Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

ታላቁ ተጋድሎ

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ፲፩—የልዑላን ተቃውሞ

    ተሐድሶውን በመደገፍ ከተነገሩት ምስክርነቶች መካከል እጅግ የከበሩ ከሆኑት አንዱ በክርስቲያን ጀርመናዊ ልዑላን በ1529 ዓ.ም በስፓይረስ በነበረው ጉባኤ የተነገረው ተቃውሞ ነበር። የእነዚያ የእግዚአብሔር ሰዎች ጀግንነት፣ እምነትና አይበገሬነት ወደፊት ለሚመጡት ዘመናት የአስተሳሰብና የህሊና ነፃነትን ያጎናጸፈ ነበር። የእነርሱ ተቃውሞ ለታደሰችው ቤተ-ክርስቲያን ፕሮቴስታንት (ተቃዋሚ) የሚል ስያሜ አሰጣት፤ መርሆዎችዋም የፕሮቴስታንታዊነት ዋና መሰረት (ፍሬ ነገር) ናቸው።GCAmh 146.1

    ለተሐድሶው የጨለማና የአደጋ ቀን ያንዣበበት ወቅት ነበር። ሉተር ህገ-ወጥ እንደሆነ የታወጀበት የዎርምስ አዋጅ እንዲሁም አስተምህሮውን ማስተማርም ሆነ አምኖ መቀበል የተከለከለ ቢሆንም የኃይማኖት መቻቻል እስከዚህ ጊዜ ድረስ በግዛቱ በስፋት ነበር። የእግዚአብሔር ምሪት እውነቱን የሚቃወሙትን ኃይላት ገድቦአቸው ነበር። ቻርለስ 5ኛ ተሐድሶውን ለማውደም ቆርጦ ቢነሳም ለመምታት እጁን ባነሳ ቁጥር ውሳኔውን ለመቀልበስ ይገደድ ነበር። በተደጋጋሚ ሮምን የተቃወሙ ሁሉ ፈጽመው መጥፋታቸው አይቀሬ በሚመስልበት፣ በዚያ አጣብቂኝ ሰዓት የቱርክ ወራሪዎች በምሥራቃዊው ድንበር ብቅ ይላሉ፤ የፈረንሳይ ንጉሥ፣ ሌላ ጊዜም [በጀርመኑ]ንጉሠ ነገሥት ስልጣን መግነን ቅናት የሚይዘው ሊቀ-ጳጳስ ራሱ በጀርመን ላይ ጦርነት ያውጀበት ነበር። በዚህ ድንግርግር የመንግሥታት ፀብ መሃል ተሐድሶው ወደ ጎን ስለሚተው ይጠናከርና ይስፋፋ ነበር።GCAmh 146.2

    ሆኖም በመጨረሻ ጳጳሳዊ ግዛቶች ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ በጋራ ሆነው ተሐድሶውን ለመቃወም አደሙ። የሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስ በ1526 ዓ.ም የተደረገው የስፓይረስ ጉባኤ የኃይማኖት ጉዳዮችን በተመለከተ እያንዳንዱ ራስ-ገዝ ክፍለ-ሃገር የራሱን ውሳኔ እንዲወስን ነፃነት ሰጥቶ ነበር፤ ሆኖም ይህ ችሮታ በመሰጠቱ አደጋው ከማለፉ ንጉሠ-ነገሥቱ በ1529 ዓ.ም ሌላ ጉባኤ ጠራ፤ አላማውም ኑፋቄን ለመደቆስ በማሰብ ነበር። የሚቻል ከሆነ ልዑላኑን በማባበል ወደ ተሐድሶው ተቃዋሚዎች ጎራ እንዲመጡ በሰላም መገፋፋት፣ ይህ ውጤት ካላመጣ ደግሞ ቻርለስ ሰይፍ ለመምዘዝ ተዘጋጅቶ ነበር።GCAmh 146.3

    ጳጳሳውያኑ ፈነደቁ። በስፓርየስ ጉባኤ በአያሌ ቁጥር በመገኘት ለተሐድሶው አራማጆችና ለሚደግፏቸው ሁሉ ያላቸውን ጥላቻ በግልጽ አንጸባረቁ። ሜላክተን፣ “የምድር እዳሪዎና ጥራጊዎች ነን፣ ክርስቶስ ግን ድሃ ሕዝቦቹን ወደ ታች ይመለከታል፤ ይጠብቃቸውማል።” አለ።-Ibid., b. 13, ch. 5። በጉባኤው የተሳተፉት ወንጌልን የተቀበሉት ልዑላን በመኖሪያ ቀያቸው እንኳ ወንጌል እንዳይሰበክ ተከለከሉ። የስፓይረስ ሰዎች ግን ለእግዚአብሔር ቃል ተጠምተው ነበር። የተከለከሉ ቢሆንም በሺዎች የሚቆጠሩ ወደ ሳክሶኒው መራጭ ፀሎት ቤት አገልግሎት ይጎርፉ ነበር።GCAmh 146.4

    ይህ ችግሩን አፋጠነው። የህሊና ነፃነት የቸረው ውሳኔ ከፍተኛ ረብሻን ስላስከተለ ሊወገድ እንደሚገባው ንጉሣዊው መልእክት ለጉባኤው አስታወቀ። ይህ ከስነ-ሥርዓት ውጪ የሆነ አሰራር የክርስትና ተከታዮችን ልዑላን ቁጣ ቀሰቀሰ። አንዱ ሲናገር፣ “ክርስቶስ እንደገና በቀያፋና በጲላጦስ እጅ ወደቀ” አለ። ሮማውያኑ የባሰ ቁጡ እየሆኑ መጡ። አንድ አክራሪ ጳጳሳዊ- “ቱርኮቹ ከሉተራውያን የተሻሉ ናቸው፤ ምክንያቱም ቱርኮቹ የጾም ቀናትን ሲያከብሩ ሉተራውያኖቹ ግን ይጥሷቸዋል። በእግዚአብሔር ቅዱስ መጻሕፍት(በመጽሐፍ ቅዱስ) እና በቤተ ክርስቲያንዋ የቀድሞ ስህተቶች መካከል መምረጥ ካለብን የመጀመሪያውን [መጽሐፍ ቅዱስን] አንቀበልም” በማለት አውጆአል። ሜላክቶን፣ “ፌበርGCAmh 146.5

    ወንጌላውያኑን በመቃወም፣ በጉባኤው ፊት፣ በእያንዳንዱ ቀን አዲስ ድንጋይ ይወረውራል” ብሏል።-Ibid., b. 13, ch. 5።GCAmh 147.1

    የኃይማኖት መቻቻል ህጋዊ መሰረት አግኝቷል፣ በመሆኑም ወንጌላዊያን ራስ ገዝ ክፍለ ሃገራት ያላቸውን ህጋዊ መብት የሚጥሱባቸውን ለመቃወም ቁርጠኞች ነበሩ። በዎርምስ አዋጅ ምክንያት ማዕቀብ ስር የነበረው ሉተር በስፓይረስ እንዲገኝ አልተፈቀደለትም ነበር። ሆኖም በዚህ የአደጋ ጊዜ ቦታውን የሚተኩ ግብረ-አበሮችና ልዑላን ለዓላማው ይቆሙ ዘንድ እግዚአብሔር አስነስቶ ነበር። የቀድሞው የሉተር ጠባቂ፣ የሳክሶኒው ክቡር ሰው ፍሬደሪክ በሞት ቢለይም በቦታው የተተካው ወንድሙ መስፍን ዮሐንስ የተሐድሶ እንቅስቃሴውን በደስታ በመቀበል፣ የሰላም ወዳጅ ሆኖ ሳለ የእምነቱን ጉዳዮች ሁሉ በተመለከተ ጥልቅ ፍላጎትና ጀግንነት ያንፀባርቅ ነበር።GCAmh 147.2

    የተሐድሶውን እንቅስቃሴ የተቀበሉ ራስ ገዝ ክፍለ-ሃገራት ያለምንም ጥያቄ ሙሉ በሙሉ በሮማዊ ሕግ ስር መሆንን እንዲቀበሉ ቀሳውስቱ አዘዙ። ተሐድሶ አድራጊዎቹ ደግሞ ቀደም ብሎ የተሰጠውን ነፃነት አወሱ። በታላቅ ደስታ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበሉትን ክፍለ-ሃገራት ሮም እንደገና በቁጥጥሯ ስር ታደርጋቸው ዘንድ ሊፈቅዱላት አይቻላቸውም።GCAmh 147.3

    በመጨረሻ እንደ አስታራቂ ሃሳብ ሆኖ የቀረበው ተሐድሶው መሰረት ያልጣለባቸው ክፍለ-ሃገራት በዎርምስ የተደነገገውን አዋጅ በጥብቅ እንዲተገብሩ የሚል ነበር፤ ክርስትናን በተቀበሉት ደግሞ የአመጽ አደጋ ባለባቸው ስፍራዎች አዲስ ተሐድሶ እንዳይተዋወቅ፣ በሚያከራክሩ ነጥቦች ላይ ስብከት እንዳይሰበክ፣ የሮማ ካቶሊክ [የቁርባን] ስነ-ሥርዓት ተቃውሞ እንዳይገጥመው፣ እንዲሁም ማንኛውም ካቶሊካዊ ሉተራዊነትን ይቀበል ዘንድ እንዳይፈቀድለት የሚሉ ነበሩ። ለጳጳሳዊ ቀሳውስቱና የቤተ-ክህነት ባለስልጣናት ታላቅ እርካታ ያመጣው ይህ አዋጅ በጉባኤው ፀደቀ።GCAmh 147.4

    ይህ አዋጅ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ተሐድሶው ወዳልደረሰባቸው ቦታዎች መስፋፋትም ሆነ በደረሰባቸው ስፍራዎች ጠንካራ መሰረት መጣል አይችልም። የመናገር ነፃነት ይገፈፋል። መለወጥም (ኃይማኖት መቀየርም) አይፈቀድም። የተሐድሶው ወዳጆችም ለእነዚህ ገደቦችና መከላከያዎች ወዲያውኑ መታዘዝ ይጠበቅባቸው ነበር። የዓለም ተስፋ ሊዳፈን የተቃረበ መሰለ። የጳጳሳዊው ሥርዓተ-አምልኮ እንደገና መመስረት በጥንት የነበሩትን ጉስቁልናዎች እንደሚመልሳቸው ጥርጥር የለውም። በጠብና በአክራሪነት የተናወጠውን ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለማውደምም አጋጣሚ የሚታጣ አይሆንም።-Ibid., b. 13, ch. 5።GCAmh 147.5

    የወንጌላዊ (Evangelical) ፓርቲዎች ለምክክር ሲገናኙ በፍጹም ተስፋ መቁረጥ እርስ በርስ ይተያዩ ነበር። “ምንድን ነው መደረግ ያለበት?” የሚለው ጥያቄ ከአንዱ ወደሌላው ይተላለፍ ነበር። የዓለም ከባድ ጉዳዮች አጣብቂኝ ውስጥ ነበሩ። “የተሐድሶው መሪዎች ይህንን አዋጅ በመቀበል ይታዘዙት? በዚህ ከባድ በሆነ ችግር ውስጥ የተሐድሶ አራማጆቹ እንዴት በቀላሉ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ለመጓዝ ይስማማሉ! እጅ ለመስጠትስ ምን ያህል አሳማኝ ሰበብና ሚዛናዊ ምክንያት ያገኛሉ! የሉተራውያን ልዑላን ሐይማኖታቸውን በነፃነት የማካሄድ መብቱ ነበራቸው። በግዛቶቻቸው ስር ያሉ ከዚህ አዋጅ በፊት ተሐድሶውን የተቀበሉትም እንዲሁ ነፃነት ነበራቸው። ይህ ሊያረካቸው አይገባም? እጅ መስጠት ስንት አደጋን ይታደጋል! ምን አይነት ያልታወቀ አደጋና ተጋድሎ ላይ ነው ተቃውሞ የሚጥላቸው? መጪው ጊዜ ይዞ የሚመጣውን ዕድሎችስ ማን ያውቃል? ሰላምን በደስታ እንቀበል፤ ሮም የዘረጋችውን የወይራ ቅርንጫፍ እንያዝና የጀርመንን ቁስል እንክደነው። እነዚህንና የመሳሰሉትን መከራከሪያዎች በማንሳት፣ የተሐድሶ አራማጆቹ፣ በእርግጥም ብዙም ሳይቆይ ለአላማቸው መገልበጥ ምክንያት የሚሆነውን መንገድ መምረጥ ይችሉ ነበር።GCAmh 148.1

    “ይህ ስምምነት የቆመበትን መርህ በደስታ ተመለከቱ፣ በእምነትም ወደ ተግባር ገቡ። ያ መርህ ምን ነበር? ህሊናን በማስገደድ ነፃ ሆኖ ጥያቄ ማቅረብን መከልከል የሮም መብት ነበር። ነገር ግን ራሳቸውና የፕሮቴስታንት ተገዥዎቻቸው ሐይማኖታዊ ነፃነት ተካፋይ ሊሆኑ አይገባቸውምን? አዎ እንደ በጎ ስጦታ ተደርጎ፣በስምምነቱ ውስጥ ተለይቶ ተጠቅሶ፣ ይፈቀድላቸዋል እንጂ እንደ መብት ሆኖ ግን አይደለም። ከዚህ ስምምነት ውጭ ላሉት ሁሉ ግን ታላቁ የስልጣን መርህ [በበላይነት]መግዛት ነበር። ህሊና ከችሎት ውጪ ነበረ፤ ሮም ልትሳሳት የማትችል ፈራጅ ነበረች፤ ስለሆነም ሁሉም ሊታዘዟት ይገባል። የቀረበውን ሃሳብ መቀበል ማለት ሐይማኖታዊ ነፃነት ለታደሰው የሳክሶኒ ግዛት ብቻ ነው መሰጠት የሚችለው የሚለውን አባባል ከመቀበል የሚተናነስ አይደለም። ለሌላው የክርስትና ዓለም በነፃነት የመጠየቅና የተሐድሶውን እምነት መመስከር ወንጀል በመሆናቸው በወህኒና በቃጠሎ የሚያስቀጡ ይሆናል። ሐይማኖታዊ ነፃነት የአንድ አካባቢ ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ይስማሙ? ተሐድሶው አዲሱን እምነት የተቀበለ የመጨረሻውን አማኝ እንደተረከበ፣ የመጨረሻውን ቀደማ መሬት እንደያዘ ለማወጅ እሺ ይበሉ? በዚህ ሰዓት የበላይነቱን የያዘችው ሮም ስልጣንዋ እንዲቀጥል ይተው? ይህንን ስምምነት ለመተግበር ሲባል በጳጳሳዊ ምድር ሕይወታቸውን ለሚያጡ በመቶዎችና በሺዎች ለሚቆጠሩት ሰዎች የተሐድሶ አራማጆች ከደማቸው ንጹህ ነን ብለው መሙዋገት ይችሉ ነበርን? በዚያ ከባድ ሰዓት ይህንን ማድረግ የወንጌሉን ዓላማና የክርስትናን ነፃነቶች መካድ ይሆናል።” ግዛታቸውን፣ ማዕረጋቸውንና የራሳቸውን ሕይወት ጭምር መሰዋት ይሻላቸዋል።-D’Aubigné, b. 13, ch. 5።GCAmh 148.2

    “ይህንን አዋጅ እንቃወመው” አሉ ልዑላኑ። “ህሊናን በሚመለከቱ ጉዳዮች የአብላጫ ድምጽ ኃይል የለውም።” ምክትሎቹ ሲናገሩ ጀርመን እያጣጣመችው ያለው ሰላም የተገኘው በሐይማኖት ነፃነቱ አዋጅ እንደሆነ፣ ይህንን ማስቀረት ደግሞ ንጉሣዊ ግዛቱን በችግርና በመከፋፈል ውስጥ እንደሚከተው አወጁ። “መማክርቱ እንደገና እስኪሰበሰቡ ድረስ ሐይማኖታዊ ነፃነትን ጠብቆ ከማቆየት በቀር” አሉ “ተጨማሪ ነገር ለመተግበር ጉባኤው ብቁ አይደለም።”-Ibid., b. 13, ch. 5። የህሊና ነፃነትን ማስከበር የሃገሪቱ ሃላፊነት ነው፤ የኃይማኖትን ጉዳዮች በተመለከተ ያላት ስልጣን እዚህ ላይ ያበቃል። ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን ለማስተካከል፣ ወይም በኃይል ለመተግበር የሚሞክር እያንዳንዱ መንግሥታዊ አስተዳደር ክርስቲያኖች በክብር የታገሉለትን መርህ የሚሰዋ ነው።GCAmh 148.3

    ድፍረት የተሞላበት ግትርነት ብለው የሰየሙትን ለማዳፈን ጳጳሳውያኑ ቆረጡ። ተሐድሶውን በሚደግፉ መካከል መከፋፈል እንዲኖር ጣሩ። ተሐድሶውን በግልጽ ያልደገፉትን ሁሉ ደግሞ ማስፈራራት ያዙ። በመጨረሻም ነፃነት ያላቸው ከተሞች ተወካዮች በጉባኤው ፊት ቀርበው በቀረበው ሃሳብ መስማማት አለመስማማታቸውን እንዲናገሩ ተጠየቁ። እንዲዘገይ ቢጠይቁም አልተሳካላቸውም። ሲጠየቁ ግማሽ የሚሆኑት ተሐድሶ አድራጊዎቹን ደገፉ። የህሊና ነፃነትንና በግል የመወሰን መብትን ለመሰዋት ፈቃደኛ ያልሆኑቱ አቋማቸው ለወደፊት ነቀፋ፣ ውግዘትና ስደት እንደሚያበቃቸው ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ከልዑካኑ አንዱ “የእግዚአብሔርን ቃል መካድ ወይም መቃጠል ግድ ይሆንብናል” ብሏል።-Ibid., b. 13, ch. 5። የንጉሠ ነገሥቱ የጉባኤ ወኪል የሆነው ንጉሥ ፈርዲናንድ ልዑላኑ ተገፋፍተው እንዲቀበሉት፣ እንዲጸናም ካላደረጉት በስተቀር በአዋጁ ምክንያት ጠንካራ ክፍፍል እንደሚኖር አስተዋለ። በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ ኃይል መጠቀም የባሰ ግትር እንደሚያደርጋቸው በመገንዘብ የማግባባት ጥበቡን ለመጠቀም ሞከረ። አዋጁን መቀበላቸው ንጉሠ ነገሥቱን እጅግ እንደሚያስደስተው በማረጋገጥ እንዲቀበሉት ለመናቸው። ነገር ግን እነዚህ ታማኝ ሰዎች ከምድራዊ ገዥዎች በላይ ላለ ኃይል እውቅና በመስጠት ረጋ ብለው፣ “ፀጥታን በሚያስጠብቅና እግዚአብሔርን በሚያከብር ነገር ሁሉ ንጉሠ ነገሥቱን ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነን” አሉ።-Ibid., b. 13, ch. 5።GCAmh 149.1

    በጉባኤው ፊት አዋጁ ወደ ንጉሣዊ ትዕዛዝ እንደሚቀየርና እንደሚታተም፣ ለመራጩና ለጓዶቹ የቀረው ብቸኛው አማራጭ ለአብላጫው ድምጽ መታዘዝ እንደሆነ ንጉሡ ተናገረ። ይህንን ካለ በኋላ ለተሐድሶ አራማጆቹ የመወያየት ወይም የመመለስ ዕድል ሳይሰጣቸው ወጥቶ ሄደ። እንዲመለስ መልዕክተኞች ቢልኩም ሳይሳካላቸው ቀረ። ለምሬታቸው የመለሰው፣ “ይህ ያለቀለት ጉዳይ ነው የቀረው ነገር መታዘዝ ብቻ ነው” የሚል ነበር።-Ibid., b. 13, ch. 5።GCAmh 149.2

    ክርስቲያን ልዑላኑ መጽሐፍ ቅዱሳት ከሰው አስተምህሮዎችና መስፈርቶች በላይ እንደሆኑ አድርገው እንደሚመለከቱአቸው የንጉሣዊው አባላት ያወቁት ጉዳይ ነበር። ይህ መርህ ተቀባይነት ባገኘበት ስፍራ ሁሉ የጳጳሳዊ ሥርዓት የኋላ ኋላ መገርሰሱ እንደማይቀርም ያውቁታል። ከእነርሱ ዘመን ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ እንዳደረጉት “የሚታየውን ብቻ” [2ኛ ቆሮ 4÷18] በመመልከት፣ የንጉሠ ነገሥቱና የሊቀ-ጳጳሱ ጉዳይ ጠንካራ፣ የተሐድሶ አድራጊዎቹ ደግሞ ልፍስፍስ እንደሆነ አድርገው ራሳቸውን ይደልሉ ነበር። የተሐድሶ አራማጆቹ በሰው እርዳታ ብቻ ተደግፈው ቢሆን ኖሮ ጳጳሳዊያኑ እንዳሉትም አቅመ-ቢስ በሆኑ ነበር። ሆኖም በቁጥር ጥቂት፣ ከሮምም የማይስማሙ ቢሆኑም፣ እነርሱም ጉልበት ነበራቸው። ከጉባኤው ውሳኔ ይልቅ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከጀርመን ንጉሠ ነገሥት ይልቅ ደግሞ ወደ ሰማይና ምድር ገዢ ይግባኝ አሉ።-Ibid., b. 13, ch. 5።GCAmh 149.3

    በጥንቃቄ የወሰዱትን አቋም ፈርዲናንድ እንዳልተቀበለው ሲያዩ ልዑላኑ የንጉሡን አለመገኘት ከምንም ሳይቆጥሩ ተቃውሞአቸውን ወደ ብሄራዊው ጉባኤ በአፋጣኝ ለማምጣት ወሰኑ። መግለጫ አውጥተውም ለጉባኤው አቀረቡት፦GCAmh 150.1

    “ተቃውሞአችንን እንዲህ እናቀርባለን፣ በብቸኛው ፈጣሪያችን፣ በጠባቂያችን፣ ከኃጢአት ባነፃን፣ በአዳኛችን፣ ወደፊት አንድ ቀን ፈራጃችን በሚሆነው በእግዚአብሔር ፊት፣ እንዲሁም በሰዎች ሁሉ እና በፍጡራን ሁሉ ፊት፣ ከእግዚአብሔር፣ ከእርሱ ቃል፣ ከእኛ የህሊና ነፃነት ወይም ከነፍሳችን ድነት ጋር የሚፃረርን ማንኛውንም አዋጅ፣ በምንም አይነት መልኩ፣ እኛ፣ ለእኛም ሆነ ለሕዝባችን፣ አንስማማበትም፣ አንከተለውምም…. እግዚአብሔር አንድን ሰው ወደ እውቀቱ ሲጠራው የመለኮታዊ እውቀትን አልቀበልም ለማለት መድፈር አለበት ብለን ለመናገር አንችልም…. ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ከሚስማማ በቀር ሌላ እውነተኛ አስተምህሮ የለም። ሌላ እምነት ማስተማርን ጌታችን ይከለክላል። ቀለል ባለው በሌላኛው ጥቅስ መብራራት የሚችሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በቀላሉ መረዳት የሚቻሉ፣ እውቀትም ለመለገስ የተመቻቹ፣ ለክርስቲያኑ በሁሉም ሁኔታዎች የሚያስፈልጉ ናቸው። ስለዚህ ምንም ነገር ሳይጨመርበት በብሉይና በሃዲስ ኪዳን የተካተተውን የእግዚአብሔርን ብቸኛ ቃል ንጹህ ትምህርት ለመጠበቅ በመለኮታዊ ፀጋ ቃል እንገባለን። ይህ ቃል ብቸኛው እውነት ነው፣ የሁሉም አስተምህሮዎች እርግጠኛ መመሪያ ነው፣ ያሳስተን ዘንድም አይቻለውም። በዚህ መሰረት ላይ የሚያንጽ እርሱ የሲኦልን ኃይላት ሁሉ ተቋቁሞ ይቆማል፤ ይቃወሙት ዘንድ የተቋቋሙት ከንቱነቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ይወድቃሉ።” “ስለሆነም የተጫነብንን ቀንበር እንቃወማለን።” “ግርማዊይነቱም ከምንም ነገር በላይ እግዚአብሔርን እንደሚወድ ክርስቲያን ልዑል በመሆን ይመለከተናል ብለን እንጠብቃለን። ትክክለኛና የተገባን ሃላፊነት የሆነውን ፍቅርና መታዘዝ ለእርሱም[ለንጉሡም] ሆነ ለእናንተ ለቸሮቹ ጌቶች እንሰጥ ዘንድ ዝግጁ መሆናችንን እናውጃለን።”-Ibid., b. 13, ch. 5።GCAmh 150.2

    ጥልቅ መገረም በጉባኤው ላይ ተፈጠረ። ከተቃዋሚዎቹ ድፍረት የተነሳ ብዙዎቹ በመደነቅና በድንጋጤ ተዋጡ። የወደፊቱ ጊዜ የመናወጥና የውል-አልባ ዘመን እንደሚሆን ተመለከቱ። ልዩነት፣ ፀብና ደም መፋሰስ ሊያስቀሩት የማይችሉት ክስተት መሰላቸው። ጉዳያቸው ፍትሃዊነት እንዳለው ያረጋገጡት ተሐድሶ አራማጆች ግን በዘላለማዊ ክንድ ተደግፈው በጀግንነት የተሞሉ፣ የማይነቃነቁም ነበሩ።GCAmh 150.3

    ተቃውሞው፣ በነፍስና በእግዚአብሔር መካከል ባሉት ጉዳዮች ላይ ሕግ እንዳያወጡ የመንግሥታዊ ባለስልጣናትን በማገድ፣ ከነብያትና ከሐዋርያት ጋር “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል”[የሐ.ሥራ 5÷29] በማለት አወጀ። የቤተክህነትን ቅጥ ያጣ ስልጣንም በመቃወም፣ የሰው ትምህርቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ቅዱስ መጻሕፍት ቁጥጥር ስር መሆን ይገባቸዋል የሚለውን የማይሳሳተውን መርህ አስቀመጠ። ተቃዋሚዎቹ የፍጡርን የበላይነት ቀንበር አሽቀንጥረው ጥለው ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያኑ፣ ቃሉ ደግሞ በመድረክ የበላይ ገዥ መሆኑን ከፍ አድርገው አሳይተው ነበር። የህሊና ኃይል ከመንግሥት፣ የመፅሐፍ ቅዱስ ስልጣን ከምትታየው ቤተ ክርስቲያን በላይ ከፍ ተደረገ። የክርስቶስ ዘውድ ከሊቀ-ጳጳሱ ቲያራ(የራስ ጌጥ)፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ በልጦ ከፍ ከፍ አለ። በተጨማሪም፣ ተቃዋሚዎቹ እምነታቸውን በነፃነት የመመስከር መብታቸውንም አስረግጠው ተናገሩ። ማመናቸውና መታዘዛቸው ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሚናገረውን እንደሚያስተምሩ፣ ቀሳውስትና የአጥቢያ ዳኞችም ጣልቃ የመግባት መብት የሌላቸው እንደሆኑ ተናገሩ። በስፓይረስ የነበረው ተቃውሞ ሐይማኖታዊ አለመቻቻልን በመንቀፍ፣ እንዲሁም ሁሉም ሰዎች እንደየራሳቸው ህሊና ምሪት እግዚአብሔርን የማምለክ መብት እንዳላቸው በማረጋገጥ ረገድ ታላቅ ምስክር ነበር።GCAmh 150.4

    አዋጁ ታወጀ፤ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ፣ እንዲሁም የሰው ጥረት ሊፍቀው በማይችለው ስፍራ፣ በሰማይ መፃሕፍት ተፃፈ። መላው የጀርመን ክርስቲያን ህብረት ተቃውሞውን የእምነቱ መገለጫ አድርጎ ተቀበለው። በዚህ አዋጅ ውስጥ በሁሉም ስፍራ ያሉ ሰዎች የአዲስና የተሻለ ዘመን ተስፋ ተመለከቱ። ለስፓይረስ ፕሮቴስታንቶች አንድ ልዑል ሲናገር÷ “በኃይል፣ በነፃነትና በድፍረት እንድትመሰክሩ ፀጋ የሰጣችሁ ሁሉን ቻይ አምላክ በዚያ ክርስቲያናዊ ጥንካሬ የዘላለም ቀን እስክትመጣ ድረስ ይጠብቃችሁ።” አለ።-Ibid., b. 13, ch. 6።GCAmh 151.1

    ተሐድሶው የተወሰነ ውጤት ካስመዘገበ በኋላ ከዓለም ጋር ስምምነት ለመፍጠር ተለሳልሶ ቢሆን ኖሮ፣ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለራሱ እውነተኛ ባለመሆን የራሱን ጥፋት ባረጋገጠ ነበር። የነዚያ የተከበሩ የተሐድሶ አራማጆች ልምድ ለሚመጡት ዘመናት የሚለግሰው ትምህርት አለ። እግዚአብሔርንና ቃሉን በመቃወም ሰይጣን የሚሰራበት ዘዴ አሁንም አልተለወጠም። በአሥራ ስድስተኛው ምዕተ አመት እንዳደረገው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት መርህ መሆኑን ዛሬም ይቃወማል። በእኛ ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮና መመሪያ በስፋት ተርቆ ተሄዶአል፤ ወደ ታላቁ የፕሮቴስታንት መርህ መመለስ ያስፈልጋል - እርሱም የምግባርና የእምነት ደንብ መጽሐፍ ቅዱስና፣ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ አድርጎ መቀበል ነው። የኃይማኖትን ነጻነት ለማጥፋት መቆጣጠር በሚችለው በእያንዳንዱ ነገር አማካኝነት ሰይጣን አሁንም ሥራውን እየሠራ ነው። በስፓርየስ የነበሩት ተቃዋሚዎች አንቀበልም ያሉት የክርስትና ተቃዋሚው ኃይል የተነጠቀውን የበላይነት እንደገና ለመመስረት በታደሰ ጉልበት አሁን እየጣረ ነው። የዛሬው ተሐድሶ ብቸኛ ተስፋም በድሮው ተሐድሶ የችግር ዘመን የታየውን የማያወላውል አቋም ይዞ በእግዚአብሔር ቃል ጎን መሰለፍ ነው።GCAmh 151.2

    ለፕሮቴስታንቶቹ የአደጋ ምልክቶች ይታዩ ነበር፣ ታማኞቹን ይጠብቅ ዘንድ መለኮታዊ እጅ እንደተዘረጋም እንዲሁ ምልክቶች ነበሩ። በዚህ ጊዜ ነበር ሜላክቶን ጓደኛውን ግራይኔውስን በስፓይረስ መንገዶች በማጣደፍ ወደ ራይን በመምራት ሳይዘገይ ወንዙን እንዲሻገር የገፋፋው። ግራይኔውስም ለዚህ ድንገተኛ ፍርጥጫ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈለገ። ሜላክቶንም፦ “ረጋና ኮስተር ያለ የማያወላውል ሰው ከፊቴ ቆሞ ‘ግራይኔውስን ለመያዝ በፈርዲናንድ የተላኩ የፍርድ ቤት ሰራተኞች በደቂቃ ውስጥ ይመጣሉ’ አለኝ” በማለት መለሰለት። ወራጁ ውሃ በሚወደው ጓደኛውና ነፍሱን በሚሹአት መካከል እስኪሆን ድረስ ሜላንክቶን በራይን አፋፍ ሆኖ ይጠባበቅ ነበር። በመጨረሻም ተሻግሮ በወንዙ በዚያኛው ማዶ ሲያየው “የንፁህ ደም ከተጠሙ ጨካኝ መንጋጋዎች አመለጠ።” አለ።GCAmh 151.3

    አስቀድሞ ግራይናውስ ከአንድ የታወቀ ጳጳሳዊ ዶክተር ጋር የቅርብ ወዳጅነት ነበረው። ሆኖም ከስብከቶቹ አንዱን ካደመጠ በኋላ በድንጋጤ ወደ እርሱ ሄዶ ከእውነት ጋር መዋጋቱን እንዲያቆም ለመነው። ጳጳሳዊው ዶክተርም ቁጣውን ደብቆ ሳያስታውቅ ሁኔታውን በመንገር ተቃዋሚውን ለመያዝ የሚያስችል ስልጣን አገኘ። ሜላክቶን ከሽኝት ወደ ቤቱ ሲመለስ ግራይናውስን የሚፈልጉ የመንግሥት ሹሞች ቤቱን ከላይ እስከታች እንደፈተሹት ተነገረው። ቅዱሳን መላዕክቱን በመላክና በማስጠንቀቅ ጌታ ጓደኛውን እንዳተረፈው አመነ።GCAmh 151.4

    ተሐድሶው በዓለም ኃያላን ፊት በመቅረብ ወደ በለጠ እውቅና ይደርስ ዘንድ ነበረው። ክርስትናን የተቀበሉ ልዑላን ይግባኛቸው እንዳይሰማ ንጉሥ ፈርዲናንድ ከልክሎ ነበር፤ ሆኖም በንጉሠ ነገሥቱ ፊትና የመንግሥትና የቤተ-ክህነት ታላላቅ ሹማምንት በተገኙበት ጉዳያቸውን ለማቅረብ የሚፈቀድላቸው ጊዜ መጥቶ ነበር። የስፓይረስ ተቃውሞ ከተደረገ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ግዛቱን የረበሸውን ብጥብጥ ለማብረድ በማሰብ ንጉሠ-ነገሥት ቻርለስ 5ኛ በአውግስበርግ ጉባኤ ጠራ፤ በአካል እንደሚገኝም አሳወቀ። የተቃውሞው መሪዎችም ወደዚያ ስፍራ ተጠሩ።GCAmh 152.1

    ተሐድሶው ታላላቅ አደጋዎች ተጋርጠውበት ነበር፤ ጠበቃዎቹ ግን ጉዳያቸውን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥተው ከወንጌሉ ፈቀቅ ላለማለት ወሰኑ። የሳክሰኑ መራጭ በጉባኤው ፊት እንዳይቀርብ አማካሪዎቹ አጥብቀው ገፋፉት። ንጉሡ ሁሉም ልዑላን እንዲገኙ የፈለገበት ምክንያት ወጥመድ ውስጥ ሊያስገባቸው ፈልጎ እንደሆነ ተናገሩ። “ከኃይለኛ ባለጋራ ጋር በከተማው ቅጥሮች ውስጥ ራስን መዝጋት ሁሉን ነገር አደጋ ላይ መጣል አይደለምን? ሌሎች ግን በድፍረት፤ “ልዑላኑ ጀግና ይሁኑ ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር ሥራ ይተርፋል” አሉ። “የኛ አምላክ ታማኝ ነው፤ አይተወንም” አለ ሉተር።-Ibid., b. 14, ch. 2። ከአጃቢዎቹ ጋር ሆኖ መራጩ ወደ አውግስበርግ ጉዞ ጀመረ። የተጋረጡበትን አደጋዎች ሁሉም የሚያውቋቸው ስለነበሩ ፊታቸው ሃዘን ለብሶ፣ ልባቸው ተጨንቃ ወደፊት ገሰገሱ። ሆኖም እስከ ኮበርግ አብሯቸው የተጓዘው ሉተር “አምላካችን ጠንካራ ቅጥር ነው።” የሚለውን የውዳሴ መዝሙር በመዘመር የተንኮታኮተውን እምነታቸውን አነቃቃው። በሚያበረታቱት ዜማዎች ብዙ የአደጋና የፍርሃት ድባቦች ተወገዱ፤ የተጨነቁ ልቦች አረፉ።GCAmh 152.2

    የተለወጡት ልዑላን አቋማቸውን ለመግለጽ የሚሰጡት ቃል በጥንቃቄ እንዲዘጋጅ፣ መረጃውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተወስዶ በጉባኤው ፊት እንዲቀርብ ወስነው ነበር። ይህንን የማዘጋጀቱ ኃላፊነትም በሉተር፣ በሜላክቶንና በአጋሮቻቸው ላይ ተጥሎ ነበር። ይህ የእምነት ቃል ለፕሮቴስታንቶቹ እንደ የእምነታቸው መግለጫ ስለነበር በዚህ አስፈላጊ ሰነድ ላይ ስማቸውን ለማስፈር ተሰበሰቡ። ከባድና ፈታኝ ጊዜ ነበር። አላማቸው በፖለቲካዊ ጥያቄዎች አቅጣጫ በመሳት የሚደናገር እንዳይሆን የተሐድሶ አቀንቃኞቹ ተጨንቀው ነበር። ከእግዚአብሔር ቃል ከሚወጣው በስተቀር ተሐድሶው ሌላ ተጽዕኖ ለመፍጠር መሥራት እንደሌለበት ተሰማቸው። ክርስቲያን የሆኑት ልዑላን የእምነት ቃል ሰነዱን ለመፈረም ሲገሰግሱ ሜላክቶን ጣልቃ በመግባት “እነዚህ ነገሮች ላይ ሃሳብ ማቅረብ ያለባቸው የኃይማኖት ምሁራንና አገልጋዮች ናቸው፤ የምድር ኃያላን ስልጣን ለሌሎች ጉዳዮች ሊቆይ ይገባዋል” አለ። “እግዚአብሔር ይህንን ያርቅ” አለ የሳክሶኒው ዮሐንስ “እኔን ከዚህ ነገር አለማካተት በጭራሽ አይሆንም። ስለ ዘዴው ሳልጨነቅ ሥራዬን አከናውን ዘንድ ቃል ገብቻለሁ። ጌታን እመሰክር ዘንድ ሃሳቤ ነው። የተመራጭነቴ [የማዕረግ]ቆብና አልባሳት የየሱስ ክርስቶስን መስቀል ያህል ለእኔ የከበሩ አይደሉም” አለ። ንግግሩን ሲጨርስ ስሙን ፃፈ። ሌላኛው ልዑል ስሙን ለመፃፍ ብዕር ሲያነሳ፣ “ለአምላኬ ለየሱስ ክርስቶስ ክብር ከሆነ ጥሪቴንና ሕይወቴን ለመተው ዝግጁ ነኝ።” ቀጠለ፦ “በዚህ የእምነት ቃል ከተካተተው ውጪ ሌላ አስተምህሮ ከምቀበል በስሬ ያሉትን ተገዥዎችና ግዛቶቼን ብተው፣ ያባቶቼን አገርና የእጅ በትር ብተው እመርጣለሁ።” አለ።-Ibid., b. 14, ch. 6። የእነዚያ የእግዚአብሔር ሰዎች እምነትና ድፍረት ይህን ይመስል ነበር።GCAmh 152.3

    በንጉሠ ነገሥቱ ፊት የመቅረቢያው ሰዓት ደረሰ። ቻርለስ 5ኛ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ በመራጮችና በልዑላን ተከቦ ለፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች መድረኩን ሰጠ። የእምነታቸው ቃል ተነበበ። በዚህ ግርማ ሞገስ በተላበሰ ጉባኤ ፊት የወንጌሉ እውነቶች ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተነገሩ፣ የጳጳሳዊ ቤተ ክርስቲያንዋ ስህተቶችም ተጠቀሱ። ያ ቀን “የተሐድሶው ታላቅ ቀን፣ በክርስትናና በዓለም ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው” በመባል ተነግሮለታል።-Ibid., b. 14, ch. 7።GCAmh 153.1

    ነገር ግን የዊተንበርጉ መነኩሴ በዎርምስ በብሄራዊው መማክርት ፊት ብቻውን ከቆመ ጥቂት ዓመታት አልፈው ነበር። አሁን በርሱ ፋንታ በግዛቱ እጅግ የተከበሩና ኃያል ልዑላን ቆሙ። ሉተር በአውግስበርግ እንዲገኝ ባይፈቀድለትም በቃልና በፀሎቱ ግን እዛው ነበር። “በደስታ እፈነድቃለሁ” አለ “በተከበረ ጉባኤ ፊት እነዚህን በመሰሉ በድንቅ ምስክሮች ዘንድ ክርስቶስ በአደባባይ ከፍ ከፍ ሲል ለማየት እስከዚህች ሰዓት በመቆየቴ በደስታ እፈነድቃለሁ፤ ‘በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ’ [መዝ 119÷46] የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተፈፀመ” አለ።-Ibid., b. 14, ch. 7።GCAmh 153.2

    በጳውሎስ ዘመን ለእስር የተዳረገው ወንጌል በልዑላንና በተከበሩ ሰዎች ፊት በንጉሣዊቷ ከተማ ቀርቦ ነበር። በዚህም ክስተት “ንጉሠ ነገሥቱ በመድረክ እንዳይነገር የከለከለው ወንጌል በቤተ መንግሥቱ ታወጀ፣ አገልጋዮች እንኳ ይሰሙት ዘንድ ያልተገባ ብለው ብዙዎች የፈረጁት በግዛቱ ሹማምንቶችና ጌቶች ዘንድ በግርምት ተደመጠ። ታዳሚዎቹ ነገሥታትና ኃያል ሰዎች፣ ሰባኪዎቹም ዘውድ የደፉ ልዑላን፣ ስብከቱ ደግሞ ንጉሣዊው የእግዚአብሔር እውነት ነበረ።” “ከሐዋርያት ዘመን በኋላ” አለ አንድ ፀሐፊ “ከዚህ የተሻለ ሥራ ወይም የደመቀ የየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት የለም።”-D’Aubigné, b. 14, ch. 7።GCAmh 153.3

    “ሉተራውያኑ ያሉት ሁሉ እውነት ነው። ልንክደውም አንችልም” አለ አንድ ጳጳሳዊ። “በመራጩና በግብረ አበሮቹ የተሰጠውን የእምነት ቃል፣ በሚያሳምን ምክንያት፣ እውነት አለመሆኑን ማረጋገጥ ይቻልሃልን?” በማለት ሌላኛውን ዶክተር ኦክን ጠየቀ፣ “ሐዋርያትና ነብያት በፃፉት ጽሁፍ ይህን መመለስ አይቻልም” ነበር መልሱ፤ “በአባቶችና በመማክርቱ (በጉባኤዎቹ) ግን እችላለሁ።” “የተረዳሁት” አለ ጠያቂው ሲመልስ “ሉተራውያኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ምሽግ ውስጥ ናቸው፣ እኛ ከውጭ ነን።”-Ibid., b. 14, ch. 8። የተወሰኑት የጀርመን ልዑላን ተሐድሶውን ተቀላቀሉ። ንጉሠ ነገሥቱ ራሱ የፕሮቴስታንቶቹ ጽሁፎች እውነት እንደሆኑ ተናገረ። የእምነታቸው ቃል በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በመላው አውሮፓ ተሰራጨ። የእምነታቸው መገለጫ ተደርጎም በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎችና ቀጣይ ትውልዶች ተቀባይነትን አገኘ።GCAmh 153.4

    የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች ብቻቸውን አልለፉም። “ከአለቆችና ከስልጣናት ከሰማያዊም ስፍራ ያለ የክፋት መንፈሳዊያን” [ኤፌ 6÷12] ተባብረው ቢቃወሙአቸውም እግዚአብሔር ግን ሕዝቦቹን አልጣለም። ዓይናቸው ቢከፈትና ቢያዩ ኖሮ ለጥንቱ ነብይ እንደተደረገለት ሁሉ የመለኮትን መገኘት ማረጋገጫ በተመለከቱ ነበር። አገልጋዩ ለኤልሳዕ እየከበባቸው ያለውን ሰራዊት ሲያመላክተው ማምለጫውንም ሁሉ ሲዘጉት ነብዩ፣ “አቤቱ ያይ ዘንድ አይኖቹን እባክህ ግለጥ ብሎ ፀለየ” [2ኛ ነገስት 6÷17] እነሆ ተራራው በእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተሞልቶ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ሰው ይጠብቅ ዘንድ የሰማይ ጭፍራ ሰፍሮ ነበረ። እንዲሁም መላዕክት የተሐድሶውን እንቅስቃሴ ይጠብቁ ነበር።GCAmh 153.5

    ሉተር ውልፍት ሳይል ከጠበቃቸው መርሆዎች አንዱ ተሐድሶውን ለመደገፍ ወደ መንግሥታዊ ስልጣን፣ ጥቃት ለመከላከልም ጠመንጃ ወደ ማንሳት፣ ማምራት የለብንም የሚለው ነበር። የግዛቱ ልዑላን ራሳቸው ወንጌልን መመስከራቸው አስፈንድቆታል፤ ሆኖም ተቀናጅተን በአንድነት እንከላከል የሚል ሃሳብ ሲያቀርቡ ግን “የወንጌሉ አስተምህሮ ሊጠበቅ የሚገባው በእግዚአብሔር ብቻ ነው። በሥራው ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች በቀነሰ ቁጥር እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ የሚያከናውነው ተግባር የበለጠ አንፀባራቂ እየሆነ ይሔዳል። በእርሱ እይታ ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው የተሰነዘሩት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ዋጋ ከሌለው ፍርሃትና ኃጢአት ከሚሆን አለመተማመን የዘለለ ትርጉም አልነበራቸውም።”-D’Aubigné, London ed., b. 10, ch. 14።GCAmh 154.1

    የተሐድሶውን እምነት ለመገልበጥ ኃያል ጠላቶች ሲያብሩ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰይፎች ተመዘው የተቀሰሩበት ሲመስል፣ ሉተር፦ “ሰይጣን እጅግ ተቆጥቷል፤ እግዚአብሔርን የማይመስሉ ቀሳውስት በአንድ እየመከሩ፣ ጦርነት እንደሚከፈትብንም ያእያስፈራሩን ነው። ጠላቶቻችን በእግዚአብሔር መንፈስ ተሸንፈው ወደ ሰላም ይመጡ ዘንድ፣ በጌታ ዙፋን ፊት፣ ከልባቸው ተደፍተው በእምነትና በፀሎት ይምዋገቱ ዘንድ ሕዝቡን ተማጸኑ። የሚያስፈልገን አጣዳፊው ነገር፣ መጀመሪያ ማድረግ የሚጠበቅብን ነገር፣ መፀለይ ነው። በዚህ ሰዓት ለሰይፍ ስለትና ለሰይጣን ቁጣ ተጋልጠው እንዳሉ ሕዝቡ እንዲያውቁት ይደረግ፣ ይፀልዩ።” አለ።-D’Aubigné, b. 10, ch. 14።GCAmh 154.2

    እንደገናም ቆይቶ፣ ግንባር ለመፍጠር ሲያሰላስሉ ስለነበሩ ተሐድሶውን የተቀበሉ ልዑላን ሲናገር በዚህ ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውለው መሳሪያ “የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ” ብቻ ነው አለ። ለሳክሶኒው መራጭ ሲፅፍ፦ “የታሰበውን ህብረት/ግንባር ለመደገፍ ህሊናችን አይፈቅድም። ክርስቶስ ጌታችን እጅግ ኃያል ነው፤ ከአደጋ ይጠብቀን ዘንድ መንገዶችን ማዘጋጀት ይችላል፤ የክፉ ልዑላንንም ሃሳብ መና ያደርገዋል… ቃሉን እንደምንታዘዝ፤ ወይስ እንደማንታዘዝ፣ በእርግጥ እውነት እንደሆነ እንደምንቀበለው ለማየት ክርስቶስ እየፈተነን ነው። በእኛ ምክንያት ወንጌሉ የደም ፍሰት ወይም የጉዳት መንስኤ ከሚሆን አሥር ጊዜ ብንሞት ይሻለናል። በትዕግስት ብንሰቃይ ባለመዝሙሩ እንዳለው እንደሚታረዱ በጎች [መዝ 44÷22] ብንሆን ይሻለናል፤ ለራሳችን ከመከላከል ወይም የበቀል እርምጃ ከመውሰድ ለእግዚአብሔር ቁጣ ቦታ እንልቀቅ።”አለ። “የክርስቶስ መስቀል እንሸከመው ዘንድ የተገባው ነው። ግርማውያን ሆይ አትፍሩ፤ ሁሉም ጠላቶቻችን በእብሪት ከሚናገሩት ይልቅ በፀሎታችን ብዙ ማከናወን እንችላለን። እጃችሁ በወንድሞቻችሁ ደም እንዳይጋጅ ብቻ ተጠበቁ። ንጉሠ ነገሥቱ ለፍርድ ቤቶቹ አሳልፎ ቢሰጠን፣ በዚያ ለመገኘት ዝግጁ ነን። ለእምነቱ የመከላከል አቅም የላችሁም። የተጋረጠበትን አደጋና አስከፊ ሁኔታ እያንዳንዱ አምኖ መቀበል አለበት።”GCAmh 154.3

    በታላቁ ተሐድሶ ዓለምን ያናወጠ ኃይል ከፀሎት ድብቅ ስፍራ ወጣ። በዚያ በተቀደሰ መረጋጋት የአምላክ አገልጋዮች በተስፋው ቋጥኝ ላይ እግራቸውን አፀኑ። በአውግስበርግ በነበረው ትንቅንቅ ሉተር በቀን ሶስት ሰዓት ለፀሎት ከመመደብ ዝንፍ አላለም ነበር። እነዚህም ሰዓታት የተወሰዱት ለማጥናት ምቹ ከሆኑበት ጊዜያት ተቀንሰው ነበር። በግል ክፍሉ ሆኖ ሲፀልይ ልክ ከጓደኛው ጋር እንደሚነጋገር ያህል የአክብሮት የፍርሃትና የተስፋ ቃላት ሲናገር፣ በእግዚአብሔር ፊት ነፍሱን ሲያፈስ ይሰማ ነበር። “አንተ አባታችንና አምላካችን እንደሆንህ አውቃለሁ” አለ “ልጆችህን የሚያሳድዱትንም ትበትናቸዋለህ ምክንያቱም አንተም ከእኛ ጋር አደጋ ተጋርጦብሃልና። ሁሉም ያንተ ጉዳይ ነው፤ እኛም ወደዚህ ነገር እጃችንን ያስገባነው ባንተ ምክንያት ነው። ስለዚህ ከልለን፣ ኦ አባት ሆይ!”-Ibid, b. 14, ch. 6። በስጋትና በፍርሃት ለደቀቀው ሜላክቶን ሲጽፍ “ፀጋና ሰላም በክርስቶስ! በዓለም ሳይሆን በክርስቶስ እላለሁ፤ አሜን! እየረመረሙህ ያሉትን እጅግ የገዘፉ ጭንቀቶች(ሀዘኖች) በመሪር ጥላቻ እጠላቸዋለሁ። ይህ ጉዳይ ልክ ካልሆነ ተወው፤ የቆምንለት ዓላማ ልክ ከሆነ ደግሞ ያለፍርሃት እንድንተኛ ያዘዘንን የእርሱን የተስፋ ቃል በሃሰት ለምን እናስመስላለን?” “እውነትንና ፍርድን ለማድረግ ክርስቶስ እጅ የሚያጥረው አምላክ አይደለም፤ ይኖራል፤ ይገዛልም፤ ታዲያ ምን አይነት ፍርሃት ነው የሚይዘን?”-Ibid, b. 14, ch. 6።GCAmh 155.1

    እግዚአብሔር የባሪያዎቹን ጩኸት ሰማ። የዚህን የጨለማ ዓለም ገዥዎች ይቃወሙ ዘንድ፣ እውነትን ጠብቀው ይቆሙ ዘንድ፣ ለልዑላንና ለአገልጋዮች እግዚአብሔር ፀጋና ድፍረት ሰጠ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም።” [1ኛ ጴጥ 2÷6]። የፕሮቴስታን ተሐድሶ አራማጆች በክርስቶስ ላይ ተመስርተው ነበር፤ የገሃነም ደጆችም ይቋቋሟቸው ዘንድ አልቻሉም።GCAmh 155.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents