ምዕራፍ 26—ሞትን እየተጋፈጡ ላሉት የተሰጠ መተማመኛ
መከራ እየደረሰባት ለነበረች ምራት የተሰጡ የማጽናኛ መልእክቶች
{የደብሊዩ ኤም ሲ ኋይት በላቤት እና የሚስስ ኋይት ምራት የሆነችው ሜሪ ኬልሲ ኋይት ከልጅነቷ ጀምሮ በፓስፊክ ፕሬስ የሪቪውና ሄራልድ እና በእስዊዘርላንድ አገር በባስል ባለው ማተሚያ ቤታችን ትጉህና መክሊት ያላት ሰራተኛ ነበረች፡፡ በአውሮፓ እያለች የሳንባ ነቀርሳ ያዛትና ታማ ከሦስት ዓመት በኋላ በ33 ዓመቷ ኮሎራዶ ውስጥ ቦልደር በሚባል ቦታ ሞተች፡፡ እዚህ ላይ የቀረቡት ንባቦች ለእሷ በሕመም ላይ በነበረችበት በመጨረሻው ዓመት ከተጻፉት መልእክቶች የተወሰዱ ናቸው፡፡ …አሰባሳቢዎች }Amh2SM 246.1
ባትል ክሪክ፣ ሚሽጋን
ሕዳር 4 ቀን 1889 ዓ.ም
ውድ ልጃችን ሜሪ፡-
ውድ ልጄ ሆይ፣ ስለ አንቺ መጸለይን አናቋርጥም፣ የእግዚአብሔር በጎነትና ምህረት እጅግ ግልጽና ጥርት ብሎ እንደሚታየኝ በጸለይሁ ሰዓት ሁሉ አዳኙ በክንዶቹ ያቀፈሽና አንቺም በእርሱ ክንዶች ላይ ያረፍሽ ይመስለኛል፡፡ በአንቺ ጉዳይ ላይ እምነት አለኝ፡፡ ስለ አንቺ የሚጸለየውን ጸሎት ጌታ እንደሰማ ስለማምን ለአንቺ መልካም የሆነውንና ለስሙ ክብር ይሰራል፡፡ እንዲህ ብሏል፣ «የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል» (ዮሐ. 15፡ 7)፡፡ «አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” (ማቴ. 21፡ 22)፡፡ Amh2SM 246.2
ሞገድ ያለባቸው ጊዜያቶች ከፊታችን ስለሆኑ እንዴት እንደምንታመን እና የብርታታችንን ምንጭ እንዴት አጥብቀን እንደምንይዝ ማወቅ አለብን፡፡ ጌታ ለሚታመኑት መልካም ስለሆነ አይሸነፉም፡፡ የአንቺን ጉዳይ በተመለከተ የነቢዩን ቃላቶች አስባለሁ፣ «ነፍሴ ሆይ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድሃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ” (መዝ. 43፡ 5)፡፡ Amh2SM 246.3
ሜሪ ሆይ፣ በእግዚአብሔር እረፊ፡፡ ጌታን በትዕግሥት ጠብቂው፡፡ በችግርሽ ጊዜ ሁሉ ረዳትሽ ይሆናል፡፡ ጌታ መልካም ነው፡፡ ቅዱስ ስሙን አወድሺ፡፡ ጌታ እንድንታመንበት ይፈልጋል፣ በተስፋዎቹም እምነት እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ ብናምን የእግዚአብሔርን አሰራር እናያለን፡፡ -- Letter 71, 1889.Amh2SM 247.1
ባትል ክሪክ፣ ሚሽጋን
ታህሳስ 6 ቀን 1889 ዓ.ም
ውድ ሜሪ፡-
እየተሰቃየሽ ያለሽ ውድ ልጄ ሆይ፣ አንረሳሽም፡፡ በየቀኑ ከልባችን እንጸልይልሻለን፡፡ በጸሎት ነጻነት አለኝ፡፡ ወንድሞቻችንን ኤ ዲ ኦልሰንን፣ ጄ ጂ ማቴሰንን እና ሌሎች ስቃይ የደረሰባቸውን አንረሳቸውም፡፡ እንጸልያለን፤ ማድረግ የምንችለው ይህንን ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከእናት ፍቅር በሚበልጥ ፍቅር በሚወዳችሁ በእሱ እጅግ በትህትና በመታመን እንተዋችኋለን፡፡ እሱ ስለሚጠነቀቅልሽና እጆቹን ከአንቺ ላይ ስለማያነሳ፣ ነገር ግን እራሱ ስለሚመራሽ በኢየሱስ ተጣበቂና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ታመኚ፡፡ Amh2SM 247.2
ውድ ሜሪ ሆይ፣ ንጉሱን ተወዳዳሪ በሌለው ውበቱ ማየት እና ስቃይ፣ ሀዘን፣ እና ሕመም በሌለበት መሆን እንዴት አስደሳች ነው፡፡ አሸናፊዎች እንደምንሆን እና በእግዚአብሔርና በነፍስሽ መካከል የግንኙነት መስመር ክፍት እንደሆነ በግልጽ ይሰማኛል፡፡ መለኮታዊ መገኘት አብሮሽ እንዳለ እና ኢየሱስ የማያቋርጥ ረዳትሽ መሆኑ እርግጠኛ ይመስላል፡፡ ኦ! እሱ ይወድሻል፤ ስለሚወድሽ ገርነት ባለበት ርኅራኄ እየተመለከተሽ ነው፡፡ ለአንዳፍታ እንኳን አትጠራጠሪው፡፡ ለዘላለማዊው ፍላጎትሽ የተሻለውን እንደሚያደርግልሽ በማመን ጉዳይሽን ለእርሱ አሳልፈሽ ስጪ፡፡. . . .Amh2SM 247.3
ለሁላችሁም በየቀኑ ከልብ እጸልያለሁ፡፡ ጌታ ይኖራል፣ ጌታ ጸሎትን ሰምቶ ይመልሳል፡፡ ውድ ልጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ተመልከቺ፡፡ ወደ ላይ ተመልከቺ፣ ድፍረት ይኑርሽ፣ ጌታ ረዳትሽ፣ ሐኪምሽ እና አዳኝሽ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ታመኚ፡፡ --Letter 75, 1889.Amh2SM 247.4
ባትል ክሪክ፣ ሚሽጋን
ታህሳስ 12 ቀን 1889 ዓ.ም
ውድ ሜሪ፡-
ሕመምተኞች፣ ደካሞች እና ብቸኞች ሆይ፣ ስለ እናንተ በዚህ ብርሃን አስባለሁ…፡፡ ሜሪ ሆይ፣ ከሁሉ የተሻለ እና እጅግ አፍቃሪና ርኅሩኅ የሆነ፣ እንዲሁም በላይሽ ሊያበራልሽ የጽድቅ ፀሐይ አለልሽ፡፡ ወደ ላይ ተመልከቺ፣ ወደ ላይ ተመልከቺ፡፡ በመቃብር ማረፍ ለእኔ ይህን ያህል ክፉ ነገር እንዳልሆነ ይሰማኛል፡፡ ብዙ ራስ ወዳድነትንና ብዙ የሰይጣን መንፈስ ሥራን ከመመልከቴ የተነሣ በጣም ደክሞኛል፣ እጅግ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ኢየሱስ እመለከትና በእርሱ ብቻ ሰላም አገኛለሁ፡፡…Amh2SM 248.1
በእምነት በኢየሱስ ጉያ (ደረት) ላይ አስቀምጥሻለሁ፡፡ እርሱ ይወድሻል፡፡ ከክርስቶስ ርቀሽ እንዳልቆምሽ አውቃለሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ደምና ጽድቅ ላይ ዝቅ ብለሽ በመደገፍ እርግጠኛ ሆነሽ በሙሉ እምነት ወደ እርሱ ቅረቢ፡፡ እርሱ ስለተናገረ በተስፋው በማመን ድነትን እንደ ጸጋ ስጦታ አድርሽ ተቀበዪ፡፡ ወደ ኢየሱስ ተመልከቺ፤ ይህ ለእኔ ብቸኛው መጽናኛዬ እና ተስፋዬ ነው፡፡ ጌታ አስቸጋሪ በሆነ መዋረድ ውስጥ ሲመራሽ ነበር፡፡ ከዕቃ ወደ ዕቃ ስትገለበጪ ነበር፡፡ ደረጃ በደረጃ፣ በእርሱ እጅግ ጥልቅ ወደ ሆነ ሸለቆ ተመርተሻል፣ ነገር ግን ይህ የሆነበት ምክንያት በክርስቶስ የሕይወት ውርደት ከእርሱ ጋር ወደ ቀረበ ግንኙነት ሊያመጣሽ ነው፡፡ Amh2SM 248.2
የተወደድሽ ክቡር ልጄ ሆይ፣ ኢየሱስ ከአንቺ ጋር አብሮ ያልተጓዘበት እርምጃ አለን? እሱ የማይሰማው አንድ የሕመም ስቃይ አለን? እርሱ ያልተሸከመው አንድ ኃጢአት፣ እርሱ ያልተሸከመው መስቀል፣ እርሱን ያላሳዘነው ሀዘን አለን? የድካማችን ስሜት ሁሉ ነክቶታል፡፡ የክርስቶስ መከራ ተካፋይ መሆን ምን ማለት እንደሆነ እያወቅሽ ነው፡፡ የክርስቶስ ስቃይ ተካፋይ ነሽ፡፡ አንቺ ደፋር፣ ራስን የካድሽ ልጅ፣ እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል፡፡ ወደ አንቺ የሚያስተላልፈው የራሱን መከራ የሚጨምርበትን ጽዋ ነው፡፡ የመስቀሉን ቀለል ያለ ወገን በአንቺ ትካሻ ላይ ይጭናል፣ ጥላን በነፍስሽ ላይ ያሳርፋል፡፡…Amh2SM 248.3
ራስሽን በኢየሱስ እጆች በመታመን አስቀመጪ፡፡ አትጨነቂ፡፡ እግዚአብሔር ለአንቺ ቸር መሆንን እንደረሳ አይሰማሽ፡፡ ኢየሱስ ይኖራል አይተውሽምም፡፡ ጌታ ምርኩዝሽ፣ ድጋፍሽ፣ ከፊትሽ ዘብ፣ ከኋላሽ ደጀን ይሁንሽ፡፡ --Letter 56, 1890.Amh2SM 248.4
ባትል ክሪክ፣ ሚሽጋን
ታህሳስ 13 ቀን 1890 ዓ.ም
ውድ ልጄ፡-
ሁላችሁንም ጌታ ይባርካል ያጽናናችሁማል፣ ጽኑ የሆነ ማጽናኛና ሰላምም ይሰጣችኋል፡፡ ዝም ብላችሁ በእጆቹ እንድታርፉ እና ሁሉንም ነገር በጥሩ ሁኔታ እንደሚያከናውን እንድታምኑ ይፈልጋል፡፡....Amh2SM 249.1
ድፍረት ይኑርሽ፡፡ ወደ ላይ መመልከትሽን ቀጥይበት፡፡ የሁላችንም ብቸኛው ተስፋ ኢየሱስ ነው፡፡ አይተውሽም አይጥልሽምም፡፡ የእግዚአብሔር ተስፋዎች የከበሩ ናቸው፡፡ አጥብቀን እንይዛቸዋለን፡፡ ከእጃችን እንዲያመልጡ አናደርግም፡፡ --Letter 57, 1890.Amh2SM 249.2
ሰይንት ሄሌና፣ ካሊፎርኒያ
ግንቦት 28 ቀን 1890 ዓ.ም
ውድ ልጆች፡-
አስብላችኋለሁ ለሁላችሁም እጸልይላችኋለሁ፡፡ ሜሪ ጤንነቷ እየተሻሸለ ቢሆን ኖሮ ምንኛ ልቤን ደስ ይለው ነበር፡፡ ጌታ ሻማው በዙሪያችሁ እንዲበራ ያደርጋል፡፡ በዚህ የፈተናና የጭንቀት ጊዜ ውስጥ ይባርካችኋል፣ ያበረታችኋል፣ ይደግፋችኋልም፡፡ አዳኙ በርህራሄ፣ በሀዘኔታና በፍቅር የተሞላ ነው፡፡ እግዚአብሔርን እንደ ታማኝ ፈጣሪ በማየት የነፍስ ጥበቃችሁን ለእርሱ አሳልፎ የመስጠት ጊዜ አሁን ነው፡፡ እንዴት ያለ የተባረከ ተስፋ ነው ያለን! ፈተናና መከራ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ጥንካሬው እየጨመረ የሚሄድ ተስፋ አለን፡፡ አሁን ሕይወቱን ለእናንተ አሳልፎ በሰጠው ላይ ያላችሁን መታመን አሳዩ፡፡ Amh2SM 249.3
ሜሪ ሆይ፣ ጊዜያዊ የሆኑት ቀላል ፈተናዎች እጅግ የላቀ እና ዘላለማዊ የሆነ ክብደት ያለው ክብር ስለሚያስገኙልሽ እግዚአብሔርን አመስግኚ፡፡ ያመንሽውን ታውቂያለሽ፣ ለእርሱ አሳልፈሽ የሰጠሽውን አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ እንደሚጠብቅም ተረድተሻል፡፡ ፈተናዎቹ ከባድ ቢሆኑም በራስሽ ጥረት ለማድረግ ሳይሆን በእሱ ፍቅር ለማረፍ በእያንዳንዱ ደቂቃ ወደ ኢየሱስ ተመልከቺ፡፡ እሱ ይጠነቀቅልሻል፡፡ Amh2SM 249.4
ፈተናዎች እየቀረቡ በሄዱ ቁጥር ተስፋ እየጠነከረ እንደሚሄድ አውቃለሁ፡፡ ከጽድቅ ፀሐይ የሚፈነጥቁ ጮራዎች በፈዋሽ ኃይላቸው በልብሽ ውስጥ ያበራሉ፡፡ ከደመናው ባሻገር ወዳለው የጽድቅ ፀሐይ ብርሐን ብሩህነት ተመልከቺ፡፡ በፈተና ማዕበል ውስጥ መልህቁ አጥብቆ ስለሚይዝ እግዚአብሔርን አመስግኚ፡፡ የእያንዳንዳችንን ጉዳይ በአብ ፊት የሚያማልድ ሁልጊዜ የሚኖር፣ ሁልጊዜ የሚያሸንፍ አማላጅ አለን፡፡ የዘላለም ደስታ ሽልማት የተገዛው በዘላለማዊ ዋጋ ነው፡፡ Amh2SM 249.5
የየዕለቱ ጸሎቴ ጌታ እንዲያጽናናሽ፣ እንዲያበረታሽ እና እንዲባርክሽ ነው፡፡ ንጉሱን በውበቱ የምንመለከትበት ቀን እንዴት ያለ የደስታ ቀን ይሆን ይሆን፡፡ በእግዚአብሔር መልካም ተስፋዎች እናርፋለን፡፡ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ይሆንልናል እንጂ በፍጹም አይጥለንም፡፡--Letter 77, 1890.Amh2SM 250.1
ባትል ክሪክ፣ ሚሽጋን
ሰኔ 16 ቀን 1890 ዓ.ም
ውድ ዊሊ፡-
ስለሁላችሁም፣ በተለይም ስለ ሜሪ እጨነቃለሁ፡፡ ለእሷ ቀንና ሌሊት እጸልይላታለሁ፣ በእጆቹ ባለው ክፍተት ውስጥ እንደሚጠብቃትም አውቃለሁ፡፡ አሁን ሜሪ በሙሉ መታመን፣ «ያመንሁትን አውቃለሁና፣ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ» (2ኛ ጢሞ. 1፡ 12) ማለት ትችላለች፡፡ Amh2SM 250.2
የሜሪን ጉዳይ በተመለከተ ጥርጣሬና እምነተቢስነት የለብኝም፡፡ እሷ በጌታ የተወደደች ነች፡፡ «የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው» (መዝ. 116፡ 15)፡፡ ሜሪ ከጳውሎስ ጋር እንዲህ ማለት ትችላለች፣ «መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፣ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” (2ኛ ጢሞ. 4፡ 7፣ 8)፡፡ Amh2SM 250.3
ነፍስን በሚፈትን ሰዓት ውስጥ ያለ አዳኝ ምን ማድረግ አለብን? የሕይወት ምዕራፍ መዝጊያ ላይ ነፍሳችንን ለማርካት የሕይወት ውኃን እንድንጠጣ ሊሰጡን አገልጋይ መላእክት በዙሪያችን ናቸው፡፡ በኢየሱስ የሚያንቀላፉትን ክርስቶስ ከራሱ ጋር ከመቃብር እንደሚያስነሳቸው ትንሳኤና ሕይወት ከሆነው ቃለ-መሃላ አለ፡፡ መለከት ይነፋልና ሙታንም ከእንግዲህ ወዲህ ላይሞቱ ወደ ሕይወት ይነሳሉ፡፡ በእግዚአብሔር ከተማ ውስጥ ሌሊት ስለሌለ ዘላለማዊው ንጋት መጥቶላቸዋል፡፡ Amh2SM 250.4
ሜሪ ፈተናዎችን በጀግንነት ተጋድላለች፤ ማድረግ የምትችለውን አድርጋለች፡፡ በቃልና በተግባር የሌሎችን ባሕርይ በመቅረጽ ረገድ በክርስቶስ ጸጋ ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡ እሷ በእምነት እየሞተች ነው፣ ነገር ግን ሥራዎቿ ሕያው ሆነው ይኖራሉ፡፡ --Letter 78, 1890.Amh2SM 250.5