Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፳—ታላቅ ኃይማኖታዊ መነቃቃት

    የክርስቶስ በቅርብ መምጣት በሚታወጅበት ጊዜ ታላቅ ኃይማኖታዊ መነቃቃት እንደሚኖር በመጀመሪያው መልአክ መልእክት በራዕይ 14 ትንቢት ተነግሯል፦ “በምድር ለሚኖሩ ለሕዝብ ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ” መልአክ ሲበር ይታያል። “በታላቅ ድምጽም” መልእክቱን አወጀ፦ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፣ ሰማይንና ምድርንም ባህርንም የውኃውንም ምንጮች ለሰራው ስገዱለት አለ።” [ራዕይ 14÷6-7]።GCAmh 259.1

    የዚህ ማስጠንቀቂያ አዋጅ ነጋሪ መልአክ ነው የመባሉ ጭብጥ በጣም አስፈላጊ ነው። በመልእክቱ አማካኝነት ሊፈፀም ያለውን ከፍ ያለ የሥራ ባህርይና አብሮት የሚሆነውንም ኃይልና ክብር በትክክል ለመወከል መለኮታዊ ጥበብ በሰማያዊ መልዕክተኛ ንጽህና፣ ክብርና ስልጣን መጠቀም ፈለገ [እግዚአብሔር ከፍተኛ ክብር ያለውን መልአክ መጠቀሙ ሊሰራ ያለው ሥራም ምን ያህል ክቡር እንደሆነ ለማሳየት ስለፈለገ ነው]። የመልአኩ “በሰማይ መካከል” መብረር፣ ማስጠንቀቂያው የተነገረበት “ታላቅ ድምጽ” “በምድር ለሚኖሩ” ሁሉ መታወጁ፣ “ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም” መነገሩ፣ እንቅስቃሴው በፍጥነት የሚከናወንና ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው ማስረጃ የሚሰጥ ነው።GCAmh 259.2

    ይህ እንቅስቃሴ መቼ እንደሚሆን መልእክቱ ራሱ የሚያመላክት ነው። “የዘላለሙ ወንጌል” አካል መሆኑን የሚናገር ሲሆን ስለ ፍርድ መጀመርም ያውጃል። የድነት መልእክት በሁሉም ዘመናት ሲሰበክ ኖሮአል፤ ይህ መልእክት ግን በመጨረሻዎቹ ቀናት ብቻ የሚታወጅ ወንጌል አካል ነው። ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል የሚለው ቃል ትክክል የሚሆነው ያን ጊዜ ብቻ ነውና። ትንቢታቱ የሚያቀርቡት፣ ወደ ፍርዱ መከፈት የሚያመሩ ተከታታይነት ያላቸውን ክስተቶች ነው። የዳንኤልን መጽሐፍ በተመለከተ ይህ በተለይ እውነት ነው። ነገር ግን ከመጨረሻዎቹ ቀናት ጋር የሚዛመደውን የእርሱን ትንቢት ክፍል እስከ “ፍፃሜ ዘመን ድረስ” እንዲዘጋና እንዲያትም ዳንኤል ተነግሮታል። በእነዚህ ትንቢታት አፈፃፀም መሰረት ወደዚህ ጊዜ እስክንደርስ ድረስ ፍርዱን በተመለከተ የተሠጠው መልእክት አይታወጅም። ሆኖም “በመጨረሻው ዘመን” አለ ነብዩ፣ “ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፤ እውቀትም ይበዛል” [ዳን 12÷4]።GCAmh 259.3

    በእርሱ ዘመን የሚከናወን ነው ብላ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መገለጥ እንዳትጠብቅ ሐዋርያው ጳውሎስ አስጠንቅቋታል። [ያ ቀን ደርሷል ብላችሁ… እንዳትናወጡ] ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና “የኃጢአት ሰው” እርሱም “የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ” ይላል ጳውሎስ “አይደርስምና” [2ኛ ተሰሎ 2÷3]። ከታላቁ ክህደት፣ ከ”ኃጢአት ሰው” የረጅም ዘመን ግዛት በፊት የጌታችን መገለጥ አይጠበቅም። “የአመፅ ምስጢር”፣ “የጥፋት ልጅ” እንዲሁም “ያ ክፉ” ተብሎ በተጨማሪ የተገለፀው [2ኛ ተሰሎ 2÷3፤ 7፣8] ያ “የኃጢአት ሰው” ጳጳሳዊው ሥርዓት ሲሆን በትንቢት አስቀድሞ እንደተነገረውም የበላይነቱን አስጠብቆ ለ1260 ዓመታት የሚቆይ ነበር። ይህ ዘመን በ1798 ዓ.ም አብቅቷል። የክርስቶስ መገለጥ ከዚያ ጊዜ በፊት ሊሆን አይችልም። ጳውሎስ እስከ 1798 ዓ.ም ድረስ ያለውን የክርስቲያን ዘመን በሙሉ በማስጠንቀቂያው አካቶታል። የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት መልእክት የሚታወጀውም ከዚያን ጊዜ በኋላ ባለው ነው።GCAmh 259.4

    እንደዚህ አይነት መልእክት ባለፉት ዘመናት ተነግሮ አያውቅም። እንደተመለከትነውም ጳውሎስ አልሰበከውም፤ የጌታን መምጫ ገና ሊመጣ ያለው፣ በዚያን ጊዜ ገና ብዙ እርቀት ወደ ነበረው፣ ወደ ፊት ወንድሞቹን አመልክቷቸዋል። የተሐድሶ አራማጆች አላወጁትም። ማርቲን ሉተር እርሱ ከነበረበት ዘመን አንስቶ ሶስት መቶ አመት በኋላ የፍርድ ጊዜ እንደሚሆን ነበር የተናገረው። ነገር ግን ከ1798 ዓ.ም ጀምሮ የዳንኤል መጽሐፍ ማህተም ስለተከፈተ፣ የትንቢታቱ እውቀት ጨምሯል፤ ክቡር የሆነውን የፍርድ ጊዜ መልእክትም በማወጅ ጊዜው እንደቀረበ ብዙዎች መስክረዋል።GCAmh 260.1

    በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደነበረው ታላቅ ተሐድሶ ሁሉ የአድቬንት (የዳግም ምጽዓቱ) እንቅስቃሴ በተለያዩ የክርስቲያን ሃገራት በተመሳሳይ ጊዜ ብቅ ብቅ ማለት ጀመረ። በአውሮፓና በአሜሪካ የነበሩ የእምነትና የፀሎት ሰዎች ትንቢታቱን እንዲያጠኑ ተመሩ። በመንፈስ የተፃፈውን መዝገብ ዱካ በመከተልም የሁሉም ነገር ፍጻሜ በደጅ እንደቀረበ አሳማኝ መረጃ አስተዋሉ። በተለያዩ ስፍራዎች፣ ለየብቻቸው የነበሩ የክርስቲያን ስብስቦች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ብቻ የአዳኙ ምፅዓት እንደቀረበ አመኑ።GCAmh 260.2

    የፍርድ ሰዓቱን በተመለከተ ትንቢታት ስለሚጠቁሙት ጊዜ ሚለር ግኝቱን ካብራራ ከሶስት ዓመት በኋላ በ1821 ዓ.ም፣ “የዓለም ሚሲዮናዊ” ዶክተር ዮሴፍ ዎልፍ የጌታን በቅርብ መምጣት መስበክ ጀመረ። ዎልፍ የተወለደው በጀርመን አገር፣ ከዕብራዊያን ወላጆች ሲሆን፣ አባቱ የአይሁድ መምህር ነበር። የክርስቲያን ኃይማኖት እውነት እንደነበረ የገባው ገና ወጣት እያለ ነበር። የተሰጡ [ኃይማኖተኛ] ዕብራውያን በየቀኑ እየተሰበሰቡ ሕዝባቸው ወደፊት የሚጠብቋቸውን ተስፋዎች፣ የሚመጣውን መሲህ ክብርና የእሥራኤልን መልሶ መገንባት ለማውራት በአባቱ ቤት ሲሰባሰቡ፣ ንቁና መጠየቅ የሚያበዛ አእምሮ የነበረው ወልፍ በጉጉት ያዳምጣቸው ነበር። አንድ ቀን የናዝሬቱ የሱስ ሲነሳ ሲሰማ ማን እንደሆነ ጠየቀ። “ተወዳዳሪ የሌለው ክህሎት ያለው ሰው” የሚል ነበር መልሱ፤ “ግን መሲሁን ለመምሰል ስለሞከረ የአይሁድ ፍርድ ቤት ሞት ፈረደበት።” “እንደዚያ ከሆነ ታዲያ” አለ ጠያቂው “የሩሳሌም ለምን ጠፋች፣ ለምንድን ነው በባርነት ያለነው? ወይኔ! ወይኔ! አለ አባቱ “አይሁዶች ነብያትን ስለገደሉ ነዋ!” አለው። ለልጁ የጠቀመው ሃሳብ፣ “ምናልባት የናዝሬቱ የሱስም ነብይ ኖሮ ይሆናል፤ እናም ጥፋት ባይኖርበትም አይሁዳዊያን ገደሉት።” የሚለው ነበር።-Travels and Adventures of the Rev. Joseph Wolff, vol. 1, ገጽ 6። ይህ ሃሳቡ እጅግ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ፣ የክርስቲያን ቤተ መቅደስ ውስጥ መግባት የተከለከለ ቢሆንም በውጭ ተጠግቶ ስብከቱን ያዳምጥ ነበር።GCAmh 260.3

    ገና ሰባት ዓመት እያለ ለአንድ በእድሜ ለገፋ ጎረቤቱ መሲሁ ሲመጣ ስለሚሆነው ስለወደፊቱ የእሥራኤል ድል ሲነግረው ሳለ ሽማግሌው መልሶ በትህትና፣ “ውድ ልጅ ትክክለኛው መሲህ ማን እንደነበረ እነግርሃለሁ፦ ልክ የጥንት ነብያትን እንዳረዱ ሁሉ የጥንት አያቶችህ የሰቀሉት የናዝሬቱ የሱስ ነው። ወደ ቤትህ ሂድና የኢሳይያስን ሃምሳ ሶስተኛ ምዕራፍ አንብብ፤ የሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ትረዳለህ” አለው።-Ibid., vol. 1, ገጽ 7። በአንድ ጊዜ ጽኑ እምነት ያዘው። ወደ ቤቱ ሂዶ ጥቅሱን አነበበው፤ በናዝሬቱ የሱስ በኩል ትንቢቱ እንዴት በትክክል እንደተፈፀመ እየተገረመ አነበበው። የክርስቲያኑ ንግግር እውነት ይኖረው ይሆን? ልጁ ትንቢቱን እንዲያብራራለት አባቱን ጠየቀው። ነገር ግን አባቱ የሰጠው የዝምታ ኮስታራ መልስ ስለ ጉዳዩ ሁለተኛ እንዳያወራ አደረገው። ይህ ሁኔታ ግን የክርስቲያንን ኃይማኖት የማወቅ ፍላጎቱን የበለጠ ጨመረው እንጂ አልገታውም።GCAmh 260.4

    ለማወቅ የሚመኘው እውቀት ከአይሁድ ቤቱ ሆን ተብሎ እንዳያገኘው ተደርጓል፤ ሆኖም ገና በአሥራ አንድ ዓመቱ የአባቱን ቤት ጥሎ ወጣ፤ ለራሱ የሚሆነውን ትምህርት ለመማር፣ እምነቱንና የሕይወት ዘመን ሥራውን ለመምረጥ ወደ ዓለም ወጣ። ለተወሰነ ጊዜ ከዘመዶቹ መጠጋት ቢችልም፣ ብዙም ሳይቆይ ከሃዲ ነህ ተብሎ ተባረረ። በብቸኝነት፣ ምንም ነገር ሳይኖረው በወዘ ልውጦች መካከል ለመኖር ተገደደ። በንቃት እያጠናና፣ ዕብራይስጥኛ በማስተማር ከሚያገኘው ገቢ ኑሮውን እየገፋ ከቦታ ቦታ ይዘዋወር ነበር። በአንድ የካቶሊክ መምህር ተጽዕኖ፣ የካቶሊክን እምነት እንዲቀበል ተመራ፤ ለራሱ ሕዝቦች ሚስዮናዊ ለመሆንም እቅድ አወጣ። ይህንን አላማ ይዞ ጥናቱን ለመቀጠል ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሮም ወደሚገኘው የፕሮፓጋንዳ ኮሌጅ አመራ። በዚህ ሥፍራ በራሱ ሃሳብ የመመራት ልምዱና ሃቀኛ ንግግሩ መናፍቅነት እንዲላከክበት አደረገው። ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽመውን ብልሹ አሰራር በግልጽ በመንቀፍ ተሐድሶ አስፈላጊ እንደሆነ ግፊት አደረገ። መጀመሪያ አካባቢ በጳጳሳዊ ልዑካኑ በኩል የተለየ ሞገስ ያገኘ ቢሆንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ከሮም እንዲወገድ ተደረገ። በሮማዊነት ቀንበር ስር መደረግ ፈጽሞ እንደማይችል በግልጽ እስኪረጋገጥ ድረስ ቤተ ክርስቲያንዋ እየተከታተለችው ከቦታ ቦታ ይዘዋወር ነበር። መስተካከል የማይችል ነው ተብሎ ከታወጀ በኋላ ወደሚፈልገው እንዲሄድ ተተወ። በዚህ ጊዜ ወደ እንግሊዝ አገር በመጓዝ የፕሮቴስታንት እምነትን በመቀበል የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን ተቀላቀለ። ለሁለት ዓመት ካጠና በኋላ በ1821 ዓ.ም ተልዕኮውን ጀመረ።GCAmh 261.1

    የክርስቶስ የመጀመሪያ ምፅዓት “የህመም ሰው ደዌንም የሚያውቅ” ሆኖ እንደነበረ የሚገጸውን ታላቅ እውነት ወልፍ ተቀብሎ እንዲሁ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ዳግም ምፅዓቱ በኃይልና በክብር እንደሚሆን ትንቢታቱ እንደሚናገሩ አስተዋለ። የናዝሬቱ የሱስ ይመጣ ዘንድ ተስፋ የተገባ እንደሆነ፣ ለሰዎች ኃጢአት መስዋዕት ይሆን ዘንድ በመዋረድ እንደመጣ ሲያመላክታቸው ሳለ ንጉሥና ተቤዢ ሆኖ እንደገና እንደሚመጣም ያስተምራቸው ነበር።GCAmh 261.2

    “እጆቹና እግሮቹ የተወጉት፣ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ የህማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ የነበረው፣ በትረ-መንግሥቱ ከይሁዳ፣ የሕግ አውጪነት ኃይሉም ከእግሮቹ መካከል፣ ከተወሰደ በኋላ፤ መጀመሪያ የመጣው” አለ፣ “የናዝሬቱ የሱስ፣ እውነተኛው መሲህ”፣ “በሰማይ ደመና በመላእክት አለቃ መለከት ሁለተኛ ይመጣል”፤ “በደብረ-ዘይት ተራራ ላይም ይቆማል፤ በፍጡራን ላይ ይገዛ ዘንድ ለአዳም ተሰጥቶት የነበረው በቅጣት የተወሰደበት (ራሱ ያጣው) ስልጣን [ዘፍ 1÷26፤ 3÷17] ለየሱስ ይሰጣል።(Joseph Wolff, Researches and Missionary Labors, ገጽ 62) በምድር ሁሉ ላይ ይነግሳል። የፍጥረት ማቃሰትና ሰቆቃ ቀርቶ የምስጋናና የውዳሴ መዝሙሮች ይሰማሉ።” “በአባቱ ክብር ከመላእክት ጋር የሱስ ሲመጣ የሞቱ አማኞች አስቀድመው ይነሳሉ” [1ኛ ተሰሎ 4÷16፤ 1ኛ ቆሮ 15÷23]፤ ይህ እኛ ክርስቲያኖች የመጀመሪያው ትንሳኤ ብለን የምንጠራው ነው። በዚያን ጊዜ የእንስሳት ዓለምም ተፈጥሮውን ይቀይራል [ኢሳ 11÷6-9] ለየሱስም ይገዛል፤ [መዝ 8]። ዓለም አቀፍ ሰላም ይፀናል። ”- Journal of the Rev. Joseph Wolff, ገጽ 378, 379። “ጌታም እንደገና ወደ ምድር ይመለከታል። ‘እነሆ እጅግ መልካም ነው’ ይላል።”-ibid, ገጽ 294።GCAmh 261.3

    የጌታ ምፅዓት ቅርብ እንደሆነ ወልፍ አመነ። የትንቢትን ዘመናት አተረጓጎም ታላቁ ፍፃሜ ይከሰታል ብሎ የሰራው ቀመር ሚለር ካስቀመጠው ጊዜ ስሌት የሚለያየው በጣም ጥቂት በሆኑ ዓመታት ነበር። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት” ግን የሚያውቅ የለም የሚለውን ጥቅስ በማንሳት፣ ስለምፅዓቱ መቅረብ ሰዎች የሚያውቁት ነገር መኖር የለበትም ለሚሉ ወልፍ ሲመልስ “ጌታ ያቺ ቀንና ያቺ ሰዓት መታወቅ የለባትም ብሎአልን? በለስ ቅጠሉ ሲያቆጠቁጥ በጋ እንደቀረበ እንደሚታወቅ ሁሉ ቢያንስ የመምጣቱ ጊዜ እንደቀረበ እናውቅ ዘንድ የዘመኑን ምልክቶች አልሰጠንምን? ነብዩ ዳንኤልን እንድናነብ ብቻ ሳይሆን እንድንረዳው በጥብቅ አሳስቦን ሳለ እኛ ያንን ጊዜ ወይም ዘመን ፈጽሞ ማወቅ የለብንም? በዚያው በዳንኤል መጽሐፍ ቃላቱ እስከ ፍጻሜ ዘመን እንደተዘጉ (በእርሱ ዘመን እንደሆነው)፣ ‘ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ’ (ዘመኑን ስለመጠበቅና ስለማሰላሰል ያለው የእብራዊያን አገላለፅ)፣ ‘እውቀትም (ያንን ዘመን በተመለከተ) ይበዛል።’ [ዳን 12፥4]’ በተጨማሪም ጌታችን እንደዚህ ማለቱ የዘመኑ መቅረብ አይታወቅም ማለቱ ሳይሆን ‘ስለዚያች ቀንና ስለዚያች [እቅጭ] ሰዓት ማንም የሚያውቅ [ሰው]’/knows no man’ የለም ማለቱ ነው። ኖህ መርከቡን እንዳዘጋጀ ሁሉ እኛም ለምፅዓቱ እንዘጋጅ ዘንድ ያነሳሳን፣ በዘመኑ ምልክቶች አማካኝነት በቂ እውቀት እንደሚገኝ እርሱ ይናገራል።”-Wolff, Researches and Missionary Labors, ገጽ 404, 405።GCAmh 262.1

    መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ወይም አሳስቶ በመተርጎም ረገድ በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ስላለው አካሄድ ወልፍ ሲጽፍ፦ “አብላጫው የክርስትና ቤተ ክርስቲያን ክፍል ግልጽ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በፍጥነት አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ቡድሂስቶች መናፍስታዊ አሰራር ተቀይሯል። የወደፊቱ የሰው ልጅ ደስታ በአየር ላይ መንሳፈፍን እንደሚጨምር ያምናሉ፤ እናም አይሁዳዊያን የሚለውን ሲያነቡ አሕዛብ ብለው መረዳት እንዳለባቸው ያስባሉ፤ የሩሳሌም የሚል ሲያነቡ ቤተ ክርስቲያን ብለው ይረዳሉ፣ ምድር የሚል ከሆነ ደግሞ ሰማይ ማለት ይሆናል። የክርስቶስ መምጣት የሚለው ደግሞ የሚስዮናዊ ማህበራት እድገት (መስፋፋት) ማለት መሆን አለበት ይላሉ፤ ወደ ጌታ ቤት ተራራ መውጣት ደግሞ የሚያመለክተው ታላቅ የሜተዲስቶች ስብሰባ ነው ብለው ያምናሉ።”-Journal of the Rev. Joseph Wolff, ገጽ 96።GCAmh 262.2

    ከ1821 እስከ 1845 ዓ.ም ባሉት ሃያ አራት ዓመታት ወልፍ አያሌ ጉዞዎችን አደረገ፤ በአፍሪካ ግብጽንና አቢሲንያን ጎበኘ፤ በእስያ ደግሞ በፍልስጥኤም፣ በሶሪያ፣ በፋርስ፣ በቦክሃራ [የአሁኑ ኡዝበኪስታን]፣ እና በህንድ ተጉዟል። ወደዚያ ሲሄድ ሳለ በቅድስት ሄለና ደሴት በመስበክ አሜሪካንም ጎብኝቷል። በ1837 በነሐሴ ወር ላይ ኒው ዮርክ ደረሰ፤ በዚያች ከተማ ከሰበከ በኋላ በፍላደልፊያና በባልቲሞርም ሰብኮ በመጨረሻ ወደ ዋሽንግተን አመራ። በዚህ ስፍራ እንዲህ አለ፦ “በቀድሞ ፕረዘዳንቱ በጆን ኩይንስ አዳምስ አማካኝነት ወደ አንዱ ምክር ቤት ሃሳቡ ቀርቦ የምክር ቤቱን አዳራሽ ለማስተማር እንድጠቀምበት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ፈቅዶልኝ ሁሉም የምክር ቤት አባላት፣ የቨርጂኒያ ጳጳስ፣ የቤተክህነት መሪዎችና የዋሽንግተን ነዋሪዎች በተገኙበት፣ በዕለተ ቅዳሜ፣ ትምህርቱን አቀረብኩ። ይህ ተመሳሳይ ሞገስ በኒው ጀርሲና በፔንሲልቫኒያ አስተዳደር አካላት ተችሮኝ እነርሱ በተገኙበት በኤስያ ምርምሮቼና በየሱስ ክርስቶስ አካላዊ ግዛት ላይ ትምህርት ሰጠሁ።”-ibid., ገጽ 398, 399።GCAmh 262.3

    ዶ/ር ዎልፍ ያለ ማንኛውም አውሮፓዊ ስልጣን ጥበቃ፣ ብዙ ችግሮችን እየተጋፈጠና ቁጥር ስፍር በሌላቸው አደጋዎች ተከቦ እጅግ አረመኔ በሆኑ አገራት መካከል ተጓዘ። የእግሩ መዳፍ ተገርፎ በርሃብ ተቀጣ፣ እንደባርያ ተሸጠ፤ ሶስት ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈረደበት። በዘራፊዎች ተጠቃ፣ የተወሰኑ ጊዜያትም ከውኃ ጥም ሊሞት ምንም አልቀረውም ነበር። በአንድ ወቅት የነበረው ነገር ሁሉ ተዘርፎ፣ በረዶ ፊቱን እየደበደበው፣ በቅዝቃዜ በረጋው መሬት ላይ በባዶ እግሩ ሲጓዝ እግሩ እየደነዘዘ በመቶ ለሚቆጠሩ ማይሎች እንዲጓዝ ተገድዶ ነበር።GCAmh 263.1

    በጨካኝና ነውጠኛ ነገዶች መካከል መሣሪያ ሳይታጠቅ እንዳይሄድ ማስጠንቀቂያ ሲቀርብለት የጦር መሳሪያ አቅርቦት ማለትም “ፀሎት፣ ጽኑ ፍላጎት ለክርስቶስ፣ በእርዳታው መተማመን” እንዳለው ይናገር ነበር። “ደግሞም” አለ “በልቤ የእግዚአብሔርና የባልንጀራዬ ፍቅር አለኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስም በእጄ ውስጥ ነው።”-W. H. D. Adams, In Perils Oft, ገጽ 192። የዕብራይስጥና የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱሱን በሄደበት ቦታ ሁሉ ይዞ ይሄድ ነበር። በኋላ ካደረጋቸው ጉዞዎቹ ስለ አንዱ ሲናገር፣ “መጽሐፍ ቅዱስን ገልጬ በእጄ ያዝኩት፣ ጉልበቴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳለ፣ ኃይሉም እንደሚያፀናኝ ይሰማኝ ነበር።” ይላል።-Ibid., ገጽ 201።GCAmh 263.2

    የፍርዱ መልእክት ሰው በሚኖርበት ዓለም አብዛኛው ክፍል እስኪሰራጭ ድረስ በእንዲህ ሁኔታ ሥራውን በጽናት ቀጠለ። በአይሁዳዊያን፣ በቱርኮች፣ በፋርሶች [ኢራናዊያን]፣ በሂንዱዎች [ህንዳዊያን] ሌሎች በርካታ ሕዝቦችና ዘሮች መካከል ሆኖ የእግዚአብሔርን ቃል በእነዚህ ቋንቋዎች በተነ፤ በሄደበት ሁሉ፣ እየቀረበ ያለውን የመሲሁን መንግሥት አወጀ።GCAmh 263.3

    በጉዞዎቹ መካከል በቦክሃራ (ኡዝበኪስታን) የጌታን በቅርብ መምጣት አስተምህሮ የያዙ በሩቅ የተገለሉ ሕዝቦችን አገኘ። ስለ የመን አረቦችም ሲናገር፦ “ስለ ክርስቶስ መምጣትና በክብር ስለ መግዛቱ የሚጠቅስ ‘ሲራ’ የሚባል መጽሐፍ እንዳላቸው፣ በ1840 ዓ.ም ታላላቅ ክስተቶች ይኖራሉ ብለው እንደሚጠብቁ” ተናግሯል።-Journal of the Rev. Joseph Wolff, ገጽ 377። “በየመን ከሬካባዊያን ጋር ስድስት ቀን አሳለፍኩ። ወይን አይጠጡም፣ የወይን ዛፍ አይተክሉም፤ ዘርም አይዘሩም፣ የሚኖሩት በድንኳን ውስጥ ነው፤ የሬካብን ልጅ የኢዮናዳብን ቃላት ያሰላስላሉ እንደ ሬካብ ልጆች ሁሉ በሰማይ ደመና የመሲሁን በፍጥነት መገለጥ የሚጠብቁ… ከእነርሱ ጋር የሚኖሩ ከዳን ወገን የሆኑ የእሥራኤል ልጆች ነበሩ።”-Ibid., ገጽ 389።GCAmh 263.4

    በታርታሪ [ከካስፒያን ባህር ኡራል ተራራ እስከ ፓስፊክ ውቅያኖስ ያለው ሰሜናዊ ክፍል] ይህንን እምነት የያዙ እንደነበሩ በሌላ ሚስዮናዊ ታውቋል። አንድ የታርታር ቄስ ክርስቶስ ሁለተኛ የሚመጣው መቼ እንደሆነ ለሚስዮናዊው ጥያቄ አቀረበለት። ሚስዮናዊው ምንም እንደማያውቅ ሲመልስለት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ነኝ እያለ በእንደዚህ ዓይነት ድንቁርና ውስጥ መሆኑ እጅግ አስደንቆት፣ የራሱን እምነት ሲነግረው ሳለ እምነቱ በትንቢት ላይ የተመሠረተ እንደሆነና ክርስቶስ በ1844 ገደማ እንደሚመጣ ነገረው። ከ1826 ዓ.ም ጀምሮ የአድቬንት (የምፅዓቱ) መልእክት በእንግሊዝ አገር መሰበክ ጀመረ። ይህ እንቅስቃሴ እንደ አሜሪካው ግልጽ የሆነ መልክ የያዘ አልነበረም፤ የምፅዓቱ ትክክለኛ ጊዜ እምብዛም አይሰበክም ነበር። ሆኖም የክርስቶስ በኃይልና በክብር መምጣት ታላቅ እውነት በስፋት ይታወጅ ነበር። ይህ የሆነው ለየት ያለ ሃሳብ ባላቸውና በአፈንጋጮች መካከል አልነበረም። እንግሊዛዊው ፀኃፊ ሞውራንት ብሮክ እንደሚለው ሰባት መቶ ያህል የሚሆኑ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን (Church of England) አገልጋዮች በ”መንግሥቱ ወንጌል” ስብከት ተጠምደው ነበር። የጌታ ምፅዓት በ1844 ዓ.ም እንደሚሆን የሚጠቁመው መልእክት በታላቋ ብሪታንያም ይሰጥ ነበር። በአሜሪካ የሚታተሙ የአድቬንት ህትመቶች በስፋት ይሰራጩ ነበር። መጻሕፍትና መጽሄቶች በስፋት ይታተሙ ነበር። በ1842፣ በትውልድ እንግሊዛዊ የነበረውና የአድቬንትን እምነት በአሜሪካ የተቀበለው ሮበርት ዊይንተር የጌታን ምፅዓት ለማወጅ ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ። በሥራው ብዙዎች ተባበሩ፤ የፍርዱ መልእክትም በተለያዩ የእንግሊዝ ስፍራዎች ታወጀ።GCAmh 263.5

    በደቡብ አሜሪካ በአረመኔያዊነትና በቀሳውስት ዓለማዊነት መካከል ስፔናዊው ጀስዊት ላኩንዛ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የክርስቶስን በቶሎ የመመለስ እውነት ተቀበለ። ማስጠንቀቂያውን ለመስጠት በራሱ ተገዶ፣ ነገር ግን የሮማን ነቀፋ ለማምለጥ በማሰብ ራሱን የተለወጠ አይሁድ እንደሆነ አድርጎ “ራቢ ቤን-እሥራኤል” በሚል ስም አቋሙን (እይታዎቹን) አሳተመ። ላኩንዛ በሕይወት የኖረው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቢሆንም መጽሐፉ ግን ወደ ለንደን መጥቶ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ የተተረጎመው በ1825 ዓ.ም ገደማ ነበር። መታተሙ በዳግም ምፅዓቱ ዙሪያ ከወዲሁ እየተቀሰቀሰ የነበረውን ፍላጎት የበለጠ ስር እንዲሰድ አገዘ።GCAmh 264.1

    በጀርመን አገር በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሉተራዊያን ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ተደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህርና ተቺ በነበረው በቤንግል አማካኝነት አስተምህሮው ይሰጥ ነበር። “ኮስታራና ወደ ኃይማኖት ያዘነበለ አዕምሮ የነበረውና ገና በልጅነቱ ያገኘው ስልጠናና ስነ-ሥርዓት ይህን ዝንባሌውን ስር ያሰደደና ያጠናከረለት ቤንግል በተፈጥሮው ወደዚህ ጥናት ያዘነበለ ስለነበር” ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ለስነ-መለኮት ጥናት ራሱን አሳልፎ ሰጠ። “እንደሌሎች፣ ሚዛናዊ የአስተሳሰብ ባህርይ እንዳላቸው ወጣት ወንዶች ሁሉ፣ ከመጀመሪያውም ሆነ ከዚያ በኋላ በኃይማኖት ጉዳይ ከጥርጥርና ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ሲታገል የነበረ ሲሆን ‘ምስኪን ልቡን በመውጋት የወጣትነት ሕይወቱን መሸከም እንዲያቅተው ስላደረጉ በርካታ ቀስቶች’ በስሜት ይናገራል። የወርተምበርግ ካውንስል አባል በመሆን ለኃይማኖት ነፃነት በመታገል በወቅቱ ተመስርታ ከኖረችው ቤተ ክርስቲያን ለመውጣት የሚፈልጉና እንዳይወጡ እንደታሰሩ ለሚሰማቸው ለእነርሱ ከህሊና አንፃር ሚዛናዊ የሆነ ነፃነት ሊሰጣቸው እንደሚገባ” ይገፋፋ ነበር።-Encyclopaedia Britannica, 9th ed., art. “Bengel።” የመርሃ ግብሩ ጥሩ ውጤቶችም በትውልድ ክፍለ ሃገሩ እስካሁን ድረስ ይስተዋላሉ።GCAmh 264.2

    “ምጽዓተ እሁድ” በሚል ርዕስ አንድ ስብከት ከራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ 21 እያዘጋጀ እያለ ነበር፣ ለቤንግል፣ የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ብርሐን ለአዕምሮው የበራለት። የራእይ ትንቢታት ከምንጊዜውም በላይ ቁልጭ ብለው ተገለፁለት። በነብዩ በቀረቡት፣ ግዙፍ አስፈላጊነት ባላቸውና በላቀው የትዕይንቶቹ ክብር እጅግ ተደምሞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ጉዳዩን ከማሰላሰል እንዲገደብ ተገድዶ ነበር። መድረክ ላይ ደግሞ ይህ ጉዳይ ግልጽ በሆነ ትዕይንትና ኃይል ራሱን አቀረበለት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለ ትንቢታቱ በተለይም ስለ ዓለም ጥፋት ለማጥናት በመወሰን ብዙም ሳይቆይ የክርስቶስ ምፅዓት ቅርብ እንደሆነ እንደሚጠቁሙ ተረዳ። የዳግም ምፅዓቱ ጊዜ ይሆናል ብሎ የያዘው ቀን፣ በኋላ በሚለር ከታመነው በጣም ጥቂት ዓመታት ልዩነት የነበረው ነበር።GCAmh 264.3

    የቤንግል ጽሁፎች በክርስትናው ዓለም ሁሉ ተሰራጭተዋል። በትንቢታት ረገድ ያለው እይታ በራሱ አገር በወርተንበርግ በአብዛኛው ተቀባይነት ሲያገኝ በሌሎች የጀርመን ክፍሎችም የተወሰነ ተቀባይነት አግኝቷል። ከሞተም በኋላ የአድቬንት መልክት እንቅስቃሴው ቀጥሎ ጉዳዩ በሌሎች ስፍራዎች ትኩረት መሳብ በጀመረበት በዚያው ጊዜ በጀርመንም ይሰማ ነበር። ቀደም ባለው ጊዜ አማኞች ወደ ሩሲያ በመሄድ መንደሮችን መሰረቱ፤ እስካሁንም ድረስ የክርስቶስ በቶሎ የመምጣቱ እምነት በዚያ አገር ባሉ የጀርመን አብያተ ክርስቲያናት ይታመናል።GCAmh 265.1

    በፈረንሳይና በስዊዘርላንድም ብርሃኑ በርቷል። ፋረልና ካልቪን የተሐድሶውን እውነቶች ባሰራጩበት በጀኔቫ፣ ጋውሰን የዳግም ምፅዓቱን መልእክት ሰበከ። ጋውሰን ተማሪ እያለ በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማገባደጃና በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሁሉንም አውሮፓ እየወረረው የነበረው በእምነት ሳይሆን በምክንያት መመስረት አለበት (rationalism) የሚለው መንፈስ ገጥሞት ነበር። ወደ አገልግሎት ሲገባ የእውነተኛው እምነት እውቀት ያልነበረው ከመሆኑም በላይ ወደ መጠራጠር ያዘነበለ ነበር። ወጣት እያለ ነበር ትንቢት ማጥናት ይወድ የጀመረው፤ “የሮሊንስ ጥንታዊ ታሪክ/Rollin’s Anicient History” የሚለውን ካነበበ በኋላ ትኩረቱ ወደ ዳንኤል ሁለተኛው ምዕራፍ ዞረ፤ ልክ እንደ ታሪክ ፀሐፊው ዘገባ፣ ትንቢቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ ዝንፍ ሳይል፣ እቅጩን መፈፀሙ እጅግ አስገረመው። ወደ መጨረሻ ዓመታት በመጡት አደጋዎች ውስጥ እንደመልህቅ ሆኖ ያገለገለው መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ መሆኑን በዚህ መሰረት ማረጋገጫ አገኘ። በምክንያት በተመሠረተ አስተምህሮ ረክቶ መቀመጥ አልተቻለውም። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ግልጽ ብርሐን በመፈለግ ውስጥ ሆኖ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደማያጠራጥር እምነት ተመራ።GCAmh 265.2

    የትንቢታቱን ምርመራ በመቀጠል የጌታ መምጣት በደጅ እንደሆነ አመነ። በዚህ ታላቅ እውነት ግዝፈትና አስፈላጊነት ተጽዕኖ ስር ሆኖ፣ ወደ ሕዝቡ ለማምጣት ፈለገ፤ ነገር ግን የዳንኤል ትንቢት ምስጢራዊና ሊስተዋል የማይችል ነው የሚለው በአብዛኛዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት እንቅፋት ሆነበት። ከእርሱ በፊት ፋረል ጀኔቫን በወንጌል ለመድረስ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በልጆች ጀምሮ፣ በእነርሱ ምክንያት ወላጆችን ለመድረስ ተስፋ አድርጎ ሥራውን ለመጀመር በመጨረሻ ወሰነ።GCAmh 265.3

    “ይህ እንዲስተዋል ምኞቴ ነው” አለ የዚህን ሥራ አላማውን በኋላ ሲገልጽ፣ “አስፈላጊነቱ ትንሽ ስለሆነ አይደለም፣ በተቃራኒው ታላቅ ዋጋ ስላለው ነው በዚህ ሁኔታ ላቀርበው፣ ለልጆችም ላስተምረው የፈለግሁት። መደመጥ እጅግ ፈልጌ ነበር። ማስተማሬን በጎልማሶች ከጀመርኩ ደግሞ የሚሰማኝ የለም ብዬ ፈርቼ ነበር።” “ስለዚህ ወደ ህፃናት ለመሄድ ወሰንሁ። ልጆችን እሰበስባለሁ፣ ብዛታቸው እየጨመረ ከሄደ፣ የሚሰሙ፣ ደስ የተሰኙ፣ ፍላጎት ያደረባቸው ከሆኑ፣ ከገባቸውና ነጥቡን ማብራራት ከቻሉ፣ ሁለተኛ ስብስብ በቅርቡ እንደሚኖረኝ እርግጠኛ ነኝ፤ በተራቸውም ትልልቅ ሰዎች ቁጭ ብለው ቢያጠኑ ጠቃሚ እንደሆነ ያያሉ። ይህ ሲሆን አላማው ይሳካል።”-L. Gaussen, Daniel the Prophet, vol. 2, Preface።GCAmh 265.4

    ጥረቱ ውጤታማ ነበር፤ ልጆችን ሲያስተምር ሳለ ትልልቅ ሰዎች ለመስማት መምጣት ጀመሩ። የቤተ ክርስቲያኑ ሰገነቶች በሙሉ ጀሮ በሚሰጡ አድማጮች ተሞሉ። በመካከላቸው የተከበሩና የተማሩ፣ ጀኔቫን የሚጎበኙ እንግዶችና የውጪ አገር ሰዎች ነበሩ፤ በመሆኑም መልእክቱ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ተሰራጨ።GCAmh 266.1

    በዚህ ስኬት ተበረታቶ፣ የትንቢት መጻሕፍትን ጥናት በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች መካከል ያበረታታል በሚል ተስፋ ጋውሰን ትምህርቶቹን አሳተመ። “ለልጆች የተሰጠውን ትምህርት ማሳተም” አለ ጋውሰን “የተደበቁ/የማይስተዋሉ ናቸው በሚል የሃሰት ሰበብ እንደዚህ አይነቶቹን መጻሕፍት ቸል ለሚሉ ጎልማሶች፣ ልጆቻቸው ካስተዋሉአቸው እንዴት የተሰወሩ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ በልጆች መናገር ነው። በመንጎቻችን መካከል ተወዳጅ የሆኑትን የትንቢታት እውቀት ለመለገስ” አለ ሲጨምር “ጽኑ ፍላጎት ነበረኝ፤ በእኔ እይታ የጊዜውን አስፈላጊ ጥያቄ የሚመልስ ከዚህ የተሻለ ጥናት በእርግጥ የለም። በደጅ ላለው ከባድ አበሳ ለመዘጋጀትና የሱስ ክርስቶስን በንቃት ለመጠበቅ የምንዘጋጀው በዚህ ነው።”GCAmh 266.2

    በፈረንሳይኛ ቋንቋ ከሚሰብኩ እጅግ ታዋቂና ተወዳጅ ከሆኑት መካከል የነበረ ቢሆንም፣ ጋውሰን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከአገልግሎቱ ታገደ። ዋና ጥፋቱ ነው የተባለውም የለዘበና፣ በእውቀትና በምክንያት የተመሠረተ መመሪያ የሆነውንና እውነተኛ እምነት ፍፁም የለውም ከመባል የደረሰውን የቤተ ክርስቲያኒቱን [የካቶሊክ እምነትን] ማስተማሪያ መጽሐፍ በመጠቀም ፈንታ ለወጣቱ መጽሐፍ ቅዱስን አስተምሯል የሚል ነበር። ከዚያ በኋላ በአንድ የስነ-መለኮት ትምህርት ቤት አስተማሪ በመሆን፣ በእሁድ ቀን ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ ማስተማሪያ መጽሐፍ ሰባኪ (ካቴችስት/catechist) ሆኖ ልጆችን በማስጠናት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራቸው ነበር። በትንቢት ላይ የሰራቸው ሥራዎች መጠነ-ሰፊ ፍላጎት አነሳሱ። (እንደ ፕሮፌሰር ሆኖ) ከሚያስተምርበት ጠረጴዛ ፣ በህትመት እንዲሁም በሚወደው ልጆችን በማስተማር ሥራው፣ ለብዙ አመት በመቀጠል ታላቅ ተጽዕኖ መፍጠር ቻለ፤ የብዙ ሰዎች ትኩረት የጌታ ምፅዓት እንደቀረበ ወደሚያሳየው ወደ ትንቢት ጥናት እንዲዞር በማድረጉ ጥረት ዋና መሳሪያ ሊሆን ችሏል።GCAmh 266.3

    በስካንዲናቪያም የምፅዓት መልእክቱ ታውጆ ሰፊ የሆነ ፍላጎት ተቀጣጥሎ ነበር። ብዙዎች ከግድየለሽ የደህንነት ስሜት በመንቃት፣ ኃጢአታቸውን በመናዘዝና በመተው፣ በክርስቶስ ስም ይቅርታን ለመኑ። ነገር ግን የመንግሥታዊ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች/ካህናት እንቅስቃሴውን ተቃወሙ፤ በተጽዕኖአቸውም ምክንያት መልእክቱን የሰበኩ አንዳንዶች ወደ ወህኒ ቤት ተወረወሩ። በበርካታ ስፍራዎች የጌታን በቅርብ መገለጥ የሚሰብኩ በእንዲህ ሁኔታ ዝም እንዲሉ ሲደረግ፣ በተአምራዊ መንገድ መልእክቱን በልጆች አማካኝነት ሊልክ እግዚአብሔር ወደደ። ከሚጠበቀው እድሜ በታች ስለነበሩ መንግሥት ሊገድባቸው አልቻለም፤ ምንም ሳይደረጉም እንዲናገሩ ተፈቀደላቸው።GCAmh 266.4

    አብዛኛው እንቅስቃሴ በዋናነት በዝቅተኛው መደብ መካከል ነበር። በጉልበት ሰራተኞች ደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ እየተሰባሰቡ ማስጠንቀቂያውን ይሰሙ ነበር። የህፃናት ሰባኪዎችም በአብዛኛው ከደሃ ጎጆዎች የመጡ ነበሩ። የተወሰኑት ልጆች እድሜ ከስድስት እና ከስምንት አመት አይበልጥም ነበር። አዳኙን እንደሚወዱት ሕይወታቸው ሲመሰክር ሳለ፣ የእግዚአብሔርንም ቅዱስ መጠይቆች በመታዘዝ ለመኖር እየሞከሩ ሳለ፣ ማንፀባረቅ የቻሉት ግን በዚያ እድሜ ክልል ያለ ልጅ የሚያሳየውን የተለመደ ብልህነትና ችሎታ ነበር። በሰዎች ፊት ሲቆሙ ግን ከራሳቸው ተፈጥሯዊ ክህሎት በላቀ ተጽዕኖ ስር እንደሚንቀሳቀሱ ግልጽ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ራሱን በመጠቀም፣ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” [ራዕይ 14÷7] እያሉ በከበረ ኃይል የፍርዱን ማስጠንቀቂያ ሲናገሩ የድምጻቸው ቅላፄና የሚናገሩበት አኳኋን ይቀየር ነበር። የስነ ምግባር ብልሹነትንና የባህርይ ልሽቀትን በመኮነን ብቻ ሳይሆን ዓለማዊነትንና ወደኋላ ማፈግፈግን በመንቀፍ እንዲሁም ሊመጣ ካለው ቁጣ ያመልጡ ዘንድ አድማጮቻቸውን በማስጠንቀቅ የሕዝቡን ኃጢአት አወገዙ።GCAmh 266.5

    ሰዎች በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ አዳመጡ፤ የሚወቅሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ለልባቸው ተናገራቸው። ብዙዎች በአዲስና በጥልቅ ፍላጎት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩ ተመሩ፤ ገደብ-የለሾችና ምግባረ ብልሹዎች ተለወጡ፤ ሌሎችም ታማኝነት የጎደለው ተግባራቸውን አቆሙ። ሊደበቅ የማይችል ሥራ ከመሰራቱ የተነሳ የመንግሥታዊ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንኳ በእንቅስቃሴው ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለበት እውቅና ለመስጠት ተገደው ነበር።GCAmh 267.1

    የአዳኙ መምጣት የምሥራች በስካንዲናቪያን አገራት ይሰማ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ የአገልጋዮቹ ድምፆች ዝም እንዲል ሲደረግ ሥራው ይከናወን ዘንድ መንፈሱን በልጆች ላይ አደረገ። ደስታ በተሞሉ እልፍ አዕላፋት፣ ዘንባባ እያወዛወዙ የድል ጩኸት እያሰሙ የዳዊት ልጅ መሆኑን በሚናገሩ ሰዎች ተከቦ የሱስ ወደ የሩሳሌም በቀረበ ጊዜ ቀናተኛ ፈሪሳዊያኑ ዝም እንዲያሰኛቸው ነገሩት፤ ክርስቶስም ይህ ሁሉ የትንቢት ፍፃሜ መሆኑን በመመለስ፣ እነዚህ ሰዎች ዝም ቢሉ እንኳ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው። የካህናትንና የአለቆችን ዛቻ በመፍራት ወደ የሩሳሌም በሮች ይገቡ የነበሩት ሕዝቦች በደስታ የተሞላ አዋጃቸውን ከመናገር ቢቆጠቡም በቤተ መቅደስ ሰገነቶች የነበሩት ህፃናት አዝማቹ ከቆመበት በመቀጠል ዘንባባቸውን እያወዛወዙ “ሆሳዕና የዳዊት ልጅ” [ማቴ 21÷8-16] እያሉ ይጮኹ ነበር። ፈሪሳዊያኑ በጣም ተቆጥተው “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” ባሉት ጊዜ “ከህፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። በመጀመሪያው ምፅዓት እግዚአብሔር በልጆች እንደሰራ ሁሉ የዳግም ምፅዓቱን መልእክትም በልጆች በኩል አከናወነ። የእግዚአብሔር ቃል መፈፀም አለበት፤ የአዳኙ መምጣት አዋጅ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋም መነገር አለበት።GCAmh 267.2

    ማስጠንቀቂያው በአሜሪካ ይነገር ዘንድ ኃላፊነቱ ለዊሊያም ሚለርና ለግብረ አበሮቹ ተሰጠ። ይህች አገር የታላቁ የአድቬንት (የምፅዓቱ መልእክት) እንቅስቃሴ እምብርት ሆነች። የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ትንቢት እጅግ ቀጥተኛ የሆነ ፍፃሜ ያገኘው እዚህ ነው። የሚለርና ጓደኞቹ ጽሁፎች ወደ ሩቅ ስፍራዎች ተሰራጩ። ሚስዮናዊያን መድረስ የቻሉበት የዓለም ክፍል ሁሉ የክርስቶስ በቶሎ መመለስ መልካም ዜናዎች ተበተኑ። “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” የሚለው የዘላለሙ ወንጌል መልእክት በስፋትና በርቀት ተሰራጨ።GCAmh 267.3

    ክርስቶስ በ1844 ዓ.ም ፀደይ ወቅት እንደሚመጣ የሚያመለክቱ የሚመስሉት የትንቢታቱ ምስክርነቶች በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ሰርገው ገብተው ነበር። መልእክቱ ከክፍለ ሀገር ወደ ክፍለ ሀገር (state to state) ሲሰራጭ በሁሉም ስፍራ መነቃቃትና መጠነ ሰፊ ፍላጎት ይንፀባረቅ ነበር። በትንቢት ዘመናት የቀረቡት መከራከሪያዎች እውነት እንደሆኑ በማመን፣ የአመለካከታቸውን ኩራት በመሰዋት እውነትን በደስታ ተቀበሉ። አንዳንድ አገልጋዮች የተለየ አመለካከታቸውንና ስሜታቸውን ወደ ጎን በመተው፣ ደመወዛቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን በመተው የየሱስን መምጣት ለማወጅ ወገኑ። ሆኖም በአንፃሩ ይህንን መልእክት የሚቀበሉ አገልጋዮች ብዙ አልነበሩም። እናም ሥራው በአብዛኛው ያረፈው በምስኪን ምዕመናን ነበር። ገበሬዎች እርሻቸውን፣መካኒኮች መሳሪያዎቻቸውን፣ ነጋዴዎች ሸቀጦቻቸውን፣ የተማሩ ሰዎች ደግሞ ሥራቸውን ተው፤ ያም ሆኖ ሊሰራ ካለው ሥራ ጋር ሲነፃፀር የሰራተኞች ቁጥር ጥቂት ነበር። እግዚአብሔርን መሰልነት ያጣች ቤተ ክርስቲያን ሁኔታና በኃጢአት የተዘፈቀው ዓለም የእውነተኛ ጠባቂዎችን ልቦች በሸክም አቅመደመዱት፤ እናም ሰዎችን ወደ ንስሐ ብሎም ወደ ድነት ለመጥራት ሲሉ በፈቃደኛነት ፍጋትን፣ ችጋርንና መከራን ቻሉ። በሰይጣን ተቃውሞ ቢገጥመውም ሥራው በቀጣይነት ወደፊት ተራምዶ የምፅዓቱ እውነትም በበርካታ ሺዎች ተቀባይነትን አገኘ።GCAmh 268.1

    ዓለማዊያንም ሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባላት፣ ከሚመጣው ቁጣ እንዲያመልጡ ኃጢአተኞችን እያስጠነቀቀ የሚሰረስረው ምስክርነት በሁሉም ስፍራ ተሰማ። የክርስቶስ መቅድም እንደነበረው መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሰባኪዎች መጥረቢያውን በዛፉ ስር አስቀምጠው ለንስሐ የሚገባ ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ሁሉንም አስገነዘቡ [ማቴ 3÷8]። የሚቀሰቅሰው ልመናቸው በሕዝባዊ መድረኮች ላይ ከሚሰሙት የሰላምና የደህንነት ማረጋገጫዎች ጋር ቁልጭ ያለ ልዩነት ነበረው፤ መልእክቱ በተሰጠበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቡን ይቀሰቅስ ነበር። ቀላልና ቀጥተኛ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት ይስተዋል ዘንድ በመደረጉ ያመጣው የጥፋተኝነት ስሜት ሸክም ሙሉ ለሙሉ ሊቋቋሙት የቻሉ አልነበሩም ማለት ይቻላል። የኃይማኖት ለፋፊዎች ከሐሰተኛ የደህንነት ስሜታቸው እንዲነቁ ሆኑ። ወደ ኋላ መንሸራተታቸውን፣ ዓለማዊነታቸውንና እምነት ማጣታቸውን፣ ትዕቢታቸውንና ራስ ወዳድነታቸውን ተመለከቱ። ብዙዎች በንስሐና ራስን በማዋረድ እግዚአብሔርን ፈለጉት። ለረጅም ጊዜ በዓለማዊ ነገሮች ላይ ተጣብቀው የነበሩት ፍላጎቶቻቸው አሁን በሰማይ ላይ አረፉ። የእግዚአብሔር መንፈስ አረፈባቸው፤ በለሰለሰና በተደቆሰ ልብ ሆነው “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” የሚለውን ጩኸት ለማሰማት አበሩ። [ራዕይ 14÷7]።GCAmh 268.2

    ኃጢአተኞች እያለቀሱ “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” [የሐዋ ሥራ 16÷30] ይሉ ነበር። በእምነት አጉዳይነት ሕይወት ውስጥ የነበሩ እነርሱ ካሳ ለመመለስ በሽብር ተራወጡ። በክርስቶስ ሰላም ያገኙ ሁሉ፣ ሌሎችም የዚህ በረከት ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ተመኙ። የወላጆች ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችም ልብ ወደ ወላጆች ተመለሰ። የኩራትና የመገለል ግድግዳዎች ተጠራርገው ሄዱ። ልባዊ ፀፀቶች ተደረጉ፤ የቤተሰቡ አባላትም በቅርበት ያሉ እጅግ የሚወዷቸው መዳንን ያገኙ ዘንድ ለፉ። ልባዊ የምልጃ ፀሎት ድምፆችን መስማት የተለመደ ነበር። እግዚአብሔርን በመለመን በሁሉም ስፍራ ነፍሳት በመቃተት ውስጥ ነበሩ። ብዙዎች፣ ኃጢአታቸው ይቅር መባሉን እርግጠኛ ለመሆን ወይም ለዘመዶቻቸው ወይም ለጎረቤቶቻቸው መለወጥ ሲሉ ሌሊቱን በሙሉ ይፀልዩ ይቃትቱ ነበር።GCAmh 268.3

    ሁሉም የሕብረተሰብ መደቦች ወደ አድቬንቲስት ስብሰባዎች ይጎርፉ ነበር። ከተለያዩ ሁኔታዎች የመጡ፣ ሃብታሞች፣ ድሆች፣ የተከበሩና ምስኪኖች ሁሉ የዳግም ምፅዓት አስተምህሮን ራሳቸው በቀጥታ ለመስማት በፍርሃት ይመጡ ነበር። አገልጋዮቹ የእምነታቸውን ምክንያቶች በሚያስረዱበት ጊዜ እግዚአብሔር የመቃወምን መንፈስ ገደበ። አንዳንድ ጊዜ መሳሪያው ልፍስፍስ ቢሆንም የእግዚአብሔር መንፈስ ግን ለእውነቱ ኃይል ለገሰ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የቅዱሳን መላእክት መገኘት ይታወቅ ነበር፤ በየቀኑም አዳዲስ ነፍሳት ወደ አማኞች ተጨመሩ። የክርስቶስ በቅርብ መምጣት ማስረጃዎች ሲደጋገሙ፣ ሕዝብ በብዛት እየተሰበሰበ የከበሩትን ቃላት ትንፋሽ በሌለው ፀጥታ ያዳምጡ ነበር። ሰማይና ምድር የተቀራረቡ መሰሉ። ሽማግሌ ሆነ ወጣት ወይም ጎልማሳ፣ የእግዚአብሔር ኃይል በእነርሱ ላይ ታወቀች። ምስጋና በከንፈራቸው ላይ ሆና ሰዎች ወደ ቤታቸው ይሄዱ ነበር። ፀጥ ባለው የሌሊት አየር የደስታ ደወል ያቃጭል ነበር። እነዚያን ስብሰባዎች የተካፈለ ማንም ሰው የነበረውን የጥልቅ ፍላጎት ትዕይንት ፈጽሞ ሊረሳው አይችልም።GCAmh 269.1

    ክርስቶስ የሚመጣበት ጊዜ በትክክል ይታወቃል የሚለው አዋጅ፣ በመድረክ ከሚሰብከው አገልጋይ ጀምሮ እስከ ግድ የለሽ፣ ሰማይን ተገዳዳሪ ኃጢአተኛ ድረስ በሁሉም መደቦች ታላቅ ተቃውሞን አስነሳ። የትንቢት ቃል ፍጻሜን አገኘ፦ “በመጨረሻው ዘመን በራሳቸው እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ ይህነን በፊት [አስቀድማችሁ] እወቁ። እነርሱም የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው አባቶች ከሞቱበት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራል ይላሉ” [2ኛ ጴጥ 3÷3-4]። አዳኙን እንደሚወዱ የሚናገሩ ብዙዎች በዳግም ምፅዓቱ አስተምህሮ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው ተናገሩ፤ ያልተስማሙት መቼ እንደሆነ በታወቀው የመምጫው ጊዜ ነበር። ሁሉን የሚያይ አምላክ ግን ልባቸውን አነበበ። ዓለምን በጽድቅ ሊፈርድ ክርስቶስ እንደሚመጣ የመስማት ፍላጎት አልነበራቸውም። እምነት የጎደላቸው ባሪያዎች ነበሩ፤ ልብን የሚመረምረውን አምላክ ፍተሻ የሚያልፍ ሥራ አልነበራቸውም፤ ጌታቸውንም ለመገናኘት ፈሩ። በክርስቶስ የመጀመሪያ ምፅዓት እንደነበሩት አይሁዳዊያን የሱስን ይቀበሉ ዘንድ የተዘጋጁ አልነበሩም። የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ መከራከሪያ ለመስማት ካለመፈለጋቸው በተጨማሪ ጌታን የሚፈልጉትን ያላግጡባቸው ነበር። ሰይጣንና መላእክቱ ተፍነከነኩ፤ በክርስቶስና በቅዱሳን መላእክት ፊት ስላቃቸውን በመሰንዘር እንደሚወዱት የሚናገሩት ሕዝቦቹ ለእርሱ ያላቸው ፍቅር ጭላጭ ከመሆኑ የተነሳ መገለፁን እንደማይፈልጉት በአሽሙር ተናገሩ።GCAmh 269.2

    “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን….የሚያውቅ የለም” የሚለው ጥቅስ የአድቬንትን (የምፅዓቱን) እምነት በማይቀበሉ ዘንድ የሚጠቀስ መከራከሪያ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ፦ “ያንን ቀን ግን ያችንም ሰዓት ማንም አያውቃትም’ የሰማይ መላእክት ስንኳ’ ካንዱ ካባቴ በቀር’” [ማቴ 24÷36] ይላል። የዚህ ጥቅስ ግልጽና የሚስማማ ማብራሪያ ጌታን በሚፈልጉ የተሰጠ ሲሆን ተቃዋሚዎቻቸው እንዴት በተሳሳተ መንገድ እንደሚጠቀሙበትም በግልጽ ታይቷል። እነዚህ ቃላት የተነገሩት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ፣ ከቤተ መቅደሱ ለመጨረሻ ጊዜ ከተለየ በኋላ፣ ከትውስታ በማይጠፋው ውይይታቸው ላይ ነበር ክርስቶስ የተናገራቸው። ደቀ መዛሙርቱ “ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር [ማቴ 24÷3፣33፣42-51]። የሱስ ምልክት ሰጣቸውና “እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ” [ማቴ 24÷3፣33፣42-51] አላቸው። አዳኙ የሚናገረው አንዱ ነገር ሌላኛውን ለማጥፋት ጥቅም ላይ መዋል የለበትም። የሚመጣበትን ቀን ወይም ሰዓት ማንም ሰው ባያውቅም እንደቀረበ ግን እናውቅ ዘንድ ተምረናል፣ ታዘናልም። በተጨማሪም ማስጠንቀቂያው እንደሌለ መቁጠርና የመምጫው ጊዜ መቼ እንደቀረበ ለማወቅ እምቢ ማለት ወይም ቸል ማለት፣ የጥፋት ውኃው መቼ እንደሚመጣ እንዳላወቁት በኖህ ዘመን እንደነበሩ ሰዎች አደገኛ እንደሆነም ተምረናል። በዚያው ምዕራፍ ያለው ምሳሌ ታማኝና እምነት የጎደለውን ባሪያ በማነፃፀር፣ “በልቡ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል” በሚለው ባሪያ ላይ የሚመጣውን ጥፋት መግለፁ የሚያሳየው በንቃት እየተጠባበቁት ስለመምጣቱም እየሰበኩ የሚያገኛቸውንና የሚክዱትን በምን ሁኔታ እንደሚያያቸውና ዋጋቸውንም እንደሚሰጣቸው የሚገልጽ ነው። “እንግዲህ ንቁ” ይላል “ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ ብፁዕ ነው” [ማቴ 24÷3፣33፣42-51]። “እንግዲያስ ባትነቃ እንደሌባ እመጣብሃለሁ በማንኛውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።” [ራዕይ 3÷3]።GCAmh 269.3

    የጌታ መገለጥ በድንገት ስለሚሆንባቸው መደቦች ጳውሎስ ይናገራል፦ “የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ… ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” አዳኙ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለሰሙት ሲጨምርም፦ “እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም። ሁላችሁ የብርሐን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም።” (1ኛ ተሰሎ 5÷2-5)።GCAmh 270.1

    እናም ስለ ክርስቶስ ምፅዓት መቅረብ ሰዎች በድንቁርና እንዲቀመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ፈቃድ እንደማይሰጥ ታይቷል። እውነትን ላለመቀበል ሰበብ ብቻ የሚፈልጉ እነርሱ ግን ለዚህ ማብራሪያ ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ፤ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን የሚያውቅ [ሰው] የለም” የሚለው ቃል በደፋር አሿፊዎች፣ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ በሚለው ሳይቀር ማስተጋባቱን ቀጠለ። ሰዎች ሲነቃቁና የመዳንን መንገድ መጠየቅ ሲጀምሩ፣ በሐሰት መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል በመተርጎም ፍራቻቸውን ዝም ለማሰኘት በማሰብ ኃይማኖታዊ አስተማሪዎች በሰዎቹና በእውነት መካከል ተሳጉ። ያልታመኑ ጠባቆች ከታላቁ አታላይ ሥራ ጋር በማበር፣ እግዚአብሔር ስለ ሰላም ሳይናገር፣ ሰላም፣ ሰላም እያሉ ያንባርቁ ነበር። በክርስቶስ ዘመን እንደነበሩት ፈሪሳዊያን ሁሉ፣ ብዙዎች ወደ ሰማይ መንግሥት ለመግባት እምቢ አሉ፤ የሚገቡትንም አሰናከሉ። የእነዚህ ነፍሳት ደም ከእጃቸው ይጠየቃል።GCAmh 270.2

    አብዛኛውን ጊዜ፣ መልእክቱን በመቀበል ረገድ የመጀመሪያ የሚሆኑት በአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ እጅግ ትሁት የሆኑና የተሰጡ ሰዎች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስን ራሳቸው ያጠኑ፣ በብዙዎች ተቀባይነት ያለው አመለካከት እንዴት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ባህርይ ያለው መሆኑን ማየት ሊሳናቸው አልቻለም፤ ሕዝቡ በቤተክህነት መሪዎች ተጽዕኖ ቁጥጥር ስር ባልሆነበት ስፍራ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በራሳቸው መመርመር በቻሉበት ስፍራ፣ መለኮታዊ ስልጣኑን ለመመስረት ተቀባይነት ለማግኘት የአድቬንት አስተምህሮ የሚፈልገው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መነፃፀር ብቻ ነበር።GCAmh 270.3

    ብዙዎች በማያምኑ ወንድሞቻቸው ተሳደዱ፤ በቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን ቦታ ለመጠበቅ ሲሉ ስለ ተስፋቸው ዝም ለማለት አንዳንዶች ሲመርጡ፣ ሌሎች ደግሞ በአደራ የተሰጣቸውን እውነት ይደብቁ ዘንድ ለእግዚአብሔር ያላቸው ታማኝነት አላስቻላቸውም። በክርስቶስ መምጣት ያላቸውን እምነት በመግለፃቸው ምክንያት ብቻ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን አባልነት ተገለሉ። የእምነታቸውን ፈተና ለተሸከሙ ሁሉ እነዚህ የነብዩ ቃላት እጅግ ወርቃማ ነበሩ፦ “የጠሉአችሁ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ ወንድሞቻችሁ ደስታችሁን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ።” [ኢሳ 66÷5]።GCAmh 271.1

    የማስጠንቀቂያውን ውጤት የእግዚአብሔር መላእክት በጥልቅ ፍላጎት እየተመለከቱት ነበር። መልእክቱ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በአብዛኛው ተቀባይነት ሲያጣ በሃዘን ይመለሱ ነበር። ሆኖም የአድቬንትን እውነት በተመለከተ ገና ያልተፈተኑ ብዙዎች ነበሩ። ብዙዎች በባሎች፣ በሚስቶች፣ በወላጆች ወይም በልጆች በተሳሳተ መንገድ ተመሩ፤ በአድቬንቲስቶች የሚሰጡትን ትምህርቶች እንደ ሐሰት (የመናፍቅ ትምህርትነት) በመቁጠር ማዳመጥ እንኳ ኃጢአት እንደሆነ እንዲያምኑ ተደረጉ። ገና የሚመጣ ሌላ ብርሐን ከእግዚአብሔር ዙፋን ሊያበራ ነበረውና እነዚህን ነፍሳት በታማኝነት እንዲጠብቁ መላእክት ታዘዙ።GCAmh 271.2

    መልእክቱን የተቀበሉ እነርሱ የአዳኛቸውን መምጣት መነገር በማይችል ጥልቅ ፍላጎት ይጠባበቁ ነበር። እንገናኘዋለን ብለው የጠበቁበት ሰዓት ደረሰ። በእርጋታና በዝምታ ወደዚህ ሰዓት ቀረቡ። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የእነርሱ በሚሆነው እውነተኛ ሰላም፣ በእግዚአብሔር ጣፋጭ አብሮነት አረፉ። ይህንን ተስፋና እምነት የተለማመደ ማንም እነዚያን ወርቃማ መጠበቂያ ሰዓታት ሊረሳቸው አይችልም። ይመጣበታል ከተባለው ጊዜ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ ዓለማዊ ሥራ በአብዛኛው ቆሞ ነበር። በሞት አፋፍ አልጋቸው ላይ ሆነው ከእንግዲህ ዓለማዊ ነገሮችን ላያዩ ዓይናቸው ለሁልጊዜው እንደሚከደን ያህል እየተሰማቸው እውነተኛ አማኞች እያንዳንዱን የልባቸውን ሃሳብና ስሜት በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር። “የማረጊያ መጎናፀፊያ” የሚሰራ ባይኖርም [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 4ን ይመልከቱ] አዳኙን ለመገናኘት እንደተዘጋጁ የሚያሳይ (ውስጣዊ) መረጃ ሊኖር እንደሚገባ ግን ሁሉም ይሰማቸው ነበር። ነጭ ልብሶቻቸው የነፍሳቸው ንጽህና ነበረች - በሚያነፃው በክርስቶስ ደም ከኃጢአት የታጠበች ባህርያቸው። የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች ሲያደርጉት የነበረውን የልብ ምርመራና እውነተኛ፣ ቁርጠኛ እምነታቸውን ቢቀጥሉበት እንዴት መልካም ነበር። በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ማዋረዳቸውን ቢቀጥሉበት በስርየት መክደኛውም ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡ አሁን ካላቸው ተሞክሮ ይልቅ ሰፊና ጥልቅ የልምምድ ባለቤት ይሆኑ ነበር። ፀሎት የለም፣ እውነተኛ የኃጢአት ፀፀት የለም፣ የሕያው እምነት መታጣትም ብዙዎች በአዳኛችን በገፍ ከቀረበው ፀጋ ደሃ ሆነዋል።GCAmh 271.3

    ሕዝቦቹ እክክለኛ መሆናቸው ይረጋገጥ ዘንድ እግዚአብሔር እቅድ ነበረው። የትንቢት ዘመናት ሲሰሉ የተሰራውን ስህተት እጁ ሸፈነች። [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 3ን ይመልከቱ]። አድቬንቲስቶቹ ስህተቱን አላወቁትም፤ ከተቃዋሚዎቻቸው እጅግ ተምረዋል በሚባሉትም አልተደረሰበትም። የተማሩ ተቃዋሚዎች “የትንቢት ዘመናትን ያሰላችሁበት ስሌት ትክክል ነው። አንድ የሆነ ታላቅ ክስተት ሊከናወን ነው፤ አቶ ሚለር የሚተነብየው ግን አይደለም፤ ዓለም የሚለወጥበት ነው እንጂ የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት አይደለም” ይሉ ነበር። [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 5ን ይመልከቱ]።GCAmh 271.4

    የተጠበቀው ጊዜ አለፈ፤ ሕዝቦቹን ይታደግ ዘንድ ክርስቶስ አልመጣም። በእውነተኛ እምነትና ፍቅር አዳኛቸውን የጠበቁ እነርሱ መሪር ቅሬታ ደረሰባቸው። ሆኖም የእግዚአብሔር አላማዎች እየተፈፀሙ ነበር። መገለጡን እየጠበቅን ነው ብለው የመሰከሩትን የእነርሱን ልብ እየፈተነ ነበር። ከመካከላቸው ከፍርሃት የተሻለ ያነሳሳቸው ነገር የሌላቸው ብዙዎች ነበሩ። እንደሚያምኑ መመስከራቸው ልባቸውን ወይም ሕይወታቸውን አልነካውም ነበር። የተጠበቀው ክስተት ሳይፈፀም ሲቀር፣ እነዚህ ሰዎች በሁኔታው ቅር እንዳልተሰኙ ተናገሩ፤ ከበፊቱም ክርስቶስ ይመጣል ብለው ፈጽመው አላመኑም ነበር። በእውነተኛ አማኞች መሪር ሃዘን ከተሳለቁት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ነበሩ።GCAmh 272.1

    የሱስና የሰማይ ሰራዊት ግን የተፈተኑትን፣ ታማኝም የሆኑትን፣ ሆኖም ቅሬታ የገጠማቸውን ሕዝቦች በፍቅርና በርኅራኄ ተመለከቷቸው። የሚታየውን ዓለም ከማይታየው የሚለየው መጋረጃ ቢገለጥ መላእክት ወደነዚህ የማይነቃነቁ ነፍሳት ሲቀርቡ፣ ከሰይጣን ፍላጻም ሲከልሏቸው ይታዩ ነበር።GCAmh 272.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents