Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ምዕራፍ ፴፬—መናፍስታዊነት - ሙታን ወገኖቻችን ሊያናግሩን ይችላሉን?

    በቅዱስ መጻሕፍት እንደተቀመጠው የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት ለእያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ እጅግ አጽናኝና የከበረ ዋጋ ያለው ነው። ነገር ግን በብዛት ተቀባይነት ባገኘው የስነ-መለኮት ትምህርት ስህተቶች አማካኝነት በዚህ ነጥብ ላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተጋርዶና ተጣምሞ ይገኛል። መጀመሪያ ከጣዖት አምልኮ በውሰት የተወሰደው በኋላም በታላቁ የክህደት ጽልመት ወደ ክርስትና እምነት የተዋሃደው የነፍስ አትሞትም አስተምህሮ “ሙታን አንዳች አያውቁም” [መክ 9÷5] በማለት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያስተምረውን እውነት ተክቶታል። “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት” [ዕብ 1÷14] የሙታን መናፍስት እንደሆኑ እልፍ አዕላፋት አምነዋል። ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ገና ሞትን ሳይቀምስ ስለ ሰማያዊ መላእክት መኖርና ከሰው ታሪክ ጋር ስላለው ግንኙነት መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምስክርነት ገሸሽ በማድረግ ነው።GCAmh 399.1

    ሰው ሞቶም ንቃተ ህሊናው እንዳለነ ነው የሚለው አስተምህሮ በተለይም የሞቱ ሰዎች መናፍስት ሕያዋንን ለማገልገል ይመለሳሉ የሚለው እምነት ለዘመናዊ መናፍስታዊነት መንገድ ጠርጓል። ሙታን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ቅዱሳን መላእክት ፊት መቅረብ ከቻሉ እንዲሁም በፊት ከነበራቸው ይልቅ እጅግ በላቀ እውቀት ተባርከው ከሆነ ሕያዋንን በእውቀት ለማቅናትና ለማስተማር ለምን ወደ ምድር አይመለሱም? ዝነኛ የስነ መለኮት መምህራን እንደሚያስተምሩት የሙታን መናፍስት ምድር ላይ ባሉ ወዳጆቻቸው ዙሪያ የሚያንዣብቡ ከሆነ፣ ከክፋት ያስጠነቅቋቸው ዘንድ ወይም ከሃዘን ያጽናኑዋቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር እንዲነጋገሩ ለምን አይፈቀድላቸውም? ሰው ከሞተ በኋላም ንቃተ ህሊናው አይሞትም ብለው የሚያምኑ እነርሱ ከፍ ከፍ ባሉ መናፍስት አማካኝነት እንደመለኮት ብርሐን ወደ እነርሱ የሚመጣውን እንዴት እምቢ ማለት ይቻላቸዋል? ይህ ቅዱስ መስሎ የሚታየው መንገድ አላማዎቹን ያሳካ ዘንድ ሰይጣን የሚሰራበት ዘዴ ነው። የእርሱን ትዕዛዝ የሚጠብቁ የወደቁ መላእክት ከመናፍስት ዓለም የመጡ መልዕክተኞች እንደሆኑ ያስመስላሉ። ሕያዋንን ከሙታን ጋር እንደሚያገናኛቸው በሚናገርበት ጊዜ የክፋት ልዑል የአስማታዊ ተጽዕኖውን በአዕምሯቸው ላይ ያሳርፋል።GCAmh 399.2

    ሰይጣን የሞቱ ወዳጆቻቸውን ምስል በሰዎች ፊት የማቅረብ ኃይል አለው። እውነት የሚመስል ምትኩ (የማስመሰል ኃይሉ) ፍፁም ነው። ተመሳሳይ ገጽታው፣ ቃላቶቹ፣ የድምጽ ቃናው፣ በሚያስደንቅና ልቅም ባለ ተመሳሳይነት በድጋሜ ይሰራሉ። የሚወዱአቸው እነርሱ የሰማይን ፍፁም ደስታ እያጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጣቸው ብዙዎች ይጽናናሉ። አደጋ እንዳለበት ሳይጠረጥሩም “የሚያስቱ መናፍስትና የአጋንንትን ትምህርት” ለመስማት ጀሮአቸውን ይሰጣሉ [1ኛ ጢሞ 4÷1]።GCAmh 399.3

    ሙታን ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር እንደሚመለሱ እንዲያምኑ ከተመሩ በኋላ የሞቱት ሰዎች ሳይዘጋጁ ወደ መቃብር እንደወረዱ አድርጎ ሰይጣን ያስመስላቸዋል። በሰማይ ደስተኛ እንደሆኑ፣ እንዲያውም ከፍተኛ ደረጃ እንደያዙ ይናገራሉ፤ በእንዲህም ሁኔታ በፃድቁና በኃጥኡ መካከል ልዩነት እንደሌለ ተደርጎ ስህተቱ በስፋት ይስተማራል። በአስመሳይነት የቀረቡት ከመናፍስት ዓለም የመጡ እንደሆኑ የተደረጉት ጎብኝዎች እውነትነት ያላቸው ማስጠንቀቂያዎችና ተግሳፆች አልፎ አልፎ ይናገራሉ። ተአማኒነቱ እየጎለበተ ሲሄድም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለውን እምነት በቀጥታ የሚያኮስስ አስተምህሮ ያቀርባሉ። በምድር ስላሉት ወዳጆቻቸው ደህንነት ጥልቅ ፍላጎት እንዳላቸው በማስመሰል እጅግ አደገኛ የሆኑ ስህተቶችን በተዘዋዋሪ ይናገራሉ። አንዳንድ እውነት መናገራቸውንና አንዳንድ ጊዜም የወደፊት ክስተቶችን መተንበይ መቻላቸው ለንግግሮቻቸው የተአማኒነት መልክ ያጎናጽፋቸዋል፤ እጅግ የተቀደሱት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንደሆኑ ተደርገው፣ ያለምንም ጥርጣሬ ታምነው፣ በእልፍ አዕላፋት በቀላሉ ተቀባይነት ያገኛሉ። የእግዚአብሔር ሕግ ወደ ጎን ይገፋል፤ የፀጋ መንፈስ ይንቋሸሻል፤ የቃል ኪዳኑ ደምም ቅዱስ እንዳልሆነ ነገር ተደርጎ ይቆጠራል። መናፍስቱ የክርስቶስን መለኮታዊነት ይክዳሉ፤ እንዲያውም ፈጣሪን ከእነርሱ ደረጃ ጋር እኩል ያስቀምጣሉ። በእንደዚህ አይነት አዲስ ሽፋን በሰማይ የጀመረውንና በምድር ላይ ለስድስት ሺህ ዓመት የቀጠለውን በእግዚአብሔር ላይ ያነሳውን ጦርነት ታላቁ አማፂ ወደፊት ቀጥሎበታል።GCAmh 399.4

    የመንፈሳዊ መገለፆች፤ ማዕከሉ (አገናኙ) የሚተውናቸው ማጭበርበሪያዎችና ማታለያዎች እንደሆኑ አድርገው ለማስቆጠር ብዙዎች ይጥራሉ። የማታለል ተግባራት ተደብቀው እንደ እውነተኛ መገለጥ ተደርገው መወሰዳቸው እውነት ቢሆንም ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይልም በግልጽ ሲንፀባረቅ ቆይቷል። ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ በማውራት የተጀመረው ዘመናዊ መናፍስታዊነት የሰብአዊ ፍጡር ማታለያ ወይም ማጭበርበሪያ ውጤት ሳይሆን፣ ነፍሳትን ከሚያወድሙ እጅግ ከተዋጣላቸው ማታለያዎች አንዱ የሆነውን መንገድ በእንዲህ ሁኔታ ያስተዋወቁት የርኩሳን መላእክት ቀጥተኛ ሥራ ነው። መናፍስታዊነት ከፍጡር አስመሳይነት የዘለለ አይደለም ብለው በማመን ብዙዎች በወጥመድ ይያዛሉ፤ ከሰብዓዊ ባህርይ ውጪ ናቸው ከማለት በቀር ሌላ ፍርጃ በማይሰጧቸው ክስተቶች ፊት ለፊት ሲፋጠጡ፣ ይታለላሉ። የእግዚአብሔር ታላቅ ኃይል እንደሆኑ አድርገው እንዲቀበሏቸው ይመራሉ።GCAmh 400.1

    እነዚህ ሰዎች ሰይጣንና ወኪሎቹ ለሚያከናውኑአቸው ድንቅና ተዓምራት በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠውን ምስክርነት ቸል ይላሉ። የፈርኦን አስማተኞች የእግዚአብሔርን ሥራ አስመስለው ይተውኑ ዘንድ የተቻላቸው በሰይጣናዊ እርዳታ ነበር። ከክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በፊት ተመሳሳይ የሆነ ሰይጣናዊ ኃይል እንደሚገለጥ ጳውሎስ ይመሰክራል። የጌታ መገለጥ “በተዓምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኛ ድንቆችም በዓመጽም በመታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሰራር” [2ኛ ተሰሎ 2÷9፣10] ከሚሆነው ክስተት በኋላ ይሆናል። ሐዋርያው ዮሐንስም በመጨረሻው ቀን የሚሆነውን ተዓምር ሰሪ ኃይል ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል። ከተሰጡት ምልክቶች የተነሳ በምድር የሚኖሩትን ያስታል።” [ራዕይ 13÷13፣14]። እዚህ ላይ የተተነበዩት እንዲሁ ተራ የሆኑ አስመሳይነቶች አይደሉም። ሰዎች እየተታለሉ ያሉት የሰይጣን ወኪሎች ለመፈፀም ኃይል ባላቸው ተዓምራት እንጂ እናደርጋቸዋለን ብለው በሚያስመስሏቸው ሙከራዎች አይደለም።GCAmh 400.2

    የምጡቅ አዕምሮውን ኃይላት የማታለል ሥራ ላይ ይውሉ ዘንድ የገበረው የጨለማው ልዑል ማሳሳቻዎቹ ለሁሉም የሰው ልጅ መደቦችና ሁኔታዎች እንዲገጥሙ አድርጎ በብልሃት ያበጃጃቸዋል። የጠራና ጨዋ ማንነት ላላቸው ሰዎች መናፍስታዊነትን በተሻለ ጥራት እንዲሁም የማሰብና የመመራመር መልክ አላብሶ በማቅረብ ብዙዎችን ወደ ወጥመዱ ለመሳብ የሚሳካለት ይሆናል። መናፍስታዊነት የሚያካፍለው ጥበብ በሐዋርያው ያዕቆብ የተገለጠው አይነት ሲሆን “ከላይ የሚወርድ አይደለም ነገር ግን የምድር ነው፤ የስጋም ነው፤ የአጋንንትም ነው” [ያዕቆ 3÷15]። መደበቅ (መሸፋፈን) አላማውን የበለጠ ሲገጥምለት ግን ታላቁ አታላይ ይህንን ይደብቀዋል። የሰማያዊ ሱራፌሎችን ብርሐን ተላብሶ በፈተናው ምድረ በዳ በክርስቶስ ፊት የቀረበው እርሱ፣ ተወዳዳሪ የሌለውን የሚስብ ውበት ተላብሶ የብርሐን መልአክ ሆኖ ወደ ሰዎች ይመጣል። ቀልብን የሚማርኩ ርዕሶችን በማቅረብ ስለ አመክንዮ ተማጽዕኖ ያቀርባል፤ በሚያስፈነድቁ ትዕይንቶች ምናብን (ስሜትን) ያስደስታል፤ ስለ ፍቅርና ችሮታ በአንደበተ ርቱዕ አቀራረብ በመናገር ፍቅርን ማግኘት ይችላል። አስተሳሰብን በማነሳሳት፣ ኃሳብን አግዝፎ በማንሳፈፍ ሰዎች በራሳቸው ጥበብ ታላቅ ኩራት እንዲሰማቸው በማድረግ በልባቸው ዘላለማዊ እግዚአብሔርን እንዲያቀልሉ (እንዲንቁ) ያደርጋቸዋል። የዓለምን አዳኝ እጅግ ከፍታ ወዳለው ተራራ ወስዶ፣ የዓለምን ሁሉ ነገሥታት ከነክብራቸው በፊቱ ያቀረበለት ያ ኃያል ፍጡር በመለኮታዊ ኃይል ያልተከለሉትን ሁሉ የስሜት ህዋሳቶቻቸውን (አስተሳሰባቸውን) ማጣመም በሚችልበት አኳኋን ፈተናዎቹን ለሰዎች ያቀርባል።GCAmh 400.3

    በሚያማልሉ ቃላት፣ የተከለከለ እውቀትን ለማግኘት ያለውን ፍላጎት በማቀጣጠል፣ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ምኞትን በማነሳሳት ሔዋንን በኤደን ገነት እንዳሳሳተ ሁሉ ዛሬም ሰይጣን ሰዎችን ያታልላል። ራሱ ለውድቀት የተዳረገው እነዚህን ክፋቶች ማበረታታቱ ነበር፤ እናም በእነዚሁ ክፋቶች አማካኝነት የሰውን ውድመት እውን ለማድረግ ያልማል። “እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ” ይላል “ክፉና በጎን ታውቃላችሁ” [ዘፍ 3÷5]። መናፍስታዊነት “ሰው የእድገት (የለውጥ) ፍጥረት ነው፤ ከመወለዱ ጀምሮ ለማደግ፣ እንዲያውም እስከ ዘላለም ወደ እግዚአብሔር አብነት ለመድረስ፣ ዕድል ፈንታው (መዳረሻው) ነው” በማለት ያስተምራል። እንደገናም “እያንዳንዱ ህሊና በራሱ ላይ ይፈርዳል እንጂ በሌላው ላይ አይበይንም” “ፍርዱም ትክክል ይሆናል ምክንያቱም የራስ ፍርድ ነው… ዙፋኑ በራስህ/በራስሽ ውስጥ ነው” ይላል። በውስጡ ያለው “መንፈሳዊው ንቃተ ህሊናው” ሲነቃ አንድ የመናፍስታዊ አስተማሪ እንዲህ አለ፦ “ባልንጀሮቼ ሁሉም ያልወደቁ ግማሽ አማልክት ነበሩ” አለ። ሌላኛው ሲናገር “ትክክልና ፍፁም የሆነ ማንኛውም ፍጡር እርሱ ክርስቶስ ነው” ብሏል።GCAmh 401.1

    በመሆኑም የእውነተኛ አክብሮት ምክንያት መሆን በሚገባው በእግዚአብሔር ፃድቅነትና ፍጽምና ፈንታ፣ የሰው ልጅ የሚደርስበት ደረጃ ትክክለኛ መለኪያና ፍፁም ፃድቅ በሆነው በሕጉ ቦታ፣ በብቸኝነት ሊመለክ የሚገባው፣ ብቸኛው የፍርድ መመሪያ ወይም የባህርይ መመዘኛ የሚሆነው፣ ኃጢአተኛውና ስህተት የሚሰራው፣ የሰው የራሱ ባህርይ እንደሆነ አድርጎ ሰይጣን ተክቶታል። ይህ ሽቅብ ሳይሆን ቁልቁል የሆነ እመርታ ነው።GCAmh 401.2

    በማየት እንለወጣለን የሚለው ሕግ፣ የአዕምሮና የመንፈሳዊ ተፈጥሮ፣ የሁለቱም ሕግ ነው። አዕምሮ፣እንዲያብሰለስለው ከተፈቀደለት ሐሳብ ጋር ቀስ በቀስ ራሱን እያስማማ ይሄዳል። እንዲወደውና እንዲያከብረው ተደርጎ የተለማመደውን እየመሰለ ይሄዳል። ሰው ከራሱ የንጽህና፣ የመልካምነት ወይም የእውነት ደረጃ በላይ ከፍ ሊል ፈጽሞ አይችልም። [ይደርስበት ዘንድ የሚመኘው] የመጨረሻ ከፍታው እኔነት ከሆነ ከዚያ የተሻለ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ፈጽሞ ሊደርስ አይችልም። ከዚያ ይልቅ በቀጣይነት ዝቅ ዝቅ እያለ እየሰጠመ ይሄዳል። ሰውን ከፍ የማድረግ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ፀጋ ብቻ ነው። ለራሱ ከተተወ፣ መንገዱ ቁልቁል የሚወርድ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው።GCAmh 401.3

    በተሻለ ከነጠረውና ከብልሁ ይልቅ፣ የራሱን ፍላጎት በገደብ የለሽነት ለሚያራምደው፣ ለደስታ (pleasure) አፍቃሪውና ለፍትወተኛው፣ መናፍስታዊነት ያን ያህል በማያታልል ሁኔታ፣ ራሱን ሳይደብቅ ይቀርባል። እንዲሁ በጥቅሉ ሲመለከቱት ከዝንባሌዎቻቸው ጋር የተስማማ የሆነ ነገር ያገኛሉ። ሰይጣን የሰብአዊ ተፈጥሮን ደካማ ጎን የሚያሳየውን እያንዳንዱን ምልክት ያጠናል፤ እያንዳንዱ ሰው ሊሰራው የሚዳዳው ኃጢአት ላይ ምልክት ያደርጋል፤ ክፋት ለመሥራት ያለውን ዝንባሌ ለመቆስቆስ እድሎች እንዳይጠፉ ጥንቃቄ ያደርጋል። ቢደረግ በራሱ ህገ-ወጥ ያልሆነውን ነገር ከልክ በላይ እንዲያደርጉት በመፈተን መጠንን በመጣስ አማካኝነት አካላዊ፣ አዕምሯዊና ግብረ-ገባዊ ኃይላቸውን እንዲያደክሙ ያደርጋቸዋል። ፍላጎትን በማርካት አባዜ በሺዎች የሚቆጠሩትን አውድሟቸዋል፤ አሁንም እያጠፋቸው ነው። በዚህም አጠቃላይ የሰውን ተፈጥሮ የጨካኔ መልክ አላብሶታል። ሥራውንም ለመቀምቀም በመናፍስቱ አማካኝነት “እውነተኛ እውቀት የሰውን ልጅ ከሁሉም ሕግ በላይ ያደርገዋል።” “ምንም ቢሆን፣ ትክክል ስለሆነ እግዚአብሔር አይኮንንም”፤ “የሚፈፀሙ ኃጢአቶች ሁሉም የሚደረጉት ከቅንነት ነው” በማለት ይናገራል። የሰዎች ፍላጎት የመጨረሻው፣ ከፍተኛው ሕግ እንደሆነ እንዲያምኑ በሚመሩበት ጊዜ ነፃነት እንዳሻቸው የሚጠቀሙበት ፈቃድ እንደሆነ፣ ሰውም ተጠያቂነቱ ለራሱ ብቻ እንደሆነ እንዲያምኑ ሲሆኑ፣ ብልሹነትና የሞራል ዝቅጠት በእያንዳንዱ እጅ ላይ የተትረፈረፈ ቢሆን ማን ይገረማል? እልፍ አዕላፋት ስጋዊ ልባቸው እንዲያደርጉት የሚያነሳሳቸውን ነገሮች ለመፈፀም ነፃነት የሚሰጧቸውን ትምህርቶች በጉጉት ይቀበላሉ። ራስን የመቆጣጠር ልጓም በከፍተኛ ፍላጎት አንገት ላይ ይጋደማል፤ የአዕምሮና የነፍስ ኃይላት በእንስሳዊ ዝንባሌዎች ሥር ይደረጋሉ፤ ከዚያም ሰይጣን እየተፍነከነከ የክርስቶስ ተከታይ ነን የሚሉትን፣ በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ መረቡ ጠርጎ ያስገባቸዋል።GCAmh 402.1

    በመናፍስታዊ የሐሰት አባባሎች ግን ማንም ሊታለል አይገባውም። ወጥመዱን ማየት ይቻላቸው ዘንድ እግዚአብሔር ለዓለም በቂ ብርሐን ሰጥቷል። ከወዲሁ እንደታየው የመናፍስታዊነትን መሰረት ያነፀው ጽንሰ ሐሳብ እጅግ ግልጽ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ጋር ጦርነት ላይ ነው። ሙታን ምንም እንደማያውቁ፣ ሀሳባቸውም እንደጠፋ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ከፀሐይ በታች በሚከናወን ማናቸውም ነገር ላይ ዕድል ፈንታ የላቸውም፤ በምድር ላይ ስላሉ እጅግ የሚወዷቸው ሰዎች ደስታም ይሁን ኃዘን ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።GCAmh 402.2

    በተጨማሪም ከሞቱ ሰዎች መናፍስት ጋር እንደሚደረግ የሚመስለውን ግንኙነት ሁሉ እግዚአብሔር በግልጽ ከልክሏል። እንደዛሬዎቹ መናፍስት ጠሪዎች ሁሉ በዕብራዊያን ዘመንም ከሙታን ጋር እንደሚነጋገሩ የሚያትቱ መደቦች ነበሩ። ነገር ግን “የተለመዱ መናስፍት” ተብለው ይጠሩ የነበሩት እነዚህ ከሌላ ዓለም የመጡ ጎብኚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ “የአጋንንት መናፍስት” በመባል ይጠራሉ [ዘሁል 25÷1-3፤ መዝሙር 106÷28፤ 1ኛ ቆሮ 10÷20፤ ራዕይ 16÷14]። ከተለመዱ መናፍስት ጋር የሚደረገው ግንኙነት በጌታ ዘንድ ፀያፍ እንደሆነ፣ በሞት ቅጣትም የሚያስቀጣ ፍፁም የተከለከለ እንደሆነ ተነግሯል [ዘለዋ 19÷31፤ 20÷27]። የጥንቆላ ስም ራሱ አሁን እንደ ስድብ የሚታይ ነው። ሰዎች ከርኩስ መናፍስት ጋር ግንኙነት መፈፀም ይችላሉ የሚለው አባባል የጨለማው ዘመን አፈ ታሪክ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ነገር ግን በመቶ ሺዎች፣ አዎ በሚሊየኖች ምዕመናት ያሉት፣ በሳይንሳዊ ክበባት ውስጥ የገባው፣ አብያተ ክርስቲያናትን የወረረው፣ በሕግ አውጪ አካላት ዘንድ፣ በነገሥታት ሰገነቶች ጭምር ተቀባይነት ያገኘው፣ መናፍስታዊነት፣ ይህ ግዙፍ ማታለያ ግን በአዲስ የማታለያ ካባ የተነቃቃው፣ ጥንቆላ ተብሎ በጥንት ዘመን የተኮነነውና የተከለከለው ራሱ ነው።GCAmh 402.3

    የመናፍስታዊነትን እውነተኛ ባህርይ ለማወቅ ሌሎች ማስረጃዎች ባይኖሩ እንኳ፣ መናፍስቶቹ በጽድቅና በኃጢአት መካከል፣ እጅግ በከበሩትና በንፁሆቹ የክርስቶስ ሐዋርያትና እጅግ በተበላሹት የሰይጣን አገልጋዮች መካከል ልዩነት አለማድረጋቸው ለክርስቲያኑ በቂ ምስክር ነው። በሰው መካከል እጅግ የረከሱ ሰዎች ሰማይ እንደገቡና እዛም ከፍ ከፍ እንዳሉ በማሳየት ሰይጣን ለዓለም እንዲህ ይላል፦ “ምንም ያህል ኃጢአተኛ ብትሆን ምንም አይደለም፤ እግዚአብሔርንና መጽሐፍ ቅዱስን ብታምን ወይም ባታምን ምንም አይደል፤ እንዳሻህ ሆነህ ኑር፤ ሰማይ ያንተ ቤት ነው።” መናፍስታዊ አስተማሪዎች እንዲህ ብለው ያውጃሉ፦ “ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፤ እርሱም በእነርሱ ዘንድ ደስ ይለዋል። “ወይስ የፍርድ አምላክ ወዴት አለ?” [ሚል 2÷17] የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ ጨለማውንም ብርሐን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ… ወዮላቸው።” [ኢሳ 5÷20]።GCAmh 403.1

    በእነዚህ ውሸታም መናፍስት ተመስለው የሚቀርቡት ሐዋርያት፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካኝነት ምድር ላይ ሳሉ የፃፉትን እንዲቃረኑ ይደረጋሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ መለኮት መሆኑን ይክዳሉ። በዚህም የክርስቲያኑን የተስፋ መሰረት በመቦጫጨቅ ወደ ሰማይ የሚወስደውን መንገድ የሚገልጠውን ብርሀን ያጠፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ተራ ልብ ወለድ እንደሆነ፣ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ለሰብአዊ ዘር የቀድሞው ትውልድ የሚገጥም፣ አሁን ግን እንደ ዘመን-ያለፈበት ተደርጎ እንዲናቅ ወይም ወደ ጎን እንዲገፋ ዓለምን ለማሳመን ሰይጣን እየሰራ ነው። የእግዚአብሔርንም ቃል ቦታ ይወስድ ዘንድ መንፈሳዊ መገለጦችን ያቀርባል። ይህ ሙሉ ለሙሉ በእርሱ ቁጥጥር ስር የሆነ መስመር ነው፤ በዚህ አማካኝነት እርሱ ማን እንደሆነ ዓለምን ማሳመን ይችላል። በእርሱና በተከታቹ ላይ ይፈርድ ዘንድ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ልክ እርሱ የሚፈልገው ቦታ፣ በጽልመት ስር ያስቀምጠዋል፤ የዓለምን አዳኝ ከአንድ ተራ ሰው ያልበለጠ እንደሆነ ያደርገዋል። የየሱስን መቃብር ይጠብቁ የነበሩት ሮማዊ ወታደሮች ትንሳኤውን ያስተባብሉ ዘንድ ካህናቱና ሽማግሌዎቹ በአንደበታቸው ያስቀመጡላቸውን የሐሰት ዜና እንዳሰራጩ ሁሉ በመንፈሳዊ መገለጦች የሚያምኑትም እንዲሁ በአዳኛችን ሕይወት ዙሪያ ምንም ተዓምራዊ የሆነ ነገር እንደሌለ ሊያስመስሉ ይሞክራሉ። ክርስቶስን ከመጋረጃው ጀርባ ለማድረግ ጥረት ካደረጉ በኋላ ወደራሳቸው ተዓምራት ትኩረት በመሳብ የእነርሱ ሥራዎች ከክርስቶስ እጅግ የላቁ እንደሆኑ ይናገራሉ።GCAmh 403.2

    በአሁኑ ጊዜ መናፍስታዊነት መልኩን እየቀየረ መሆኑ እሙን ነው። የበለጠ ጥያቄ የሚያስነሱትን ባህርያቱን በመደበቅ የክርስቲያን ገጽታ እየያዘ ነው። ነገር ግን ከመድረኩና ከህትመት የሚወጡት ንግግሮቹ በሕዝብ ፊት ለብዙ ዓመታት ኖረዋል፤ በዚህም ትክክለኛ ማንነቱ ተገልጦአል። እነዚህ ትምህርቶች ሊካዱ ወይም ሊደበቁ አይችሉም።GCAmh 403.3

    አሁን ያለበት ደረጃም ቢሆን ከቀድሞው ጊዜ የተሻለ እንዲታገሱት ከማድረግ የራቀ ነው፤ እንዲያውም የበለጠ አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም የበለጠ የጮሌ ማታለያ ስልት ይዟልና። ቀደም ባለው ጊዜ ክርስቶስንና መጽሐፍ ቅዱስን ሲያወግዝ የነበረ ቢሆንም አሁን ሁለቱንም እንደሚቀበል ይመሰክራል። ነገር ግን የከበሩትና አስፈላጊ እውነቶቹ ምንም ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ ተደርገው ሳለ መጽሐፍ ቅዱስ ላልተለወጠው ልብ አስደሳች እንዲሆን ተደርጎ ይተረጎማል። ፍቅር ዋነኛው የእግዚአብሔር ባህርይ መሆኑ ቢቀርብም ወደ ደካማ ስሜታዊነት ቀጭጮ በመልካምና በክፋት መካከል የሚያስቀምጠው ልዩነት ኢምንት ይሆናል። የእግዚአብሔር ፍርድ፣ የኃጢአት ውግዘቱና የቅዱስ ሕጉ መጠይቆች ከእይታ ውጪ ይደረጋሉ። ሰዎች፣ ሕጉ (አሥርቱ ትዕዛዛት) ሙት የሆነ ደብዳቤ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት ይማራሉ። አስደሳችና አነሁላይ (አስማታዊ) ተረቶች ስሜትን እንዲያቅበጠብጡ ይደረግና፣ ሰዎች የእምነታቸው መሰረት መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን እንዳይቀበሉ ይመራሉ። ክርስቶስ ልክ እንደበፊቱ ይካዳል፤ ነገር ግን ሰይጣን የሕዝቡን አይን እጅግ ስላሳወረው ማታለያው አይስተዋልም።GCAmh 404.1

    የመናፍስታዊነት አታላይ ኃይልና በተጽዕኖውም ስር የመውደቅ አደጋው ትክክለኛ መረዳት ያላቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። እንዲያው ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ለማርካት ሲሉ ብዙዎች ይጎነትሉታል። በእርሱ ላይ [በመናፍስታዊነት] እውነተኛ እምነት የላቸውም፤ በመንፈሱ ቁጥጥር ስር ብንሆንስ ብለው ሲያስቡትም በድንጋጤ ይሞላሉ። እነዚህ ሰዎች ግን በተከለከለ ምድር ላይ ለመቆም ይደፍራሉ፤ ኃያሉ አጥፊም ያለፈቃዳቸው ኃይሉን ይተገብርባቸዋል። በእርሱ ትዕዛዝ ስር አዕምሮአቸውን ለማስገዛት አንድ ጊዜ እንዲግባቡ ከተደረጉ፣ ከዚያ ወዲያ እስረኛው አድርጎ ይይዛቸዋል። ከዚያ የሚያነሆልል አታላይ ድግምት ለመላቀቅ በራሳቸው ኃይል ፈጽሞ የማይቻላቸው ይሆናሉ። በእምነት ከልብ ለሚፀልይ ፀሎት መልስ ሆኖ ከሚመጣው ከእግዚአብሔር ኃይል ብቻ በቀር እነዚህን በወጥመድ የገቡ ነፍሳት ነፃ ሊያወጣ የሚችል አንዳች ኃይል የለም።GCAmh 404.2

    ኃጢአት ያዘለን ባህርይ ለመተግበር ልቅ የሚሆኑ ወይም የሚታወቅ ኃጢአትን በፈቃዳቸው የሚያበረታቱ እነርሱ የሰይጣንን ፈተናዎች የሚጋብዙ ናቸው። ከእግዚአብሔር እንዲሁም ከመላእክቱ ጥንቁቅ ጥበቃ ራሳቸውን ይነጥላሉ፤ ክፉው ማሳሳቻዎቹን ሲያቀርብ፣ ያለ መከላከያ ምሽግ ይሆናሉ። ቀላል ታዳኝ ሆነውም ይወድቃሉ። ስለዚህ በእርሱ ኃይል ስር ራሳቸውን ያስቀመጡ እነርሱ የአቅጣጫቸው ፍፃሜ የት እንደሆነ እምብዛም አያስተውሉም። መሸነፋቸውን ካረጋገጠ በኋላ፣ ሌሎችን እያታለሉ ወደ ውድመት ያመጡ ዘንድ ፈታኙ ሰራተኛ አድርጎ በወኪልነት ይቀጥራቸዋል።GCAmh 404.3

    ነብዩ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፦ “የሚጮኹትንና ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፣ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን? ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም [በውስጣቸው ብርሐን ስለሌለ ነው/if they speak not according to this word, it is because there is no light in them]” [ኢሳ 8÷19፣20]። ስለ ሰው ተፈጥሮና ስለሙታን ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተቀመጠውን ለመቀበል ሰዎች ፈቃደኛ ቢሆኑ፣ በመናፍስታዊነት ንግግሮችና መገለጦች ውስጥ በኃይል በምልክትና በሀሰተኛ ተዓምራት የሚያከናውነውን የሰይጣንን ሥራ ማየት ይችሉ ነበር። ነገር ግን ከስጋ ልብ ጋር በቀላሉ የሚስማማውን ነፃነት ከመተው ይልቅ፣ የሚወዱአቸውንም ኃጢአቶች ከመጣል ይልቅ፣ እልፍ አዕላፋት ዓይናቸውን ለብርሐን ጨፍነው፣ ማስጠንቀቂያውን ቸል ብለው፣ ሰይጣን በዙሪያቸው ወጥመዱን ሲተበትብ ሳለ፣ ቀጥ ብለው ተራምደው ታዳኙ ሆነው ይያዛሉ። “ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስህተትን አሰራር ይልክባቸዋል።” [2ኛ ተሰ 2÷10፣11]።GCAmh 404.4

    የመናፍስታዊነት ትምህርቶችን የሚቃወሙ እነርሱ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሰይጣንንና መልአክቱን ጭምር እያጠቁ ናቸው። ከአለቆችና ከስልጣናት በሰማያዊው ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊያን [ኤፌ 6÷12] ጋር ግብግብ ገጥመዋል። በሰማያዊ መልዕክተኞች ኃይል ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ካልተደረገ በስተቀር ሰይጣን አንዲት ስንዝር መሬት እንኳ አይሰጥም። አዳኛችን እንዳደረገው ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች “ተጽፏል” በሚለው ቃል ይገጥሙት ዘንድ ይገባቸዋል። በክርስቶስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ሰይጣን አሁንም መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ይችላል፤ እውነት መሳይ ማደናገሪያዎቹን ለማስቀጠልም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርችን ያጣምማል። በዚህ አደገኛ ወቅት የሚቆሙ እነርሱ የመጽሐፍ ቅዱስን ምስክርነት ለራሳቸው ያውቁ ዘንድ ግድ ይሆንባቸዋል።GCAmh 405.1

    የተወደዱ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን መስለው በሚቀርቡ፣ እጅግ አደገኛ የሆኑ ኑፋቄዎችን በሚናገሩ የዲያቢሎስ መናፍስት ብዙዎች ግድድሮሽ ይገጥማቸዋል። እነዚህ ጎብኚዎች ስስ ብልቶቻችንን በመኮርኮር፣ አስመሳይነታቸውን ያስቀጥሉ ዘንድ ተአምራትን ይሰራሉ። ሙታን ምንም እንደማያውቁ፣ መስለው የሚገለጡትም የአጋንንት መናፍስት እንደሆኑ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንቋቋማቸው ዘንድ መዘጋጀት የግድ ያስፈልገናል።GCAmh 405.2

    “በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ያለው የፈተናው ሰዓት” [ራዕይ 3÷10] ከፊታችን ነው። እምነታቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ በጽናት ያልተመሠረተ ሁሉ ይታለላሉ፤ ይሸነፋሉም። የሰውን ልጆች መቆጣጠር ይችል ዘንድ ሰይጣን “በአመጽ ማታለል ሁሉ” ይሰራል፤ ማጭበርበሪያዎቹም በቀጣይነት እየጨመሩ ይሄዳሉ። አላማውን የሚያሳካው ግን ሰዎች በፈቃዳቸው ለፈተናዎቹ እጅ መስጠት ሲመርጡ ብቻ ነው። ከልባቸው የእውነትን እውቀት ለማግኘት የሚሹ፣ በመታዘዝም ነፍሳቸውን ለማንፃት የሚፍገመገሙ፣ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ለፍልሚያው የሚዘጋጁ እነርሱ፣ ያለ ጥርጥር፣ በእውነት አምላክ በኩል ምሽግ ያገኛሉ። “የትዕግስቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ እጠብቅሃለሁ” [ራዕይ 3÷10] የሚለው የአዳኙ ቃል ኪዳን ነው። በእርሱ የምትታመን አንዲት ነፍስ በሰይጣን እንድትሸነፍ ከሚተው ይልቅ ሕዝቦቹን ይጠብቅ ዘንድ እያንዳንዱን መልአክ ፈጥኖ ከሰማይ ቢልክ ይመርጣል።GCAmh 405.3

    በኃጥአን ላይ የሚመጣውን አስፈሪ መታለል፣ ይህ መሞኘታቸውም ከእግዚአብሔር ፍርድ የተጠበቁ እንደሆነ አድርገው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ የሚያደርጋቸውን ሁኔታ ነብዩ ኢሳይያስ ወደ እይታ ሲያመጣው፦ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፤ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፤ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ትላላችሁ” ይላል [ኢሳ 28÷15]። እዚህ ላይ ከተገለፁት መደቦች ውስጥ በግትር ንስሐ አልገባ ባይነታቸው ለኃጢአተኛው የሚመጣ ቅጣት የለም በሚለው ማረጋገጫ ራሳቸውን የሚያጽናኑ ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች፣ የሰው ዘር በሙሉ ምኑንም ያህል ብልሹ ቢሆን ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ እንደሚሉና የእግዚአብሔር መላእክት እንደሚሆኑም ያምናሉ። የመናፍስታዊነትን አታላይ አስመሳይነቶች፣ በሰይጣን የተበረከተውን የሐሰት መሸሸጊያ በምትኩ የሚቀበሉ፣ በመከራ ዘመን ለፃድቃን ምሽግ ይሆኑ ዘንድ የተበረከቱትን የሰማይ እውነቶች በግልጽ አሻፈረኝ የሚሉ፣ በይፋ ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ያሰሩ፣ ከሲኦልም ጋር የተስማሙ ደግሞ አሉ።GCAmh 405.4

    የዚህ ትውልድ እውርነት መግለጽ ከሚቻለው በላይ አስደናቂ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ የእግዚአብሔር ቃል ሊታመን የማይገባው እንደሆነ አድርገው አሻፈረን ይሉና፣ ተንሰፍስፈው የሰይጣንን ማታለያዎች በልበሙሉነት ይቀበላሉ። ተጠራጣሪዎችና አላጋጮች ለነብያትና ለሐዋርያት እምነት የሚታገሉትን አክራሪ እንደሆኑ አድርገው ያወግዟቸዋል። ስለ ክርስቶስና ስለ ማዳን እቅዱ በሚያወሱት ክቡር የመጽሐፍ ቅዱስ አዋጆች፣ እውነትንም እምቢ ባሉ ጊዜ ሊጎበኝ ባለው ቅጣት ላይ በመቀለድ ትኩረታቸውን ይቀይራሉ። ለእግዚአብሔር መጠይቅ እውቅና የሚሰጡትን የሕጉንም መጠይቆች የሚታዘዙትን ጠባብ፣ ልፍስፍስና አጉል እምነት የሚከተል አዕምሮ ባለቤት አድርገው በታላቅ ሀዘን ይመለከቱአቸዋል። በእርግጥም ከሞት ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረጉ፣ ከሲኦልም ጋር እንደተስማሙ፣ በእነርሱና በእግዚአብሔር የበቀል ብድራት መካከል ሊታለፍ፣ ሊጣስ ፈጽሞ የማይችል ቅጥር የገነቡ አስመስለው እርግጠኛነታቸውን ያንፀባርቃሉ። ፍርሃት ሊቀሰቅስባቸው የሚችል አንዳች ነገር የለም። ለፈታኙ ሙሉ ለሙሉ እጃቸውን ስለሰጡ፣ ከእርሱ ጋር እጅግ በቅርበት ስለተቆራኙ፣ በእርሱም መንፈስ እጅግ ስለተሞሉ፣ ከወጥመዱ ያመልጡ ዘንድ ኃይሉም ሆነ ዝንባሌው የላቸውም።GCAmh 406.1

    ዓለምን ያሳስት ዘንድ መጨረሻ ለሚያደርገው ጥረቱ ሰይጣን ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። የሥራው መሰረት የተጣለው “በእርግጥ አትሞቱም” በሚለው በኤደን ለሔዋን በተሰጠው ማረጋገጫ ነው። “ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይናችሁ ይከፈታል፤ እንደ አምላክም ትሆናላችሁ፤ መልካምንና ክፉንም ታውቃላችሁ” [ዘፍ 3÷4፣5]። መናፍስታዊነትን በመኮትኮት ወደር የሌለው ማታለያው ለሆነው ስልቱ ቀስ በቀስ መንገዱን ሲጠርግ ቆይቷል። ወደ ንድፎቹ ሙሉ አፈጻጸም ላይ ገና አልደረሰም፤ በመጨረሻ ጭላጭ ቀናት ግን የሚደረስበት ይሆናል። ነብዩ እንዲህ ይላል፦ “ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሶስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፣ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ” [ራዕይ 16÷13፣14]። በቃሉ ካላቸው እምነት የተነሳ በእግዚአብሔር ኃይል ከሚጠብቁት በቀር ዓለም ሁሉ ወደማወናበጃው ተርታ ተጠርጎ ይወሰዳል። የእግዚአብሔር ቁጣ ወርዶ እስኪያነቃቸው ድረስ በአደገኛ የደህንነት ስሜት ውስጥ ሰዎች በጥድፊ ያእንዲያንቀላፉ እየተደረጉ ነው።GCAmh 406.2

    ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ፍርድን ለሚዛን አደርጋለሁ፤ ጽድቅንም ለመጠን፣ በረዶም የሐሰትን ተስፋ ይሰብራል፣ ውኃውም መሸሸጊያውን ይድሳል። ከሞት ጋራም ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይጠፋል፤ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይፀናም። የሚያልፍ ጅራፍ ባለፈ ጊዜ መርገጫ ትሆናላችሁ።” [ኢሳ 28÷17፣18]።GCAmh 406.3