Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፳፪—ትንቢቶች ተፈፀሙ

    የጌታ መምጫ መጀመሪያ የተጠበቀበት፣ የ1844 ዓ.ም ፀደይ ወቅት ሲያልፍ መገለፁን በእምነት ሲጠባበቁ የነበሩ ለተወሰነ ጊዜ መጠራጠርና እርግጠኛ ባለመሆን ውስጥ ነበሩ። ፍፁም ሽንፈት እንደደረሰባቸውና ምናብ ሲከተሉ እንደነበር አድርጎ ዓለም ቢያያቸውም የመጽናናታቸው ምንጭ ግን አሁንም የእግዚአብሔር ቃል ነበር። የእምነታቸውን ማስረጃዎች እንደ አዲስ እየመረመሩ፣ ተጨማሪ ብርሐን ለማግኘት ትንቢቶችን በጥንቃቄ እያጠኑ፣ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ቀጠሉ። አቋማቸውን በመደገፍ ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ግልጽና አሳማኝ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። ሊሳሳቱ የማይችሉ ግልጽ ምልክቶች የክርስቶስ መምጣት እንደቀረበ ይጠቁሙ ነበር። በኃጢአተኞች መለወጥም ሆነ በክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት መነቃቃት ረገድ የነበረው የተለየ የእግዚአብሔር በረከት መልእክቱ የሰማይ እንደሆነ ምስክር ነበር። እናም አማኞች ለቅሬታቸው ማብራሪያ መስጠት ባይችሉም እስካሁን በነበረው ልምምዳቸው ግን እግዚአብሔር ሲመራቸው እንደነበረ እርግጠኛነት ተሰማቸው።GCAmh 285.1

    በዳግም ምፅዓቱ እንደሚከናወኑ አድርገው ከተቀበሏቸው ትንቢታት ጋር የተሸመነ፣ በእምነታቸው ሆነው በትዕግስት እንዲጠብቁ የሚያበረታታቸው፣ አሁን ለመረዳት ጨለማ የሆነውም በጊዜው ግልጽ እንደሚሆን የሚጠቁም፣ የመጠራጠርና ልብ አንጠልጣይ ለሆነው ሁኔታቸው በተለይ የሚገጥም መመሪያ ተሰጥቶ ነበር።GCAmh 285.2

    ከእነዚህ ትንቢታት መካከል አንዱ እንባቆም 2÷1-4 ነበር፦ “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፣ በአምባ ላይም እወጣለሁ፣ የሚናገረኝንም ስለ ክርክሬም የሚመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ። እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ፦ አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራዕዩን ፃፍ በጽላትም ላይ ግለጠው። ራዕዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው ወደ ፍፃሜውም ይቸኩላል፤ እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሰው፣ እርሱ አይዘገይም። እነሆ ነፍሱ ኮርታለች በውስጡም ቅን አይደለችም፣ ፃድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል።”GCAmh 285.3

    “አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራዕዩን ፃፍ በጽላትም ላይ ግለጠው” በሚለው ትንቢት የተሰጠው ትዕዛዝ፣ ቀደም ብሎ በ1842 ዓ.ም የዳንኤልንና የዮሐንስን ራዕዮች በምሳሌ ለማስረዳት የትንቢት ሰንጠረዥ ያዘጋጅ ዘንድ ለቻርለስ ፊች ጠቁሞት ነበር። የዚህ ሰንጠረዥ መታተም በእንባቆም የተሰጠው ትዕዛዝ ፍፃሜ እንዳገኘ ተደርጎ ተወሰደ። ሆኖም ግን በዚያው ትንቢት ውስጥ የተቀመጠ፣ ግልጽ የሆነ፣ በራዕዩ መፈፀም ዙሪያ ማርፈድ፣ የዘገየ ጊዜ፣ እንደሚኖር የተጠቀሰውን ትንቢት ያን ጊዜ ማንም ያስተዋለው አልነበረም። ከቅሬታው በኋላ ይህ ጥቅስ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ታየ። “ራዕዩ ገና እስከተወሰነው ጊዜ ነው፤ ወደ ፍፃሜውም ይቸኩላል፤ እርሱም አይዋሽም፣ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና፣ ታገሰው፤ እርሱ አይዘገይም….ፃድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል።”GCAmh 285.4

    የሕዝቅኤል ትንቢት አንዱ ክፍልም ለአማኞች የብርታትና የመጽናናት ምንጭ ሆኖላቸው ነበር። “የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ በእሥራኤል ምድር፦ ዘመኑ ረዝሞአል ራዕዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው? ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦….ዘመኑና የራዕዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል…. እኔ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈፀማል ደግሞም አይዘገይም፤ እነሆ የእሥራኤል ቤት ይህች የሚያያት ራዕይ ለብዙ ዘመን ናት እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ። ስለዚህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈፀማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም።” [ሕዝ 12÷21-25፣27፣28]።GCAmh 286.1

    እናም መጨረሻውን መጀመሪያ የሚያውቀው እርሱ፣ ዘመናትን አቆልቁሎ በማየት የሚደርስባቸውን ቅሬታ በመገንዘብ የብርታትና የተስፋ ቃላትን እንደሰጣቸው በማመን ይጠብቁ የነበሩ ሃሴት አደረጉ። በትዕግስት እንዲጠብቁ፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያላቸውን አመኔታ አጥብቀው እንዲይዙ የሚገስጿቸው እንደዚህ አይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ባይኖሩ ኖሮ በዚያ ፈታኝ ሰዓት እምነታቸው በጠፋ ነበር።GCAmh 286.2

    በማቴዎስ 25 የሚገኘው የአሥርቱ ደናግልት ምሳሌም የአድቬንቲስት ሕዝብን ተሞክሮ የሚያብራራ ነው። በማቴዎስ 24 ስለ መምጣቱና ስለ ዓለም መጨረሻ ምልክት በተመለከተ ደቀ መዛሙርቱ ለጠየቁት ጥያቄ ሲመልስ ከመጀመሪያ ምፅዓቱ እስከ ሁለተኛ ምፅዓቱ ያሉትን በዓለምና በቤተ ክርስቲያንዋ ታሪክ እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉት ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ክርስቶስ ጠቁሞ ነበር። በስም ሲጠቀሱ፦ የየሩሳሌም ጥፋት፣ በጣዖት አምላኪና በጳጳሳዊ ሥርዓት ጭፍጨፋዎች ሥር የነበረ የቤተ ክርስቲያን ታላቁ መከራ፣ የፀሐይና የጨረቃ መጨለምና የከዋከብት መውደቅ ናቸው። ከዚህ በኋላ በመንግሥቱ ስለመምጣቱ ተናገረ፤ ከዚያም መምጣቱን ይጠብቁ ስለነበሩ ሁለት አይነት ባሪያዎች ምሳሌ አያይዞ ተናገረ። ምዕራፍ 25 “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት… አሥር ደናግልትን ትመስላለች” በማለት ይጀምራል። በምዕራፍ 24 መዝጊያ የተጠቆመችው ያችው ቤተ ክርስቲያን ናት በመጨረሻው ዘመን የምትኖር መሆኑ እዚህ ላይ የተገለፀው። በዚህ ምሳሌ፣ ተሞክሮአቸው የተብራራው በምሥራቃዊው [በኢስያ] የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ክስተቶች አማካይነት ነበር።GCAmh 286.3

    “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን [ደናግልት/virgins] ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮቻቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩለ ሌሊትም ሲሆን፦ “ጩኸት ሆነ፣ እነሆ ሙሽራው ደረሰ። ውጡ ትቀበሉት ዘንድ።”GCAmh 286.4

    በመጀመሪያው መልአክ የታወጀው የክርስቶስ መምጣት መልእክት ይስተዋል የነበረው በሙሽራው መምጣት እንደሚወከል ተደርጎ ነበር። በቅርብ እንደሚመጣ በታወጀበት መልእክት ስር በስፋት የተስፋፋው ተሐድሶ የደናግልቱን መቀስቀስ የሚወክል ነበር። በዚህም ምሳሌ፣ ልክ እንደ ማቴዎስ 24፣ የተወከሉት ሁለት መደቦች ናቸው። ሁሉም መብራታቸውን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው በእርሱ ብርሐን አማካኝነት ሙሽራውን ሊገናኙ ወጡ፤ ሆኖም “ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት” ሳይዙ የነበሩ ቢሆንም “ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።” የኋለኞቹ ቡድን፣ ቃሉን ለእግር መብራትና ለመንገድ ብርሐን የሚያደርገውን፣ እንደገና የሚያድሰውንና የሚያሳውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ የእግዚአብሔርን ፀጋ ተቀብለው ነበር። በፈሪሃ-እግዚአብሔር ስር ሆነው እውነትን ይማሩ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ፣ ለልብና ለሕይወት ንጽህናም ከምር ይተጉ ነበር። እነዚህ ቡድኖች በቅሬታ ወይም በመዘግየት ምክንያት ሊገረሰስ የማይችል ግላዊ ልምምድ፣ በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይም እምነት ነበራቸው። ሌሎቹ “መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙም” ነበር። የተነቃቁት ከስሜት ተነስተው ነበር። በከበረው መልእክት ምክንያት ፍርሃት ይዟቸው ነበር፤ ነገር ግን በባልንጀሮቻቸው እምነት ላይ ተደግፈው፣ ብልጭ ድርግም በሚለው የመልካም ስሜት ብርሐን ረክተው፣ ያለ ጥልቅ የእውነት ማስተዋል፣ ወይም ያለ እውነተኛ የልብ ውስጥ የፀጋ ሥራ ነበሩ። እነዚህ የቅጽበታዊ ሽልማት ዕድል ባለሙሉ ተስፋ ሆነው ጌታን ለመቀበል የሄዱ ናቸው፣ ሆኖም ለመዘግየትና ለቅሬታ (ለሃዘን) የተዘጋጁ አልነበሩም። ፈተና ሲመጣ እምነታቸው መከነ፤ መብራቶቻቸውም ጨለሞሱ።GCAmh 286.5

    “ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።” ጌታ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የቀረበት፣ ቅሬታቸውና ያረፈደ የሚመስልበት ጊዜ፣ በሙሽራው መዘግየት የሚወከል ነው። በዚህ ጥርጥር በሞላበት ጊዜ አስመሳይና ግማሽ ልብ ያላቸው ሁሉ ፍላጎት ወዲያውኑ ዋዠቀ፣ ጥረታቸውም እየላላ ሄደ፤ እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ግላዊ እውቀት ላይ የተመሰረቱት ግን የቆሙት የቅሬታ ማዕበላት ጠርገው ሊወስዱት በማይችሉት ቋጥኝ ላይ ነበር። አንደኛው ቡድን በቸልተኛነትና እምነቱን በመተው ውስጥ ሆኖ፣ ሌላው ቡድን ደግሞ የበለጠ ግልጽ የሆነ ብርሐን እስኪሰጥ ድረስ በታጋሽነት እየጠበቀ ሳለ “ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።” ሆኖም በፈተና ሌሊት የኋለኛው ቡድን በተወሰነ ደረጃ ቅንዓታቸውንና ትጋታቸውን ያጡ ይመስል ነበር። የከፊል ልብ ያላቸውና አስመሳዮች በባልንጀሮቻቸው እምነት ላይ መደገፍ መቀጠል የሚችሉበት ሁኔታ አብቅቶ ነበር። እያንዳንዱ ለራሱ መቆም ወይም መውደቅ ነበረበት።GCAmh 287.1

    በዚህ ጊዜ ገደማ አክራሪነት ብቅ ብቅ ማለት ጀመረ። ልባዊና ጠንካራ አማኞች መሆናቸውን ይናገሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔር ቃል የማይሳሳት መሪ እንደሆነ አንቀበልም አሉ፤ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት አለን በማለት በራሳቸው ስሜቶች፣ ግምቶችና ምናቦች ቁጥጥር ስር ወደቁ። አካሄዳቸውን የማያፀድቁላቸውን ሁሉ በመኮነን ጭፍንና የመረረ የጥላቻ መንፈስ ያንፀባረቁ አንዳንዶች ነበሩ። የአክራሪነት ሃሳቦቻቸውና ድርጊቶቻቸው ከታላቁ የአድቬንቲስቶች ህብረት ኀዘኔታ ባይቸራቸውም በእውነት ግብ ላይ ነቀፌታ እንዲመጣ ግን አገልግለዋል።GCAmh 287.2

    በዚህ መንገድ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ ለመቃወምና ለማፈራረስ እየጣረ ነበር። ከአድቬንት ንቅናቄ የተነሳ ሕዝቦች እጅግ ተነቃቅተው ነበር፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኃጢአተኞች ተለወጡ፤ ታማኝ ሰዎች በዚያ በመዘግየት (የሱስ ሳይመጣ በዘገየበት ጊዜ) እንኳ እውነቱን ለማወጅ ሥራ ራሳቸውን እየሰጡ ነበር። የክፋት ልዑል ባሪያዎቹን እያጣ ነበር። በእግዚአብሔር ዓላማ ላይ ነቀፋ ለማምጣት በማሰብ የተወሰኑ አማኞችን በማታለል ወደ ጽንፈኛነት ሊነዳቸው ይፈልግ ነበር። ከዚያም እያንዳንዷን ስህተት፣ እያንዳንዷን ውድቀት፣ እያንዳንዷን ተገቢ ያልሆነች እንቅስቃሴ ነቅሶ በማውጣትና በሕዝቡ ፊት እጅግ አጋነው በማቅረብ አድቬንቲስቶችን እምነታቸው የተጠላ እንዲሆን ለማድረግ የሰይጣን እንደራሴዎች በተጠንቀቅ ቆመው ነበር። ልባቸውን የሰይጣን ኃይል የተቆጣጠራቸው በዳግም ምፅዓት በሚያምኑት ውስጥ የበዛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን መሰብሰብ ቻለ ማለት የሁሉም አማኞች ህብረት ወኪል እንዲሆኑ አድርጎ ለማሳየት ይችል ዘንድ ትኩረት በመሳብ ብልጫ ያለው ጥቅም ማግኘት ይቻለዋል ማለት ነው።GCAmh 287.3

    ሰይጣን “የወንድሞች ከሳሽ” ነው። የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ስህተቶችና ጉድለቶች በመንቀስ ገሃድ እንዲያወጡ፣ መልካም ሥራዎቻቸው ግን ምንም ሳይጠቀሱ ተሸፋፍነው እንዲያልፉ እንዲያደርጉ ሰዎችን የሚያነሳሳው የእርሱ መንፈስ ነው። እግዚአብሔር ነፍሳት ለማዳን በሚሰራበት ጊዜ ሰይጣን ሁልጊዜም በሥራ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ራሳቸውን በአምላክ ፊት ሊያቀርቡ በሚመጡበት ጊዜ ሰይጣንም በመካከላቸው ይመጣል።በእያንዳንዱ መነቃቃት ከልባቸው ያልተቀደሱትንና አዕምሯቸው የተዛባባቸውን ሰዎች ለማምጣት ዝግጁ ነው። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የእውነትን የተወሰኑ ነጥቦች ተቀብለው በአማኞች መካከል ስፍራ ሲያገኙ፣ በእነዚህ ሰዎች በኩል ጽንሰ-ሃሳቦችን በማስተዋወቅ ያልጠረጠሩትን ለማታለል ይሠራል። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር ስለሆነ፣ ከዚያም አልፎ በአምልኮ ስፍራና በእግዚአብሔር ገበታ ዙሪያ ስለተገኘ ብቻ እውነተኛ ክርስቲያን ነው ብሎ ማረጋገጥ አይቻልም። ወኪሉ አድርጎ ሊጠቀማቸው የሚችላቸውን ሰዎች መልክ ይዞ ዘወትር ሰይጣን ክቡር በሆኑ ዝግጅቶች ላይ ይገኛል።GCAmh 288.1

    የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ ሰማያዊቷ ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ፣ ወደፊት የሚራመዱበትን እያንዳንዷን ስንዝር መሬት የክፋት ልዑል ይሟገታቸዋል። በቤተ ክርስቲያንዋ ታሪክ ሁሉ ከባድ እንቅፋቶች ሳይገጥመው ወደፊት የተራመደ ተሐድሶ የለም። በጳውሎስ ዘመንም እንደዚሁ ነበር። ሐዋርያው ቤተ ክርስቲያን ባቋቋመበት ስፍራ ሁሉ እምነቱን መቀበላቸውን የመሰከሩ፣ ነገር ግን ኑፋቄዎችን ይዘው የገቡ፣ ያመጡት አቋምም ተቀባይነት ቢያገኝ ቀስ በቀስ ለእውነት ያለውን ፍቅር አጨናንቆ የሚያስወጣ፣ እምነት የያዙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ሉተርም እንዲሁ እግዚአብሔር በእነርሱ በኩል በቀጥታ እንደተናገረ የሚያትቱ፣ ብሎም የራሳቸውን ሃሳቦችና አስተያየቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት በላይ በሚያስቀምጡ አክራሪ ሰዎች አቋም ምክንያት ለከባድ ግራ መጋባትና ጭንቀት ተዳርጎ ነበር። እምነትና ልምድ የሚጎድላቸው ብዙዎች፣ ሆኖም በራሳቸው ከፍተኛ ብቁነት የሚሰማቸው፣ የሆነ አዲስ ነገር መስማትና መናገር የሚወዱ እነርሱ በአዲሶቹ አስተማሪዎች የማስመሰል ተግባራት ተማርከው፣ እግዚአብሔር ሉተርን አስነስቶ የገነባውን ለማፈራረስ የሰይጣንን ወኪሎች ተቀላቀሉ። ዓለምን በተጽዕኖአቸውና በእምነታቸው የባረኩ ዌስሊዎችና ሌሎችም፤ ልክ ያጣ ቀናኢነት ያላቸውን፣ ሚዛን ያልጠበቁና ያልረኩ ሰዎችን ወደ ሁሉም አይነት አክራሪነት የሚገፋፉ የሰይጣን ማታለያዎች በእያንዳንዱ እርምጃቸው ይገጥሟቸው ነበር።GCAmh 288.2

    ዊሊያም ሚለር ወደ ጽንፈኛነት ለሚመሩ ተጽዕኖዎች ምንም አይነት ርኅራኄ አልነበረውም። እርሱም ከሉተር ጋር ሆኖ እያንዳንዱ መንፈስ በእግዚአብሔር መንፈስ መፈተሽ (መፈተን) እንዳለበት አውጆአል። “ሰይጣን” አለ ሚለር፣ “በዚህ ወቅት በአንዳንድ ሰዎች አዕምሮ ላይ ታላቅ ኃይል አለው። ከምን ዓይነት መንፈስ እንደሆኑ እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ ሲመልስ “በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” ይላል፤ “ወደ ዓለም የተበተኑ ብዙ መናፍስት አሉ፤ መናፍስቱን እንፈትን ዘንድ ታዘናል። በዚህ ዘመን ባለው ዓለም በመጠን፣ በፅድቅና እግዚአብሔርን በመምሰል እንድንኖር የማያደርገን መንፈስ እርሱ የክርስቶስ መንፈስ አይደለም። የእነዚህ የማይጨበጡ እንቅስቃሴዎች አድራጊ-ፈጣሪ ሰይጣን እንደሆነ የበለጠ እያመንኩ መጥቻለሁ።” “በመካከላችን ያሉ ብዙዎች ሙሉ ለሙሉ እንደተቀደሱ የሚያስመስሉ፣ የሰዎችን ወግና ባህል የሚከተሉ ናቸው። እነርሱም የዚህን ዓይነት አስመሳይነት እንደማያንፀባርቁት ሰዎች ሁሉ የእውነቱ ገልቱ እንደሆኑ ግልጽ ነው።”-Bliss, ገጽ 236, 237’ “የስህተት መንፈስ ከእውነት እንድንርቅ ይመራናል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እውነት ይመራናል። አንተ ግን እንበል፣ አንድ ሰው በስህተት ውስጥ ሆኖ እውነት አለኝ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ከዚያስ ምን ይደረግ? እኛም የእግዚአብሔር መንፈስና ቃሉ ይስማማሉ ብለን እንመልሳለን። አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ራሱን ከመዘነና ከሙሉው ቃሉ ጋር ፍፁም ስምሙ ከሆነ፣ እውነት እንዳለው ማመን አለበት። ነገር ግን የሚመራበት መንፈስ ከእግዚአብሔር ሕግ ወይም መጽሐፍ ጠቅላላ ትርጉም (ከሙሉ ትርጉሙ) ጋር የማይስማማ ከሆነ በሰይጣን ወጥመድ እንዳይጠለፍ በጥንቃቄ ይራመድ።”-The Advent Herald and Signs of the Times Reporter, vol. 8, No. 23 (Jan. 15,1845)። “በክርስትናው ዓለም ካለው ጫጫታ ሁሉ ይልቅ ቁልጭ ቁልጭ በሚል አይን፣ በረጠበ ጉንጭና ሳግ በያዘው ንግግር የውስጥ ቅድስናን ማረጋገጫ ሁልጊዜም አገኛለሁ።”-Bliss, Page 282።GCAmh 288.3

    በተሐድሶ ዘመናት፣ የእንቅስቃሴው ጠላቶች፣ ወግ አጥባቂነትን በፍፁም ታማኝነት የሚዋጉትን እነርሱኑ በመክሰስ ለአክራሪነት ጥፋቶች ተጠያቂ ያደርጓቸው ነበር። የአድቬንትን (የዳግም ምፅዓትን) እንቅስቃሴ የተቃወሙትም የተከተሉት ተመሳሳይ መንገድ ነበር። የጽንፈኛነትና የአክራሪነት ስህተቶችን ማጣመምና ማጋነን አላረካቸው ሲል፣ ከእውነቱ ጋር ቅንጣት ታህል የማይመሳሰል መልካም ያልሆነ ወሬ ማናፈስ ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች የተነሳሱት ከመሰረተ-ቢስ እይታና ጥላቻ ነበር። ክርስቶስ በደጅ እንደቀረበ የታወጀው አዋጅ ሰላማቸውን ያውከው ነበር። እውነት ሊሆን ይችል ይሆን ብለው ይፈራሉ፤ ባይሆን ብለው ደግሞ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ይህ አድቬንቲስቶችንና እምነታቸውን የሚዋጉበት የጦርነት ስልት፣ ምስጢራቸው ነበር።GCAmh 289.1

    በጳውሎስ ወይም በሉተር ዘመናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአክራሪዎችና የአሳሳቾች መኖር ሥራቸውን ለማውገዝ በቂ ምክንያት እንዳልነበረ ሁሉ፣ ጥቂት ወግ አጥባቂዎች በአድቬንቲስቶች እርከን (የኃላፊነት ቦታ) ውስጥ በዝግታ መግባት የመቻላቸው ጭብጥ እንቅስቃሴው ከእግዚአብሔር አይደለም ብሎ ለመወሰን በቂ ምክንያት አይደለም’ እስኪ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከእንቅልፋቸው ይነሱና ልባዊ የሆነ የንስሐና የተሐድሶ ሥራ ይስሩ፣ በክርስቶስ ያለውን እውነት ለመማር መጽሐፍ ቅዱሳትን ይመርምሩ፣ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ይቀደሱ፤ ከዚያም ሰይጣን ንቁና አሁንም በሥራ ላይ ያለ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አይጠፋም። በመንግሥቱ ያሉትን የወደቁ መላእክት ሁሉ ለእርዳታ በመጥራት፣ በሚችለው ማታለያዎች ሁሉ ኃይሉን ይገልጣል።GCAmh 289.2

    አክራሪነትንና መከፋፈልን የፈጠረው የዳግም ምፅዓቱ መታወጅ አልነበረም። እነዚህ ነገሮች ብቅ ያሉት በ1844 በጋ ወቅት አድቬንቲስቶች ትክክለኛ አቋማቸውን በተመለከተ በጥርጥርና በድንግርግር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነበር። የመጀመሪያው መልአክ መልእክትና “የእኩለ-ሌሊቱ ጩኸት” ስብከት በቀጥታ አክራሪነትንና የሐሳብ መከፋፈልን ለመዋጋት ረድቶ ነበር። በእነዚህ ክቡር እንቅስቃሴዎች የተሳተፉ ሁሉ ስምሙ ነበሩ፤ ለእርስ በርሳቸውና በቅርብ እንደሚያዩት ሲጠብቁት ለነበረው የሱስ ያላቸው ፍቅር ልባቸውን ሞልቶት ነበር። አንድ እምነት፣ አንድ የተባረከ ተስፋ፣ ከማናቸውም የፍጡር ተጽዕኖ በላይ ከፍ አደረጋቸው፤ ከሰይጣን ጥቃቶችም መከለያ ጋሻ መሆኑ ተረጋገጠ።GCAmh 289.3

    “ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።” እኩለ ሌሊትም ሲሆን፣ “ጭኸት ሆነ፣ ሙሽራው ደረሰ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ደናግልት ሁሉ ተነሱና መብራታቸውን አዘጋጁ” [ማቴ 25÷5-7]። የ2300 ቀናቶቹ መጨረሻ ነው ተብሎ በታመነበት በ1844 በጋ እና በኋላ እንደታወቀውም ጊዜውን እስከ አራዘሙበት፣ የዛው ዓመት መከር ወቅት መካከል እኩሌታ አካባቢ ድረስ፣ “እነሆ ሙሽራው ደረሰ” የሚለው ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መልእክት እየታወጀ ነበር።GCAmh 290.1

    ለዚህ እንቅስቃሴ ማለትም ጊዜው ከበጋ 1844 ወደ መከር የተራዘመበት ምክንያት የሆነው የ2300 ቀናት መነሻ (መጀመሪያ) የነበረው የሩሳሌምን እንደገና ለመገንባት የወጣው የአርጤክስስ አዋጅ ተግባራዊ የሆነው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ457 የመከር ወቅት እንጂ በፊት ይታመን እንደነበረው የአመቱ መጀመሪያ እንዳልሆነ ስለተደረሰበት ነበር። ከክ. ል. በፊት 457 ዓ.ዓ ጀምሮ 2300 ቀናቱ ሲቆጠሩ በ1844 ዓ.ም መከር ወቅት ያበቃሉ። [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 3ን ይመልከቱ]።GCAmh 290.2

    በብሉይ ኪዳን ጥላዎች ከነበሩ ክስተቶች የተወሰዱት ሃሳቦችም “የመቅደሱ መንፃት” የሚወክላቸው ክስተቶች የሚፈፀሙት በዚያው መከር ወቅት እንደሆነ የሚጠቁሙ ነበሩ። የክርስቶስን መጀመሪያ አመጣጥ ይጠቁሙ የነበሩ ጥላ የምንላቸው ክስተቶች እንዴት እንደተፈፀሙ ለመረዳት ትኩረት ሲሰጣቸው ይህ ጉዳይ የበለጠ ግልጽ ሆነ።GCAmh 290.3

    የፋሲካው በግ መታረድ የክርስቶስ ሞት ጥላ ነበር። ጳውሎስ ሲናገር፦ “ክርስቶስ ፋሲካችን ታርዶአልና” ይላል [1ኛ ቆሮ 5÷7]። ከፍሬዎቹ የመጀመሪያው፣ ማለትም በፋሲካ ወቅት በጌታ ፊት የሚወዘወዘው ነዶ የክርስቶስን ከሞት መነሳት የሚያመለክት ነበር። ጳውሎስ ስለ ጌታና ስለ ሁሉም ሕዝቦቹ ከሞት መነሳት ሲናገር “ክርስቶስ እንደበኩራት ነው በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው” ይላል [1ኛ ቆሮ 15÷23]። ልክ ከመከር በፊት የሚጎመራው የመጀመሪያ/የበኩር እህል እንደሚወዘወዘው ነዶ፣ ክርስቶስም ወደፊት በሚመጣው ትንሳኤ ወደ እግዚአብሔር ጎተራ የሚከማቹት፣ የተዋጁት፣ የማይሞት መከር በኩራት ነው።GCAmh 290.4

    እነዚህ ምሳሌዎች ደግሞ እንደ ድርጊቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ጊዜውም ተፈጽመዋል። ለአሥራ አምስት ረጅም ምዕተ ዓመታት የፋሲካው በግ ሲታረድ በኖረበት ፣ በዚያው ቀንና በዚያው ወር፣ በአይሁድ የመጀመሪያው ወር አሥራ አራተኛ ቀን ላይ ፋሲካን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከበላ በኋላ “የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያስወግድ” እንደሆነ የሚያስታውሰውን የራሱ ሞት መታሰቢያ የሆነውን በዓል ክርስቶስ አቋቋመ። በዚያው ምሽት ይሰቀልና ይታረድ ዘንድ በኃጢአተኞች እጅ ተወሰደ። የሚወዘወዘው ነዶ ምሳሌ ገሃድ (አካላዊ ፍጻሜ) ሆኖ፣ “ለአንቀላፉት በኩራት ሆኖ” [1ኛ ቆሮ 15÷20]፣ “የተዋረደ ስጋቸው” ተለውጦ “ክቡር ስጋውን እንዲመስል”[ፊልጵ 3÷21] ተደርጎ የሚሰራላቸው፣ ከሙታን የሚነሱ ፃድቃን ሁሉ ናሙና ሆኖ፣ በሶስተኛው ቀን የኛ ጌታ ከሙታን ተነሳ።GCAmh 290.5

    በተመሳሳይ ሁኔታም ከሁለተኛው ምፅዓት ጋር የሚዛመዱ ጥላዎችም በምሳሌያዊው አገልግሎት በተጠቀሰው ጊዜ የግድ መፈፀም ይኖርባቸዋል። በሙሴያዊ ሥርዓት የቤተ መቅደሱ መንፃት ወይም የታላቁ የመንፃት ቀን፣ ሊቀ ካህኑ ለእሥራኤል ሁሉ ስርየት አድርጎ ኃጢአታቸውን ከመቅደሱ ካስወገደ በኋላ ወደ ውጪ ወጥቶ ሕዝቡን የሚባርክበት ቀን የሚውለው በአይሁድ ሰባተኛው ወር አስረኛው ቀን ነበር። [ዘሌዋ 16÷29-34]። ክርስቶስ፦ ታላቁ ሊቀ ካህን፣ ኃጢአትንና ኃጢተኞችን በማጥፋት ምድርን ለማንፃት፣ የሚጠብቁትን ሕዝቦቹንም በዘላለማዊነት ሊባርካቸው እንደሚገለጽ ይታመን ነበር። በ1844 በጥቅምት ወር በ22ተኛው ቀን ላይ ያረፈው፣ የመቅደሱ የመንፃት ጊዜ፣ ታላቁ የመንፃት ቀን፣ የሰባተኛው ወር አስረኛው ቀን፣ የጌታ መምጫ ተደርጎ ተወሰደ። ይህ ደግሞ ቀደም ብሎ ከተደረሰበት ማስረጃ፣ 2300 ቀናቱ በመከር ወቅት እንደሚያበቁ ከተረጋገጠው እውነት ጋር የሚስማማ በመሆኑ መደምደሚያው ይቋቋሙት ዘንድ የማይቻል መሰለ።GCAmh 291.1

    በማቴዎስ 25 ባለው ምሳሌ ከመጠበቅና ከማንቀላፋት ጊዜው በኋላ የተከተለው የሙሽራው መምጣት ነበር። ይህ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሰው ትንቢትም ሆነ ከምሳሌዎቹ/ከጥላዎቹ ማብራሪያዎች ጋር የሚጣጣም ነበር። የእውነተኛነታቸውን ጠንካራ ማረጋገጫ፣ በጽኑ እምነት ያዘሉ ነበሩ፤ እናም “የእኩለ ሌሊት ጩኸት” በሺዎች በሚቆጠሩ አማኞች ተበሰረ።GCAmh 291.2

    ንቅናቄው ልክ እንደ ማእበል ምድሪቱን አጥለቀለቃት። በመጠባበቅ ላይ የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እስኪነቁ ድረስ ከከተማ ከተማ፣ ከመንደር መንደር፣ ወደሩቅ የገጠር ስፍራዎች ሁሉ ደረሰ። የንጋት ጉም፣ ፀሐይ ስትወጣ እንደሚበተን አክራሪነት ከዚህ አዋጅ ፊት ጠፋ። አማኞችም ጥርጣሬያቸውና ግራ መጋባታቸው ተወግዶ ተስፋና ብርታት ልባቸውን ሕያው ሲያደርገው ተመለከቱ። የመቆጣጠር ተጽእኖ የሚፈጥረው የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ሳይኖር ሲቀር ሁሌም የሚንፀባረቀው የሰብአዊ ፍጡር የጦፈ ስሜታዊነት ሳይታይ፣ ሥራው ከጽንፈኛነት ነፃ የሆነ ነበር። በጥንታዊ እሥራኤል ዘመን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሕዝቡን ከዘለፉ በኋላ የሚሆነው አይነት ባህርይ ያለው ራስን የማዋረድና ወደ ጌታ የመመለስ ወራት ሆኖ ነበር። በእያንዳንዱ ዘመን እግዚአብሔር የሚሰራውን ሥራ ባህርያት ምልክት ያዘለ ነበር። የሞቀ ደስታ አልነበረም፤ ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ልብን መመርመር፣ ኃጢአትን መናዘዝና ዓለምን መተው ነበር። ይቃትቱ የነበሩ ነፍሳት ሸክም እግዚአብሔርን ለመገናኘት መዘጋጀት ነበር። የማያቋርጥ ፀሎት፣ ያለገደብ ለእግዚአብሔር መቀደስ፣ ነበር።GCAmh 291.3

    ያንን ሥራ ሲገልጽ ሚለር እንዲህ አለ፦ “ታላቅ የሆነ የደስታ መግለጫ የለም፤ ያ፣ እንደነበረው፣ መላው ሰማይና ምድር በአንድ ላይ ሆነው መነገር በማይችል ደስታ፣ በክብር ሙላት ሀሴት ለሚያደርጉበት ለዚያ ለወደፊት ጊዜ ተቆጥቧል። ጩኸትም የለም፤ እርሱም ቢሆን ከሰማይ ለሚሆነው ጩኸት ተጠብቋል። ዘማሪያን ፀጥ ብለዋል፤ የመላእክትን ሰራዊት፣ ሰማያዊውን ኳየር ለመቀላቀል እየጠበቁ ናቸው። የአስተሳሰብ መጋጨት የለም። ሁሉም በአንድ ልብና በአንድ ሀሳብ ናቸው።” በንቅናቄው የተሳተፈ ሌላኛው ሲመሰክር፣ “በሁሉም ስፍራ እጅግ ጥልቅ የሆነ የልብ ምርመራና የነፍስ መዋረድን አስከትሎ ነበር….ለዚህ ዓለም ነገሮች ያለው ፍቅር እንዲጠፋ፣ ክርክሮችና ጥላቻዎች እንዲሽሩ፣ ስህተትን እንዲናዘዙ በእግዚአብሔር ፊት መሰባበርን፣ ይቅርታንና ተቀባይነትን ለማግኘት በፀፀት በተሞላች የተሰበረች ልብ መለመን እንዲሆን አድርጎ ነበር። ከዚያን ጊዜ በፊት አይተነው በማናውቅ ሁኔታ ራስን የማዋረድና የነፍስን መዝለፍለዝ አፍርቶ ነበር። እግዚአብሔር በነብዩ ኢዩኤል እንዳዘዘው ታላቁ የጌታ ቀን በደጅ በሆነ ጊዜ [ኢዮኤ 2÷13] እንደሚከሰተው ሁሉ የልብስ ሳይሆን የልብ መቀደድን፣ በፆም በለቅሶና በዋይታ ወደ ጌታ መመለስን አስከተለ። እግዚአብሔር በዘካርያስ አማካኝነት እንደተናገረ የፀጋና የምልጃ መንፈስ በልጆች ላይ ፈሰሰ፤ የወጉትን እርሱን እንደሚመለከቱ ሆኑ፤ በምድሪቱ ታላቅ ዋይታ ሆነ…. ጌታን የሚሹ እነርሱ ነፍሳቸውን በፊቱ አሰቃዩ።”-Bliss, in Advent Shield and Review, vol. 1. ገጽ 271(January 1845)’GCAmh 291.4

    ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከተደረጉት ታላላቅ የሐይማኖት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በ1844 ዓ.ም የመከር ወቅት እንደተደረገው ያለ ከፍጡር ጉድለትና ከሰይጣን ማታለያዎች የፀዳ ንቅናቄ አልነበረም። አሁንም ቢሆን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በዚያ እንቅስቃሴ የተሳተፉና በእውነት መድረክ የቆሙ ሁሉ፣ የዚያ የተባረከ ሥራ ቅዱስ ተጽእኖ እስካሁን ይሰማቸዋል፤ ከእግዚአብሔር እንደነበረም ምስክሮች ናቸው።GCAmh 292.1

    “እነሆ ሙሽራው ደረሰ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ” የሚለው ጥሪ ሲሰማ ይጠብቁት የነበሩ “ተነሱና መብራታቸውን አዘጋጁ።” ቀድሞ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የእግዚአብሔርን ቃል በታላቅ ፍላጎት አጠኑ። ተስፋ የቆረጡትን አነቃቅተው መልእክቱን እንዲቀበሉ ያዘጋጁአቸው ዘንድ መላእክት ከሰማይ ተላኩ። ሥራው ፀንቶ የቆመው በሰዎች ጥበብና ትምህርት ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል ነበር። ጥሪውን በመስማትና በመታዘዝ መጀመሪያ የሆኑት፣ እጅግ ትሁትና የተሰጡ የሆኑ እንጂ ከፍተኛ ችሎታ የነበራቸው አልነበሩም። ገበሬዎች ሰብሎቻቸው በእርሻ ውስጥ ሳይሰበሰቡ እንደቆሙ ትተው፣ መካኒኮችም መሳሪያዎቻቸውን ጥለው በእንባና በሐሴት ማስጠንቀቂያውን ለመናገር ወጡ። ይህንን ዓላማ ቀድሞ ሲመሩ የነበሩ ንቅናቄውን መጨረሻ ላይ ከተቀላቀሉት መካከል ነበሩ። በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት ለዚህ መልእክት በራቸውን ዘጉ፤ መልእክቱን የተቀበሉ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋረጡ። በእግዚአብሔር አቅርቦት አማካኝነት ይህ አዋጅ ከሁለተኛው መልአክ መልእክት ጋር ተዋህዶ ለዚያ ሥራ ጉልበት ሆነለት።GCAmh 292.2

    የመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ግልጽና የማያሻማ ቢሆንም “እነሆ ሙሽራው ደረሰ!” የሚለው መልእክት እምብዛም የመከራከሪያ ነጥብ አልነበረም። ነፍስን የሚያንቀሳቅስ አጥብቆ የሚገፋፋ ኃይል አብሮት ይሄድ ነበር። ጥርጥርም ጥያቄም አልነበረም። ክርስቶስ በድል አድራጊነት ደስታ ወደ የሩሳሌም ይገባ በነበረበት ጊዜ፣ በዓሉን ለማክበር ከምድሪቱ የተለያየ አቅጣጫ ሁሉ የተሰበሰበው ሕዝብ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ጎረፈ፤ የሱስን አጅበው እየተጓዙ የነበሩትን ሕዝቦች በተቀላቀሉ ጊዜ የሰዓቱን አነቃቂ መንፈስ በመጨበጥ፣ ጩኸቱን የበለጠ ደመቅ በማድረግ፣ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” [ማቴ 21÷9] አሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ አንዳንዶች ምን እንደሆነ ለማወቅ ካላቸው ጉጉት፣ ሌሎች ደግሞ ለመሳለቅ ሲሉ ወደ አድቬንቲስት ስብሰባዎች የሄዱ የማያምኑ ሰዎች “እነሆ ሙሽራው ደረሰ!” ከሚለው መልእክት ጋር የሚወጣው አሳማኝ ኃይል ተሰምቷቸዋል።GCAmh 292.3

    በዚያን ጊዜ ለፀሎት መልሶችን የሚያመጣ፣ የመካስን ሽልማት ክብር የሚሰጥ እምነት ነበር። ልክ በተጠማች መሬት ላይ ዤቅ እንደሚል ዶፍ ዝናብ የፀጋ መንፈስ ከልብ በሚሹት ላይ ወረደ። ከአዳኛቸው ጋር በቅርብ ፊት ለፊት እንደሚቆሙ የጠበቁ ሁሉ ሊነገር የማይችል እጅግ ጥልቅ ደስታ ተሰማቸው። በታማኝነት በሚያምኑት ላይ የተትረፈረፈ በረከት በወረደ ጊዜ የሚያለሰልሰውና የሚያሸንፈው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ልቦችን አቀለጠ።GCAmh 292.4

    በጥንቃቄና በልባዊነት መልእክቱን የተቀበሉ እነርሱ ጌታቸውን ሊቀበሉ ተስፋ ወዳደረጉበት ጊዜ ደረሱ። በእያንዳንዱ ጠዋት ተቀባይነት እንዳገኙ የሚያረጋግጥላቸውን ማስረጃ ማግኘት ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውት ነበር። ልቦቻቸው በቅርበት ተቆራኝተው፣ አንድ ላይ ሆነው ለእርስ በርሳቸው እጅግ ይፀልዩ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኙ ዘንድ ብዙ ጊዜ የሚገናኙት ገንጠል ባለ ቦታ ነበር፤ የስርየት ፀሎትም ከመስኮችና ከዋሻዎች ወደ ሰማይ ይወጣ ነበር። ለእነርሱ፣ የአዳኙ ተቀባይነት ማረጋገጫ ከእለት ምግባቸው ይልቅ አስፈላጊ ነበር፤ ጭጋግ አዕምሯቸውን ካጨለመው ተጠራርጎ እስኪሄድ ድረስ እረፍት አልነበራቸውም። የይቅርታ ፀጋ ምስክር ሲሰማቸው ነፍሳቸው የወደደችውን እርሱን ያዩ ዘንድ ናፈቁ።GCAmh 293.1

    ሆኖም እንደገና ወደ ቅሬታ መዳረሻ እየገሰገሱ ነበር። ተስፋ ያደረጉት ጊዜ አለፈ፤ አዳኛቸውም አልተገለፀም። በማይንገዳገድ እርግጠኛነት መምጣቱን ተጠባብቀው ነበር፤ ማሪያም ወደ አዳኙ መቃብር መጥታ ባዶ መሆኑን ስታይ እያለቀሰች “ጌታዬን ወስደውታል ወዴት እንዳኖሩት አላውቅም” [ዮሐ 20÷13] ብላ ስትጮህ የተሰማት ስሜት ነበር የተሰማቸው።GCAmh 293.2

    አግራሞታዊ ፍርሃት፣ መልእክቱ እውነት ቢሆንስ የሚለው ፍርሃት፣ ለተወሰነ ጊዜ የማያምነውን ዓለም ገድቦት ነበር። ጊዜው ካለፈ በኋላ ይህ በአንድ ጊዜ አልጠፋም፤ በመጀመሪያ አካባቢ ቅር በተሰኙት ላይ ድል መቀዳጀት አልደፈሩም ነበር፤ ሆኖም የእግዚአብሔር ቁጣ ምልክቶች አልታይ ሲሉ፣ ከፍርሃታቸው አገግመው ነቀፋቸውንና ፌዛቸውን እንደገና ቀጠሉበት። ክርስቶስ በቅርብ እንደሚመጣ እንደሚያምኑ የመሰከሩ ብዛት ያላቸው ሕዝቦች እምነታቸውን ካዱ። እጅግ ተማምነው የነበሩ አንዳንዶች ክብራቸው ክፉኛ ከመነካቱ የተነሳ ከምድር ኮብልሎ የመጥፋት ስሜት ተሰማቸው። ልክ እንደ ዮናስ በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ፤ ከመኖር መሞትን መረጡ። እምነታቸውን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሳይሆን በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ያደረጉ እነርሱ አሁንም እይታቸውን ለመቀየር ዝግጁ ነበሩ። አላጋጮች ደካሞችንና ፈሪዎችን ከጎናቸው ማሰለፍ ቻሉና ሁሉም በአንድ ላይ በመተባበር አሁን ፍርሃትም ሆነ የሚጠበቅ ነገር ሊኖር እንደማይችል አወጁ። ጊዜው አልፎአል ጌታም አልመጣም፤ እናም ዓለም ለበርካታ ሺህ ዓመታት ሳይለወጥ ሊቆይ ይችላል።GCAmh 293.3

    ልባዊና ታማኝ አማኞች ለክርስቶስ ሲሉ ሁሉን ትተው መገኘቱንም ከምንም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተጋርተው ነበር። እንደ እምነታቸው ከሆነ የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ ለዓለም ሰጥተዋል፤ በቅርቡ ከመለኮታዊ ጌታቸውና ከሰማያዊ መላዕክት ጋር እንደሚቀላቀሉ በመጠበቅ በአብዛኛው መልእክቱን ካልተቀበሉት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠው ነበር። በታላቅ ፍላጎት “አዎን የሱስ ሆይ ቶሎ ና!” በማለት ፀልየው ነበር። ነገር ግን ሳይመጣ ቀረ። አሁን የሕይወትን ችግሮችና ግራ የመጋባት ከባድ ቀንበር ማንሳት፣ የሚያፌዘውን ዓለም ንቀትና ማንጓጠጥ መቻል በነበረባቸው፤ እምነትንና ትዕግስትን የሚፈታተን እጅግ አስቸጋሪ ፈተና ነበር።GCAmh 293.4

    ነገር ግን ይህ ቅር መሰኘት በክርስቶስ የመጀመሪያ ምፅዓት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን የገጠማቸውን ያህል ከባድ አልነበረም። ክርስቶስ በድል ክብር ወደ የሩሳሌም ሲሄድ ተከታዮቹ በዳዊት ዙፋን ላይ እንደሚቀመጥና እሥራኤልን ከጨቋኝ ገዥዎችዋ እንደሚታደጋት አምነው ነበር። በታላቅ ተስፋና ሀሴት በተሞላበት ናፍቆት ለንጉሣቸው የተሻለ ክብር ለማሳየት እርስ በእርስ ይሽቀዳደሙ ነበር። ብዙዎች ከላይ የደረቡትን ልብሳቸውን እያወለቁ እንደምንጣፍ በፊቱ ይዘረጉ ነበር፤ ወይም የዘንባባ ዝንጣፊዎችን ወስደው መሬት ላይ ያነጥፉ ነበር። በቀለጠ ደስታቸው ውስጥ ሆነው በአንድ ላይ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ” [ማቴ 21÷15] እያሉ ያሞግሱት ነበር። እየገነፈለ በነበረው ደስታ የተረበሹትና የተናደዱት ፈሪሳዊያን ደቀ መዛሙርቱን እንዲገስጽ በወደዱ ጊዜ እንዲህ አላቸው “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” [ሉቃ 19÷40]። ትንቢት መፈፀም አለበት። ደቀ መዛሙርቱ የእግዚአብሔርን እቅድ እያከናወኑ ነበር፤ ሆኖም መሪር ቅሬታ አይቀርላቸውም ነበር። የክርስቶስን አሰቃቂ ሞት አይተው በመቃብር ውስጥ ከማጋደማቸው በፊት ያለፉት ግን ጥቂት ቀናት ብቻ ነበሩ። ተስፋ ካደረጉት ውስጥ አንዳች እንኳ ሳይፈፀምላቸው ተስፋቸው ከየሱስ ጋር ሞተ። ክርስቶስ ከመቃብር በድል ተነስቶ እስኪመጣ ድረስ አስቀድሞ በትንቢት መነገሩን “ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሳ” [የሐዋ ሥራ 17÷3] ማስተዋል አልቻሉም ነበር።GCAmh 294.1

    አምስት መቶ ዓመት ቀደም ብሎ እግዚአብሔር በነብዩ ዘካርያስ አማካኝነት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ፤ እነሆ ንጉሥሽ ፃድቅና አዳኝ ነው፤ ትሁትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” [ዘካ 9÷9]። ክርስቶስ ወደ ፍርድና ወደ ሞት እንዲሄድ ደቀ መዛሙርቱ ቢያውቁ ኖሮ ይህንን ትንቢት መፈፀም ባልቻሉ ነበር።GCAmh 294.2

    በተመሳሳይ ሁኔታ ሚለርና ግብረ አበሮቹ ትንቢትን ፈፀሙ፤ መንፈስ አስቀድሞ ለዓለም ሊሰጥ እንደሚገባ የተናገረውን መልእክት ሰበኩ። ነገር ግን ወደ ቅሬታዎቻቸው የሚመሯቸውን ትንቢታት ሙሉ ለሙሉ ቢረዱአቸው፣ ጌታ ከመምጣቱ በፊት ለአሕዛብ ሁሉ የሚሰበክ ሌላ መልእክት እንዳለ ቢያውቁ ኖሮ፣ ለዓለም ያበረከቱትን መልእክት መስጠት ባልቻሉም ነበር። የመጀመሪያውና የሁለተኛው መልአክ መልእክቶች የተሰጡት በትክክለኛው ጊዜ ነበር። እንዲፈጽሙት እግዚአብሔር ያቀደውንም ሥራ አከናውነዋል።GCAmh 294.3

    ጊዜው ካለፈና ክርስቶስ ካልመጣ የአድቬንቲስት አጠቃላይ መዋቅር ይተዋል ብሎ ዓለም አንጋጦ እየተመለከተ ነበር። ሆኖም፣ ብዙዎች በከባድ ፈተና ሲያልፉ እምነታቸውን ቢክዱም ፀንተው የቆሙ ጥቂቶች ነበሩ። የአድቬንት ንቅናቄ ፍሬዎች፣ የመዋረድና ልብን የመመርመር መንፈስ፣ ሥራውን ያጀበው ዓለም-በቃኝ የማለትና የሕይወት መታደስ፣ ይታዩ የነበሩ እነዚህ ውጤቶች፣ ሥራው የእግዚአብሔር እንደነበር ምስክሮች ነበሩ። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስለ ዳግም ምፅዓቱ ስብከት አልመሰከረም ብለው ለመካድ ድፍረቱ አልነበራቸውም፤ በትንቢታዊ ጊዜያት ስሌታቸውም ስህተት እንዳለ ማወቅ አልቻሉም። ተወዳዳሪ የሌላቸው ሊቆች ናቸው የተባሉት ተቃዋሚዎቻቸውም የትንቢታዊ ትርጉማቸውን አካሄድ ለመገልበጥ አልተሳካላቸውም። ልባዊ በሆነ፣ ፀሎት በተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ እውቀት በገለጠላቸው አእምሮዎች፣ ሕያው በሆነው ኃይሉ የቀለጡ ልቦች በመቃተት የደረሱባቸውን አቅዋሞቻቸውን፤ እጅግ ከባድ የሚባሉ የሚያብጠለጥሉ ውግዘቶችን፣ የታዋቂ ሐይማኖታዊ መምህራንና የዓለማዊ-ሊቆችን እጅግ መራር ተቃውሞ የተቋቋሙትን አቅዋሞቻቸውን፤ የምሁራንና የአንደበተ ርዕቱዎችን ጥምር ኃይል፣ የክቡራንና የምናምንቴዎችን የስድብ ፍጥጫና ነቀፋ በጽናት ቆመው መጋፈጥ የቻሉትን አቋሞቻቸውን፤ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ለመተው ይስማሙ ዘንድ አልተቻላቸውም።GCAmh 294.4

    አዎ እውነት ነው፤ ይከናወናል የተባለው ክስተት አልሆነም፤ ነገር ግን ይህ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያላቸውን እምነት ሊያነቃንቀው አልቻለም። በነነዌ ጎዳናዎች፣ ከተማዋ በአርባ ቀናት ውስጥ ትገለበጣለች ብሎ ዮናስ ሲለፍ፣ እግዚአብሔር የነነዌያዊያንን መዋረድ ተቀብሎ የምሕረት ጊዜያቸውን አራዘመላቸው፤ የዮናስ መልእክት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር፤ ነነዌም የተፈተነችው እንደ እርሱ ፈቃድ ነበር። አድቬንቲስቶች ያመኑትም በተመሳሳይ ሁኔታ የፍርድ ማስጠንቀቂያውን እንዲያውጁ እግዚአብሔር እንደመራቸው ነበር። “የሰሙትን ልቦች ሁሉ ፈትንዋል” አሉ፣ “ለጌታ መገለጥም ፍቅር ቀስቅሷል፤ ያለዚያም ከሞላ ጎደል የሚስተዋል፣ ግን በእግዚአብሔር የታወቀ፣ ለመምጣቱ ጥላቻን አምጥቷል። ልባቸውን የሚመረምሩ ሁሉ በዚያን ጊዜ ጌታ ቢመጣ ኖሮ በየትኛው ጎራ ተሰልፈው ይገኙ እንደነበር የሚያሳውቃቸውን መለያ መስመር ዘርግቷል”፤ “አምላካችን ይህ ነው ተስፋ አድርገነዋል ያድነንማል” በማለት ይጮሁ እንደነበር ወይም በዙፋን ከተቀመጠው ፊት፣ ከበጉ ቁጣ ይሸሽጓቸው ዘንድ ድንጋዮችና ተራሮች ውደቁብን ይሉ እንደነበር አሳውቋቸዋል። ስለዚህ እኛም እምናምነው እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ፈትኖአል፣ እምነታቸውን ፈትኖአል፤ በፈተና ሰዓት ያስቀምጣቸው ዘንድ ተገቢ ነው ካለው ስፍራ ይሸሹ እንደሆነ፣ ይህንን ዓለም ትተው በእግዚአብሔር ሥራ [ቃል] በማያወላውል መተማመን ይደገፉ እንደሆነ ሕዝቦቹን ፈትኖ አረጋግጧል።”-The Adent Herald and Signs of the Times Reporter, Vol. 8, No. 14 (Nov 13, 1844)’GCAmh 295.1

    ባለፈው ተሞክሯቸው እግዚአብሔር እንደመራቸው አሁንም ያምኑ የነበሩት ስሜት በዊሊያም ሚለር ቃላት እንዲህ ተገልፆአል፦ “ያኔ የነበረኝ ማረጋገጫ አሁንም ኖሮኝ ሕይወቴን እንደገና የምኖረው ቢሆን ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ታማኝ መሆንን ያኔ እንዳደረኩት አሁንም መድገም አለብኝ” “ከነፍሳት ደም ልብሴን አንጽቻለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በተቻለኝ መጠን ከሚኮነኑበት ኃጢአት ሁሉ ራሴን ነፃ እንዳደረኩ ይሰማኛል።” “ሁለት ጊዜ ቅር ብሰኝም” አለ ሲጽፍ የእግዚአብሔር ሰው፣ “ገና አልተጣልኩም፤ ተስፋም አልቆረጥኩም፤ የክርስቶስ መምጣት ተስፋዬ እንደማንኛውም ጊዜ ጠንካራ ነው። ከዓመታት የምር ማሰላሰል በኋላ የከበረ ኃላፊነቴ መስሎ የተሰማኝን ብቻ አድርጌአለሁ። አጥፍቼ ከሆነ፣ ጥፋቴ በፍቅር የተደረገ ነው፤ ለባልንጀራዬ ያለኝ ፍቅር፣ ለእግዚአብሔር ላለብኝ ኃላፊነት መሰጠቴ ነው። የማውቀው አንድ ነገር ቢኖር ካመንኩበት በቀር አንዳች አልሰበኩም፤ የእግዚአብሔር እጅ ከእኔ ጋር ነበረች፤ ኃይሉ በሥራው ላይ ተገልጧል፤ ብዙ መልካም ነገርም ተከናውኖአል።” “ከሁሉም አይነት ሰው የተውጣጡ ብዙ ሺዎች፣ በዘመኑ ስብከት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ሆነዋል። በዚያም ምክንያት በእምነታቸውና በክርስቶስ ደም ታጥበው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀዋል።”-Bliss, ገጽ, 256, 255, 277, 280, 281’ “የኩራተኞችን ፈገግታ ለማግኘት በጭራሽ ጥሬ አላውቅም፣ ዓለም ግንባርዋን ስትቋጥርም አልተሸማቀቅሁም። አሁን ድጋፋቸውን አልገዛም፣ ጥላቻቸውንም ለመፈተን ከሥራዬ አልፌ አልሄድም። ሕይወቴን ከእጃቸው በጭራሽ አልለምንም፤ እግዚአብሔር እንደመልካም ቸርነቱ ካዘዘም ሕይወቴን ከማጣት እንደማላፈገፍግ ተስፋ አደርጋለሁ።”-J. White, Life of Wm. Miller, page 315’GCAmh 295.2

    እግዚአብሔር ሕዝቦቹን አልጣለም፤ የተቀበሉትን ብርሐን በችኮላ ካልካዱት ጋር የአድቬንትንም እንቅስቃሴ ካላወገዙት ጋር የእግዚአብሔር መንፈስ አሁንም ያድር ነበር። ወደ ዕብራውያን በተላከው መልእክት ውስጥ የማበረታቻና በዚህ ችግር ውስጥ እየጠበቁ ላሉ ለተፈተኑ የማስጠንቀቂያ ቃል አለ፦ “እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም። ፃድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።” [ዕብ 10÷35-39]።GCAmh 296.1

    ይህ ተግሳጽ በመጨረሻው ዘመን ላለችው ቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠ የጌታን በቅርብ መምጣት ከሚጠቁሙት ቃላት መረዳት ይቻላል። “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም።” እውነት የሚመስል መዘግየት እንዳለ በግልጽ የሚያመላክት፣ ጌታ እንደሚዘገይ የሚያሳይ ነገር አለ። እዚህ ላይ የተሰጠው ትምህርት በዚህ ዘመን ላሉ አድቬንቲስቶች ተሞክሮ በተለየ ሁኔታ እንዲስማማ የተደረገ ነው። እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች እምነታቸውን የሚያንኮታኩት አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። የቃሉንና የመንፈሱን ምሪት በመከተል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽመዋል፤ ሆኖም ባለፈው ተሞክሮአቸው የእርሱን አላማ መረዳት፣ በፊታቸውም ያለውን ጎዳና ማወቅ አልቻሉምና በእርግጥም ሲመራቸው የነበረው እግዚአብሔር መሆኑን የመጠራጠር ፈተና ውስጥ ወደቁ። “ፃድቅ ግን በእምነት ይኖራል” የሚሉት ቃላት አሁን ጥቅም ላይ ዋሉ። “የእኩለ-ሌሊቱ ጩኸት” ቦግ ያለ ብርሐን መንገዳቸውን ሲያበራ ሳለ፣ ትንቢታትም ሲከፈቱ፣ የክርስቶስ ምፅዓት ቅርብ መሆኑን የሚናገሩት ምልክቶችም በፍጥነት ሲፈፀሙ ሲመለከቱ፣ [በአይን] እያዩ ይራመዱ ነበር። አሁን ግን ባልተፈፀሙ ተስፋዎች ጎብጠው፣ ቀጥ ብለው መቆም የሚችሉት በእግዚአብሔርና በቃሉ ባላቸው እምነት ብቻ ነበር። የሚያፌዘው ዓለም እንዲህ ይል ነበር፦ “ተታላችኋል፣ እምነታችሁን ተው፣ የአድቬንት እንቅስቃሴም ከሰይጣን ነበር በሉ።” የእግዚአብሔር ቃል ግን የተናገረው “ወደኋላ ቢያፈገፍግ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” የሚል ነው። እምነታቸውን አሁን በገሃድ መተው፣ ከመልእክቱ ጋር የነበረውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መካድ፣ ወደ ጥፋት ማፈግፈግ ይሆናል። ፀንተው ይቆሙ ዘንድ በጳውሎስ ቃላት ተበረታቱ። “መጽናት ያስፈልጋችኋልና።” “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም።” ብቸኛው አደጋ የሌለበት መንገድ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ብርሐን ዋጋ በመስጠት፣ ተስፋዎቹን አጥብቀው በመያዝ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር መቀጠልና ተጨማሪ ብርሐን እስኪያገኙ ድረስ መጠበቅና መቆየት ነበር።GCAmh 296.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents