Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የልጅ አመራር

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First

    ምዕራፍ 6—የተፈጥሮ መጽሐፍ

    የማያቋርጥ የመማሪያ ምንጭ— ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ፣ ተፈጥሮ ታላቁ የመማሪያ መጽሐፋችን መሆን አለበት፡፡ 59 Testimonies For The Church 6:185.CGAmh 43.1

    ከታተሙ መጻሕፍት መማር ወይም ወደ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች መሄድ ለማይችሉ ጨቅላ ሕጻናት፣ ተፈጥሮ የማያቋርጥ የመማሪያ ምንጭ እና ደስታን የምትሰጥ ናት፡፡ ከክፋት ጋር ባለው ንክኪ ያልደነደነ ልብ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ለተንሰራፋው መገኘት አድናቆቱን ለመስጠት ፈጣን ይሆናል፡፡ በዓለም ጩኸት ያልደነቆረ ጆሮ በተፈጥሮ ውስጥ የሚናገረውን ድምጽ ለመስማት ንቁ ነው፡፡ እንዲሁም በዕድሜ ጠና ያሉና ዘወትር ስለ መንፈሳዊና ዘላለማዊ ጉዳዮች ድምጽ አልባ አስታዋሽነቱን ለሚፈልጉ፣ ተፈጥሮ የደስታና የመማሪያ ምንጭ ይሆንላቸዋል፡፡ 60Education, 100. CGAmh 43.2

    በኤደን ገነት ውስጥ እንደ መጽሐፍ ጥቅም ላይ ይውል ነበር— መላው የተፈጥሮ ዓለም ነገረ እግዚአብሔርን ለማብራራት የታቀደ ነው፡፡ ለአዳምና ለሔዋን በኤደን ቤታቸው ውስጥ ተፈጥሮ በእግዚአብሔር እውቀት የተሞላ እና በመለኮት ትምህርት የተጥለቀለቀ ነበር፡፡ ንቁ ለነበረው ጆሮአቸው እርሱ የጥበብን ድምጽ የሚያሰማ ነበር፡፡ ጥበብ ለአይን ትናገርና ወደ ልብ ትገባለች፣ ምክንያቱም በፍጥረት ሥራው ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኙ ነበር፡፡ 61Counsels to Parents, Teachers, and Students, 186 CGAmh 43.3

    ሕያው ትምህርቱን በፊታቸው የሚዘረገው የተፈጥሮው መጽሐፍ የማያልቅ የመመሪያና የደስታ ምንጭ ነው፡፡ እያንዳንዱ ደን ውስጥ በሚገኘው ቅጠል እና በተራራዎች ድንጋይ፣ በሚያበራ ኮከብ፣ በምድር፣ በባሕር እና ሰማይ ላይ፣ የእግዚአብሔር ሥም ተጽፏል፡፡ ሕይወት ባላቸውና ሕይወት በሌላቸው ላይ— ቅጠል፣ አበባ እና ዛፍ ላይ እንዲሁም እያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ላይ፣ ውሃ ውስጥ ከሚገኘው ሌዋታን እስከ የፀሐይ ጨረር ውስጥ ከሚገኝ ብናኝ ድረስ— የኤደን ነዋሪዎች ከእነርሱ ጋር በመነጋገር ከእነርሱ ጋር በመነጋገር ከእያንዳንዱ የሕይወትን ሚስጥር ይቀስሙ ነበር፡፡ በሰማያት ውስጥ የሚታይ የእግዚአብሔር ክብር፣ በሥርዓተ ዑደታቸው ያሉ ከቁጥር በላይ የሆኑ ዓለማት፣ “የደመናው ሚዘን” (ኢዮብ 37፡16)፣ የብርሃንና የድምጽ፣ የቀንና የሌሊት ምስጢራት— እነዚህ ሁሉ የምድር ነዋሪ የመጀመሪያ ክፍል ተማሪዎች መማር ያለባቸው ናቸው፡፡ 62Education, 21.CGAmh 43.4

    ከውድቀት ጊዜ ጀምሮ ተጨማሪ ትምህርቶችን ይሰጥ ነበር— ምድር በእርግማን የተመታች ብትሆም እንኳ እስከ አሁን ድረስ ተፈጥሮ የሰብአዊው ሰው የመማሪያ መጽሐፍ መሆን አለበት፡፡ እርሱም አሁን መልካምነትን ብቻ የሚያሳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ክፋት በሁሉም ሥፍራ ምድርን፣ ባሕርንና አየርን በእርከሰቱ ስላበላሸ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር ባህሪይ ማለትም የመልካም ነገር እውቀት በተጻፈበት ሥፍራ አሁን የሰይጣን ባህሪይ የሆነው በክፋት እውቀት ተተክቷል፡፡ አሁን የመልካምና ክፉ እውቀት በተገለጠበት ተፈጥሮ ላይ የሰው ልጅ በቀጣይነት የኃጢአትን ውጤት ማስጠንቀቂያ መቀበል አለበት፡፡ 63Education, 26.CGAmh 44.1

    ተፈጥሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ያብራራል— የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አያሌ ማብራሪያዎችን ከተፈጥሮ ተጠቅመዋል፤ በተፈጥሮ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን ስንመለከትም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የእግዚአብሔር ቃል ትምህርቶችን ይበልጥ እንድንረዳ ዘንድ ያስችለናል፡፡ 64Education, 120.CGAmh 44.2

    እግዚአብሔር በተፈጥሮ ዓለም ውስጥ የቃሉን ግምጃ ቤት መክፈቻ ቁልፍ በሰው ልጅ እጅ አስቀምጧል፡፡ የማይታየው በሚታዩት ነገሮች ተገልጸዋል፤ መለኮታዊው ጥበብ፣ የዘላለም እውነት፣ ቁጥር ሥፍር የሌለው ጸጋ፣ እግዚአብሔር በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ልንረዳቸው እንችላለን፡፡ 65Counsels to Parents, Teachers, and Students, 187.CGAmh 44.3

    ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች የሚያሳዩትን ነገሮች በተፈጥሮ ውስጥ ለማወቅና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተፈጥሮ የተገኙትን ምሳሌዎች ለመመርመር ሊበረታቱ ይገባል፡፡ በተፈጥሮም ሆነ በቅዱስ ጽሑፉ፣ ክርስቶስን የሚወክሉ እያንዳንዳቸውን ነገሮች እና እነርሱን ለመግለጥ የሚጠቀሙባቸውንም መፈተሸ ይኖርባቸዋል፡፡ እንደዚሁም በዛፍና በሐረግ፣ በአበባ እና በጽጌሬዳ, በፀሀይ እና በኮከብ ውስጥ እርሱን ማየትን ይማሩ፡፡ በወፍ ዝማሬ፣ በዛፎቹ ሹክሹክታ፣ በሚጮኸው ነጎድጓድ, እና በባህር ውስጥ ሙዚቃ ድምፁን መስማትን ሊማሩ ይችላሉ፡፡ እናም በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ነገር ወድ ትምህርቶቹን ያስተጋባል፡፡ CGAmh 44.4

    ከክርስቶስ ጋር ራሳቸውን ላላመዱ ሁሉ፣ ምድርም ከዚህ በኋላ የብቸኝነትና ባዶ ስፍራ አይሆንም፡፡ በአንድ ወቅት በእነርሱ መካከል ሲያድር በነበረው በእርሱ መገኘት በመሞላት፣ የአባታቸው ቤት ይሆናል፡፡ 66Education, 120. CGAmh 45.1

    መጽሐፍ ቅዱስ የተፈጥሮ ምስጢሮችን ይተረጉማል—ልጅ ከተፈጥሮ ጋር መገናኘት ሲጀምር ግራ የመጋባትን መንስኤ ይመለከታል፡፡ እርሱ ተቃዋሚ ኃይሎች የሚሰሩትን ስራ ግን ለይቶ ማወቅ አይችልም፡፡ እዚህ ጋር ነው ተፈጥሮ አስተርጓሚ የሚያስፈልጋት፡፡ በፍጥረተ ዓለም ውስጥ እንኳን የክፋት ድርጊትን በመመልከት ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ አሳዛኝ ትምህርት ማለትም “ጠላት ይህን እንዳደረገ” (ማቴዎስ 13፡28) ያገኛሉ፡፡CGAmh 45.2

    ተፈጥሮ የምታስተምረው ነገር በትክክል ሊነበብ የሚችለው ከቀራኒዮ በሚበራ ብርሃን ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በቤተልሔም እና በመስቀል ታሪክ ውስጥ ክፋትን ማሸነፍ ምን ያህል መልካም እንደሆነ፣ እና ወደ እኛ የሚመጡ እያንዳንዱ በረከት የመቤዠት ስጦታ እንዴት እንደሆነ ይታይ፡፡ CGAmh 45.3

    ውድመትና ጥፋትን የሚያመጣ ክፉ በእሾህ፣ በኮሻሽላ እና በእንክርዳድ ተወክሏል፡፡ በወፎች ዝማሬ እና በአበባ ፍካት፣ በዝናብ እና በፀሐይ ብርሃን፣ በበጋ ነፋስና ጤዛ ላይ፣ በአሥር ሺህ ተፈጥሮዎች ላይ፣ ከጫካው ዛፎች አንስቶ እስከ ሐምራዊው ድረስ ወደ ነበረበት የሚመለስ ፍቅር ይታያል፡፡ ተፈጥሮ አሁንም የእግዚአብሔርን ቸርነት ይናገራል፡፡ 67Education, 101.CGAmh 45.4

    በሐሳባዊ መማሪያ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶች—የኤደን ገነት ነዋሪዎች ከተፈጥሮ ገጾች እንደተማሩ ሁሉ፣ ሙሴ በአረብ አገር ሜዳዎችና ተራሮች ላይ የእግዚአብሔርን የእጅ ጽሑፍ ለይቶ እንዳወቀ ሁሉ፣ ልጅ የነበረው የሱስ በናዝሬቱ ኮረብቶች አጠገብ እንደነበረው ሁሉ፣ የዚህ ዘመን ልጆችም ከእርሱ መማር ይችላሉ፡፡ የማይታየው በሚታየው ተብራርቷል፡፡ 68Education, 100.CGAmh 45.5

    ለተፈጥሮ ያለንን ፍቅር ማሳደግ— እናት… ራስዋም ሆነ ልጆቿ ውስጥ በተፈጥሮ ውስጥ ለሚገኙ ውብ ነገሮች ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ ጊዜ ይኑራቸው፡፡ ሰማያትን ወደ ሞላው ክብር፣ ምድር እንድትዋብ ወደ አደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ውብ ቅርጾች፣ በመጠቆም ሁሉን ስለ ፈጠረ ፈጣሪ ትንገራቸው፡፡ በዚህ መንገድ ጨቅላ አዕምሮአቸውን ወደ ፈጣሪ በመምራት የበረከቶች ሁሉ ሰጪ ለሆነው ያላቸውን አክብሮትና ፍቅርን በልቦቻቸው ውስጥ መቀስቀስ ትችላለች፡፡ ሜዳዎችና ተራሮች— የተፈጥሮን ድምጽ እንደሚያስተጋባ አዳራሽ— ለልጆች መማሪያ ክፍል መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ተፈጥሮዎች የሚያቀርቧቸው መዝገቦች ማስተማሪያ መጽሐፎቿ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ አዕምሮአቸው ላይ የተቀረጹ ትምህርቶች ወዲያው ሊረሱ አይችሉም፡፡ CGAmh 46.1

    ወላጆች እርሱ የሰጠውን ተፈጥሮ እንዲወዱና በሚቀበሏቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ለሰጪው እጅ እውቅና እንዲሰጡ በማበረታታት ልጆቻቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ማቆረኘት ይችላሉ፡፡ በጊዜው የሚበለቅለውን እና እጀግ ብዙ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለውን ወድ የእውነትን ዘር ለመዝራት በዚህ መንገድ የልባቸው ማሳ ገና ከጅምሩ መዘጋጀት አለበት፡፡ 69The Signs of the Times, December 6, 1877.CGAmh 46.2

    ወፎች የምስጋና መዝሙር ሲዘመሩ ከእነርሱ ጋር ዘምሩ— ትናንሽ ልጆች በተለይም ወደ ተፈጥሮ መጠጋት አለባቸው፡፡ የፋሽን ሰንሰለት ከምታደርጉላቸው ይልቅ፣ አስደሳችና ብሩኅ የጸሐይ ብርሃን ውስጥ እንደ ጠቦት በነጸነት እንዲጫወቱ ይተውአቸው፡፡ ወደ ቁጥቋጦና አበቦች፣ ዝቅ ወደሉ ሣሮችና ክብር ወዳላቸው ዛፎች ጠቁሟቸው፣ ፈርጀ ብዙ ከሆነ ውበታቸው እና ማራኪ ቅርጾቻቸው ጋር ይላመዱ፡፡ በፍጥረት ሥራው ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥበብና ፍቅር አስተሯቸው፤ ልቦቻቸውም በደስታና በአመስጋኝነት ፍቅር ሲሞላ፣ ወፎች የምስጋና መዝሙር ሲዘመሩ ከእነርሱ ጋር ይዘምሩ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ልቦቻቸውን ሲገዛ፣ የቅድስናን ውበት ወደ ሕይወታቸው ያምጡ፡፡ በዚህ መንገድ ችሎታዎቻቸውን ለሌሎች በረከትና ለእግዚአብሔር ክብር ማዋል ይችላሉ፡፡ 70Counsels to Parents, Teachers, and Students, 188.CGAmh 46.3

    ከተፈጥሮ የተፈጥሮ አምላክ ወደ ሆነው ይጠቁሟቸው— ልጆች ክፋትን የሚቋቋሙበትን ድፍረት በውስጣቸው ሊያሳድግ የሚችል ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከተፈጥሮ የተፈጥሮ አምላክ ወደ ሆነው ይጠቁሟቸው፡፡ ልጆቼ እግዚአብሔርን እንዲየገለግሉትና እንዲያከብሩት በላቀ ሁኔታ እንዴት ማስተማር እችላለለሁ? የሚለው የወላጆችን አዕምሮ የሞላ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ሰማይ ሁሉ በሰብዓዊ ዘር ደህንነት ፍላጎት ያለው ከሆነ፣ ለልጆቻችን ደህንነት በአቅማችን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ትጉህ መሆን የለብንምን?13Manuscript Releases 2:9, 1886CGAmh 47.1

    ስለ ተፈጥሮ ማጥናት አዕምሮን ያጎለብታል— የእግዚአብሔር ክብር በእጅ ሥራው ታይቷል፡፡ አዕምሮ በሚያጠናበት ጊዜ ጠንካራ የሚያደርጉት ምስጢሮች እነኚህ ናቸው፡፡ ልብ ወለድን በማንበብ የተደሰተና የተጎዱ አዕምሮዎች ተፈጥሮ ውስጥ የተከፈተ መጽሐፍ ያገኛሉ፣ በአከባቢያቸውም ከሚገኙ የእግዚአብሔር ሥራዎች እውነትን ያነባሉ፡፡ በደን ውስጥ ካለ ተራ የዛፍ ቅጠል፣ በአረንጓዴ አጥላስ ምንጣፍ ምድርን የሸፈነ የሣር ጉልላት፣ እጽዋትና አበቦች፣ ባለ ግርማ ሞገሶቹ የደን ዛፎች፣ አስገራሚዎቹ ተራሮች፣ ጥቋቁር ድንጋዮች፣ እረፍት ያለሹ ውቅያኖስ፣ ሌሊትን ውብ ለማድረግ ሰማያት ላይ የተንጠለጠሉ ብርቅዬ ብርሃናት፣ የማያልቅ የጸሐይ ብርሃን ሀብት፣ የከበረ የጨረቃ ውበት፣ የክረምቱ ቅዝቃዜ፣ የበጋው ሙቀት፣ ገደብ በሌለው ኃይል ቁጥጥር ሥር ያሉ ፍጹም በሆነ ሥርዓት እና መጣጣም ውስጥ የሚኖሩ ተለዋዋጭ እና ድግግሞሽ ያላቸው ወቅቶች ውስጥ ሁሉም የጥናቶቻቸውን አብይ ሐሳብ ያገኛሉ፤ አይነሕሊናን ለማስፋትም ጥልቅ አስተሳሰብን የሚፈልጉ ርዕሰ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው፡፡ CGAmh 47.2

    እርባነ ቢስ እና ደስታ ፈላጊ የሆኑ ሰዎች አዕምሮአቸው ተጨባጭና እና እውነተኛ በሆነ ነገር ላይ ሲያተኩር ልቦቻቸው በአክብሮት መሞላት ባይችልም፣ ነገር ግን የተፈጥሮ አምላክን ያመልኩታል፡፡ በራሱ የተፈጥሮ ሥራ ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ባህሪይ ማሰላሰልና ማጥናት ወራዳ፣ ርካሽ እና አድካሚ ከሆኑ መደሰቻዎች ላይ አእዕምሮን የሚያነሳ የአስተሳሰብ ዘርፍ ይከፍታል፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ እውቀትና በዚህ ዓለም ላይ ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ፤ ጥናቱ እስከዘላለም ድረስ ይቀጥላል፡፡ እያንዳንዱን የአዕምሮ ችሎታ ወደ ተግባር የሚያመጠበትን የሐሳብ ርዕሰ ጉዳይን እግዚአብሔር ለሰዎቸ ሰጥቷል፡፡ የፈጣሪን ባህሪይ በላይ በሰማይ እና ከምድር በታች ልብን በአመስጋኝነት እና በምስጋና አቅራቢነት ሲሞላ ማንበብ እንችላለን፡፡ እያንዳንዱ ጅማት እና ስሜት በዕጹብ ድንቅ ሥራዎቹ ውስጥ ለእግዚአብሔር ፍቅር ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ 71Testimonies For The Church 4:581.CGAmh 48.1

    ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ የየሱስ መማሪያ መጽሐፍት ነበሩ— የእርሱ [የየሱስ] ትምህርት የተገኘው ከስዩመ-ሰማይ ምንጮች ነበር፣ ከጠቃሚ ተግባር፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ከተፈጥሮ፣ ከሕይወት ተሞክሮ— የእግዚአብሔር መማሪያ መጽሐፍት፣ ለፈቃደኛ እጅ፣ ለሚያይ አይን፣ እና ለሚገነዘብ ልብ ሁሉ በመመሪያ የተሞላ ነው፡፡15The Ministry of Healing, 400.CGAmh 48.2

    ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው የቅርበት ትውውቅ የልጅነት ጊዜው ምን ያህል በትጋት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተሰጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ በፊቱ የተዘረጋው የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራዎች ታላቅ ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ሁሉን የፈጠረ እርሱ የራሱ እጅ በምድር፣ በውቅያኖስ እና በሰማይ ላይ የጻፈውን ትምህርት አጠና፡፡ ቅዱስ ካልሆኑ የዓለም አካሄዶች ባሻገር፣ ከተፈጥሮ ግምጃ ቤት ሳይነሳዊ እውቀትን ቀሰመ፡፡ የእፅዋትና የእንስሳትን ሕይወት እንዲሁም የሰውን ሕይወት አጠነ፡፡ ገና ከልጅነቱ ዓመታት ጀምሮ በአንድ ዓለማ ተይዞ ነበር፤ ሌሎችን ለመባረክ ኖረ፡፡ ለዚህም ተፈጥሮ ውስጥ የሚያነሳሳውን ነገር አገኘ፤ የእፅዋት ሕይወትና የእንስሳት ሕይወትን ሲያጠና አዳድስ የሐሳብ መንገዶችና ዘዴዎች በአዕምሮው ላይ ብልጭ አሉ፡፡… CGAmh 48.3

    የነገሮችን ምክንያት ለመረዳት ሲጥር፣ የእግዚአብሔር ቃል እና ሥራዎች ትርጉም ለየሱስ የተገለጠለት በዚህ መንገድ ነበር፡፡ ሰማያዊ አካለት ጠባቂዎቹ ነበሩ፣ ቅዱስ የአስተሳሰቦች እና የግንኙነቶች ባሕል የእርሱ ነበር፡፡ ከመጀመሪያዋ የእውቀት ንጋት ጀምሮ በመንፈሳዊ ጸጋና የእውነት እውቀት ዘወትር ያድግ ነበር፡፡72The Desire of Ages, 70. CGAmh 49.1

    ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ እያንዳንዱ ልጅ እውቀትን ማግኘት ይችላል፡፡ በቃሉ አማካይነት ከሰማያዊ አባታችን ጋር ለመተዋወቅ በምናደርገው ጥረት፣ መላእክት ወደ እኛ ይቀርባሉ፣ አዕምሮአችን ብርቱ ይሆናል፣ ባህሪያችን የከበረ እና የጠራ ይሆናል፡፡ CGAmh 49.2

    በኋላም ትምህርቱ ላይ ተጠቅሞባቸዋል— ታላቁ መምህር አድማጮቹ በፍጥረታት ሁሉ ውስጥ የሚናገረውን ድምጽ ይሰሙ ዘንድ ከተፈጥሮ ጋር አገናኛቸው፣ ልቦቻቸው ሩህሩህ እና አዕምሮዎቻቸው ተቀባይ ሲሆኑ፣ አይኖቻቸው የሚያርፉባቸው መንፈሳዊ አስተምህሮ ትዕይንቶችን መተርጎም ይችሉ ዘንድ ረዳቸው፡፡ እርሱ የእውነት ትምህርቶችን ለማስተማር ሊጠቀምባቸው የወደዳቸው ምሳሌዎች፣ የእርሱ መንፈስ ምን ያህል ለተፈጥሮ ተጽዕኖ ክፍት እንደሆነ እና እንዴት እርሱ በዙሪያችን ካሉ የእለት ተእለት ኑሮ መንፈሳዊ አስተምህሮን በመቅሰም እንደሚደሰት የሚያሳይ ነው፡፡ CGAmh 49.3

    የሰማይ አዕዋፍት፣ የመስክ አበቦች፣ የዘር ዘሪው፣ እረኛውና በጎቹ— እነዚህን በመጠቀም ክርስቶስ ዘላለማዊውን እውነት አብራርቷል፡፡ ከሕይወት ክስተቶችም ማለትም ለአድማጮቹ የተለመዱ የተሞክሮ እውነታዎች ማብራሪያ ወስዷል— እርሾ፣ የተሰወረው መዝገብ፣ ዕንቁ፣ የአሳ መረብ፣ የጠፋችዋ ሳንቲም፣ የጠፋው ልጅ፣ እና በድንጋይ እና በአሸዋ ላይ የተሰራው ቤት፡፡ በትምህርቱ ውስጥ እያንዳንዱን አዕምሮ የሚያነሳሳ እና ለእያንዳንዱ ልብ ማራኪ የሆነ ነገር አለው፡፡ በዚህ መልኩ የየዕለት ተግባር አድካሚ ኡደት፣ የላቀ አስተሳሰብ የጎደለው ከመሆን ይልቅ፣ በመንፈሳዊ እና በዓይን በማይታይ የዘወትር አስታዋሽ የደመቀና የተነቀቃ ነበር፡፡ CGAmh 49.4

    ስለዚህ ማስተማር አለብን፡፡ ልጆች በተፈጥሮ ውስጥ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ጥበብ መገለጥን ይማሩ፤ የእርሱ እሳቤ ከወፎች፣ ከአበቦችና ከዛፎች ጋር ይጣመር፤ የሚታዩ ነገሮች ሁሉ የማይታዩትን የሚተረጉሙ ይሁኑላቸው፣ የሕይወት ክስተቶችም በሙሉ የመለኮት አስተምህሮ ዘዴ ይሁኑ፡፡ CGAmh 50.1

    በዚህ ሁኔታ በፍጥረታት ሁሉ እና የሕይወት ተሞክሮዎች በሙሉ ውስጥ ያለውን ትምህርት ሲያጠኑ፣ ፍጥረታትን እና የሕይወትን ክስተቶች የሚገዛው ሕግ ራሱ እኛን እንደሚገዛ፣ ለእኛ ጥቅም እንደተሰጡን፤ እና በመታዘዝ ብቻ እውነተኛውን ደስታና ስኬትን ማግኘት እንደምንችል እነዚህ ትምህርቶች ያሳያሉ፡፡ 73Education, 102, 103.CGAmh 50.2