Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የአድቬንቲስት ቤት

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ ሰባ አንድ—ንግግር

    ድምፅ ተሰጥኦ ነው፦ ድምፅ በአደራ የተሰጠ ክህሎት ነው። መሰል ወገኖችን ለመርዳት ለማበረታታትና ለማጠንከር እንጠቀምበት ዘንድ የተሰጠ ነው። ፍርድና ቅንነት ያደርጉ ዘንድ ወላጆች እግዚአብሔርን ቢወዱና የጌታንም መንገድ ቢከተሉ ቋንቋቸው ጤናማ ያልሆነ ስሜት መገለጫ አይሆንም። እውነተኛ ንጽህና የማነጽ ባህርይ ይኖረዋል። በውጭም ሆኑ በቤት ውስጥ ቃሎቻቸው በጥንቃቄ የተመረጡ ይሆናሉ፤ ወደ ርካሽነት ዝቅ አይሉም።1Manuscript 36, 1899.AHAmh 317.1

    እያንዳንዱ ቃል ተጽዕኖ አለው፡- በአባቶችና በእናቶች የሚነገረው እያንዳንዱ ቃል በልጆች ላይ የመልካም ወይም የጥፋት ተጽዕኖ አለው። ወላጆች በስሜት የሚናገሩ ከሆነ፤ የዚህ ዓለም ልጆች የሚያሳዩትን መንፈስ የሚያንፀባርቁ ከሆነ፤ የሚያልፈው ዓለም ልጆች እንደሆኑ እንጂ የእርሱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንደሆኑ እግዚአብሔር አይቆጥራቸውም።2Manuscript 100, 1902.AHAmh 317.2

    በጊዜው የተነገረ ቃል በወጣት አዕምሮ እንደ መልካም ዘር ሊሆን፤ ለጋዎቹን እግሮች ወደ እውነተኛ መንገድ ሊመራ ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ አንድ የስህተት ቃል እግሮቻቸውን ወደ ጥፋት ጎዳና እንዲጓዙ ሊያደርግ ይችላል።3Review and Herald, June 24, 1890.AHAmh 317.3

    በቤት ውስጥ የሚነገሩትን ቃላት መላእክት ይሰሙአቸዋል። ስለዚህ ፈጽሞ አትሳደቡ፤ በምትኩ የምትናገሯቸው ቃላት ተጽዕኖ እንደሚያውድ እጣን ወደ ሰማይ የሚወጣ ይሁን።4Letter 10, 1912.AHAmh 317.4

    በለዘቡ ቃላትና ከአንጀት በሆነ አዘኔታ ወላጆች የቤትን ከባቢ አየር የሚያውድ መዓዛ ያድርጉት። ሆኖም ከመመሪያቸው ፍንክች የማይሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ለልጆቻችሁ ግትር ብትሆኑ እንደማትወዷቸው ሊያስቡ ይችላሉ። ሸካራነትን ግን ፈጽማችሁ አታሳዩዋቸው። ፍትህና ምህረት ይጨባበጡ፤ ተለዋዋጭነት ወይም ስሜታዊ እንቅስቃሴዎች መኖር የለባቸውም።5Review and Herald, March 30, 1897.AHAmh 317.5

    ቋንቋ የውስጣዊ ፀጋን ወደ ውጭ መግለጫ ይሁን፡- የቋንቋ ዋናው አስፈላጊ ነገር ንጹህ፣ ቸርና እውነተኛ መሆኑ ነው፤ “የውስጣዊውን ፀጋ ወደ ውጭ የሚገልጽ” ነው… ለዚህ ቋንቋ ጥናት ወደር የሌለው ትምህርት-ቤት፣ ቤት ነው።6Education, p. 235.AHAmh 317.6

    ደጋግ ቃላት ለነፍስ እንደ ማለዳ ጤዛ ቀስ ብሎም እንደሚወርድ ዝናብ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ሲናገር ፀጋ በከንፈሩ ላይ ፈሰሰ “የደከመውን በቃል እንዴት እንደሚደግፍ ያውቅ ዘንድ” ይላል። እግዚአብሔር ያዘናል፡- “ንግግራችሁ ሁልጊዜ በፀጋ ይሁን” “ለሚሰሙት ፀጋን ይሰጥ ዘንድ።” 7The Youth’s Instructor, March 31, 1908.AHAmh 317.7

    የድምፅ ቅላጼ እንዴት መሆን እንዳለበት በቤት መመሪያ መሰጠት አለበት፡- የድምፅ አወጣጥ ትምህርት ለቤቱ ክበብ መሰጠት አለበት። ልጆች ጥርት ባለ መልኩ እንዲናገሩና የሚያዳምጧቸው ሰዎች እያንዳንዱን ቃል በግልጽ መስማት እንዲችሉ ወላጆች ያስተምሯቸው። ጉልህና ግልጽ በሆነ አነጋገር እግዚአብሔርን በሚያስከብር አኳኋን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነብቡ ወላጆች ልጆቻቸውን ሊያስተምሩ ይገባቸዋል። በቤተሰቡ መሠውያ ዙሪያ የሚንበረከኩ ፊታቸውን በእጃቸው ወይም በወንበር ሸፍነው አይጸልዩ። በተቀደሰ አክብሮታዊ ፍርሐትና ልበ-ሙሉነት ራሳቸውን ወደ ፀጋው ዙፋን ቀና አድርገው ይም ጡ።8Manuscript 4, 1901.AHAmh 318.1

    በንግግራችሁ ንጹህ ሁኑ፤ የሚያመነጫጭቅና ፈላጭ ቆራጭ ሳይሆን ለስላሳና አሳማኝ የድምፅ ቃና አዳብሩ። ስለ ድምፅ አወጣጥ ልጆችን አስተምሩ። ፈተና በሚገጥማቸው ጊዜ ምንም ዓይነት ሸካራ ወይም ከርዳዳ ቃል በዘፈቀደ ከአፋቸው እንዳይወጣ የንግግር ልማዳቸውን አሠልጥኑ።9Manuscript 60, 1903.AHAmh 318.2

    የድምፅ አወጣጥ ጉዳይ ከተማሪዎች ጤና ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። የማንበብና የመተንፈስ ሥራ በሆድ እቃ አካባቢ ባሉ ጡንቻዎች በጋራ የሚፈጸም በመሆኑ በትክክል እንዲተነፍሱና ሲያነቡም ኢ-ተፈጥሮአዊ የሆነ ጫና በጉሮሮአቸውም ሆነ በሳንባቸው እንዳይፈጠር ወጣቶች መማር አለባቸው። በጉሮሮ በመናገር ከላይኞቹ የድምፅ አካላት እንዲወጣ ማድረግ የእነዚህን የሰውነት ክፍሎች ጤንነት የሚጎዳና ውጤታማነታቸውንም የሚቀንስ ነው። ጉሮሮ እንደመተላለፊያ ቧንቧ ሆኖ የሆድ ዕቃ ጡንቻዎች ናቸው ከባዱን ሥራ መሥራት ያለባቸው። ድምጻቸውን በሥነ-ሥርዓት እንዲጠቀሙ ቢማሩ ኖሮ በሕይወት ሊቆዩ የሚችሉ ልጆች አልፈዋል፤ በንባብና በንግግር ጊዜ ትክክለኛ የሆድ ጡንቻዎች አጠቃቀም ለብዙ የድምጽና የደረት ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ሕይወትን ለማራዘም ይረዳል።10Counsels to Teachers, Parents, and Students, p. 297.AHAmh 318.3

    የቁጣና ሸካራ ቃላት ውጤት፡- ሸካራ፣ ቁጡና የዘለፋ ቃላት የሚነገሩበት ቤት፣ ልጅ በጣም የሚያለቅስበት ሥፍራ ነው፤ በልጁ ገራም ስሜቶች የደስታ-ቢስነትና የብጥብጥ አሻራዎች ይታተማሉ። ስለዚህ እናቶች ሆይ ፊታችሁ የደስታ ፀሐይ ብርሃን የተላበሰ ይሁን። ብትችሉስ ፈገግ በሉ። አንድ አርቲስት የሰውን መልክ በሥዕል እንደሚገልጽ ሁሉ ጨቅላ ልጃችሁም በአዕምሮውና በልቡ የፊታችሁን ብርሃን ያንጸባርቃል። ወላጆች! በልጆቻችሁ ተለጣጭ አእምሮ መለኮታዊ ምሣሌ ይቀረጽ ዘንድ ክርስቶስ በውስጣችሁ ተተክሎ የሚኖር ለመሆኑ እርግጠኞች ሁኑ።11Review and Herald, Sept. 8, 1904.AHAmh 318.4

    ክው የሚያደርግ ድምፅ አይኑር፡- ምንም አይነት ጠብና ሁከት ወደ ቤት እንዲመጣ አትፍቀዱ። በለሆሳስ ተናገሩ፤ ድምፃችሁ ፈጽሞ ወደ ሸካራነት ከፍ አይበል፤ የተረጋጋችሁ ሁኑ። ሃሰተኛነትንና ጥፋትን የመፈለግ ዝንባሌ አስወግዱ። የሚያውክ ድምፅ ለማይሰማበት፣ ሁሉም ሰላም ለሆነበት፣ ቅዱስ ሰማይ ይዘጋጁ ዘንድ ልትረዷቸው እንደምትፈልጉ ለልጆቻችሁ ንገሯቸው። ለእናንተ ቀላልና ትኩረት የማያሻው ቢመስሏችሁም ለእነርሱ ከባድ ናቸውና በፈተናዎቻቸውና በችግሮቻቸው ሁሉ ታጋሾች ሁኑላቸው።12Manuscript 14, 1905.AHAmh 318.5

    እናቶችና አባቶች ሲታደሱ የአስተዳደር መርሆዎቻቸው በተሟላ ሁኔታ ይለወጣሉ። አስተሳሰባቸውና ንግግራቸውም ይለወጣል…. በጩኸት የሚሰነዘር ቁጡ ንግግር በቤት ውስጥ አይኖርም። የሚነገሩት ቃላት ለሰሚው የመባረክና የማረጋጋት ባህርይ ያላቸው ይሆናሉ…. አስጠሊታውን ቅላጼ ሁሉ ከድምፃችሁ አውጡት።13Letter 73, 1898.AHAmh 319.1

    በንዴት ግንፍል የሚሉ ስሜቶቻችንንና ቃሎቻችንን እንቆጣጠር፤ ይህንን በመተግበራችን ታላላቅ ድሎችን እንቀዳጃለን። ቃሎቻችንና ንዴቶቻችን መቆጣጠር እስካልቻልን ድረስ የሰይጣን ባሪያዎች ነን። ለእርሱ የምንገዛ የእርሱ እሥረኞች ነን። የሚያናድዱ፣ የማያስደስቱ፣ ትዕግሥት የሌላቸውና የሚያበሳጩ ቃላት ሁሉ ለሰይጣናዊ ግርማዊነቱ የሚበረከቱ ሥጦታዎች ናቸው። ዋጋ የሚያስከፍል ሥጦታ ነው፤ ለጌታ ከምናበረክተው ማንኛውም መሥዋዕት በላይ ዋጋ የሚያስከፍል። የጠቅላላውን ቤተሰብ ሠላምና ደስታ ያጠፋል፤ ጤናቸውን ያውካል፤ በመጨረሻም ዘለዓለማዊ የደስታ ሕይወትን የማጣት ምክንያት ይሆናል።14Testimonies for the Church, Vol. 1, p. 310.AHAmh 319.2

    ንግግሮች ፈገግታን ያምጡ ወይስ ጽልመትን?፦ ለሚናገሩትና ለሚያደርጉት ይጠነቀቁ ዘንድ ልጆችና ወጣቶች ሊሠለጥኑ ይገባል። ምክንያቱም የሚከተሉት መንገድ የፀሐይ ብርሃን ወይም ጽልመት የሚያመጣው በቤት ውስጥ ላሉ ብቻ ሳይሆን ለሚገናኟቸው ሰዎች ሁሉ ነው።15The Youth’s Instructor, Nov. 5, 1896.AHAmh 319.3

    የንግግር ችሎታን በጥበብ አለመጠቀም ሁልጊዜ ደስታ-ቢስነትን ያመጣል። ያለመስማማት ስሜትንና አለመደሰትን በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጥር ሸካራ ንግግርን ማንም እንዲናገር እግዚአብሔር ሥልጣን አልሰጠም። እንደዚህ ለሚናገር ሰው ሌሎች የቤተሰብ አባላት ክብር አይሰጡም፤ ስሜቱን ቢቆጣጠር ግን የሁሉንም ፍቅርና አመኔታ ያተርፋል።16Manuscript 60, 1903.AHAmh 319.4

    አስደሳች ቃላት ለልጆች፤ የአክብሮት ቃላት ለወላጆች፦ ወላጆች አስደሳች ቃላት ለልጆች፤ ልጆች ደግሞ ክብር የሚሰጡ ቃላት ብቻ ለወላጆች ይናገሩ። በቤት ውስጥ ኑሮ ለነዚህ ነገሮች ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው። ባህርያቸው በሚቀረጽበት ጊዜ ልጆች ትክክለኛ ልማድ የሚመሠርቱ ከሆነ ከእግዚአብሔር ለመማርና ትዕዛዛቱንም ለመፈጸም ቀላል ይሆንላቸዋል።17Review and Herald, Nov. 17, 1896.AHAmh 319.5

    በየትኛውም መልኩ ጋጠ-ወጥነትን አስወግዱ፦ እናቶችና አባቶች ሚስቶችና ባሎች ወንድሞችና እህቶች በቃልም፣ በንግግርም፣ በተግባርም በባለጌነት መስመር እራሳችሁን አታሰማሩ። ከርዳዳ አነጋገሮች፣ ተራ ቀልዶች፣ የየዋህነትና የእውነተኛ ደግነት እጦት እንደ ሁለተኛ ተፈጥሯችሁ ይሆኑና በእውነት ከተቀደሱት ጋር ሕብረት ትፈጥሩ ዘንድ የማትገጥሙ ያደርጓችኋል። በስድ ስሜታዊነት በወንጃይነትና በአሉባልታ ይበከል ዘንድ አይገባውም፤ ቤት እጅግ የተቀደሰ ሥፍራ ነውና። መጥፎውን ቃል ዝም አትበሉት፤ ያልተቀደሰውን ሐሳብ አስወግዱት። እውነተኛው ምሥክር [ክርስቶስ] እያንዳንዱን ቃል ይመዝናል፤ ለእያንዳንዱ ተግባር ዋጋ ያወጣል፤ እንዲህም ይላል “ሥራችሁን አውቃለሁ።” 18Signs of the Times, Nov. 14, 1892.AHAmh 320.1

    የተዋረደ ርካሽና ተራ ንግግር በቤት ውስጥ ቦታ ማግኘት የለበትም። ልብ ንጹህ ሲሆን የጥበብ ሀብት ክምችት ወደ ውጭ ይፈስሳል።19Review and Herald, May 17, 1898.AHAmh 320.2

    የማይረባ ንግግር በቤታችሁ አትናገሩ። ገና በጣም ሕፃን የሆኑ ልጆች እንኳ “በትክክለኛ ቃላት ቅርጽ” ተጠቃሚ ይሆናሉ። በእናትና በአባት መካከል የሚለዋወጡ ከንቱና የማይረቡ ቃላት በተመሳሳይ ሁኔታ በልጆቻቸው አንደበት የሚደገሙ ይሆናሉ። ቀጥተኛ፣ ቅን፣ እውነተኛና ቧልት የሌለባቸው ቃላት ግን ወደ መልካምነትና ወደ ትክክለኛ ተግባር ቤተሰቡን ሁሉ ይመራሉ።20Review and Herald, April 14, 1885.AHAmh 320.3

    የችኩልና ቁጡ ቃላት ጥፋቶች፦ ለልጆቻችሁ በቁጡ ቃላት ስትናገሩ የጽድቅን ጠላት ዓላማ እየደገፋችሁ ነው። እያንዳንዱ ልጅ ከህፃንነቱ ጀምሮ የሚገባው እድል ሊሰጠው ያስፈልጋል። መጥፎና ጭቅጭቅ የበዛበት ሳይሆን ቸርነትና ትዕግስት የተላበሰ ትምህርት መጀመር ያለበት ገና በልጅነታቸው ነው። ይህ ትምህርት ሴቶችም ሆኑ ወንዶች፣ ጎልማሶች እስኪሆኑ ድረስ ባሉት ዓመታት ሁሉ መቀጠል አለበት።21Manuscript 53, 1912.AHAmh 320.4

    የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት እርዳታ ያገኝ ዘንድ እያንዳንዱ ቤተሰብ በቀናኢ ፀሎት ጌታን ይጠይቅ። ሌሎችን ለመኮነን ያላቸውን ተነሳሽነትና የችኩል አነጋገር ልማዳቸውን ያሸንፉ። የአሳቢነትንና የተንከባካቢነትን ልማድ ለመቅረጽ በቤት ውስጥ እንዴት ቸርና ደግ እንደሚሆኑ ያጥኑ።22Manuscript 31, 1907.AHAmh 320.5

    ትዕግሥት-የለሽ የሆነ ንግግር በቤተሰቡ ክበብ እንዴት ዓይነት ጉዳት ያመጣል! አንድ ትዕግሥት-የለሽ ቃል ሌላውን ወደ ተመሳሳይ ስሜትና ጠባይ ይገፋፋል። ከዚያም የበቀል ቃላትና ራስን ነፃ የማድረግ ንግግር ይከተላል። እንደዚህ ባለ ንግግር ነው ከባድና አሰቃቂ ቀንበር አንገታችሁ ላይ የሚጫነው፤ እነዚህ ያወጣችኋቸው መራራ ቃላት በመከር ወቅት ከማያስደስት ምርት ጋር ተመልሰው ወደ ነፍሳችሁ ይመጣሉ።23Review and Herald, Feb. 27, 1913.AHAmh 320.6

    ከባድ ቃላት በጆሮ በኩል ልብን የሚገርፉ ናቸው፤ ፈጽሞ መጥፎ የሆነውን የነፍስን ፍላጎት በሕይወታቸው በመቀስቀስ ወንዶችና ሴቶች የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዲጥሱ የሚገፋፉ ናቸው…. ቃላት እንደሚተከሉ ዘሮች ናቸው።24Letter 105, 1893AHAmh 321.1

    ስሜታዊ ቃላት የመሐላ ዝርያዎች ናቸው፦ በብዙ የቤተሰብ አባላት ለከትየለሽና ኃላፊነት የጎደለው አባባሎችን የመናገር ልማድ አለ። የሚተነኩሱና ሸካራ የሆኑ ቃላትን የመናገር ልማድ እየጠነከረ ይሄድና ብዙ ሊነገሩ የማይገባቸው ቃላት ይወጣሉ፤ ይህ እንደ ሰይጣን እንጂ እንደ እግዚአብሔር ሥነ-ሥርዓት አይደለም…. በሚቃጠል ስሜት የሚነገሩ ቃላት ፈፅሞ ከአፍ መውጣት የለባቸውም። እነዚህ ቃላት በእግዚአብሔርና በቅዱሳን መላእክቱ እይታ እንደ መሐላ ዝርያዎች የሚቆጠሩ ናቸው።25The Youth’s Instructor, Sept. 20, 1894.AHAmh 321.2

    አንድ አባት የልጆቹን አመኔታ እንዴት እንዳጣ፦ ወንድሜ ሆይ ፈላጭ ቆራጭ ንግግርህ ልጆችህን እየጎዳ ነው። ዕድሜአቸው እየገፋ ሲመጣ ሌሎችን የመኮነን ዝንባሌአቸውም እንዲሁ እያደገ ይሄዳል። የስህተት ፍለጋ ሥራህ ሕይወትህን እያበላሸው ነው፤ ይህ ብልሽትም ወደ ሚስትህና ልጆችህ እየተጋባ ነው። ልጆችህ አመኔታ እንዲጥሉብህም ሆነ ስህተታቸውን እንዲያምኑ እየተበረታቱ አይደሉም፤ ምክንያቱም ምንም ቢያደርጉ ደረቅ ተግሳጽህ እንደማይቀርላቸው እርግጠኞች ናቸው። ቃሎችህ ብዙውን ጊዜ ለጋ ተክሎችን አውድሞ መሬቱን ምድረ-በዳ እንደሚያደርግ በረዶ ናቸው። ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ እንኳ መገመት አይቻልም። የምትናገረውን የሚሰብር ቃል ለማምለጥ ሲሉ ማታለልን ይለማመዳሉ። ተግሳጽንና ቅጣትን ለማምለጥ እውነትን ያድበሰብሳሉ። ከባዱና ቀዝቃዛው ትዕዛዝህ ለመልካም አይሆንላቸውም።26Letter 8a, 1896AHAmh 321.3

    ማሳሰቢያ፦ ለቤቱ በቸርነት ሲናገር ንግግሩን የፍቅር ሕግ ሊገዛው ይችል ዘንድ ቃል ቢገባና ቢፈርም ለእያንዳንዱ ወንድ መልካም ይሆንለታል። ወላጆች ሆይ ፈጽሞ በችኩል አነጋገር አትናገሩ። ልጆቻችሁ ካጠፉ አርሟቸው፤ ነገር ግን ንግግራችሁ በልስላሴና በፍቅር የተሞላ ይሁን። በእያንዳንዱ ወቀሳችሁ የይቅርባይነትና ታጋሽነትን ትምህርት የመስጠት ወርቃማ ዕድላችሁን ታጣላችሁ። ስህተትን በምታስተካክሉበት ጊዜ ገዝፎ የሚታየው ባህርይ ፍቅር ይሁን።27Letter 29, 1902.AHAmh 321.4

    የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት፦ ስንቶች ቤተሰቦች ናቸው የዕለት ምግባቸው ላይ የጥያቄና የጥርጥር ቅመም የሚነሰንሱት! የጓደኞቻቸውን ባህርያት ሰንጥቀውና ሰንጥረው ከዋና ምግብ በኋላ እንደሚበላ ማጣጣሚያ (dessert) አሞናሙነው የሚያቀርቡት! በሁሉም አባላት አስተያየት ይሰጥበት ዘንድ ብርቅየው የሐሜት ቁራሽ በታላላቆች ብቻ ሳይሆን በልጆችም ጭምር በጠረጴዛው ዙሪያ ይመላለሳል። በዚህም እግዚአብሔር ይዋረዳል።28Testimonies for the Church, Vol. 4, p. 195.AHAmh 321.5

    ኩነኔና ጥፋትን የመፈለግ መንፈስ በቤት ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። የቤት ውስጥ ሠላም እጅግ ክቡር ነውና በዚህ ዓይነት መንፈስ ሊረበሽ አይገባውም። ሆኖም የቤተሰቡ አባላት በጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀመጡ ምን ያክል ጊዜ ነው የነቀፌታ፤ የስህተት ፍለጋና የአሉባልታ ገበታ የሚዘዋወረው? ክርስቶስ ዛሬ ቢመጣ ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ ቤተሰቦች በጎነት የሌለበትን የትችት መንፈስ ሲያሽሞነሙኑ አይገኙም? የእንደዚህ ዓይነቶቹ የቤተሰብ አባላት በሰማይ ያለውን ቤተሰብ ለመገናኘት የተዘጋጁ አይደሉም።29Signs of the Times, Feb. 17, 1904.AHAmh 322.1

    የቤተሰቡ ኮሚቴ ውይይት በልጆች ላይ መልካም መዓዛ ያለው ተጽዕኖ ትቶ በሚያልፍበት ስሌት መተግበር ይኖርበታል።30Manuscript 49, 1898.AHAmh 322.2

    አሉባልታና ወሬኛነት፦ ገና ትኩስና የሚንቀጠቀጥ ሥጋ ያለውን የተጠቂውን እንስሳ አካል እየቦጨቀ የሚመገበውን አውሬ ስናስብ በድንጋጤ እንሞላለን። ያለ ስሙ ስም የመስጠት ዝንባሌ ስምና ዝናን የሚያጎድፍና የባህርይ አቃቂር የማውጣት ሥራ የሚፈጥረው ሥቃይና ጥፋት ከዚህ የባሰ አሰቃቂ አይደለምን? እግዚአብሔር ስለነዚህ ነገሮች ምን እንደሚል ልጆችና ወጣቶች ትምህርት ይውሰዱ፤ “ሞትና ሕይወት በምላስ ውስጥ ናቸው።” 31Education p. 235.AHAmh 322.3

    የአሉባልታና ወሬኛነት መንፈስ ጠብና ልዩነት በመዝራት ጓደኛሞችን ለመለያየት የሚጠቀምባቸው የሰይጣን ልዩ መሣሪያዎቹ ናቸው። ለአቋማችን እውነተኛነት ሌሎች ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር የሚያደርጉ ናቸው።32Testimonies for the Church, Vol 4, p. 195.AHAmh 322.4

    የጥርጥር ዘር መዝራት ጠላትን ያግዛል፦ ወቃሽ፣ ነቃሽ የሆኑ ቃላትን መናገር በሰዎች ዘንድ የተለመደ ነው። ለዚህ ዝንባሌ እጅ የሚሰጡ ሰዎች የሌሎችን ጥፋትና ስህተት በማስታወስ ረገድ ፈጣን ይሆኑ ዘንድ ሰይጣን ወደ ልባቸው እንዲገባ በር የሚከፍቱለት ናቸው። ውድቀቶቻቸው እንዲታዩ፣ ጎደሎአቸውንም ልብ እንዲሉ በንግግር በማቁሰል ከእግዚአብሔር ጋር በመተባበር ኃላፊነቱን ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ያለውን ሰው ልበ-ሙሉነቱ እንዲከዳው ያደርጋሉ። ብዙውን ጊዜ የጥርጣሬው ዘር የሚዘራው መልካም ነገር ወይም አድልኦ ሊደረግለት ሲገባ እንዳልተደረገለት በሚያስብ ሰው አማካይነት ነው።33Letter 169, 1904.AHAmh 322.5

    ስህተትን መፈለግ እንዲያቆሙ ችኩልና ቸርነት ያልተላበሱ ንግግሮችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ እግዚአብሔር አማኞቹን ይጠራል። ወላጆች ሆይ ልጆቻችሁን ወደ ክርስቶስ በማቅረቡ ሥራ ላይ መላእክት ረዳት ይሆኑላችሁ ዘንድ የምትናገሯቸው ቃላት ደግና አስደሳች ይሁኑላቸው። የቤት ውስጥ ቤተ-ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ተሐድሶ ያስፈልገዋል፤ አሁኑኑ ይጀመር። ማማረሩም ጭቅጭቁም ወቀሳውም ይቁም። የሚጨቃጨቁና የሚወቃቀሱ እነርሱ ለሰማያዊ መላእክት በራቸውን ጠርቅመው ለሰይጣን መላእክት ወለል አድርገው የሚከፍቱ ናቸው።34Letter 133, 1904.AHAmh 322.6

    እንዲቆጠቡና ታጋሽ እንዲሆኑ ለወላጆች የቀረበ ተማጽኖ፦ ወላጆች ሆይ የመጨቃጨቅ ስሜት ሲኖራችሁ ዘወር በሉ፤ ቤተሰቡን በሙሉ የመመረዝ ታላቅ ኃጢአት ለመሥራት ለዚህ አደገኛ ብስጭት ዕድል አትስጡ። እራሳችሁን አሳልፋችሁ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ እራሳችሁን እጥፍ ተቆጣጠሩ፤ በከንፈራችሁም ላትበድሉ በልባችሁ ቃል ግቡ፤ መልካምና አስደሳች ቃላት ብቻ ልትናገሩ ራሳችሁን አሳምኑ። ለራሳችሁ እንዲህ በሉ “በሚያስጨንቅ ቃል የልጆቼን ደስታ አልበጠብጥም።” በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ራሳችሁን ስትቆጣጠሩ ጠንካሮች እየሆናችሁ ትሄዳላችሁ። የነርቭ አካላችሁ በቀላሉ የሚሰማው አይሆንም፤ በእውነት ምርሆዎች የጠነከራችሁ ትሆናላችሁ። ኃላፊነታችሁን በሚገባ እየተወጣችሁ እንደሆነ ማወቃችሁ ብርታት ይሆናችኋል። የእግዚአብሔር መላእክት ለጥሪያችሁ ፈገግታን በመቸር ይረዷችኋል።35Testimonies for the Church, Vol. 1, pp. 386, 387AHAmh 323.1

    እናቶችና አባቶች ሆይ ልጆቻችሁን በቸርነት አነጋግሩ፤ ጥፋተኞች ናችሁ ስትባሉ ስሜታችሁ በቀላሉ እንዴት እንደሚነካ፣ ምን ያህል መታገስ እንደማትችሉ አስታወሱ። ልጆቻችሁ እናንተን የሚመስሉ እንደሆኑ አጢኑ፤ እወቁም። እናንተ ተግሳጽና ኩነኔ የማትታገሱ ከሆነ የእናንተን ያህል ጠንካራ ያልሆኑት ልጆቻችሁ ሊቋቋሙት አይችሉም። መልካምና አስደሳች ቃሎቻችሁ ለቤተሰባችሁ እንደ ፀሐይ ጮራ ይሁንላቸው። እራስን የመግዛት የአሳቢነትና የታጋሽነት ፍሬዎች መቶ እጥፍ ይሆናሉ።36Id., p. 401.AHAmh 323.2

    ጊዜው የዝምታ ወይም የመዝሙር መሆን ሲያስፈልገው፦ ሙሉ በሙሉ ለተቀደሱት እንኳ ቢሆን ፈተናዎች መምጣታቸው እውነት ነው። የታጋሾች ሁሉ ታጋሽ በጽኑ ይፈተሻል። ችኩል መልስን የሚያነሳሱ ንግግሮች ባል ወይም ሚስት ይናገሩ ይሆናል፤ ሌላኛው ወገን ግን ዝም ይበል፤ በዝምታ አደጋ የለም። ሁልጊዜም በከንፈሩ ለበደለው ሰው ከሁሉም የሚከብደው የአፀፋ በትር ዝም ታ ነው።37Manuscript 70, 1903.AHAmh 323.3

    እነርሱ [ልጆችና ወጣቶች] እራሳቸውን መግዛት ሲሳናቸውና ስሜታዊ ሆነው ሲናገሩ ከሁሉም የተሻለው መልስ የተግሳጽ፣ የክርክር ወይም የውግዘት መስመር መያዝ ሳይሆን ዝም ማለት ነው። ፀፀት ወዲያውኑ ይመጣል። ወርቃማው ዝምታ ከሚነገሩት ቃላት ሁሉ የተሻለ ሥራ ይሠራል።38Manuscript 59, 1900.AHAmh 323.4

    እራስ ዝቅ ባለማለቱ ምክንያት ሌሎች ትዕግሥት-የለሽና ጨቅጫቃ ሲሆኑ አንዳንዶቹን የጽዮን መዝሙሮች ማንጎራጎር ጀምሩ። ክርስቶስ በአናጺው ጠረጴዛ አጠገብ ሲሠራ ሳለ ትዕግሥቱን ለመሟጠጥ በማሰብ ሌሎች ይከብቡት ነበር፤ እርሱም ግሩም መዝሙሮችን መዘመር ሲጀምር በሥፍራው በነበረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጽዕኖ ሥር ይሆኑና የሚያደርጉትን በውል ሳያስተውሉት አብረውት ማዜም ይጀምሩ ነበር።39Manuscript 102, 1901.AHAmh 324.1

    በንግግር ራስን ለመግዛት የሚካሄድ ፍልሚያ፡- እራስን በመግዛትና በጠንካራ የባህርይ መሠረት ምሣሌነት በራሳቸው ትንሽ መንጋ ውስጥ ወላጆች የብርሃን ጮራን እንዲያሰራጩ እግዚአብሔር ይፈልግባቸዋል። ተራና የማይረባ ንግግር መፈቀድ የለበትም። እግዚአብሔር እያንዳንዱን የሕይወት ምሥጢር ይመለከታል። በአንዳንዶቹ ዘንድ እራስን የመቆጣጠር ትግል በቋሚነት ይካሄዳል። ስለ ሸካራ አነጋገራቸውና ባህርያቸው በፀሎት ውስጥ ሆነው በዝምታ በየቀኑ ይጥራሉ። እነዚህ ጥረቶች በሰዎች ፈጽሞ ዋጋ አይሰጣቸው ይሆናል። ሊነገሩ የቀረቡትን ችኩል ቃላት ዋጥ አድርገው በማስቀረታቸው ከፍጡራን ከንፈር ምሥጋና አያገኙ ይሆናል። እነዚህን ድሎች ዓለም ፈጽሞ አያያቸውም፤ እንዲያውም ከተሳካለት ይህ ምድር ማድረግ የሚፈልገው ቢኖር ድል አድራጊዎቹን መናቅና ማጣጣል ነው። በሰማይ መዝገብ ግን በአሸናፊነታቸው ይጻፋሉ። እያንዳንዱን የምሥጢር ፍልሚያ፣ እያንዳንዱን የዝምታ ድል የሚያይ አንድ አለ፤ እንዲህ ይላል፡- “ትዕግሥተኛ ሰው ከብርቱ ሰው ይሻላል። በመንፈሱ ላይ የሚገዛ አገር ከሚወስድ ይበልጣል።” 40.Signs of the Times, Aug. 23, 1899.AHAmh 324.2

    ለመደንፋት ለመጨቃጨቅና ለመውቀስ እምቢ ብትሉ ጌታ ማለፊያ መንገዱን ያሳያችኋል። የንግግርን ችሎታ በክርስቶስ መሰል አካሄድ ትተገብሩት ዘንድ ወርቃማዎቹን የትዕግሥት፣ የማጽናናትና የፍቅር ባህርያትን ወደ ቤታችሁ ማምጣት ትችሉ ዘንድ እርሱ ይረዳችኋል።41.Manuscript 67, 1901.AHAmh 324.3

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents