Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የአድቬንቲስት ቤት

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ምዕራፍ ሃያ ስምንት—የልጅ የመጀመሪያው ትምህርት ቤት

    እግዚአብሔር ለትምህርት የነበረው የመጀመሪያው ዕቅድ፦ በኤደን የተመሠረተው የትምህርት ደንብ ቤተሰብን ማዕከል ያደረገ ነበር። አዳም “የእግዚአብሔር ልጅ” ነበር (ሉቃ 3፡38)። ትምህርት ከላይኛው አባታቸው ከልዑል እግዚአብሔር ተቀበሉ። ያ ትክክለኛ ትርጉሙን የተገበረ የቤተሰብ ትምህርት-ቤታቸው ነበር።AHAmh 121.1

    ከውድቀቱ በኋላ ለሰው እንዲስማማው ተደርጎ በመለኮታዊ እቅድ ለተዘጋጀው ትምህርት ክርስቶስ የአባቱ ወኪል ሆኖ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የመገናኛ መንገድ ሆነ፤ እርሱ ታላቁ የሰው ዘር መምህር ነው። ሴቶችና ወንዶች ደግሞ የእርሱ ወኪል እንዲሆኑ ሾማቸው። ቤተሰቡ ትምህርት ቤት፣ ወላጆች ደግሞ መምህራን ነበሩ። AHAmh 121.2

    ቤተሰብ-ተኮር የሆነው ትምህርት በመሳፍንት ጊዜ ተሰፋፍቶ የነበረውን ይመስል ነበር። ያኔ ለተመሠረቱት ትምህርት ቤቶች መልካም ባህርያት እንዲጎለብቱ የሚያደርገውን ምቹ ሁኔታ እግዚአብሔር አዘጋጀ፤ በእርሱ ምሪት ሥር የነበሩት ሕዝቦች በመጀመሪያ አቅዶት የነበረውን ዓላማ የሚከተሉ ነበሩ። ከእግዚአብሔር የተለዩ እነርሱ ለራሳቸው ከተማዎችን ቆረቆሩ፤ ተከማቹባቸውም፤ የዛሬው ዓለም ኩራት ሆኖም እርግማን የሆኑትን ከተሞች በውበታቸው፣ በምቾቶቻቸውና በዝሙታቸው ተመኩባቸው። የእግዚአብሔርን መመሪያ በጥብቅ የያዙ ግን በኮረብታውና በመስኩ መኖሪያቸውን አደረጉ፤ ገበሬዎች፣ የከብትና የበግ መንጋ ጠባቂዎች ነበሩ። በዚህ ነፃና ግላዊ በሆነ ሕይወት ለመሥራት፣ ለማጥናትና በጥልቀት ለማሰብ እድል በሚፈጥረው ቦታ ስለ እግዚአብሔር ተማሩ፤ ስለ ሥራውና መንገዱ ልጆቻቸውን አስተማሩ። እግዚአብሔር በእራኤል ላይ ሊመሠርተው የወደደው የትምህርት ዑደት ይህ ነበር።1Education, pp. 33, 34.AHAmh 121.3

    ያልተወሳሰበው የቤተሰብ ሕይወት ለቤተሰቡ ትምህርት ቤትም፣ ቤተ-ክርስቲያንም ነበር፤ ወላጆች የምድራዊ አኗኗርና የሃይማኖታዊ ትምህርት መምህራን ነበሩ።2 Id., p. 41.AHAmh 121.4

    የቤተሰብ ክበብ ትምህርት ቤት ነው፦ እግዚአብሔር በጥበቡ ቤተሰብ ከሁሉም የበለጠ የትምህርት ተቋም እንዲሆን አውጇል። የልጁ ትምህርት የሚጀምረው በቤት ውስጥ ነው። ይህ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ነው። በወላጆቹ መምህርነት አማካይነት ዕድሜ-ልኩን የሚመሩትን ባህርያት ማለትም አክብሮትን፣ መታዘዝን፣ ራስን መቆጣጠርንና ውዳሴን ይማራል። በቤት የሚያገኛቸው ሥልጠናዎች ለመልካም ወይም ለክፋት እንደሚያዘጋጁት እርግጥ ነው። በአብዛኛው በዝምታ የሚናገሩና ቀስ በቀስ የሚሰርጹ ናቸው፤ ሆኖም በትክክለኛው መንገድ ከተተገበሩ መጠነ-ሰፊ የሆነ የእውነትና የጽድቅ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ልጁ እውነተኛውን ትምርት አሁን ካልተማረ ሰይጣን በመረጣቸው ወኪሎቹ ያስተምረዋል። በቤት ውስጥ ያለው ትምህርት ቤት እንዴት አስፈላጊ ነው!3Counsels to Teachers, Parents, and Students, p. 107.AHAmh 121.5

    የቤተሰቡ ክበብ የሥልጠና ትምህርት ቤት እንደሆነ አድርጋችሁ ውሰዱት። በቤት ውስጥ፣ በማህበረሰቡና በቤተ-ክርስቲያን ዙሪያ ያለባቸውን የሥራ ድርሻ በብቃት እንዲወጡ የምታስተምሩበት ነው። 4Signs of the Times, Sept. 10, 1894.AHAmh 122.1

    ከጠቀሜታው አኳያ ሲታይ የቤት ውስጥ ትምህርትን የሚስተካከለው የለም፦ የቤት ውስጥ ትምህርትና ሥልጠና በአሁኑ ወጣት ቸል መባሉ ዓለም ያወቀው አሳዛኝ ክስተት(እውነታ) ሆኗል።5Review and Herald, Aug. 30, 1881.AHAmh 122.2

    ለቤት መሥራቾችና ጠባቂዎች የተሰጠ ከዚህ የሚበልጥ የሥራ መስክ የለም። ለሰው ልጅ በአደራነት ከተሰጠው ሥራ ሁሉ የሚበልጠው፣ ወሰነ ሰፊ የሆነ ተጽዕኖ ያለው ለወላጆች የተሰጠ ሥራ ነው። በአሁኖቹ ልጆችና ወጣቶች ነው የወደፊቱ ህብረተሰብ የሚወሰነው፤ እነዚህ ልጆችና ወጣቶች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሚሆኑ የሚወስነው ደግሞ በቤት ነው። ለሰው ዘር እርግማን የሆነው በሽታ፣ ስቃይና ወንጀል ምንጩ በአብዛኛው በትክክለኛው መንገድ ለቤተሰቡ ሥልጠና ያልሰጠ ቤት ነው። የቤት ውስጥ ሕይወት ንጹህና እውነተኛ ቢሆን ኖሮ ከእንክብካቤውና ከእቅፉ የሚወጡት ልጆች ለኑሮ ኃላፊነቶችና አደጋዎች በጥሞና ተዘጋጅተው ቢሆኑ ኖሮ በዓለም ምን ዓይነት ለውጥ በታየ ነበር! 6Ministry of Healing, p. 351.AHAmh 122.3

    ሌላው ሁሉ ቀጥሎ የሚመጣ(ሁለተኛ) ነው፦ ወደ ዓለም የመጣ እያንዳንዱ ልጅ የየሱስ ክርስቶስ ንብረት ነው። በመሆኑም እግዚአብሔርን እንዲወድና እንዲታዘዘው ምክርና በተምሳሌነት የተደገፈ ትምህርት ያስፈልገዋል። ሆኖም ከመጀመሪያው ግንዛቤ ጀምሮ ልጆቻቸው ክርስቶስን እንዲያወቁትና እንዲወዱት እንዲያስተምሩ በእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሥራ አብዛኛዎቹ ወላጆች ቸል ብለውታል። ወላጆች ሌላውን የቤት ኃላፊነት ሁሉ ሁለተኛ ደረጃ ሰጥተው፣ ክፍትና ለመቀበል ዝግጁ የሆነውን የልጆቻቸውን አዕምሮ በማሠልጠን በእግዚአብሔር በራሱ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በመስማት መልካሙን ግዴታቸውን በብቃት ይወጡ ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።7Manuscript 126, 1896.AHAmh 122.4

    ወላጆች ልጆቻቸውን ገና በጨቅላነታቸው እንዲተዉ፣ ከፍ እያሉ ሲሄዱም አስፈላጊውን ትምህርት እንዳይለግሱ ከሚያደርጓቸው የሥራ ሐሳቦችና ጭንቀቶች፣ ዓለማዊ ልማዶችና መመሪያዎች እንዲሁም በፋሽን ቁጥጥር ሥር መሆንን ለራሳቸው መፍቀድ የለባቸውም።8Signes of the Times, Sept. 17, 1894.AHAmh 122.5

    ዛሬ በዓለማችን እንዲህ ርኩሰት እንዲበዛ ካደረጉት ዋና ምክንያቶች አንዱ ሰዎች እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ተግባር ገሸሽ ብለው አዕምሮአቸውን በሌሎች ነገሮች ስለሞሉ ነው። የተውት ነገር ልጆቻቸው የእግዚአብሔርን መንገድ ይከተሉ ዘንድ እንዴት እራሳቸውን አስተካክለው በትዕግስትና በቸርነት መሥራት እንደሚችሉ ማወቅን ነው። መጋረጃው ቢገለጥና ብናስተውል በወላጆች ቸልተኝነት ምክንያት ከትክክለኛው መንገድ ያፈነገጡና ለመልካም ተጽዕኖም የሞቱ ብዙ፤ ብዙ ልጆች ማየት እንችላለን። ወላጆች ሆይ በሕይወታችሁ ይህ ይፈጸም ዘንድ ይቻላችኋል? እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ መታዘዝና ማመን ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባቸው ታስተምሯቸው ዘንድ አስፈላጊውን ጊዜ ሁሉ ከመስጠት የሚያግዳችሁ ከዚህ የበለጠ ጠቃሚ ሥራ አይኑራችሁ….AHAmh 123.1

    ለዚህ ጥረታችሁ ታዲያ ሽልማታችሁ ምንድን ነው? የምትጠቁሙትን መስመር ሊከተሉ፤ የምትሉትን ነገር ሊቀበሉና ከእናንተ ጋር ሊተባበሩ ፈቃደኛ የሆኑ ከጎናችሁ የሚቆሙ ልጆች ታፈራላችሁ፤ ሥራችሁ በእጅጉ ተቃሎላችሁ ታገኙታላችሁ።9Manuscript 53, 1912.AHAmh 123.2

    የእግዚአብሔር አስተማሪዎች በቤት ትምህርት ውስጥ፦ ልክ አብርሃም እንዳደረገው ሁሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ያስተምሩ ዘንድ በእግዚአብሔር የተወከሉ እንደሆኑ አድርገው የተለየ ስሜት ሊሰማቸው ይገባል። የእግዚአብሔርን መንገድ እንዲያውቁ ለቤተሰቦቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሉን በትጋት ይመርምሩ። ትንቢተ ሚክያስ እንዲህ ይላል “ፍርድ ታደርግ ዘንድ አይደለምን ምህረትም ትወድ ዘንድ ከአምላክህም ጋር በትህትና ትሄድ ዘንድ” አይደለምን?። መምህራን ለመሆን መጀመሪያ ወላጆች መማር ያስፈልጋቸዋል። ከእግዚአብሔር ቃል የማያቋርጥ ብርሃን በመሰብሰብ በመመሪያነትና በምሣሌነት ይህንን የከበረ ብርሃን ወደ ልጆቻቸው ትምህርት ማምጣት ያስፈልጋቸዋል።10Christian Temperance and Bible Hygiene, p. 145.AHAmh 123.3

    ባልና ሚስት በቤት ውስጥ ለልጆቻቸው አገልጋይ፣ ሐኪም(ዶክተር) ነርስ እንዲሁም መምህር በመሆን እራሳቸውንና ልጆቻቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ሊያቆራኙ፤ አምላክ በአካላቸው ላይ ሊሠራ ያለውን ከሚያስቀር ነገር ሁሉ እንዲርቁ ሊያሠለጥኗቸው፤ ለእያንዳንዱም የአካል ብልት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሊያስተምሯቸው ይገባቸዋል። ከእግዚአብሔር ባገኘሁት ብርሃን የተረዳሁት ይህንን ነው።11Manuscript 100, 1902.AHAmh 123.4

    ልጆችን በማሠልጠን ረገድ እናት የላቀውን ደረጃ ይዛ መገኘት አለባት። ከባድና አስፈላጊ ኃላፊነት በአባት ላይ የወደቀ ቢሆንም በተለይ በጨቅላ ዕድሜአቸው እናት ባላት ያልተቋረጠ አብሮነት ሁልጊዜም ጓደኛቸውና ልዩ መምህራቸው ልትሆን ይገባታል። በልጆችዋ ውስጥ ንጽህናና ሥርዓት እንዲጎለብቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ታድርግ። ትክክለኛ ልምድና ምርጫ እንዲቀረጽባቸው ትምራቸው። ታታሪዎች፣ ራሳቸውን መርዳት የሚችሉና ሌሎችን የሚያግዙ እንዲሆኑ በኑሮአቸው፣ በሥራቸውና በማንኛውም እንቅስቃሴአቸው ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ዕይታ ሥር እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጋ ታሠልጥናቸው።12Pacific Health Journal, January, 1890.AHAmh 123.5

    ታላላቅ እህቶች በታናናሽ የቤተሰቡ አባላት ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላሉ። ሁልጊዜ ከሚደጋገመው የወላጅ መመሪያ ይልቅ፣ ታላላቆቻቸው የሚያደርጉትን በማየት እንደ እነርሱ ለመሆን ባላቸው ምኞት ታላላቆቻቸው የሚያደርጉትን ለመድገም ሲጥሩ ታናናሾች ይማራሉ። በዕድሜ ከሁሉ የምትበልጠው ሴት ልጅ ላብ አንጠፍጣፊ የሆነውን የእናትዋን ሸክም ማቃለል ክርስቲያናዊ ግዴታዋ እንደሆነ ሊሰማት ይገባል።13Testimonies for the Church, Vol. 3, p. 337.AHAmh 124.1

    ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ በቤት መገኘት አለባቸው። በምሣሌነትና በምክር ልጆቻቸው እግዚአብሔርን እንዲወዱትና እንዲፈሩት ያስተምሯቸው። ጎበዝ፣ ተግባቢና አፍቃሪ እንዲሆኑ ታታሪነትንና ንብረትን በብቃት የማስተዳድር ችሎታን እንዲሁም ራስን መካድ እንዲያጎለብቱ ያስተምሯቸው። ወላጆች ለልጆቻቸው በቤትውስጥ ፍቅር፣ ርኅራኄና ብርታት በመስጠት ከብዙው የዓለም ፈተና ማምለጫ ሥፍራ ሊያዘጋጁላቸው ይችላሉ።14Fundaments of Christian Education, p. 65.AHAmh 124.2

    ለቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ቤት ዝግጅት፦ ሴቶችና ወንዶች ልጆችን ለቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ቤት የምናዘጋጃቸው በቤት ውስጥ ነው። ወላጆቸ ይህን ሁልጊዜ በአዕምሮአቸው በማስቀመጥ የቤት መምህራን እንደመሆናቸው ልጆቻቸው ከፍተኛውንና የተቀደሰውን ተልእኮአቸውን ጥግ ያደርሱ ዘንድ ኃይላቸውን ሁሉ ለእግዚአብሔር መቀደስ ይኖርባቸዋል። ትጉህና ታማኝ የቤት ውስጥ ሥልጠና ላቂያ (የበለጠ) ለማይገኝለት የትምህርት ቤት ሕይወት የሚያዘጋጅ ተግባር ነው።15Counsels to Teachers, Parents, and Students, p. 150.AHAmh 124.3

    የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ዋነኞቹ ይሁኑ፦ ወላጆችንም ሆነ ልጆችን የሚመራ ቅዱስና ከፍ ያለ ደረጃ የያዘ፣ መዋዠቅ ሊኖርበት የማይችል ለሁሉም የተሰጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ አለን። የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የላቀውን ደረጃ መያዝ አለባቸው። የቤተሰቡ እናትና አባት ልብን በሚመረምረው በእግዚአብሔር ፊት ቃሉን ዘርግተው በእውነት “እግዚአብሐር ምን አለ”? ብለው ይጠይቁ።16Review and Herald, Sept. 15, 1891.AHAmh 124.4

    ወደ ታላቁ ሥራ ለመግባት ብቁ በመሆን የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል፣ የሰማያዊ ንጉሥ ልጆች ለመሆን የተገባቸው እንደሆኑ ለማረጋገጥ በሚከፈተው ሰማያዊ ችሎት ፊት ለታላቁ የፍርድ ምርመራ መቆም ይችሉ ዘንድ በቅድስና የሚያጸናቸው እውነት ነውና፣ እውነት እውነት ስለሆነ ብቻ እንዲወዱት ለልጆቻችሁ አስተምሩ።17Signs of the Times, Sept. 10, 1894.AHAmh 125.1

    ለሚመጣው ተጋድሎ ተዘጋጁ፦ ሰይጣን ሠራዊቱን እያሰለፈ ነው። ለዚህ በፊታችን ላለው አስፈሪ ጦርነት በግላችን ተዘጋጅተንበታል? ለታላቁ መከራ ልጆቻችንን እያዘጋጀን ነው? የጠላቶቻችንን አቀማመጥና የውጊያ ስልት ለመረዳት እራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን እያዘጋጀን ነው? በእያንዳንዱ መርህና የኃላፊነት ጉዳይ ላይ ፍንክች የማይል አቋም መያዝ ይችሉ ዘንድ ልጆቻችን የውሳኔ ሰዎች እየሆኑ ነው? በጦርነቱ ጊዜ እግዚአብሔር መከታችንና መጠለያችን ይሆን ዘንድ እራሳችንና ልጆቻችን እንድናዘጋጅ ሁላችንም የዘመኑን ምልክቶች ከወዲሁ እናስተውል ዘንድ ጸሎቴ ነው።18Review and Herald, April 23, 1889.AHAmh 125.2