Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የአድቬንቲስት ቤት

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ክፍል ፲፪—የቤተሰብ ኑሮ ደረጃዎች

    ምዕራፍ ሃምሳ ሁለት—የቤት አስተዳደር

    ወላጆች ሊከተሉት የሚገባ መመሪያ፦ በዓለም ብዙ ሰዎች ፍላጎታቸው ያረፈው በራሳቸው ጉዳት የማያመጡ ነገሮች ላይ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሕሊናቸው በነዚህ ነገሮች ይረካና ክርስቶስ ሊሰጣቸው የሚፈልገውን ታላቅና ከፍ ያለ መልካም ነገር ከመሻት ይታቀባሉ። እኛም ትህትና በጎደለው አካሄድ እነዚህ ሰዎች ዋጋ የሚሰጧቸውን ነገሮች ልናካክስባቸውና ልንቀማቸው መጣር አይገባንም። ይልቅስ የእውነትን ውበትና ክቡርነት ግለጹላቸው። ክርስቶስንና ማራኪነቱን እንዲያዩ ምሯቸው፤ ከዚያም ከእርሱ ከሚያርቋቸው ነገሮች ሁሉ ፈቀቅ ይላሉ። ልጆቻቸውን ለማሠልጠን ወላጆች ሊመረኮዙት የሚገባ መርህ ይህ ነው። እነዚህን ታናናሽ ፍጡራን የምትቀርቡበት ሁናቴ በክርስቶስ ፀጋ ለዘለዓለም ሕይወት የሚያበቃቸው ባህርያት እንዲቀረጽባቸው ሊያደርግ ይችላል። 1Manuscript 4, 1893.AHAmh 216.1

    የሰው ጥረት ከመለኮታዊ እርዳታ ጋር ተዳምሮ፣ ልጆቻቸው ፍፁማን መሆን ይችሉ ዘንድ ይህ የእናቶችና የአባቶች የዕድሜ ልክ ጥረትና ጥናት መሆን አለበት። የዚህን ሥራ አስፈላጊነትና ኃላፊነት እሺ ብለው የተቀበሉት ደግሞ ልጆችን ወደዚህ ዓለም ያመጡ ጊዜ ነው። 2Fundamentals of Christian Education, p. 67.AHAmh 216.2

    ቤትን ለማስተዳደር አስፈላጊ የሆኑ ደንቦች፦ እያንዳንዱ የክርስቲያን ቤት ደንብ ሊኖረው ይገባል። ወላጆችም በንግግራቸውና ለእርስ በእርስ በሚያሳዩት ጠባይ ልጆቻቸው እንዲከተሉት የሚመኙትን ዓይነት ባህርይ እራሳቸው በመተግበር ሕያው ምሣሌ ሊሆኑላቸው ይገባቸዋል…. ልጆችና ወጣቶች ለራሳቸው ክብር እንዲሰጡ፤ ለእግዚአብሔር ሐቀኛ ለመመሪያም ታማኝ ይሆኑ ዘንድ አስተምሯቸው። የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያከብሩና እንዲታዘዙት አሠልጥኗቸው። ከዚያም እነዚህ መመሪያዎች ሕይወታቸውን ይቆጣጠራሉ፤ ከሌሎች ጋር በሚመሠርቱት ጓደኝነት ውስጥም ተግባራዊ ይሆናሉ። 3Letter 74, 1896.AHAmh 216.3

    የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል አስፈላጊ ነው፦ የቤተሰብ አስተዳደር መሠረት የሆኑት መመሪያዎች ቸል እንዳይባሉ ሁልጊዜም ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በምድር ያሉት ቤተሰቦች በሰማይ ያለው ቤተሰብ ምሣሌ ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ዓላማ ነው። በትክክለኛው መስመር የሚመሩ ቤተሰቦች በቤት የሚያገኙት የመንፈስ ቅዱስ እርካታ ወደ ቤተ-ክርስቲያንም ይመጣል። 4Manuscript 80, 1898.AHAmh 216.4

    በቤት ውስጥ እንዲኖር እግዚአብሔር ያቀደውን ዓይነት አስተዳደር በትክክል መወከል ከሚችሉበት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት፣ ወላጆች እራሳቸው መለወጥና ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አውቀው እንደ ትንንሽ ልጆች ሐሳባቸውን ለየሱስ ማስረከብ አለባቸው። 5Review and Herald, Mar. 13, 1894.AHAmh 216.5

    የቤተሰብን ግንኙነት እግዚአብሔር እራሱ መሠረተው። በልጆች አስተዳደር አደጋ የሌለበት ምሪት መስጠት የሚችለው ቃሉ ብቻ ነው። የሰው ፍልስፍና እግዚአብሔር ከሚያውቀው በላይ የደረሰበት ግኝት የለም፤ በልጆች ግንኙነት ዙሪያም ከጌታችን የተሻለ የቀየሰው ብልህ ዘዴ አላየንም። ከፈጣሪያቸው የበለጠ የልጆችን ፍላጎት ሊረዳ የሚችል ማን ነው? በራሱ ደም ከገዛቸው ከእርሱ የበለጠ ደህንነታቸው የሚያገባውና በጥልቀት የሚሰማው ማን ነው? የእግዚአብሔር ቃል በጥንቃቄ ቢጠናና በታማኝነት ቢከበር፣ ርጉም በሆኑ ልጆች የተጣመመ ጠባይ ምክንያት የሚመጣው የነፍስ ስቃይ በቀነሰ ነበር። 6Signs of the Times, Nov. 24, 1881.AHAmh 217.1

    የልጆችን መብት አክብሩ፦ ልጆች ሊከበሩላቸው የሚገባ መብት እንዳላቸው አስታውሱ። 7Letter 47a, 1902.AHAmh 217.2

    ልጆች ወላጆቻቸው ዕውቅና ሊሰጧቸውና ሊያከብሯቸው የተገባቸው መጠይቆች አሏቸው። በዚህ ዓለም ጠቃሚ ክቡርና ተወዳጅ የሕብረተሰብ አካል የሚያደርጋቸውን፣ ከዚህም ሕይወት በኋላ ለሚመጣው ንጹህና ክቡር ማህበረሰብ የግብረ-ገብነት ብቃት የሚያገኙበትን ትምህርትና ሥልጠና የማግኘት መብት አላቸው። የአሁኑ ጊዜያቸውና የወደፊቱ ሕልውናቸው በስፋት የሚወሰነው፣ በልጅነትና በወጣትነት በሚመሠርቷቸው ልማዶች እንደሆነ ወጣቶች ሊማሩ ይገባቸዋል። ገና በሕፃንነታቸው መሸነፍንና ራስን መካድን እንዲሁም ለሌሎች ደስታ ደንታ መስጠትን ቢለማመዱ መልካም ነው። ግንፍል የሚለው ጠባያቸው ይለሰልስ ዘንድ በስሜት የሚወጣን ቃል መዋጥን፤ አድልኦ የሌለው ቸርነት ማድረግንና ለጋስነትን እንዲሁም ራስን መቆጣጠርን እንዲማሩ ያስፈልጋል። 8Fundamentals of Christian Edication, p. 67.AHAmh 217.3

    በጭፍን ፍቅር ለሚጃጃል ወላጅ፦ ጭፍን መውደድና ርካሽ የፍቅር መግለጫ ለረዥም ጊዜ ተለማምዳችሁት ይኖራል። አንገት ላይ ጥምጥም ማለት ቀላል ነው፤ ትክክለኛ ዋጋ እንዳላቸው በፍጹም መታዘዝ እስካልተረጋገጡ ድረስ ግን [ልጆቻቸው የሚያሳዩአቸው] የፍቅር መግለጫዎች ሊበረታቱ አይገባም። የራሳችሁን ፍላጎት ማርካታችሁና በእግዚአብሔር ለተደነገጉት ደንቦች ክብር አለመስጠታችሁ ፈጽሞ የከፋው አረመኔነት ማለት ያ ነው። አለመታዘዝን በሚያበረታታ ሁኔታ ማስተባበያ በመፈለግ እንዲህ ትላላችሁ:- “ልጄ ይወደኛል”፤ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ርካሽና አታላይ ነው። በጭራሽ ፍቅር አይደለም። በቤተሰቡ ውስጥ የሚያድገው እውነተኛ ፍቅር ዋጋ የሚያስከፍል ነው፤ በታዛዥነት የሚረጋገጥ ነውና….AHAmh 217.4

    የልጆቻችሁን ነፍስ የምትወድዱ ከሆነ ሥርዓት አስይዟቸው። ሆኖም ደጋግመው ሲስሟችሁና በተጋነነ የፍቅር ንግግር ሲያቀልጧችሁ አይናችሁ ይታወራል። ይህንንም ልጆቻችሁ ያውቁታል። እንደማቀፍና መሳም ያሉትን ውጫዊ መግለጫዎች ቀንሳችሁ ነገሮችን ፍርጥርጥ አድርጋችሁ ልጅ ለወላጅ የሚኖረው እውነተኛ ፍቅር ምን ምን እንደሚያካትት አሳዩአቸው። እነዚህ መግለጫዎቻቸው በታዛዥነታቸውና በአክባሪነታቸው የሚደገፉ ካልሆነ ለማታለልና ለማጭበርበር ዘዴያቸው እምቢ በሉ። 9Letter 52, 1886.AHAmh 217.5

    ጭፍን ፍቅርም ሆነ ተገቢ ያልሆነ ኃይለኝነት አታሳዩ፦ ጭፍን ፍቅርን እንደማናበረታታ ሁሉ ከመጠን ያለፈን ኃይለኝነትም ልናሳይ አይገባንም። ልጆች በግድ ወደ ጌታ ሊመጡ አይችሉም። ሊመሩ ይችላሉ፣ ሊነዱ ግን አይደለም። “በጎቼ ቃሌን ይሰማሉ። እኔም አውቃቸዋለሁ እርሳቸውም ይከተሉኛል።” ይላል ክርስቶስ። በጎች ድምጼን ይሰማሉ ወደ መታዘዝ መንገድም እንዲመጡ ይገደዳሉ አላለም፤ በልጆች አስተዳደር ፍቅር መታየት አለበት። አገናዛቢ ባልሆነ ኃይል በማስገደድ ወይም በሸካራነት ወላጆች ለልጆች ህመም ሊፈጥሩባቸው አይገባም። ጭካኔ ነፍሳትን ወደ ሰይጣን መረብ ይነዳቸዋል። 10Review and Herald, Jan. 29, 1901.AHAmh 218.1

    የሥልጣን፣ የኃይልና የፍቅር ጥምረት ተጽዕኖ የቤተሰብ አስተዳደር ልጓም በጥብቅ ሆኖም በየዋህነት እንዲያዝ ያስችላል። ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የተሰጠው ዓይናችን እንዲሁም ለልጆቻችን ምን ያህል ባለውለታቸው እንደሆነ ስናስብ፣ ልጆቻችንን መረን ለቅቀን ለርኩሰት ፈቃድ እንዳንሰጥ እንታቀባለን። 11Manuscript 24, 1887.AHAmh 218.2

    ቁጡነት ለታዛዥነት አስፈላጊ አይደለም፦ መታዘዝ እንዲኖር ቁጡነትና ጭካኔ አስፈላጊዎች ናቸው ብሎ…. ማንም እንዳያስብ። ከባድ ቃላት ወይም ቁጡ ፊት ሳያስፈልገው ወደር በሌለው ብቃት የሚተዳደር ቤተሰብ አይቻለሁ። አለቃው ማን እንደሆነ በሚያሳውቅ ድምፅ ትዕዛዛት በተደጋጋሚ የሚወጣባቸው ከባድ ተግሳጽና የጭካኔ ግርፋት የሚካሄድባቸው ቤተሰቦችንም አይቻለሁ። በመጀመሪያው ቤተሰብ ልጆች ወላጆቻቸው የሚከተሉትን አካሄድ የያዙ ለእርስ በእርሳቸው መልካም ባልሆኑ ቃላት ብዙም የማይነጋገሩ ነበሩ። በሁለተኛው ቤተሰብ የወላጆች ምሣሌ በልጆች ተደግሞ ነበር፤ መሰዳደብን መወነጃጀልንና ጠብን ከጠዋት እስከ ማታ ሲያሰሙ ይውሉ ነበር። 12Signs of the Times, Mar. 11, 1886.AHAmh 218.3

    የሚያንቀጠቅጡ ቃላት ፍርሃት በመፍጠር ፍቅርን ከነፍስ የሚያባርሩ ስለሆኑ ሊገቱ ይገባቸዋል። ብልህ የዋህና እግዚአብሔርን የሚፈራ አባት ፍቅርን እንጂ የሚያንቦጀቡጅ ፍርሃት ይዞ ወደ ቤት አይገባም። ከሕይወት ውኃ የምንጠጣ ከሆነ ምንጩ የሚያፈልቀው ጣፋጭ ውኃን እንጂ እሬትን አይደለም። 13Letter 8a, 1896AHAmh 218.4

    ሻካራ ቃላት ጠባይን የሚያኮመጥጡና የልጆችን ልብ የሚያቆስሉ ናቸው፤ በአንዳንድ ሁኔታዎችም እነዚህ ቁስሎች ለመሻር የሚከብዱ ናቸው። ልጆች ትንሽዋ የፍርድ መጓደል እንኳ በጣም ትሰማቸዋለች። አንዳንዶችም ተስፋ በመቁረጥ አባታቸው የሚያንቧርቀውን ቁጡ የትዕዛዝ ጩኸት አይሰሙም፤ ለቅጣት ማስፈራሪያም ቁብ አይሰጡም። 14Testimonies for the Church, Vol. 3, p. 532.AHAmh 218.5

    ጥቃቅን ነገሮችን በከባድ ሁኔታ ተመልክቶ መኮነን አደጋ አለው። ከመጠን ያለፈ ትችትና ያለቅጥ ግትር የሆኑ ሕጎች ሁሉንም ደንቦች ቸል ወደ ማለት የሚመሩ ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተማሩ ልጆች ለክርስቶስ ሕግጋትም እንዲሁ አክብሮት-የለሽነታቸውን ያሳያሉ። 15Manuscript 7, 1899.AHAmh 219.1

    ወጥና አንድ ዓይነት ጥብቅነትና ስሜታዊ ያልሆነ ቁጥጥር ያስፈልጋል፦ ልጆች ምላሽ ሰጭና አፍቃሪ ተፈጥሮ አላቸው። በቀላሉ ደስተኛ ይሆናሉ፤ በቀላሉ ሊዝናኑም ይችላሉ። በገራም ሥነ-ሥርዓት ደስ በሚያሰኝ ቃላትና ተግባር እናቶች ልጆቻቸውን ከልባቸው ጋር ማቆራኘት ይችላሉ። ጭካኔን ማሳየት ልቅም ያለና ነቁጥ የሌለበት ሥራ ከልጆች መጠበቅ ትልቅ ስህተት ነው። ለእያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የተቀመጠው መመሪያ ተመሳሳይ የሆነና ቁጥጥራችሁም ግንፍል በሚል ስሜት የማይፈጸም መሆኑ አስፈላጊ ነው። ማለት የምትፈልጉትን ተረጋግታችሁ ተናገሩ፤ በማመዛዘን ተንቀሳቀሱ፤ ከተናገራችሁት ፈቀቅ ሳትሉ ፈጽሙት።AHAmh 219.2

    ከልጆቻችሁ ጋር ባላችሁ ህብረት የምታሳዩት ፍቅር መልሶ የሚከፈላችሁ ነው። በልጅነት ጨዋታቸው ደስታቸውና ሐዘናቸው ሁሉ በርኅራኄ እጦት ልጆቻችሁን አትግፏቸው። ግንባራችሁ አይቋጠር፤ ከርዳዳ ቃላትም ከአፋችሁ አይውጣ። እግዚአብሔር እነዚህን ቃላት ሁሉ በመዝገቡ ይጽፋቸዋል። 16Testimonies for the Church, Vol. 3, p. 532.AHAmh 219.3

    ቁጥጥርና ማስጠንቀቂያ በቂ አይደለም፦ ውድ ወንድሞች ሆይ እንደ ቤተ-ክርስቲያን ለልጆችና ለወጣቶች ያላችሁን ኃላፊነት በአሳዛኝ ሁኔታ ቸል ብላችሁታል። ሕግና ቁጥጥር ተጭኖባቸው ሳለ የክርስቶስ መሰል ባህርያችሁን እንጂ ሰይጣናዊ ጎናችሁን እንዳታሳዩአቸው ተጠንቀቁ። ልጆች ቋሚ እንክብካቤና ለስላሳ ፍቅር ይፈልጋሉ። ከልባችሁ ጋር ይቆራኙ፤ የእግዚአብሔር ፍቅርና ፍርሃት በፊታቸው ይሂዱ። የራሳቸውን ስሜት የማይቆጣጠሩ ወላጆች ሌሎችን ማስተዳደር አይችሉም። ከእናንተ የሚጠበቀው ልጆቻችሁን መቆጣጠርና ማስጠንቀቅ ብቻ አይደለም። እናንተ እራሳችሁ ትክክል የሆነውን ልታደርጉ፤ምህረት ማድረግን ልትወዱ ይገባል። እንዲሁም ዝቅ ብላችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ልትራመዱ መማር ያስፈልጋችኋል። 17Id., Vol. 4, p. 621.AHAmh 219.4

    በባህርይዋ ግትር የሆነች ልጅ ላላት እናት የተሰጠ ምክር፦ ልጅሽ የግልሽ አይደለችም፤ የጌታ ንብረት ናትና እንደ ፈለግሽ ልታደርጊያት አትችይም። በማያቋርጥ ጽኑ ቁጥጥር ሥር አድርጊያት፤ የእግዚአብሔር እንደሆነች አስተምሪያት። በእንደዚህ ዓይነት ትምህርት ስታድግ በዙሪያዋ ላሉ ሁሉ በረከት ትሆናለች። ግልጽነትና ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት ዕውቀት ሊኖርሽ ግን ይገባል። ምክንያቱም ሁለታችሁንም ሊቆጣጠር የሚፈልገውን ዝንባሌዋን እንዲሁም የራስዋን ፈቃድና መንገድ እንደፈለገች የመምራት አካሄዷን መግታት እንድትችይ ነው። 18Letter 69, 1896.AHAmh 219.5

    ተመሳሳይና ወጥ የሆነ አስተዳደር፦ በንግግርና በስምምነት ሁሉንም በመልካም ማለፍ ሲቻል ቁጥጥር በማብዛት ብዙ ቤተሰቦች ሲንኮታኮቱ አይቻለሁ። የአስተዳደር መዋዠቅ በቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል። እንዲያውም ከአስተዳደር ጨርሶ አለመኖር አይተናነስም። ሁሌም የሚጠየቅ ጥያቄ አለ:- የሃይማኖተኛ ወላጆች ልጆች ሁልጊዜ ግትር፣ ዕምቢተኛና አመጸኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ምክንያቱ ያለው በቤት ውስጥ በሚሰጠው ስልጠና ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች በቤተሰብ አስተዳደር አንድ ዓይነት አቋም ይዘው የሚተባበሩ አይደሉም። 20Signs of the Times, Feb. 9, 1882.AHAmh 220.1

    የሚለዋወጥ አስተዳደር - ማለትም አንዳንድ ጊዜ ጥብቅ ሆኖ መስመር ማስያዝ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተወገዘውን ነገር መፍቀድ - ልጅን የሚያጠፋ ነገር ነው። 21Letter 69, 1896.AHAmh 220.2

    የጋራ ሕግ ለወላጆችና ለልጆች፦ እግዚአብሔር ሕግ ሰጫችንና ንጉሣችን ነው። በመሆኑም ወላጆች በእርሱ ሕግ ሥር መገዛት ይኖርባቸዋል። ይህ ሕግ ማንኛውንም ጭቆና ከወላጆች ሁሉንም አለመታዘዝ ከልጆች የሚከለክል ነው። ጌታ በአፍቃሪ ቸርነት በምህረትና በእውነት የተሞላ ነው። ሕጉ ቅዱስ ቅንና መልካም ነውና በወላጆችም ሆነ በልጆች ሊከበር የተገባው ነው። የወላጆችንና የልጆችን ሕይወት የሚቆጣጠረው ደንብ ከዘለዓለማዊ የፍቅር ልብ የሚፈስ ነው። የእግዚአብሔርም የተትረፈረፈ በረከት ሕጉን በቤታቸው በሚተገብሩ ወላጆችና ይህንን ሕግ በሚጠብቁ ልጆች ላይ ይወርዳል። የምህረትና ፍርድ ጥምር ተጽዕኖ ሊታወቅ ይገባል “ቸርነትና እውነት ተገናኙ፣ ጽድቅና ሠላም ተሳሳሙ።” በዚህ ሥነ-ሥርዓት ሥር ያሉ ቤተሰቦች በጌታ መንገድ የሚራመዱና በቅን የሚፈርዱ ይሆናሉ። 22Manuscript 133, 1898.AHAmh 220.3

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents