Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፲—የተሐድሶ እድገት በጀርመን

    የሉተር ምስጢራዊ መሰወር በመላው ጀርመን ግርምትን ፈጥሮ ነበር። በሁሉም ስፍራ እርሱን የተመለከቱ ጥያቄዎች ይቀርቡ ነበር። ወፍ ዘራሽ ጭምጭምታዎች በየቦታው ይወሩ ነበር፤ ብዙዎች ተገድሏል ብለው አምነውም ነበር። ጓዶቹ እንደሆኑ በሚታወቁት ዘንድ ብቻ ሳይሆን አቋማቸውን ገና በግልጽ ያላሳወቁ በሺዎች በሚቆጠሩ የተሐድሶው ደጋፊዎች መካከልም መራር ሃዘን ነበር። ብዙዎች ሞቱን ለመበቀል ቁርጥ መሃላ አድርገው ነበር።GCAmh 137.1

    በእነርሱ ላይ የተነሳው የተቃውሞ ስሜት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ሲገነዘቡ ሮማውያኑ በድንጋጤ ተዋጡ። መጀመሪያ አካባቢ ሉተር ሞቷል መባሉ ቢያስደስታቸውም በኋላ ግን ከሕዝቡ ቁጣ መደበቅ አማራቸው። ጠላቶቹ፣ መጥፋቱ ያስጨነቃቸውን ያህል፣ በመካከላቸው ሆኖ ደፋር ምግባራትን ሲያከናውን አላሳሰባቸውም ነበር። ደፋሩን የለውጥ አራማጅ ለማጥፋት በቁጣ ሲንሩ የነበሩ ሁሉ አሁን ረዳት የለሽ እስረኛ ሆኖ ይሆናል በማለት በፍርሃት ተያዙ። “ከዚህ ሊያላቅቀን የሚችለው ብቸኛው አማራጭ” አለ አንዱ “ችቦአችን ለኩሰን ለምትፈልገው አገሩ እስክንመልሰው ድረስ ሉተርን ፍለጋ ምድሪቱን ማሰስ ነው።”-D’Aubigné, b. 9, ch. 1። የንጉሠ ነገሥቱ አዋጅ ምንም ኃይል የሌለው መሰለ። ከሉተር ዕጣ ፈንታ ያነሰ ትኩረት ስለተሰጠውም የጳጳሳዊው መሪዎች በቁጭት ተንገበገቡ።GCAmh 137.2

    የደህንነቱ ወሬ ሲሰማም እስረኛም ቢሆን የሕዝቡን ፍራቻ አረገበው፤ ለእርሱ ያላቸውን ድጋፍም አጠናከረው። ጽሁፎቹ ከምን ጊዜውም በበለጠ በጉጉት ይነበቡ ጀመር። በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ ለእግዚአብሔር ቃል የቆመውን ጀግና አላማ የሚደግፉ ቁጥራቸው እየጨመረ ሄደ። የተሐድሶ እንቅስቃሴው አቅም በቋሚነት እየጨመረ ነበር። ሉተር የበተነው ዘር በሁሉም ስፍራ ያቆጠቁጥ ጀመር። በአካል እያለ መፈፀም ያልቻለውን ሥራ መጥፋቱ አከናወነው። አሁን ታላቁ መሪያቸው ስለተወገደ ሌሎች ሰራተኞች የበለጠ ሃላፊነት ተሰማቸው። በታላቅ ጽናት የተጀመረው ሥራ እንዳይደናቀፍ በአዲስ እምነትና ልባዊ ተነሳሽነት ባላቸው ኃይል ሁሉ ወደፊት ሊያራምዱት ቆርጠው ተነሱ።GCAmh 137.3

    ሆኖም ሰይጣንም ሥራ-ፈት አልነበረም። በእያንዳንዱ የተሐድሶ እንቅስቃሴ የሞከረውን ተግባር እዚህም ጀመረው። እርሱም በእውነተኛው ሥራ ምትክ ሌላ ሐሰት እውነት አስመስሎ በማቅረብ ሕዝቡን ማጥፋት ነው። በክርስቲያንዋ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደተነሱ ሁሉ በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም እንዲሁ ሆነ።GCAmh 137.4

    በሐይማኖታዊው ዓለም በተነሳው ንውጠት በጥልቀት የተነኩ ጥቂት ሰዎች ከሰማይ የተለየ ራዕይ እንደተቀበሉ አድርገው ራሳቸውን በመቁጠር፣ በተልፈሰፈሰ ሁኔታ በሉተር ተጀምሯል ብለው ያወጁትን ተሐድሶ ጥግ ለማድረስ መለኮታዊ ውክልና እንደተሰጣቸው ተናገሩ። እውነታው ግን፣ ሉተር ያከናወነውን ያንኑ ሥራ እያፈራረሱ ነበር። የተሐድሶ መሰረት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ሁሉን በሁሉ የሆነ የእምነትና የሥራ መመሪያ ሕግ ነው የሚለውን ታላቅ መርህ አንቀበልም ብለው፣ በማይሳሳተው መመሪያ ምትክ የሚለዋወጠውን፣ እርግጠኛ መሆን የማይቻልበትን የራሳቸውን ስሜትና መረዳት አስቀመጡ። በዚህ ጥፋትንና ሐሰተኛነትን የሚያሳውቀውን ታላቁን ጠቋሚ (መለያ) ወደ ጎን የመገፍተር ድርጊት ሰይጣን እንዳሻው አዕምሮን የሚቆጣጠርበት በር ወለል ብሎ ተከፈተለት።GCAmh 137.5

    ከእነዚህ ነብያት አንዱ በመልአኩ ገብርኤል እንደታዘዘ ተናገረ። ከእነርሱ ጋር ይተባበር የነበረ አንድ ተማሪ ትምህርቱን በመተው ቃሉን ያብራራ ዘንድ በእግዚአብሔር በራሱ ጥበብ እንደተሰጠው አወጀ። ሌሎችም በተፈጥሯቸው ወደ ተስፈንጣሪነት ያጋደሉ ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ። የእነዚህ አንቀሳቃሾች ተግባራት የፈጠረው ስሜት ቀላል አልነበረም። የሉተር ትምህርት የለውጥን አስፈላጊነት በሁሉም ስፍራ አነሳስቶ ነበርና በዚህ ጊዜ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ጭምር በአዳዲሶቹ ነብያት አስመሳይነት ተታለሉ።GCAmh 138.1

    የእንቅስቃሴው መሪዎች ወደ ዊተንበርግ በመሄድ መጠይቃቸውን በሜላክቶንና በግብረ-አበሮቹ ላይ ለማስፈን ሞከሩ። “ሕዝቡን እናስተምር ዘንድ በእግዚአብሔር ተልከናል። ከእግዚአብሔር ከራሱ የተለየ መገለጥ ተቀብለናል፣ ስለሆነም ሊሆን ያለውን እናውቃለን፤ እኛ ሐዋርያቶችና ነብያቶች ነን፣ የምንናገረው እውነት ስለመሆኑም ዶክተር ሉተርን እንጠይቃለን።” አሉ -Ibid., b. 9, ch. 7።GCAmh 138.2

    የተሐድሶ አራማጆቹ ተደነቁ፤ ግራ ተጋቡም። ይህ ጉዳይ ከአሁን በፊት ገጥሟቸው የነበረ ባለመሆኑ ምን ዓይነት መንገድ መምረጥ እንዳለባቸው አላወቁም። ሜላክቶን እንዲህ አለ፦ “በእነዚህ ሰዎች ውስጥ ያሉት መናፍስት ተራ የሚባሉ አይነት አይደሉም፤ ሆኖም ምን አይነት መናፍስት?” “በአንድ በኩል የእግዚአብሔርን መንፈስ ማጥፋት እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሰይጣን መንፈስ እንዳንታለል እንጠንቀቅ።”-Ibid., b. 9, ch. 7።GCAmh 138.3

    የአዲሱ ትምህርት ፍሬ ሳይዘገይ ግልጽ ሆነ። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጎን እንዲያደርጉ ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲተውት ተመሩ። ትምህርት ቤቶች ሁሉ ወደ ድንግርግር ሰጠሙ። ተማሪዎቹ ቁጥጥሮችን ሁሉ እምቢ ብለው ትምህርታቸውን ትተው ከዩኒቨርሲቲ ወጡ። የተሐድሶውን ሥራ ለማነቃቃትና ለመቆጣጠር ራሳቸውን በበቂ ሁኔታ ያስተማሩ ሁሉ ማድረግ የቻሉት ተሐድሶውን ወደ ጥፋት አፋፍ ላይ ማድረስ ነበር። አሁን ሮማውያኑ ልበ ሙሉነታቸውን እንደገና ተጎናጽፈው በኩራት “አንድ ተጨማሪ ጥረት፣ ከዚያ ሁሉም የኛ ይሆናል” አሉ።-Ibid., b. 9, ch. 7።GCAmh 138.4

    በዋርትበርግ የነበረው ሉተር የሆነውን ሲሰማ በጥልቅ ጭንቀት “ሰይጣን ይህንን ወረርሽኝ እንደሚልክብን ሁሌም እጠብቅ ነበር።” አለ።-Ibid., b. 9, ch. 7። የአስመሳዮቹን ነብያት ባህርይ በመረዳት የእውነትን ግብ የተገዳደረውን አደጋ ተመለከተ። የሊቀ-ጳጳሱና የንጉሠ ነገስቱ ተቃውሞ እንደዚህ ታላቅ ግራ መጋባትና መጨነቅ ውስጥ አልከተተውም ነበር። ከተሐድሶው ታማኝ ወዳጆች መካከል ተወዳዳሪ የሌላቸው ጠላቶች ተነሱ። ለሉተር ታላቅ ደስታና መጽናናት የለገሱት እውነቶች ጥልንና ድንግርግርን በቤተ ክርስቲያን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ዋሉ።GCAmh 138.5

    በተሐድሶ ሥራው ሉተር የተነሳሳው ወደፊትም የተራመደው በእግዚአብሔር መንፈስ ነበር፤ ከራሱ አቅምም እንዲያልፍ ተደርጎ ነበር። የያዛቸውን ስፍራዎች ለመያዝም ሆነ ይህን ያህል መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አልሞ አልተነሳም። ወሰን በሌለው ኃይል እጅ ውስጥ መሳሪያ ከመሆን ውጪ ሌላ አላደረገም። ሆኖም ለሥራው ውጤት በመንቀጥቀጥ ይተጋ ነበር። በአንድ ወቅት ሲናገር፣ “ድሃና የማይታወቅ ቢሆንም እንኳ፣ አስተምህሮዬ አንድን ሰው ጎድቶ ከሆነ - ያው ራሱ ወንጌል ስለሆነ መጉዳት አይቻለውም እንጂ - ቢጎዳ ኖሮ [አስተምህሮዬን]ሳልተወው ከምቀጥል አሥር ጊዜ የሞት ቅጣት ብቀበል ይሻለኛል” ብሏል።-Ibid., b. 9, ch. 7።GCAmh 138.6

    አሁን ደግሞ ዊተንበርግ ራሱ - የተሐድሶ እንብርት የሆነው ከተማ - በጽንፈኝነትና በሕግ-አልባነት ኃይል ሥር በፍጥነት እየወደቀ ነበር። ይህ አሰቃቂ ክስተት ከሉተር አስተምህሮ የተነሳ የተፈጠረ አልነበረም። ሆኖም በመላው የጀርመን አገር ጠላቶቹ በሙሉ የርሱ ሥራ እንደሆነ አድርገው ይከሱት ጀመር። ነፍሱ መራራ ስትሆንበት “የዚህ የተሐድሶው ታላቅ ሥራ መጨረሻ ይህ ይሆንን?” ብሎ አንዳንዴ ይጠይቅ ነበር። እንደገና ደግሞ በፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገል ሰላም ወደ ልቡ ይፈስ ነበር። “ሥራው የእኔ አይደለም፤ የራስህ ነው” ይላል “በመላምትና አክራሪነት ይበላሽ ዘንድ አትተወውም።” በእንደዚያ ያለ ችግር ውስጥ ከትግሉ ርቆ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚቻለው ስላልነበር ወደ ዊተንበርግ ለመመለስ ወሰነ።GCAmh 139.1

    ሳይዘገይም አደገኛውን ጉዞ ተያያዘው። በመንግሥት ማዕቀብ ስር ነበር። ጠላቶቹም ሕይወቱን ለማጥፋት ነፃነት ነበራቸው። ወዳጆቹ እንዳይረዱት፣ እንዳያስጠጉትም ተከልክለዋል። በተከታዮቹ ላይ ከባድ እርምጃ ለመውሰድ ዘውዳዊው መንግሥት በዝግጅት ላይ ነበር። ነገር ግን የወንጌሉ ሥራ ከባድ አደጋ ሲወድቅበት ሲመለከት ያለፍርሃት ለእውነት ይጋደል ዘንድ በጌታ ስም ሊፋለም ወጣ።GCAmh 139.2

    ለመራጩ በተጻፈ ደብዳቤ ዋርትበርግን ለመልቀቅ ያለውን ውሳኔ ከገለጸ በኋላ ሉተር፦ “ወደ ዊተንበርግ ልሄድ መሆኔን ለግርማዊነትዎ እያሳወቅሁ ከመራጭ ጥበቃ ኃይል ይልቅ እጅግ ኃያል በሆነው ጥበቃ ስር መሆኔን እገልጻለሁ። የርስዎን ጥበቃ የመጠየቅ ሃሳብ የለኝም። ከግርማዊነትዎ ለእኔ ጥበቃ ከመጠየቅ ይልቅ ምኞቴ እርስዎን መጠበቅ ነው። የግርማዊነትዎ ጥበቃ የሚከልለኝ መሆኑን ባውቅ ኑሮ ወደ ዊተንበርግ አልመጣም ነበር። ይህንን አላማ መንግሥታዊ ሰይፍ ወደፊት ሊያራምደው አይችልም። ያለ ሰው እርዳታ ወይም ትብብር እግዚአብሔር ሁሉንም ማከናወን አለበት። ተወዳዳሪ የሌለው እምነት ያለው እርሱ ጠንካራ ምሽግ ነው።”-Ibid., b. 9, ch. 8።GCAmh 139.3

    ወደ ዊተንበርግ እየሄደ ለሁለተኛ ጊዜ በፃፈው ደብዳቤ ሉተር ሲናገር፣ “እነሆ የግርማዊነትዎን ነቀፋና የዓለሙን ሁሉ ንዴት ልሸከም ዝግጁ ነኝ። የዊተንበርግ ነዋሪዎች የእኔ የራሴ በጎች አይደሉምን? እግዚአብሔር ለእኔ ጥበቃ አደራ አልሰጣቸውምን? አስፈላጊ ከሆነስ ሕይወቴን እሰጥላቸው ዘንድ አይገባኝምን? በተጨማሪም እግዚአብሔር አገራችንን የሚቀጣበት በጀርመን አገር ሁሉ የሚነሳ አመጽን ማየት አልወድም።”-Ibid., b. 9, ch. 8።GCAmh 139.4

    በታላቅ ጥንቃቄና ትህትና ሆኖም በጠንካራ ውሳኔና አይበገሬነት ወደ ሥራው ገባ። “በቃሉ አማካኝነት” አለ “በአመጽ ቦታና ተፅዕኖ ያተረፈውን፣ ያንን፣ ሃሰት መሆኑን አጋልጠን ማባረር አለብን። የአጉል አምልኮ ተከታዮችንና እምነት የሌላቸውን በመቃወም ኃይል አልጠቀምም።” “የማስገደድ ተግባር አይከናወንም። ለህሊና ነፃነት ስለፋ ኖሬአለሁ። የእምነት ፍሬ ነገሩ ነፃነት ነው።”-Ibid., b. 9, ch. 8።GCAmh 139.5

    ብዙም ሳይቆይ፣ ሉተር እንደተመለሰ ሊሰብክም እንደሆነ በዊተንበርግ ሁሉ ወሬው ተሰራጨ። ከሁሉም አቅጣጫ ሕዝቡ ጎረፈ፣ ቤተ ክርስቲያኑም ሞልቶ ተትረፈረፈ። ወደ መድረኩ ወጥቶ በታላቅ ጥበብና ትህትና አስተማረ፤ መከረ፤ ገሰፀም። የካቶሊክን ሐይማኖታዊ ስነ-ሥርዓት ለማጥፋት ኃይል የተጠቀሙ አንዳንድ ሰዎችን ሲገስጽም እንዲህ አለ፦GCAmh 140.1

    “የቁርባን-ስርዓቱ መጥፎ ነገር ነው። እግዚአብሔር የሚቃወመው ነው። መቅረት የሚገባው ነው፤ በእርሱ ምትክ የወንጌሉ መብል (የጌታ እራት) በሁሉም ስፍራ ቢቋቋም ምኞቴ ነው። ማንም ግን በግዳጅ እንዲተወው አይሁን። ውጤቱን ለእግዚአብሔር እንተወው። መሥራት ያለብን እኛ ሳንሆን ቃሉ ነው ‘ለምን እንደዚህ ይሆናል?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ ምክንያቱ ደግሞ እንደ ሸክላ ሰሪው ሸክላ የሰዎች ልብ በመዳፌ ውስጥ አይደለም። የመናገር መብት አለን፤ የማስገደድ ግን አንዳችም መብት የለንም። እኛ እንስበክ የቀረው የእግዚአብሔር ጉዳይ ነው። ኃይል ብጠቀም ምን አተርፋለሁ? የተኮሳተረ ፊት፣ የሚያምሩ ገፅታዎች፣ የተጨናነቀ አንድ-አይነትነትና ግብዝነት። ልባዊ ሀቀኝነት ግን የለም፤ እምነት የለም፤ ፍቅር የለም። እነዚህ በጎደሉበት ሁሉም ጎዶሎ ነው። ለእንደዚህ አይነቱ ድል ቅንጣት (ምንም) ዋጋ አልሰጥም። እኔና እናንተ፣ ዓለም ሁሉ በአንድ ላይ ሆነን ማከናወን ከሚንችለው ይልቅ እግዚአብሔር ቀላል በሆነው የቃሉ ኃይል የበለጠ ይሰራል። እግዚአብሔር ልብን በቁጥጥሩ ስር ያደርጋል፣ ልብ ከተወሰደ ሁሉም ይሸነፋል።”GCAmh 140.2

    “ለመስበክ፣ ለመከራከር፣ ለመፃፍ ዝግጁ ነኝ፤ ማንንም ግን አላስገድድም፤ እምነት የፈቃደኝነት ተግባር ነውና። እስካሁን ያደረኩትን አስታውሱ። ሊቀ-ጳጳሱን፣ የስርየት ሽያጮችንና ጳጳሳዊያኑን ተቃውሜ ቆሚያለሁ፤ በአመጽና በግርግር ግን አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል አቀረብኩ፤ ሰበኩ፤ ጻፍኩ፤ እዚያ ላይ አቆምኩ። እኔም ስጋደምና ስተኛ አንድም ልዑል ወይም ንጉሠ-ነገስት ያላደረገውን የሰበኩት ቃል የሊቀ-ጳጳሱን ኃይል አንኮታኮተው። በእኔ በኩል ያደረኩት ምንም ያህል አይደለም ሊባል የሚችል ነው። የቃሉ ኃይል ሁሉን ሥራ አከናወነ። ጉልበት ወደ መጠቀም ዞሬ ቢሆን ኖሮ ጀርመን በደም ጎርፍ ትታጠብ ነበር። ግን ውጤቱ ምን ይሆን ነበር? የአካልና የነፍስ ጥፋት። ስለሆነም እኔ ዝም ብዬ ቃሉ በምድሪቱ ወርድና ርዝመት እንዲሰራጭ አደረግሁ።”-Ibid., b. 9, ch. 8።GCAmh 140.3

    ቀን በቀን፣ ሳምንቱን ሙሉ ሉተር በጉጉት ለሚያዳምጠው ሕዝብ ሰበከ። የእግዚአብሔር ቃል የአክራሪነትን ስሜት ሰበረ። የወንጌሉ ኃይል በስህተት የተመሩትን ሰዎች ወደ እውነት መንገድ መለሳቸው።GCAmh 140.4

    ሥራቸው ታላቅ ክፋት ያመጣውን ተስፈንጣሪዎች ሊጋጠማቸው ሉተር ፍላጎት አልነበረውም። ሚዛናዊ አስተያየት የሌላቸው፣ ያልተቀጣ ፍላጎት ያላቸው ከሰማይ ልዩ መገለጽ የተሰጠን ነን ቢሉም ትንሿን ልዩነት ታግሰው ማለፍ የማይችሉ፣ ከመልካም የመነጨ ተግሳጽ ወይም ምክር የማይቀበሉ እንደሆኑ ያውቅ ነበር። ከፍተኛውን ስልጣን ለራሳቸው ወስደው ሌላው ሕዝብ ያለጥያቄ ጌትነታቸውን እንዲቀበል የሚፈልጉ ነበሩ። ከእርሱ ጋር ቃለ-መጠይቅ እንዲያደርጉ ጥያቄ ሲያቀርቡለት ግን ሊገናኛቸው ፍቃደኛ ሆነ። አስመሳይነታቸውን በተሳካ ሁኔታ ስላጋለጠባቸው አጭበርባሪዎቹ ወዲያውኑ ዊተንበርግን ለቀው ሄዱ።GCAmh 140.5

    አክራሪነት ለተወሰነ ጊዜ ተገታ፣ ሆኖም ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንደገና በከባድ ነውጥና በአሰቃቂ ውጤት ታጅቦ ፈነዳ። የዚህን እንቅስቃሴ መሪዎች አስመልክቶ ሉተር ሲናገር፦ “ለእነርሱ ቅዱስ መፃሕፍት ምውት ቃላት ናቸው፤ ሁሉም ‘መንፈስ! መንፈስ!’ ብለው መጮህ ጀመሩ። በእርግጥ መንፈሳቸው ወደሚመራቸው እኔ አልሄድም። ከእንደነዚህ አይነት ቅዱሳን በስተቀር ሌላ ወደሌለባት ቤተ ክርስቲያን እንዳልሄድ እግዚአብሔር በምህረቱ ይጠብቀኝ። ድጋፉንና ማጽናናቱን ያገኙ ዘንድ ከልባቸው ወደ እግዚአብሔር ከሚቃትቱትና ከሚያለቅሱት ኃጢአታቸውን ከሚያውቁት ትሁት ደካማና ህመምተኛ ሰዎች ጋር እንዳመልክ ምኞቴ ነው።”-Ibid., b. 9, ch. 10።GCAmh 141.1

    የአክራሪዎቹ ዋና አቀንቃኝ የነበረው ቶማስ ሙንዘር፣ ግሩም ችሎታ ያለው፣ ለመልካም ቢጠቀምበት ጥሩ መሥራት የሚያስችለው ሰው ነበር፤ የእውነተኛ ኃይማኖት የመጀመሪያዎቹን መርሆዎች ግን ያልተማረ ነበር። ሌሎቹ አጫፋሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ መታደስ የሚጀምረው ከራሱ መሆኑን ዘንግቶ ዓለምን ይለውጥ ዘንድ እግዚአብሔር እንደቀባው አድርጎ ያስብ ነበር። የስልጣን እርከንንና ተፅዕኖ ማሳረፍን እጅግ ይመኝ ነበርና ሁለተኛ መሆን፣ በሉተር ስር መሆን እንኳ ፈቃደኛ አልነበረም። የተሐድሶ አራማጆቹ የጳጳሳዊውን ስልጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን በመተካት ለየት ያለ ጳጳሳዊ ሥርዓትን ከመገንባት በቀር ሌላ እንዳላደረጉ አወጀ። ትክክለኛውን ለውጥ ለማስተዋወቅ እርሱ ራሱ በመለኮት እንደተላከ ተናገረ። “መንፈሱ ያለው እርሱ” አለ ሙንዘር “መጽሐፍ ቅዱስን በእድሜው ሙሉ አይቶ የማያውቅ ቢሆንም እውነተኛ እምነት አለው።”-Ibid., b. 9, ch. 10።GCAmh 141.2

    የአክራሪዎቹ መምህራን እያንዳንዱ ሃሳብና ትርታ ከእግዚአብሔር የመጣ ድምጽ እንደሆነ እየቆጠሩ በግምት ይተዳደሩ ነበር። ከዚህም የተነሳ ወደ ጥልቅ ጽንፈኝነት አመሩ። እንዲያውም አንዳንዶቹ “ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” [2ኛ ቆሮ 3÷6] እያሉ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አቃጠሉ። የሰውን ሃሳብና ግምት ከእግዚአብሔር ቃል በላይ በማስቀመጥ የኩራት ጥማታቸውን በማርካት ማራኪ ነገር የሚመኘውን የሰውን ፍላጎት በማሟላቱ የሙንዘር ትምህርት ተቀባይነት አገኘ። አስተምህሮዎቹ በሺዎች ተቀባይነትን አገኙ። የሕዝባዊ አምልኮ ሥርዓትን በመኮነን ልዑላንን መታዘዝ እግዚአብሔርንና ቤልሆርን (ሰይጣንን) በአንድ ላይ ለማምለክ መሞከር መሆኑን አወጀ።GCAmh 141.3

    የጳጳሳዊውን ሥርዓት ቀንበር አሽቀንጥሮ መጣል የጀመረው የሕዝቡ አዕምሮ በመንግሥታዊ ስልጣን ገደቦችም ትዕግስቱ እያለቀ መጣ። መለኮታዊ ፈቃድ እንዳለው የሚናገረው የሙንዘር አብዮታዊ አስተምህሮ ከማናቸውም ቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ፣ በራሳቸው ሚዛን ያልጠበቀ አስተሳሰብና ጠንካራ ፍላጎት እንዲተዳደሩ መራቸው። አሰቃቂ የአመጽና የጥል ገጽታዎች ተከሰቱ፤ የጀርመን መስኮች በደም ረሰረሱ።GCAmh 141.4

    ሉተር በኤርፈርት እያለ ገና ቀደም ብሎ የነፍሱ ውጋት የነበረ ጉዳይ ቢኖርም አሁን አክራሪነት በተሐድሶው ላይ አንዣቦ ሲመለከት ስቃዩ በእጥፍ ይደቁሰው ጀመር። ጳጳሳዊያኑ ልዑላን የተከሰተው አመጽ ከሉተር አስተምህሮ የሚጠበቅ ውጤት መሆኑን አወጁ፤ ብዙዎችም ይህንን አነጋገር ሊደግፉ ዝግጁ ነበሩ። ይህ ክስ ምንም ዓይነት መሰረት የሌለው ቢሆንም በተሐድሶ አራማጁ ላይ ያመጣው ነገር ቢኖር ውጥረትን ነበር። የእውነት ጉዳይ ከተዋረደው አክራሪነት ጋር ተመድቦ ውርደት ሲደርስበት ማየት መሸከም ከሚችለው በላይ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሉተር አስተምህሮአቸውን መቃወሙና በመለኮት የተነሳሱ መሆናቸውን ካለመቀበሉ በተጨማሪም የመንግሥትን አገዛዝ አሻፈረኝ ያሉ ናቸው ብሎ በመናገሩ የአመጹ መሪዎች ጠሉት። በአጸፋውም ሉተር ወራዳ አስመሳይ ነው ብለው አወጁበት። የልዑላንንና የሕዝቡን ጥላቻ በራሱ ላይ ያመጣ ይመስል ነበር።GCAmh 141.5

    ተሐድሶው በፍጥነት እንደሚንኮታኮት ጠብቀው ሮማውያኑ ተፍነከነኩ። ለማስተካከል እጅግ ሲለፋባቸው የነበሩትን ስህተቶች እንኳ የሉተር ጥፋት እንደሆኑ አድርገው ወነጀሉት። የአክራሪው መደብ ታላቅ የፍርድ መጓደል እንደተፈጸመበት አድርጎ በሃሰት በማስመሰሉ የብዙ ሕዝብ አዘኔታን ማግኘት ቻለ። በስህተት ጎን የተሰለፉ ሁሉ እንደሚያጋጥማቸው የተለመደ ሁኔታ፣ ሰማዕታት እንደሆኑ ተቆጠሩ። እንደዚህም ተሐድሶውን በሚችሉት ሁሉ ኃይላቸው የተቃወሙት ታዘነላቸው፤ የጭካኔና የጭቆና ሰለባ እንደሆኑም ተወራላቸው። ይህ በተመሳሳዩ የአመጽ መንፈስ የተነሳሳ መጀመሪያ በሰማይ የተገለጸው የሰይጣን ሥራ ነበር።GCAmh 142.1

    ሰይጣን በተደጋጋሚ ሰዎችን ለማሳት ይጥራል፤ ኃጢአትን ጽድቅ፣ ጽድቅን ደግሞ ኃጢአት ብለው ይጠሩ ዘንድ ይመራቸዋል። ሥራው ደግሞ እንዴት ውጤታማ ሆኖአል! እውነትን ደግፈው ያለ ፍርሃት በመቆማቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ታማኝ ባሪያዎች ምን ያህል ውግዘትና ነቀፋ ይሰነዘርባቸዋል! የሰይጣን ልዑካን የሆኑ ሰዎች ይመሰገናሉ፣ በስንቱ ውዳሴ ይደለላሉ፤ ይባስ ብሎም እንደ ሰማዕታት ይታያሉ። ለእግዚአብሔር ባላቸው ታማኝነት የተነሳ መከበርና መደገፍ የሚገባቸው ሰዎች በጥርጣሬና በእምነት ማጣት እየታዩ ብቻቸውን ይተዋሉ።GCAmh 142.2

    ትክክለኛ የሚመስል የኃሰት ቅድስና (counterfeit holiness)፣ እንዲሁም የውሸት ቅድስና (supurious sanctification) አሁንም የማታለል ሥራውን እየሰራ ነው። አዕምሮዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በመለየት ሰዎች ለእግዚአብሔር ሕግ ለመታዘዝ ይሁንታቸውን ከመስጠት ይልቅ የራሳቸውን ስሜትና ሀሳብ እንዲከተሉ በመምራት፣ በሉተር ዘመን እንዳደረገው ሁሉ በተመሳሳይ መንፈስ፣ ሆኖም የተለያየ ቅርጽና ይዘቶች በመላበስ ይሰራል። ይህ በንጽህናና በእውነት ላይ ነቀፋ ለመሰንዘር የሚጠቀምበት አካሄድ እጅግ ከተዋጡለት ስልቶች ውስጥ አንዱ የሰይጣን መሳሪያ ነው።GCAmh 142.3

    ሉተር ከሁሉም አቅጣጫ የመጡትን ጥቃቶች ያለፍርሃት በመከላከል ወንጌሉን ደግፎ ቆመ። የእግዚአብሔር ቃል በእያንዳንዱ ጦርነት ኃያል መሳሪያ መሆኑን አስመሰከረ። ያንን ኃይል በመጠቀም በጉልበት የተገኘውን የሊቀ-ጳጳሱን ስልጣን፣ ምክንያታዊ ለመሆን የሚሞክረውን የሊቃውንት ፍልስፍና ተዋጋ። ይህን ያደረገው ከተሐድሶው ጋር ራሱን ለማሰለፍ ጥረት ያደርግ የነበረውን አክራሪነት እንደ ቋጥኝ ጠንክሮ እየተዋጋ ባለበት ጊዜ ነበር።GCAmh 142.4

    እነዚህ የሚቃረኑ አካላት በየግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጎን እየገፈተሩ የሰው ጥበብ የሐይማኖታዊ እውነትና እውቀት ምንጭ እንደሆነ አድርገው ከፍ ከፍ ያደርጉት ነበር። ስነ-አመክንዮ (Rationalism)፣ ምክንያትን እንደ ጣዖት በመቁጠር ይህን ጉዳይ ለኃይማኖት ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ያስቀምጠዋል። ሉዓላዊ ሊቀ-ጳጳስዋን ያነሳሳው መንፈስ ሳይቆራረጥ ከዘመን ዘመን የሐዋርያትን መስመር ተከትሎ እንደመጣ ቤተ ክርስቲያንዋ የምታትተው ሮማዊይነት እያንዳንዱ ብክነትና ብልሹነት በሐዋርያቱ የቅድስና ተልዕኮ ስር ተደብቆ እንዲቀጥል ምቹ ዕድል የሚፈጥር ነው። ሙንዘርና አባሮቹ አገኘነው የሚሉት መንፈሳዊ መነሳሳትም ወዲያው ወዲያው ከሚለዋወጠው ምናባዊ አስተሳሰብ የተሻለ ምንጭ ያልነበረው ሲሆን ተፅዕኖውም - የሰውንም ሆነ የመለኮታዊውን - የሁሉንም ስልጣን የሚያዳክም ነበር። ክርስትና ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል የመንፈሳዊ እውነት ግምጃ ቤት እንዲሁም ሁሉም መንፈስ የሚፈተንበት እንደሆነ አድርጎ ይቀበላል።GCAmh 142.5

    ከዋርትበርግ እንደተመለሰ ሉተር የአዲስ ኪዳንን ትርጉም ጨረሰ፤ ወዲያውም ወንጌሉ በራሳቸው ቋንቋ ተዘጋጅቶ ለጀርመን ሕዝብ ተሰጠ። እውነትን የሚወዱ ሁሉ ይህንን ትርጉም በታላቅ ደስታ ተቀበሉት። የሰውን ወግና የፍጡርን ትዕዛዛት የመረጡት ግን በንቀት ተመልክተው ሳይቀበሉት ቀሩ።GCAmh 143.1

    አሁን የእግዚአብሔርን ቃል መመሪያዎች ተራው ሕዝብ ከእነርሱ ጋር መወያየት እንደሚችል ሲረዱ፣ የራሳቸውም ድንቁርና እንደሚጋለጥ ሲያውቁ ቀሳውስቱ ደነገጡ። የስጋ ምክንያታዊነት መሳሪያዎቻቸው የመንፈስን ሰይፍ ሊቋቋሙት አልቻሉም። ቅዱሳት መፃሕፍት እንዳይሰራጩ ለማድረግ ሮም ያላትን ኃይል ሁሉ አሰባሰበች፤ ሆኖም አዋጆች፣ ውግዘቶችና ግርፋቶች አንዳች የሚፈይዱ አልሆኑም። መጽሐፍ ቅዱስን ባወገዘችና በከለከለች መጠን የሚያስተምረው በእርግጥም ምን እንደሆነ ለማወቅ የነበረው የሕዝቡ ጉጉት በዛው ልክ ይጨምር ነበር። ማንበብ የሚችሉ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል በራሳቸው ለማንበብ ቋምጠው ነበር። በሄዱበት ይዘውት እየዞሩ አብዛኛውን ክፍል በአእምሮአቸው ማስታወስ እስኪችሉ ድረስ መልሰው መላልሰው ቢያነቡትም አይረኩም ነበር። አዲስ ኪዳን ምን ያህል ተቀባይነትን እንዳገኘ ሲመለከት ሉተር ወዲያውኑ የብሉይ ኪዳንን ትርጉም ጀመረ፤ ያለቀውንም ክፍል ወዲያውኑ ያትመው ነበር።GCAmh 143.2

    የሉተር ጽሁፎች በከተማም ሆነ በመንደር በተመሳሳይ ተቀባይነት አገኙ። “ሉተርና ጓዶቹ ያዘጋጁትን ማንኛውም ነገር ሌሎቹ በርቀትና በስፋት ያሰራጩት ነበር። ሥራ ፈትነትን በሥራ መተካት የፈለጉ ሆኖም ራሳቸው የእግዚአብሔርን ቃል የመስበክ በቂ እውቀት ያልነበራቸው፣ የገዳም ኑሮ ግዴታዎች ህጋዊ አለመሆናቸውን የተገነዘቡ መነኩሴዎች ሉተርና ጓደኞቹ የጻፏቸውን ጽሑፎች ይዘው በየክፍለ ሃገራቱ ዞሩ። ብዙም ሳይቆይ የጀርመን ሃገር በእነዚህ ታታሪ የመጽሐፍ ሻጮች ተወረረች።”GCAmh 143.3

    እነዚህ ጽሁፎች በሃብታሙም፣ በድሃውም በተማረውም ባልተማረውም ዘንድ በጥልቅ ፍላጎት ተነበቡ። በገጠር ያሉ ትምህርት ቤቶች አስተማሪዎች በእሳት ዙሪያ ለተቀመጡ ትናንሽ ስብስቦች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያነቡላቸው ነበር። በእያንዳንዱ ጥረት ጥቂት ነፍሳት ቃሉን በደስታ ተቀብለው ይድኑ ነበር፤ የዳኑትም እንደገና መልካሙን ዜና ለሌሎች ያካፍሉ ነበር።GCAmh 143.4

    የመንፈስ ቃላት ትክክል መሆናቸው ተረጋግጦ ነበር። “የቃልህ ፍቺ ያበራል፤ ህጻናትንም አስተዋዮች ያደርጋል።” [መዝ 119÷130]። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሕዝቡ ልብና አእምሮ ላይ ታላቅ ለውጥ የማምጣት ሥራ እየተገበረ ነበር። የጳጳሳዊው ሥርዓት በተገዥዎች ላይ የብረት ቀንበር በመጫን በድንቁርና ተብትቦ አኮስሷቸው ነበር። መሰረተ-ቢስ ሥርዓትን በጥንቃቄ፣ አንዳች ዝንፍ ሳይሉ ይጠብቁ ነበር፤ በዚህ ሁሉ አገልግሎት ግን የህሊናና የልብ ተሳትፎ እጅግ አናሳ ነበር። በቀላሉ የተነገረው የሉተር የእግዚአብሔር ቃል አስተምህሮ፣ በኋላም በተራው ሕዝብ እጅ የገባው ራሱ ቃሉ መንፈሳዊ ተፈጥሯቸውን በማንፃትና በማነጽ ብቻ ሳይሆን ለአዕምሮአቸው አዲስ ኃይልና አቅም በመፍጠር ፈዘው ደንግዘው የተቀመጡትን ኃይላት ቀሰቀሰ።GCAmh 143.5

    በሁሉም የኑሮ ደረጃ የነበሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በእጃቸው ይዘው የተሐድሶን አስተምህሮ ደግፈው በመቆም ሊታዩ ነበራቸው። የመጽሐፍ ቅዱሳትን ጥናት ለቀሳውስቱና ለመነኮሳቱ የተውት ጳጳሳውያን በዚህ ጊዜ ቀሳውስቱንና መነኮሳቱን አዲሱን ትምህርት እንዲያስተባብሉ ጠሩዋቸው። ሆኖም ከጳጳሳውያኑ ባልተሻለ ድንቁርና የነበሩት የቃሉና የእግዚአብሔር ኃይል እውቀት ያልነበራቸው ቀሳውስትና መነኮሳት ያልተማሩና መናፍቃን ብለው ባጣጣሏቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተሸነፉ። “በአሳዛኝ ሁኔታ” አለ አንድ የካቶሊክ ፀሐፊ፣ “ሉተር ተከታዮቹን እምነታቸው በቅዱስ መጻሕፍት ላይ ብቻ የተመሰረቱ እንዲሆኑ አሳምኖአቸው ነበር።” -D’Aubigne, b. 9, ch. 11። እውነትን ይሰሙ ዘንድ እውነት በሚናገሩ ሆኖም ባልተማሩ ሰዎች ዙሪያ ብዙ ሕዝብ ይሰበሰብ ነበር፤ ከተማሩና በኃይማኖት ትምህርት ከሰለጠኑ እንደበተ-ርዕቱ ሰዎች ጋር ሳይቀር ይወያዩ ነበር። የእነዚህ ታላላቅ ሰዎች አሳፋሪ ገልቱነት፣ የሚያቀርቡት መከራከሪያ ባልተወሳሰበው የእግዚአብሔር ቃል አስተምህሮ ሲመከት፣ እርቃኑን እንዲቀር ተደረገ። ወዝ-አደሮች፣ ወታደሮች፣ ሴቶችና ልጆች እንኳ ሳይቀር ከቀሳውስቱና ከተማሩ ዶክተሮች የተሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እውቀት ነበራቸው።GCAmh 144.1

    በወንጌሉ ደቀ-መዛሙርትና የጳጳሳዊውን አጉል አምልኮ በያዙ ሰዎች መካከል የነበረው ልዩነት ሲታይ ልዩነቱ ከተራው ሕዝብ ይልቅ በተማሩ ሰዎች መካከል ያነሰ አልነበረም። “የቋንቋ እውቀትንና የስነ-ጽሁፍን ጥበብ ቸል ካሉት፣ አሮጌውን ተዋረድ ከሚደግፉት በተቃረነ ሁኔታ አብዛኛዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና ለመመርመር፣ የጥንቱን የስነ-ጽሁፍ እምቅ ቅርስ ለማወቅ የሚጥሩ፣ ሰፋ አድርገው የሚያስቡ ወጣቶች ነበሩ። በመረዳት ቅልጥፍናቸው፣ ነፍስን ወደ ከፍታ በማምጣታቸውና በልበ-ሙሉነታቸው እነዚህ ወጣቶች ወዲያው ማንም ሊወዳደራቸው ወደማይችል የላቀ ችሎታ አደጉ።” “በሕዝባዊ ስብሰባዎች እነዚህ ወጣት የተሐድሶው ጠበቆችና የሮማውያኑ ዶክተሮች ሲገናኙ፣ ልበ ሙሉነታቸውና ነገሩን እንደምንም ያለመቁጠራቸው በትር የተቃራኒዎቻቸውን አሳፋሪ ደነዝነት እያቆሰለ ለተገባቸው ውርደት በሕዝቡ ፊት ያጋልጣቸው ነበር።”-Ibid., b. 9, ch. 11።GCAmh 144.2

    የሮማውያኑ መሪዎች ምዕመናኖቻቸው እየተመናመኑ መሄዳቸውን ሲመለከቱ የፈራጆችን እርዳታ በመጠየቅ በሚችሉት በማንኛውም ሁኔታ አድማጮቻቸውን ለመመለስ ይጥሩ ነበር። የነፍሳቸውን ጉድለቶች የሚሞላ ነገር በአዲሱ ትምህርት ያገኙ እነዚያ ሰዎች ግን ጥቅም-ቢስ የአጉል አምልኮ ሥርዓትና የፍጡር ወግ ገለፈት ለረጅም ጊዜ ሲመግቡአቸው ከነበሩ ከነዚያ ሸሹ።GCAmh 144.3

    በእውነት አስተማሪዎች ላይ ማሳደድ ሲጀመር ለክርስቶስ ቃላት ትኩረት ሰጡ፣ “በአንዲቱ ከተማም መከራ ሲያሳዩዋቸው ወደ ሌላይቱ ሸሹ” [ማቴ 10÷23]። ብርሃኑ በሁሉም ስፍራ ሰርጎ ገባ። ተሳዳጆቹ በሄዱበት የሚያስጠጋቸው ምቹ በር ተከፍቶ ያገኙ ነበር፤ በዚያም እየኖሩ አንዳንዴ በቤተ ክርስቲያን፣ ካልተፈቀደላቸው ደግሞ በግለሰቦች ቤት ውስጥ ያለዚያም በውጪ ክርስቶስን ይሰብኩ ነበር። የሚሰማ ያገኙበት ስፍራ ሁሉ የተቀደሰ የፀሎት ቤት ነበር። በእንደዚያ አይነት ኃይልና እርግጠኝነት የታወጀው እውነት መቋቋም በማይቻል ኃይል ተስፋፋ።GCAmh 144.4

    ኑፋቄን ለመደምሰስ የቤተ-ክህነት ሰዎችና መንግሥታዊ ባልስልጣናት በከንቱ ደከሙ። ወደ እስር፣ ግርፋት፣ የእሳት ቃጠሎና ሰይፍ ቢዞሩም ልፋታቸው ውጤት-አልባ ሆነ። በሺዎች የሚቆጠሩ አማኞች እምነታቸውን በደማቸው አተሙ፣ ሥራው ግን ወደ ፊት ቀጠለ። ስደት ያደረገው ነገር ቢኖር እውነትን ማስፋፋት ነበር። ሰይጣን ከተሐድሶው ጋር ሊያቆራኘው ሲጥር የነበረው አክራሪነትም ውጤቱ በሰይጣን ሥራና በእግዚአብሔር ሥራ መካከል ያለውን ልዩነት የበለጠ አጉልቶ ማሳየት ነበር።GCAmh 145.1

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents