Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፲፪—የፈረንሳይ ተሐድሶ

    የተሐድሶውን ድል ያረጋገጠው የስፓይረስ ተቃውሞና የአውግስበርግ ምስክርነት ለዓመታት የሚዘልቅ ብጥብጥና ጽልመትን አስከተለ። በደጋፊዎቹ መካከል በነበረው መከፋፈል ተዳክሞ፣ በኃያላን ጠላቶቹ በትር በልዞ፣ ፕሮቴስታንታዊነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የመደምሰስ ዕጣ ፈንታ የገጠመው መሰለ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምስክርነታቸውን በደማቸው አተሙ። የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ የፕሮቴስታንት ጉዳይም ከቀንደኛ ደጋፊዎቹ አንዱ በሆነው ክህደት ተፈፀመበት። ተሐድሶውን የተቀበሉ እጅግ የተከበሩ ልዑላን በንጉሠ ነገሥቱ እጅ ወደቁ፣ እንደ እስረኛም ሆነው ከከተማ ወደ ከተማ ይጎተቱ ነበር። በዚህ ግልጽ በሆነው ድሉ መሃል ግን ንጉሠ ነገሥቱ በሽንፈት ተመታ። በእጁ የያዘው ታዳኝ ከመዳፉ ፈንቅሎ ሲወጣ ተመለከተ፤ ከዚያም ይደመስሰው ዘንድ የሕይወቴ ዓላማ ብሎ የያዘውን፣ ያጠፋው ዘንድ የቆረጠበትን አስተምህሮ በመቻቻል አልፎ ይተወው ዘንድ ግድ ሆነበት። ኑፋቄን ለመደምሰስ ግዛቱን፣ ሃብቱን ብሎም የራሱን ሕይወት እንኳ ሳይቀር አደጋ ላይ ጣለ። ሰራዊቱ በጦርነት ሲመናመን፣ ሃብቱ ሲሟጠጥ፣ ብዙ ግዛቶቹ የአመጽ አደጋ ሲጋረጥባቸው ይጨቁነው ዘንድ በከንቱ የደከመበት ኃይማኖት ግን በሁሉም ስፍራ ሲስፋፋ ተመለከተ። ቻርለስ 5ኛ ሲዋጋ የኖረው ሁሉን ቻይ ኃይልን [አምላክን] ነበር። እግዚአብሔር አለ፦ “ብርሐን ይሁን” [ዘፍ 1÷3] ንጉሠ ነገሥቱ ግን ጨለማው ሳይሰበር እንዲዘልቅ ደከመ። ዓላማው ከሸፈበት፣ ያለ እድሜው አርጅቶ በረጅም ትግል ተጎሳቁሎ፣ ዙፋኑን በፈቃዱ ለቆ ራሱን ገዳም ውስጥ ሰወረ።GCAmh 156.1

    ለተሐድሶው፣ በጀርመን እንደሆነው ሁሉ በስዊዘርላንድም እንዲሁ የጽልመት ቀናት መጡ። በርካታ ክፍለ ሃገራት (Cantons) የተሐድሶውን እምነት ቢቀበሉም ሌሎች ደግሞ በጭፍን የሮምን ብሂል(እምነት) የሙጥኝ ብለው ነበር። እውነትን ለመቀበል የሚፈልጉትን ሁሉ ለማሳደድ የሚያደርጉት ጥረት በመጨረሻ የእርስ በርስ ጦርነት ቀሰቀሰ። ዝዊንግልና ከእርሱ ጋር ያበሩ ብዙዎች በደም በተጠመቀው የካፐል መስክ ወደቁ። እነዚህን አሰቃቂ ጥፋቶች አይቶ መቋቋም ያልቻለው አይኮላምፖዲየስም ብዙም ሳይቆይ ሞተ። ሮም ድል ተቀዳጀች፤ በብዙ ስፍራም ያጣችውን ሁሉ ለማስመለስ የተቃረበች መሰለች። ምክሩ ዘላለማዊ የሆነው እርሱ ግን ሥራውን ወይም ሕዝቦቹን አልተወም። እጁ ያተርፋቸው ዘንድ ነበረው። በሌሎች ስፍራዎች ተሐድሶውን ወደፊት የሚያራምዱ ሰራተኞችን አስነስቶ ነበር።GCAmh 156.2

    በፈረንሳይ አገር ቀኑ ጎህ መቅደድ የጀመረው ገና የሉተር ስም በተሐድሶ አራማጅነት ከመሰማቱ አስቀድሞ ነበር። ብርሃኑን ከተቀበሉት ከቀዳሚዎቹ አንዱ የዕድሜ ባለጸጋው ለፈቭሪ በጣም የተማረ፣ በፓሪስ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የነበረ፣ በቅንነትና በታማኝነት ጳጳሳዊውን ሥርዓት ከልቡ የሚደግፍ ሰው ነበር። ጥንታዊ መዛግብትን በሚመረምርበት ጊዜ አትኩሮቱ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተሳበ፤ ተማሪዎቹንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ጀመረ። ለፈቭሪ ቅዱሳንን እጅግ በስሜት የሚወድ ከመሆኑ የተነሳ በቤተ ክርስቲያንዋ እንደሚነገረው ጥንታዊ አፈ ታሪክ የቅዱሳንንና የሰማዕታትን ታሪክ አጠናቅሮ ለማዘጋጀት እየሰራ ነበር። ይህ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ሥራ ነበር፣ በሥራው ብዙ ገፍቶበት ስለነበር ለሥራው የሚረዳው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ አገኛለሁ ብሎ በማሰብ፣ ለዚህ አላማ ጥናቱን ጀመረ። በእርግጥ እዚህም ቅዱሳንን አግኝቷል፤ በሮማዊቷ የዘመን መዝገብ እንደተገለጹት ግን አልነበሩም። የመለኮታዊ ብርሐን ጎርፍ አዕምሮውን አጥለቀለቀው። በመገረምና በመፀየፍ፣ በራሱ አነሳሽነት የጀመረውን ሥራ ትቶ ራሱን ለእግዚአብሔር ቃል ገበረ። ከዚያ ያገኛቸውን ወርቃማ እውነቶች ብዙም ሳይቆይ ማስተማር ጀመረ። በ1512 ዓ.ም፣ ሉተርም ሆነ ዝዊንግል የተሐድሶን ሥራ ሳይጀምሩ በፊት ለፈቭሪ ሲጽፍ፦ “ከፀጋው የተነሳ ለዘላለም ሕይወት ብቁ የሚያደርገንን በእምነት የተገኘ ጽድቅ የሚሰጠን እግዚአብሔር ነው” አለ።-Wylie, b. 13, ch. 1። በድነት ምስጢራት ላይ በማተኮር ሲናገር፣ “ኦህ መናገር የማይቻለው የዚያ መተካካት ታላቅነት - ኃጢአት የሌለበት ተኮነነ፤ ኃጢአተኛው ደግሞ ነፃ ተለቀቀ። በረከት መርገምን ተሸከመ፤ መርገምም ወደ በረከት ተለወጠ፤ ሕያው ሞተ፤ የሞተውም ሕያው ሆነ፤ ክብር የሆነው በጽልመት ተዋጠ፣ ከውርደት በቀር ምንም ያላወቀው እርሱ ደግሞ ክብርን ተላበሰ።” አለ።-D’Aubigné, London ed., b. 12, ch. 2።GCAmh 156.3

    የድነት ክብር የእግዚአብሔር የራሱ ብቻ እንደሆነ ሲያስተምር ሳለ የመታዘዝ ኃላፊነት ደግሞ የሰው እንደሆነ አወጀ። “የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አባል ከሆንክ” አለ፣ “የአካሉ ብልት ነህ። አካሉ ከሆንክ ደግሞ የመለኮታዊ ባህርይ ሙላት አለህ።” “ኦህ ሰዎች ወደዚህ ዕድል መረዳት ቢመጡ እንዴት ባለ ያልረከሰ ንጹህና ቅዱስ ሕይወት ውስጥ በኖሩ ነበር። በውስጣቸው ካለው ክብር ጋር ሲነፃፀር - የስጋ ዓይን የማያየውን ክብር ቢያዩ - የዚህን ዓለም ክብር እንዴት ባንቋሸሹት ነበር።”-Ibid, b. 12, ch. 2።GCAmh 157.1

    ለፈቭሪ ሲያስተምር በተመስጦ ሲያዳምጡት የነበሩ፣ የመምህራቸው ድምጽ ዝም እንዲል ከተደረገ ከረጅም ጊዜ በኋላ እውነትን ማወጅ የሚቀጥሉ ከተማሪዎቹ መካከል ነበሩ። ከእነዚህ አንዱ ዊሊያም ፋረል ነበር። ከሐይማኖተኛ ወላጆች የተገኘው ልጅ የቤተ ክርስቲያንዋን አስተምህሮ ሙሉ በሙሉ እንዲቀበል ተደርጎ የተማረ ከመሆኑ የተነሳ እርሱም ከሐዋርያው ከጳውሎስ ጋር “… በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ” [የሐ ሥራ 26÷5] ማለት የሚችል አይነት ሰው ነበር። ሮማዊነትን ከልቡ የሚደግፍ ቤተ ክርስቲያንዋን ለመቃወም የሚደፍሩትን ሁሉ ለመደምሰስ በቅንዓት የሚቃጠል ሰው ነበር። ስለዚህ የሕይወቱ ክፍል ቆየት ካለ በኋላ ሲናገር “ማንም ሊቀ-ጳጳሱን ተቃውሞ ሲናገር ከሰማሁ” አለ “እንደ ተቆጣ ተኩላ ጥርሴን አፋጭ ነበር።”-Wylie, b. 13, ch. 2። ቅዱሳንን በማምለክ (በማክበር) የማይታክት ነበር፤ ከለፈቭሪ ጋር ሆኖ የፓሪስን አብያተ ክርስቲያናት በመዞር፣ በመሰውያቸው በማምለክ፣ ቅዱስ ሐውልታትን በስጦታ በማስጌጥ የሚተጋ ነበር። እነዚህ ጥረቶች ግን የነፍስ ሰላም ያመጡለት ዘንድ አልተቻላቸውም። የኃጥአተኝነት ስሜት ተጣብቆ ሊለቀው አልቻለም፤ ያከናወናቸው የመፀፀት ተግባራት ሁሉ ሊያሸሹት ያልቻሉት የበደለኝነት ስሜት ነበረበት። ከሰማይ እንደመጣ ድምጽ አድርጎ የተሐድሶ አራማጁን ቃላት አደመጠ፣ “ድነት ከፀጋ የተነሳ ነው፤ በደል የሌለበት [ክርስቶስ] ተኮነነ፤ ወንጀለኛውም ነፃ ወጣ።” “የሰማይን ደጅ የሚከፍት፣ የገሃነምንም በሮች የሚዘጋው የክርስቶስ መስቀል ብቻ ነው።”-Ibid, b. 13, ch. 2።GCAmh 157.2

    ፋረል እውነቱን በደስታ ተቀበለ። ልክ እንደ ጳውሎስ ባለ ለውጥ፣ ከባህል ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት ነፃነት ተለወጠ። “የገዳይ ልብ ካለው እጅግ ከተራበ አዳኝ ተኩላ ይልቅ” ፣ “ድምጹን አጥፍቶ፣ ወደ የዋህና የማይጎዳ የበግ ጠቦትነት በመቀየር ልቡን ሙሉ ለሙሉ ከሊቀ-ጳጳሱ በመውሰድ ለየሱስ ክርስቶስ አስረክቦ” ተመለሰ-D’Aubigné, b. 12, ch. 3።GCAmh 157.3

    ለፈቭሪ ብርሃኑን በተማሪዎቹ መካከል ማሰራጨቱን ቀጥሎ ሳለ ለሊቀ-ጳጳሱ ቀናኢ እንደነበረ ሁሉ ለክርስቶስ ጉዳይም በመትጋት ፋረል እውነትን በአደባባይ አወጀ። በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ያለው የሜውክሱ ጳጳስ ብዙም ሳይቆይ ከእነርሱ ጋር አበረ። በትምህርታቸው የላቁና በችሎታቸው የተወደሱ ብዙ መምህራን ወንጌልን በማወጅ ተባበሩ፤ ከእጅ ሙያተኞችና ከጪሰኞች ቤት ጀምሮ እስከ ቤተ-መንግሥት፣ በሁሉም መደብ ያሉ ሰዎች ድጋፍም አገኘ። በዚያን ጊዜ ገዢ የነበረው የንጉሠ-ነገሥት ፍራንሲስ 1ኛ እህት የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያኑን እምነት ተቀበለች። ንጉሠ-ነገሥቱና ልዕልት እናቱም ጭምር ለተወሰነ ጊዜ የደገፉት መስለው ነበር፤ በመሆኑም የተሐድሶ አራማጆቹ ፈረንሳይ ወንጌሉን የምትቀበልበትን ጊዜ ወደፊት በታላቅ ተስፋ ይጠባበቁ ነበር።GCAmh 158.1

    ተስፋቸው ግን እውን አይሆንም ነበር። የክርስቶስን ደቀ-መዛሙርት መከራና ስደት ይጠብቃቸው ነበር። ይህ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ግን በምህረቱ ተጋርዶላቸው ነበር። ማዕበሉን ለመቋቋም ኃይል ያጠራቅሙ ዘንድ ለተወሰነ ጊዜ ሰላም ሰፍኖ ነበር፤ ተሐድሶውም በፍጥነት ተስፋፋ። በሥሩ ያሉትን የቤተ-ክህነት ባለስልጣናትና ሕዝቡን ለማስተማር የሜውክሱ ጳጳስ በቅንነት ለፋ። ገልቱና ስነ-ምግባር የሌላቸው ቀሳውስት ተወግደው በምትካቸው፣ እስከተቻለ ድረስ፣ በተማሩ ቅዱስ ሰዎች ተተኩ። ሕዝቦቹ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት እንዲችሉ የጳጳሱ ከፍተኛ ፍላጎት ነበርና ይህ፣ ብዙም ሳይቆይ መሳካት ቻለ። ለፈቭሪ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም የማዘጋጀቱን ሥራ ተያያዘው። የሉተር ጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ በዊተንበርግ እየታተመ በነበረበት ጊዜ የፈረንሳይ አዲስ ኪዳን በሜውክስ ታተመ። ጳጳሱ ወደ አጽቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ መጽሐፍ ቅዱሱን ለማስፋፋት ያልጣረው ጥረት፣ ያላወጣውም ገንዘብ አልነበረም፣ ወዲያውም የሜውክስ ጪሰኞች መጽሐፍ ቅዱሳትን በእጃቸው አስገቡ።GCAmh 158.2

    ከጥም የተነሳ የሚያልቁ መንገደኞች ሕያው የውኃ ምንጮችን በታላቅ ደስታ እንደሚቀበሉ እነዚህ ነፍሳት የሰማይን መልእክት ተቀበሉ። በመስክ የሚሰሩ ወዝ አደሮች፣ በመስሪያ ጣቢያዎች የሚሰሩ የእጅ ሙያተኞች የመጽሐፍ ቅዱስን ወርቃማ እውነቶች በማውራት የየዕለት ልፋታቸውን በደስታ ያሞቋቸው ነበር። ሲመሽ ደግሞ ወደ የወይን መጠጥ መሸጫ ሱቆች በመሄድ ፈንታ በቤታቸው በመሰበሰብ የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናት በፀሎትና በምስጋና ይተባበሩ ነበር። በእነዚህ ማህበረሰቦች ዘንድ ታላቅ ለውጥ በፍጥነት መጣ። የመጨረሻዎቹ ዝቅተኛ መደቦች፣ ያልተማሩና ጥረው ግረው የሚያድሩ ጭሰኞች ቢሆኑም፣ የሚለውጠውና ከፍ ከፍ የሚያደርገው የመለኮታዊ ፀጋ ኃይል በሕይወታቸው ይንፀባረቅ ነበር። ወንጌሉን በቅንነት ለሚቀበሉ ሁሉ መልእክቱ ምን ማከናወን እንደሚችል ሕያው ምስክር ሆነው በየዋህነት፣ በፍቅርና በቅድስና ቆሙ።GCAmh 158.3

    በሜውክስ የፈነጠቀው ብርሐን ወደ ሩቅ ስፍራም ጮራውን ወገግ አደረገ። የተለወጡ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ ይጨምር ነበር። የመዋቅሩ ቁጣ፣ የመነኩሴዎችን ከአክራሪነት የመነጨ ጠባብ ጥላቻን ባልወደደው ንጉሥ አማካኝነት ለተወሰነ ጊዜ ተገድቦ ቢቆይም፣ በመጨረሻ ግን ጳጳሳዊ መሪዎቹ አሸነፉ። አሁን የማቃጠያ ቋሚው ተዘጋጀ። የሜውክሱ ጳጳስ በእሳትና በክህደት መካከል እንዲመርጥ ሲገደድ ቀላሉን መንገድ (ክህደትን - አጥፍቻለሁ ብሎ መፀፀትን) መረጠ፤ ሆኖም መሪው ቢወድቅም ተከታዮቹ ግን ፀንተው ቆሙ። ብዙዎች በነበልባል ውስጥ ምስክርነታቸውን ሰጡ። በቆራጥነታቸውና በታማኝነታቸው እሳት ያልበገራቸው እነዚህ ትኁት፣ ከዝቅተኛ መደብ የተገኙ ክርስቲያኖች በሰላም ጊዜ ምስክርነታቸውን መስማት ላልቻሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በሞታቸው ወንጌልን ሰበኩ።GCAmh 158.4

    በስቃይና በውርደት መካከል ለክርስቶስ ምስክር ለመሆን የቆረጡት ግን ዝቅተኛ መደቦችና ደሃዎች ብቻ አልነበሩም። በንጉሣውያን መኖሪያ ግንቦችና በቤተ-መንግሥት ሳይቀር ከሃብት ከማዕረግ እንዲያውም ከሕይወት ሳይቀር አስበልጠው ለእውነት ዋጋ የሰጡ ንጉሣዊ ነፍሳትም ነበሩ። የአርበኞች ጥሩር፣ ከጳጳሳዊ መጎናፀፊያና ቆብ ይልቅ የገዘፈና የተሰጠ መንፈስ ደብቆ ነበር። ሉይስ ዴ በርኩይን ከተከበረ ቤተሰብ የተወለደ ነበረ። ጀግና፣ ሰው አክባሪው አርበኛ፣ ጥናት ላይ ያተኮረ፣ ፀባዩ የተሞረደ፣ ስነምግባሩም ሂስ የማይወጣለት ነበር። አንድ ጸሐፊ ስለርሱ ሲጽፍ “የጳጳሳዊ ሕጎችና ደንቦች ታላቅ ተከታይ፣ የሥርዓተ-ቁርባን ስብሰባዎችና የስብከቶች ተከታታይ ነበር።” “ሌላው የሚታወቅበት ባህርይ ደግሞ ሉተራዊነትን በከፍተኛ ጥላቻ መጥላቱ ነበር።” ብሏል። ሆኖም እንደሌሎቹ ብዙ ሰዎች በእግዚአብሔር እርዳታ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በመመራት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኘው የሉተርን አስተምህሮ እንጂ የጳጳሳውያኑን አለመሆኑ አስገረመው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ሙሉ በሙሉ ራሱን ለወንጌሉ አሳልፎ ሰጠ።-Ibid, b. 14, ch. 6።GCAmh 159.1

    “ከፈረንሳይ ልዑላን መካከል በትምህርት የላቀው” የምጡቅነት ተሰጥኦውና አንደበተ ርዕቱነቱ፣ የማይጣሰው ድፍረቱ፣ ጀብደኝነቱ፣ ንጉሡም ከሌሎቹ ይልቅ እርሱን ከመውደዱ የተነሳ በፍርድ ቤት የነበረው ተጽዕኖ፣ በብዙዎች ዘንድ የሃገሩ ተሐድሶ አድራጊ እንደሚሆን ይታመን ነበር። ቤዛ ሲናገር፣ “በፍራንሲስ 1ኛ ዘንድ ሁለተኛ መራጭነት ቢያገኝ ኖሮ በርኩይን ዳግማዊ ሉተር ይሆን ነበር”። “ከሉተርም የባሰ ነው” ብለው ጮሁ ጳጳሳዊያኑ።-Ibid, b. 13, ch. 9። በርግጥም በፈረንሳይ ሮማዊያን ዘንድ እጅግ የተፈራ ነበር። መናፍቅ ነህ ብለው ወደ እስር ቤት ቢወረውሩትም በንጉሡ አማካኝነት ነፃ ሆነ። ትግሉ ለረጅም ዓመታት ቀጠለ። ፍራንሲስ በሮምና በተሐድሶ ንቅናቄው መካከል እያወላወለ (አንዴ እዚያ አንዴ እዚህ እያለ) የመነኮሳቱን ኃይለኛ ፍላጎት አንዳንዴ ሲገድብ አንዳንዴ ሲለቅ ቆየ። በርኩይን ሶስት ጊዜ ቢታሰርም በጥበቡና በተከበረ ባህርይው የሚያደንቀው ንጉሡ የመዋቅሩ ሸር ሰለባ ይሆን ዘንድ ስላልፈቀደ ሶስቱንም ጊዜ ከእስር ቤት አስወጣው።GCAmh 159.2

    በርኩይን በፈረንሳይ ስለተጋረጠበት አደጋ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በፈቃዳቸው ወደሌላ ስፍራ ኮብልለው መጠጊያ ያገኙትን ፈለግ እንዲከተል ተመከረ። ከነሙሉ አንፀባራቂ የትምህር ደረጃው፣ ሕይወትና ክብርን የእውነት ተገዢ በሚያደርገው የስነ-ምግባር ታላቅነት የወደቀው፣ ፈሪውና አድር ባዩ ኢራስመስ ለበርኩይን ሲፅፍ፦ “ወደ ሌላ አንድ አገር አምባሳደር ሆነህ እንድትላክ ጥያቄ አቅርብ፤ ወደ ጀርመን ሂድና ተዘዋወር። ቤዳንና መሰሎቹን ታውቃቸዋለህ፣ እርሱ አንድ ሺህ ራስ ያለው በሁሉም አቅጣጫ መርዝ የሚተፋ ጭራቅ ነው። ጠላቶችህ ሌጊዮን ይባላሉ። ዓላማህ ከየሱስ ክርስቶስ የተሻለ እንኳ ቢሆን በአሰቃቂ ሁኔታ ሳያጠፉህ አይለቁህም። ንጉሡ በሚሰጥህ ጥበቃ ብዙ አትተማመን። በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን በስነ-መለኮት ትምህርት ክፍል አታዳክመኝ።” ብሎታል።-Ibid, b. 13, ch. 9።GCAmh 159.3

    ሆኖም አደጋዎች እየጠነከሩ ሲሄዱ የበርኩይን ወኔ የበለጠ ኃይለኛ እየሆነ መጣ። ከሁኔታው አንፃር ሚዛናዊ ከሚመስሉትና ራስን ከሚጠቅሙ የኢራስመስ ምክሮች በተቃረነ ሁኔታ የበለጠ ድፍረት የተሞላባቸው እርምጃዎችን ለመውሰድ ቆረጠ። እውነትን ደግፎ መቆም ብቻ ሳይሆን በስህተት ላይም ጥቃት ሊያደርስ ወሰነ። ሮማዊያኑ ከእርሱ ጋር ለማቆራኘት የሚደክሙበትን የኑፋቄ ክስ መልሶ ከራሳቸው ጋራ ያጣብቀው ዘንድ ነበረው። ወደር ያልተገኘላቸው የማይተኙና መራር ተቃዋሚዎቹ በከተማይቱና በሃገሪቱ ካሉ ከፍተኛ የኃይማኖታዊ ስልጣናት መካከል አንዱ ከሆነው ከስመ-ጥሩ የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ የኃይማኖት ጥናት ክፍል የመጡ የተማሩ ዶክተሮችና መነኩሴዎች ነበሩ። እነዚህ ዶክተሮች ከጻፏቸው ጽሁፎች መካከል በርኩይን አሥራ ሁለት ነጥቦችን በማውጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ተጻራሪ ናቸው ብሎ በአደባባይ በማወጅ የመናፍቃን ተግባር እንደሆኑ ተናገረ። በክርክሩም ንጉሡ ፈራጅ ይሆን ዘንድ ለመነ።GCAmh 160.1

    የተቀናቃኝ ወገኖችን ኃይልና ብርቱነት ማነፃፀር ያልሰነፈው ንጉሠ ነገሥት የሚንቦጠረሩትን መነኩሴዎች ኩራት ለማዋረድ ዕድል ማግኘቱ አስደስቶት፣ ሮማውያኑ ጉዳያቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እንዲያስረዱ አዘዛቸው። ይህ መሣሪያ እንደማይጠቅማቸው ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። እስር፣ ግርፋትና ቃጠሎ፣ ይጠቀሙአቸው ዘንድ በተሻለ የሚያውቁአቸው መሳሪያዎች ነበሩ። አሁን ነገር ተገልብጦ በርኩይንን ሊወረውሩበት አስበው በማሱት ጉድጓድ ራሳቸው ሊዳፈኑበት እንደቀረቡ አወቁት። በመገረም፣ አንዳች ማምለጫ ቀዳዳ በመፈለግ አይኖቻቸው በዙሪያቸው ይንከራተቱ ነበር።GCAmh 160.2

    ልክ በዚህ ጊዜ ከሕዝባዊ ጎዳናዎች መካከል በአንዱ ጥግ ቆሞ የነበረው የድንግሏ ምስል እንዳልሆነ ሆኖ፣ተቆራርጦ ተገኘ። በከተማዋ ታላቅ ውሽንፍር ተቀሰቀሰ። ብዙ ሰው ወደዚያ ሥፍራ በመጉረፍ ሃዘኑንና ቁጣውን ገለፀ። ንጉሡም እንዲሁ ስሜቱ እጅግ ተነክቶ ነበር። መነኮሳቱ ለሚፈልጉት ጉዳይ የሚጠቀሙበት ጥሩ አጋጣሚ አገኙ፣ የበለጠ ሊያበጃጁት ጊዜ አልወሰደባቸውም። “እነዚህ የበርኩይን አስተምህሮ ፍሬዎች ናቸው” በማለት አቅራሩ፣ “በዚህ ሉተራዊ አድማ፣ ኃይማኖት፣ ሕግጋቱ፣ ዙፋኑም ራሱ፣ በአጠቃላይ ሁሉም ነገር ሊገለበጥ ደርሷል” አሉ።-Ibid, b. 13, ch. 9።GCAmh 160.3

    በርኩይን እንደገና ተያዘ። ንጉሡ ከፓሪስ በመውጣቱ መነኮሳቱ በበርኩይን ላይ ያሻቸውን ሊያደርጉ ነፃነት ተቀዳጁ። የተሐድሶ አራማጁ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተፈርዶበት እንዲሞት ተወሰነበት። ፍራንሲስ አሁንም እንደገና ሊያድነው ጣልቃ እንዳይገባ ፍርዱ በተሰጠበት በዚያው ቀን እንዲፈፀም ተደረገ። በእኩለ ቀን በርኩይን ወደ መሞቻ ስፍራው ተወሰደ። ለመመልከት እጅግ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከምርጦቹና በጀግንነት ተወዳዳሪ ከሌላቸው ከፈረንሳይ ክቡራን ቤተሰቦች የወጣው ሰው ለዚህ መመረጡ ብዙዎችን ያስደመመና ያሳዘነ ክስተት ነበር። ግርምት፣ ንዴት፣ ንቀትና መሪር ጥላቻ የሚተመውን ሕዝብ ፊት ጥላሸት አስመሰለው። ጥላ ያልወደቀበት ግን አንድ ፊት ነበር። የሰማዕቱ ሀሳብ ከነበረው የድንግርግር ትዕይንት ፈጽሞ የተለየ ነበር። ልብ ያለው የአምላኩን በዚያ ስፍራ መገኘት ብቻ ነበር።GCAmh 160.4

    የተሳፈረበት የወላለቀ ሰረገላ፣ የአሳዳጆቹ የተቋጠረ ግንባር፣ ሊገናኘው የሚሄደው አሰቃቂ ሞት ትኩረቱን ፈጽሞ አልሳበውም ነበር። ሞቶ የነበረው ሕያው የሆነው፣ ለዘላለምም የሚኖረው እርሱ፣፣ የሞትና የገሃነም መክፈቻ ቁልፍ ያለው እርሱ፣ አጠገቡ ነበር። የበርኩይን ፊት በሰማይ ሰላምና ብርሐን ፈክቶ ነበር። በሚያምር ልብስ ራሱን አስውቦ ነበር። “የከፋይ ካባ፣ በመስመር ያጌጠ ሃር እንዲሁም ወርቃማ የእግር ሹራብ” አድርጎ ነበር።-D’Aubigné, History of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 2, ch. 16። በነገሥታት ንጉሥ[በጌታ] እና በሚመለከተው ዓለማት ሁሉ ፊት የእምነቱን ምስክርነት ሊሰጥ ነበርና የሃዘን አሻራ ደስታውን ሊሸፍንበት አይገባውም።GCAmh 160.5

    በተጨናነቀው መንገድ መሃል ሲያልፉ ሳለ በሚያዩበት ያልደበዘዘ ሰላም፣ የድል ደስታ በሚንፀባረቅበት ገጽታውና እንቅስቃሴው ሕዝቡ ይገረሙ ነበር። “በቤተ መቅደስ ተቀምጦ ስለ ቅዱስ ነገሮች የሚያሰላስል ይመስል ነበር” አሉ።-Wylie, b. 13, ch. 9።GCAmh 161.1

    በማቃጠያው ስፍራ በርኩይን ለተሰበሰበው ሕዝብ ጥቂት ቃላት ለመናገር ሙከራ ቢያደርግም ውጤቱን የፈሩት መነኮሳት መጮህ፣ ወታደሮቹም መሳሪያዎቻቸውን ማፋጨት በመጀመራቸው የሰማዕቱ ድምጽ በጫጫታው ተዋጠ። እንዲህም በማድረግ በ1529 ዓ.ም የስመ-ጥርዋ ፓሪስ ከፍተኛ የስነ-ጽሁፍና የኃይማኖት ጉዳዮች ባለስልጣን “በሚሰውበት መድረክ ላይ፣ የሚሞቱ ሰዎችን ቅዱስ ቃላት እንዴት እንደሚያፍን ያሳየበትን፣ ለ1793 ዓመተ ምህረቱ ነዋሪዎች መሠረት የሆነውን ድርጊት ፈፀመ።”-Ibid, b. 13, ch. 9።GCAmh 161.2

    በርኩይን ተጠፍሮ ታስሮ በእሳት ነበልባል ከሰመ። የመሞቱ ወሬ በመላ ፈረንሳይ ለነበሩ የተሐድሶው ደጋፊዎች መሪር ሃዘን ነበር። ምሳሌነቱ ግን አልጠፋም። “ወደፊት በሚመጣው ሕይወት ላይ ዓይናችንን ጥለን ሞትን በደስታ ለመገናኘት” አሉ የእውነቱ ምስክሮች፣ “እኛም ዝግጁ ነን።”-D’Aubigné, History of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 2, ch. 16።GCAmh 161.3

    “በሜውክስ ስደት ጊዜ የተሐድሶው እምነት አስተማሪዎች የመስበክ ፈቃዳቸውን ተነጥቀው ወደ ሌሎች ስፍራዎች ተበተኑ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለፈቭሪ ወደ ጀርመን አገር ሲሄድ ፋረል ደግሞ ወደ አደገበት የልጅነት ከተማው ወደ ምሥራቃዊው ፈረንሳይ በመሄድ ብርሃኑን ያሰራጭ ጀመር። በሜውክስ ይከናወን የነበረው ሁሉ ወሬው እዛም ደርሶ ስለነበር ያለፍርሃት በስሜት ያስተምረው የነበረው እውነት አድማጮችን አገኘ። ብዙም ሳይቆይ ባለስልጣናቱ ዝም ሊያሰኙት በመንቀሳቀሳቸው ከዚያ ከተማ እንዲሰደድ ተደረገ። በአደባባይ መስበክ ባይችልም ከቦታ ቦታ፣ ከመንደር መንደር እየተዘዋወረ በግል መኖሪያዎችና ዘወር ባሉ መስኮች በማስተማር በልጅነቱ በሚያውቃቸው ጫካዎችና ድንጋያማ ዋሻዎች ይኖር ነበር። እግዚአብሔር ለበለጠ ፈተና እያዘጋጀው ነበር፣ “አስቀድሜ ያስተዋልኩአቸው፣ የመስቀሎች፣ የስደትና የሰይጣን ደፈጣ እጥረቶች አልነበሩም”፣ አለ፣ “እንዲያውም እኔ በራሴ ኃይል ልሸከማቸው ከምችለው በላይ ነበሩ። ሆኖም እግዚአብሔር አባቴ ነው፤ እስካሁን ድረስ ሰጥቶኛል፣ ለወደፊትም የሚያስፈልገኝን ብርታት ሁሉ ይሰጠኛል።”-D’Aubigné, History of the Reformation of the Sixteenth Century, b. 12, ch. 9።GCAmh 161.4

    እንደ ሐዋርያት ዘመን ሁሉ ስደቱ “ወንጌልን ለማስፋፋት” [ፊል 1÷12] የሚረዳ ሆነ። ከፓሪስና ከሜውክስ ተሰደው “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ።” [ሐዋ ሥራ 8÷4]። በዚህም ምክንያት ወንጌሉ ሩቅ ወደሆኑ የፈረንሳይ ክፍለ ሃገራት ደረሰ።GCAmh 161.5

    እግዚአብሔር አሁንም አላማውን ለማስፋፋት ሰራተኞቹን እያዘጋጀ ነበር። ከፓሪስ ትምህርት ቤቶች መካከል አንድ አስተዋይና ዝምተኛ፣ ኃይለኛና ሰርስሮ የሚገባ አዕምሮ ያለው መሆኑን እያስመሰከረ የነበረ፣ ከእውቀት ብስለቱና ለኃይማኖት ከመሰጠቱ ባልተናነሰ በሕይወቱ ነውር የሌለበት አንድ ወጣት ነበረ። ልቀቱና ተግባራዊነቱ ብዙም ሳይቆይ የኮሌጁ ኩራት እንዲሆን አደረገው፤ በመሆኑም ቤተ ክህነትን ከሚጠብቁ እጅግ ከተከበሩና ችሎታውም ካላቸው ሰዎች መካከል ጆን ካልቪን አንዱ ይሆናል የሚል እምነት ነበር። ነገር ግን የመለኮት ብርሐን ጮራ ካልቪንን የከበበውን የምድራዊ ትምህርትና የመላምት ግድግዳ ዘልቆ ገባ። ካልቪን አዲሶቹን አስተምህሮዎች ሲሰማ አንዘፈዘፈው፤ መናፍቆች የእሳት እራት መሆናቸው የሚገባቸው ለመሆኑ ቅንጣት ጥርጥር አልነበረውም። ነገር ግን ሳያስተውለው ከኑፋቄው ጋር ግንባር ለግንባር ተፋጠጠ፤ የፕሮቴስታንቱን አስተምህሮ ለመመከት የሮም መንፈሳዊ ትምህርት ያለውን ጉልበት እንዲፈትንም ተገደደ።GCAmh 162.1

    ተሐድሶውን የተቀላቀለ የካልቪን የአጎት ልጅ በፓሪስ ይኖር ነበር። ሁለቱ ዘመዳሞች ቶሎ ቶሎ እየተገናኙ የክርስትናውን ዓለም እያናወጡ ስላሉት ጉዳዮች ይወያዩ ነበር። “በዓለም ያሉት ሁለት ሐይማኖቶች ብቻ ናቸው።” አለ ፕሮቴስታንቱ ኦሊቬታን። “አንዱ ኃይማኖት፣ ሰዎች የፈጠሩት፣ በሚያካሂደው ሥነ-ሥርዓትና በሚሰራው መልካም ሥራ ሰው ራሱን የሚያድንበት ነው። ሌላኛው ኃይማኖት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለፀው ሲሆን ሰዎች ለመዳናቸው በእግዚአብሔር ወደ ተሰጠው የነፃ የፀጋ ስጦታ እንዲመለከቱ የሚያስተምረው ነው።” “ከአዲሶቹ አስተምህሮዎችህ ውስጥ አንዳች የምቀበለው የለኝም” አለ ካልቪን ፈርጠም ብሎ፣ “ሕይወቴን በሙሉ በስህተት ውስጥ የኖርኩ ይመስልሃልን?”።-Wylie, b. 13, ch. 7።GCAmh 162.2

    ነገር ግን እንደፈለገ ሊያዳፍናቸው ያልቻላቸው ሃሳቦች በውስጡ ተቀስቅሰው ነበር። ብቻውን በክፍሉ ውስጥ ሆኖ የአጎቱ ልጅ የተናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ ይመረምር ነበር። የበደለኝነት ስሜት ያዘው። በጻድቅና ቅን ፈራጅ ፊት ያለ አማላጅ ሆኖ ራሱን ተመለከተ። የቅዱሳን አስታራቂነት፣ መልካም ሥራ፣ የቤተ ክርስቲያንዋ የተለያዩ ሥነ ሥርአቶች ኃጢአትን ያስተሰርዩ ዘንድ ኃይል የሌላቸው ሆኑ። የዘላለማዊ ተስፋ-ቢሰኝነት ድቅድቅ ጨለማ ብቻ ይታየው ነበር። ችግሩን ለመፍታት የቤተ ክርስቲያን ዶክተሮች በከንቱ ደከሙ። ኑዛዜ፣ የንስሐ መግቢያ ቅጣት፣ በከንቱ ተግባራዊ ሆኑ፤ ነፍስን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቁ ዘንድ አልተቻላቸውም።GCAmh 162.3

    በእነዚህ ፍሬ-አልባ ግብግቦች ተጠምዶ ባለበት ሰዓት አንድ ቀን ካልቪን ከሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባዮች መካከል እንደ አጋጣሚ አንዱን ለመጎብኘት ሲወጣ መናፍቅ ሲቃጠል ተመለከተ። በሰማዕቱ ፊት ላይ ሲንፀባረቅ የነበረውን ሰላም ሲያይ በመገረም ተሞላ። በዚያ አሰቃቂ ሞት ስቃይ ውስጥ፣ እንዲሁም የበለጠ ዘግናኝ በሆነው የቤተ ክርስቲያንዋ እርግማን መሃል ሆኖ ሟቹ ያሳየውን እምነትና ጥንካሬ ሲመለከት፣ ወጣቱ ተማሪ፣ ውልፍት ሳይል የቤተ ክርስቲያንዋ ታዛዥ ሆኖ የሚኖር ቢሆንም ከራሱ ተስፋ መቁረጥና ጽልመት ጋር ሲያነጻጽረው አሳመመው። መናፍቃኑ እምነታቸውን ያስደገፉት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሆነ አውቋል። ከተቻለው የደስታቸው ምስጢር ምን እንደሆነ ያውቅ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ቆረጠ።GCAmh 162.4

    በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ክርስቶስን አገኘ። “ኦ አባት ሆይ” በማለት ጮኸ፣ “የእርሱ መስዋዕትነት ቁጣህን አብርዷል፤ ደሙ ቆሻሻነቴን አጥቧል፤ መስቀሉ መርገሜን ተሸከመ፤ ሞቱ ለእኔ ስርየት ሆነልኝ። ብዙ ጥቅመ-ቢስ መጃጃያዎችን ለራሳችን ፈጠርን፤ አንተ ግን እንደ ችቦ ቃልህን በፊቴ አስቀመጥህ፤ የሱስ ከፈጸመው በቀር ሌሎችን ሥራዎች እንደ ፀያፍ እቆጥራቸው ዘንድ ልቤን ነካህ።”-Martyn, vol. 3, ch. 13።GCAmh 163.1

    ካልቪን የተማረው ለካህንነት ነበር። ገና አሥራ ሁለት አመት ሲሆነው በአንድ ትንሽ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኖ ተመድቦ ነበር፤ እንደ ቤተ ክርስቲያንዋ ቀኖናም በጳጳሱ አማካኝነት ጸጉሩን ተላጭቶ ነበር። ለኃይማኖት አገልግሎት አልተቀባም፣ ካህን ለመሆን የሚያበቁትን መስፈርቶችም አላሟላም ነበር፤ ነገር ግን የቤተ-ክህነት መሪዎች አባል በመሆን ለያዘው ቢሮ ተሰይሞ ስለነበር ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ገንዘብ ይከፈለው ነበር።GCAmh 163.2

    አሁን ደግሞ ፈጽሞ ካህን እንደማይሆን ሲረዳ፣ ወደ የሕግ ጥናት ለተወሰነ ጊዜ ፊቱን ቢያዞርም በመጨረሻ ግን ይህንንም ትቶ ሕይወቱን ለወንጌል ለመስጠት ወሰነ። ሆኖም ሰባኪ ለመሆን አመነታ። በተፈጥሮው ድንጉጥ (ዓይናፋር) የነበረው ካልቪን የዚህ ቦታ ሃላፊነት ሸክም ስለከበደው አሁንም ጥናቱን በትጋት ለመቀጠል ወሰነ። የጓደኞቹ ልባዊ ውትወታ ግን በመጨረሻ አሸነፈው። “ትውልዳቸው እጅግ ዝቅተኛ ከሆኑት መካከል አንዱ ወደዚህ ታላቅ ክብር ከፍ ከፍ ማለቱ ግሩም ነው።” አለ።-Wylie, b. 13, ch. 9።GCAmh 163.3

    ካልቪን ያለ ኮሽታ ወደ ሥራው ገባ፤ የሚናገራቸው ቃላትም በምድር ላይ እንደሚወርድና እንደሚያድስ ጠል ነበሩ። ወንጌሉን በመውደድዋ ምክንያት ለወንጌሉ ደቀ-መዛሙርት ሁሉ ጥበቃዋን በዘረጋችው ልዕልት ማርጋሬት ጥበቃ ሥር ሆኖ ከፓሪስ ወጥቶ ከክፍለ ሃገር ከተሞች በአንዱ ይኖር ነበር። ካልቪን ደግ፣ አስመሳይነት የሌለበት ገና ለጋ ወጣት ነበረ። በየሰዎች ቤት በመሄድ ሥራውን ጀመረ። በቤተሰቡ አባላት ተከቦ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበ የድነትን እውነት ገለጠ። የሰሙ ሁሉ መልካሙን ወንጌል ለሌሎች እያሰሙ ብዙም ሳይቆይ አስተማሪው ከከተማው ወጥቶ በአቅራቢያው ወዳሉት ጥቃቅን ከተሞች ብሎም መንደሮች ሁሉ ዘለቀ። ከግንብ እስከ ጎጆ ድረስ መግቢያ በማግኘት ለእውነት ምስክሮች ለመሆን ለፍርሃት እጅ የማይሰጡ ክርስቲያኖችን የሚያፈሩ የአብያተ ክርስቲያናት መሰረት እየጣለ ወደ ፊት ገሰገሰ።GCAmh 163.4

    ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ፓሪስ ተመለሰ። ያልተለመደ ሽብር በተማሩ ሰዎችና ሊቃውንት ዙሪያ ነበር። የጥንታዊ ቋንቋዎች ጥናት ሰዎችን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መርቷቸዋል፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ልባቸው ያልተነካ በርካታ ሰዎች በፍላጎት ይወያዩባቸው፣ እንዲያውም ከሮማዊነት ቀንደኞች ጋር ጦርነት ይገጥሙባቸው ነበር። በመንፈሳዊ ትምህርት ዙሪያ የሚነሳን አለመግባባት በአሸናፊነት ለመወጣት ብቃቱ የነበረው ቢሆንም ካልቪን ግን ከእነዚህ ምላሳም ምሁራን የላቀ የሚያከናውነው ግብ ነበረው። የሰዎች አዕምሮ ተነቃቅቶ ስለነበር ይህ ጊዜ እውነቱን ያውቁ ዘንድ ትክክለኛ ሰዓቱ ነበር። የዩኒቨርሲቲዎቹ አዳራሾች በስነ-መለኮት ንትርክ ጩኸት ተሞልተው ሳለ ካልቪን ቤት ለቤት እየዞረ ለሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እየገለጠ ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ ይሰብክላቸው ነበር።GCAmh 163.5

    በእግዚአብሔር አቅርቦት ፓሪስ ወንጌሉን ትቀበል ዘንድ ሌላ ጥሪ ሊቀርብላት ነበር። በለፈቭሪና በፋረል የተደረገው ጥሪ ተቀባይነት ባያገኝም በዚያች ታላቅ መዲና በሚኖሩ ሁሉም የሕብረተሰብ መደቦች እንደገና መልእክቱ ይሰማ ዘንድ ነበረው። የፖለቲካዊ እሳቤዎች ተጽዕኖ ያደረጉበት ንጉሡ ሙሉ ለሙሉ ከሮም ጋር ተባብሮ የተሐድሶው ጠላት ገና አልሆነም ነበር። ማርጋሬትም ፕሮቴስታንታዊነት በፈረንሳይ የበላይነቱን ይይዛል የሚለውን ተስፋዋን አሁንም አጥብቃ እንደያዘች ነበረች። የተሐድሶው እምነት በፓሪስ መሰበክ አለበት ብላ ቆረጠች። ንጉሡ ባልነበረበት ጊዜ በከተማዋ በነበሩ አብያተ ክርስቲያናት የፕሮቴስታንት አገልጋይ እንዲሰብክ አዘዘች። ይህ ውሳኔዋ በጳጳሳዊ ባለስልጣናት በመከልከሉ ልዕልቷ ቤተ መንግሥቱን ወለል አድርጋ ከፈተችው። አንድ የቤተ መንግሥቱ ፎቅ የፀሎት ቤት እንዲሆን ተመቻችቶ በየቀኑ በተወሰነ ሰዓት ስብከት እንደሚሰበክ በማወጅ በየትኛውም አካባቢ፣ የየትኛውም መደብ አባል የሆኑ ሰዎች መጥተው እንዲሳተፉ ጥሪ ተደረገ። ሕዝብ ወደ ቦታው ጎረፈ። ለቤተ ክርስቲያንነት የተዘጋጀው ስፍራ ብቻ ሳይሆን የበሩ መዳረሻዎችና አዳራሾች ሳይቀሩ በሕዝብ ተጥለቀለቁ። የተከበሩ ሰዎች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የሕግ ሰዎች፣ ነጋዴዎችና የእጅ ሙያተኞች…. በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ ይሰበሰቡ ነበር። ንጉሡ ስብሰባዎቹን በመከልከል ፈንታ፣ በፓሪስ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ሁለቱ ክፍት እንዲሆኑ አዘዘ። ከአሁን በፊት ከተማዋ እንዲህ በእግዚአብሔር ቃል ስትነቃቃ ታይቶ አይታወቅም። ከሰማይ የመጣ የሕይወት መንፈስ በሕዝቡ ላይ እፍ የተባለበት መሰለ። ራስን መግዛት፣ ንጽህና፣ ሥነ-ሥርዓትና ታታሪነት የሰካራምነትን፣ የሴሰኝነትን፣ የፀብንና የቦዘኔነትን ቦታ ተኩ።GCAmh 164.1

    [ጳጳሳዊው] የስልጣን ተዋረድ ግን አርፎ አልተቀመጠም ነበር። ንጉሡ ስብከቱን ለማስቆም ጣልቃ ለመግባት እምቢ ስላለ ፊታቸውን ወደ ሕዝቡ አዞሩ። ያልተማረውንና በአጉል አምልኮ (በመላምት) ተጠፍሮ የተያዘውን ሕዝብ ፍርሃት፣ አግባብነት የሌለው ጥላቻና ወግ አጥባቂነት ለመኮርኮር ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም። ለሐሰተኛ አስተማሪዎች በጭፍን አጅዋን በመስጠት፣ ፓሪስ፣ እንደ ጥንትዋ የሩሳሌም የመጎብኘትዋን ጊዜ አላወቀችም፤ ለሰላምዋም የሚሆነውን ልብ ትል ዘንድ አልተቻላትም። የእግዚአብሔር ቃል ለሁለት ዓመት በከተማዋ ተሰበከ። ብዙ ወንጌሉን የተቀበሉ ሰዎች ቢኖሩም ቅሉ አብዛኛው ሕዝብ ግን አሻፈረኝ አለ፤ ፍራንሲስ የመቻቻል ባህርይ ያንፀባረቀው ለራሱ ጥቅም ሲል ነበርና ጳጳሳዊያኑ የበላይነቱን ለመቆናጠጥ ተሳካላቸው። ዛሬም እንደገና አብያተ ክርስቲያናት ተዘጉ፤ የመቃጠያ ስፍራው ተዘጋጀ።GCAmh 164.2

    ካልቪን በጥናት በተመስጦና በፀሎት ጊዜ በመውሰድ ለቀጣይ ሥራው እየተዘጋጀ፣ ብርሃኑንም እያስፋፋ ገና በፓሪስ ነበር። ሆኖም በመጨረሻ [የህገ-ወጥነት] ጥርጣሬ ተላከከበት። ገዥዎች ወደ እሳት ያመጡት ዘንድ ቆርጠው ተነሱ። በተገለለው ስፍራ የነበረው ካልቪን በራሱ ላይ አደጋ ይመጣል የሚል ጥርጣሬ ያልነበረው ሲሆን ወዳጆቹ በፍጥነት ወደ ክፍሉ በመምጣት ሹሞች ሊይዙት እየመጡ እንደሆነ ነገሩት። በዚህ ቅጽበት የውጨኛው በር በኃይል ተንኳኳ። የደቂቃ ፍርቃጭ ሊባክን አይገባም። የተወሰኑት ወዳጆቹ የመጡትን ሹሞች በማገድ፣ የተቀሩት በመስኮት እንዲወርድ በመርዳት ወደ ከተማዋ ዳርቻ በፍጥነት እንዲኮበልል ተደረገ። በዚያም የተሐድሶው ደጋፊ በሆነ ሰው ጎጆ ተጠልሎ ያስጠጋውን ሰው ልብስ ለብሶ ራሱን በመደበቅ መኮትኮቻ በትከሻው ይዞ ጉዞውን ጀመረ። ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመጓዝ በማርጋሬት ግዛት ሥር መጠጊያ አገኘ። (D’Aubigné, History of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 2, ch. 30ን ይመልከቱ።)GCAmh 164.3

    በኃይለኛ ወዳጆች ጥበቃ ስር ሆኖ፣ እንደተለመደው በጥናት ተወጥሮ ለጥቂት ወራት በዚህ ስፍራ ተቀመጠ። ፈረንሳይን በወንጌል ለመድረስና ክርስቲያን ለማድረግ በልቡ ወስኖ ስለነበር ምንም ሳይሰራ ለብዙ ጊዜ መቀመጥ አልተቻለውም። ማዕበሉ ቀዝቀዝ ከማለቱ ዩኒቨርሲቲ ባለበት፣ አዲሱ አስተሳሰብም በመልካም በሚታይበት በፓይቲየርስ አዲስ የሥራ መስክ ለማግኘት ሞከረ። በሁሉም መደቦች ያሉ ሰዎች ወንጌሉን በደስታ አደመጡ። በግልጽ ስብከት አይካሄድም ነበር፤ በዋና ዳኛው ቤት፣ በመኝታ ክፍሉ፣ አንዳንድ ጊዜም በሕዝባዊ መናፈሻ ስፍራዎች መስማት ለሚፈልጉ ሁሉ ካልቪን የዘላለምን የሕይወት ቃል ከፈተላቸው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሚሰሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ ከከተማ ውጪ መሰብሰቡ አደጋ የሌለው መሆኑ ታመነበት። የተንጠለጠሉ ቋጥኞችና ዛፎች የሸፈኑት ጥልቅና ጠባብ በሆነ ሸለቆ ጎን ያለ ዋሻ ለመሰብሰቢያነት ተመረጠ። ሰዎች በትናንሽ ቡድን እየሆኑ፣ በተለያዩ መንገዶች ወደዚህ ስፍራ ይሄዱ ነበር። በዚህ ፀጥ ባለ ዘዋራ ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ ይነበብና ይብራራ ነበር። በዚህ ስፍራ የጌታ እራት በፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈፀመ። ከዚህ ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ታማኝ ወንጌላዊያን ወደ ሌሎች ስፍራዎች ተልከዋል።GCAmh 165.1

    አሁንም እንደገና ካልቪን ወደ ፓሪስ ተመለሰ። ፈረንሳይ እንደ አገር ተሐድሶውን ትቀበላለች የሚለው ተስፋው አሁንም አልጠፋም ነበር። ሆኖም፣ ሁሉም ማለት ይቻላል፣ እያንዳንዱ የሥራ ደጃፍ ተከርችሞ አገኘው። ወንጌሉን መስበክ ቀጥታ ወደ መቃጠያ ስፍራ የሚወስደውን መንገድ መከተል መሆኑን ሲያውቀው በመጨረሻ ወደ ጀርመን ለመሄድ ወሰነ። እርሱ በለቀቀበት ቅጽበት በፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች ላይ ማዕበል በመነሳቱ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ በእርግጥ መጥፊያው በሆነ ነበር።GCAmh 165.2

    አገራቸው ከጀርመንና ከስዊዘርላንድ ጋር መሳ ለመሳ እንድትራመድ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው የፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች የሮምን መሰረተ-ቢስ መላምቶች ከስሩ በመምታት አገሪቱን የሚያነቃንቅ የጀግንነት ተግባር ለመፈጸም ቆርጠው ተነሱ። በመሆኑም በአንድ ሌሊት የካቶሊክን የቁርባን ሥርዓት የሚያወግዙ ማስታወቂያዎች (ጽሁፎች) በፈረንሳይ አገር በሙሉ ተለጥፈው አደሩ። ይህ ቀናኢ ሆኖም የሚያመጣው ውጤት በስህተት የተገመተው ተግባር፣ ይህንን ሥራ ለሰሩት ብቻ ሳይሆን የተሐድሶው እምነት ወዳጆች በሆኑት በፈረንሳይ አገር በሞላ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እልቂትን አመጣ። ይህ ድርጊት ሮማውያኖቹ ሲጠብቁት የነበሩትን፣ ማለትም ለዙፋኑ መረጋጋትና ለአገሪቱ ሰላም ጠንቅ የሆነ አደጋ የሚሰብኩ እንደሆኑ በማሳየት መናፍቃውያን ፈጽመው እንዲደመሰሱ ጥያቄ ለማቅረብ፣ ለረጅም ጊዜ ሲሹት የነበረውን ምክንያት ማግኘት አስቻላቸው።GCAmh 165.3

    በምስጢራዊ እጅ - ጥንቃቄ በጎደለው ወዳጅ ይሁን በጽኑ ጠላት ፈጽሞ ባልታወቀ ሁኔታ - ከተበተኑት ጽሁፎች አንዱ በንጉሡ ግላዊ ክፍል በር ላይ ተለጥፎ ተገኘ። ንጉሠ ነገሥቱ በድንጋጤ ተሞላ። ለዘመናት ክብር ይሰጣቸው የነበሩ አጉል እምነቶች ያለገደብ ተነቅፈው፣ ተዋርደው ነበር። ግልጽና አስገራሚ የሆኑትን ንግግሮች ታይቶ በማይታወቅ ድፍረት ወደ ንጉሣውያን ስፍራ በማምጣታቸው የንጉሡ ቁጣ ነደደ። ከመገረሙ የተነሳ መናገር አቅቶት እየተንቀጠቀጠ ለጥቂት ጊዜ ቆመ። ከዚያም በእነዚህ አስደንጋጭ ቃላት አፉን መክፈት ቻለ፦ “ሁሉም ይያዙ፤ ሉተራዊነት ሙሉ በሙሉ ይደምሰስ።”-Ibid, b. 4, ch.10። ዕጣው ተጣለ። ንጉሡ በሮም ጎን ሙሉ በሙሉ ለመሰለፍ ቆረጠ።GCAmh 165.4

    በፓሪስ እያንዳንዱን ሉተራዊ ለመያዝ እንቅስቃሴዎች ወዲያው ተጀመሩ። አማኞችን ወደ ምስጢራዊ መሰብሰቢያቸው ሁልጊዜ የሚጠራ የተሐድሶው እምነት ደጋፊ የሆነ ድሃ፣ የእጅ ሥራ ሞያተኛ ተያዘ። የሚባለውን ካልፈፀመ በስተቀር ወዲያውኑ በእሳት እንደሚቃጠል ተነግሮት የጳጳሱን ልዑክ በፓሪስ ወደሚኖር ወደ እያንዳንዱ ፕሮቴስታንት ቤት እንዲመራ ታዘዘ። በዚህ ሃሳብ በድንጋጤ ቢሸማቀቅም በመጨረሻ በእሳት የመቃጠሉ ፍርሃት አሸንፎት የወንድሞቹ ከሃዲ ይሆን ዘንድ ተስማማ። በጳጳሱ ልዑክ የተመራ፣ በዕጣን ተሸካሚዎች፣ በቀሳውስት፣ በመነኩሴዎችና በወታደሮች ተከቦ ንጉሣዊው መርማሪ ሞሪን ከከሃዲው ጋር በመሆን በዝግታና በፀጥታ በፓሪስ ከተማ መንገዶች አለፈ። ይህ ሰልፍ የተደረገው በተቃዋሚዎቹ አማካኝነት የተዋረደውን ስነ-ሥርዓት ማለትም “ቅዱስ ቁርባን” የሚገባውን ክብር ለመስጠት ማስመሰያ አጀብ ነበር። በዚህ አጀብ ስር ግን የተደበቀ አላማ ነበር። በሉተራዊ ቤት ተቃራኒ አቅጣጫ ሲደርሱ፣ ከሃዲው ምልክት ያሳይ ነበር፤ ቃል ግን ትንፍሽ አይባልም ነበር። ሰልፉ ይቆምና ወደ ቤት ተገብቶ ቤተሰቡ ተጎትቶ ይወጣና በሰንሰለት ተጠፍሮ አዲስ ተጠቂዎችን ለመያዝ ወደፊት ይገሰገስ ነበር። “ትንሽም ሆነ ትልቅ የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች እንኳ ሳይቀሩ፣ ምንም የተረፈ ቤት አልነበረም። ሞሪን መላ ፓሪስ እንድትንቀጠቀጥ አደረገ።” “የሽብር ግዛት ተጀምሮአል።”-Ibid, b. 4, ch.10።GCAmh 166.1

    ሰለባዎቹ በአሰቃቂ ስቃይ፣ ጣዕረሞታቸው እንዲራዘም እሳቱ ለሰስ ብሎ እንዲነድድ ተደርጎ ተገደሉ። ነገር ግን እንደ ድል አድራጊዎች ሞቱ። አቋማቸው ሳይናወጥ፣ ሰላማቸው ሳይደበዝዝ አረፉ። አሳዳጆቻቸው፣ ፍንክች የማይለውን አቋማቸውን ለማስለወጥ አቅመ ቢስ በመሆናቸው፣ ተሸናፊነት ተሰማቸው። “የወንጀለኛ መገደያ መድረኮች በፓሪስ ከተማ ተሰራጩ፣ በተከታታይ ቀናትም ቃጠሎ ተካሄደ፤ ግድያውን በማስፋፋት የኑፋቄን ድንጋጤ ለማሰራጨት ታልሞ ድርጊቱ ተከናወነ። ሆኖም በመጨረሻ ድርጊቱ የጠቀመው ወንጌሉን ነበር። አዲሱ አስተሳሰብ ምን ዓይነት ሰዎችን ማፍራት እንደሚችል ፓሪስ በሞላ እንዲገነዘብ አደረገ። እንደ ሰማዕታት የሬሳ ቁልል ያለ የስብከት መድረክ የለም። ወደ መታረጃ ስፍራው ሲሄዱ ፊታቸውን ያፈካው ሰላማዊ ደስታ፤ በሚያርመጠምጠው ቋያ መሃል ቆመው ያስመሰከሩት ጀግንነት፤ በጉዳታቸው እንኳ ያንፀባረቁት የይቅር-ባይነት ትህትና፤ ጥቂት የማይባሉ ተመልካቾችን ቁጣ ወደ ሃዘን፣ ጥላቻቸውን ወደ ፍቅር በቅጽበት በመቀየር ወንጌሉን ወክሎ ሊቋቋሙት በማይችሉት አንደበተ ርቱዕነት ተማጽኖውን አስተጋባ።”-Wylie, b. 13, ch. 20።GCAmh 166.2

    የሕዝቡ ቁጣ እንደገነፈለ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚጥሩት ቀሳውስት በአሰቃቂ ወንጀሎች ፕሮቴስታንቶቹን በመኮነን ወሬውን አሰራጩት። ካቶሊኮችን ለመጨረስ፣ መንግሥትን ለመገልበጥና ንጉሡን ለመግደል እንዳሴሩ ተደርገው ተወነጀሉ። የቀረበውን ውንጀላ የሚደግፍ አንድ ስንኳ መረጃ ሊቀርብ አልቻለም። ከዚህ ፍጹም በተለየ ሁኔታ እና ተቃራኒ በሆነ የገፀ ባህርይ መንስኤነት ቢሆንም እነዚህ የክፋት ትንቢቶች ይፈፀሙ ዘንድ ነበራቸው። በካቶሊኮቹ አማካኝነት በንጹሀን ፕሮቴስታንቶች ላይ የተፈፀመው ጭካኔ፣ ሲጠራቀም ቆይቶ፣ ይመጣብናል ብለው ራሳቸው የተነበዩት፣ ያው እልቂት ከምዕተ ዓመታት በኋላ በንጉሡ፣ በመንግሥቱና በተገዥዎቹ ላይ ደርሷል። የደረሰው ግን በከሃዲ ሰዎችና በጳጳሳውያኑ በራሳቸው አማካኝነት ነበር። ከሦሥት መቶ ዓመታት በኋላ በፈረንሳይ ላይ የደረሰውን አስከፊ እልቂት ያመጣው የፕሮቴስታንትነት መመስረት ሳይሆን መጨቆን ነበር።GCAmh 166.3

    ጥርጣሬ፣ አለመተማመንና ፍርሃት ሁሉንም የሕብረተሰብ ከፍሎች ወረራቸው። በዚህ አጠቃላይ ነውጥ መካከል የሉተራዊያን አስተምህሮ፣ በተፅዕኖ፣ በትምህርትና በመልካም ስነ-ምግባር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባሉ ሰዎች አእምሮ ምን ያህል ስር እንደሰደደ የታየበት ነበር። የታማኝነትና የክብር የሥራ ቦታዎች በድንገት ባዶ ሆኑ። የጥበብ ሰዎች፣ አታሚዎች፣ ምሁራን፣ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ፕሮፌሰሮች፣ ፀሃፊያን፣ የንጉሣውያን አባላት ሳይቀሩ ደብዛቸው ጠፋ። ለመጀመሪያ ጊዜ የተሐድሶ እምነቱን እንደመረጡ በሚያስታውቅ ሁኔታ፣ በትውልድ አገራቸው ለመኖር እንደተከለከሉ ሆነው በመቶዎች የሚቆጠሩ ፓሪስን ለቀው ሸሹ። ሳይጠረጠሩ በመካከላቸው ሲኖሩ ስለነበሩት ስለነዚህ መናፍቃን ሲያስቡ ጳጳሳውያኑ በግርምት ተሞሉ። የነደደው ቁጣቸው ሊቆጣጠሯቸው በተቻላቸው ደካማ ብዙሃን ላይ ወረደ። ወህኒ ቤቶች ተጨናነቁ፤ የወንጌሉን መስካሪዎች ለማቃጠል በተቀጣጠለው እሳት ከሚነደው የሬሳ ክምር ከሚወጣው ጭስ የተነሳ አየሩ ጠቆረ።GCAmh 167.1

    የአሥራ ስድስተኛውን ምዕተ ዓመት የከፈተው ታላቁ የእውቀት ተሐድሶ እንቅስቃሴ መሪ በመሆኑ ፍራንሲስ 1ኛ ኩራት ይሰማው ነበር። ከእያንዳንዱ ስፍራ የተማሩ ሰዎችን በቤተ መንግሥቱ መሰብሰብ ያስደስተው ነበር። ለትምህርት ያለው ፍቅር፣ እንዲሁም ለመነኮሳቱ ድንቁርናና አጉል እምነት ያለው ንቀት ነበር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተሐድሶውን እንዲታገሰው ያደረገው። ነገር ግን ኑፋቄን ለማጥፋት ካለው ፍላጎት የተነሳ ይህ የእውቀት ደጋፊ በፈረንሳይ አገር ሁሉ የህትመት ሥራ እንዲቀር አዋጅ አወጣ! ፍራንሲስ 1ኛ፣ የማሰብና የመመራመር ባህል፣ ሐይማኖታዊ አለመቻቻልንና ስደትን ለማስቀረት መከለያ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ፣ ተመዝግበው ከሚገኙ፣ ከብዙዎቹ ምሳሌዎች አንዱ ነው።GCAmh 167.2

    በከበረና በሕዝብ ፊት በሚከናወን ሥነ-ሥርዓት ፈረንሳይ ፕሮቴስታንታዊነትን ለማጥፋት ሙሉ ለሙሉ የተሰጠች መሆንዋን ልትምሰክር ነበራት። ሥርዓተ-ቁርባን በመወገዙ ምክንያት ሰማይ ለደረሰበት ውርደት፣ በደም ስርየት እንዲደረግ፣ ንጉሡም ሕዝቡን ወክሎ ይህ አስከፊ ተግባር መታገዱን በአደባባይ እንዲናገር ቀሳውስቱ ጠየቁ።GCAmh 167.3

    ይህ አሰቃቂ ሥነ-ሥርዓት በጥር 21 ቀን 1535 ዓ.ም እንዲፈፀም ተወሰነ። መሰረተ-ቢሱ ፍርሃትና የአክራሪነት ጥላቻ በሃገሪቱ እንዲራገብ ተደረገ። በአቅራቢያው ስፍራዎች በመጡ እልፍ አእላፋት የፓሪስ መንገዶች ተጥለቀለቁ። ቀኑ ሊጀመር የታቀደው በታላቅና አሳማኝ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር። ሰልፉ በሚያልፍበት መስመር ያሉ ቤቶች በሃዘን አልባሳት ተጋርደው ነበር። በክፍተት በክፍተቶቹ ደግሞ መሰውያዎች ቆመው፣ በእያንዳንዱ በር ደግሞ “ለቁርባኑ/ለሥርዓተ-ሐይማኖቱ” ክብር ሲባል ችቦዎች ተቀጣጥለው ነበር። ገና ጎህ ሳይቀድ ሰልፉ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ጀመረ። ከሰበካዎች መስቀልና ሰንደቅ ቀጥሎ ሕዝቡ ሁለት በሁለት ሆኖ የተቀጣጠለ ችቦ ይዞ ይራመድ ጀመር። በአራት ደረጃ የሚቀመጡት መነኮሳት የየደረጃቸውን አልባሳት ለብሰው ተከተሉ። ከዚያም የጥንታዊ ቅዱሳት ስብስብ ቀጠለ። ከዚያም ሐይማኖታዊ ጌቶች በወይንጠጅና በደማቅ ቀይ መጎናጸፊያቸው ተሸልመው በጌጣጌጣማ ልብሳቸው አምረውና ደምቀው በሠረገላ ይከተሉ ነበር።GCAmh 167.4

    ዋና አስተናጋጁ በተጌጠ ጃንጥላ ስር፣ ከፍተኛውን ማዕረግ በያዙ አራት ልዑላን ታጅቦ ሲጓዝ፣ ከእነርሱ በኋላ ንጉሡ ያለ ዘውዱና ያለ ንጉሣዊ ልብሱ፣ ጭንቅላቱ ሳይሸፈን መሬት መሬት እየተመለከተ፣ የሚነድ ጧፍ በእጁ ይዞ ይከተል በር። እንዲህ ተደርጎ የፈረንሳይ ንጉሥ ለሰራው ሥራ እንደተፀፀተ በአደባባይ አሳየ። ነፍሱን ላረከሱት የክፋት ሥራዎች ሳይሆን፣ እጁን በደም ለነከረበት የንፁሃን ደም ሳይሆን፤ የቁርባን ሥርዓትን ለማውገዝ የደፈሩ በስሩ ያሉ ተገዥዎቹ ለሰሩት አሰቃቂ ኃጢአት ሲል በእያንዳንዱ መሰውያ ፊት በውርደት ራሱን ዝቅ እያደረገ ይሰግድ ነበር። ከእርሱ ቀጥሎ ሁለት በሁለት ሆነው የሚራመዱ፣ የሚነድ ችቦ የያዙ መንግሥታዊ ባለስልጣናትና ንግስቲቱ ነበሩ።GCAmh 168.1

    የቀኑ ፕሮግራም ሲቀጥል ንጉሡ በግዛቱ ላሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጳጳሱ ቤተ-መንግሥት ባለው በታላቁ አዳራሽ ንግግር አደረገ። ሃዘን በወረሰው ፊት በፊታቸው በመቆም፣ በሃገሪቱ ላይ የመጣውን “ወንጀል፣ ስድብ፣ የሐዘንና የውርደት ቀን” ልብን በሚነካ ታላቅ የፀፀት ሃዘን ተናገረ። እያንዳንዱ ታማኝ ተገዥም ፈረንሳይን ለማጥፋት የተገዳደራትን የኑፋቄ ቸነፈር ሙሉ ለሙሉ ቆርጦ ለመጣል በሚደረገው ጥረት እንዲረዳ ጠየቀ። “ክቡራን በእውነት ንጉሣችሁ እንደመሆኔ” አለ “በዚህ ቀፋፊ መበስበስ ከእግሬ ወይም ከእጄ አንዱ እንደ ቆሸሸ ወይም እንደ ተመረዘ ባውቅ፣ እንድትቆርጡት እሰጣችኋላሁ…. በተጨማሪም ከልጆቼ አንዱ በእርሱ [በኑፋቄ] ረክሶ ባይ አልምረውም…. እኔ ራሴ አቅርቤው ለእግዚአብሔር እሰዋዋለሁ።” የእንባ ስቅታ ንግግሩን ያቋርጠው ነበር። የተሰበሰቡት ሁሉ አለቀሱ፤ በአንድ ድምጽ ሆነውም “በካቶሊክ ኃይማኖት እንኖራለን፣ እንሞታለንም” ሲሉ ጮሁ። D’Aubigné, History of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 4, ch. 12።GCAmh 168.2

    የእውነትን ብርሐን አሻፈረኝ ያለችው አገር የወደቀባት ደጎጎን እጅግ አሰቃቂ ሆነ። “የሚያድን…. ፀጋ” [ቲቶ 2÷11] ተገለጠ፤ ሆኖም ፈረንሳይ ሃይሉንና ቅድስናውን ካየች በኋላ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ በመለኮታዊ ውበቱ ከተሳቡ በኋላ፤ ከተሞችና ጎጆዎች በብርሐን ጮራው ከፈኩ በኋላ፤ በብርሐን ፈንታ ጽልመትን መርጣ ፊትዋን አዞረች። ሰማያዊ ስጦታ ሲሰጣቸው አንፈልግም ብለዋል። በራሳቸው ፈቃድ ወደ ራስ ማታለል እስኪወድቁ ድረስ ክፋትን መልካም፣ መልካምንም ክፋት በማለት ፈርጀዋል። አሁን ሕዝቦቹን በማሳደድ እግዚአብሔርን እያገለገሉ እንደሆነ በእርግጥ ቢያምኑ እንኳን ቅንነታቸው ከበደል ነፃ ያደርጋቸው ዘንድ አልቻለም። ከመታለል የሚያድናቸውን፣ በደም-በደለኝነት ነፍሳቸውን ከመበከል የሚያተርፋቸውን ብርሐን በፈቃዳቸው እምቢ ብለዋል።GCAmh 168.3

    ሕያው እግዚአብሔርን በምትረሳ፣ ከሶስት መቶ ዓመታት አካባቢ በኋላ “የአመክንዮ ጣዖት አምላክ”ን (Goddess of Reason) መሪ አድርጋ በታላቁ ቤተ መቅደስ ውስጥ በምትሾም አገር፣ በዚሁ ታላቅ ቤተ-መቅደስ ውስጥ ኑፋቄን ለማጥፋት ቃለ መሃላ ተፈፀመ። አሁንም እንደገና ሰልፉ ተካሄደ፤ ቃል የገቡትን ሥራ ለመጀመር የፈረንሳይ ልዑካን ተንቀሳቀሱ። ወደ ተነሱበት ሲመለሱ በየክፍተቱ መናፍቃንን የሚያርዱበት የመግደያ ስፍራዎች ተዘጋጁ። ንጉሡ ሲመጣም የሬሳ ክምሩ እንዲቀጣጠል፣ ንጉሡም የተፈፀመው አጠቃላይ አሰቃቂ ድርጊት ምስክር እንዲሆን ተመቻቸ። ዘግናኝ ከመሆናቸው የተነሳ፣ እነዚህ የክርስቶስ ምስክሮች ያለፉባቸውን ሰቆቃዎች ለመዘርዘር የሚቻል አይሆንም። በተጠቂዎች ዘንድ ግን አንዳች መዋዠቅ አይታይም ነበር። እንዲክድ ሲጠየቅ አንዱ እንዲህ አለ፦ “ያመንኩት ነብያትና ሐዋርያት በጥንት የሰበኩትን፣ ሁሉም ቅዱሳን በህብረት ያመኑትን ነው። እምነቴ የገሃነምን ኃይል የሚቋቋም፣ በእግዚአብሔር የታመነ ነው።” D’Aubigné, History of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 4, ch. 12።GCAmh 168.4

    ሰልፉ በተደጋጋሚ በማሰቃያ ስፍራዎቹ ይቆም ነበር። ጧት ከተነሱበት ከቤተ መንግሥቱ ሲደርሱ፣ ሕዝቡ ተበተነ፤ በቀኑ በተደረገው ነገር ረክተው፣ ራሳቸውን እንኳን ደስ ያለህ ብለው፣ አሁን የተጀመረው ሥራ የኑፋቄን መደምሰስ ለመቋጨት እንደሚቀጥል በማመን ንጉሡና የቤተ ክህነት መሪዎችም ወደየስፍራቸው ሄዱ።GCAmh 169.1

    ፈረንሳይ አልቀበልም ያለችው የሰላም ወንጌል በእርግጥም ፈጽሞ ሊመነገል ነበረው፤ ውጤቱም እጅግ አሰቃቂ የሚሆን ነበረ። ፈረንሳይ ተሐድሶ አራማጆችን ለማሳደድ ሙሉ ለሙሉ ራስዋን ከሰጠች ልክ ከሁለት መቶ ሃምሳ ስምንት ዓመታት በኋላ፣ በጥር 21 ቀን 1793 ዓ.ም፣ በዛው ቀን፣ ከበፊቱ እጅግ የተለየ ዓላማ ያነገበ ሰልፍ በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ተደረገ። “አሁንም ዋና ተዋናዩ ንጉሡ ነበር፤ እንደገናም ኹከትና ጩኸት ነበር፤ ዛሬም እንደገና ለተጨማሪ ሰለባዎች ጥያቄ ይቀርብ ነበር፤ እንደገና ዛሬም ጥቁር የመግደያ ስፍራዎች ነበሩ፤ እንደገና ዛሬም የቀኑ ክስተቶች በዘግናኝ እልቂት የተደመደሙ ነበሩ። ሉይስ ፲፮ኛ በአሳሪዎቹና በገዳዮቹ እጅ ለእጅ እየታገለ ወደ መጋደሚያው ተመራ፤ መጥረቢያው እስኪወድቅበት ድረስ በኃይል ተጭኖ ከተያዘ በኋላ የተቆረጠ አንገቱ በመግደያ አግዳሚው ላይ ወደቀ።”-D’Aubigné, b. 13, ch. 21። ተጠቂው ግን ንጉሡ ብቻ አልነበረም። እዛው በተገደለበት ስፍራ አቅራቢያ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ሰዎች፣ በማረጃ ማሽን ተገድለው፣በደም አፋሳሾቹ የሽብር ግዛት ቀናት ሰለባ ሆነዋል።GCAmh 169.2

    የእግዚአብሔርን ሕግ መመሪያዎች ማህተም በመግለጥና በሰዎች ህሊና ላይ ያለውን መጠይቅ በማስቀመጥ ተሐድሶው ለዓለም የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ አበረከተ። ዘላለማዊ ፍቅር የሰማይን ሕጎችና ደንቦች ለሰዎች ገለጠ። እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ጠብቁአት አድርጓአትም፤ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው። በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና።” [ዘዳ 4÷6]። ፈረንሳይ የሰማይን ስጦታ እምቢ ስትል የብጥብጥና የጥፋትን ዘር ዘራች። የማይቀረው የመንስኤና ውጤት ሂደትም በአብዮቱና በሽብር የግዛት ዘመኑ ተንፀባረቀ።GCAmh 169.3

    በመፈክሮቹ (በሕዝባዊ አዋጆቹ) አማካኝነት የተቀሰቀሰው ስደት ከመጀመሩ ቀደም ካለ ጊዜ በፊት ደፋርና ቆራጡ ፋረል ከተወለደበት ቀየው እንዲኮበልል ተገድዶ ነበር። በስዊዘርላንድ በመቀመጥ የዝዊንግልን ሥራ በመድገም ሚዛኑ ወደ ተሐድሶው እንዲደፋ አደረገ። የመጨረሻዎቹ ዓመታቱ በዚሁ ሥፍራ ሆኖ ያለፉ ቢሆኑም በፈረንሳይ ለነበረው ተሀድሶ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን መቀጠል ችሏል። በስደቱ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በተለይ በተወለደበት አገሩ ወንጌል እንዲስፋፋ ጥሯል። ብጥብጡን በታላቅ ትኩረትና ትጋት በመከታተል በምክሩና በአበረታች ንግግሩ በመርዳት በድንበር አካባቢ ሆኖ ለአገሩ ሰዎች ወንጌልን በመስበክ አያሌ ጊዜ አጥፍቷል። ከሌሎች ስደተኞች ጋር በመተባበር በጀርመን ተሐድሶ መሪዎች የተፃፉት ጽሁፎች ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ፤ ከፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጋርም በብዛት እንዲታተሙ አድርጓል። በመጽሐፍ አዙዋሪዎችም አማካኝነት እነዚህ ሥራዎች በስፋት በፈረንሳይ አገር ተሸጠዋል። በዝቅተኛ ዋጋ ለመጽሐፍ ሻጮቹ በማስረከብ ከዚያ የሚገኘው ትርፍ ሥራውን ለማስቀጠል ችሏል።GCAmh 169.4

    ፋረል ሥራውን በስዊዘርላንድ ሲጀምር ተራ አስተማሪ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ደብቆ ነበር። ፈንጠር ወዳለ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በዚያ የልጆች አስተማሪ ሆነ። በልጆቻቸው አማካኝነት ወላጆቻቸውን የመድረስ ተስፋ ይዞ ከተለመደው የትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ በጥንቃቄ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች አስተዋወቀ። የተወሰኑ ያመኑ ነበሩ፤ ነገር ግን ቀሳውስቱ ሥራውን ሊያስቆሙ መጡ፤ በአጉል እምነት የተያዙ የገጠር ሰዎችም በተቃውሞ እንዲነሳሱ ተደረጉ። “መሰበኩ የሚያመጣው ሰላም ሳይሆን ጦርነት መሆኑ የሚታይ በመሆኑ” እያሉ ቀሳውስቱ ገፋፉ፣ “ይህ የክርስቶስ ወንጌል ሊሆን አይችልም።”-Wylie, b. 14, ch. 13። ልክ እንደመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በአንዱ ሲያባርሩት ወደ ሌላው ከተማ ኮበለለ። ከመንደር መንደር፤ ከከተማ ወደ ከተማ ይዘዋወር ነበር። በእግሩ እየሄደ ድካምን፣ ቅዝቃዜንና ረሃብን እየተጋፈጠ፣ ለሕይወት አደጋ በሞላበት ስፍራ ሁሉ ለፋ። በገበያ ስፍራዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ አንዳንድ ጊዜም በካቴድራል መድረክ ላይ ይሰብክ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑ ፍጹም ባዶ ሆኖ ያገኘዋል፤ ሌላ ጊዜም ስብከቱ በጫጫታና በውግዘት ይቋረጣል፤ ከመድረክም በኃይል ተጎትቶ ይወርድ ነበር። ከአንድ ጊዜ በላይ በጀሌው ሕዝብ ሊሞት እስኪል ድረስ ተደብድቦ ያውቃል። ቢሆንም ሥራውን ወደፊት ቀጠለ። ቢመከትበትም ኧህ በማይል ፅናት እንደገና ወደ ማጥቃቱ ይመለሳል። አንዱ ሌላውን እየተከተለ፣ የጳጳሳዊ ሥርዓት አይነተኛ ምሽግ የነበሩ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች ለወንጌሉ በራቸውን ወለል አድርገው ሲከፍቱ ተመለከተ። መጀመሪያ ሥራ የጀመረባት ትንሿ ሰበካ የተሐድሶ እምነትን ተቀበለች። የሞራትና የኒውቻቴል ከተሞችም የሮማዊ ሥርዓተ-አምልኮን በማውገዝ የጣዖት ቅርጻቅርጻቸውን ከአብያተ ክርስቲያናቶቻቸው አስወገዱ።GCAmh 170.1

    ፋረል የፕሮቴስታንትን እምነት በዠኔቫ ለመትከል የረጅም ጊዜ ፍላጎት ነበረው። ይህች ከተማ ልትማረክ ብትችል በፈረንሳይ፣ በስዊዘርላንድና በኢጣሊያ ላለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ማዕከል መሆን ትችላለች። ይህንን አላማ አንግቦ በከተማዋ ዙሪያ ያሉት ብዙ ትንንሽ ከተሞችና መንደሮች እስኪለወጡ ድረስ ጣረ። ከዚያም አንድ ረዳት ብቻ አስከትሎ ጀኔቫ ገባ። የተፈቀደለት ግን ሁለት ስብከት ብቻ ነበር። በመንግሥት ባለስልጣናት እንዲወገዝ ያደረጉት ጥረት ያልተሳካላቸው ቀሳውስት ሕይወቱን ለማጥፋት ቆርጠው በመጎናጸፊያቸው ስር መሳሪያ ደብቀው ወደ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዲመጣና እንዲገኝ አደረጉት። በቁጣ የነደደ፣ ዱላና ሰይፍ የያዘ ሕዝብ፣ ከቀሳውስቱ ቢያመልጥና ቢወጣ ለመግደል ተዘጋጅቶ አዳራሹን ከውጪ ከቦ ነበር። የዳኞችና የታጠቁ ወታደሮች መኖር ግን ሕይወቱን አተረፈው። በሚቀጥለው ማለዳም ከጓደኛው ጋር ሃይቁን አቋርጦ እንዲሄድና ከአደጋ እንዲያመልጥ ተደረገ። ጀኔቫን በወንጌል ለመድረስ ያደረገው የመጀመሪያው የወንጌል ጥረትም በእንዲህ ሁኔታ አለቀ።GCAmh 170.2

    ለሚቀጥለው ሙከራ አንድ ምስኪን መሳሪያ ይሆን ዘንድ ተመረጠ። ይህ ተራ ሰው እዚህ ግባ የማይባል ገጽታ ስለነበረው በተሐድሶው ታማኝ ወዳጆች እንኳ ቀዝቃዛ መስተንግዶ እንዲደረግለት የሚጋብዝ አይነት ነበር። ፋረል ተቀባይነት ባጣበት ስፍራ እንዲህ አይነቱ ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል? እጅግ ጠንካራና ጀግና የተባለው ሰው እንዲፈረጥጥ ያስገደደውን ማዕበል እንዴት ድፍረትና ልምድ የሌለው ሊቋቋመው ይችላል? “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” [ዘካ 4÷6]። “ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤” ምክንያቱም “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፤ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።” [1ኛ ቆሮ 1÷27፣ 25]።GCAmh 170.3

    ፍሮመንት አስተማሪ ሆኖ ሥራውን ጀመረ። እርሱ ለልጆች በትምህርት ቤት ያስተማራቸውን እውነቶች እነርሱ ደግሞ በየቤታቸው ደገሙአቸው። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ሲብራራ ለመስማት ወላጆች መጡ፣ የትምህርት ቤቱ ክፍልም በጥሞና በሚያዳምጡ ሰዎች ተሞላ። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትና በራሪ ጽሑፎች ያለ መከልከል ተሰራጩ፤ አዲሱን አስተምህሮ በአካል መጥተው ለመስማት ላልደፈሩ ለብዙዎች መልእክቱ በዚህ አማካኝነት ደረሳቸው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህ አገልጋይም ለመኮብለል ተገደደ፤ ያስተማራቸው እውነቶች ግን በሰዎች አእምሮ ውስጥ ሥር ሰደው ነበር። የተሐድሶው ችግኝ ተተክሎአል፤ እየተጠናከረና እየሰፋም ሄደ። ሰባኪዎቹ ተመለሱ፤ በልፋታቸውም በስተመጨረሻ የፕሮቴስታንት አምልኮ በዠኔቫ ተመሠረተ።GCAmh 171.1

    ከብዙ መንከራተትና ውጣ ውረድ በኋላ ካልቪን የዚችን ከተማ በሮች ከፍቶ ሲገባ፣ ከተማዋ ቀደም ብላ ተሐድሶውን እንደተቀበለች አውጃ ነበር። የትውልድ መንደሩን ለመጨረሻ ጊዜ ጎብኝቶ ሲመለስ ወደ ባሰል እያቀና በነበረበት ቀጥተኛ መንገድ ላይ የቻርለስ 5ኛ ጦር ሰራዊት ስለነበር፤ ወደ ዠኔቫ የሚወስደውን ጠመዝማዛማ መንገድ መጓዝ ግድ ሆነበት።GCAmh 171.2

    ፋረል ይህ ጉብኝት የእግዚአብሔር እጅ እንዳለበት ተገነዘበ። ዠኔቫ የተሐድሶውን እምነት ብትቀበልም ገና መሰራት ያለበት ብዙ ሥራ ይቀር ነበር። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያለባቸው በግል እንጂ በአንድነት እንደ ማህበረሰብ አይደለም። በግለሰቡ ልብና ህሊና ውስጥ መጀመር ያለበት እንደገና የመወለድ ሥራ የሚተገበረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንጂ ጉባኤዎች ባስተላለፏቸው አዋጆች አይደለም። የሮምን ስልጣን ከላያቸው ቢያወርዱም በአስተዳደርዋ ስር ተንሰራፍተው የነበሩትን የክፋት ሥራዎች ለመተው ግን የዠኔቫ ነዋሪዎች ያን ያህል ዝግጁ አልነበሩም። እዚህ ስፍራ ንጹህ የወንጌሉ መርሆዎችን ለመመስረትና አምላክ እንዲይዙት እየጠራቸው የሚመስለውን የሃላፊነት ደረጃ ለመቆናጠጥ የተገባቸው ይሆኑ ዘንድ ማዘጋጀት ቀላል ሥራ አልነበረም።GCAmh 171.3

    ከራሱ ጋር ተቀናጅቶ በዚህ ሥራ ላይ በአንድነት ሊሰራ የሚችል አጋር በካልቪን እንዳገኘ ፋረል እርግጠኛ ነበር። ወጣቱ ወንጌላዊ በዚህ ስፍራ በመሆን እንዲሰራ በእግዚአብሔር ስም በጥብቅ ተማፀነው። ካልቪን በስጋት ወደ ኋላ አፈገፈገ። ዓይናፋርና ሰላም ወዳድ የነበረው ካልቪን፣ ከደፋሩ፣ ግላዊና አንዳንዴም ነውጠኛ መንፈስ ካለው ዠኔቫዊ ጋር መነካካትን ስላልፈለገ አፈገፈገ። የማያኮራው ጤናውና የማጥናት ልምዱ ይህንን ሥራ ላለመሥራት እንዲወስን መሩት። በብዕሩ አማካኝነት የተሐድሶውን አላማ በላቀ ሁኔታ አሳካለሁ የሚለው እምነቱ ለጥናት ምቹ የሆነ ፀጥተኛ ስፍራ እንዲመርጥና በዚያም በመሥራት በህትመት አማካኝነት አብያተ ክርስቲያናትን ማስተማርና መገንባት ለመቀጠል እንዲወስን ገፋፋው። የፋረል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ግን ከሰማይ እንደመጣ ጥሪ ሆነበት፤ እምቢ ይል ዘንድ አልተቻለውም። “የእግዚአብሔር እጅ ከሰማይ ተዘርግቶ የያዘውና፣ እስኪለቀው ቸኩሎ ከነበረው ስፍራ ጋር እንዳይላቀቅ ያጣበቀው” እንደመሰለው ተናግሯል። D’Aubigné, History of the Reformation in Europe in the Time of Calvin, b. 9, ch. 17።GCAmh 171.4

    በዚህ ጊዜ የፕሮቴስታንቱ ጉዳይ ከባድ አደጋ ተጋርጦበት ነበር። የሊቀ ጳጳሱ የእርግማን ነጎድጓ በዠኔቫ ላይ አስተጋባ፣ ኃያላን መንግሥታትም እንደሚያጠፏት ዛቱ። ነገሥታትና ንጉሠ ነገሥታትን ያንበረከከን ይህንን ኃያል የስልጣን ተዋረድ ይህች ትንሽ ከተማ እንዴት ልትቋቋም ትችላለች? የዓለማችን ታላላቅ ድል አድራጊዎችን ሰራዊት እንዴት አድርጋ ልትቋቋም ትችላለች?GCAmh 172.1

    በመላው የክርስትና ዓለም ፕሮቴስታንታዊነት በኃይለኛ ባላንጣዎች ጥቃት ሲጋረጥበት ኖሯል። የመጀመሪያዎቹ የተሐድሶው ድሎች ካለፉ በኋላ ጥፋቱን ለማረጋገጥ ተስፋ በማድረግ ሮም አዲስ ኃይል አሰባሰበች። በዚህ ጊዜ እጅግ ጨካኝ፣ ይሉኝታ ቢስ፣ በኃይል ተወዳዳሪ የሌላቸው የጳጳሱ ደጋፊዎች፣ የጀስዊቶች መዋቅር ተፈጥሮ ነበር። ከእያንዳንዱ ምድራዊ ትስስርና ሰብዓዊ ፍላጎት ፈጽመው የተገለሉት፣ ለተፈጥሮአዊ ፍላጎት መጠይቆች ምውት የሆኑት፣ ምክንያታዊነትንና ህሊናን ፈጽመው የለጎሙት፣ ከራሳቸው መዋቅር በቀር ሌላ ሕግ ወይም ትብብር የማያውቁት ጀስዊቶች፣ የእነርሱን መዋቅር ስልጣን ከማስፋፋት በቀር ሌላ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የክርስቶስ ወንጌል፣ የተቀበሉት አደጋን እንዲጋፈጡ፣ ስቃይን እንዲችሉ፣ ቁር፣ ረሃብ፣ ልፋትና ድህነት ሳይበግራቸው የመሰዊያውን እንጨት፣ ወህኒ ቤቱንና የመቃጠያ ስፍራውን ፊት ለፊት እየተገናኙ የእውነትን ሰንደቅ እንዲያውለበልቡ አስችሏቸዋል። እነዚህን ኃይላት ለመመከት፣ ተመሳሳይ አደጋዎችን መጋፈጥ እንደሚገባቸው፣ ጀስዊትነት ተከታዮቹን በማበረታታት የእውነትን ኃይል ለመቋቋም የማታለያ መሳሪያዎች ሁሉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አደረገ። ለጀስዊታዊያን፣ ለመፈጸም የሚከብድ፣ አሰቃቂ ነው ብለው የሚፈርጁት ወንጀል፣ ለማከናወን ወራዳ ነው የሚሉት ማጭበርበሪያ፣ ለመደበቅ ከባድ ስለሆነ አንሞክረውም የሚሉት ተግባር አልነበራቸውም። በድህነትና ሁል ጊዜ ዝቅ ብሎ ለመኖር ቃል ገብተው፣ ፕሮቴስታንታዊነትን ለመገልበጥና ጳጳሳዊ የበላይነትን እንደገና ለመመስረት ይጠቀሙበት ዘንድ ሃብትና ስልጣን ማካበት የተጠና አላማቸው ነበር።GCAmh 172.2

    የመዋቅራቸው አባላት ሆነው በሚታዩበት ጊዜ የቅድስና አልባሳታቸውን በመልበስ፣ ወህኒ ቤቶችንና የህክምና ተቋማትን በመጎብኘት ለበሽተኞችና ለድሆች እርዳታ በማድረግ፣ መልካም እያደረገ ከቦታ ቦታ ይዞር የነበረውን የተቀደሰውን የየሱስን ስም ተሸክመው ዓለም-በቃኝ ማለታቸውን ለማሳየት ይሞክሩ ነበር። ነገር ግን በዚህ ነቀፋ በማይቀርብበት ውጫዊ ማንነት ሥር ዘግናኝ ወንጀልና ገዳይ የሆኑ አላማዎች ተደብቀው ነበር። የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው [መልካም የሆነን ነገር ለማስገኘት ሲባል የሚፈፀም ማንኛውም አይነት ጥፋት እንደክፋት አይቆጠርም] የሚለው አባባል የመዋቅሩ መሰረታዊ መመሪያ ነበር። በዚህ ደንብ መሰረት የቤተ ክርስቲያንን ጥቅም ለማስከበር እስከዋሉ ድረስ መዋሸት፣ መስረቅ፣ የሐሰት የምስክርነት ቃል መስጠትና ሰውን መግደል ይቅርታ የሚደረግላቸው በደሎች ብቻ ሳይሆኑ የሚበረታቱም ነበሩ። በተለያዩ ሽፋኖች አማካኝነት ጀስዊቶች የመንግሥትን የኃላፊነት ስፍራዎች ለመቆናጠጥ በመሥራት፣ የነገሥታት አማካሪዎች በመሆን የአገራትን ፖሊሲዎች ቅርጽ ለማስያዝ ለፉ። በበላዮቻቸው ላይ ሰላይ ይሆኑ ዘንድ አገልጋዮቻቸው ሆኑ። ለልዑላንና ለተከበሩ ሰዎች ኮሌጆችን፣ ለተራው ሕዝብ ደግሞ ትምህርት ቤቶችን መሰረቱ። ከዚያም ፕሮቴስታንት ወላጅ ያላቸው ልጆች የጳጳሳዊውን ኃይማኖት ሥርዓት (ፀሎተ-ፍትሃት) ያከብሩ ዘንድ ተሳቡ። ይህ ደማቅና የውጫዊ ታይታ ያለበት የሮማዊነት አምልኮ አዕምሮን ለማደናበር፣ ለማስደመምና ትኩረት በመሳብ ህሊናን ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ ዋለ። በመሆኑም አባቶቻቸው የለፉለትና የደሙለት ነፃነት በልጆቻቸው ክህደት ተፈፀመበት። ጀስዊቶች በመላው አውሮፓ በፍጥነት በመሰራጨት በሄዱበት ሁሉ ጳጳሳዊ ሥርዓት እንደገና ይታደስ ነበር።GCAmh 172.3

    ከቀድሞው የበለጠ ስልጣን ያጎናጽፋቸው ዘንድ የካቶሊክን የመንፈሳዊ ልዩ ፍርድ ቤት (the lnquisition) እንደገና የሚያቆም አዋጅ ታወጀ። ለዚህ ነገር አጠቃላይ ጥላቻ ቢኖርም፣ ካቶሊካዊ አገራት እንኳ ሳይቀር በከፍተኛ ጥላቻ የሚመለከቱት ቢሆንም፣ ይህ አሰቃቂ ፍርድ ቤት በጳጳሳዊ አስተዳደሮች አማካኝነት እንደገና እንዲቋቋም ተደርጎ፣ በብርሐን ለመፈጸም የሚዘገንኑ ግፎች በምስጢራዊ የምድር ውስጥ ወህኒ ቤቶች ተደገሙ። በንጽህናና በከበሩ ባህርያት ተወዳዳሪ የሌላቸው፣ የአስተሳሰብ ልቀት የነበራቸውና በጣም የተማሩ ሰዎች፣ ቅዱስና የተሰጡ ፓስተሮች፣ ታታሪና የሃገር ፍቅር ያላቸው ዜጎች፣ ድንቅ ምሁራን፣ ስጦታው ያላቸው የጥበብ ሰዎችና ባለሙያዎች፣ ባለእጆች፣ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር አበባዎች ታረዱ፤ የተቀሩትም አገር ለቀው ለመሰደድ ተገደዱ።GCAmh 173.1

    የተሐድሶውን ብርሐን ለማዳፈን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከሰዎች ለመንጠቅና የጨለማ ዘመኑን ድንቁርናና አጉል እምነት መልሳ ለማስፈን ሮም የምትተቀምባቸው መሳሪያዎች እንደዚህ አይነቶች ነበሩ። ነገር ግን በእግዚአብሔር በረከትና ሉተርን ይተኩ ዘንድ ባስነሳቸው በእነዚህ የከበረ ባህርይ ባለቤት በነበሩ ሰዎች ጥረት አማካኝነት ፕሮቴስታንታዊነት ይገለበጥ ዘንድ አልቻለም። የኃይሉ ምንጭ የልዑላን ድጋፍ ወይም የጦር መሳሪያዎቻቸው አልነበሩም። ከሁሉም ያነሱ ጥቃቅን ሃገራት፣ ዝቅተኛና ደካማ የተባሉ ሃገራት ጠንካራ ምሽጎቹ ሆኑ። ጥፋትዋን በሚያቀነባብሩ ኃያላን ባላንጣዎች ተከባ ትንሽዋ ዠኔቫ፤ በዚያን ዘመን ከነበሩት ንጉሣዊ ሃገራት በታላቅነትና በሃብት ተወዳዳሪ ያልነበራትን ፈላጭ ቆራጭዋን ስፔንን በሰሜናዊ ባህር በአሸዋ በተከበቡ ዳርቻዎችዋ የምትታገለው ሆላንድ፤ ገላጣና ባዶ የነበረችው ስዊድን፣ ነበሩ ለተሐድሶው ድልን ያጎናጸፉት።GCAmh 173.2

    መጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስን መርህ የሚከተል ቤተ ክርስቲያን ለመመስረት ከዚያም ተሐድሶውን በአውሮፓ በሙሉ ለማስፋፋት ካልቪን ለሰላሳ ዓመት ገደማ በዠኔቫ ለፋ። እንደ ሕዝባዊ መሪነቱ የተከተላቸው መንገዶች ከብልሽት የፀዱ፣ አስተምህሮውም ስህተት የሌለበት አልነበረም። ሆኖም እንደገና በፍጥነት እየተመለሰ የነበረውን የጳጳሳዊነት ማዕበል በመቃወም በጊዜው የተለየ አስፈላጊነት የነበራቸውን እውነቶች በማወጅ አብይ አጋዥ ኃይል ነበር። በተቋቋሙት የተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናትም በሮማዊ ትምህርት ይስፋፉ በነበሩት እብሪትና ብልሹነት ፈንታ ቀለል ያለና ንጹህ ሕይወት በማበረታታት ጉልህ ሚና ነበረው።GCAmh 173.3

    የተሐድሶውን አስተምህሮዎች ያሰራጩ ዘንድ ህትመቶችና አስተማሪዎች ከዠኔቫ ይወጡ ነበር። ስደት የሚካሄድባቸው አገራት ሁሉ ወደዚህች ቦታ ለትምህርት፣ ለምክርና ለመበረታታት ፊታቸውን ያዞሩ ነበር። የካልቪን ከተማ በምዕራባዊ አውሮፓ አገራት ሁሉ ለተሰደዱ መጠጊያ ሆነች። ለብዙ ምዕተ ዓመታት የቀጠለውን የስደት ማዕበል በመሸሽ ኮብላዮች ወደ ዠኔቫ በሮች ጎረፉ። ቆስለውና ተርበው ቤታቸውንና ወገናቸውን ተነጥቀው የመጡ ሁሉ ሞቅ ባለ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር። ይህንንም ስፍራ ቤታቸው በማድረግ በጉዲፈቻነት የተቀበለቻቸውን ከተማ በሞያቸው፣ በትምህርታቸውና በቅድስናቸው ባረኩዋት። በዚህ ስፍራ መጠለያ ሽተው የመጡ ብዙዎች የሮምን አምባገነናዊነት ለመቃወም ወደ መጡበት ተመልሰዋል። ጀግናው የስኮትላንድ ተሐድሶ አራማጅ ጆን ኖክስ፣ በርካታ የእንግሊዝ ፒዩሪታዊያን፣ የሆላንድ ፕሮቴስታንቶችና የፈረንሳይ ሂውጉኖቶች የእውነትን ችቦ ከዠኔቫ በመያዝ የየትውልድ አገራቸውን ጽልመት በብርሐን ለማፍካት ተንቀሳቅሰዋል።GCAmh 174.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents