Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፬—ዋልደንሶች

    በጳጳሳዊ ሥርዓት የበላይነት ረጅም ዘመን፣ በምድር ላይ ሰፍኖ በነበረው ጽልመት መኃል የእውነትን የብርሐን ጮራ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አልተቻለም ነበር። በየዘመናቱ እግዚአብሔር ምስክሮች ነበሩት። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ብቸኛው አስታራቂ ክርስቶስ የመሆኑን እምነት የያዙ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የሕይወት መመሪያ መሆኑን የተቀበሉና ትክክለኛውን ሰንበት በቅድስና የጠበቁ ሰዎች እግዚአብሔር ነበሩት። ዓለም ለእነዚህ ሰዎች ምን ያህል ባለ ዕዳ እንደሆነ ትውልድ ፈጽሞ ሊያውቀው አይችልም። ሃሳባቸውና ምክንያታቸው እየተተቸ፣ ባህርያቸው በተንኮልና በግፍ እየተበረዘ፣ ጽሁፎቻቸው እንዳይሰራጩ እየተገደቡ፣ ያልሆነ ስም እየተሰጣቸውና እየተበጫጨቁ፣ የመናፍቅነት ስያሜ ይሰጣቸው ነበር። ሆኖም ንቅንቅ ሳይሉ ከዘመን ዘመን የእምነታቸውን ንጽህና ጠብቀው በቅዱስ ቅርስነት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲቆይ በቆራጥነት ቆመዋል።GCAmh 48.1

    ሮም ስልጣኑን መቆጣጠርዋን ተከትሎ በሰፈነው የጨለማ ዘመን የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ታሪክ በሰማይ ተጽፏል፤ በፍጡር መዛግብት ውስጥ ግን ቦታ አልተሰጠውም። ከአሳዳጆቻቸው ይቀርብባቸው ከነበረው ክስ በስተቀር የመኖራቸው ፈለግ የትም አይገኝም ማለት ይቀላል። ሮም፣ ከአስተምህሮዋ ወይም ከአዋጆችዋ መካከል እንዳንዱን የተቃውሞ ዱካ በነቂስ ፈልጎ የማውደም መርሃ-ግብር ትከተል ነበረች። ኑፋቄአዊ የሆነ ሁሉ፣ ሰውም ይሁን ጽሁፍ ፈጽሞ እንዲጠፋ ተደርጓል። ሊቀ-ጳጳሱ ስለደነገጋቸው ቀኖናዎች ስልጣን የተንጸባረቀች ቅንጣት ጥርጥር፣ ወይም የቀረበች አንዲት ጥያቄ፣ የከፍተኛውንም ይሁን የዝቅተኛውን፤ የሃብታሙንም ይሁን የድሃውን ነፍስ ለመቅጠፍ በቂ ምክንያት ነበረች። በተቃዋሚዎች ላይ የፈጸመችው እያንዳንዱ የግፍና የጭካኔ መዝገብም እንዲጠፋ ሮም ያለሰለሰ ጥረት አድርጋለች። ጳጳሳዊ ጉባኤዎች እንደዚህ አይነቶቹ መዛግብት በእሳት እንዲቃጠሉ በአዋጅ አጽድቀው ነበር። [ዘመናዊ] ህትመት ከመፈጠሩ በፊት መጻሕፍት በቁጥር ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ፣ አሰራራቸው ለረዥም ጊዜ ጠብቆ ለማቆየት የሚመች አልነበረም፤ በመሆኑም ሮማውያኑ እቅዳቸውን እንዳያከናውኑ የሚያግድ ብዙም መደረግ የሚችል ነገር አልነበረም።GCAmh 48.2

    የህሊና ነጻነትን ከማጣጣም ሳይረበሽ ለረጅም ጊዜ የቆየ፣ በሮማ የስልጣን ወሰን ውስጥ የነበረ ቤተ ክርስቲያን አልነበረም። ጳጳሳዊው ሥርዓት የበላይነት ስልጣን እንዳገኘ፣ ወዲያውኑ [ሮማዊ ቤተ ክርስቲያን] ለስልጣንዋ እውቅና በማይሰጡ ላይ ሁሉ እጅዋን ዘርግታ ትደቁሳቸው ነበረች። አንዱ ቤተ ክርስቲያን ሌላውን እየተከተለ፣ ሁሉም ለስልጣንዋ ተንበረከኩ።GCAmh 48.3

    በታላቋ ብሪታንያ ጥንታዊ ክርስትና ቀደም ብሎ ስር ሰዶ ነበር። በመጀመሪያዎቹ መቶ ዓመታት እንግሊዞች የተቀበሉት ወንጌል በሮም ክህደት አልተበረዘም ነበር። በእምነት-የለሽ ነገሥታት ሲካሄድ የነበረው ግድያና ስደት ወደነዚህ ሩቅ ዳርቻዎች ደርሶ የመጀመሪያዎቹ የእንግሊዝ አብያተ ክርስቲያናት ከሮም የተቀበሉት ስጦታ ቢኖር ስደትን ነበር። ብዙ ክርስቲያኖች ከእንግሊዝ ስደትን በመሸሽ በስኮትላንድ መጠጊያ አገኙ፤ በዚህ ሁኔታም እውነቱ ለአየርላንድ ደረሰ፤ በእነዚህ አገራት ሁሉ በደስታ ተቀባይነትን አገኘ።GCAmh 48.4

    ሳክሰኖች [አሁን ጀርመን ተብሎ በሚጠራው አገር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ] እንግሊዝን ሲወሩ አረማዊነት የበላይነቱን ተቆጣጠረ። ባርያዎቻቸው ያስተምሯቸው ዘንድ ወራሪዎች በንቀት ስላልተቀበሉአቸው፣ ክርስቲያኖቹ ወደ ተራሮችና የዱር ጠፍ ጎባባ ስፍራዎች ለመሸሽ ተገደዱ፤ ለተወሰነ ጊዜ የተደበቀው ብርሐን ግን መብራቱን ቀጠለ። በስኮትላንድ፣ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ፣ ብርሐኑ፣ ሩቅ ወደ ሆኑ ስፍራዎች መሰራጨት በሚችል ጮራ አንጸባረቀ።GCAmh 49.1

    በአየርላንድ ፈሪሐ-እግዚአብሔር ያለው ኮሉምባና ግብረ አበሮቹ ፈንጠር ብላ በተቀመጠችው የአዮና ደሴት የተበታተኑ አማኞችን በማሰባሰብ፣ ይህንን ስፍራ የሚስዮናዊ ሥራቸው ማዕከል አደረጉት። በእነዚህ ወንጌላውያን መካከል የመጽሐፍ ቅዱስን ሰንበት የሚጠብቅ ስለነበር ይህ እውነት በሕዝቡ መካከል እንዲተዋወቅ ተደረገ። በአዮና ትምህርት ቤት ተከፍቶ አገልጋዮቹ ወደ ስኮትላንድና እንግሊዝ ብቻ ሳይሆን ወደ ጀርመንና ስዊዘርላንድ፣ አልፈውም እስከ ኢጣሊያ ድረስ ሄዱ።GCAmh 49.2

    ሮም ግን በብሪታንያ ላይ አይንዋን ጥላ ነበረች፣ በግዛትዋ ስር ለማድረግም ቆርጣ ተነሳች። በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም ቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊያን እምነት የለሾቹን ሳክሰናዊያንን የመለወጥ ሥራ ተያያዙት። እነርሱም በኩሩዎቹ በርበሮች በደስታ ተቀባይነትን አገኙ፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩም የሮምን እምነት እንዲቀበሉ ተደረጉ። ይህ ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ ጳጳሳዊ መሪዎችና የተለወጡት ሰዎች ጥንታዊ ክርስቲያኖችን ተጋጠሟቸው። በሁለቱ መካከል እጅግ የሰፋ ልዩነት ነበር። ጥንታዊ ክርስቲያኖቹ ተራና ትሁት፤ በባህርይ፣ በአስተምህሮና በአጠቃላይ ስነ ምግባር መጽሐፍ ቅዱሳዊ የነበሩ ሲሆን በአንጻሩ ሮማውያኑና የእነርሱን እምነት የተቀበሉ ደግሞ በጳጳሳዊ ሥርዓት አጉል እምነት የተያዙ፣ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት የታጀቡና በእብሪት የተወጠሩ ነበሩ። የሮማው ልዑክ እነዚህ የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ከፍ ከፍ ላለውና ከሁሉ በላይ ለሆነው ለሊቀ-ጳጳሱ ስልጣን እውቅና እንዲሰጡ ጥያቄ አቀረበ። ብሪታንያውያኑ፣ ሁሉንም የሰው ዘር መውደድ እንደሚፈልጉ በትህትና በመግለጽ ሊቀ-ጳጳሱ ግን በቤተ ክርስቲያን የበላይነት ስፍራ እንደሌለው፣ ለማንኛውም የክርስቶስ ተከታይ የሚሰጡትን ክብር ወይም መታዘዝ ለእርሱም እንደሚለግሱ ተናገሩ። ለሮም ታማኝነታቸውን እንዲያሳዩ ተደጋጋሚ ሙከራ ተደረገ፤ ሆኖም እነዚህ ትሁት ክርስቲያኖች በልዑካኑ ትዕቢት ተደንቀው ከክርስቶስ በቀር ሌላ ጌታ እንደማያውቁ ሳያወላውሉ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ እውነተኛው የጳጳሳዊ ሥርዓት መንፈስ ተገለጠ። የሮማው መሪ እንዲህ አለ፦ “ሰላም የሚያመጡላችሁን ወንድሞች ካልተቀበላችሁ፤ ጦርነት የሚያመጡባችሁን ጠላቶች ትቀበላላችሁ፤ ለሳክሰኖች የሕይወትን መንገድ እናሳያቸው ዘንድ ከእኛ ጋር ካልተባበራችሁ፣ ከእነርሱ ዘንድ የሞት ምትን ትቀበላላችሁ።”- J. H. Merle D’ Aubigné, History of the Reformation of the Sixteenth Century, b. 17, ch. 2። እነዚህ ተራ ማስፈራሪያዎች አልነበሩም። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት ምስክሮች የነበሩባቸው የብሪታንያ አብያተ ክርስቲያናት እስኪወድሙ ወይም ተገደው የሊቀ-ጳጳሱን የበላይነት እስኪቀበሉ ድረስ ጦርነት፣ ስውር ሴራና ማጭበርበር ተፈጸመባቸው።GCAmh 49.3

    ከሮማ ግዛት ውጪ በሆኑ ስፍራዎች ከጳጳሳዊ ሥርዓት ብክለት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል፣ ነጻ የሆኑ፣ ለብዙ መቶ ዓመታት የኖሩ ክርስቲያኖች ነበሩ። በአሕዛብ ተከበው የኖሩ ከመሆናቸው የተነሳ ዘመን ሲቆጠር በስህተቱ ተጽእኖ ደርሶባቸው ነበር፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የእምነት መርህ መሆኑን በመጠበቅ አብዛኛውን እውነት ይከተሉ ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ሕግ ዘላለማዊነት በመቀበል የአራተኛውን ትዕዛዝ ሰንበትንም ያከብሩ ነበር። ይህንን እምነትና ምግባር የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያናት በመካከለኛው አፍሪካ እንዲሁም በእስያ አርመኖች መካከል ነበሩ።GCAmh 50.1

    የሊቀ-ጳጳሱን ስልጣን [ወደ ግዛታቸው] መግባት ከተቃወሙት መካከል ግን ዋልደንሶች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። ጳጳሳዊ ሥርዓት መሰረት በጣለበትና በተቀመጠበት፣ በዚያው ስፍራ ነበር ውሸቱና ብልሽቱ ከፍተኛ ቆራጥነት የታየበት ተቃውሞ የገጠመው። ለብዙ መቶ ዓመታት የፒየድሞንት አብያተ ክርስቲያናት ነጻነታቸውን ጠብቀው ቆይተው ነበር። ነገር ግን በመጨረሻ ሮም በስርዋ ይሆኑ ዘንድ ጥያቄዋን ያበረታችበት ጊዜ መጣ። ጨቋኝ የአገዛዝ ስርዓቷን ለመቃወም ቢጥሩም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተው፣ በመጨረሻ ዓለም ሁሉ የሚያከብረው ለሚመስለው ሊቀ-ጳጳስ፣ የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ፈራ ተባ እያሉ፣ ያለፍላጎታቸው ለስልጣን የበላይነቱ እውቅና ሰጡ። ሆኖም ለሊቀ-ጳጳሱ ወይም ለቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናቱ አገዛዝ እጅ አንሰጥም ያሉ ጥቂቶች ነበሩ። ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት ለመቀጠል፣ የእምነታቸውንም ንጽህናና ግልጽነት ለመጠበቅ የቆረጡ ነበሩ። ሁለቱ ጎራዎች ተነጣጠሉ። የጥንቱን ኃይማኖት የጠበቁ አፈግፍገው ወደ ሌላ ስፍራ ሄዱ። ገሚሶቹ የተወለዱበትን አልፕስን ለቀው በመሰደድ በባዕድ ሀገራት የእውነትን ሰንደቅ አላማ ያውለበልቡ ጀመር። ሌሎቹ ደግሞ ወደ ገለልተኛ ሸለቆዎች፣ ተፈጥሮአዊ መከለያነታቸው ወደሚመቸው ድንጋያማ ተራሮች በመሸሽ እግዚአብሔርን የማምለክ ነጻነታቸውን በዚያ ስፍራ መጠበቅ ቻሉ።GCAmh 50.2

    ለብዙ መቶ ዓመታት የዋልደንሳዊያን ክርስቲያኖች ጠብቀው ያቆዩትና ያስተማሩት እምነት ከሮም ከሚወጣው የሐሰት አስተምህሮ ግልጽ ልዩነት ነበረው። እምነታቸው የተመሠረተው የክርስትና እውነተኛ ሥርዓትና መዋቅር በሆነው፣ በተጻፈው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ተራ ገበሬዎች፣ በመንጎቻቸውና በወይን ስፍራዎቻቸው መሃል በየቀኑ የሚለፉ ምስኪኖች፣ ከዓለም ተዘግተው፣ በተደበቀው ቀያቸው እየኖሩ፣ እውነትን ያገኙት የከሃዲዋ ቤተ ክርስቲያንን ሕጎችና ኑፋቄዎች በተቃወሙበት ጊዜ አልነበረም። የእነርሱ እምነት አዲስ የተቀበሉት አልነበረም። ይህ እምነታቸው ከአባቶቻቸው የወረሱት ነበር። ለሐዋርያት ዘመን ቤተ ክርስቲያን እምነት “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ኃይማኖት” [ይሁዳ 3] የሚጋደሉ ነበሩ። ለዓለም ይሰራጭ ዘንድ እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ የሰጠውን የእውነት ቅርስ ጠባቂ የነበረችው እውነተኛዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ “በምድረ በዳ በማህበሩ ውስጥ” የነበረችው ቤተ ክርስቲያን [የሐ. ሥራ 7÷38] እንጂ፣ በዓለም ታላቅ ከተማ በዙፋን ላይ ተቀምጦ የነበረው ኩሩው መዋቅር[ጳጳሳዊ ሥርአቱ] አልነበረም።GCAmh 50.3

    እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን እና ሮም እንዲለያዩ ካደረጉት መሪ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሮም ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሰንበት የነበራት ጥላቻ ነበር። በትንቢት አስቀድሞ እንደተነገረው ጳጳሳዊ ስልጣን እውነትን ወደ ታች፣ ወደ ትቢያ ጣለው። የሰዎች ባህልና ወግ ከፍ ከፍ ሲል የእግዚአብሔር ሕግ ግን አቧራ ላይ ይረጋገጥ ነበር። በጳጳሳዊ ሥርዓት አገዛዝ ስር የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት አስቀድሞ እሁድን በቅዱስ ቀንነት እንዲያከብሩ ተገደው ነበር። በተንሰራፋው ስህተትና መላምት ተወናብደው ብዙዎች፣ የእግዚአብሔር ታማኝ ባርያዎች እንኳ ሳይቀር፣ እውነተኛውን ሰንበት እያከበሩ ሳለ በእሁድ ቀን ሥራ ከመሥራት ተቆጥበው ነበር። ይህ ግን ጳጳሳዊ መሪዎቹን አላረካቸውም። እሁድ እንዲቀደስ ብቻ ሳይሆን ሰንበት[ቅዳሜ] እንዲረክስ ጭምር ጠየቁ። ቋንቋቸው ውስጥ ማግኘት በቻሉት ከባድ ቃልም የሚያከብሩትን አወገዙ። የእግዚአብሔርን ሕግ በሰላም ለመታዘዝ የነበረው ብቸኛው አማራጭ ከሮም ስልጣን መሸሽ ነበር።GCAmh 50.4

    ዋልደንሶች ከአውሮፓ ሕዝቦች ሁሉ አስቀድመው የመጽሐፍ ቅዱሳት ትርጉም ያገኙ ሰዎች ነበሩ። ተሐድሶ ከመጀመሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በራሳቸው ቋንቋ በእጅ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ነበራቸው። ያልተበረዘው እውነት ነበራቸው፤ ይህም የጥላቻና የስደት ኢላማ እንዲሆኑ አደረጋቸው። የሮም ቤተ ክርስቲያን በመጨረሻ የምትጠፋው ከሃዲዋ ባቢሎን እንደሆነች አወጁ፤ ለነፍሳቸውም ሳይሳሱ ብክለትዋን ተቃውመው ተነሱ። ለረጅም ዘመን ከቀጠለው ስደት የተነሳ ጥቂት በጥቂት ልዩ ከሆኑት መመሪያዎቹ እየተንሸራተቱ የተወሰኑት እምነታቸውን ቢደራደሩበትም ሌሎች ግን ለእውነት በጽናት ቆሙ። ለዘመናት በሰፈነው ጽልመትና ክህደት ውስጥ የሮምን የበላይነት የካዱ፣ ለምስል መስገድ ጣዖትን እንደማምለክ ነው በማለት ያልተቀበሉ፣ እውነተኛውን ሰንበት ሲጠብቁ የነበሩ ዋልደንሶች ነበሩ። ተወዳዳሪ በሌለው የተቃውሞ ማዕበል ውስጥ እንኳ እምነታቸውን ጠብቀው ቆመዋል። በሳቮያርድ ጦር ቢቆረሱም፣ በሮም ትንታግ ቢርመጠመጡም፣ ለእግዚአብሔር ቃልና ለእርሱ ክብር ሲሉ ፍንክች ሳይሉ ቆመዋል።GCAmh 51.1

    በሁሉም ዘመናት የሚጨቆኑና የሚሰደዱ ሁሉ መጠለያ በነበሩት፣ በግዙፎቹ የተራራ ቅጥሮች በስተጀርባ ዋልደንሶች መሸሸጊያ ስፍራ አገኙ። በዚህ ስፍራ፣ በመካከለኛው ዘመናት ጨለማ መሃል የእውነት ችቦ መብራቱን እንዲቀጥል ተደርጎ ነበር። በዚህ ስፍራ የእውነት ምስክሮች የጥንቱን ኃይማኖት ለአንድ ሺህ ዓመት ጠብቀው ቆይተዋል።GCAmh 51.2

    በአደራ የተሰጣቸውን ታላላቅ እውነቶች የሚገጥም አስደማሚ ውበት የተላበሰ ማደሪያ እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ አዘጋጅቶላቸው ነበር። ለእነዚያ ታማኝ ስደተኞች እነዚህ ተራሮች የእግዚአብሔር የማይለወጥ ጽድቁ አርማዎች ነበሩ። በማይለወጥ ግርማ ሞገስ በላያቸው ወዳንዣበቡት ከፍታዎች ልጆቻቸውን በማመልከት፣ ተለዋዋጭነት ስለሌለው፣ አቅጣጫ የሚቀይር ጥላ ስለማይጥልበት ቃሉ፣ ለዘላለም እንደ ቆሙት ኮረብታዎች የጸና ስለሆነው እግዚአብሔር ይነግሯቸው ነበር። ተራሮችን እግዚአብሔር አጽንቶ አቆማቸው፣ ኃይልም አስታጠቃቸው፤ ከመለኮታዊ ኃይል በቀር ከስፍራቸው ሊያንቀሳቅሳቸው የሚችል ክንድ የለም። በተመሳሳይ ሁኔታ በሰማይና በምድር የመንግሥቱ መሰረት የሆነውን ሕጉን አጸና። የሰው ክንድ ተዘርግቶ የመሰል ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ይሆናል፤ ያ [የፍጡር] ክንድ ከእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ አንድ መመሪያ መለወጥ ይችላል ማለት ግን፣ ተራሮችን ከስር መሰረታቸው በቀላሉ መንግሎ ወደ ባህር ሊወረውራቸው ይችላል፤ ፈቃዱን ለሚያደርጉት ጌታ የሰጠውን ተስፋ ሙሉ ለሙሉ መሰረዝ ይሳካለታል ማለት ነው። የእግዚአብሔር ባርያዎች ለሕጉ ያላቸው ታማኝነት እንደማይነቃነቁት ኮረብታዎች የጸና መሆን ይገባዋል።GCAmh 51.3

    ጎድጓዳ ሸለቆዎቻቸውን ተጠማጥመው የቆሙት ተራሮች የእግዚአብሔር የፈጠራ ችሎታ ቋሚ ምስክሮች፣ ፈጽሞ የማይቋረጠው ጥበቃውና እንክብካቤው ዋስትና ነበሩ። እነዚያ የእምነት መንገደኞች የእግዚአብሔርን መገኘት የሚያሳዩትን የማይናገሩ ምልክቶች ይወድዋቸው ዘንድ ተማሩ። ዕጣ ፈንታቸው በሆነው የመከራ ኑሮ ያማርሩ ዘንድ ለራሳቸው አልፈቀዱለትም፤ ጭር ባለው ተራራ መሃል ፈጽሞ ብቸኝነት አልተሰማቸውም። ከሰዎች ቁጣና ጭካኔ የሚያመልጡበት የጥገኝነት ስፍራ እግዚአብሔር ስላዘጋጀላቸው ያመሰግኑት ነበር። በፊቱ ቆመው ያመልኩት ዘንድ ነጻነት ስላገኙ በደስታ ይፈነድቁ ነበር። ጠላቶቻቸው ባሳደዱዋቸው ጊዜ የኮረብታዎቹ ብርታት አስተማማኝ መከለያ ሆኖአቸው ነበር። ከበርካታ ግዙፍ የገደል ጠርዞች ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ የምስጋና መዝሙራቸውን ከመዘመር ዝም ያሰኝ ዘንድ የሮም የጦር ሰራዊት አልተቻለውም።GCAmh 52.1

    የእነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች እምነት፣ ንጹህ፣ ያልተወሳሰበና ልብን የሚነካ ነበር። ለእውነት መርሆች የሰጡት ዋጋ ከቤት፣ ከይዞታ፣ ከጓደኛ፣ ከዘመድ፣ ከራሱ ከሕይወት እንኳን ሳይቀር የላቀ ነበር። እነዚህን መርሆዎችም በወጣቶች ልብ ውስጥ ለማተም በትጋት ይለፉ ነበር። ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ወጣቶች በእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ይገነቡ ነበር፤ የእግዚአብሔርን ሕግ መጠይቅም በቅድስና ይጠብቁ ዘንድ ይማሩ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች [ማግኘት] ብርቅ ነበር። በመሆኑም የከበረ ዋጋ ያላቸው ቃላት (ጥቅሶች) በአእምሮ ማስታወሻ መቀመጥ ነበረባቸው። ብዙ ሰዎች የብሉይና የአዲስ ኪዳን ብዙ መጻሕፍትን በቃላቸው መድገም ይችሉ ነበር። ስለ እግዚአብሔር ያለው ሀሳብ፣ ግርማ ሞገስ ከተላበሰው የተፈጥሮ ገጽታና ከእለት ተዕለት ኑሮ ጥቃቅን በረከቶች ጋራ ተቆራኝቶ ነበር። የእያንዳንዷ ውለታ፣ የእያንዳንዷ መጽናኛ፣ ሰጪ እንደሆነ አድርገው በምስጋና ወደ እግዚአብሔር ይመለከቱ ዘንድ ህጻናት ተማሩ።GCAmh 52.2

    ደግና አፍቃሪ የነበሩት ወላጆች ጥበብ ከተሞላው ፍቅራቸው የተነሳ ልጆቻቸው ራስን የማርካት ልማድ ይወርሱ ዘንድ አልተዋቸውም። የሚጠብቃቸው የፈተናና የመከራ ሕይወት፣ ምናልባትም ሰማዕትነት ነው። አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንዲያልፉ፣ ለቁጥጥር እጅ የሰጡ፣ ሆኖም የሚያደርጉትን ነገር ራሳቸው አስበው እንዲተገብሩት ሆነው ገና ከልጅነታቸው ተማሩ። ገና በህጻንነት እድሜያቸው ሃላፊነት እንዲሸከሙ፣ በንግግር ጥንቁቅና ቁጥብ እንዲሆኑ እንዲሁም የዝምታን ጥበብ እንዲያውቁ ሆነው ተማሩ። ተኩላ አደን እንደሚያድን፣ የእምነት ነጻነት ይኖራቸው ዘንድ የደፈሩ ሁሉ በጠላቶቻቸው ይታደኑ ስለነበር፣ አንድ ጥበብ የጎደለው አነጋገር ጠላቶቻቸው ጆሮ ቢገባ የተናጋሪው ብቻ ሳይሆን በመቶ የሚቆጠሩ ወንድሞች ሕይወትም አደጋ ላይ ይወድቃል።GCAmh 52.3

    ዋልደንሶች ለእውነት ሲሉ ዓለማዊ ብልጽግናን ሰዉ፤ በፅኑ ትዕግስትም ለዕለት ጉርሳቸው ይለፉ ነበር። በተራሮች መካከል የተገኘች መታረስ የምትችል ቁራጭ መሬት ሁሉ የተሻለ ምርት እንድትሰጥ ተዘጋጀች። ሸለቆዎችና ብዙም ለም ያልሆኑት ኮረብታማ ቦታዎች የተሻለ ምርት እንዲሰጡ ተደረጉ። ቁጠባና ጥብቅ ራስን መካድ የልጆች ብቸኛ ውርስ ከነበረው ትምህርት ውስጥ ከፊሎቹ ነበሩ፤ ከትምህርት በቀር ውርስ አልነበረላቸውም ነበርና። ሕይወት ራሱ ትምህርት(ሥነ-ሥርዓት) እንዲሆን አድርጎ እግዚአብሔር እንደሚያዘጋጀው ተማሩ፣ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሊሟሉላቸው የሚችሉት በግል ጥረት፣ ስለ ወደፊቱ እቅድ በማውጣት፣ በጥንቃቄና በእምነት እንደሆነ ተማሩ። ይህ የትምህርት ሂደት ብዙ ጉልበት የሚጨርስና አድካሚም ነበር፣ ሆኖም የሰው ልጅ በውድቀቱ (በወደቀ ሁኔታው ሆኖ) የሚያስፈልገው፤ የስነ-ምግባርና የጤና ሙሉነት የሚያመጣ፣ ለስልጠናና ለእድገት እግዚአብሔር ያመቻቸው ትምህርት ቤት ነበር።GCAmh 52.4

    ወጣቶች ከልፋትና ከችግር ጋር እንዲለማመዱ ተደርገው ሳለ የአእምሮ መዳበር ጉዳይም ችላ አልተባለም ነበር። ችሎታዎቻቸውና ጉልበቶቻቸው ሁሉ የእግዚአብሔር ንብረት እንደሆኑ፣ ለእርሱ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሊሻሻሉና ሊጎለብቱ እንደሚገባ ተማሩ።GCAmh 53.1

    የቫውዶይስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በንጽህናቸውና በቀጥተኝነታቸው በሐዋርያት ዘመን የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት ይመስሉ ነበር። የሊቀ-ጳጳሱንና ተዛማጅ ባለስልጣናትን የበላይነት እምቢ በማለት፣ ብቸኛ የበላይና ስህተት የማይሰራው ስልጣን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ አቋም ወሰዱ። ፓስተሮቻቸው ምድራዊ ግርማ ሞገስ ተላብሰው የቀብራራነት መልክ እንደሚታይባቸው የሮማ ቀሳውስት ሳይሆን፣ “ሊያገለግል… እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” [ማቴ 20÷28] ተብሎ የተጻፈለትን የጌታቸውን ምሳሌ ተከተሉ። ወደ ቅዱስ ቃሉ የለመለመ መስክና ሕያው ምንጮች እየመሩ መንጋውን መገቡ። የሰዎች ታይታና ኩራት ማስታወሻ ሆነው ከተገነቡ ህንጻዎች ርቀው፣ ይሰበሰቡ የነበሩት፣ በሚያማምሩ ቤተ ክርስቲያናት ወይም በታላላቅ ቤተ መቅደሶች ሳይሆን የተራሮች ጥላ በሚያርፍባቸው በአልፓይን ሸለቆዎች፤ በአደጋ ጊዜ ደግሞ በድንጉር ድንጋዮች ውስጥ ነበር። በዚያም ስፍራ የእውነትን ቃል ከክርስቶስ ባርያዎች ያደምጡ ነበር። ፓስተሮቹ ወንጌልን መስበክ ብቻ ሳይሆን የታመመን ይጠይቁ፣ በጥያቄና መልስ ልጆችን ያስተምሩ፣ የሚያጠፉትን ይገስጹ፣ አለመግባባትን ለማስወገድ መስማማትና የወንድማማችነት ፍቅር ይሰፍን ዘንድ ይተጉ ነበር። ሆኖም እንደ ድንኳን ሰፊው ጳውሎስ አስፈላጊ ሲሆን ራሳቸውን መርዳት የሚያስችላቸው ንግድ ወይም ሞያ እያንዳንዳቸው ተምረው ነበር።GCAmh 53.2

    ወጣቶች ከፓስተሮቻቸው ትምህርት ይቀበሉ ነበር። ለአጠቃላይ የትምህርት ዘርፎች ትኩረት ቢሰጥም የጥናታቸው ዋናው ክፍል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። የማቴዎስና የዮሐንስ ወንጌሎች፣ ብዙ [የጳውሎስና የመሳሰሉት] መልእክቶችን ጨምሮ በቃላቸው ሸምድደው ለመያዝ ያጠንዋቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳትን የማባዛት ሥራም ይሰሩ ነበር። አንዳንዶቹ ጽሁፎች ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን የያዙ የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ አጠር አጠር ያሉ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ተንትነው ማስረዳት የሚችሉ ሰዎች ገለጻዎች ተካተውባቸው ነበር። እንዲህም በመሆኑ፣ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ ከፍ በሚያደርጉት ዘንድ ለረዥም ጊዜ ተደብቀው የነበሩት የእውነት እምቅ ሃብቶች መውጣት ችለዋል።GCAmh 53.3

    በትዕግስትና ታከተኝ በማይል ጥረት፣ አንዳንድ ጊዜ በጥልቅና ብርሐን በሌለበት ዋሻ ውስጥ በኩራዝ መብራት ጥቅስ በጥቅስ፣ ምዕራፍ በምዕራፍ ቅዱሳት መጻሕፍት ተገለበጡ። በዚህ ሁኔታ የተገለጸው የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ንጹህ ወርቅ እያንጸባረቀ ሥራው ቀጠለ። ለዚህ ሥራ ሲባል ከተጋፈጧቸው ፈተናዎች የተነሳ ስኬቱ ምን ያህል አንጸባራቂ፣ ብሩህና ኃያል እንደነበረ ሥራውን ከሰሩት በቀር ሊረዳው የሚችል የለም። መላዕክት ከሰማይ እነዚህን ታማኝ ሰራተኞች ይከብቡ ነበር።GCAmh 53.4

    ሰይጣን በአጉል እምነት፣ በኑፋቄ፣ እንዲሁም በስህተት ድሪቶ ስር የእውነትን ቃል ይቀብሩ ዘንድ ጳጳሳዊ ቀሳውስቱንና መሪዎቹን ቢያነሳሳም ቅሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሳይበላሽና ሳይበረዝ በጨለማ ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ሊቆይ ችሏል። የያዘው የሰውን ማህተም ሳይሆን የእግዚአብሔርን አሻራ ነበር። ግልጽና ቀላል የሆኑትን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም ለመደበቅ፣ እርስ በርሳቸውም የሚጋጩ እንደሆኑ ለማስመሰል ሰዎች ሳይታክቱ ለፍተዋል። ነገር ግን በተናወጠ ባህር ላይ እንዳለች መርከብ ሊያጠፋው የተነሳውን ማዕበል የእግዚአብሔር ቃል በድል ቀዝፎ ይወጣል። በወርቅና በብር የበለፀገ የማዕድን ስፍራ፣ የከበሩት ክምችቶች መውጣት ይችሉ ዘንድ የሚፈልጓቸው ሁሉ አጥብቀው መቆፈር እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስም ሃቀኛ፣ ትሁትና ጸሎት አዘውታሪ ብቻ ሊያገኘው የሚችለው የእውነት ክምችት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም የሰው ዘር፣ በልጅነት፣ በወጣትነትና በጎልማሳነት የመማሪያ መጽሐፍ እንዲሆን፣ ሁልጊዜም ይጠና ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀው ነው። የራሱ መግለጫ አድርጎ ቃሉን ለሰው ልጆች ሰጠ። እያንዳንዱ የሚስተዋል አዲስ እውነት የፀሐፊውን የአምላክን ባህርይ የሚያሳውቅ ትኩስ መገለጥ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሰዎችን ወደ ፈጣሪያቸው ለማቅረብና ለማቆራኘት፤ ስለ ፈቃዱም ያላቸው እውቀት የበለጠ ግልጽ ይሆን ዘንድ በመለኮት የተሾመ (የተቀባ) ነው። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የመግባቢያ ቋንቋ ነው።GCAmh 54.1

    ዋልደንሶች የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ቢያውቁም ከዓለም ጋር በመገናኘት ስለሰዎችና ስለ ነባራዊ ሕይወት በሚገኘው እውቀት አእምሮ እንደሚሰፋ፣ የመገንዘብ ችሎታም እንደሚነቃቃ አልጠፋቸውም ነበር። ከአልፕስ ከሚገኘው ቀያቸው የተሻለ ለጥናት አስተሳሰብን ለማዳበርና በጥልቀት ለማስተዋል የሚያግዙ፣ ሰፋ ያሉ የጥናት ዘርፎች ወዳሏቸው ተቋሞች አንዳንድ ወጣቶቻቸው ከተራራው ትምህርት ቤታቸው ወጥተው በፈረንሳይና በኢጣሊያ ወደሚገኙ ከተሞች ይላኩ ነበር። የተላኩት ወጣቶችም ለፈተና ይጋለጡ ነበር፤ ብልሹ ስነምግባር ተመለከቱ፤ ተወዳዳሪ የሌላቸው ብልጠት የተላበሱ ክህደቶችንና አደገኛ ማጭበርበሮችን ይቀበሉ ዘንድ በብልሃተኛ የሰይጣን ወኪሎች ይገፋፉ ነበር። ሆኖም ከልጅነት ጀምሮ የተማሩት ትምህርት ለእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ እንዲዘጋጁ የማድረግ ባህርይ ነበረው።GCAmh 54.2

    በገቡባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ ምስጢረኛ ይኖራቸው ዘንድ አይፈቅዱም ነበር። ልብሶቻቸውም ታላቁን ቅርሳቸውን፣ በእጅ የተፃፉትን፣ የከበሩትን የመጽሐፍ ቅዱሳት ቅጅዎች እንዲደብቁ ሆነው በጥንቃቄ የተሰፉ ነበሩ። የወራትና የዓመታት ልፋት ውጤት የሆኑትን እነዚህን ጥቅል ጽሁፎች ይዘዋቸው በመዞር፣ ጥርጣሬ ሳይጭሩ ማድረግ በሚችሉበት ሰዓት፣ ልባቸው እውነትን ለመቀበል ክፍት በሚመስሉት መራመጃ መንገድ ላይ የጽሁፎቻቸውን ከፊል ያኖሩ ነበር። ይህንን እቅድ በማሰብ ነበር የዋልደንሶች ወጣቶች በእናቶቻቸው ጉልበት ስር ሆነው የሰለጠኑት። ሥራቸውን በሚገባ ይረዱ፣ በታማኝነት ይፈጽሙትም ነበር። በዚህ ሁኔታ እውነተኛውን እምነት የተቀበሉ ሰዎች በትምህርት ተቋማቱ ተገኙ፣ የእውነት መርሆችም አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ቤቱ በሙሉ ሰርገው ገብተው ይታዩ ነበር። ጳጳሳዊ መሪዎች በቅርበት ቢመረምሩና ቢያጣሩም፣ የሚበክል ኑፋቄ ብለው የሚጠሩትን ትምህርት ምንጭ ማወቅ አልተቻላቸውም።GCAmh 54.3

    የክርስቶስ መንፈስ ሚሲዮናዊ መንፈስ ነው። የተለወጠው ልብ የመጀመሪያ ትርታው ሌሎቹንም እንዲሁ ወደ አዳኙ ማምጣት ነው። የቫውዶይስ ክርስቲያኖች መንፈስ ይህን ይመስል ነበር። እውነትን በንጽህናው በራሳቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ጠብቀው ከማቆየት ባለፈ እግዚአብሔር የሚፈልግባቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸው ነበር። በጨለማ ላሉ ሁሉ ብርሃናቸው ያንጸባርቅ ዘንድ ታላቅ ሃላፊነት እንደተጣለባቸው ያውቁ ነበር። በማይበገረው በእግዚአብሔር ቃል ኃይል ሮም የጫነችውን ቀንበር መስበር ጽኑ ፍላጎታቸው ነበር። የቫውዶይስ አገልጋዮች የሚሰለጥኑት ሚሲዮናዊ እንዲሆኑ ነበር፤ ወደ አገልግሎት መግባት የሚፈልግ እያንዳንዱ፣ መጀመሪያ ወንጌላዊ ሆኖ ልምድ ማግኘት ነበረበት። የአንድን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የማገልገል ኃላፊነት ከመውሰዱ በፊት በሌላ የሚሲዮናዊ የአገልግሎት ስፍራ ሶስት ዓመት መሥራት ነበረበት። ይህ ከጅማሮው ራስን መካድንና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ አገልግሎት፤ በነዚያ የሰዎችን ነፍስ በሚፈትኑ ዘመናት ለነበረ የፓስተር ሕይወት የሚገጥም መንደርደሪያ ነበር። ወደ ተቀደሰው የሥራ መስክ ገብተው እንዲሰሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወጣቶች ሊሆን ያለውን፣ ወደፊት የሚገጥማቸውን ሲመለከቱ፣ የሚያዩት ምድራዊ ብልጽግናንና ክብርን ሳይሆን የልፋትና አደጋ የሞላበት ሕይወት፣ ምናልባትም የሰማዕትነትን ዕጣ ነበር። ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ እንዳደረገው ሚስዮናውያኑ ሁለት ሁለት ሆነው ለአገልግሎት ይወጡ ነበር። አንድ ወጣት በእድሜና በልምድ ከበሰለ አጋር ጋር ይላክ ነበር፤ ወጣቱም በአጋሩ ምሪት ስር ሆኖ፣ የማሰልጠን ኃላፊነቱ በጎልማሳው ላይ የሚጣል ሲሆን፣ ትዕዛዛቱንም ሁሉ የማክበር ግዴታ በወጣቱ ላይ ነበር። እነዚህ የሥራ ጓደኞች ሁልጊዜ አንድ ላይ አልነበሩም፣ ለጸሎትና ለመመካከር ግን ዘወትር ይገናኙ ነበር፤ ይህም እርስ በርሳቸው በእምነታቸው እንዲጠነክሩ ይረዳቸው ነበር።GCAmh 55.1

    የተልኮአቸው ግብ ምን እንደሆነ ይፋ ቢያደርጉ የጥረቱ ሽንፈት ይረጋገጥ ነበር። በመሆኑም ትክክለኛ ባህርያቸውን በጥንቃቄ ይደብቁ ነበር። እያንዳንዱ አገልጋይ የንግድ ወይም የሙያ እውቀት ነበረው፣ እናም መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በዓለማዊ ማለትም ለመተዳደሪያ በሚሰሩት ሥራ ሽፋን ያከናውኑት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የነጋዴነት ወይም የሱቅ-በደረቴ (እያዞሩ መሸጥ) ሥራ ይመርጡ ነበር። ይይዟቸው የነበሩት እቃዎች እንደ ሃር፣ ዳንቴሎች፣ የከበረ ድንጋይ ፈርጦች ያሉ ተመራጭና ውድ፣ በዚያን ዘመን በቀላሉ የማይገኙ ነገሮችን ስለነበር፣ እንደነዚህ አይነት እቃዎችን ባይዙ ኖሮ መግባት ይከለከሉበት በነበረበት ስፍራ ሁሉ መድረስ ቻሉ። ይህንንም ሲያከናውኑ ከወርቅ፣ ከከበሩ ድንጋዮችም የሚልቀውን ውድ እቃ [ወንጌሉን] እንዴት ማቅረብ ይችሉ ዘንድ ጥበብ እንዲሰጣቸው ልባቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጣ ነበር። በሙሉም ሆነ በከፊል መጽሐፍ ቅዱስን ደብቀው ይይዙና ዕድል ሲገጥማቸውም ወደ እነዚህ ጽሁፎች የደንበኞቻቸውን ትኩረት ይስቡ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ፍላጎታቸው ይነሳሳ ነበር፤ መቀበል ለሚፈልጉም ሁሉ ክፋዩ በደስታ ይተውላቸው ነበር።GCAmh 55.2

    የእነዚህ ሚስዮናዊያን ሥራ የጀመረው በራሳቸው ተራሮች ስር በነበሩ ሜዳዎችና ሸለቆዎች ቢሆንም ርቆ መሰራጨት ግን ቻለ። ልክ እንደ ታላቁ ጌታቸው በባዶ እግራቸው ከርዳዳና መንገድ ያሳደፈው ልብስ ለብሰው በታላላቅ ከተማዎች አለፉ፤ ወደ ሩቅ ሃገራትም ሰርገው ገቡ። በደረሱበት ሁሉ የከበረውን ዘር በተኑ። ባለፉባቸው መንገዶች አብያተ ክርስቲያናት ብቅ ብቅ አሉ፤ የሰማዕታት ደምም የእውነት ምስክር ሆነ። በእነዚህ ታማኝ ሰዎች ጥረት ተሰብስቦ የተከማቸው የተትረፈረፈ ምርት በእግዚአብሔር ቀን የሚገለጥ ይሆናል። በዝምታ ተሸፍኖ የእግዚአብሔር ቃል በክርስቲያኑ ዓለም ተሰራጨ፤ በሰዎች ልጆችና በቤታቸው በደስታ ተቀባይነትን አገኘ።GCAmh 55.3

    ለዋልደንሶች መጽሐፍ ቅዱሳት እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ቀድሞ የፈጸማቸው የታሪክ መዛግብት ወይም የአሁኑ ሃላፊነቶችና ሥራዎች ነጸብራቅ ብቻ አልነበሩም፤ የወደፊቱ ጥፋትና ክብር መግለጫ መዛግብትም ነበሩ። የሁሉ ነገር መቋጫ በጣም ሩቅ እንዳልሆነ ያምኑ ነበር፤ በጸሎትና በእንባ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ በከበረው ቃሉ (ንግግሩ) የበለጠ እየተመሰጡ በመሄድ ሕይወት የሚሰጡትን እውነቶች ለሌሎች ያሳውቁ ዘንድ ያለባቸው ሃላፊነት እየጎላባቸው ይሄድ ነበር። በተቀደሱት ገጾች በግልጽ የተቀመጠውን የድነት እቅድ ተመለከቱ፤ በየሱስም በማመን መጽናናትን፣ ተስፋንና ሰላምን አገኙ። ብርሃኑ መረዳታቸውን ሲጨምርና ልባቸውን በደስታ ሲሞላ በጳጳሳዊ ሥርዓት የስህተት ጨለማ ውስጥ ላሉ ጨረሩ ይደርሳቸው ዘንድ ተመኙ።GCAmh 56.1

    በሊቀ-ጳጳሱና በቀሳውስቱ ምሪት፣ እልፍ አእላፋት ለሰሩት ኃጢአት ይቅርታ ያገኙ ዘንድ አካላቸውን ሲጎዱ፣ በእርባና ቢስ ጥረት ሲደክሙ ተመለከቱ። መልካም ሥራቸው እንደሚያድናቸው እንዲያምኑ ሆነው ሰልጥነው ሁልጊዜም ወደራሳቸው እየተመለከቱ አእምሮአቸው ኃጢአት በወረሰው ሁኔታቸው ውስጥ ተመስጦ ለእግዚአብሔር ቁጣ የተጋለጡ እንደሆኑ በማየት ነፍሳቸውንና አካላቸውን ቢጎዱም እረፍት የላቸውም ነበር። በዚህ ሁኔታ ጥንቁቅ(ህሊናቸውን የሚያዳምጡ) ነፍሳት በጳጳሳዊ አስተምህሮዎች ተተብትበው ነበር። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጥለው ሕይወታቸውን ሙሉ በገዳም ያሳልፉ ነበር። ሁልጊዜ በሚደጋገሙ ጾሞች፣ በርኅራኄ-የለሽ ግርፋት፣ በውድቅት የዝምታ ጸሎቶች፣ በቀዝቃዛ፣ በደነዝና ግዑዝ ድንጋዮች ላይ ለረዥምና አድካሚ ሰዓታት በግንባራቸው ተደፍተው በመስገድ፣ በረጅም የሐይማኖት ጉዞዎች፣ በሚያዋርዱ የንስሐ መግቢያ ቅጣቶችና አስፈሪ ስቅይቶች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የህሊና ሰላም ለማግኘት በከንቱ ይደክሙ ነበር። በኃጢአተኝነት ስሜት ተጨቁነው፣ በእግዚአብሔር የበቀል ቁጣ ተሸብረው፣ ያለ አንዲት የብርሐን ፍንጣቂ ወይም ተስፋ የደከመው ተፈጥሮ እጅ እስኪሰጥ ድረስ ዘመናቸውን ሙሉ ተሰቃይተው በመጨረሻ ወደ መቃብር ይወርዱ ነበር።GCAmh 56.2

    ዋልደንሶች ለነዚህ የተራቡ ነፍሳት የሕይወት እንጀራን ይቆርሱላቸው ዘንድ፣ በእግዚአብሔር ተስፋዎች ውስጥ የተካተቱትን የሰላም መልእክቶች ይከፍቱላቸው ዘንድ፣ የመቤዠታቸው ብቸኛ ተስፋ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ ይጠቁሟቸው ዘንድ ይጓጉ ነበር። የእግዚአብሔርን ሕግ ከመተላለፍ የሚመጣን ኃጢአት መልካም ሥራ ሊያስተሰርይ ይችላል የሚለው ትምህርት በሃሰት ላይ የተመሰረት እንደሆነ ያውቁ ነበር። በሰው ችሎታ(መልካም ሥራ) መደገፍ፣ መጠን የለሹን የክርስቶስን ፍቅር ይጋርዳል። ክርስቶስ ለሰው ልጅ ቤዛ የሆነበት ምክንያት የወደቀው ዘር በእግዚአብሔር ፊት ምንም ቢያደርግ ብቁነቱን በራሱ መመስከር ስለማይችል ነው። የተሰቀለውና ከሞት የተነሳው አዳኝ የፈፀመው ሥራ የክርስቲያኑ እምነት መሰረት ነው። በክርስቶስ ላይ ያላት የነፍስ ጥገኝነት፣ እንዲሁም ከርሱ ጋር ያለው ቁርኝቷ እጅና እግር ከአካል ጋር፣ ወይም ቅርንጫፍ ከወይን ግንዱ ጋር እንዳለው ቅርበት ያህል እውን ነው።GCAmh 56.3

    የሊቀ-ጳጳሱና የቀሳውስቱ ትምህርት፣ ሰዎች የእግዚአብሔርን ባህርይ፣ የክርስቶስንም ጭምር፣ የማያፈናፍን፣ ጽልመት የተላበሰ፣ ተስፋ አስቆራጭ፣ አስፈሪና ከልካይ አድርገው እንዲመለከቱት መርቷቸው ነበር። ክርስቶስ ለወደቀው የሰው ዘር ቅንጣት ርኅራኄ እንደሌለው ተደርጎ ተወክሎ፣ የቀሳውስትና የቅዱሳን የማስታረቅ (የሽምግልና) አገልግሎት መጠየቁ ግድ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቦ ነበር። ከነድካማቸው፣ ከነችግራቸውና ከነየኃጢአት ሸክማቸው ወደርሱ ይመጡ ዘንድ እጁን ዘርግቶ ወደሚለምናቸው ወደ ሩኅሩኁና አፍቃሪ አዳኛቸው፣ ወደ የሱስ ያመለክቷቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ቃል ማስተዋል ያገኙ ሰዎች ጽኑ ፍላጎት ነበር። ሰዎች ተስፋዎቹን እንዳያዩ፣ በቀጥታም ወደ እግዚአብሔር መጥተው ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ይቅርታና ሰላም ያገኙ ዘንድ እንዳይችሉ የጋረደበትን፣ ሰይጣን የቆለላቸውን መሰናክሎች ያጸዱ ዘንድ ተመኙ።GCAmh 56.4

    የቫውደይሱ አገልጋይ በጥያቄ ውስጥ ላለ አእምሮ የወንጌሉን የከበሩ እውነቶች በደስታ ይገልጥ ነበር። በጥንቃቄ የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፋይ አውጥቶ ይሰጥ ነበር። ፍርድ ለመስጠት የሚጠባበቅ የበቀል አምላክን ብቻ ለሚያይ፣ እውነትን ማወቅና መፈጸም ለሚፈልግ በኃጢአት ለተመታ ነፍስ፣ ተስፋ መፈንጠቅ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ደስታ ይሰጠው ነበር። ሁልጊዜም በጉልበቱ ተንበርክኮ እንባ ባቀረሩ አይኖች፣ በሚንቀጠቀጡ ከንፈሮች፣ የኃጢአተኛው ብቸኛ ተስፋ የሆኑትን የከበሩ ቃል ኪዳኖች ለወንድሞች ይገልጥ ነበር። በዚህም ሁኔታ የጽድቅ ጸሐይ በልባቸው አብርቶ በጮራው ብርሐን እስኪፈውሳቸው ድረስ፣ በጥልቀት የገባ የጽልመትን ደመና እየጠቀለለ የእውነት ብርሐን ወደ ብዙ የጨለሙ አእምሮዎች ሰርጎ ገባ። አብዛኛውን ጊዜ የተነገረውን በትክክል እንደሰማ ለማረጋገጥ የፈለገ ይመስል አድማጩ እንዲደጋግምለት ይፈልግ ነበር። በተለይም የነዚህ ቃላት ድግግሞሽ በጉጉት ይጠበቅ ነበር፦ “የልጁ የየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል” [1ኛ ዮሐ 1÷7]፤ “ሙሴም እባብ እንደሰቀለ በምድረ በዳ እንዲሁ ይገባዋል የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ እንዳይጠፋ የዘላለም ሕይወት ትሆንለት ዘንድ እንጂ።” [ዮሐ 3÷14-15]።GCAmh 57.1

    የሮምን መጠይቅ በተመለከተ ብዙዎች ከመታለል እንዲተርፉ ተደረጉ። ኃጢአተኛውን ወክሎ በሰዎች ወይም በመላዕክት የሚደረግ የማስታረቅ (የማማለድ) ሥራ እንዴት እርባና ቢስ እንደሆነ ተመለከቱ። እውነተኛው ብርሐን በአእምሮአቸው ወገግ ሲል “ክርስቶስ ካህኔ ነው፤ ደሙ መስዋዕቴ ነው፤ መሰውያው ንስሐ መግቢያዬ ነው” በማለት በደስታ ተናገሩ። “ያለ እምነት [እግዚአብሔርን] ደስ ማሰኘት አይቻልም” [ዕብ 11÷6]፤ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፣ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” [የሐዋ ሥራ 4÷12]፤ የሚሉትን ቃላት እየደጋገሙ ክርስቶስ በፈጸመላቸው ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተደገፉ።GCAmh 57.2

    ውሽንፍር ሲያፈናጥራቸው ለነበሩ፣ ለአንዳንድ ምስኪን ነፍሳት፣ የአዳኙ የፍቅር ዋስትና ከሚችሉት በላይ ሆነባቸው። ያመጣው እፎይታ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የወደቀባቸው የብርሐን ጎርፍ ጠራርጎ ሰማይ ያስገባቸው ይመስሉ ነበር። እጃቸውን በእምነት በክርስቶስ መዳፍ ውስጥ በአደራ አስቀመጡ፤ እግሮቻቸውም በዘመናት ቋጥኝ ላይ ተተከሉ። የሞት ፍርሃት ሁሉ ድራሹ ጠፋ። እንደዚያ በማድረጋቸው፣ የአዳኛቸውን ስም የሚያስከብሩ ከሆነ፣ ወህኒ ቤትና ችቦ ሆኖ መቃጠል ዕጣቸው ይሆን ዘንድ ተመኙ።GCAmh 57.3

    በዚህም ሁኔታ በድብቅ ቦታዎች፣ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰው ብቻ፣ ሌላ ጊዜ ለጥቂት ሰዎች፣ እውነትንና ብርሐንን ለተጠሙ ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ይነበብ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ሁኔታ ሙሉ ሌሊቱ ያልቅ ነበር። የሚያዳምጡት አድናቆትና ግርምት እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የድነትን የምሥራች በውል እስኪጨብጡ ድረስ፣ የሰላም መልእክተኛው አሁንም ቅድምም ማንበቡን ማቆም ይገደድ ነበር። በአብዛኛው እንደዚህ አይነቶቹ ቃላት ይነገሩ ነበር፦ “እግዚአብሔር ስጦታዬን በእርግጥ ይቀበል ይሆን? ፈገግታ ይቸረኝ ይሆንን? ይቅር ይለኝ ይሆንን?” መልሱም ቀጥሎ ይነበብ ነበር፦ “ወደኔ ኑ እላንት ደካሞች ሁሉ ሸክማችሁም የከበደ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” [ማቴ 11÷28]።GCAmh 58.1

    እምነት ተስፋውን ጨበጠ፣ የደስታ ምላሽም ተሰማ፦ “ረጅም ሐይማኖታዊ ጉዞ ከእንግዲህ የለም፤ ወደ ተቀደሱ ስፍራዎች የሚደረግ አስቸጋሪ ጉዞ ቀረ። ከነኃጢአቴና ከነርኩሰቴ፣ ራሴን ሆኜ ወደ የሱስ እመጣለሁ፤ የንስሐን ፀሎት እርሱ አልቀበልም አይልም። ‘ኃጢአትህ ተሰረየችልህ።’ [ማር 2÷5]፤ የእኔ፣ አዎ የእኔም ኃጢአት እንኳ ይቅር ይባላል!”GCAmh 58.2

    የተቀደሰ ሃሴት ልብን ይሞላ ነበር፤ የየሱስም ስም በምስጋናና በውዳሴ ከፍ ከፍ ይል ነበር። እነዚያ በደስታ የፈነደቁ ነፍሳት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ብርሐን ያሰራጩ ነበር፤ በተቻላቸውም መጠን ያገኙትን አዲስ ተሞክሮ ለሌሎች ይደግሙ ነበር፤ ሕያውና እውነተኛ የሆነውን መንገድ እንዳገኙ ይናገሩ ነበር። እውነትን ለሚፈልጉ ነፍሳት ለልብ ቀጥተኛ የሚናገር፣ ልዩና ክቡር ኃይል በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ውስጥ ይሰራ ነበር። የእግዚአብሔር ድምፅ ነበር፣ ለሚሰሙትም ጽኑ እምነትን የያዘ ነበር።GCAmh 58.3

    ከዚያም የእውነት መልዕክተኛው መንገዱን ይሄድ ነበር፣ የትህትና ገጽታው፣ ሃቀኝነቱ፣ ቅንነቱ፣ ጥልቅና የጋለ ስሜቱ ግን የዘውትር መወያያ ጉዳዮች ነበሩ። ብዙውን ጊዜ አድማጮቹ ከየት እንደመጣ፣ ወደ የትም እንደሚሔድ ጠይቀውት አያውቁም። መጀመሪያ በግርምት፣ በኋላም በምስጋናና በደስታ ተሸንፈው ይጠይቁት ዘንድ ሃሳቡ አይመጣላቸውም ነበር። ወደ ቤታቸው አብሯቸው እንዲሄድ ሲለምኑት፣ ሁልጊዜም ከመንጋው የጠፉትን በጎች ይጎበኝ ዘንድ እንዳለው ይነግራቸው ነበር። ከሰማይ የመጣ መልአክ ኖሮ ይሆን? በማለት ይጠይቁ ነበር።GCAmh 58.4

    በብዙ አጋጣሚዎች፣ የእውነት መልእክተኛው እንደገና አልታየም፤ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሄዶ ይሆናል፤ በአንድ በማይታወቅ የጨለማ ወህኒ ቤት እድሜውን እየፈጀ፣ ወይም ስለ እውነት ይመሰክርበት በነበረበት በዚያው ስፍራ አጥንቶቹ እየበሰበሱ ይሆናል። ትቷቸው ያለፋቸው ቃላት ግን ይጠፉ ዘንድ አልቻሉም። በሰዎች ልብ ውስጥ ሥራቸውን እየሰሩ ነበሩ፤ የተባረከው ውጤት ሙሉ በሙሉ የሚታወቀው በፍርድ ቀን ብቻ ይሆናል።GCAmh 58.5

    የዋልደንሶች የወንጌል መልዕክተኞች የሰይጣንን ግዛት እየወረሩ ነበሩ፤ የጨለማ ኃይላትም በበለጠ ንቃት ተቀሰቀሱ። እያንዳንዷ እውነት፣ ወደፊት ለማራመድ የምትደረግ ጥረት ሁሉ በክፋት ልዑል እይታ ውስጥ ነበረች፤ በወኪሎቹም ላይ ፍርሃትን ይቀሰቅስ ነበረ። የእነዚህ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ትሁት አገልጋዮች ጥረት፣ ለአላማቸው ከባድ አደጋ እንደሚያስከትልባቸው ጳጳሳዊ መሪዎች ተገነዘቡት። የእውነት ብርሐን ያለመከልከል፣ ሳይጋረድ እንዲበራ ከተፈቀደለት፣ ሰዎችን ጀቡኖ የያዘውን ከባድ፣ ጥቁር የስህተት ደመና ይጠራርገዋል። ይህም የሰዎችን አእምሮ ወደ እግዚአብሔር ብቻ በመምራት የኋላ ኋላ የሮምን የበላይነት ይደመስሳል።GCAmh 58.6

    የእነዚህ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን እምነት የጠበቁ ሰዎች በሕይወት መኖር የሮምን ክህደት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ቋሚ ምስክር ነበር። እናም እጅግ መሪር ጥላቻንና የማሳደድ መንፈስን አነሳሳ። መጽሐፍ ቅዱሳትን አናስረክብም ማለታቸውም ሮም በዝምታ የምታልፈው ወንጀል አልነበረም። ከምድር ገጽ ልታጠፋቸው ወሰነች። አሁን በተራራማው ቤታቸው እንዳሉ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት እጅግ ከባድና አስፈሪ የኃይማኖት ጦርነት ዘመቻ ተጀመረ፤ ሐይማኖታዊ መርማሪዎች በየስፍራው ተመደቡ፤ ኃጢአት የሌለበት አቤል በነፍሰ ገዳዩ በቃየን ፊት የወደቀበት ትዕይንት ተደጋገመ።GCAmh 59.1

    ለም መሬታቸው በተደጋጋሚ ጠፍ እንዲሆን ተደረገ፣ መኖሪያዎቻቸውና የፀሎት ቤቶቻቸው ፈራረሱ። በአንድ ወቅት የበለጸገው የእርሻ ቦታቸው፣ የየዋህና ታታሪ ሕዝቦች መኖሪያ አሁን ምድረ በዳ ሆነ። የተራበ አውሬ ደም ሲቀምስ የበለጠ ቁጡ እንደሚሆን ሁሉ፣ በሚሰቃዩት ተጠቂዎቻቸው ላይ የነበራቸው የጳጳሳውያኑ ቁጣም እንዲሁ የበለጠ እየገነፈለ ይሄድ ነበር። የንጹህ እምነት ምስክሮች የሆኑት እነዚህ ሰዎች አብዛኛዎቹ በተራሮች መካከል ተሳደዱ፣ በተደበቁባቸው ሸለቆዎች፣ በተጠለሉባቸው ጥቅጥቅ ጫካዎችና ረጃጅም ቋጥኞች ውስጥ ታድነው ተያዙ።GCAmh 59.2

    በእነዚህ በተወገዙ መደቦች ላይ የስነምግባር ክስ ሊቀርብባቸው አልቻለም። ጠላቶቻቸው ጭምር ሰላማዊ ዝምተኞችና ጻድቃን እንደሆኑ መሰከሩላቸው። ከባዱ ወንጀላቸው እንደ ሊቀ-ጳጳሱ ፈቃድ እግዚአብሔርን አለማምለካቸው ነበር። ለዚህም ወንጀል ሰዎች ወይም አጋንንት መፈልሰፍ የቻሉት ውርደት ስድብና ግርፋት ሁሉ ተቆለለባቸው።GCAmh 59.3

    በአንድ ወቅት ሮም የተጠሉትን የኃይማኖት ወገኖች ከምድር ገጽ ለማጥፋት ስትወስን ሊቀ-ጳጳሱ አዋጅ አውጥቶ ነበር [ኢኖሰንት 8ኛ፣ 1487 ዓ.ም]። ይህም አዋጅ ተቃዋሚዎች መናፍቃን እንደሆኑና ሊታረዱ እንደሚገባ የሚያዝ ነበር። የተከሰሱት ሰነፎች፣ አጭበርባሪዎች ወይም ሁከት ፈጣሪዎች ሆነው አይደለም፤ የቅድስናና የአምልኮ አስመሳይ መልክ ይዘው “የእውነተኛውን መንጋ በጎች” አባብለው ያሳምናሉ ተብለው ነው። በመሆኑም ሊቀ-ጳጳሱ ትዕዛዝ ሰጠ፦ “ተንኮለኛና አፀያፊ የሆኑት፣ እርጉማን” እምነታቸውን ለመካድ እምቢ ካሉ፣ “እንደ መርዛማ እባቦች ይጨፍለቁ” አለ።- Wylie b. 16. Ch . 1። ይህ ፈላጭ ቆራጭ መሪ እነዚያ አባባሎች ወደፊት ይገናኙኛል ብሎ ጠብቆ ይሆን? በሰማይ መጻሕፍት እንደተመዘገቡ፣ በፍርድ ቀንም ፊት ለፊት እንደሚገጥሙት ያውቅ ኖሮ ይሆን? “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት”፣ አለ የሱስ፣ “ለእኔ አደረጋችሁት።” [ማቴ 25÷40]።GCAmh 59.4

    ይህ አዋጅ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባላት በመናፍቃን ላይ እንዲነሱ ጥሪ ያደረገ ነበር። ለዚህ የጭካኔ ሥራቸው ማበረታቻ ይሆን ዘንድ ለሚሳተፉት ሁሉ አዋጁ “ከቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ ከሚመጣ ጉዳትና ቅጣት በነቂስም ቢሆን በአጠቃላይ ነጻ እንዲሆኑ ፈቀደ። ጦርነቱን የሚቀላቀሉ ሁሉ ከገቡት ቃለ መሃላ ነጻ እንዲሆኑ አደረገ። በህገ ወጥ መንገድ ያገኙትን ንብረት ህጋዊ አደረገላቸው፤ መናፍቅ ቢገድሉ እንኳ ኃጢአታቸው ሁሉ ይቅር እንደሚባልላቸው ቃል ተገባላቸው። ቫውደይሶችን በመደገፍ የተገቡ ስምምነቶችን ሁሉ ሻረ፤ የቤት ሠራተኞቻቸው ትተዋቸው እንዲሄዱ ትዕዛዝ አሰጠ፤ ማንም ሰው ማንኛውንም እርዳታ እንዳያደርግላቸው ከለከለ፣ ንብረታቸውን የመውሰድና የራሱ የማድረግ መብት ለማናቸውም ሰው ሰጠ።”- Wylie b. 16. Ch. 1። ከድርጊቱ በስተጀርባ የነበረው አቀናባሪ ማን እንደነበር ይህ መዝገብ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በዚያ ይሰማ የነበረው የዘንዶው ጩኸት እንጂ የክርስቶስ ድምጽ አልነበረም።GCAmh 59.5

    ጳጳሳዊ መሪዎች ባህርያቸውን ከታላቁ የእግዚአብሔር ሕግ ደረጃ ጋር ያስማሙ ዘንድ አልፈለጉም፤ ነገር ግን እነርሱ የሚስማማቸውን ደረጃ(መስፈርት) ተክለው የሮም ፍላጎት ስለሆነ ብቻ ሌላው እነርሱን አሜን ብሎ እንዲቀበል ያስገድዱ ነበር። እጅግ አስከፊና አሳዛኝ የሆኑ ድርጊቶች ተፈጻሚ ሆኑ። ብልሹና እግዚአብሔርንም የናቁ ካህናትና ጳጳሳት፣ ይፈጽሙ ዘንድ ሰይጣን ያዘዛቸውን ሥራ ያከናውኑ ነበር። በተፈጥሮአቸው (በውስጣቸው) ምሕረት የሚባል ነገር አልነበረም። ክርስቶስን የሰቀለው፣ ሐዋርያትን ያረደው ተመሳሳይ መንፈስ፣ ደም የጠማውን ኔሮን በዘመኑ አንቀሳቅሶ ታማኞችን ያስጨረሰው ያው ራሱ፣ የእግዚአብሔር ውዶች ከምድረ ገጽ ይጠፉ ዘንድ በሥራ ላይ ነበረ።GCAmh 60.1

    እነዚህ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሕዝቦች ለብዙ መቶ ዓመታት የዘለቀውን፣ የሚፈጸምባቸውን ስደትና ግድያ፣ አዳኛቸውን ባስከበረ አይበገሬነትና ትዕግስት ተቋቁመው አልፈዋል። ጦርነት ቢታወጅባቸውም፣ ኢ-ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ቢታረዱም፣ እውነትን ያሰራጩ ዘንድ ሚስዮናውያኖቻቸውን ከመላክ አልቦዘኑም ነበር። ታድነው ይገደሉ ነበር፤ ሆኖም ደማቸው የተዘራውን ዘር አጠጣ፤ ምርትም ከመስጠት አልሰነፈም። በዚህ ሁኔታ ሉተር ከመወለዱ ከምዕተ ዓመታት በፊት ዋልደንሶች ለእግዚአብሔር ምስክሮች ሆኑ። በዋይክሊፍ የጀመረውን፣ በስፋትና በጥልቀት በሉተር ዘመን የቀጠለውን፣ ብሎም “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ የሱስ ምስክር” [ራዕ 1÷9] ሲሉ ሁሉንም ስቃይ ለመሸከም በሚፈቅዱ ሁሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚቀጥለውን የተሐድሶ ዘር በብዙ ሃገራት ተበትነው ዘሩ።GCAmh 60.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents