Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የአድቬንቲስት ቤት

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ምዕራፍ አርባ ዘጠኝ—የእናት ረዳቶች

    በቤተሰብ ድርጅት ውስጥ ልጆች ሸሪኮች ይሁኑ፦ በቤት ውስጥ ልጆችም ሆኑ ወላጆች አስፈላጊ ኃላፊነቶች አሉባቸው። የቤት ድርጅቱ አካል እንደሆኑ ተደርገው ሊሠለጥኑ ይገባቸዋል። ፍቅርና እንክብካቤ ያገኛሉ፤ ይበላሉ ይለብሳሉ፤ ስለዚህ የድርሻቸውን ቀንበር በመሸከም እንደ አባልነታቸው ወደ ቤት ሊያመጡት የሚችሉትን ደስታ ሁሉ በማምጣት ለእነዚህ ብዙ ቸርነቶች ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። 1Ministry of Healing, p. 394.AHAmh 199.1

    የቤተሰቡ ኩባንያ አባል እንደሆኑና በድርጅቱ ውስጥ ያለባቸውን ኃላፊነት መሸከም እንደሚገባቸው እያንዳንዷ እናት ልጆችዋን ማስተማር አለባት። የቤተ-ክርስቲያን አባላት የፀሎት ቤት ግንኙነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ሁሉ፣ እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባልም ድርሻውን በታማኝነት ይወጣ። ትንንሽ የመላላክ ሥራዎችን በመሥራት ልጆች አባትና እናታቸውን እየረዱ እንደሆነ ይወቁ። ለእናንተ የሚሠሩትን ሥራ ስጧቸው፤ ሲጨርሱም ለመጫወት ጊዜ እንደምትሰጧቸው ንገሯቸው። 2Review and Herald, June 23, 1903.AHAmh 199.2

    የልጆች አዕምሮ ንቁ ነው፤ የኑሮን ሸክም ለማንሣት በሚደረገው ልፋት ውስጥ በሥራ ሊጠመድ ይገባዋል.… ሥራቸውን እራሳቸው እንዲመርጡ ፈጽሞ መፈቀድ የለበትም። ይህንን ጉዳይ ወላጆች እራሳቸው ሊቆጣጠሩት ይገባል። 3Manuscript 57, 1897.AHAmh 199.3

    እናቶችም ሆኑ ልጆቻቸው ግዴታዎች አሉባቸው፦ ወላጆች ልጆቻቸውን የመመገብ፣ የማልበስና የማስተማር ግዴታ አለባቸው፤ ልጆች ደግሞ በቅንነት፣ በእምነትና በደስታ ወላጆቻቸውን የማገልገል ግዴታ አለባቸው። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ያለባቸውን ልፋትና ሸክም መጋራት ቸል ሲሉ፣ ወላጆቻቸውስ ለእነርሱ ያላቸውን ኃላፊነት ቢረሱ ምን ይሰማቸዋል? ለወላጆቻቸው ጠቃሚ የሚሆኑበትን የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሲረሱ፤ የሚያስፈጋቸውንና የማይስማሙበትን ሆኖም የወላጆቻቸውን ሸክም የሚያቃልለውን ሥራ ቸል ሲሉ፤ ለወደፊት ጠቃሚነታቸው ገጣሚ የሚያደርጋቸውን ተወዳዳሪ የሌለው አስፈላጊ ትምህርት የሚያገኙበት ዕድል ያልፋቸዋል። 4The Youth’s Instructor, July 20, 1893.AHAmh 199.4

    ወላጆቻቸው ለእነርሱ የሚያደርጉትን የእንክብካቤ ሸክም ይጋሩ ዘንድ ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንዲሠለጥኑ፣ ሁሉንም የአማኝ ልጆች እግዚአብሔር ይፈልግባቸዋል። ቤቱ ተከፍሎ የራሳቸውን ክፍል ወስደዋል፤ በቤተሰቡ ገበታ ይቀመጡ ዘንድ መብትና እድሉ ተሰጥቷቸዋል። ልጆቻቸውን ያለብሱና ይመግቡ ዘንድ ጌታ ወላጆችን ይጠይቃቸዋል። የወላጆችና የልጆች ግዴታዎች ግን የጋራ ናቸው። ወላጆቻቸውን ማክበርና ከፍ ከፍ ማድረግ የልጆች ፋንታ ነው። 5Manuscript 128, 1901.AHAmh 199.5

    ልጆች ግድ-የለሾችና የማይጨነቁ፣ ሁሉንም ሸክም በወላጆቻቸው ላይ የሚጭኑ ሆነው እንዲያድጉ ሊፈቀድላቸው አይገባም። ሁሉንም መስዋዕትነት እራሳቸው በመክፈል፣ ወላጆች የልጆቻቸው አሽከሮች (ባርያዎች) መሆን የለባቸውም።፡ 6Manuscript 126, 1897.AHAmh 200.1

    መስመሩን የሳተ ደግነት ስንፍናን ያስተምራል፦ ልጆች ጠቃሚ እንዲሆኑ እራሳቸውንና ሌሎችን እንዲረዱ ገና በጨቅላነታቸው መማር አለባቸው። እናታቸው ስትማስን፣ ስታበስል፣ ስታጥብና ስትተኩስ ምንም ሳይሰማቸው በማረፊያ ክፍላቸው ተጎልተው የሹራባቸውን ክፈፍ የሚዘመዝሙ፣ በመርፌ ጌጥ የሚሠሩ የሚጠልፉና ተረታ-ተረቶችን የሚያነብቡ ብዙ የዚህ ዘመን ልጃገረዶች አሉ። ልባቸው እንደ ድንጋይ የደነደነ ምንም ስሜት የሌለው ግዑዝ ነው።AHAmh 200.2

    ይህ ችግር ግን የመነጨው ከየት ነው? በዚህ ጉዳይ በአብዛኛው ጥፋተኛ ሊባሉ የሚችሉት እነማን ናቸው? - ምስኪኖቹ የተታለሉት ወላጆች። የልጆቻቸውን የወደፊት መልካም ሁኔታ አያስተውሉም። በተሳሳተ ምኞታቸውም ምንም ሳይሠሩ እንዲቀመጡ ወይም አዕምሮንና ጡንቻን በማያፍታታ እርባና በሌለው ነገር ላይ እንዲትኮሰኮሱ ይፈቅዳሉ። ከዚያም ሰነፍ ልጆቻቸው ሥራ የማይሠሩት አቅም ስለሌላቸው እንደሆነ ምክንያት ይሰጣሉ። ልፍስፍስ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ የወላጆች አካሄድ ነው። በቤት ዙሪያ ያለው በቂ እንቅስቃሴ አካልንና አዕምሮን የሚያጎለብት ነው። ልጆች ግን በተሳሳቱ ግንዛቤዎች ይህንን ተነፍገዋል፤ ሥራን የሚጠሉ እንዲሆኑ ተደርገዋል። 7Testimonies for the Church, Vol. 1, p. 686.AHAmh 200.3

    ልጆቻችሁ የመሥራት ልምድ የሌላቸው ከሆኑ ብዙም ሳይቆዩ የዛሉ ይሆናሉ፤ የጎን ውጋት፣ የትክሻ ህመም እንዲሁም የእጅና የእግር ድካም ይሰማቸዋል። ትንሽም እንኳ የሥራ ስቃይ እንዳያገኛቸው በማድረግ በርኅራኄያችሁ ብዛት ሁሉንም ሥራ የመሥራት አደጋ ይገጥማችኋል። የልጆችን ሥራ መጀመሪያ በጣም ቀላል አድርጉት፤ ከዚያም ብዙ ሳይደክሙ በቂ ሥራ መሥራት እስኪችሉ ድረስ በየቀኑ ትንሽ ትንሽ ጨምሩላቸው። 8Id., p. 687.AHAmh 200.4

    የስንፍና አደጋዎች፦ የብዙ ኃጢአት መንስኤ ስንፍና እንደሆነ አይቻለሁ። በሥራ የተጠመዱ እጆችና አዕምሮዎች ጠላት የሚያቀርበውን እያንዳንዱን የማታለያ ፈተና ለመስማት ጊዜ የላቸውም። ያለ ሥራ የተቀመጡ እጆችና ጭንቅላቶች ግን በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ለመሆን የተዘጋጁ ናቸው። አዕምሮ በመልካም ነገር ካልተሞላ የማይረቡ ነገሮች መኖሪያ ይሆናል። ወላጆች ስንፍና ኃጢአት እንደሆነ ለልጆቻቸው ማስተማር ይኖርባቸዋል። 9Id., p. 395.AHAmh 200.5

    ሁሉንም ሸክም ከልጆች በማንሣት ሥራ-ፈትና ዓላማ የሌለው ሕይወት እንዲኖራቸው፤ ምንም ነገር እንዳይሠሩ ወይም እነርሱ የመረጡትን ብቻ እንዲያደርጉ እንደመተው ያለ ልጆችን በእርግጠኝነት ወደ ርኩሰት የሚመራ ነገር የለም። የልጆች አዕምሮ ንቁ ነው፤ መልካምና ጠቃሚ በሆነ ነገር ካልተያዘ ወደ መጥፎ መዞሩ አይቀሬ ነው። የመዝናኛ ጊዜ ትክክልና አስፈላጊ ቢሆንም መሥራትን መማር አለባቸው። የጉልበት ሥራ የሚሠሩበት፣ የማንበቢያና የማጥኛ ቋሚ ሰዓታት ሊኖሯቸው ይገባል። ለዕድሜያቸው ተገቢ የሆነ ሥራ እንደተሰጣቸውና ጠቃሚና አዝናኝ መጻሕፍት እንዳሏቸው አረጋግጡ። 10Christian Temperance and Bible Hygiene, pp. 134, 135.AHAmh 200.6

    እርግጠኛው መከለያ በጠቃሚ ሥራ መጠመድ ነው፦ ወጣቱ ከክፉ እንዲጠበቅ፣ በእርግጠኝነት ውጤታማ ከሆኑት መከላከያዎች መካከል አንዱ በጠቃሚ ሥራ መጠመድ ነው። የታታሪነት ባህል እንዲያዳብሩ ቢሠለጥኑ፣ ያሏቸው ሰዓታት ሁሉ ለጠቃሚ ነገር እንዲውሉ ቢደረግ፣ በዕድላቸው ለማጉረምረም ወይም ተጎልተው በመዋል የህልም እንጀራ ለመብላት ጊዜ አያገኙም። ምግባረ ብልሹነት ለሚገለጥባቸው ባህርያት ወይም ጉድኝቶች የመጋለጣቸው አደጋ በጣም የጠበበ ይሆናል። 11Review and Herald, Sept. 13, 1881.AHAmh 201.1

    ወላጆች በሌሎች ነገሮች ተይዘው ልጆቻቸው በጠቃሚ ነገሮች ላይ እንዲጠመዱ ማድረግ ካልቻሉ ሰይጣን በራሱ ሥራ ያሳትፋቸዋል። 12Signs of the Times, April 3, 1901.AHAmh 201.2

    ልጆች ሸክምን የመሸከም ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፦ ልጆቻቸው ሊማሩት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ትምህርት የድርሻቸውን የቤት ቀንበር መሸከም ግዴታቸው እንደሆነ ማሳወቅ ነው፤ ለዚህ እውነታ ወላጆች ሊነቁ ይገባቸዋል….ከተፈጥሮአዊ እውቀት በመነሣት ሚዛናዊ የሕይወት እይታ እንዲኖራቸው፣ ለዚህ ዓለም ጥቅም ሊሆኑ እንደተፈጠሩ እንዲያስተውሉ ለልጆቻቸው ያስተምሩ። በቤት ውስጥ በእናትየዋ ብልህ ቁጥጥር ሴቶችና ወንዶች ልጆች የሕይወትን ቀንበር ስለመሸከም የመጀመሪያውን ትምህርት ማግኘት አለባቸው። 13Letter 106, 1901.AHAmh 201.3

    ልጅን ለመልካም ወይም ለጥፋት የሚያበቃው ትምህርት የሚጀምረው ገና ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ጀምሮ ነው…. ታላላቆች ታናናሾቻቸውን በመንከባከብ ቤተሰቡን መርዳት አለባቸው። ልጆች መሥራት በሚችሉት ወይም መሥራት ባለባቸው ሥራ ላይ እናት ራስዋን ልታደክም አይገባትም። 14Manuscript 126, 1903.AHAmh 201.4

    ሸክምን መጋራት እርካታ ይሰጣል፦ ወላጆች ሆይ! ልጆቻችሁ እንደ የቤተሰብ አባልነታቸው መወጣት ያለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነት በመሥራት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፈጽሙ ዘንድ እርዷቸው። ይህ ተወዳዳሪ የሌለው ጠቃሚ ልምድ ይሰጣቸዋል። ይህ ልምድ ሃሳባቸው ራሳቸውን ብቻ ማዕከል ያደረገ፤ እራሳቸውን ብቻ የሚያስደስቱና ስለራሳቸው መዝናናት ብቻ ግድ የሚላቸው እንዳይሆኑ ያስተምራቸዋል። በቤተሰቡ ክበብ ያለባቸውን ድርሻ እንዲወጡ የእናትና አባታቸውን፣ የእህቶችና ወንድሞቻቸውን ቀንበር ለመሸከም በማገዝ፣ ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ በትዕግሥት አስተምሯቸው። በቤተሰብ ውስጥ አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆኑም በማወቅ እርካታ ያገኛሉ። 15Manuscript 27, 1896.AHAmh 201.5

    ልጆች አጋዥ እንዲሆኑ ሊማሩ የሚችሉ ናቸው። በተፈጥሮ ንቁና በሥራ የመጠመድ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው። ይህም ዝንባሌ በትክክለኛው መንገድ ለመሠልጠንና ለመመራት በቀላሉ መማረክ የሚችል ነው። ልጆች የሚሰጧቸውን የየዕለት ሸክሞች መሸከም ይችሉ ዘንድ ገና በጨቅላነታቸው መማር ይችላሉ። እያንዳንዱ ልጅ በወላጆቹ ወይም ባሳዳጊወቹ፣ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ መሠልጠን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ልጅ እያሉ የሥራን ቀንበር መሸከምን ይማራሉ፤ ጥቃቅን ሥራዎቻቸውን በመፈጸም ደስታን ያገኛሉ - ሥራን በጥሩ ሁኔታ በማከናወን ብቻ የሚገኝ ደስታ። እራሳቸውን ከማስደሰት ባለፈ ሕይወት ለእነርሱ አስፈላጊ ሥራ እንዳላት በመረዳት ግዴታንና ኃላፊነትን የተለማመዱ የመሥራትን ጣዕም ያወቁ ይሆናሉ።AHAmh 201.6

    ሥራ ለልጆች መልካም ነው፤ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጠቃሚ ሥራ ቢያሳልፉት የበለጠ ደስተኞች ይሆናሉ፤ ሥራቸውን በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላ ጨዋታቸውን ከፍ ባለ ድምቀት ይደሰቱበታል። ሥራ ጡንቻንና አዕምሮን ያጠነክራል። እናቶች በልጆቻቸው ውድና ትናንሽ ረዳቶችን ማግኘት ይችላሉ፤ ጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያስተምሯቸውም ጊዜ እራሳቸው ስለ ሰው ተፈጥሮ ዕውቀት ይቀስማሉ፤ ከእነዚህ ትኩስና ወጣት ፍጡራን ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችሉ በማወቅም የራሳቸው ልብ ሞቃትና ለጋ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ ይማራሉ። ልጆቻቸው በፍቅርና በመተማመን ሲመለከቷቸው እነርሱ ደግሞ ለእርዳታና ምሪት ወደ አዳኙ ሊያንጋጥጡ ይችላሉ። በሥነ-ሥርዓት የሠለጠኑ ልጆች ዕድሜአቸው እየጨመረ ሲሄድ የጓደኞቻቸውን ሸክም የሚያቀልለውን ተግባር የበለጠ እየወደዱት ይሄዳሉ። 16Health Reformer, Dec., 1877.AHAmh 202.1

    የአዕምሮ ሚዛንን ይጠብቃል፦ ልጆች እንዲሠሩ የተመደበላቸውን ሥራ በመፈጸም ውስጥ የማስታወስ ችሎታን ያጎለብታሉ፤ ትክክለኛ የአዕምሮ ሚዛንን ይጠብቃሉ፤ የባህርይ መረጋጋትንና ቅልጥፍናን ያዳብራሉ። የእለቱ ጥቃቅን ተግባራት ጥልቅ ሃሳብን፣ ስሌትንና የክንውን እቅድን ይጠይቃሉ። ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ የበለጠ ይጠበቅባቸዋል። የሚሠሩት ሥራ የሚያዝለፈልፍና ረዥም ከመሆኑ የተነሣ የሚያደክም ሐሞትም የሚያፈስ መሆን የለበትም። በብልሃት የተመረጠ ለአካላቸው መጎልበት አስፈላጊና አግባብነት ያለው ለአዕምሮና ለባህርይ እድገት ጠቃሚ የሆነ ሥራ ይሁን። 17Health Reformer, Dec., 1877AHAmh 202.2

    ከሰማይ ሠራተኞች ጋር ያቆራኛል፦ ጥቃቅንና ተራ የሆኑትን የዕለት ተዕለት ተግባራት በትክክል ይከተሏቸው ዘንድ ጌታ የኮለኮላቸው (ያስቀመጣቸው) መስመሮች እንደሆኑ በማመን በታማኝነትና በብቃት እርሱን ማገልገል እንዲችሉ የሚሠለጥኑበት ትምህርት ቤት አድርገው ቢቆጥሩት፣ ሥራቸው ምን ያህል አስደሳችና ክቡር ሆኖ ይታያቸው ነበር! እያንዳንዱ ሥራ የጌታ እንደሆነ አድርጎ መፈጸም አጅግ ተራ የተባለው ተግባር በትጋት እንዲተገበር ከመርዳቱ በተጨማሪ በምድር ያሉ ሠራተኞች የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሰማይ ከሚያደርጉ ቅዱስ ፍጡራን ጋር በሥራ እንዲዛመዱ ያደርጋል። 18Patriarchs and Prophets, p. 574.AHAmh 202.3

    በሰማይ ሁልጊዜም ሥራ አለ። ቦዘኔዎች እዚያ የሉም። “አባቴ አስከዛሬ ያደርጋል [ይሠራል]” የሱስ አለ፤ “እኔም አደርጋለሁ [እሠራለሁ]።” የመጨረሻው ድል ሲመጣ የተዘጋጁትን እልፍኞች ስንረከብ ደስታ የሞላበት ሥራ-ፈትነትና ቦዘኔነት እጣ ፈንታችን እንደሚሆን እንዳንጠብቅ። 19Manuscript 126, 1897.AHAmh 202.4

    የቤት ውስጥ ሕብረትን ያጠናክራል፦ በወጣቶች የቤት ውስጥ ሥልጠና የመተባበር መርህ ዋጋ የማይገኝለት ነው…. ታላላቆቹ ልጆች የወላጆቻቸው ረዳት በመሆንና በእቅዳቸው በመሳተፍ ኃላፊነታቸውንና ቀንበራቸውን ሊጋሯቸው ያስፈልጋል። አባቶችና እናቶች ልጆቻቸውን ለማስተማር ጊዜ ይውሰዱ፤ ለእርዳታቸው ዋጋ እንደሚሰጡት፤ መተማመናቸውን እንደሚፈልጉት፤ ሕብረታቸው እንደሚያስደስታቸው ያሳዩአቸው፤ ልጆችም ጥሪያቸውን ለመመለስ አይዘገዩም። የወላጆች ሸክም መቅለሉ ብቻ አይደለም፤ ልጆች ሊገመት የማይችል ዋጋ ያለው ተግባራዊ ትምህርት መማራቸው ብቻም አይደለም፤ የቤተሰብን ሕብረት የሚያጠናክር የባህርይን መሠረት ጥልቅ የሚያደርግ ውጤትም አለው። 20Education, p. 285.AHAmh 203.1

    የአዕምሮ የግብረ-ገብነትና የመንፈስ ጥልቀትን ያሳድጋል፦ የእናት አባትን ችግር ለማቃለል ራስ-ወዳድ ያልሆነውን ፈቃዳቸውን በማሳየት፣ ልጆችና ወጣቶች ሊደሰቱ ይገባቸዋል። የድርሻቸውን ሸክም በደስታ ሲያነሡ በእግረ-መንገዱ እምነትና የጠቃሚነት ዋጋ ለሚጠይቁ ደረጃዎች ብቁ እንዲሆኑ ይሠለጥናሉ። በእያንዳንዱ ዓመት ያላሰለሰ እድገት እያሳዩ ቀስ በቀስ ሆኖም በእርግጠኝነት ተሞክሮአቸው እየጨመረ የልጅነትን ዘመን እየለቀቁ ጎልማሳ ወንዶችና ሴቶች የሚያደርጋቸውን ልምድ እየወረሱ ያድጋሉ። የቤትን ቀላል ኃላፊነቶች በታማኝነት ሲፈጽሙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች የአዕምሮ፣ የግብረ-ገብነትና የመንፈስ እድገት መሠረት ይጥላሉ። 21Messages to Young People, pp. 211, 212.AHAmh 203.2

    ለአካል ጤናና ለአዕምሮ ሠላም ይሰጣል፦ በቤት ውስጥ ኑሮ የድርሻቸውን በደስታ በሚወጡና የወላጆቻቸውን ቀንበር በሚጋሩ ልጆች ላይ የእግዚአብሔር አድናቆት በአፍቃሪ አዎንታ ያርፋል። በአካል፣ ጤንነትና በአዕምሮ ሠላም ይሸለማሉ፤ ወላጆቻቸው የፋንታቸውን ማህበራዊ ደስታ ሲያገኙና ጤናማ መዝናናት ሲያደርጉ ልጆች በሐሴት ይሞላሉ፤ በዚህም የወላጆቻቸውን ዕድሜ ያራዝማሉ። ለነባራዊ የሕይወት ግዴታዎች በሚገባ የሠለጠኑ ልጆች፣ ድካምን ለመቋቋም የሕሊናና የአካል ጥንካሬ እንደሌላቸው፣ በጨቅላነታቸው ትምህርት ቤት ገብተው ታፍነው ከሚውሉት ተማሪዎች የላቀ ትምህርት ቀስመው፣ ጠቃሚ የሕብረተሰብ አካል ለመሆን ከቤት ይወጣሉ። 22Counsels to Teachers, Parents and Students, p. 148.AHAmh 203.3

    አንዳንድ ጊዜ ልጆች ትምህር ቤት ከሚሠሩት የበለጠ በቤት ውስጥ ሥራ ሥልጠና ቢሠጣቸው የተሻለ ነው። ከሁሉም በላይ አሳቢና ለመርዳት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ከመጽሐፍ ሊማሯቸው የሚጠበቅባቸው ብዙወቹ ትምህርቶች፣ ከተግባራዊ ሥራና ከሥነ-ምግባር ትምህርት ጋር ሲነፃጸሩ አስፈላጊነታቸው ታህታዊ (ዝቅ ያለ) ነው። 23Manuscript 126. 1903.AHAmh 203.4

    ዕረፍት ያለው እንቅልፍ ያስተኛል፦ እናቶች ሴት ልጆቻቸውን ወደ ወጥ-ቤት ሊወስዷቸውና በትዕግሥት ሊያስተምሯቸው ይገባል። በቀኑ መጨረሻ ለእንዲህ ዓይነቱ ሥራ የተሻለ አደረጃጀት ያላቸው ጡንቻቸው ጠንካራና ቅርጽ የያዘ፤ የሚያወጡትና የሚያወርዱት ሐሳብም ጤናማና ከፍ ያለ ይሆናል። ይደክማቸው ይሆናል፤ ሆኖም ተገቢውን ሥራ ካከናወኑ በኋላ የሚወስዱት ዕረፍት እንዴት ጣፋጭ ነው! እንቅልፍ - የተፈጥሮ ጣፋጭ አዳሽ - የደከመውን ሰውነት በኃይል ሞልቶ ለሚቀጥለው ቀን ሥራ ያዘጋጀዋል። ቢሠሩም ባይሠሩም ምንም እንዳይደለ በምንም ዓይነት መንገድ ለልጆቻችሁ እንዳትጠቁሙ። እርዳታቸው እንደሚያስፈልጋችሁ፣ ጊዜያቸው ዋጋ እንዳለ ውና በአስተዋጾአቸው እንደምትደገፉ አስተምሯቸው። 24Testimonies for the Church, Vol. 1, p. 395.AHAmh 203.5

    ልጆች ሥራ-ፈት ሆነው እንዲያድጉ መፍቀድ ኃጢአት ነው። የሚያደክማቸው ቢሆንም እንኳ እጅ እግራቸውንና ጡንቻቸውን የሚያንቀሳቅስ ሥራ ይሥሩ። ከመጠን በላይ ካልሆነ በቀር ድካም እናንተን ከሚጎዳው በላይ እነርሱን እንዴት ይጎዳቸዋል? በድካምና በመዝለፍለፍ መካከል ብዙ ልዩነት አለ። ልጆች የሚሠሩት ሥራ ቶሎ ቶሎ እንዲቀየርላቸው ይፈልጋሉ፤ ከትልቅ ሰውም በበለጠ በመሃል ዕረፍት ቶሎ ቶሎ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሆኖም ገና ሕፃን እያሉ የመሥራት ትምህርት ይጀምሩ፤ ራሳቸውን ጠቃሚ የማድረጋቸው ግንዛቤ ያስደስታቸዋል። ከጤናማ ሥራ በኋላም የሚተኙት ዕንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ ለሚቀጥለውም ቀን ሥራ ታድሰው ይነሣሉ። 25Christian Temperance and Bible Hygiene, p. 135.AHAmh 204.1

    “ልጆቼ ያስቸግሩኛል” አንበል፦ “እህ” ይላሉ አንዳንድ እናቶች፣ “ልጆቼ ሊያግዙኝ ሲሞክሩ ያስቸግሩኛል”፣ የእኔም ልጆች እንደዚያው ነበሩ፤ እንዲያውቁት ግን ያደረግኋቸው ይመስላችኋል? ልጆቻችሁን አድንቁ። በሐረግ ላይ ሐረግ፣ በመመሪያ ላይ መመሪያ እየጠቀሳችሁ አስተምሯቸው። ይህ ልብ-ወለድ ከማንበብ እጅግ የተሻለ ነው፤ ስልክ ከመደወል የበለጠ ነው፤ የዓለምን ፋሽን ከመከተል የላቀ ነው። 26Manuscript 31, 1901.AHAmh 204.2

    የምሣሌነቱ ጨረፍታ፦ ለተወሰነ ዘመን የሰማይ ልዑል፣ የክብር ንጉሥ በቤተልሄም ሕፃን ነበረ፤ በእናቱ እቅፍ ውስጥ ያለውን ሕፃንም ይወክላል። በልጅነቱ ታዛዥ ልጅ የሚያደርገውን ብቻ ይፈጽም ነበር፤ እንደ ልጅነቱ መጠን የሚችለውን ሥራ በማከናወን የወላጆቹን ፈቃድ ያደርግ ነበር። ልጆች ሊያደርጉት የሚችሉት ይህንን ነው፤ የክርስቶስን ምሣሌ ይከተሉ ዘንድ ሊሠለጥኑና ሊማሩ ይገባቸዋል። ወላጆቹን በመታዘዝ፣ በቤት ሕይወቱ ሚሲዮናዊ ሥራ በመሥራት እንቅስቃሴው ሁሉ ለገባበት ቤት በረከት የሚያመጣ ነበር። ተጽፏል:- “ሕፃኑ ግን አደገ፣ በመንፈስም ፀና፤ ጥበብም ሞልቶበት። የእግዚአብሔርም ፀጋ በእርሱ ነበረችበት።” “የሱስም በጥበብና በቁመት ያድግ ነበረ በፀጋም በእግዚአብሔር በሰውም ዘንድ።” 27Signs of the Times, Sept. 17, 1894.AHAmh 204.3

    የእርሱን ምሣሌነት እንዲከተሉ በማስተማር የክርስቶስን የደስታ ሕይወት እንዴት እንደሚጎነጩ ለማሳየት መተባበር ለወላጆችና ለመምህራን የተሰጠ የማይገኝ ዕድል ነው። የአዳኙ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ጠቃሚ ዘመናት ነበሩ፤ የእናቱ ረዳት ነበረ፤ የቤት ውስጥ ኃላፊነቱን ሲያከናውን በአናፂው ወንበር ሲሰራ ልክ ሕዝባዊ አገልግሎቱን ያካሂድ እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የቤት ውስጥ ተልዕኮውን እየፈፀመ ነበር። 28Review and Herald, May 6, 1909.AHAmh 204.4

    ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ ለሰው ዘር ሁሉ ምሳሌ ነበር። በቤትም ታዛዥና ረዳት ነበረ፤ የአናፂነትን ሥራ ተምሮ በራሱ እጆች በትንሹዋ ሱቅ ውስጥ በናዝሬት ይሠራ ነበር…. በልጅነቱና በወጣትነቱ ሲሠራ ሰውነቱና አዕምሮው ጎልብቶ ነበር። ብልቶቹ ጤናማ ሆነው በእያንዳንዱ የሥራ መስክ ግሩም ተግባር ማከናወን እንዲያስችሉት አደረጋቸው እንጂ አካላዊ ጥንካሬውን በግድ-የለሽነት አልተጠቀመበትም። 29Counsels to Teachers, Parents, and Students, p. 147.AHAmh 205.1