Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የአድቬንቲስት ቤት

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ክፍል ፲፫—የገንዘብ አጠቃቀም

    ምዕራፍ ስድሳ—የእግዚአብሔር አገልጋዮች

    ለእግዚአብሔር ባለቤትነት ዕውቅና መስጠት አለብን፦ የሥራ ግብረገብነትና የዕውነተኛ ስኬት መሠረቱ ለእግዚአብሔር ባለቤትነት እውቅና መስጠት ነው። የሁሉ ፈጣሪ የሆነው እርሱ የመጀመሪያው ባለቤት ነው። እኛ የእርሱ አገልጋዮች ነን፤ ያለን ሁሉ እንደ እርሱ ፈቃድ እንጠቀምበት ዘንድ በአደራ የተሰጠን ነው። AHAmh 266.1

    ይህ በእያንዳንዱ የሰው ዘር ላይ የተጣለ ግዴታ ነው። ሁሉንም የሰው ልጅ የእንቅስቃሴ ወሰን ያካተተ ነው። አወቅነውም አላወቅነውም እግዚአብሔር በቸረን ችሎታና ክህሎት የተሰጠንን ሥራ እናከናውን ዘንድ በምድር የተቀመጥን አገልጋዮች ነን። 1Education, p. 137.AHAmh 266.2

    ገንዘቡ የእኛ አይደለም፤ መሬቱና ፈረሶቹ [ግድግዳ ላይ የተንጠለጠሉ] ስዕሎችና የቤት እቃዎቹ፤ ልብሶቹና የቅንጦት ነገሮቹ ሁሉ የእኛ አይደሉም። እኛ የዕምነት መንገደኞች፣ እንግዳዎች ነን። ለጤናችንና ለሕይወታችን የሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ በሥጦታ ተሰጥተውናል…. ምድራዊ በረከቶቻችን ጌታ ሊያወርሰን ላለው ዘለዓለማዊ ሀብት የተገባን እንደሆንን እናስመሰክር ዘንድ እምነት አጉዳይ አለመሆናችንን ለማረጋገጥ በአደራ የተረከብናቸው ናቸው። የእግዚአብሔርን የሙከራ ፈተና በጽናትና በአሸናፊነት ከተወጣን ያ የተገዛው ንብረት የራሳችን ይሆን ዘንድ ይሰጠናል - እርሱም ግርማ ሞገስ ክብርና ዘለዓለማዊነት ነው። 2Letter 8, 1889.AHAmh 266.3

    ተጠያቂዎች ነን፦ የራሳችን ሰዎች [የቤተ-ክርስቲያን አባላት] ከእግዚአብሔር በአደራ የተበደሩትን ገንዘብ ለእርሱ ጉዳይ ቢያውሉት፤ የራስ-ወዳድ ፍላጎትን ለማርካትና ለዝሙት የሚያጠፉትን ገንዘብ ለጌታ ቢያደርጉት፤ በሰማይ መዝገብ ባከማቹ ነበር። እግዚአብሔር እንዲሠሩ የጠራቸውን ያንኑ ሥራም በሠሩ ነበር። ነገር ግን በምሣሌው እንደተጠቀሰው ባላፀጋ ሰው በድሎት ይኖራሉ። ለስሙ ክብር ይጠቀሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ያበደራቸውን ገንዘብ በብክነት ያጠፉታል። ለእግዚአብሔር ያለባቸውን ተጠያቂነት ቆም ብለው አያጤኑትም። በአገልጋይነታቸው የሚጠየቁበት የፍርድ ቀን በቅርብ እንደሚመጣ ቆም ብለው አይመረምሩም። 3Letter 21, 1898.AHAmh 266.4

    በፍርድ ጊዜ የእግዚአብሔርን ገንዘብ እንዴት እንደተጠቀምንበት የሚያትተውን መዝገብ እንደምንገናኘው ሁልጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። አብዛኛው ገንዘብ የሚጠፋው እራስን ለማርካት፣ እራስን ለማስደሰት ምንም መልካም ነገር በማያመጡልን እንዲያውም በእርግጥ በሚጎዱን ነገሮች ላይ ነው። እግዚአብሔር የመልካም ነገር ሁሉ ሰጪ እንደሆነ ብናስተውል፤ ገንዘቡ የእርሱ እንደሆነ ቢገባን፤ የእርሱን ቅዱስ ፈቃድ በሚስማማ መልኩ በጥበብ እንጠቀምበታለን፤ ዓለም ከነ ልማዱና ከነ ፋሽኑ ደረጃችንን የሚመጥን አይሆንም፤ ዓለም እንደሚያደርገው ለማድረግ ፍላጎቱ አይኖረንም፤ ዝንባሌዎቻችን እንዲቆጣጠሩን አንፈቅድላቸውም። 4Letter 8, 1889.AHAmh 266.5

    የገንዘብ አጠቃቀማችን ለመንፈሳዊ ነገር መጎልበት የሚረዳ ሥራ የሚያስፈጽም የተቀደሰ አደራ እንጂ ለጉራ፣ ለከንቱነት፣ ለሆድና ለተግበሰበሰ ፍላጎት የሚውል አይደለም። 5Letter 8, 1889.AHAmh 267.1

    ለእግዚአብሔር የተሰጠውን ወደ ጎተራውም የገባውን እያንዳንዱን ሥጦታ፤ የተሰጠውም ሥጦታ ምን ተሠርቶበት ምን ውጤት እንዳስገኘ በታማኝነት መልአክ ሲመዘግበው አይቻለሁ። ለእርሱ ጉዳይ የተሰጠችውን እያንዳንዷን ሳንቲም እንዲሁም የሰጪውን የልብ ፈቃደኝነት ወይም ንፉግነት እግዚአብሔር ይመለከታል። ሰዎች በውስጣቸው ምን አስበው ሥጦታውን እንደለገሱ የሚያሳይ መዝገብ አለው። 6Testimonies for the Church, Vol. 2, pp. 518, 519.AHAmh 267.2

    ቤተሰቡ እንዲለግስ የማድረግ ዘዴ (Systematic Giving)፦ “እያንዳንዱም ከእርሱ ዘንድ ያኑር እንደ ተቻለው” ከታላቁ እስከ ታናሹ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በዚህ የቸርነት ተግባር ላይ መሳተፍ ይችላል…. በእቅድ የሚደረግ የበጎ አድራጎት (systematic benevolence) *ማስታወሻ፡- ቀደም ብሎ ቤተ-ክርስቲያን ስትከተለው የነበረችው ሳምንታዊ የአሥራትና የሥጦታ ገ ንዘብ አመላለስ (Systematic giving) የሚባለው ነው፡፡ እዚህ ላይ መግለጫ የተሰጠበት - አዘጋጆች፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ ገንዘቡን አላስፈላጊ ነገር ላይ ከማዋል ፈተና እንዲጠበቅ ይረዳዋል፤ በተለይም ሀብታሞች አባካኝነት የሚንፀባረቅበት ራስን የማርካት ተግባር ላይ እንዳይጠመዱ ይጠብቃቸዋል። በየሣምንቱ እግዚአብሔር ከእያንዳንዱ ቤተሰብ የሚጠይቀው ጥያቄ ወደ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አዕምሮ እንዲመጣ በማድረግ እቅዱ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ያደርጋል። ወደ ጎተራው ከሚያስገቡት ገንዘብ ያተርፉ ዘንድ ከሚያስፈልጋቸው በላይ እንዳይጠቀሙ፣ እራሳቸውን መግታታቸው ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉም እራሳቸውን መካዳቸውን የሚያስተምር ወርቃማ ትምህርት በልባቸው ይቀርፃል። በሣምንት አንድ ጊዜ እያንዳንዱ አባል ባለፈው ሣምንት የተከናወነውን ይመለከታል፤ ቆጣቢ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ገቢ ሊኖረው እንደሚችልና ለግላዊ እርካታው ሲል ያጠፋው ገቢው ምን ያህል እንደሆነ እንዲያስተውል ይረዳዋል። በእግዚአብሔር ፊት እንደሆነ ሁሉ የሰውየው ሕሊና በቁጥጥር ሥር ይደረጋል፤ ትክክለኛ ምሪት ያገኝ ዘንድ ጭንቅላቱ ያደፋፍረዋል ወይም ይወቅሰዋል። ይህ ሰው የእግዚአብሔር ሞገስና የአዕምሮ ሠላም ካለው የሚበላው የሚጠጣውና የሚለብሰው ሁሉ ለጌታ ክብር መሆን እንዳለበት ይማራል። 7Id., Vol. 3, p. 412.AHAmh 267.3

    የእግዚአብሔር ፈቃድ መጀመሪያ ይሁን፦ እግዚአብሔር የሚፈልግብን ነገሮች መጀመሪያ ይሁኑ። ዓይነ-ሕሊናችን የፈቀደውን ሁሉ ካሟላን በኋላ ከገቢያችን የተረፈውን ለእግዚአብሔር ብንቀድሰው እንደ ፈቃዱ እያደረግን አይደለም። ከገቢያችን ከመቅመሳችን በፊት ለእርሱ የሚገባውን ድርሻ መለየት አለብን። በድሮው የኃይማኖት ሥርዓት የምሥጋና መስዋዕት በመሰውያው ላይ ሁልጊዜ ይነድ ነበር፤ ይህም የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ያለበትን የማይቆም ግዴታ የሚያመላክት ነበር። ኃይማኖታዊ ድርጅት ባልሆነ የንግድ ሥራችን ብልጽግናን ብናገኝ ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠን በረከት ነው። ከዚህ ገቢ የተወሰነው ለድኆች አብዛኛው ደግሞ ለእግዚአብሔር ሥራ መዋል አለበት። ለእግዚአብሔር የሚገባው ሲሰጠው የቀረው እንጠቀምበት ዘንድ የተቀደሰና የተባረከ ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚጠይቀውን ሰው ሳይሰጥ ሲቀር መርገም በሁሉም ላይ ይወርዳል። 8Id., Vol. 4, p. 477.AHAmh 267.4

    ምስኪን ድሆችን አስታውሱ፦ የክርስቶስን ባህርይ የምንወክል ከሆነ እያንዳንዱ የራስ-ወዳድነት ቅንጣት ከነፍስ ላይ ተለቅሞ መውጣት አለበት። እግዚአብሔር በእጃችን ያስቀመጠውን ሥራ ወደ ፊት ለመግፋት መለገስ የምንችለውን እያንዳንዱን ቃርሚያና ፍርፋሪ ሁሉ መስጠት ይኖርብናል። የሌሎች ቤተሰቦች ደህንነትና ጭንቀት በተለያየ መንገድ ወደ ማስተዋላችን ይምጣ፤ የተጎዱና የተቸገሩ ስቃያቸው ሊቃለልላቸው ይገባል። በዙሪያችን ስላለው የሰው ልጅ መከራ የምናውቀው በጣም በጣም ጥቂቱን ነው። ሆኖም በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ በከባድ መከራ ለሚያልፉ ነፍሳት አጣዳፊ እርዳታ ልናደርግላቸው ይገባናል። 9Manuscript 25, 1894.AHAmh 268.1

    በቅንጦት ነገሮች ላይ የሚባክነው ንብረት ድኆች ለምግብና ለልብስ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ያሳጣቸዋል። በአልባሳት በሕንፃዎች በቤት ዕቃዎችና በማስጌጫዎች የትምክህተኛነትን መንፈስ ለማርካት የሚወጣው ገንዘብ የተንኮታኮቱና በችግር ላይ ያሉ ብዙ ቤተሰቦችን ጭንቀት ማስታገስ የሚችል ነው። የእግዚአብሔር መጋቢዎች የተቸገሩትን መርዳት አለባቸው። 10Review and Herald, Dec. 8, 1896.AHAmh 268.2

    የእግዚአብሔር መፍትሔ ለራስ-ወዳድነትና ስግብግብነት፦ እራስን የመካድ ፍሬ የሆነው ለጋስነት ለሰጪው ትልቅ እርዳታ ነው። መልካም ለማድረግ ሲንከራተት፤ የተቸገሩትን ሲረዳ፤ የተራቆቱትን መሻት ሲያሟላ የነበረውን የእርሱን [የክርስቶስን] ሥራ በበለጠ ሙላት እንድንረዳው ትምህርት ያካፍለናል። 11The Youth’s Instructor, Sept. 10, 1907.AHAmh 268.3

    ቋሚ የሆነ እራስን የካደ በጎ አድራጎት፣ ተጣብቆ ከሚያበሰብስ የራስ-ወዳድነትና የስስታምነት ኃጢአት በሽታ የሚፈውስ የእግዚአብሔር መድኃኒት ነው። የራሱ ሥራ እንዲቀጥል እንዲሁም የተጎዱና የተቸገሩ ሁሉ ፍላጎት ይሟላ ዘንድ እግዚአብሔር በደንብ የሚሠራ የበጎ አድራጎት ሥርዓት ዘርግቷል። አደገኛና አሳሳች የሆነውን የስግብግብነት ኃጢአት ለመከላከል መስጠት ልማድ እንዲሆን እግዚአብሔር ደንግጓል። የማያቋርጥ ስጦታ ስስትን አስርቦ ይገድለዋል። ይህ የተዘረጋ የበጎ አድራጎት ወይም የልግስና አሠራር ሀብት በስስታሞች እጅ እንደገባ ሳይቆይ እንዲወሰድ፣ ራሳቸውም የእርሱ እንደመሆናቸው ለጌታ የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያቀደው ነው….AHAmh 268.4

    ይህን የእግዚአብሔር እቅድ የሆነውን የበጎ አድራጎት አሠራር በቋሚነት መተግበር፣ ስስታምነትን አድክሞ ለጋስነትን ያጠናክራል። ሀብት ከጨመረ እግዚአብሔርን ስለመምሰል የሚናገሩት ሰዎች እንኳን ልባቸውን ይጥሉበታል። የበለጠም ሲኖራቸው በጌታ ጎተራ የሚያስገቡት ያነሰ ይሆናል። የሀብት ብዛት ሰዎችን ራስወዳድ ያደርጋቸዋል። ማከማቸትም መጎምጀትን ያበረታታል፤ እነዚህ ርኩሰቶች በእንደዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ የበለጠ ይጠናከራሉ። እግዚአብሔር የተጋረጠብንን አደጋ ያውቃል፤ በሀብታችን ዙሪያም አጥር አስቀምጧል። የመልካም ልምድ ጉልበት በተቃራኒ አቅጣጫ የሚሠራውን ኃይል ይሰብረው ዘንድ የበጎ አድራጎትን ተግባር በቀጣይነት እንድንተገብረው እግዚአብሔር ይፈልጋል። 12Testimonies for the Church, Vol. 3, p. 548.AHAmh 269.1