል። ለብዙ መቶ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ተከልክሎ ኖሯል። ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ፣ በቤታቸውም እንዳያስቀምጡ ተከልክለው ሳለ፣ መርህ-አልባዎቹ ካህናትና ባለስልጣናት የራሳቸውን አስመሳይ ሃሳቦች እንዲደግፍ አድርገው ይተረጉሙት ነበር። በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያንንና አገርን የመግዛት ስልጣን ተችሮት፣ ሊቀ-ጳጳሱ የእግዚአብሔር ወኪል በምድር ተደርጎ በሁሉም የዓለም ሕዝብ ማለት ይቻላል፣ እውቅና ተሰጠው።GCAmh 40.4

    ስህተት ጠቋሚው ተወግዶአልና ሰይጣን እንዳሻው ሥራውን ይሰራ ነበር። ጳጳሳዊ ስርዓቱ፣ “ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ” እንደሚያስብ [ዳን 7÷25] ትንቢት አስቀድሞ ተናግሯል። ይህንን ተግባር ለመሞከር አልዘገየም። ከአሕዛብነት ለተለወጡት ሰዎች የቀሩባቸውን ጣኦታትን በሌላ ለመተካት፣ ብሎም የይስሙላ ክርስትናን እንዲቀበሉ ለመገፋፋት፣ ለተቀረጹ ምስሎችና ለታሪካዊ ቁሶች ክብር መስጠት ቀስ በቀስ ወደ ክርስትናው አምልኮ እንዲገባ ተደረገ። የአጠቃላይ ጉባኤው አዋጅ (የኒስ ሁለተኛው አዋጅ 787 ዓ.ም) በመጨረሻ ይህንን የጣዖት አምልኮ ሥርዓት መሰረተ። ይህንን የረከሰ ተግባር ለማጠናቀቅም የስዕልና ምሳሌ አምልኮ የሚከለክለውን ሁለተኛውን ትዕዛዝ ከእግዚአብሔር ሕግ በማስወገድ፣ የትእዛዛቱ ቁጥር ግን እንዳይጎድል አስረኛውን ትዕዛዝ ለሁለት ለመክፈል ሮም የድፍረት ሃሳብ ወጠነች።GCAmh 41.1

    ከጣዖት አምልኮ ጋር የመደራደር መንፈስ የሰማይ ስልጣን ወደ ጎን ይገፈተር ዘንድ ተጨማሪ በር ከፈተ። ያልተቀደሱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በመጠቀም፣ ሰይጣን፣ በአራተኛው ትዕዛዝም እጁን በማስገባት፣ እግዚአብሔር የባረከውና የቀደሰው [ዘፍ 2÷2፣3] የጥንቱ ሰንበት እንዲቀር አድርጎ፣ በምትኩ፣ “ክቡሩ የፀሐይ ቀን” በመባል በአሕዛብ የሚከበረውን በዓል ከፍ ከፍ ማድረግ ሞከረ። ይህ ለውጥ መጀመሪያ በገሃድ የተሞከረ አልነበረም። በመጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት ትክክለኛው ሰንበት በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ይጠበቅ ነበር። ለእግዚአብሔር ክብር ቀናተኛ ነበሩ፤ ሕጉም የማይለወጥ እንደሆነ በማመን የመመሪያዎቹን ቅድስና በጥንቃቄ ይጠብቁ ነበር። ነገር ግን በታላቅ የማታለል ጥበብ በተወካዮቹ አማካኝነት ሰይጣን የራሱን ዓላማ ለማስፈጸም ሰራ። የሰዎች ትኩረት ወደ እሁድ ይሳብ ዘንድ ክርስቶስ ከሞት የተነሳው በዚህ ቀን መሆኑን በማውሳት ለጌታ ክብር ሲባል ይህ ቀን በክብረ በዓልነት እንዲከበር ተደረገ። በእሁድ ቀን አምልኮ መካሄድ የጀመረ ቢሆንም እንደ የመዝናኛ ቀን ይቆጠር ነበር፣ ትክክለኛው ሰንበትም በቅድስና መከበሩ ቀጥሎ ነበር።GCAmh 41.2

    ለነደፈው እቅድ የስኬት መንገድ ያመቻች ዘንድ፣ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሰንበትን ማክበር ሸክም እስኪሆን ድረስ የማያፈናፍን የአከባበር ሥነ-ሥርዓት እንዲጭኑበት ሰይጣን አይሁዳውያንን መርቷቸው ነበር። አሁን [የሰንበት ትክክለኛ አከባበር] የተሳሳተ ብርሐን ሆኖ እንዲታይ ያደረገበትን ሁኔታ ለራሱ ጥቅም በማዋል፣ ሰንበት የአይሁዳውያን ተቋም እንደሆነ በማሳየት ንቀቱን አንጸባረቀበት። ክርስቲያኖች እሁድን የደስታ ክብረ በዓል አድርገው ማክበራቸውን ቀጥለው ሳለ ለአይሁዳውያን ያላቸውን ጥላቻ ያሳዩ ዘንድ ሰንበትን [ቅዳሜን] የጾም የሃዘንና የጽልመት ቀን አድርገው እንዲያዩት ዲያብሎስ መራቸው።GCAmh 41.3

    በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ እሁድ በመላው የሮማ ግዛት ሕዝባዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር የሚያዝ አዋጅ አወጣ። [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 1ን ይመልከቱ]። የፀሐይ ቀን በጣዖት አምላኪ ግዛቶቹ ሲመለክ በክርስቲያኖቹ ዘንድ ደግሞ ይከበር ነበር። ቆስጠንጢኖስ ተቃራኒ ፍላጎት የሚያራምዱትን አሕዛባዊነትንና ክርስትናን አንድ የማድረግ አላማ ነበረው። ይህንን እንዲያደርግ የገፋፉትም የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ነበሩ፤ በአሕዛብና በክርስቲያኖች ዘንድ የሚከበረው ቀን አንድ ከሆነ፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ በስም ብቻም ቢሆን ወደ ክርስትና ይለወጣሉ፣ በዚህም የቤተ ክርስቲያን ኃይልና ክብር ይጨምራል ብለው የተገነዘቡ፣ ምኞታቸውንና የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የሚኳትኑ የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ይህንን አደረጉ። እሁድ የተወሰነ ቅድስና እንዳለው ይቀበሉ ዘንድ ክርስቲያኖች ቀስ በቀስ እየተመሩ የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ትክክለኛው ሰንበት[ቅዳሜ] የተቀደሰው የጌታ ቀን እንደሆነ አምነው ለአራተኛው ሕግ በመታዘዝ ይጠብቁት ነበር።GCAmh 41.4

    ቀንደኛው አታላይ ሥራውን ገና አላጠናቀቀም ነበር። የክርስቲያኑን ዓለም በሰንደቅ አላማው ስር ለማሰለፍና የክርስቶስ ወኪል ነኝ በሚለው፣ ሆኖም የራሱ [የዲያብሎስ] ወኪል በሆነው በኩሩው ሊቀ-ጳጳስ አማካኝነት ሃይሉን ሊተገብር ቆርጦ ተነሳ። በከፊል በተለወጡ ጣዖት አምላኪያን፣ በምኞት በሰከሩ የኃይማኖት ባለስልጣናትና ዓለምን በሚያፈቅሩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች አማካኝነትም አላማውን ማሳካት ቻለ። በዓለም ዙሪያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን የሚወክሉ ልኡካን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰፊ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። በእያንዳንዱ ስብሰባ እግዚአብሔር ያቋቋመው ሰንበት ወደታች በትንሹ ዝቅ ሲደረግ እሁድ ደግሞ በዚያው ልክ ወደ ላይ ከፍ ይደረግ ነበር። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ሰንበት የአይሁድነት ታሪክ አካል እንደሆነ ተቆጥሮ፣ የሚያከብሩትም የተረገሙ እንደሆኑ ሲታወጅ፣ በመጨረሻ የጣዖት አምላኪያን ክብረ በዓል የነበረው [እሁድ] እንደ መለኮታዊ ተቋም ተደርጎ ይከበር ጀመር።GCAmh 42.1

    ታላቁ ከሃዲ “አምላክ ከተባለው ሁሉ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ” [2ኛ ተሰሎ 2÷4] ራሱን ከፍ ከፍ ማድረግ ተሳክቶለታል። የሰውን ዘር ሁሉ ወደ እውነተኛውና ሕያው አምላክ በማያወላዳ ሁኔታ የሚጠቁመውን የመለኮታዊውን ሕግ ብቸኛ መመሪያ ይቀይር ዘንድ ደፍሯል። አራተኛው ትዕዛዝ እግዚአብሔር የሰማያትና የምድር ፈጣሪ እንደሆነ ስለሚገልጽ፣ ጌታ ከሌሎች ሐሰተኛ አማልክት የሚለይበት ነው። ለሰው ዘር ማረፊያ ሆኖ ሰባተኛው ቀን የተቀደሰው እንደ የፍጥረት ሥራ መታሰቢያነት ነበር። የፍጥረት ምንጭ የሆነው ሕያው አምላክ ክብርና አምልኮ የሚገባው እንደሆነ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ለዘላለም እንዲቀመጥ ታቅዶ የተሰጠ ነው። ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት እንዲተውና ለሕጉም መታዘዛቸውን እንዲያቆሙ ሰይጣን ይጥራል። ስለዚህ እግዚአብሔር ፈጣሪ እንደሆነ በሚያመለክተው ትዕዛዝ ላይ ሃይሉን የበለጠ አጠናክሮ የተቃውሞ ሥራ ይሰራል።GCAmh 42.2

    ክርስቶስ በእሁድ ቀን ከሞት መነሳቱ የክርስቲያኖች ሰንበት እንዲሆን አድርጎታል በማለት ፕሮቴስታንቶች አሁን ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ግን የለውም። እንደዚህ ዓይነት ክብር በክርስቶስም ሆነ በሐዋርያቱ ለቀኑ [ለእሁድ] አልተሰጠውም። እንደ የክርስቲያን ተቋም እሁድ መከበር የጀመረው በጳውሎስ ዘመን ሳይቀር ሥራውን ጀምሮ በነበረው “የህግ አልባነት መስጢር/the mystery of lawlessness]” [2ኛ ተሰሎ 2÷7, Revised version] አስጀማሪነት ነው። የጳጳሳዊነት ልጅ የሆነውን [ይህንን እሁድ] ክርስቶስ የተቀበለው የትና መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የማያጸድቀውን ለውጥ መተግበር ምን ዓይነት ትክክለኛና አሳማኝ ምክንያት ሊቀርብለት ይችላል?GCAmh 42.3

    በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጳጳሳዊው ሥርዓት በጠንካራ መሰረት ላይ ቆመ። መቀመጫውን የንጉሠ ነገሥታዊቷ ከተማ ተድርጎ የሮም ጳጳስ የጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሆነ ታወጀ። ጣዖት አምላኪነት ለጳጳሳዊ ሥርዓት ቦታ ለቀቀ። ዘንዶው “ሃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ስልጣን” ለአውሬው ሰጠው [ራዕ 13÷2፤ በመግለጫ ስር ማስታወሻ 2ን ይመልከቱ]። በዚህ ጊዜ በዳንኤልና በራዕይ የተነገሩት የ1260 የጳጳሳዊው ሥርዓት የጭቆና ዓመታት ጀመሩ። [ዳን 7÷25፤ ራዕይ 13÷5-7]። ታማኝነታቸውን ሰውተው የጳጳሳዊ አምልኮና ሥርዓት መቀበልን አለበለዚያ በወህኒ ቤት መማቀቅን፤ እጅና እግር ተወጥሮ ታስሮ (ግራ እጅና እግር በአንድ በኩል ቀኝ እጅና እግር በሌላ በኩል ታስሮ በመመንጨቅ) ተሰቃይቶ መሞትን፤ መቃጠልንና አንገትን በፋስ መቀላትን ይመርጡ ዘንድ ክርስቲያኖች ተገደዱ። አሁን የየሱስ ቃላት ተፈጸሙ፦ “ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ። በሁሉም ስለስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።” [ሉቃ 21÷16፣17]። ከምንጊዜውም በላይ በበለጠ ቁጣ አማኞችን ማሳደድ ተጀመረ፤ ዓለም ሰፊ የጦርነት ቀጠና ሆነች። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በመገለልና ከእይታ ውጪ በመሆን ውስጥ መጠጊያ(ደህንነት) አግኝታ ለብዙ መቶ ዓመታት ኖረች። ስለዚህም ነብዩ ይላል፦ “ሴቲቱም ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሃ ሸሸች።” [ራዕይ 12÷6]።GCAmh 42.4

    የሮም ቤተ ክርስቲያን ስልጣን ላይ መውጣት የጨለማው ዘመን መባቻ ነበር። ኃይልዋ እየጨመረ ሲሄድ ጽልመቱም ጥልቅ እየሆነ ሄደ። እምነት፣ ትክክለኛ መሰረት ከሆነው ከክርስቶስ ወደ ሮማው ሊቀ-ጳጳስ ተላለፈ። ለኃጢአት ይቅርታና ለዘላለማዊ ድነት በእግዚአብሔር ልጅ በማመን ፈንታ ሰዎች ወደ ሊቀ-ጳጳሱና እርሱ ወደ ሾማቸው ቀሳውስትና የኃይማኖት መሪዎች ተመለከቱ። ምድራዊ አማላጃቸው ሊቀ-ጳጳሱ እንደሆነና በእርሱ በኩል ካልሆነ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንደማይቻል ተማሩ። በተጨማሪም፣ ለእነርሱ፣ በእግዚአብሔር ቦታ የተቀመጠ ከመሆኑ የተነሳ በፍጹም መታዘዝ እንዲከተሉት ተማሩ። ከእርሱ መስፈርቶች ዝንፍ ማለት በአመጸኞች አካልና ሕይወት ላይ ከፍተኛውን አሰቃቂ ቅጣት ለማስከተል በቂ ምክንያት ነበር። በመሆኑም የሰዎች አእምሮ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ፣ ስህተት መፈጸም ወደሚቀናቸው፣ ጥፋት ወደሚሰሩና ወደ ጨካኝ ሰዎች፣ እንዲያውም ሃይሉን በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት ተግባራዊ ወደሚያደርገው ወደ ጨለማው ልዑል እንዲዞር ተደረገ። ኃጢአት በማሳሳቻ የቅድስና ካባ ተደበቀ። መጽሐፍ ቅዱስ ሲጨቆንና ሰው የሁሉ በላይ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ሲቆጥር፣ ልናይ የምንችለው አጭበርባሪነትን አታላይነትንና የሚያዋርድ ኃጢአትን ብቻ ነው። የሰው ሕግጋትና ባህሎች ከፍ ከፍ ሲደረጉ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ወደ ጎን የመገፍተር የምንጊዜም ውጤት የሆነው ብልሹነት ተንጸባረቀ።GCAmh 43.1

    እነዚያ ዘመናት ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በጣም አደገኛ ነበሩ። የክርስትናን ደረጃ የጠበቁ አማኞች እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። እውነት ያለ ምስክሮች የቀረ ባይሆንም አንዳንድ ጊዜ ስህተትና መላምት ሙሉ በሙሉ የሚያሸንፍ፣ እውነተኛ ኃይማኖትም ከምድር የሚጠፋ ይመስል ነበር። ወንጌሉ ከእይታ ውጭ ሆነ፣ ኃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ተበራከቱ፤ ዝንፍ በማያስብሉ ሐይማኖታዊ ጭነቶች ሕዝቡ ጎበጠ።GCAmh 43.2

    ሊቀ-ጳጳሱን እንደ አማላጅ እንዲያዩት ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸው [መልካም]ሥራ ለኃጢአት ስርየት እንደሚሆን እንዲያምኑ ጭምር ተማሩ። ረጅም ሐይማኖታዊ ጉዞዎች፣ የንስሐ መግቢያ ቅጣቶች፣ የጥንታዊ ቅርሶች አምልኮ፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ቅዱስ ስፍራዎችንና መሰውያዎችን ማስገንባት፣ አያሌ መጠን ያለው ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን መክፈል፣ እነዚህንና የመሳሰሉትን በርካታ ተግባራት ማከናወን የእግዚአብሔርን ቁጣ ከማብረድ ወይም አዎንታውን ከማግኘት ጋር እንዲያያዙ ተደረገ። እግዚአብሔር ሰው ይመስል፣ በጥቃቅን ነገሮች የሚበሳጭ፣ በስጦታና ንስሐ ለመግባት በሚደረግ አካላዊ ልፋት የሚለዝብ አይነት እንደሆነ ተደርጎ፣ እነዚህን ሁሉ ተግባራት ይፈጸሙ ነበር።GCAmh 43.3

    ብልሹነት መስፋፋቱ፣ በሮማ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል ጭምር መብዛቱ፣ የቀጠለ ቢሆንም እንኳ ተጽእኖዋ ግን በቀጣይነት የሚጨምር ይመስል ነበር። በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መደምደሚያ ገደማ በቤተ ክርስቲያንዋ የመጀመሪያዎቹ አመታት በሮም ጳጳሳት ላይ የነበረው ተመሳሳይ መንፈሳዊ ኃይል አሁንም በእነርሱ ላይ እንዳለ ተናገሩ። ለዚህም አባባል መሰረት ለመጣል የስልጣን መልክ ያገኝ ዘንድ የተወሰኑ ነገሮች መተግበር ነበረባቸው፣ ይህም በሐሰት አባት የተቀነባበረ ነበር። የጥንት ጽሁፎች እንደሆኑ እንዲመስሉ ተደርገው መጻሕፍት በመነኮሳት ተጻፉ። የሊቀ-ጳጳሱን ዓለምአቀፋዊ ተቀናቃኝ የሌለው የስልጣን የበላይነት የሚያረጋግጡ፣ ከጥንት ጀምሮ የተደነገጉ፣ ከአሁን በፊት ተሰምተው የማያውቁ፣ በጥንታዊ ጉባኤዎች የተሰጡ ናቸው የተባሉ አዋጆች ተገኙ ይባል ጀመር። እውነትን አሻፈረኝ ያለችው ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ማታለያዎች ተስገብግባ ተቀበለቻቸው።GCAmh 44.1

    የሐሰት አስተምህሮ ትርኪ ምርኪ ሥራውን ሲያደናቅፍ፣ ትክክለኛውን መሰረት የሚገነቡ ጥቂት ታማኝ አናጺዎች [1ኛ ቆሮ 3÷10፣11] ግራ ተጋቡ፤ ተስተጓጎሉም። በነህምያ ዘመን የየሩሳሌምን ግንብ ሲገነቡ እንደነበሩት ግንበኞች፣ አንዳንዶች “የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፣ ፍርሥራሹም ብዙ ነው ቅጥሩንም እንሰራ ዘንድ አንችልም” ለማለት ተቃርበው ነበር [ነህም 4÷10]። ከማያባራ ስደት ጋር በሚያደርጉት ትንቅንቅ፣ ማጭበርበርና ኃጢአት እንዲሁም እድገታቸውን ለማደናቀፍ ሰይጣን ማዘጋጀት በሚችለው መሳሪያ ሁሉ ዝለው፣ ታማኝ ገንቢዎች የነበሩ አንዳንዶች ተስፋ ቆረጡ። ለንብረታቸውና ለሕይወታቸው ሰላምና ደህንነት ሲሉ ከእውነተኛው መሰረት ፈቀቅ አሉ። ሌሎች ደግሞ የጠላቶቻቸው ተቃውሞ ሳይበግራቸው፣ ያለ ፍርሃት “አትፍሩአቸው ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ” [ነህም 4÷14] በማለት እያንዳንዳቸው ሰይፋቸውን በጎናቸው ታጥቀው ሥራቸውን ቀጠሉ [ኤፌ 6÷17]።GCAmh 44.2

    ይህን እውነት በመቃወም የሚንጸባረቀው የጥላቻና የተቃርኖ መንፈስ የእግዚአብሔርን ጠላቶች በየዘመናቱ ሲያነሳሳ ኖሯል፤ ተመሳሳይ ንቃትና ታማኝነትም ከባርያዎቹ ሲጠበቅ ቆይቷል። ክርስቶስ ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የተናገራቸው ቃላት ለተከታዮቹ እስከ ዘመን ፍጻሜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፦ “ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።” [ማር 13÷37]።GCAmh 44.3

    ጨለማው የበለጠ ጥቅጥቅ እያለ የሚሄድ መሰለ። ምስልን (ሀውልትን) ማምለክ የበለጠ እየተለመደ መጣ። በምስሎች ፊት ሻማዎች ተለኩሰው ወደ እነርሱም ፀሎት ይደረግ ነበር። እጅግ የማይመስሉ፣ አጉልና ከንቱ ልማዶች ተስፋፉ። ምክንያት/አመክንዮ የማሳመን ሃይሏን ያጣች እስኪመስል ድረስ የሰዎች አእምሮ ሙሉ ለሙሉ በከንቱ አስተሳሰቦች ቁጥጥር ስር ሆኖ ነበር። ቀሳውስትና ጳጳሳት ራሳቸው ቅንጦት ወዳጅ፣ ፍትወታዊና ብልሹ ከሆኑ፣ ለምሪት ወደ እነርሱ የሚመለከተው ሕዝብ በድንቁርናና በክፋት ሥራ ውስጥ መዘፈቁ የሚጠበቅ ነው።GCAmh 44.4

    በአሥራ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግሪጎሪ 7ኛ የሮማዊቷን ቤተ ክርስቲያን ፍጹምነት ሲያውጅ፣ ሌላ ተጨማሪ የጳጳሳዊ ስልጣን ሚና ሥራ ላይ ዋለ። ካቀረባቸው ሃሳቦች መካከል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው መሰረት፣ ቤተ ክርስቲያንዋ ከአሁን በፊት ስህተት ሰርታ አታውቅም፣ ከአሁን በኋላም ፈጽማ ጥፋት አትሰራም የሚለው ይገኝበታል። ለንግግሩ ማረጋገጫነት ግን መጽሐፍ ቅዱስ በማስረጃነት አልተጠቀሰም ነበር። ከዚያም ኩሩው ሊቀ-ጳጳስ ነገሥታትን ከስልጣን የማውረድ መብት እንዳለው፣ እርሱ የወሰነውን ፍርድ ሊቀለብስ የሚችል ማንም እንደሌለ፣ እርሱ ግን የማንንም ውሳኔ የመለወጥ ስልጣን እንዳለው አወጀ።GCAmh 45.1

    የዚህ መሳሳት-የማይችል ስለመሆኑ የሚከራከርን ሊቀ-ጳጳስ አምባገነናዊ ባህርይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው አስገራሚ ትዕይንት የጀርመኑ ንጉሥ ሄንሪ 4ኛ ላይ የፈጸመው ድርጊት ነበር። የሊቀ-ጳጳሱን ስልጣን አያከብርም ተብሎ ስለታሰበ ንጉሡ ከቤተ ክርስቲያን አባልነቱ ተሰርዞ ከስልጣንም እንዲወርድ ታወጀበት። በጳጳዊው ትዕዛዝ እንዲያምጹበት የተበረታቱት የራሱ መኳንንት ሲተውትና ሲያስጠነቅቁት እጅግ ደንግጦ ሄንሪ ከሮም ጋር ሰላም መፍጠር እንዳለበት ተሰማው። በሊቀ-ጳጳሱ ፊት ራሱን ያዋርድ ዘንድ፣ በክረምቱ አጋማሽ የአልፕስን [የተራራ ሰንሰለት] አቋርጦ ከሚስቱና ከታማኝ አገልጋዩ ጋር ወደ ሮም ተጓዘ። ግሪጎሪ ያረፈበት ቤተ መንግሥት ሲደርስ ያለጠባቂዎቹ፣ ወጣ ወዳለ አዳራሸ ብቻውን ተወስዶ፣ በዚያ ከባድ ቀዝቃዛ ክረምት ያለ ራስ ጥምጣም፣ በባዶ እግሩና በምናምንቴ ስስ ልብስ ሆኖ፣ በሊቀ-ጳጳሱ ፊት ይቀርብ ዘንድ እንዲፈቀድለት የአዎንታ ቃሉን ይጠባበቅ ነበር። ሊቀ-ጳጳሱ ምሕረት ሊያደርግለት የተስማማው ሶስት ቀን ሙሉ ከጾመና ከተናዘዘ በኋላ ነበር። እንደዚያም ከሆነ በኋላ እንኳ ንጉሣዊውን ልብስ ለመልበስና የንጉሣዊነቱን ስልጣን ለመጠቀም የሊቀ-ጳጳሱን አዎንታ መጠበቅ ነበረበት። ግሪጎሪ በተቀዳጀው ድል እየፈነደቀ “የነገሥታትን ኩራት ማፍረስ” ሃላፊነቱ እንደሆነ በጉራ ተናገረ።GCAmh 45.2

    ይቅርታና ሰላም ያመጣ ዘንድ፣ ተቀባይነት ለማግኘት በልብ ደጃፍ ቆሞ እንዲከፈትለት በሚለምነው፣ ደቀ መዛሙርቱን “ከናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን” [ማቴ 20፤26] ብሎ ባስተማረው፣ በደጉና በየዋሁ ክርስቶስና በፈላጭ ቆራጭነትና በእብሪት በተኮፈሰው ጅንን ሊቀ-ጳጳስ መካከል ያለው ልዩነት እንዴት የሰፋ ነበር!GCAmh 45.3

    በቀጣዮቹ ምዕተ ዓመታትም ከሮም የሚወጡት የስህተት አስተምህሮዎች በቀጣይነት ሲጨምሩ ታይተዋል። ጳጳሳዊ ሥርዓት ከመመስረቱ በፊት እንኳ የከሃዲ ፈላስፋዎች ትምህርት የሰዎችን ትኩረት በመሳብ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽእኖ ማድረስ ጀምሮ ነበር። ተለውጠናል የሚሉ ብዙዎች አሁንም የጣዖት አምላኪነት ፍልስፍና እምነታቸውን እንደጨበጡ ነበሩ። እነርሱ ራሳቸው እነዚህን ፍልስፍናዎች ማጥናት ከመቀጠላቸው በተጨማሪ በአሕዛብ መካከል ያላቸውን ተሰሚነት ለማስፋፋት ሲሉ ሌሎቹንም ያስተምሩ ነበር። በመሆኑም አደገኛ ስህተቶች ወደ ክርስትናው እምነት እንዲገቡ ተደረገ። ከእነዚህ የስህተት ትምህርቶች ዋነኛው፣ የሰው ተፈጥሮአዊ ዘለዓለማዊነት (natural immortality) እና በሞት ጊዜም የማሰብ ችሎታው እንደማይወሰድ የሚያስተምረው ነው። ይህም አስተምህሮ ሮም ለጀመረችው ወደ ቅዱሳን ልመና የማቅረብና ድንግል ማርያምን የማክበር ሥርዓት ዋና የመሰረት ድንጋይ ሆኖ አገልግሏል። ቀደም ብሎ ወደ ጳጳሳዊ እምነት የተቀላቀለው፣ እስከ መጨረሻ ንስሐ የማይገቡ እነርሱ ለዘላለም እንደሚሰቃዩ የሚናገረው የኑፋቄ ትምህርትም ከዚህ የወጣ ነበር።GCAmh 45.4

    ይህም ሮም የሙታን ጊዜያዊ ማሰቃያ (purgatory) ብላ ለጠራችው፣ ፤ በቀላሉ የሚታለልን፣ ግምትን (መላምትን) ጨምሮ ምንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ የሆነውን ሕዝብ በፍርሃት ለማርበድበድ ለተጠቀመችበት፣ ለሌላ ተጨማሪ የጣዖት አምልኮ ፈጠራ መንገዱን አመቻቼ። በዚህ የኑፋቄ ትምህርትም ለዘላለማዊ ሞት የማያበቃ ኃጢአት የሰሩ ሰዎች ነፍሳት[ከሞቱ በኋላ]፣ ለፈጸሙት በደል ተገቢውን ቅጣት የሚቀበሉበት፣ ከጥፋት እድፋቸው ሲነጹም ወደ ሰማይ የሚገቡበት፣ ጊዜያዊ የማሰቃያ ሥፍራ እንዳለ ተረጋገጠ።GCAmh 46.1

    በደጋፊዎቿ ፍርሃትና ብልሹ ምግባር ሮም የበለጠ አትራፊ ትሆን ዘንድ አሁንም ሌላ ፈጠራ ያስፈልጋት ነበር። ይህም ኃጢአት ይቅርታ አስተምህሮ ስኬትን አገኘ። ምድራዊ ግዛቱን ለማስፋፋት፣ ጠላቶቹን ለመቅጣትና መንፈሳዊ የበላይነቱን ለመካድ የሚደፍሩትን ሁሉ ለማስወገድ ይቻለው ዘንድ፣ የጦር ሰራዊቱን ለመቀላቀል ለሚመዘገቡ ሁሉ ላለፈው፣ ለአሁኑና ወደፊት ለሚሰሩት ኃጢአት ሙሉ ይቅርታ እንደሚያገኙ፣ ለሚደርስባቸው ስቃይና ቅጣት ሁሉ ፍትሐት ተደርጎላቸው ነጻ እንደሚወጡ ቃል ተገባላቸው። ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን ገንዘብ በመክፈል ራሳቸውን ከኃጢአት፣ የሞቱ ጓደኞቻቸውን ደግሞ በማቆያ ሥፍራው ታጉረው ከሚሰቃዩበት የእሳት ነበልባል ማትረፍ እንደሚችሉ ተማሩ። በዚህ አኳኋን ሮም ካዝናዋን በገንዘብ በመሙላት፣ የሚተኛበት ሥፍራ እንኳ ያልነበረውን የጌታን አስመሳይ ወኪሎች የረከሰ ምግባር፣ ቅንጦትና ገናናነት ጠብቆ ለማቆየት ተጠቀመችበት።GCAmh 46.2

    በመጽሐፍ ቅዱስ የተደነገገው የጌታ ራት ሥነ ሥርዓት በጣዖት አምልኮ ቁርባን መስዋዕት አቅርቦት ተተክቶ ነበር። የጳጳሳዊ ሥርዓት ቀሳውስት በትርጉም የለሽ ድግምት እያጉተመተሙ ተራውን ዳቦና ወይን ወደ ትክክለኛው የክርስቶስ አካል(ሥጋ)ና ደም እንደሚቀይሩ ያስመስሉ ነበር። Cardinal Wiseman, the Real Presence of the Body and Blood of Our Lord Jesus Christ in the Blessed Eucharist, Proved from Scripture, lecture 8, sec 3, par. 26። እግዚአብሔርን በሚሳደብ ከልክ ያለፈ ድፍረት “የሁሉ ፈጣሪ የሆነውን፣ እግዚአብሔርን የመፍጠር” ኃይል እንዳላቸው በይፋ ተናገሩ። ይህንን አስከፊ፣ ሰማይ ዘላፊ ኑፋቄ እንደሚያምኑ በግልጽ እንዲናገሩ ክርስቲያኖች ለሞት በሚያደርስ ስቃይ ይገደዱ ነበር። ይህንን የተቃወሙ ብዙዎች የእሳት እራት ሆኑ።GCAmh 46.3

    በአሥራ ሶስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሁሉም የጳጳሳዊ መሳሪያዎች የሚበልጠው፣ እጅግ አሰቃቂ የሆነው ችሎት (the Inquisition) ተቋቋመ። የጨለማው ልዑል በጳጳሳዊ ስልጣን እርከን ውስጥ ካሉ መሪዎች ጋር ይሰራ ነበር። ምስጢራዊ ስብሰባቸውን ሲያካሂዱ፣ የእግዚአብሔር መልአክ በመካከላቸው ቆሞ በኃጢአት የተሞሉትን አዋጆቻቸውን፣ በፍጡር አይን ተገልጦ ለመታየት እጅግ ዘግናኝ የሆነውን የሥራቸውን ታሪክ፣ በአስፈሪው መዝገብ ላይ ሲጽፍ ሳለ፣ ሰይጣንና መላዕክቱ የክፉ ሰዎችን አእምሮ ይቆጣጠሩ ነበር። ። “ታላቋ ባቢሎን” “በየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ” [ራዕይ 17÷6] ነበር። አካላቸው የተቆራረጠው፣ በሚሊዮን የሚቆጠረው የሰማዕታት ግዝም፣ በዚያ ከሃዲ ኃይል ላይ የበቀል እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጮህ ነበር።GCAmh 46.4

    ጳጳሳዊው ስልጣን ዓለምን በማን አለብኝነት የሚያስተዳድር ጨቋኝ ገዥ ሆኖ ነበር። የዓለም ነገሥታትና ንጉሠ ነገሥታት ሁሉ ለሮም ጳጳስ አዋጅ (ሕግ) ይንበረከኩ ነበር። የሰዎች የጊዜያዊና የዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ በርሱ ቁጥጥር ስር ያለ መሰለ። ለብዙ መቶ ዓመታት የሮም አስተምህሮ ጥያቄ ሳይቀርብበት በስፋት ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፣ ሐይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቱ በአክብሮት ይፈጸም ነበር፤ ክብረ በዓላቱም እንዲሁ ይከበሩ ነበር። ካህናቱ በክብርና በምቾት ያለ ተቃውሞ ይኖሩ ነበር። የሮም ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ አይነት ማዕረግ፣ ሞገስና ስልጣን ተጎናጽፋ አታውቅም።GCAmh 47.1

    የጳጳሳዊ ሥርዓት ቀትር የዓለም የግብረ ገብነት ውድቅት ነበር።- J. A. Wylie, The History of Protestantism, b. 1, ch. 4። መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝቡ ብቻ አይደለም በቀሳውስቱ ጭምር አይታወቅም ነበር ማለት ይቻላል። እንደ ጥንታውያኑ ፈሪሳውያን፣ ጳጳሳዊ መሪዎችም ኃጢአታቸውን እርቃኑን የሚያስቀረውን ብርሐን ይጠሉት ነበር። የጽድቅ መለኪያ የሆነው የእግዚአብሔር ሕግ ተወግዶ፣ ስልጣናቸውን ያለ ገደብ፣ የግብረ ገብነት ልቅነታቸውንም ያለመጠን አካሄዱት። ማጭበርበር፣ ንፉግነትና መጠን-የለሽ አባካኝነት ተስፋፍቶ ነበር። ሰዎች ሃብት ወይም ስልጣን ማግኘት ከሚችሉበት ከማንኛውም የወንጀል ድርጊት ወደ ኋላ አይሉም ነበር። የጳጳሳትና በስሩ ያሉ የኃይማኖት መሪዎች መኖሪያ የነበሩት ቤተ ነገሥታት እጅግ የተዋረደ ስሜትን የማርካት ትዕይንት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ በስልጣን ላይ ያሉ ጳጳሳት የሚፈጽሙት ወንጀል እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ የተነሳ ሊታለፍ ስለማይቻል መንግሥታዊ ገዥዎች እንደ አስፈሪ ፍጡራን የሚያዩዋቸውን እነዚህን የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ከስልጣን ሊያነሱአቸው ይጥሩ ነበር። ለብዙ መቶ ዓመታት አውሮፓ በትምህርት፣ በስነ-ጥበብም ሆነ በስልጣኔ ምንም አይነት ዕመርታ አላሳየችም ነበር። የስነ-ምግባርና የአእምሮ ሽባነት በክርስትናው ዓለም ላይ ወድቆ ነበር።GCAmh 47.2

    በሮም ስልጣን ስር የነበረው ዓለም በነቢዩ ሆሴዕ የተነገረውን አስፈሪና ከባድ ትንቢት ፍጻሜ ይወክል ነበር፦ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና… እኔ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ።” “እውቀትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ፣ እርግማንና ሐሰት፣ ግዳይና ስርቆት ምንዝርም ወጥተዋል፤ ደምም ወደ ደም ደርሶአል።” [ሆሴዕ 4÷6፣1፣3]። የእግዚአብሔርን ቃል ማጥፋት ውጤቱ ይህን ይመስል ነበር።GCAmh 47.3

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents