Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ምዕራፍ ፳፱—የክፋት መነሻ

    ለብዙ አዕምሮዎች (ሰዎች) የኃጢአት መነሻና፣ የመኖሩም ምክንያት፣ የታላቅ ግራ መጋባት ምክንያት ናቸው። የክፋትን ሥራ ከስቃይና ከመራቆት ዘግናኝ ውጤቶቹ ጋር ያዩና፣ ይህ ሁሉ፣ በጥበቡ፣ በኃይሉና በፍቅሩ ወሰን በሌለው አምላክ ግዛት ውስጥ እንዴት ሊኖር ይችላል ብለው ይጠይቃሉ። ይህ ምንም ማብራሪያ ሊሰጡበት የማይችሉበት ምስጢር (ስውር ነገር) ነው። ግራ በመጋባታቸውና በጥርጥራቸው ውስጥ ሆነውም በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በግልጽ ለተቀመጡት፣ ለመዳንም አስፈላጊ ለሆኑት እውነቶች እውራን ሆነዋል። አንዳንዶች የኃጢአትን መኖር በተመለከተ ባሏቸው ጥያቄዎች እግዚአብሔር ያልገለጸውን ለመፈለግ ይጥራሉ፤ በመሆኑም ለችግራቸው መፍትሄ አያገኙም። እንደዚህ አይነቶቹ ወደ መጠራጠርና ማማረር ዝንባሌ ይገፋፋሉ፤ ይህንንም እንደሰበብ በመቁጠር የቅዱሱን ሕግ/ትዕዛዝ ቃል አሻፈረኝ ለማለት ይጠቀሙበታል። ሆኖም ሌሎች ደግሞ የእግዚአብሔርን ባህርይ፣ የመንግሥቱን ተፈጥሮ፣ በኃጢአትም ላይ የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ ባህልና አሳስቶ መተርጎም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ስለጋረደባቸው ክፋት ስላለው ታላቅ ችግር የሚያረካ ግንዛቤ የላቸውም።GCAmh 356.1

    ለኃጢአት መኖር ምክንያት መስጠት እንደማይቻል ሁሉ ስለመነሻውም ማብራራት የሚቻል አይደለም። ቢሆንም፣ ክፋትን በተመለከተ እግዚአብሔር ያሳየውን ፍትህና ቅንነት ሁሉ በሙላት ለመግለጽ ሲባል ስለመነሻውም ሆነ ስለ መጨረሻው የኃጢአት ፀባይ በቂ ማስተዋል ማግኘት ይቻላል። ለኃጢአት መግባት እግዚአብሔር በጭራሽ ተጠያቂ እንዳልሆነ ከማንኛውም ርዕስ በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጦታል፤ ለዓመጽ መነሳት ምክንያት ሊሆን የሚችል የመለኮታዊ ፀጋ መወገድ እንዳልተከናወነ፣ በመለኮታዊ መንግሥቱ ውስጥ አንዳች የጎደለ ነገር እንዳልነበረ በግልጽ ተቀምጧል። ኃጢአት፣ ለመኖሩ ምክንያት የማይገኝለት፣ ሰርጎ-ገብ (ጣልቃ-ገብ) ነው። ምስጢራዊና ምክንያት የሌለው ነው፤ ምክንያት (ሰበብ) መፈለግ ኃጢአትን መደገፍ ይሆናል። ሰበብ ቢገኝለት ኖሮ ወይም ለመገኘቱ መንስኤ ማግኘት ቢቻል፣ ኃጢአት መሆኑ ይቀራል። ያለን ብቸኛው የኃጢአት ትርጉም በእግዚአብሔር ቃል የተሰጠው ነው፤ ይኸውም “ሕግን መተላለፍ ነው”[1ኛ ዮሐ 3÷4]። የመለኮታዊ መንግሥት መሰረት ከሆነው ከታላቁ የፍቅር ሕግ ጋር ውጊያ ላይ ያለ መርህ ውጤት ነው።GCAmh 356.2

    ኃጢአት ከመግባቱ በፊት በዓለማት ሁሉ ሰላምና ደስታ ሰፍኖ ነበር። ሁሉም ነገር ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር ፍፁም የተስማማ ነበር። ፍቅር ለእግዚአብሔር የበላይ፣ ፍቅር ለእርስ በርስ የማያዳላ ነበር። በማንነት፣ በባህርይና በአላማ (በሥራ) ከዘላለማዊው አባት ጋር አንድ የሆነው፣ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ፣ በዩኒቨርስ ካለው ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ምክርና አላማ መግባት የሚችለው ብቸኛው አካል፣ ቃል የሆነው ክርስቶስ ነበር። በክርስቶስ አማካኝነት አብ ሰማያዊ ፍጡራንን ሁሉ ፈጠረ። “ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ስልጣናት በሰማይ… ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና”[ቆለ 1÷16]፤ ከአብ እኩል፣ መላው ሰማይ ለክርስቶስ ታማኝነታቸውን ይገልፁ ነበር።GCAmh 356.3

    የፍቅር ሕግ የእግዚአብሔር መንግሥት መሰረት ሆኖ፣ የፍጡራን ደስታም ከታላቁ የጽድቅ መርሆዎቹ ጋር ባላቸው ፍፁም መስማማት ላይ የተደገፈ ነበር። እግዚአብሔር፣ ከሁሉም ፍጡሮቹ ባህርይውን በውል አስተውለው ዋጋ ከመስጠት የመነጨ አክብሮት፣ የፍቅር አገልግሎት ይፈልጋል። በግዴታ በሚገኝ ታማኝነት ደስ አይሰኝም። በፍላጎታቸው ያገለግሉት ዘንድ ለሁሉም የፈቃድ ነፃነትን ይሰጣል።GCAmh 357.1

    ይህንን ነፃነት ለማጣመም የመረጠ ግን አንድ ፍጡር ነበረ። ከክርስቶስ ቀጥሎ በእግዚአብሔር እጅግ በተከበረ፣ በኃይልና በግርማ በሰማይ ነዋሪዎች መካከል የላቀ በነበረ በእርሱ ኃጢአት መነጨ። ከመውደቁ በፊት ሉሲፈር የሚጋርዱ ኪሩቤሎች ቀዳሚ፣ ቅዱስና ያልረከሰ ነበር። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። በእግዚአብሔር ገነት በኤድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቁ ሁሉ… ልብስህ ነበረ።” “አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፤ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ። ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍፁም ነበርህ” [ሕዝ 28÷12-15]።GCAmh 357.2

    ሉሲፈር ከእግዚአብሔር ጋር ስምሙ ሆኖ፣ በመላእክት ሰራዊት ተወዶና ተከብሮ፣ ሌሎችንም ለመባረክና ፈጣሪውን ለማክበር ክቡር ክህሎቶቹን እየተጠቀመ መቀጠል ይችል ነበር። ሆኖም ነብዩ እንዲህ ይላል፦ “በውበትህ ምክንያት ልብህ ኮርቶአል፤ ከክብርህም የተነሳ ጥበብን አረከስህ” [ሕዝ 28÷17]። ቀስ በቀስ ሉሲፈር ራስን ከፍ ከፍ ለማድረግ መሻት እየተገዛ ይሄድ ጀመር። “ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ… በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ ከደመናዎች ከፍታ በላይ አርጋለሁ በልዑልም እመሰላለሁ” [I will be like the Most High] አልህ [ሕዝ 28÷6፤ ኢሳ 14÷13፣14]። በፍጡሮቹ ታማኝነትና ፍቅር እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ለማድረግ በመፈለግ (በመጣር) ፈንታ፣ የእነርሱን አክብሮትና ግልጋሎት ለራሱ ያደርግ ዘንድ ሉሲፈር ይማስን ነበር። ዘላለማዊው አባት በልጁ ላይ ያደረገውን ክብር በመመኘት፣ ይህ የመላእክት ልዑል፣ ይጠቀምበት ዘንድ የክርስቶስ መብት ብቻ የሆነውን ስልጣን ፈለገ።GCAmh 357.3

    የፈጣሪውን ክብር ያንፀባርቅ ዘንድ፣ ምስጋናም ያቀርብ ዘንድ ሰማይ በሞላ ደስተኛ ነበር። በእንደዚያ ሁኔታ እግዚአብሔር በሚከበርበት ጊዜ ሰላምና ደስታ ሰፍኖ ነበር። ሆኖም የአንዲት ኖታ አለመቀነባበር ሰማያዊውን መስማማት አወከች። የፈጣሪ እቅድ ተፃራሪ የሆነው ራስን የማገልገልና ከፍ ከፍ የማድረግ ፍላጎት፣ የእግዚአብሔር ክብር የበላይ በነበረባቸው አእምሮዎች ውስጥ አደገኛ የሆነ ክፋትን የሚያስከትል ኃሳብ አነቃቃ። ሰማያዊ መማክርት ሉሲፈርን ተማፀኑት። የፈጣሪን ታላቅነት፣ መልካምነትና ፍትህ፣ የተቀደሰውንና መለወጥ የማይችል ተፈጥሮ ያለውን ሕጉን የእግዚአብሔር ልጅ አቀረበለት። የሰማይን ሥርዓት የዘረጋው ራሱ እግዚአብሔር ነበር፤ ከዚያም ፈቀቅ በማለቱ ሉሲፈር ፈጣሪውን ያዋርዳል፤ በራሱም ላይ ውድመትን ያመጣል። መጠን በሌለው ፍቅርና ምሕረት የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ግን ማድረግ የቻለው የእምቢተኝነትን መንፈስ የበለጠ ማነሳሳት ነበር። ሉሲፈር በክርስቶስ ላይ ያለው ቅንዓት እንዲያይልበት ፈቀደ፤ የበለጠ እየቆረጠ መጣ።GCAmh 357.4

    በራሱ ክብር ላይ የነበረችው ኩራት ለበላይነት የነበረውን መሻት ትመግብ ነበረች። ለሉሲፈር የተሰጡት ታላላቅ ማዕረጎች እንደ የእግዚአብሔር ስጦታ ተደርገው አድናቆት አልተቸራቸውም፤ ለፈጣሪ ምስጋናም ማስገኘት አልቻሉም። በከፍታውና በአንፀባራቂነቱ ተመካ፤ ከእግዚአብሔር ጋርም እኩል መሆን ፈለገ። በሰማይ ሰራዊት የተወደደና የተከበረ ነበረ። መላእክት የእርሱን ትዕዛዝ በመፈፀም ሐሴት ያደርጉ ነበር፤ ከሁላቸውም በላይ ጥበብንና ክብርን የተጎናፀፈ ነበር። ሆኖም እውቅና የተሰጠው የሰማይ ሉአላዊ ገዢ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፤ እርሱም በኃይልና በስልጣን ከአብ ጋር አንድ (እኩል) ነበረ። በሁሉም የእግዚአብሔር ምክሮች ውስጥ ክርስቶስ ተሳታፊ ነበረ፤ ሉሲፈር ግን ወደ መለኮት እቅዶች (purposes) መግባት አይፈቀድለትም ነበር። “ለምን”? ብሎ ጠየቀ ይህ ኃያል መልአክ፣ “ለምን ክርስቶስ የበላይነቱን ይይዛል? ከሉሲፈር በልጦ የከበረው ለምንድን ነው?”GCAmh 358.1

    ሉሲፈር በመላእክት መካከል የቅሬታ መንፈስን ያሰራጭ ዘንድ በእግዚአብሔር መገኘት (አጠገብ) የነበረውን ስፍራውን ትቶ ሄደ። ስውር በሆነ ሚስጢራዊነት በመሥራት፣ ለተወሰነ ጊዜም እውነተኛ ዓላማውን በመደበቅ ለእግዚአብሔር አክብሮት እንደሆነ በሚያስመስል ሽፋን፣ አላስፈላጊ የሆነ ገደብ የሚጭኑ እንደሆነ ፍንጭ በመስጠት ሰማያዊ አካላትን የሚያስተዳድሩ ሕጎችን በተመለከተ እርካታ የማጣትን ስሜት ለመቀስቀስ ጣረ። ተፈጥሮአቸው ቅዱስ በመሆኑ መላእክት የራሳቸው ፈቃድ የሚላቸውን አቅጣጫ መከተል እንዳለባቸው ገፋፋቸው። ከፍተኛውን ክብር ለክርስቶስ በመስጠቱ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያደረገበት ነገር ፍትሐዊ እንዳልሆነ በማሳየት ከንፈር እንዲመጠጥለት (እንዲታዘንለት ለማድረግ) ሞከረ። ከፍ ያለ ክብርና ስልጣን መፈለጉ ለሰማይ ነዋሪዎች ሁሉ ነፃነትን ለማረጋገጥ ካለው ፍላጎት የተነሳ፣ በዚህም አኳኋን ከፍ ወዳለ የሕያውነት ደረጃ እንዲደርሱ ለማድረግ እንጂ ራሱን ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳልሆነ ተናገረ።GCAmh 358.2

    እግዚአብሔርም በታላቅ ምህረቱ ሉሲፈርን ታገሰው። መጀመሪያ የቅሬታ መንፈስ ሲያድርበት፣ ከዚያም አልፎ የሐሰት አቤቱታውን በታማኝ መላእክት ፊት ማቅረብ ሲጀምር እንኳ ከክብር ማዕረጉ ወዲያውኑ እንዲወርድ አልተደረገም ነበር። ለረጅም ጊዜ በሰማይ እንዲቆይ ተደርጓል። ንስሐ ከገባና ከተመለሰ ምሕረት እንደሚደረግለት በተደጋጋሚ ዕድል ተሰጠው። ስህተቱን ያሳምኑት ዘንድ ዘላለማዊ ፍቅርና ጥበብ ብቻ ሊያቀናብራቸው የሚችላቸው ጥረቶች ተደረጉ። የቅሬታ መንፈስ ከዚያ በፊት በሰማይ አይታወቅም ነበር። ሉሲፈር ራሱ እንኳ በመጀመሪያ ወደየት እየተንሸራተተ እንደነበር አላስተዋለም ነበር፤ የአስተሳሰቡን ትክክለኛ ምንነት አልተረዳም ነበር። ነገር ግን እርካታ ማጣቱ ምንም ምክንያት የሌለው መሆኑ ሲረጋገጥበት፣ ሉሲፈር እንደተሳሳተ፣ የመለኮት አቋም (መጠይቆች) ልክ እንደሆኑ አመነ፤ እንዲሁ እንደሆነም በሰማይ ሁሉ ፊት እውቅና ይሰጥ ዘንድ ነበረበት። ይህንን አድርጎ ቢሆን ኖሮ ራሱንና ብዙ መላእክትን ባተረፈ ነበር። በዚህ ጊዜ ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ሙሉ ለሙሉ አልተወውም ነበር። የሚጋርድ ኪሩቤልነቱን ቦታ የለቀቀ ቢሆንም ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኛ ቢሆንና በእግዚአብሔር ታላቅ እቅድ ውስጥ እንዲሞላው የተፈለገውን ቦታ ቢይዝ ኖሮ ወደ ነበረበት የሥራ ገበታው ይመለስ ነበር። ነገር ግን ኩራት እጅ እንዳይሰጥ ከለከለችው። የራሱን መንገድ ትክክል እንደሆነ ሳያሰልስ ተከራከረ፤ ንስሐ መግባትም እንደማያስፈልገው ሆኖ በአቋሙ ፀና፤ ፈጣሪውን በመቃረን ለታላቁ ተጋድሎ ራሱን ሙሉ ለሙሉ ሰጠ።GCAmh 358.3

    አሁን የላቀ አእምሮው ክህሎቶች ሁሉ የማታለል ሥራ ሊሰሩ፣ በስሩ ያሉትን መላእክት ኃዘኔታ ለማትረፍ ጥቅም ላይ ዋሉ። ክርስቶስ የሰጠው ምክርና ማስጠንቀቂያ እንኳ የከሃዲነቱን እቅድ እንዲያግዝ ተደርጎ ተጣመመ። ከእርሱ ጋር በፍቅር አመኔታ ለተቆራኙ መላእክት፣ በተሳሳተ መልኩ እንደተኮነነ፣ ስልጣኑ እንዳልተከበረና ነፃነቱንም ሊያጣ እንደሆነ አድርጎ አቀረበላቸው። የክርስቶስን አባባል ከማጣመም ባለፈ ወደ የፈጠራ ታሪክና ቀጥተኛ ውሸት በማምራት በሰማይ ነዋሪዎች ፊት ሊያዋርደው እቅድ እንደያዘለት አድርጎ ክርስቶስን ከሰሰው። በእርሱና በታማኝ መልአክቱ መካከልም የሐሰት ነገር መጠንሰስ አማረው። ሊቆለምማቸውና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ጎን ሊያሰልፋቸው ያልቻለውን መላእክት ለሰማያዊ አካላት ፍላጎት ቁብ የማይሰጡ ናቸው በማለት ከሰሳቸው። ራሱ ሲሰራው የነበረውን ያነኑ ሥራ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የቆሙት እየፈፀሙት እንደሆነ አድርጎ ኮነናቸው። እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ፈፀመብኝ የሚለውን ኢ-ፍትሃዊ ክስ ደግፎ ለማቆየት የፈጣሪን ቃላትና ተግባር ማጣመሙን ተያያዘው። የእግዚአብሔርን ዓላማ በተመለከተ ብልጥ በሆኑ መከራከሪያዎቹ መላእክትን የማደናገር መርሀ ግብር እያራመደ ነበር። ቀላል የሆነውን ነገር ሁሉ ምስጢር እንዲሆን ጀቦነው፤ በብልጣብልጥ ክህሎቱ እውነቱን ለውጦ እጅግ ግልጽ በሆኑት የያህዌ ንግግሮች ላይ ጥርጥር እንዲሰርጽ አደረገ። ከመለኮታዊ አስተዳደር ጋር የነበረው ቅርበትና ከፍተኛ ስልጣኑ ላቀረባቸው ጉዳዮች ጉልበት በመጨመር፣ የሰማይን ስልጣን አሻፈረኝ በማለት ይተባበሩት ዘንድ ብዙዎች ተመሰጡ።GCAmh 359.1

    የጥላቻው መንፈስ ጎምርቶ ሕያው አመጽ እስኪሆን ድረስ እግዚአብሔር በጥበቡ ሰይጣን ሥራውን ይቀጥል ዘንድ ፈቀደለት። ትክክለኛ ተፈጥሮአቸውና (ፀባያቸውና) ዝንባሌያቸው በሁሉ ይታይ ዘንድ እቅዶቹ ሙሉ በሙሉ ይፋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊ ነበር። ሉሲፈር እንደ የተቀባ ኪሩቤልነቱ እጅግ ከፍ ከፍ ያለ ነበረ፤ በሰማይ ፍጡራን ዘንድ እጅግ የተወደደ፣ በእነርሱ ላይ ያለው ተጽዕኖም የበረታ ነበረ። የእግዚአብሔር መንግሥት የሚያካትተው የሰማይ ነዋሪዎችን ብቻ አልነበረም፤ እርሱ የፈጠራቸውን ሌሎች ዓለማትን ሁሉ ያጠቃልል ነበረ። ሰይጣንም በኃሳቡ የሰማይን መላእክት ከእርሱ ጋር በዓመጽ ማስነሳት ከቻለ፣ ሌሎቹንም ዓለማት ከእርሱ ጎን ማሰለፍ እንደሚችል አመነ። አላማውን ያሳካ ዘንድ እውነት የሚመስል ክርክርንና ማጭበርበርን ሥራ ላይ በማዋል በእርሱ በኩል ያለውን ጥያቄ በጥበብ አቅርቧል። የማታለል አቅሙ እጅግ ከፍተኛ ነበር፤ በሐሰት በርኖስ ውስጥ ራሱን በመደበቅ የሚጠቅመው ነገር አግኝቷል። ታማኝ መላእክት እንኳ ሳይቀር ባህርይውን መረዳትም ሆነ ሥራው ወደየት እያመራ እንደሆነ ሙሉ ለሙሉ መረዳት አልቻሉም።GCAmh 359.2

    ሰይጣን እጅግ የተከበረ ነበረ፤ ተግባራቱም በምስጢር የተሸፈኑ ስለነበሩ፣ የሥራውን ትክክለኛ ባህርይ ለመላእክት ለመግለጽ አስቸጋሪ ነበር። ሙሉ ለሙሉ ካልዳበረ (ካልጎለመሰ) በስተቀር ኃጢአት ምን አይነት ክፉ ነገር እንደሆነ አይታይም። እስካሁን ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ ስፍራ አልነበረውም፤ ቅዱስ ፍጡራንም የባህርይውም ሆነ የኃጢአት የክፉነቱ መረዳት አልነበራቸውም። የመለኮታዊውን ሕግ ወደ ጎን ከመገፍተር የሚመጣውን አሰቃቂ መዘዝ ሊያስተውሉት አልቻሉም። መጀመሪያ ላይ ለእግዚአብሔር አለኝ በሚለው በእውነት መሳይ የታማኝነት ንግግሩ ውስጥ ሰይጣን ሥራውን ደብቆት ነበር። የእግዚአብሔርን ክብር ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለመንግሥቱ መረጋጋት፣ እንዲሁም ለሰማይ ነዋሪዎች ደህንነት የሚጥር እንደሆነ ተናገረ። በእዙ ስር ባሉት መላእክት አዕምሮ ውስጥ ቅሬታ እየተከለ ሳለ እርካታ ማጣትን ለማስወገድ እየጣረ መሆኑን በጥበባዊ አሰራሩ ማስመሰል ቻለ። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሥርዓትና የሕግ ለውጥ መደረግ አለበት ብሎ ሲያነሳሳ፣ በሰማይ ያለውን ውህደት ለመጠበቅ እነዚህ ለውጦች አስፈላጊ እንደሆኑ በሚያሳይ የሐሰት ምክንያት ነበር።GCAmh 359.3

    የኃጢአትን ጉዳይ በተመለከተ እግዚአብሔር ሊጠቀም የሚችለው ጽድቅንና እውነትን ብቻ ነው። ሰይጣን ግን እግዚአብሔር ሊጠቀምባቸው የማይችላቸውን - ሽንገላንና ማታለልን - ሥራ ላይ ያውላቸዋል። በሰማይ ነዋሪዎች ላይ ህጎቹንና መመሪያዎቹን መጫኑ ትክክል እንዳልሆነ፣ መገዛትንና መታዘዝን ከፍጡሮቹ የሚጠይቀው ራሱን ከፍ ለማድረግ ካለው ፍላጎት ብቻ የመነጨ እንደሆነ በመናገር በመላእክት ፊት የአስተዳደሩን እቅድ አጣሞ በማቅረብ የእግዚአብሔር ቃል ሐሰት እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል። ስለዚህ በሰማይ ነዋሪዎችና በዓለማት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር መንግሥት ቅን፣ ሕጉም ፍፁም መሆኑ በተግባር መታየት የግድ ነበረበት። ሰይጣን ራሱ ያስመሰለው ለዩኒቨርስ መልካምነት እየጣረ እንደነበረ ነው። የነጣቂው ባህርይና ትክክለኛ አላማው በሁሉም ዘንድ መስተዋል አለበት። በክፋት ሥራው ራሱን ይገልጥ ዘንድ ጊዜ የግድ ያስፈልገዋል።GCAmh 360.1

    የራሱ አካሄድ በሰማይ የፈጠረውን አለመግባባት ሰይጣን በእግዚአብሔር ሕግና በመንግሥቱ ላይ አላከከ። ሁሉም ክፋት የመለኮታዊ አስተዳደሩ ውጤት እንደሆነ አወጀ። በያህዌ ሕገ-ደንቦች ላይ ማሻሻያ ያደርግ ዘንድ የራሱ ዓላማ እንደነበረ ተናግሯል። ስለዚህ የመጠይቁን (የአላማውን) ተፈጥሮ በተግባር መግለፁ፣ በመለኮታዊ ሕጉ ላይም ያቀረበው የለውጥ እቅድ ውጤት ምን እንደሆነ ማሳየቱ አስፈላጊ ነበር። የራሱ ሥራ ራሱን ማውገዝ አለበት። አመጽ ላይ እንዳልሆነ ሰይጣን ከመጀመሪያው ጀምሮ ተናግሯል። የአታላዩ ጭምብል ወልቆ ዓለማት (ዩኒቨርስ) ሁሉ ማየት አለበት።GCAmh 360.2

    ከዚያ በኋላ በሰማይ መኖር እንደማይችል ከተወሰነ በኋላ እንኳ ወሰን የለሹ ጥበብ ሰይጣንን አላጠፋውም። በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው የፍቅር አገልግሎት ብቻ በመሆኑ ፍጡራኑ ለእግዚአብሔር ያላቸው ታማኝነት በፍርዱና በቸርነቱ ባላቸው እምነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። በሰማይና በሌሎች ዓለማት የሚኖሩ እነርሱ የኃጢአትን ተፈጥሮና የሚያስከትለውንም ውጤቶች በውል መገንዘብ የሚችሉ ስላልነበሩ፣ ሰይጣንን ቢያጠፋው በዚያ ቅጣቱ ውስጥ የእግዚአብሔርን ፍርድና ምሕረት ማየት ይሳናቸው ነበር። ወዲያውኑ ወደ አለመኖር ቢመጣ (ቢደመሰስ) እግዚአብሔርን የሚያገለግሉት ከፍርሃት የተነሳ እንጂ ከፍቅር አይሆንም ነበር። የአታላዩ ተጽዕኖ ሙሉ ለሙሉ አይደመሰስም፤ የአመጽ መንፈስም ፈጽሞ አይወገድም ነበር። ክፋት እስኪጎመራ መተው አለበት። የእግዚአብሔር ፍርድና ምህረቱ እንዲሁም መለወጥ የማይችለው ሕጉ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ ለዘላለም እንዳይነሳባቸው፣ ሰይጣን በመለኮታዊው መንግሥት ላይ ያነሳቸው ክሶች በእውነተኛ መልካቸው በፍጡራን ሁሉ ፊት ቁልጭ ብለው መታየት ይችሉ ዘንድ፣ ማብቂያ በሌላቸው ዘመናት ለሚኖረው ለጠቅላላው ዓለም በጎነት ሲባል፣ ሰይጣን ሙሉ ለሙሉ መርሆዎቹን ሊያጎለብታቸው ይገባል።GCAmh 360.3

    የሰይጣን አመጽ ወደፊት ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ለዓለማት ትምህርት፣ ስለኃጢአት ባህርይና አሰቃቂ ውጤቶቹ ዘላለማዊ ምስክር ይሆን ዘንድ ነበረው። የሰይጣን አገዛዝ ውጤት፣ በሰዎችና በመላእክት ላይ የሚያመጣው ጉዳት፣ መለኮታዊውን ስልጣን ወደ ጎን መገፍተር ፍሬው ምን እንደሆነ ያሳያል። እርሱ ያበጃቸው ፍጡራን ሁሉ ደህንነት ከእግዚአብሔር መንግሥትና ከሕጉ መኖር ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይመሰክራል (ያረጋግጣል)። ስለዚህ የዚህ አመጽ አሰቃቂ ተግባራዊ ተሞክሮ ታሪክ፣ የመተላለፍን ባህርይ በተመለከተ ከመታለል ሊጠብቃቸው፣ ኃጢአት ከመሥራትና መቀጮውን ከመቀበል ሊያተርፋቸው፣ ለሁሉም ቅዱስ ፍጡራን ዘላለማዊ ዘብ ይሆን ዘንድ ነበረው።GCAmh 361.1

    በሰማይ የነበረው ተቃርኖ እስኪቋጭ፣ እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ ስልጣን ነጣቂው ራሱን ፃድቅ ማድረጉን ቀጠለ። ከደጋፊዎቹ ጋር ከደስታ መኖሪያው መወገድ እንዳለበት ሲታወጅ፣ የአመጽ መሪው ለፈጣሪ ሕግ ያለውን ጥላቻ በአደባባይ በድፍረት ተናገረ። መላእክት ቁጥጥር እንደማያሻቸው፣ ምንጊዜም ወደ ትክክል የሚመራቸውን የራሳቸውን ፈቃድ እንዲከተሉ መተው አለባቸው የሚለውን አቋሙን ደገመው። የነፃነታቸው መገደቢያ እንደሆኑ አድርጎ መለኮታዊ ደንቦችን አወገዛቸው፤ የሰማይ ሰራዊት ከዚህ ማነቆ ተላቀው የበለጠ ከፍ ከፍ ወዳለና ላቅ ያለ ክብር ያለው የኑሮ ደረጃ መድረስ ይችሉ ዘንድ አላማው የሕጉን መጥፋት ማረጋገጥ እንደሆነ ተናገረ።GCAmh 361.2

    ባይገሰፁ ኖሮ ፈጽመው አመጽ የማያስነሱ እንደነበሩ በማወጅ፣ ለአመፃቸው ተጠያቂ ሙሉ በሙሉ ክርስቶስ እንደሆነ ሰይጣንና ሰራዊቱ በአንድ ድምጽ ኮነኑት። በእምነት ማጉደላቸው ግትርና እምቢተኛ ሆነው፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት በከንቱ ለመገልበጥ እየጣሩ ሳለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነርሱ ምንም ጥፋት የሌለባቸው፣ የጨቋኝ ኃይል ተጠቂ እንደሆኑ በስድብ እየተናገሩ፣ ቀንደኛው አማፂና ደጋፊዎቹ በመጨረሻ ከሰማይ ተባረሩ።GCAmh 361.3

    በሰማይ አመጽን ያነሳሳው ያው መንፈስ አሁንም ድረስ በምድር ላይ አመጽ እንዲነሳ ይገፋፋል። ሰይጣን በመላእክት ላይ የተጠቀመበትን ያንኑ መርሀ-ግብር በሰዎች ላይ መጠቀሙን ቀጥሏል። አሁን መንፈሱ የማይታዘዙ ልጆችን ይገዛል፤ እነርሱም ልክ እንደ እርሱ የእግዚአብሔርን ሕግ ገደቦች መሰባበር ይሻሉ፤ ደንቦቹን በመተላለፍም ነፃነት እንደሚያገኙ አድርገው ለሰዎች ተስፋ ይሰጣሉ። የኃጢአት መገሰጽ አሁንም የጥላቻንና የእምቢተኝነትን መንፈስ ይቀሰቅሳል። የእግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ መልእክቶች ወደ ህሊና ዘልቀው ሲገቡ፣ ራሳቸውን ትክክል እንደሆኑ አድርገው እንዲቆጥሩ፣ በኃጢአት መንገዳቸውም የሌሎችን ሃዘኔታ እንዲሹ ሰይጣን ሰዎችን ይመራቸዋል። ስህተታቸውን እንደማረም ፈንታ፣ የችግሩ መንስኤው እርሱ ብቻ እንደሆነ አድርገው በሚገስፀው ላይ በቁጣ ይገነፍላሉ። ከፃድቁ አቤል ዘመናት ጀምሮ እስከ እኛ ዘመን ድረስ ኃጢአትን ለመኮነን በደፈሩ ሁሉ የሚንፀባረቀው መንፈስ እንደዚሁ አይነት ነው።GCAmh 361.4

    በሰማይ እንዳደረገው፣ የእግዚአብሔርን ባህርይ አጣሞ ባቀረበበት፣ ጨካኝና ፈላጭ ቆራጭ እንደሆነ አድርጎ እንዲታይ በሞከረበት፣ በዚያው ተመሳሳይ መንገድ፣ ሰይጣን፣ ኃጢአት ይሰሩ ዘንድ ሰዎችን አግባባቸው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ውጤታማ ነበርና፣ እርሱን ወደ አመጽ እንደመሩት ሁሉ፣ ኢ-ፍትሃዊ ናቸው ያላቸው የእግዚአብሔር መገደቢያዎች፣ ለሰዎችም መውደቅ ምክንያት እንደሆኑ ተናገረ።GCAmh 361.5

    ነገር ግን ዘላለማዊው ራሱ ስለ ባህርይው ይናገራል፦ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ፀጋ ያለው፣ ለቁጣም የዘገየ ባለታላቅ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ የማያነፃ” [ዘፀ 34÷6፣7]።GCAmh 362.1

    ሰይጣንን ከሰማይ በማስወገዱ እግዚአብሔር የእርሱን ፍትህ አወጀ፤ የዙፋኑንም ክብር ጠበቀ። ሆኖም ለዚህ ከዳተኛ መንፈስ ማታለያዎች እጅ ሰጥቶ ሰው ኃጢአት ሲሰራ፣ ለወደቀው ዘር አንድያ ልጁን አሳልፎ በመስጠት፣ እግዚአብሔር ያለውን ፍቅር በመረጃ በሚታይ፣ በተግባር ገለፀ። በማስተሰርያው ሥነ-ሥርዓት ውስጥ የእግዚአብሔር ባህርይ ተገልጧል። ሉሲፈር ለመረጠው የኃጢአት መንገድ በምንም አይነት መልኩ የእግዚአብሔር መንግሥት ሊኮነን እንደማይገባው ኃያሉ የመስቀሉ መከራከሪያ ለዓለማት ሁሉ በተግባር አሳይቷል።GCAmh 362.2

    በአዳኙ የምድር አገልግሎት ጊዜ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል በነበረው ፉክክር የታላቁ አታላይ ባህርይ ተገልጧል። በዓለም አዳኝ ላይ እንደከፈተው ጨካኝ ጦርነቱ ያለ፣ ሰማያዊ መላእክትና፣ ታማኙ ዓለም በጠቅላላ ለሰይጣን የነበራቸውን ስሜት ፍቱን በሆነ ሁኔታ ከስሩ ምንግል አድርጎ የሚጥልላቸው ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። ክርስቶስ ይሰግድለት ዘንድ የጠየቀበት ደፋር ስድቡ፣ ወደ ተራራ ጫፍና ወደ ቤተ መቅደሱ ቁንጮ ይዞት የሄደበት ከልክ ያለፈ ድፍረቱ፣ ሚዛን ከሚያሳጣው ከፍታ ራሱን እንዲወረውር የገፋፋበት የተደበቀው ተንኮለኛ አላማው፣ ክርስቶስ በሄደበት ሁሉ ያሳድደው የነበረው የማያባራው ክፋቱ፣ ካህናትና ሕዝቡ ፍቅሩን አሻፈረኝ እንዲሉ፣ በመጨረሻም “ስቀለው! ስቀለው!” ብለው እንዲጩኹ ያደረጋቸው ይህ ሁሉ - የዓለማትን ሁሉ ግርምትና ቁጣ ቀሰቀሰ።GCAmh 362.3

    ምድር ክርስቶስን አልቀበልም ትል ዘንድ ያነሳሳው ሰይጣን ነበር። የአዳኙ ምሕረትና ፍቅር፣ ርኅራኄውና አዛኝ ትህትናው የእግዚአብሔርን ባህርይ ለዓለም ሲገልጥ ስላየ፣ የክፋት ልዑል ክርስቶስን ያጠፋው ዘንድ ሁሉንም ሃይሉንና ማታለያውን ተጠቀመ። ሰይጣን በእግዚአብሔር ልጅ የተደረገውን እያንዳንዱን የይገባኛል ጥያቄ ተገዳደረ፤ የአዳኙም ሕይወት በሰቆቃና በሃዘን የተሞላ ይሆን ዘንድ ሰዎችን የራሱ አስፈፃሚዎቹ አድርጎ ቀጠራቸው። የየሱስን ሥራ ያደናቅፍ ዘንድ የተጠቀመባቸው እውነት የሚመስሉ ማታለያዎችና ውሸቶች፣ በማይታዘዙ ልጆች በኩል የተንፀባረቀው ጥላቻ፣ ሕይወቱ፣ ምሳሌ ሊጠቀስለት የማይችል (አምሳያ የሌለው) መልካምነት በሆነው በእርሱ ላይ ያነሳው የጭካኔ ክስ ሁሉ ስር ከሰደደ በቀል የመነጨ ነበር። ሰማይ ሁሉ እረጭ ብሎ በታላቅ ድንጋጤ ትዕይንቱ ላይ አፍጥጦ ሳለ፣ ታፍነው የነበሩት የቅናትና የክፋት፣ የጥላቻና የበቀል የእሳት ረመጦች፣ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በቀራንዮ ፈነዱ።GCAmh 362.4

    ታላቁ መስዋዕትነት ከተጠናቀቀ በኋላም “እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” [ዮሐ 17÷24] ብሎ ልመናውን እስኪያቀርብ ድረስ የመልአክቱን አክብሮት አልቀበልም ብሎ ክርስቶስ ወደ ላይ አረገ። ከዚያም በማይገለጽ ፍቅርና ኃይል፣ መልስ ከአብ ዙፋን ዘንድ እንዲህ ሲል መጣ፣ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ” [ዕብ 1÷6]። አንድ ነቁጥ እንኳ በየሱስ ላይ አልነበረም። መዋረዱ አብቅቶ፣ መስዋዕትነቱ ተጠናቆ፣ ከስም ሁሉ በላይ የሆነው ስም ተሰጠው።GCAmh 362.5

    አሁን የሰይጣን ኩነኔ ያለ ማስተባበያ እርቃኑን ቆመ። ውሸታምና ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ እውነተኛ ባህርይውን ገለጠ። የሰማይን ነዋሪዎች እንዲቆጣጠር ቢፈቀድለት ኖሮ፣ በስልጣኑ ስር የነበሩትን የሰው ልጆች ሲገዛበት የቆየውን ያንኑ መንፈስ ያንፀባርቅ እንደነበር ታዬ። የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ ነፃነትንና ከፍታን ያመጣል ብሎ ነበር፤ ውጤቱ ግን ባርነትና መቆርቆዝ መሆኑ ታዬ።GCAmh 363.1

    ሰይጣን በመለኮታዊ ባህርይና አስተዳደር ላይ የሰነዘራቸው የሐሰት ክሶች በትክክለኛ መልካቸው ታዩ። እግዚአብሔር ከፍጡራኑ የሚጠይቀው መገዛትና መታዘዝ ራሱን ብቻ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ፣ ፈጣሪ ከሌሎቹ ሁሉ ራስ-መካድን የሚፈልግባቸው ሆኖ ሳለ ራሱ ግን ራስ-መካድን እንደማይተገብር፣ መስዋዕትነትም እንዳልከፈለ አድርጎ ከሶት ነበር። “እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና” (2ኛ ቆሮ 5÷19) ለወደቀና ለኃጢአተኛ ዘር መዳን ሲል የዓለማት ሁሉ ገዢ፣ ፍቅር ሊያደርገው ከሚችለው፣ የመጨረሻውን፣ ታላቁን መስዋዕትነት እንደከፈለ አሁን ግልጽ ሆነ። ለክብርና ለበላይነት ባለው ፍላጎት የተነሳ ሰይጣን ኃጢአት ወደ ዓለም እንዲገባ በር የከፈተ መሆኑ፣ ክርስቶስ ደግሞ ኃጢአትን ያጠፋ ዘንድ ራሱን አዋርዶ፣ እስከሞት ድረስ ታዛዥ እንደነበር ጭምር ታዬ።GCAmh 363.2

    ለአመጽ መርሆዎች ያለውን ጥላቻ እግዚአብሔር አንፀባርቋል። በሰይጣን ላይ ባሳለፈው የውግዘት ውሳኔም ሆነ በሰው ልጆች መዳን፣ በሁለቱም አማካኝነት፣ ሰማይ ሁሉ የእርሱን ፍትህ አይቷል። የእግዚአብሔር ሕግ የማይለወጥ፣ ቅጣቱም የማይሻር ከሆነ እያንዳንዱ ተላላፊ ከእግዚአብሔር ቸርነት ለዘላለም መከልከል አለበት ብሎ ሰይጣን ተናግሮ ነበር። ኃጢአተኛው ዘር ከድነት መዳረሻ እርቀው የተቀመጡ [ድነትን ማግኘት የማይቻላቸው] በመሆናቸው ለእርሱ የተገቡ ታዳኞች እንደሆኑም ተናግሯል። ለሰው የተከናወነው የክርስቶስ ሞት ግን ሊገለበጥ የማይቻል (ፈቀቅ ሊያደርጉት የማይችል) መከራከሪያ ነው። የሕጉ ቅጣት፣ ከአብ ጋር እኩል በሆነው በእርሱ ላይ አረፈ፤ የክርስቶስንም ጽድቅ ይቀበል ዘንድ ሰው ነፃ ሆነ፤ በመዋረድና በፀፀት ሕይወትም፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንዳሸነፈ ሁሉ፣ እርሱም በሰይጣን ኃይል ላይ ድል እንዲነሳ ተደረገ። እግዚአብሔር እንዲህ ፃድቅ ነው፤ ያም ሆኖ በየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ የሚያጸድቅ ነው።GCAmh 363.3

    ነገር ግን ክርስቶስ ሊሰቃይና ሊሞት ወደ ምድር የመጣው የሰውን ድነት ለመፈፀም ብቻ አልነበረም። “ሕጉን ታላቅ ያደርግ” ዘንድ “ያከብርም ዘንድ” መጣ [ኢሳ 42÷21]። ሕጉን፣ የዚህ ምድር ነዋሪዎች ብቻ መከበር እንደሚገባው እንዲያከብሩት ብቻ ሳይሆን፣ በዩኒቨርስ ላሉ ዓለማት ሁሉ የእግዚአብሔር ሕግ መለወጥ የማይችል መሆኑን በተግባር ለማሳየት ነው። የሕጉ መጠይቅ ሊቀር የሚችል ቢሆን ኖሮ፣ የሕጉን መተላለፍ ያስተሰረይ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ሕይወቱን መስጠት አያስፈልገውም ነበር። የክርስቶስ ሞት ሕጉ መቀየር የማይችል መሆኑን ያረጋግጣል። ኃጥአን ነፃ ይሆኑ ዘንድ መጠን ከሌለው ፍቅር አስገዳጅነት የተነሳ አባትና ልጅ የከፈሉት፣ ከዚህ የስርየት እቅድ በቀር ሌላ ሊያከናውነው የማይችል [በመሆኑ፣ የተከፈለው] መስዋዕትነት ለዩኒቨርስ ሁሉ በተግባር የሚያረጋግጠው፣ ፍርድና ምሕረት የእግዚአብሔር ሕግና መንግሥት መሰረት መሆናቸውን ነው።GCAmh 363.4

    በመጨረሻው የፍርድ አፈጻፀም ጊዜ፣ ለኃጢአት መነሳት ምክንያት (መንስኤ) የሚሆን ምንም ነገር እንደሌለ ይታያል። የምድር ሁሉ ፈራጅ “ለምን አመጽክብኝ?፣ የመንግሥቴንስ ተገዥዎች ለምን ነጠቅኸኝ?” ብሎ ሲጠይቀው የክፋት ጠንሳሽ የሚያቀርበው ምክንያት አይኖረውም። ሁሉም አፍ ዝም ይላል፤ የአመጽ ሰራዊት ሁሉ መናገር ይሳነዋል።GCAmh 364.1

    የቀራንዮ መስቀል ሕጉ መቀየር እንደማይችል ሲናገር ሳለ፣ የኃጢአት ዋጋ ሞት መሆኑን ለዩኒቨርስ ሁሉ ያውጃል። “ተፈፀመ” በሚለው፣ ላንቃው እየተዘጋ በነበረው የአዳኙ ጩኸት ውስጥ፣ የሰይጣን ሞት ደወል ተደውሏል። ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የነበረው ታላቁ ተጋድሎ ተወሰነ፤ የመጨረሻው የኃጢአት ማስወገድ ሥራም ተረጋገጠ። “እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር” የእግዚአብሔር ልጅ በመቃብር በሮች ውስጥ አለፈ፣ “ይኸውም ዲያቢሎስ ነው” [ዕብ 2÷14]። የሉሲፈር፣ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ጥማት፣ “ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋከብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ….በልዑልም እመሰላለሁ” እንዲል አድርጎት ነበር። እግዚአብሔር ሲናገር፣ “በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ [አደርግሃለሁ]… እስከ ዘላለምም አትገኝም” ይላል [ኢሳ 14÷13፣14፤ ሕዝ 28÷18፣19]። “እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን በመጣ ጊዜ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሰሩ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል ስርና ቅርንጫፍም አይተውላቸውም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” [ሚል 4÷1]።GCAmh 364.2

    ስለ ኃጢአት ተፈጥሮና ውጤቶች መላው ዓለም (ዩኒቨርስ) ሁሉ ምስክር ይሆናል። በመጀመሪያ ቢፈፀም ኖሮ መላእክትን ያስደነግጥ እግዚአብሔርንም ያዋርድ የነበረው ኃጢአትን ሙሉ ለሙሉ የማስወገድ ሥራ፣ አሁን የተከሰሰበትን ፍቅሩን ነፃ የሚያወጣ፣ ፈቃዱን ሊያደርጉ በሚወዱ ሕጉም በልባቸው በተፃፈው ፊት ክብሩን የሚያደላድልለት ይሆናል። ኃጢአት ከእንግዲህ ፈጽሞ አይኖርም። የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “እርሱ ለጥፋት ዳርቻ ያደርጋል። መከራም ሁለተኛ አይነሳም” [ናሆም 1÷9] ይላል። ሰይጣን የባርነት ቀንበር አድርጎ ያወገዘው ሕግ፣ የነፃነት ሕግ ሆኖ ይከበራል። የተፈተነውና ያለፈው ፍጡር ፣ዲካ የሌለው ፍቅርና መጠን የሌለው ጥበብ ባለቤት የሆነው፣ ባህርይው ሙሉ ለሙሉ ከተገለጠው ከእግዚአብሔር፣ ታማኝነቱን ፈጽሞ ፈቀቅ አያደርግም።GCAmh 364.3