Loading...
Larger font
Smaller font
Copy
Print
Contents

የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

 - Contents
  • Results
  • Related
  • Featured
No results found for: "".
  • Weighted Relevancy
  • Content Sequence
  • Relevancy
  • Earliest First
  • Latest First
    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents

    ምዕራፍ 2

    ወንዶችና ሴቶች የደመቁ እና በከፍተኛ ሁኔታ የተቀመሙ ምግቦችን፣ በተለይም ቅባትና ቅመም የበዛበት መረቅ ያለባቸውን የሥጋ ምግቦችን በመመገብ እና አነቃቂ የሆኑ እንደ ሻይና ቡና ያሉ መጠጦችን በመጠቀም ተፈጥሮአዊ ያልሆነ የምግብ ፍላጎትን ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ የወረዱ ስሜቶች ተቀስቅሰው የከበሩ የአካል ክፍሎችን ስለሚቆጣጠሩአቸው የአካል ክፍሎች ያተኩሳሉ፣ የምግብ መፈጫ አካላት ይቆስላሉ፣ የአእምሮ ኃይሎች ይደበዝዛሉ፡፡ የምግብ ፍላጎት ተፈጥሮአዊነቱን ያጣና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የደም ዝውውር ያልተመጣጠነ ስለሚሆን ደም ይቆሽሻል፡፡ መላው የአካል ክፍል ሥርዓት የለሽ ይሆንና ሙሉ በሙሉ እስኪበላሽ ድረስ የምግብ ፍላጎት ጥያቄዎች ምክንያት የለሾች እና አነቃቂና ጎጂ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት የሚስገበገቡ ይሆናሉ፡፡ {2SM 420.1}Amh2SM 420.1

    የብዙዎች የምግብ ፍላጎት ትንባሆ የሚባለውን የሚያስጠላ አረምን እና ጤናን የሚጎዱና መርዘኛ ነገሮችን በመቀላቀል ኃይለኛ እንዲሆን የተደረገውን የጠላ መጠጥን ለማግኘት ጩኸቱን ያሰማል፡፡ ብዙዎች እዚህ ላይ እንኳን አያቆሙም፡፡ የወረደ የምግብ ፍላጎታቸው አእምሮን እጅግ የማደንዘዝ ተጽዕኖ ያለውን የበለጠውን ጠንካራ መጠጥ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ የተነሳ የምግብ ፍላጎት የማሰብ ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ እስኪቆጣጠር ድረስ ሁሉንም ነገር ከመጠን በላይ ይወስዳሉ፡፡ በመሆኑም በፈጣሪው ምሳሌ የተፈጠረ ሰው ራሱን ከእንስሳት በታች ዝቅ ያደርጋል፡፡ ጀግንነትና ክብር በአንድ ላይ ለምግብ ፍላጎት መስዋዕት ይሆናሉ፡፡ የአእምሮ ስሜቶችን ማደንዘዝ ጊዜን ይጠይቃል፡፡ ይህ የሚሆነው ቀስ በቀስ ቢሆንም በርግጥ ይሆናል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የተቀመመ ምግብን በነፃነት መውሰድ ጤናማ ያልሆነ የምግብ ፍላጎትን በመፍጠር ጤና እና የአእምሮ ችሎታ ለፍትወት መስዋዕት እስኪሆን ድረስ ማንኛውንም ዓይነት ፍላጎት በነፃነት እንዲፈጽሙ መንገድን ያዘጋጃል፡፡ {2SM 420.2}Amh2SM 420.2

    ብዙዎች ንብረት ሳያፈሩ እና ውርስ ሳይኖራቸው ወደ ጋብቻ ግንኙነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ንብረት ለማፍራት የአካል ብርታት ወይም የአእምሮ ችሎታ የላቸውም፡፡ እንደ እነዚህ ያሉት ለማግባት በመቸኮል በትክክል ያላሰቡባቸውን ኃላፊነቶች በራሳቸው ላይ የጫኑ ናቸው፡፡ የከበረና ከፍ ያለ ስሜት የላቸውም፣ የባልና የአባት ተግባር ምን እንደሆነ ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤም የላቸውም፣ የቤተሰብን ፍላጎት ማሟላት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍላቸውም ግንዛቤ የላቸውም፡፡ በቤተሰቦቻቸው መጨመር ላይ በንግዳቸው ላይ ከሚያሳዩት የተሻለ ምንም ዓይነት ሥነሥርዓት አያሳዩም፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ንብረትን ለማፍራት ችሎታ ያላቸው ሰዎች በበቂ ሁኔታ ፍላጎቶቻቸውን ሊያሟሉላቸው የሚችሉአቸው ልጆች ብቻ ያሉአቸው ሲሆን በንግድ ስልት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉድለት ያለባቸውና በዓለም ውስጥ ራሳቸውን ለመምራት ብቃት የሌላቸው ሰዎች ቤቶቻቸውን በልጆች ይሞላሉ፡፡ ለራሳቸው ለመጠንቀቅ ብቃት የሌላቸው ሰዎች ልጆችን ማፍራት የለባቸውም፡፡ እነዚህ ደካማ ስሌት የሚያሰሉ ሰዎች ያፈሩአቸው በርካታ ልጆች እንደ አውሬ ሆነው እንዲያድጉ ተትተዋል፡፡ በቂ ምግብ እና ልብስ አላገኙም፣ የአካልና የአእምሮ ሥልጠናም አልተሰጣቸውም፤ ለወላጆችም ሆነ ለልጆች በዓለም ውስጥም ሆነ በቤት ውስጥ ምንም ቅዱስ ነገር የለም፡፡ {2SM 420.3}Amh2SM 420.3

    የጋብቻ ተቋም ለሰው በረከት እንዲሆን ሰማይ ያቀደው ተቋም ነበር፤ በአጠቃላይ ሲታይ ግን አሰቃቂ የሆነ እርግማን እስኪሆን ድረስ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ አብዛኞቹ ወንዶችና ሴቶች ወደ ጋብቻ ሕይወት ሲገቡ የተረጋጋ ሕይወትን ለመኖር መልስ ማግኘት ያለበት ጥያቄ እርስ በርሳቸው መዋደድ ብቻ እንደሆነ አድርገው በመቁጠር እርምጃ ወስደዋል፡፡ ነገር ግን በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ከዚህ የዘለለ ኃላፊነት እንደሚያርፍባቸው መገንዘብ አለባቸው፡፡ ልጆቻቸው የአካል ጤንነት እና የአእምሮና የግብረገብ ብርታት ሊኖራቸው እንደሚገባ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡ በቀላሉ ሊተገብሩ የማይችሉትን ነገር እንደሚጠብቅባቸው እና የቤተሰቦቻቸው ተጽዕኖ ክብደት ሚዛኑ ወደ ላይ ወይም ወደ ታች መመዘኑን እንደሚያሳይ በመገንዘብ ከፍ ባለ ተነሳሽነት እና ግንዛቤ የተንቀሳቀሱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ {2SM 421.1}Amh2SM 421.1

    ሕብረተሰብ የተሰራው ከቤተሰብ ነው፡፡ የቤተሰብ ራስ የሆኑ ሰዎች ሕብረተሰብን የመቅረጽ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እንደሚገባ ሳያስቡ ወደ ጋብቻ ሕብረት ለመግባት የሚመርጡ ሰዎች ችግሩን ለመቀበል ብቻቸውን ቢሆኑ ኖሮ ክፋቱ ያን ያህልም ትልቅ አይሆንም ነበር፣ ኃጢአታቸውም ሲነጻጸር ትንሽ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ደስታ ከሌለባቸው ጋብቻዎች የሚመነጭ ሲቃይ ይህን ከመሰለ ሕብረት የሚገኙ ልጆችንም ነክቷል፡፡ የስቃይን ኑሮ አውርሰዋቸዋል፤ ልጆቹ ምንም ጥፋት ባይኖርባቸውም ወላጆቻቸው ባለማገናዘብ የወሰዱት እርምጃ ባስከተለው መዘዝ ይሰቃያሉ፡፡ ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ ግንኙነታቸው ፍላጎታቸውን ወይም ጭፍን ስሜታቸውን የመከተል መብት የላቸውም፣ በዚህ ምክንያት ከሚከሰቱ ነገሮች በመነሳት ሕይወት ደስታና ፍስሐ የሌለበት ስለሆነ ሸክም እንደሆነ እንዲገነዘቡ ወደዚህ ዓለም የዋህ ልጆችን የማምጣት መብት የላቸውም፡፡{2SM 421.2}Amh2SM 421.2

    በአጠቃላይ ልጆች የወላጆቻቸውን ልዩ ባሕርያት ይወርሳሉ፣ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ብዙዎች በዙሪያቸው ምንም ዓይነት የሚያድን ተጽዕኖ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በድህነትና በቆሻሻ ይታፈጋሉ፡፡ ይህንን በመሰለ አካባቢ እና ይህን የመሰለ ምሳሌ እያዩ የሚያድጉ ልጆች ተግባርን መፈጸም ወደሚችሉበት ዕድሜ ሲደርሱ በግብረ-ገብ መለኪያ ላይ ከወላጆቻቸው ይልቅ ወደ ታች ከመዝቀጥና በሁሉም አቅጣጫ የሚታዩባቸው ጉድለቶች ከእነርሱ የበለጠ ግልጽ ከመሆን ሌላ ምን የተሻለ ነገር ሊጠበቅ ይችላል? ከዚህ የተነሳ እነዚህ ክፍሎች ጉድለቶቻቸውን ጠብቀው በማቆየት የወደፊት ትውልድን በድህነት፣ በጅልነት እና በውርደት እርግማን መትተዋቸዋል፡፡ እነዚህ ማግባት አልነበረባቸውም፡፡ ቢያንስ የእነርሱን ሥቃይ እንዲጋሩ እና ለዘር ማሽቆልቆል አንድ ትልቅ ምክንያት የሆኑትን ጉድለቶች ከተጠራቀመ መጥፎነት ጋር ለማስተላለፍ ምንም ክፋት የማያውቁ ልጆችን ወደ መኖር ማምጣት አልነበረባቸውም፡፡ {2SM 421.3}Amh2SM 421.3

    ከዚህ በፊት በነበሩት ትውልዶች ዘመን የኖሩት ሴቶች እነርሱ በሚመርጡት ምርጫ ምክንያት የወደፊት ትውልዶች ሊከብሩ ወይም ሊዋረዱ እንደሚችሉ በመረዳት ሁልጊዜ ከፍ ያለ ግንዛቤ ይዘው ቢንቀሳቀሱ ኖሮ ለአስካሪ መጠጥ እና የነርቭ ስርዓትን በማዳከምና የከበሩ የአእምሮ ችሎታዎችን በማርከስ በቀስታ ግን በእርግጠኝነት ለሚገድል ትንባሆ ለተባለ ገዳይ መርዝ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ፍላጎት ካላቸው ወንዶች ጋር ሕይወታቸውን ላለማጣመር የራሳቸውን ምርጫ ያደርጉ ነበር፡፡ ወንዶች ከእነዚህ እርኩስ ልማዶች ጋር ጋብቻ ፈጥረው መኖርን የሚቀጥሉ ከሆነ ከመረጡአቸው ጓደኞቻቸው ጋር እንዲደሰቱ ሴቶች ለላጤነት በረከት መተው ነበረባቸው፡፡ ሴቶች የምግብ ፍላጎታቸውን መቆጣጠር ከማይችሉና ዋና ደስታ የሚሰጣቸው መብላት፣ መጠጣትና የእንስሳ ስሜታቸውን ማርካት ከሆነላቸው ወንዶች ጋር የወደፊት ሕይወታቸውን እስከማጣመር ድረስ ለራሳቸው እጅግ ዝቅ ያለ ዋጋ መስጠት የለባቸውም፡፡ ሴቶች ሁልጊዜ ስሜትን ከመከተል ይልቅ የአእምሮ ምሪትን አልተከተሉም፡፡ በልጆቻቸው ላይ ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን የግብረገብ አሻራ የማያሳርፈውን እና ጤናንና ሕይወትንም ጭምር መስዋዕት በማድረግ የረከሰ የምግብ ፍላጎትን ለማርካት ካልተሰጡ ወንዶች ጋር የሕይወት ግንኙነት የመፍጠር ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው አልተሰማቸውም፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ ለተላለፉት የአካል ጤና እና የግብረገብ ባሕርያት እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ {2SM 422.1}Amh2SM 422.1

    ንጹህ ባልሆኑ ልምዶች አካላቸውን ያረከሱ ወንዶችና ሴቶች የአእምሮ ችሎታቸውንም አርክሰዋል፣ ጥሩ የሆኑ የነፍስ የስሜት ኃይሎችንም አጥፍተዋል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚመደቡ እጅግ ብዙ ሰዎች በመጋባት ለልጆቻቸው የራሳቸውን የተበከለ የአካል መዛል እና ነውረኛ ግብረ-ገብ ውርስ ትተውላቸዋል፡፡ የእንስሳ ስሜቶችን ማርካትና ጸያፍ ፍትወት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ እና ሰብአዊ ስቃይን በሚያስፈራ መጠን በመጨመር የትውልድን ውድመት በማፋጠን ተለይተው የሚታወቁ የልጆቻቸው ባሕርያት ሆነዋል፡፡ {2SM 422.2}Amh2SM 422.2

    ታማሚ እና በሽተኛ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ብዙ ጊዜ ራስ ወዳድ በመሆን በጋብቻ ግንኙነታቸው የራሳቸውን ደስታ ብቻ ሲፈልጉ ኖረዋል፡፡ ወደፊት ከእነርሱ ለሚፈጠረው ትውልድ ሕብረተሰቡን ወደ ታች ከማስመጥ በቀር ወደ ላይ ከፍ የማያደርግ እጅግ ዝቅ ያለ የአካልና የአእምሮ ኃይል ከማውረስ አንጻር ከልጆቻቸው ምን እንደሚጠብቁ በማሰብ ጉዳዩን ከከበረ እና ከፍ ካለ መርህ በመነሳት በደንብ አላሰቡበትም፡፡ {2SM 423.1}Amh2SM 423.1

    ብዙ ጊዜ ጤናማ ሴቶች የጤና ችግር ያለባቸውን ወንዶች ያፈቅራሉ፣ እርስ በርሳቸው ስለተዋደዱ ብቻ ከባሏ በሽተኛ መሆን የተነሳ በሚፈጥሩት አንድነት ይብዛም ይነስም ሚስቲቱ እንደምትሰቃይ ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ለመጋባት ፍጹም ነጻነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ታማሚ የነበረው ባል ጤንነቱ ሲሻሻል ሚስቲቱ ግን የእርሱን በሽታ ትጋራለች፡፡ እሱ በእሷ ጥንካሬ ሲኖር እሷ ግን ብዙም ሳትቆይ ጤናዋ እየተጓደለ መሆኑን መናገር ትጀምራለች፡፡ እሱ የእሷን እድሜ እያሳጠረ የራሱን እድሜ ያስረዝማል፡፡ የዚህን ዓይነት ጋብቻ የሚፈጽሙ ሰዎች ለእግዚአብሔር ክብር እንዲውሉ ከጌታ የተሰጡትን ጤንነትና ሕይወት አቅልለው በማየታቸው ኃጢአት ይፈጽማሉ፡፡ የዚህን ዓይነት የጋብቻ ሕብረት የሚፈጥሩ ሰዎች ችግሩ በእነርሱ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ቢሆን ኖሮ ኃጢአቱ የዚህን ያህል የጎላ አይሆንም ነበር፡፡ ልጆቻቸው ከእነርሱ ከሚተላለፍ በሽታ የተነሳ ለመሰቃየት ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ በሽታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ይኖራል፡፡ ብዙዎች እነርሱ የወሰዱት የስህተት እርምጃ እርግጠኛ የሆነ ውጤት ሲያመጣባቸው በሰብአዊ ዘር ላይ ለሚደርሰው ከባድ ስቃይ ሁሉ እግዚአብሔርን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ ደካማ ዘር በመዝራት የውርስ በሽታን በማስተላለፍና ሰብዓዊ ሥቃይን በማብዛት የሰው ዘርን በማበላሸት ድርሻቸውን ተጫውተዋል፡፡ {2SM 423.2}Amh2SM 423.2

    የአሁኑ ዘመን ትውልድ በአካል ብርታትም ሆነ በግብረ-ገብ ጉድለት እንዲኖርበት ያደረገው ሌላው ነገር ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ መጣመራቸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚታየው ያረጁ ወንዶች ወጣት ሴቶችን ለማግባት ሲመርጡ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጋብቻ ሲፈጸም ብዙ ጊዜ የወንዱ ዕድሜ የሚረዝም ሲሆን ሚስቲቱ ግን በእድሜ ለገፋ ባሏ የምታጋራውን ብርታት ለራሷ ከእሱ ማግኘት አለመቻሏ ይሰማታል፡፡ እሷ ምንም እንኳን በእድሜ ብዙ የሚበልጣትን ሰው እጅግ ብትወድ እና በእሷ በኩል ይህን የመሰለ መስዋዕትነት መክፈል እንዳለባት ቢሰማትም ሕይወትንና ጤንነትን መሰዋት የማንኛውም ሴት ግዴታ አይደለም፡፡ ፍቅሯን መቆጣጠር ነበረባት፡፡ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለባቸው ከፍላጎቷ በላይ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ልጆች ቢወለዱላቸው የእነዚህ ልጆች ሁኔታ ምን ይሆናል ብላ ማሰብ አለባት፡፡ በእድሜ አነስተኛ የሆነ ወንድ በእድሜ ብዙ የምትበልጠውን ሴት ማግባት ደግሞ የከፋ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሰፊ የእድሜ ልዩነት ያላቸው ሰዎች የሚወልዱአቸው ልጆች ብዙ ጊዜ ሚዛናዊ የሆነ አእምሮ የላቸውም፡፡ የአካል ብርታት ጉድለትም ያጋጥማቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ እነዚህን በሚመስሉ ቤተሰቦች ውስጥ የተለያዩ፣ ልዩ የሆኑ እና የሚያሳዝኑ ባሕርያት ይታያሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ያለ ዕድሜያቸው የሚሞቱ ሲሆን ወደ ብስለት እድሜ የሚደርሱትም ብዙ ጊዜ የአካልና የአእምሮ ብርታት ጉድለት የሚታይባቸውና የግብረገብ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ {2SM 423.3}Amh2SM 423.3

    አባት ብርታቱ እየከዳው ስለሆነ በእድሜ ልጅ የሆነውን ቤተሰብ በትክክል ለማሳደግ ዝግጁ አይደለም፡፡ እነዚህ ልጆች ሁልጊዜ የመከላከል ተጽዕኖ የሚፈልጉ ልዩ ባሕርያት አሏቸው፣ ይህ ካልሆነ ግን ወደ ጥፋት ይሄዳሉ፡፡ በትክክል አልተማሩም፡፡ ከእድሜ የተነሳ አባትየው የሚቀጣቸው ቅጣት ብዙ ጊዜ አጭርና ከስሜታዊነት የመነጨ ነው፡፡ አባት ለተለዋዋጭ ስሜት የተጋለጠ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለመጠን ልል (አሞላቃቂ) ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ ከአግባቢነት ውጭ የሆነ ጥብቅነት ያሳያል፡፡ እነዚህን በሚመስሉ በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ሁሉም ነገር ችግር ስላለበት የቤት ውስጥ ክፋት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ የፍጡራን ክፍል የህብረተሰብ ሸክም እንዲሆን በዓለም ውስጥ ተወርውሯል፡፡ ልጆቻቸው ስላጎለበቱአቸውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለሚተላለፉት ባሕርያት ወላጆች በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ ናቸው፡፡ {2SM 424.1}Amh2SM 424.1

    የልጆቻቸውን ቁጥር የሚያበዙ ወላጆች፣ ከአእምሮአቸው ጋር ቢመካከሩ ኖሮ፣ ለልጆቻቸው የሚያወርሱት የአካልና የአእምሮ ድክመት መሆኑን ማወቅ ይችሉ ነበር፤ እያወቁ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ ሰው ለባልንጀራው ማድረግ ያለበትን የሚናገሩትን የመጨረሻዎቹን ስድስት ትዕዛዛት እየሻሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሰው ዘርን ብልሽት በመጨመርና ህብረተሰቡን ወደ ዝቅተኛ ደረጃ በማውረድ፣ ከዚህም የተነሳ ጎረቤታቸውን በማቁሰላቸው የድርሻቸውን ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የጎረቤቶችን መብት እንዲህ የሚጠብቅ ከሆነ እጅግ ለሚቀርበውና የበለጠውን ቅዱስ ለሆነው ግንኙነት ግድ አይለውምን? እሱ ሳያውቅ አንዲት ድንብጥ እንኳን በምድር ላይ የማትወድቅ ከሆነ በአካልና በአእምሮ በሽተኛ ሆነው በከፍተኛም ሆነ በአነስተኛ ደረጃ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ለመሰቃየት በዚህ ዓለም ላይ የሚወለዱ ልጆች ጉዳይ አያሳስበውምን? እግዚአብሔር የሰጣቸውን የማገናዘብ ችሎታ ወደ ኋላ በማስቀመጣቸውና የስሜት ባርያዎች በመሆናቸው ትውልዶች የእነርሱን የአካል፣ የአእምሮና የግብረገብ ጉድለቶችን ለመሸከም በመገደዳቸው እግዚአብሔር ወላጆችን ተጠያቂ አያደርጋቸውምን? በልጆቻቸው ላይ ከሚያስከትሉት ስቃይ በተጨማሪ ለሚያሳዝነው መንጋቸው ትተው የሚያልፉት ከድህነት ሌላ ነገር የላቸውም፡፡ ሊያስተምሯቸው አይችሉም፣ ብዙዎቹ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑንም አይገነዘቡም፣ አስፈላጊ መሆኑን ቢገነዘቡም በተቻለ መጠን በማስተማርና በማሰልጠን ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉትን አስከፊ ውርስ ለመቀነስ ጊዜ አያገኙም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው በቂ ጥንቃቄና ትምህርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ከሚያውቁት በበለጠ ፍጥነት የቤተሰባቸውን ቁጥር መጨመር የለባቸውም፡፡ እናት በየዓመቱ ልጅ እንድትታቀፍ ማድረግ ታላቅ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ከማህበራዊ ግንኙነት የሚገኘውን ደስታ በመቀነስና ብዙ ጊዜ ጨርሶውኑ በማጥፋት የቤት ውስጥ ክፋትን ይጨምራል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የሚሰማቸውን እንክብካቤ፣ ትምህርት እና ደስታ ይቀማል፡፡ {2SM 424.2}Amh2SM 424.2

    ባል ብዙ ልጆችን በመውለድ በሚስቱ ላይ ሸክምና ኃላፊነት ሲጨምር እና የሚስቱን ጤንነትና ደስታ ችላ ሲል የጋብቻ ቃል ኪዳንን እና በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተሰጡትን ተግባራት ይጥሳል፡፡ «ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፡፡” «እንዲሁ ደግሞ ባሎች እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፡፡ የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት ይመግበዋል ይንከባከበውማል” (ኤፌ. 5፡ 25፣ 28፣ 29)፡፡ {2SM 425.1}Amh2SM 425.1

    ይህ ቅዱስ ትዕዛዝ ክርስቲያን ነን ባዮች ዘንድ እንኳን ሙሉ ለሙሉ ተጥሶ እንመለከታለን፡፡ በምትመለከቱበት ሁሉ የጠወለጉ፣ የታመሙ፣ ሥራ ያደከማቸው፣ የተጎሳቆሉ፣ መንፈሳቸው የተጎዳ፣ ተስፋ የቆረጡ ሴቶችን ትመለከታላችሁ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ከመጠን በላይ ሥራ በዝቶባቸዋል፣ ቶሎ ቶሎ ልጅ በመውለዳቸውም አስፈላጊ የሆነው ጉልበታቸው ተንጠፍጥፏል፡፡ ዓለም ለሕብረተሰብ ምንም ጥቅም በማይሰጡ ሰብዓዊ ፍጡራን ተሞልቷል፡፡ ብዙዎች የአእምሮ ጉድለት አለባቸው፣ የተፈጥሮ መክሊት ያላቸው ብዙዎች ደግሞ ጥቅም ላለው ተግባር አይጠቀሙአቸውም፡፡ እነዚህ መክሊቶች እንዲያድጉ አልተደረጉም፣ ይህ እንዳይደረግ እንቅፋት የሆነው አንድ ትልቅ ምክንያት ማሰልጠን ከሚቻል በበለጠ ፍጥነት ልጆች በመባዛታቸው እና እንደ አውሬ ሆነው እንዲያድጉ በመተዋቸው ነው፡፡ {2SM 425.2}Amh2SM 425.2

    በዚህ ዘመን ያሉ ልጆች ይብዛም ይነስም የጤና ሕጎችን ከመጣስ የተነሳ በመጣው ቅጣት ከወላጆቻቸው ጋር አብረው እየተሰቃዩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከልጅነታቸው ጀምረው የተከተሉት መንገድ ሲታይ ያለማቋረጥ የጤና ሕጎችን የሚቃረን ነው፡፡ ይብዛም ይነስም ከወላጆቻቸው የስህተት ልምዶች የተነሳ ከመወለዳቸው በፊት በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው የሚችል አሰቃቂ የሆነ የበሽታና የመዛል ውርስን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው በልጅነት ዕድሜያቸው የአካል ሥልጠናን በሚሰጡበት ጊዜ የተሳሳተ መንገድን ከመከተላቸው የተነሳ ይህ መጥፎ ሁኔታ እያንዳንዱን መንገድ የከፋ አድርጎታል፡፡ {2SM 425.3}Amh2SM 425.3

    ወላጆች የልጆቻቸውን አካላዊ ጤንነት በተመለከተ አስገራሚ የሆነ ሞኝነት፣ ግድ የለሽነት እና ቸልተኝነት ያሳያሉ፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ የተጎሳቆለውን ሕጻን የቀረለትን ትንሽ ብርታት በማውደም በልጅነት እድሜው ለመቃብር ይዳርገዋል፡፡ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቻቸውን ከእቅፋቸው ስለቀማባቸው የሚያዝኑ ወላጆችን ትሰማላችሁ፡፡ ሰማያዊ አባታችን እጅግ ጠቢብ ስለሆነ አይሳሳትም፣ እጅግ ደግ ስለሆነም አይበድለንም፡፡ ፍጥረቶቹ ሲሰቃዩ በማየት አይደሰትም፡፡ ወላጆች የጤና ሕግ የሚያዛቸውን ነገር ካለመተግበራቸው የተነሳ በሺሆች የሚቆጠሩ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ተበላሽተዋል፡፡ ሁልጊዜ የልጆቻቸውን የወደፊት ደህንነት በመመልከት ትክክለኛ የሆነ የህሊና ውሳኔ ከመከተል ይልቅ በስሜት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ {2SM 426.1}Amh2SM 426.1

    ልጆችን በማሰልጠን ረገድ መደረስ ያለበት የመጀመሪያው ታላቁ ዓላማ በከፍተኛ ደረጃ ለአእምሮና ለግብረገብ ስልጠና መንገድ የሚያዘጋጀውን አካላዊ ጤንነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የአካልና የግብረገብ ጤንነት በቅርበት የተቆራኙ ናቸው፡፡ ወላጆች ልጆችን ከመውለዳቸው በፊት የሚከተሉት መንገድ ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ በባሕርይ እድገታቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ሲገነዘቡ የሚያርፍባቸው ኃላፊነት ምንኛ ከባድ ነው፡፡ {2SM 426.2}Amh2SM 426.2

    ብዙ ልጆች ጥሩ ገበሬ ለማይናገሩ እንስሳት ከሚሰጠው ትኩረት ያነሰ ትኩረት ተሰጥቶአቸው እንዲያድጉ ተትተዋል፡፡ በተላይ አባቶች ብዙ ጊዜ ለሚስት እና ለልጆች ከከብቶቻቸው ያነሰ ትኩረት በመስጠታቸው በደለኞች ናቸው፡፡ ርህሩህ ገበሬ ከብቶቹን ለመንከባከብ ጊዜ ይወስዳል፣ የተለየ ትኩረትም ያደርጋል፡፡ ጠቃሚ የሆኑ ፈረሶቹ ከመጠን በላይ እንዳይሰሩ፣ ከመጠን በላይ እንዳይመገቡ ወይም ሰውነታቸው አተኩሶ ሳለ በመመገብ እንዳይጎዱ በደንብ ይጠነቀቃል፡፡ የእርሻ ከብቶቹ በቸልተኝነት፣ ለአደጋ በመጋለጥ ወይም ተገቢ ባልሆነ አያያዝ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና በማደግ ላይ ያሉት ለጋ ከብቶች ዋጋ እንዳይቀንስ ጊዜ ወስዶ ይጠነቀቅላቸዋል፡፡ የመመገቢያ ጊዜያቸውን ይጠብቅላቸዋል፣ ጉዳት ሳይደርስባቸው ሊሰሩ የሚችሉትን የሥራ መጠንም ያውቃል፡፡ ይህን ለማድረግ እጅግ ጤናማ የሆነ ምግብን በተገቢ መጠን እና በተወሰነ ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ ገበሬዎች በዚህ ሁኔታ የህሊና ምሪትን በመከተል የእንስሶቻቸውን ብርታት በመጠበቅ ተሳክቶላቸዋል፡፡ እያንዳንዱ አባት ለሚስቱና ለልጆቹ ያለው ፍላጎት ለከብቶቹ ከሚያደርገው ጥንቃቄ ጋር ቢመሳሰል እና የእነርሱ ሕይወት ከማይናገሩ እንስሳት ሕይወት የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን ቢገነዘብ ኖሮ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ አጠቃላይ የሆነ ተሃድሶ ይፈጸምና የሰብዓዊ ዘር ሥቃይ ይቀንስ ነበር፡፡ {2SM 426.3}Amh2SM 426.3

    ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው እጅግ ጤናማ የሆኑ የምግብ ዓይነቶችን በማቅረብ ረገድ ወላጆች ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ወላጆች ሕሊናቸው ለልጆቻቸው ጤንነት ምቹ እንዳልሆነ የሚነግራቸውን፣ ነገር ግን የአካል ሥርዓታቸውን የሚረብሸውን እና የምግብ መፈጫ አካላትን የሚያቃውሰውን ምግብ በምንም መንገድ በልጆቻቸው ፊት ማቅረብ የለባቸውም፡፡ ወላጆች ድዳ በሆኑ እንስሳቶቻቸው እንደሚያደርጉት ልጆቻቸውን በተመለከተ ከመንስኤውና ከውጤቱ አይማሩም፣ ከመጠን በላይ መሥራት፣ ከባድ የአካል እንቅስቃሴን ካደረጉ በኋላ አካል እጅግ ዝሎ እና ደክሞ እያለ መመገብ የማይናገሩ እንስሳትን ጤንነት እንደሚጎዳ ሁሉ የሰዎችንም ጤና እንደሚጎዳና በእንስሳት እንደሚያደርግ ሁሉ በሰውም ሰባራ ለሆነ የአካል አቋም መሠረት እንደሚጥል አይገነዘቡም፡፡ {2SM 427.1}Amh2SM 427.1

    ወላጆችም ሆኑ ልጆች ቶሎ ቶሎ፣ ሥርዓት በሌለው ሁኔታ እና ከመጠን በላይ ከበሉ እጅግ ጤናማ የሆነው ምግብም ቢሆን አካልን ይጎዳል፤ ከዚህ በተጨማሪ የምግቡ ጥራት ዝቅተኛ ከሆነ እና ከቅባትና ከማይፈጩ ቅመሞች ጋር የተዘጋጀ ከሆነ ውጤቱ እጅግ በጣም ጎጂ ይሆናል፡፡ የምግብ መፍጫ አካላት እጅግ ሥራ ይበዛባቸውና የደከመ ተፈጥሮ ለማረፍና ብርታትን ለማደስ ዝቅተኛ እድል ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ዋና የሆኑ የአካል ክፍሎች ብዙም ሳይቆዩ ይጎዱና ይሰበራሉ፡፡ ለማይናገሩ እንስሳት እንኳን ጥንቃቄ ማድረግና የምግብ ሰዓቶችን መጠበቅ አስፈላጊ ከሆነ በፈጣሪያቸው ምሳሌ ለተፈጠሩትና ከማይናገር ፍጥረት እጅግ የበለጠ ዋጋ ላላቸው ሰብዓዊ ፍጡራንም እጅግ የበለጠውን አስፈላጊ ነው፡፡ {2SM 427.2}Amh2SM 427.2

    ብዙ ጊዜ አባት ለሚስቱና ከመወለዱ በፊት ለልጃቸው የሚያደርገው ጥንቃቄ ለሚያጠቡ እንስሳት ከሚያስበውና ከሚጠነቀቀው ያነሰ ነው፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች እናት ከመውለዷ በፊት የቤተሰቧንና የእንግዶችን የተዛባ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን ለማዘጋጀት በማለዳ በመነሳት እና እስከ ረፋድ በመቆየት እንድትሰራ ትደረጋለች፡፡ ብርታቷ በጥንቃቄ መጠበቅ ነበረበት፡፡ ጤናማ የሆነ ምግብን ማዘጋጀት ጤናማ ላልሆነ የምግብ ዝግጅት ከሚጠይቀው ወጪና ጊዜ ግማሹን ያህል ብቻ የሚጠይቅና ለአካል የበለጠ ጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ {2SM 427.3}Amh2SM 427.3

    ብዙ ጊዜ እናት ልጆችን ከመውለዷ በፊት ከአቅሟ በላይ እንድትሰራ ትደረጋለች፡፡ ያለባት ጫና እና ሀላፊነት አይቀነስላትም፡፡ ያ ወቅት ለእሷ ከሌሎች ጊዜያቶች ሁሉ ይልቅ የእረፍት ጊዜ መሆን ሲገባው የድካም፣ የሀዘን እና ተስፋ የመቁረጥ ጊዜ ይሆንባታል፡፡ እሷም ከመጠን በላይ በመልፋት ተፈጥሮ ለልጇ ያዘጋጀውን ምግብ ትነፍጋለች፣ ደሟን በማፍላት ለልጇ ጥራቱ የተበላሸ ደም ትሰጣለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ልጇ ንቁነቱንና የአካልና የአእምሮ ብርታቱን ይቀማል፡፡ አባት እናቲቱን እንዴት ደስተኛ እንደሚያደርጋት ማጥናት አለበት፡፡ ወደ ቤቱ በተኮሳተረ ፊት መምጣት የለበትም፡፡ ሥራው ግራ አጋብቶት ከሆነ፣ ከሚስቱ ጋር መመካከር የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር፣ የዚህን ዓይነት ነገር በመንገር ሊረብሻት አይገባም፡፡ የምትሸከመው የራሷ ኃላፊነትና ፈተና ስላለባት ተገቢ ካልሆነ ከእያንዳንዱ ሸክም ነጻ መሆን አለባት፡፡ {2SM 427.4}Amh2SM 427.4

    ብዙ ጊዜ እናት ከአባት የሚጠብቃት እጅግ ቀዝቃዛ አቀባበል ነው፡፡ ሁሉ ነገር እሱ እንደሚሻው በጥሩ ሁኔታ ካልሄደለት ሚስትና እናት የሆነችውን ጥፋተኛ ያደርጋታል፣ ለኃላፊነቶቿና ለእለታዊ ፈተናዎቿ ግድ የሌለው ይመስላል፡፡ ይህን የሚያደርጉ ወንዶች የራሳቸውን ፍላጎትና ደስታ የሚቃረን ነገር እያደረጉ ናቸው፡፡ እናት ተስፋ ትቆርጣለች፡፡ ተስፋና ደስታ ይለዩአታል፡፡ ወደ ሥራዋ የምትሄደው ደስ ሳይላት መደረግ እንዳለበት ስለምታውቅ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሥራ ብዙም ሳይቆይ የአካልና የአእምሮ ጤናን ያዳክማል፡፡ እነዚህ ወላጆች የሚወልዱአቸው ልጆች የሚወለዱት በተለያዩ ዓይነት በሽታዎች እየተሰቃዩ ነው፣ በእድሜ ዘመናቸው ሁሉ የሚሰቃዩበትን በሽታ ገና ባልተወለዱ ልጆች ላይ እንዲጣበቅባቸው ያደረገው የእነርሱ መጥፎ ልምድ ስለሆነ እግዚአብሔር እነዚህን ወላጆች በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ አንዳንዶች ከድካማቸው ጫና ጋር ለአጭር ጊዜ ይኖራሉ፡፡ እናት የልጇን ሕይወት በተሸበረ ልብ በቅርበት በመመልከት በሞት ምክንያት ዓይኖቹን ለመክደን ስትገደድ ሀዘን ይጫናታል፤ ብዙ ጊዜ የዚህ ሁሉ ስቃይ ምንጭ እግዚአብሔር እንደሆነ አድርጋ ትቆጥራለች፡፡ እውነታው ግን የልጃቸው ገዳዮች ወላጆች ራሳቸው ናቸው፡፡ {2SM 428.1}Amh2SM 428.1

    አባት በአእምሮው ውስጥ ማስቀመጥ ያለበት ነገር ቢኖር፣ እናት ከእርሱ የምትወልደውን ልጅ ከመውለዷ በፊት የሚደረግላት እንክብካቤም ሆነ መጥፎ አያያዝ፣ በዚያን ወቅት በእናቲቱ ባሕርይ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን ልጁ ከተወለደ በኋላ በሚኖረው ፀባይ ላይም ብዙ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ብዙ አባቶች ሀብትን በፍጥነት ለማግኘት ስለሚጓጉ ከፍተኛ ግምት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መስዋዕት ስለሚያደርጉ አንዳንድ ወንዶች እንደ ነፍሰ ገዳይ እስኪያስቆጥራቸው ድረስ እናቲቱንና ልጇን ችላ ብለዋል፤ ብዙ ጊዜ የሁለቱም ሕይወት ሀብትን ለማካበት ላለው ጠንካራ ፍላጎት ተሰውተዋል፡፡ ብዙዎች ለዚህ ስህተታቸው ወዲያውኑ ከባድ ቅጣት ስለማይቀጡ የወሰዱት እርምጃ ለሚያስከትለው ውጤት የተኙ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚስት ሁኔታ ከባሪያ ሁኔታ የተሻለ አይደለም፣ አንዳንዴም እሷም ዘመናዊ አኗኗርን ለመኖር ስትል የአካል ጥንካሬን በማባከን ከባሏ ጋር በተመጣጣኝ ሁኔታ ጥፋተኛ ነች፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ወላጆች የሚወልዱት ልጅ የአካል፣ የአእምሮ እና የግብረገብ ብቃት ጉድለት ያለበት ስለሚሆንና የወላጆቹን አሳዛኝ፣ የተዘጋ፣ የራስ ወዳድነት አሻራ ስለሚይዝ ልጅ መውለድ ወንጀል ሲሆን ከእነርሱ ስስታምነት የተነሳ ዓለም ይረገማል፡፡ {2SM 428.2}Amh2SM 428.2

    ሥራን በተመለከተ በማሰብ ማከናወን የወንዶችና የሴቶች ተግባር ነው፡፡ በማያስፈልግ ሁኔታ ጉልበታቸውን መጨረስ የለባቸውም፣ ይህንን በማድረጋቸው በራሳቸው ላይ ብቻ ስቃይ የሚያመጡ ሳይሆን በሚፈጽሙት ስህተታቸው በሚወልዷቸው ልጆች ላይም ስጋትን፣ ድካምን እና ስቃይን ያመጣሉ፡፡ የዚህን ያህል ሥራ እንዲሰራ የሚጠይቀው ምንድን ነው? ወደዚህ መሻትን መግዛት ወደሌለበት ሥራ የመራው በምግብና በመጠጥ መሻትን አለመግዛትና ሀብት የማግኘት ፍላጎት ነው፡፡ የምግብ ፍላጎት በቁጥጥር ሥር ቢውልና ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ብቻ ቢወሰድ ኖሮ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ማዳን ስለሚቻል ወንዶችና ሴቶች ከአቅማቸው በላይ እንዲሰሩ እና የጤናን ሕግ እንዲጥሱ አይገደዱም ነበር፡፡ ሰዎች ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት እግዚአብሔርን ባይረሱ እና ሰው ለባልንጀራው ያለውን ተግባር የሚገልጹ የመጨረሻዎቹን ስድስት ትዕዛዛት በመተላለፍ የእርሱ በሆኑት አካላቸውና መንፈሳቸው እግዚአብሔርን ማክበር በማይችሉበት ቦታ ራሳቸውን ባያስቀምጡ ኖሮ ወንዶችና ሴቶች ሀብት ለማከማቸት ያላቸው ፍላጎት ኃጢአት አይደለም፡፡ ሀብታም ለመሆን በሚያደርጉት ችኮላ ጉልበቶቻቸውን በሥራ ሲያጨናንቁና የአካል ሕጎችን ሲተላለፉ ለእግዚአብሔር ፍጹም አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ፣ ከዚህ የተነሳ የኃጢአት መንገድን እየተከተሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ የተገኘ ንብረት ከባድ መስዋዕትነት ተከፍሎበት ነው፡፡ {2SM 429.1}Amh2SM 429.1

    ከባድ ሥራ እና ሥጋት ያለበት ኃላፊነት ብዙ ጊዜ አባትን ቁጡ፣ ትዕግሥት የለሽ እና በቃኝ የማይል እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ከእሱ ጠንካራ ጉልበት ጋር በደካማ ጉልበቷ እሱ የሠራውን ያህል ጠንክራ በሰራችው ሚስቱ ፊት ላይ ያለውን የድካም ምልክት አስተውሎ አያይም፡፡ ሀብታም ለመሆን ካለው ጭንቀት የተነሳ ለሥራ በሚያደርገው ጥድፍያ ራሱን ያሰቃያል፣ ሀብታም ለመሆን ካለው ጭንቀት የተነሳ በከፍተኛ መጠን ለቤተሰቡ ያለውን ግዴታ ስሜት ያጣል፣ የሚስቱን የመሸከም ኃይልም በትክክል አይለካም፡፡ ብዙ ጊዜ ማሳውን ያሰፋል፣ ይህ ደግሞ ሥራውን የሚያግዙ ተጨማሪ ቅጥረኞችን ይሻል፣ ይህ በተራው ደግሞ የቤት ሥራን ይጨምራል፡፡ ሚስት በየዕለቱ ከእሷ ጥንካሬ ጋር የማይመጣጠን ሥራ እየሰራች መሆኗን ትገነዘባለች፣ ሆኖም ሥራው መሰራት አለበት ብላ ስለምታስብ ትለፋለች፡፡ ያለማቋረጥ ከወደፊት የኃይል ምንጮቿ ወጪ እያደረገች ከወደፊት ሕይወቷ እየተበደረች ስለምትኖር ያንን ብርታት በምትፈልግበት ወቅት ከቁጥጥሯ ውጭ ሆኖ ታገኘዋለች፤ ካልሞተች የሰውነት አቋሟ ማገገም እስከማይችል ድረስ ይሰበራል፡፡ {2SM 429.2}Amh2SM 429.2

    አባት ከአካል ጤና ሕግ ጋር ቢተዋወቅ ኖሮ ግዴታዎቹንና ሀላፊነቶቹን በተሻለ ሁኔታ ይገነዘብ ነበር፡፡ ለልጆች የሚወረስ ሀብት ለማግኘት ሲባል ብዙ ሸክሞች በእናት ላይ እንዲመጡ ዝም በማለት ልጆችን ከመውለዷ በፊት ከአቅሟ በላይ እንድትሰራ በማስገደዱ ልጆቹን የመግደል ያህል በደለኛ መሆኑን ያያል፡፡ እነዚህን ሕጻናት የሚንከባከቡት በእነርሱ የሥቃይ ሕይወት ሲሆን እነርሱ የተከተሉት የተሳሳተ መንገድ ይህንን ውጤት እንዳስከተለ ባለመገንዘብ ያለ ዕድሜያቸው ወደ መቃብር ይወስዷቸዋል፡፡ የልጆቹን እናት አድካሚ የሆነ ሥራ እንዳትሰራ በመከልከል እና ከአእምሮ ሥጋት በመጠበቅ ልጆች ጥሩ አቋም እንዲወርሱና በአባታቸው ንብረት ሳይሆን በራሳቸው ኃይል ብርታት በመደገፍ በሕይወት ውስጥ የራሳቸውን ጦርነት እንዲዋጉ ዕድል ቢሰጣቸው ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ያገኙት ልምድ የእናትንና የልጆችን ጤንነት መስዋዕት በማድረግ ከተገዛ ቤትና መሬት የበለጠ ዋጋ ይኖረው ነበር፡፡ {2SM 429.3}Amh2SM 429.3

    ለአንዳንድ ወንዶች ክፋት፣ ራስ ወዳድነት፣ በቃኝ አለማለት እና የሰውን ሀሳብ እያጣጣሉ ሌሎችን ማዘዝ ተፈጥሮአዊ ይመስላል፡፡ ራስን የመቆጣጠርን ትምህርት በፍጹም ተምረው ስለማያውቁ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ምክንያታዊ ያልሆኑ ስሜቶቻቸውን አይቆጣጠሩም፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ወንዶች የትዳር አጋሮቻቸው ታማሚ እና ተስፋ ቢስ ሆነው በማየት፣ ልጆቻቸውም የራሳቸውን ልዩ የሆኑና የማያምሩ ባሕርያት ይዘው በማየት ዋጋቸውን ይቀበላሉ፡፡ {2SM 430.1}Amh2SM 430.1

    የእርስ በርስን ስሜት ከመጉዳት በጥንቃቄ መከላከል በጋብቻ የተጣመረ የእያንዳንዱ ጥንድ ሀላፊነት ነው፡፡ እያንዳንዱን የጭንቀት ምልክትና ጠንካራ ስሜት መቆጣጠር አለባቸው፡፡ ገርነት ያለበትን አሳቢነት በማሳየት፣ የበጎነት ተግባሮችንና ለእርስ በርስ የሚደረጉት ትንንሽ የትህትና ተግባራትን በማመስገን በትንንሽ ነገሮችም ሆነ በትልልቅ ነገሮች የእርስ በርሳቸውን ደስታ ማጥናት አለባቸው፡፡ ምግብ የአካል ብርታትን ለማቆየት እንደሚያስፈልግ ሁሉ እነዚህ ትንንሽ ነገሮች ለባልና ለሚስት ደስታ በጣም አስፈላጊ ስለሆኑ ችላ መባል የለባቸውም፡፡ አባት ሚስት እና እናት በእሱ ትልቅ ፍቅር እንድትደገፍ ማደፋፈር አለበት፡፡ የሕይወት ደስታዋን በባሏ ላይ ላደረገችው ሚስት ከእሱ የሚወጡ የደግነት፣ አስደሳችና የማደፋፈሪያ ቃላት ከማንኛውም መድኃኒት ይልቅ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ የርኅራኄ ቃላት ሚስት እና እናት ለሆነችው ልብ የሚያመጧቸው የደስታ ብርሃን ጮራዎች የራሳቸውን ደስታ የሚያመጡ ጮራዎችን ወደ አባት ልብ መልሰው ያንጸባርቃሉ፡፡ {2SM 430.2}Amh2SM 430.2

    ብዙ ጊዜ ሚስት ለተበላሸ የምግብ ጣዕም ገጣሚ የሆነ ምግብን ለማዘጋጀት በመልፋት ተጎሳቁላ እና ተዳክማ ያለ ዕድሜዋ ስታረጅ ባሏ ይመለከታታል፡፡ እሱ ግን ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜና ልፋት የሚጠይቁ ነገሮችን በመብላትና በመጠጣት የምግብ ፍላጎቱን ያረካል፡፡ እነዚህ ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ነገሮች የሚመገቡአቸውን ሰዎች ተናዳጅና ቁጡ የማድረግ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው፡፡ ሚስት እና እናት ከራስ ምታት ነጻ የምትሆንበት ጊዜ የለም፣ ልጆችም ያልተሟላ ምግብን መመገብ በሚያስከትሉአቸው ውጤቶች እየተሰቃዩ ናቸው፣ በልጆችና በወላጆች መካከል ከፍተኛ የሆነ የትዕግስትና የፍቅር እጦት አለ፡፡ ጤንነት ከፍተኛ ለሆነ የምግብ ፍላጎት ስለ ተሰዋ ሁሉም አብረው እየተሰቃዩ ናቸው፡፡ ልጅ ከመወለዱ በፊት ከወላጅ እናቱ በሽታና ጤናማ ያልሆነ የምግብ ፍላጎት ተላልፎበታል፡፡ በእናቲቱ የሚታዩ የመረበሽ፣ የመቆጣት እና የትካዜ ባሕርያት የልጇም ባሕርያት ይሆናሉ፡፡{2SM 430.3}Amh2SM 430.3

    ባለፉት ትውልዶች እናቶች የአካሎቻቸውን የአሰራር ሕጎች በተመለከተ እውቀት ቢኖራቸው ኖሮ የአካሎቻቸውም ሆነ የግብረገብ ጥንካሬያቸው እና የአእምሮ ክፍሎቻቸው በከፍተኛ ደረጃ በልጆቻቸው እንደሚገለጽ ያስተውሉ ነበር፡፡ ብዙ ነገርን በሚያካትተው በዚህ ጉዳይ ላይ እውቀት ማጣታቸው ነፍስ የመግደል ድርጊት ነው፡፡ ብዙ ሴቶች እናት መሆን አልነበረባቸውም፡፡ ደማቸው ከወላጆቻቸው ወደ እነርሱ በተላለፉ ትላትሎች (scrofula) የተሞላ ሲሆን በራሳቸው የአኗኗር ሁኔታ የበለጠውን ጨምሯል፡፡ የአእምሮ ችሎታ በመውረድ እንስሳዊ የምግብ ፍላጎትን ለመፈጸም ባርያ ሆኗል፤ እነዚህን ከመሰሉ ወላጆች የተወለዱ ልጆች ስቃይ የተረፋቸው ምስኪኖችና ለሕብረተሰቡ ምንም የማይጠቅሙ ናቸው፡፡ {2SM 431.1}Amh2SM 431.1

    የሕብረተሰቡን የግብረገብ ደረጃ ከፍ በማድረግ በሕብረተሰቡ ውስጥ ጠቃሚ የሆነ ተጽዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ ሚስቶችና እናቶች ጤናን ሊጎዳ በሚችል ዓይነት የምግብ ዝግጅት ከመጠመዳቸው እና ቶሎ ቶሎ ልጅ ከመውለዳቸው የተነሳ በርካታ የቤት ሀላፊነቶችን በመሸከም ከሕብረተሰቡ ውጭ እንዲሆኑ መደረጋቸው ካለፉት ትውልዶች ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለሚታዩ ብልሽቶች አስተዋፅዖ ካደረጉት ትልልቅ መንስኤዎች አንዱ ነው፡፡ {2SM 431.2}Amh2SM 431.2

    እነዚህ እናቶች የግብረገብ እና የአእምሮ ችሎታ የእንስሳ ባሕርይን መቆጣጠር እንዲችል ጥቂት ልጆችን ወልደው ቢሆንና የአካል ጤናን እና የአእምሮ ብርታትን የሚያቆዩ ምግቦችን በጥንቃቄ ተመግበው ቢሆን ኖሮ ልጆቻቸው በሕብረተሰቡ ውስጥ ጠቃሚና ብሩህ ጌጦች እንዲሆኑ ማስተማር ይችሉ ነበር፡፡ {2SM 431.3}Amh2SM 431.3

    ባለፈው ትውልድ የነበሩ ወላጆች በዓላማ ጽናት አካልን የአእምሮ አገልጋይ አድርገው ቢሆንና የአእምሮ ችሎታ ለእንስሳ ስሜቶች ባርያ እንዲሆን ባይፈቅዱ ኖሮ በአሁኑ ዘመን በምድር ላይ ልዩ የሆኑ ፍጡራን ሥርዓት ይኖር ነበር፡፡ እናት፣ ልጇን ከመውለዷ በፊት፣ ለወደፊቱ ትውልድ የባሕርይ አሻራ እንደምትሰጥ በመገንዘብ ሁልጊዜ ራሷን ብትቆጣጠር ኖሮ አሁን እንደሆነው የሕብረተሰቡ ወቅታዊ ሁኔታ አይዘቅጥም ነበር፡፡ {2SM 431.4}Amh2SM 431.4

    እናት ለመሆን እየተዘጋጀች ያለች እያንዳንዷ ሴት፣ በዙሪያዋ ያለው ነገር ምንም ቢሆን፣ በቀጣይነት ደስተኛ የሆነ፣ ፈገግታ ያለበት፣ ባለው ነገር የሚረካ ፀባይን ማደፋፈር አለባት፡፡ ይህን ማድረግ ያለባት በዚህ አቅጣጫ ለምታደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ በልጆቿ ላይ በሚታይ አካላዊም ሆነ ግብረገባዊ ባሕርይ አሥር እጥፍ እንደሚከፈላት በማወቅ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ በልምድ ራሷን ደስተኛ ከሆነ አስተሳሰብ ጋር ታለማምዳለች፣ አአምሮ ደስተኛ እንዲሆንም ታደፋፍራለች፡፡ የራሷን የመንፈስ ደስታ ነጻብራቅ በቤተሰቧ ላይ እና ከእሷ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሰዎች ላይ ታሳርፋለች፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጤናዋም ይሻሻላል፡፡ ለሕይወት ምንጮች ኃይል ይሰጣቸዋል፣ በምትተክዝበትና በምታዝንበት ጊዜ እንደሚሆን የደም ዝውውሯ ቀርፋፋ አይሆንም፡፡ የአእምሮና የግብረገብ ጤንነቷ ባላት የደስተኝነት መንፈስ ብርታት ያገኛል፡፡ የፈቃድ ኃይል የአእምሮ አሻራዎችን መቋቋም ይችላል፣ ነርቮችንም በከፍተኛ ደረጃ ያረጋጋል፡፡ ከወላጆቻቸው መውረስ የሚገባቸውን ይህን ብርታት የተቀሙ ልጆች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ለእነርሱ የተፈጥሮን ሕጎች ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል የተሻሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ {2SM 432.1}Amh2SM 432.1

    ልጅ ለእድገቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከእናቱ የሚያገኝበት ወቅት ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን እያጠቡ ሳሉ ምግብ በማብሰል ደማቸውን የሚያተኩስ ከባድ ሥራ እንዲሰሩ በመደረጋቸው የሚጠባው ልጅ ከእናት ጡት ትኩሳት የተነሳ የተበላሻ ወተት በመጥባቱ ብቻ ሳይሆን እናቲቱ ከምትመገበው ጤናማ ካልሆነ ምግብ የተነሳ የልጁ ደም በመመረዙ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት እናቲቱ የምትመገበው ጤናማ ያልሆነ ምግብ መላ የሰውነት ክፍሎቿን ስለሚያተኩስ እና ልጁ የሚመገበውን ምግብ ስለሚጎዳ ነው፡፡ የእናቲቱ የአእምሮ ሁኔታም በሕጻኑ ላይ ተጽዕኖ ያሳድርበታል፡፡ እሷ ደስታ የሌላት፣ በቀላሉ የምትረበሽ፣ ግልፍተኛ እና ስሜቷን በጩኸት የምትገልጽ ከሆነች ሕጻኑ ከእናቱ የሚቀበለው ምግብ ከመፍላቱ የተነሳ ብዙ ጊዜ የአንጀት ሕመምን፣ የጡንቻ መኮማተርን እና በአንዳንድ አጋጣሚ ደግሞ መንቀጥቀጥንና መውደቅን ሊያስከትል ይችላል፡፡ {2SM 432.2}Amh2SM 432.2

    የልጁ ባሕርይ፣ ይብዛም ይነስም፣ ከእናቱ በሚያገኘው የምግብ ሁኔታ ተጽእኖ ሊደርስበት ይችላል፡፡ እናት ልጇን በምታጠባበት ጊዜ የራሷን አእምሮ ፍጹም በመቆጣጠር ደስታ የሰፈነበትን ሁኔታ መፍጠር ምንኛ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ሲደረግ የልጁ ምግብ ጉዳት አይደርስበትም፣ እናት ልጇን በምትንከባከብበት ጊዜ የሚኖራት መረጋጋትና ራስን መቆጣጠር የሕጻኑን አእምሮ በመቅረጽ ሂደት ብዙ የሚያደርገው ነገር አለ፡፡ ሕጻኑ ቢደናገጥ እና በቀላሉ ቢረበሽ እንኳን የእናቲቱ ጥንቃቄ ያለበት የተረጋጋ ባሕርይ የማጽናናትና የማስተካከል ተጽዕኖ ስለሚኖረው የህጻኑ ጤንነት እጅግ በጣም ሊሻሻል ይችላል፡፡ {2SM 432.3}Amh2SM 432.3

    ሕጻናት ተገቢ ካልሆነ አያያዝ የተነሳ በከፍተኛ ደረጃ በደል ሲደርስባቸው ኖሯል፡፡ ነጭናጫ ከሆነ ጸጥ እንዲል ምግብ ይሰጠዋል፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ለመነጫነጩ ዋናው ምክንያት ከእናቲቱ ተገቢ ያልሆኑ ልምዶች የተነሳ ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ምግብን ከመጠን በላይ መመገቡ ነው፡፡ ጨጓራ አስቀድሞውኑ ከመጠን በላይ ምግብ ስለተሰጠው ተጨማሪ ምግብ መስጠት ሁኔታውን የበለጠ እንዲከፋ ያደርገዋል፡፡ {2SM 433.1}Amh2SM 433.1

    ሕጻናት ከመወለዳቸው ጀምሮ የምግብ ፍላጎትን እንዲያሟሉ ተደርገው ያድጋሉ፣ የሚኖሩት ለመብላት እንደሆነም ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ እናት የልጆቿን ባሕርይ በመመሥረት ረገድ በሕጻንነታቸው ጊዜ ብዙ ታደርጋለች፡፡ የምግብ ፍላጎታቸውን እንዲቆጣጠሩ ወይም እንደፈለጉ የምግብ ፍላጎታቸውን በማሟላት ሆዳሞች እንዲሆኑ ልታስተምር ትችላለች፡፡ እናት በቀን ውስጥ የተወሰኑ ነገሮችን ለመፈጸም እቅድ ታዘጋጃለች፤ በዚህን ጊዜ ልጆች ሲያስቸግሯት የልጆቿን ትንንሽ ሀዘኖች ለማረጋጋት ጊዜ ከመውሰድ እና ሀሳብ ከማስቀየር ይልቅ ጸጥ ለማሰኘት እንዲበሉ የሆነ ነገር ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ለአጭር ጊዜ ዓላማውን ቢፈጽምም በመጨረሻ ነገሮች እንዲከፉ ያደርጋል፡፡ እነርሱ ምንም የምግብ ፍላጎት ሳይኖራቸው ጨጓራቸው በምግብ ይታጨቃል፡፡ ይፈለግ የነበረው እናት ለልጆቿ ጥቂት ጊዜና ትኩረት እንድትሰጥ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን እሷ ለልጆቿ ደስታ ጊዜ እንዳትሰጥ ጊዜዋ እጅግ ውድ እንደሆነ አድርጋ ትቆጥራለች፡፡ ምናልባት እንግዶች በሚያወድሱበት ሁኔታ ቤቷን ማዘጋጀት እና ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ ምግብን ማዘጋጀት ከልጆቿ ደስታና ጤንነት ይልቅ ከፍተኛ ቦታ የምትሰጣቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ {2SM 433.2}Amh2SM 433.2

    በአመጋገብና በሥራ መሻትን አለመግዛት ወላጆችን በማድከምና ብዙ ጊዜ ቁጡ በማድረግ ለልጆቻቸው ያለባቸውን ሀላፊነት በትክክል እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ወላጆችና ልጆች በቀን ሦስት ጊዜ ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ የተዘጋጀ ምግብ በተደረደረበት ጠረጴዛ ዙሪያ ይሰበሰባሉ፡፡ እያንዳንዱ ምግብ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተሰራ መፈተን አለበት፡፡ ምናልባት እናት ምግቡን ስታዘጋጅ ሰውነቷ እስኪያተኩስ እና እስኪዝል ድረስ ስለለፋች ለተወሰነ ጊዜ ካላረፈች በስተቀር ካዘጋጀችው ምግብ እጅግ ቀላሉን እንኳን መብላት በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ልትሆን ትችላለች፡፡ ለማዘጋጀት ራሷን ያደከመችበት ምግብ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ለእሷ ገጣሚ አይደለም፣ ነገር ግን በተለየ ሁኔታ ደም በፈላና ሰውነት በደከመ ጊዜ የምግብ መፈጫ አካላትን ያጨናንቃል፡፡ አካላዊ የተፈጥሮ ሕጎችን በመጣስ የሚቀጥሉ ሰዎች በሕይወታቸው ዘመን በሆነ ጊዜ ቅጣታቸውን ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ {2SM 433.3}Amh2SM 433.3

    በዓለም ውስጥ የምግብ አለመፈጨት አብረውት ከሚመጡት ብዙ ክፋቶች ጋር እንደሚያስቸግራቸው የሚናገሩ ብዙ የተጨነቁ ሴቶች ለመኖራቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ መንስኤውን ውጤቱ ተከትሎአል፡፡ መሻታቸውን መግዛት የማይችሉ ሰዎች ታጋሽ መሆን አይችሉም፡፡ መጀመሪያ በመጥፎ ልምዶቻቸው ላይ ተሃድሶ ማካሄድ፣ ጤናማ አኗኗርን መማር አለባቸው፣ ከዚያ በኋላ ታጋሽ መሆን አይከብዳቸውም፡፡ ብዙዎች አእምሮ ከአካል ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያስተውሉ አይመስሉም፡፡ የአካል ሥርዓት ትክክለኛ ባልሆነ ምግብ ሲናወጥ አእምሮና ነርቮች ይጎዳሉ፣ በዚህ ዓይነት ችግር የተጠቁ ሰዎች ቀላል ነገር ይረብሻቸዋል፡፡ ለእነርሱ ትንንሽ ችግሮች የተራራ ያህል ከፍ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ልጆቻቸውን በትክክል ለማሰልጠን ገጣሚዎች አይደሉም፡፡ ሕይወታቸው ጫፍ በወጡ ነገሮች ተለይቶ ይታወቃል፤ አንዳንድ ጊዜ ቸሮች ይሆናሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምንም ትኩረት በማያስፈልጋቸው ተራ ነገሮች ላይ የሚገስጹ ጨካኞች ይሆናሉ፡፡ {2SM 434.1}Amh2SM 434.1

    እናት ልጆቿ ከደስታ የተነሳ ሲቦርቁ የሚያሰሙትን ጫጫታ መታገስ እንደማትችል ስለምታስብ ብዙ ጊዜ ከፊቷ ዞር እንዲሉ ታደርጋለች፡፡ ነገር ግን የሚቆጣጠራቸው ወይም በተገቢ ጊዜ ጥፋታቸውን የሚነግር የእናት ዓይን በሌለበት ቦታ ብዙ ጊዜ የማያስደስቱ ልዩነቶች ይነሳሉ፡፡ የእናት ቃል እንደገና ሁሉን ነገር ያስተካክላል፡፡ ወዲያው ይሰለቻቸውና ለውጥ ይመኛሉ፣ ደስታን ለማግኘትም ወደ ጎዳና ይወጣሉ፡፡ ንጹህና ተንኮል የሌለበት አእምሮ ያላቸው ልጆች ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ይገጥማሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ በጆሮአቸው የሚተነፈሱ ክፉ ንግግሮች መልካሙን ባሕርያቸውን ያበላሻሉ፡፡ ብዙ ጊዜ እናት በልጆቿ ላይ መጥፎ ነገርን አይታ በሀዘኔታ እስክትነቃ ድረስ ያንቀላፋች ትመስላለች፡፡ የክፋት ዘሮች የተትረፈረፈ መከር ለመስጠት በልጅነት አእምሮአቸው ውስጥ ተዘርተዋል፡፡ ልጆቿ ስህተትን ለመስራት እንዲህ መጋለጣቸው ያስደንቃታል፡፡ ወላጆች በልጅነት አእምሮ ውስጥ በወቅቱ ጥሩ እና ትክክለኛ የሆኑ መርሆዎችን ማስረጽን መጀመር አለባቸው፡፡ በተቻለ መጠን እናት ከልጆቿ ጋር መሆን እና የከበሩ ዘሮችን በልባቸው ውስጥ መዝራት አለባት፡፡ {2SM 434.2}Amh2SM 434.2

    የእናት ጊዜ በተለየ ሁኔታ የልጆች ነው፡፡ ከማንም የበለጠ ልጆቿ የእሷን ጊዜ የመያዝ መብት አላቸው፡፡ በብዙ ሁኔታዎች ሲታይ ልጆችን መግራት ከጊዜአቸው አብዛኛውን ክፍል ስለሚፈልግ እናቶች ልጆቻቸውን ሥርዓት ማስያዝን ችላ ብለዋል፡፡ እነርሱ ጊዜአቸውን ማሳለፍ እንዳለባቸው የሚሰማቸው በምግብ ማብሰል ላይ ወይም የራሳቸውን ልብስ እና በልጅነት ልባቸው ውስጥ ኩራትን ለመትከል ፋሽንን የተከተሉ የልጆቻቸውን ልብሶች በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡ እረፍት የለሽ ልጆቻቸው ጸጥ እንዲሉ ለማድረግ ሲሉ በቀኑ ውስጥ ባሉት በእያንዳንዱ ሰዓት ላይ ኬክ ወይም ከረሜላ ይሰጡአቸዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ጨጓራቸው ጊዜን ባልጠበቁ ጎጂ ነገሮች ይታጨቃል፡፡ የልጆቹ ፊት ገርጥቶ የመታየቱ እውነታ የሚመሰክረው እናቶች የምስኪን ልጆቻቸውን የቀሩትን የሕይወት ኃይሎች ለማጥፋት ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ መሆናቸውን ነው፡፡ ምግብን የሚፈጩ የአካል ክፍሎች ሁሉጊዜ በሥራ ስለተጠመዱ የእረፍት ጊዜ አልተሰጣቸውም፡፡ ጉበት ሥራውን መሥራቱን ያቆማል፣ ደም ይቆሽሻል፣ ልጆች መሻትን ካለመግዛት የተነሳ በእርግጥ እየተሰቃዩ ስለሆነ ታማሚና ቁጡ ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ትዕግሥትን መለማመድ አይችሉም፡፡ {2SM 434.3}Amh2SM 434.3

    ልጆች ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ ለመቆጣጠር እጅግ በጣም አስቸጋሪ መሆናቸው ወላጆችን ግራ ያጋባቸዋል፡፡ በአብዛኛው ግን እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የወላጆች የራሳቸው በወንጀል የተሞላ አመራር ነው፡፡ በምግብ ጠረጴዛዎቻቸው ላይ አቅርበው ልጆቻቸው እንዲበሉ ያደፋፍሩአቸው የነበረው የምግብ ጥራት ያለማቋረጥ የእንስሳ ስሜቶችን እያነሳሳ ግብረገብን እና የአአምሮ ክፍሎችን እያዳከመ ነው፡፡ እጅግ ብዙ ልጆች በወጣትነት ዕድሜያቸው የጨጓራ በሽተኛ የሆኑበት ምክንያት ገና ሕጻናት እያሉ ወላጆቻቸው የልጆቻቸውን አስተዳደግ በተመለከተ ከተከተሉት የተሳሳተ መንገድ የተነሳ ነው፡፡ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ስላደረጉት ለዚህ ድርጊታቸው መልስ ለመስጠት ይጠራሉ፡፡ {2SM 435.1}Amh2SM 435.1

    ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው ትምህርት አይሰጡም፡፡ የምግብ ፍላጎታቸውን በማሟላት እና አንደ ፍላጎታቸው እንዲበሉና እንዲጠጡ በማድረግ የልጆቻቸውን ባሕርይ ገና በልጅነታቸው ይመሰርታሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ በወጣትነት ዕድሜያቸው የሚኖራቸው አጠቃላይ ባሕርይ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው የመሠረቱት ባሕርይ ይሆናል፡፡ ፍላጎቶቻቸው ቁጥጥር አልተደረገባቸውም፡፡ ስለዚህ እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ተራ የሆነ መሻትን ያለመግዛት ተግባራትን ብቻ የሚፈጽሙ ሳይሆን ከዚያም አልፈው ይሄዳሉ፡፡ የተበላሹም ቢሆኑ የራሳቸውን ጓደኞች ይመርጣሉ፡፡ የወላጆቻቸውን ቁጥጥር መታገስ አይችሉም፡፡ የተበላሸ ስሜታቸውን ልጓም ስለሚለቁ ለንጽህና እና ለመልካም ሥራ አክብሮት አይኖራቸውም፡፡ በአሁኑ ዘመን ወጣቶች መካከል ለንጽህና እና ለግብረገብ እጅግ አነስተኛ ቦታ የተሰጠበት ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ ወንዶችና ሴቶች ለእግዚአብሔር ሕግ የመታዘዝ ግዴታ እንደሌለባቸው እንዲሰማቸው ያደረገው ትልቁ ምክንያት ይህ ነው፡፡ አንዳንድ ወላጆች ራሳቸውን የማይቆጣጠሩ ናቸው፡፡ አስከፊ የሆኑ የምግብ ፍላጎቶቻቸውን ወይም ጥልቅ የሆኑ የግልፍልተኝነት ስሜቶቻቸውን አይቆጣጠሩም፡፡ ከዚህ የተነሳ ልጆቻቸው ተገቢ ያልሆኑ የምግብ ፍላጎቶቻቸውን እንዲተዉ እና ራሳቸውን እንዲቆጣጠሩ ማስተማር አይችሉም፡፡ {2SM 435.2}Amh2SM 435.2

    ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን ለማስተማር ጊዜ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ እንቅፋት እንዳይሆኑባቸውና ጩኸታቸውንና ረብሻቸውን ለማራቅ ወደ ትምህርት ቤት ይልኳቸዋል፡፡ ደካማ አቋምን ለወረሱ ልጆች የመማሪያ ክፍል ከባድ ቦታ ነው፡፡ የመማሪያ ክፍሎች የተገነቡት በአጠቃላይ የዋጋ ርካሽነትን እንጂ የጤና ሁኔታን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አይደለም፡፡ ክፍሎች ልጆችን ለአስከፊ ብርድ ሳያጋልጡ በቂ አየር እንደሚያስገቡ ሆነው አልተዘጋጁም፡፡ መቀመጫዎቹ ልጆች ተመቻችተው እንዲቀመጡ እና እያደጉ ያሉትን ትንንሽ የሰውነት ክፍሎች በትክክለኛ አቋም እንዲሆኑ በማድረግ የሰንባዎቻቸውንና የልባቸውን ጤንነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ አልተሰሩም፡፡ ትንንሽ ልጆች ማንኛውንም አይነት ቅርጽ ይዘው ማደግ ይችላሉ፡፡ ትክክለኛ የሆነ የአካል እንቅስቃሴን እና ትክከለኛ የሆነ የሰውነት አቀማመጥ ልምዶችን በማጎልበት የጤና ተሃድሶዎችን ማግኘት ይችላሉ፡፡ በእድሜ ለጋ የሆኑ ልጆች በመማሪያ ክፍል ውስጥ ጠንካራ በሆኑና ባልተስተካከሉ መቀመጫዎች ላይ በቀን ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት ሰዓት ያህል ለብዙ ጊዜያቶች መላልሰው የተበከለ አየርን እየተነፈሱ መቀመጥ ለጤናቸውና ለሕይወታቸው አጥፊ ነው፡፡ ደካማ የሆኑ ሳንባዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ የመላው አካል ክፍሎች የነርቭ ኃይል የሚገኝበት አንጎል የአእምሮ ክፍሎች ድካምን መቋቋም እስከሚችሉ ድረስ ወደ ብስለት ሳይደርሱ ከባድ ሥራን እንዲሰሩ በመገደዳቸው እየደከመ ይሄዳል፡፡ {2SM 436.1}Amh2SM 436.1

    በመማሪያ ክፍል ውስጥ በርግጠኝነት ለተለያዩ ዓይነት በሽታዎች መሰረት ተጥሏል፡፡ ከሁሉ በተለየ ሁኔታ፣ ከሁሉም የአካል ክፍሎች ይልቅ እጅግ በቀላሉ ለጉዳት ሊዳረግ የሚችለው አእምሮ ብዙ ጊዜ ከመጠን በላይ ከሆነ ሥራ የተነሳ ሊቀለበስ የማይችል ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ መጉረብረብን፣ ከዚያም ውኃ መቋጠርን እና መንቀጥቀጥን ከአሰቃቂ ውጤቶቹ ጋር ያስከትላል፡፡ የብዙዎች ሕይወት ጉጉ በሆኑ እናቶች ተሰውቷል፡፡ ይህን አያያዝ ለመቋቋም በቂ የሆነ የአካል ብቃት ካላቸው ልጆች መካከል እንኳን የእናቶቻቸው አያያዝ ያስከተሉአቸውን ውጤቶች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ የሚሸከሙ እጅግ ብዙዎች አሉ፡፡ የአእምሮ የነርቭ ሥርዓት ኃይል እጅግ ስለሚደክም ወደ ብስለት እድሜ ሲደርሱ ብዙ የአእምሮ ሥራን መቋቋም ያቅታቸዋል፡፡ የአንዳንድ አደጋ የማይችሉ የአእምሮ አካሎች ኃይል ያለቀ ይመስላል፡፡ {2SM 436.2}Amh2SM 436.2

    ልጆች በጨቅላነታቸው ወደ ትምህርት ቤት በመላካቸው ለአደጋ እየተጋለጠ ያለው የአካልና የአእምሮ ጤንነት ብቻ ሳይሆን ከግብረ-ገብ አንጻርም ክስረት ይደርስባቸዋል፡፡ ባሕርያቸው ተኮትኩቶ ካላደጉ ልጆች ጋር የመተዋወቅ እድልም አለ፡፡ ካልተሞረዱ እና ካልተገሩ ልጆች ጋር፣ ከውሸታሞች፣ ከሚምሉ፣ ከሚሰርቁ እና ከሚያታልሉ ጋር፣ ስለ መጥፎ ምግባር ያላቸውን እውቀት ከእነርሱ በእድሜ ለሚያንሱት ማካፈል ደስታ ከሚሰጣቸው ልጆች ጋር አብረው እንዲያሳልፉ ይደረጋሉ፡፡ ጨቅላ ልጆች ለራሳቸው ከተተዉ ከመልካም ይልቅ ክፉን በቀላሉ ይማራሉ፡፡ ክፉ ልምዶች ከተፈጥሮ ልብ ጋር በደንብ ስለሚስማሙ በሕጻንነትና በልጅነት ጊዜ የሚያዩአቸውና የሚሰሙአቸው ነገሮች በአእምሮዎቻቸው በጥልቀት ይቀረጻሉ፣ በለጋ ልባቸው ላይ የተዘራው መጥፎ ዘር ሥር ይሰድና የወላጆቻቸውን ልብ የሚያቆስል ሹል እሾህ ይሆናል፡፡ {2SM 436.3}Amh2SM 436.3

    በልጅ ሕይወት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወይም ሰባት አመታት ውስጥ ከአእምሮ ስልጠና ይልቅ ለአካላዊ ስልጠና ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ከዚህ ወቅት በኋላ፣ የአካል አቋሙ ጥሩ ከሆነ፣ የሁለቱም ትምህርት ትኩረት ማግኘት አለበት፡፡ ሕጻንነት ከስድስት እስከ ሰባት አመት ሊራዘም ይችላል፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ልጆች እንደ ትንንሽ ጠቦቶች በቤት አከባቢ እና በአጥር ግቢ ውስጥ በደስተኝነት መንፈሳቸው ከሀላፊነት እና ከጭንቀት ነጻ ሆነው እየቦረቁ እና እየዘለሉ እንዲዘዋወሩ መተው አለባቸው፡፡ {2SM 437.1}Amh2SM 437.1

    ወላጆች፣ በተለይም እናቶች፣ እንደዚህ ላለው ሕጻን አእምሮ ብቸኛ መምህራን መሆን አለባቸው፡፡ ከመጻሕፍት ማስተማር የለባቸውም፡፡ ልጆች በአጠቃላይ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ለመማር መጠየቅ ይወዳሉ፡፡ የሚያዩትንና የሚሰሙትን ነገሮችን በተመለከተ ጥያቄዎችን ስለሚጠይቁ ለማስተማር አጋጣሚውን መጠቀም እና እነዚህን ትንንሽ ጥያቄዎች በትዕግሥት መመለስ አለባቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ጥሩ ዘር በመዝራት እና መጥፎ ባሕርይ ሥር እንዲሰድ ምንም ክፍተት ባለመስጠት በጠላት ላይ የበላይነት ያገኙና የልጆቻቸውን አእምሮ ይገነባሉ፡፡ {2SM 437.2}Amh2SM 437.2

    ልጆች መማር ያለባቸው የመጀመሪያው አስፈላጊ ትምህርት ቢኖር በተገቢ ሁኔታ ለምግብ ፍላጎት እምቢታ ማሳየት ነው፡፡ ለልጆች ምግብ ከሰጡ በኋላ መመገብ በሕይወት ለሚገጥሙ በሽታዎች ፈውስ ነው ብሎ ከማስተማር ይልቅ በማለሳለስና አእምሮአቸውን አቅጣጫ በማስቀየር የልጆችን ፍላጎት ማሟላት የእናቶች ኃላፊነት ነው፡፡ {2SM 437.3}Amh2SM 437.3

    ወላጆች ቀላል በሆነ የምግብ ዓይነት በመርካት ጤናማ አኗኗር ኖረው ቢሆን ኖሮ ብዙ ወጪ ማዳን ይቻል ነበር፡፡ አባት የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ከአቅሙ በላይ ለመሥራት አይገደድም ነበር፡፡ ቀላል ሆኖ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የያዘ ምግብ የነርቭ ሥርዓቶችንና የእንስሳ ስሜቶችን ከልክ በላይ በመቀስቀስ ቱግ ማለትን እና ግልፍልተኝነትን የመቀስቀስ ተጽዕኖ አይኖረውም ነበር፡፡ አንድ ሰው ቀለል ያለ ምግብን ብቻ ተመግቦ ቢሆን ኖሮ አእምሮው የጠራ፣ ነርቮቹ ዘና ያሉ፣ ጨጓራው ጤናማ ስለሚሆን ንጹህ በሆነ የአካል ሥርዓት ውስጥ የምግብ ፍላጎት የማጣት ችግር አይኖርበትም ነበር፡፡ አሁን ያለው ትውልድም አሁን ካለበት ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በዚህ ባለቀ ዘመን ሁኔታችንን ለማሻሻል የሆነ ነገር ሊደረግ ይችላል፡፡ በሁሉም ነገር መሻትን መግዛት አስፈላጊ ነው፡፡ መሻቱን የሚገዛ አባት በምግብ ጠረጴዛው ላይ ብዙ የተለያዩ ዓይነት ምግቦች ባይኖሩ አያማርርም፡፡ ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ የቤተሰቡን ሁኔታ በሁሉም መልክ ያሻሽልና እናትና ሚስት ለልጆች የምትሰጠው ሰዓት እንዲኖራት ያደርጋታል፡፡ የወላጆች ትልቁ ጥናት የሚሆነው ልጆቻቸው በዚህ ዓለም ጠቃሚ እንዲሆኑና ለወደፊቱ ሰማይ ገጣሚ እንዲሆኑ በምን መንገድ ልጆቻቸውን ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ ማሰልጠን እንደሚችሉ ይሆናል፡፡ ልጆቻቸው ከጌጣጌጥ ነጻ የሆነ ንጹህና ቀላል ልብስ ለብሰው በማየታቸው ይረካሉ፡፡ ልጆቻቸው ውስጣዊ ውበት፣ በእግዚአብሔር እይታ ታላቅ ዋጋ ያለው የዋህ እና ዝግተኛ መንፈስ ኖሯቸው ለማየት ከልባቸው ይሰራሉ፡፡ {2SM 437.4}Amh2SM 437.4

    ክርስቲያን አባት ወደ ሥራ ለመሄድ ከቤቱ ከመውጣቱ በፊት ቤተሰቡን በዙሪያው ሰብስቦ በእግዚአብሔር ፊት በማጎንበስ ኃላፊነታቸውን ለእረኞች አለቃ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ከዚያ በኋላ በስራው ሰዓት ሁሉ ልቡን ደስተኛ ለማድረግ ከሚስቱ ፍቅርና በረከት ጋር፣ እንዲሁም ከልጆቹ ፍቅር ጋር ወደ ሥራው ይሄዳል፡፡ ሥራዋን ለማከናወን የተነሳችው እናትም አባት በሌለበት ጊዜ ልጆቿን በተመለከተ የተጣሉባትን ግዴታዎች ትገነዘባለች፡፡ የምትኖረው ለባለቤቷ እና ለልጆቿ እንደሆነ ይሰማታል፡፡ ልጆቿን በትክክል በማሰልጠን፣ መሻትን መግዛትንና ራስን መቋጣጠርን በማስተማር፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ያላቸውን ኃላፊነት በማስተማር፣ በዓለም ውስጥ ጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ የግብረገብ ደረጃን ከፍ ለማድረግ እና የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያከብሩና እንዲጠብቁ ብቁዎች እያደረገች ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምትፈራ እናት ልጆቿን በትዕግስት እና ባለመሰልቸት፣ ጨካኝና አሰልቺ በሆነ ሁኔታ ሳይሆን በፍቅር እና በገርነት፣ መስመር በመስመር እና ጥቅስ በጥቅስ እየሰጠች በማስተማር ታሸንፋቸዋለች፡፡ እሷ የምትሰጣቸውን የፍቅር ትምህርቶች ልብ ይላሉ፣ የትምህርት ቃላቶቿንም በደስታ ይሰማሉ፡፡ {2SM 438.1}Amh2SM 438.1

    በጫጫታቸው እንዳትረበሽ እና እነርሱ ትኩረት ማግኘት በሚፈልጓቸው በተለያዩ ነገሮች ከመቸገር ብላ ልጆቿን ከፊቷ ከምታርቅ ይልቅ ጊዜዋን እነርሱን ለማርካት እና እረፍት የለሽና ንቁ የሆነ አእምሮአቸውን ወደ ጨዋታ ወይም ቀላልና አስደሳች ወደ ሆነ ሥራ ለመመለስ ከመጠቀም ለተሻለ ነገር ማዋል እንደማትችል ይሰማታል፡፡ እናት ለልጆቿ አስደሳች የሆነ ጨዋታን ለመፈልሰፍ ለምታደርገው ጥረት ዋጋዋን ታገኛለች፡፡ {2SM 438.2}Amh2SM 438.2

    ለጋ ልጆች ከሌሎች ጋር ግንኙነት መፍጠርን ይወዳሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ለብቻቸው መሆን አያስደስታቸውም፡፡ እናት ይህ ተሰምቷት አብዛኛውን ጊዜ እቤት በሚሆኑበት ሰዓት እሷ ባለችበት ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ ማድረግ አለባት፡፡ ያኔ አጠቃላይ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ ትችላለች፣ በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥሮ ጥያቄ ወደ እሷ ሲመጣ እነዚህን ትንንሽ አለመግባባቶች ለማስተካከልም ትዘጋጃለች፣ የስህተት ልምዶችን ወይም የራስ ወዳድነት ምልክቶችን ወይም ኃይለኛ ስሜትን በማረም አእምሮአቸውን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መመለስ ትችላለች፡፡ ልጆች እነርሱ የሚወዱትን ነገር እናታቸውም ትወደዋለች ብለው ስለሚያስቡ ግራ በሚገባቸው በትናንሽ ነገሮች እንኳን እናታቸውን ማማከራቸው ተፈጥሮአዊና ትክከል የሆነ ነገር ነው፡፡ እናት ለጉዳዩ ግድ የለሽ በመሆን ወይም እነዚህን በመሰሉ ጥቃቅን ነገሮች መረበሽን እምቢ በማለት የልጆቿን በቀላሉ የሚነካውን ልብ ማቁሰል የለባትም፡፡ ለእናት ትንሽ የሚመስለው ነገር ለእነርሱ ትልቅ ነው፡፡ በትክክለኛ ጊዜ የሚሰጥ የመመሪያ ወይም የማስጠንቀቂያ ቃል ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የሚያደርጉትን ነገር ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ እይታ፣ ከእናት የሚወጣ የማበረታቻ ወይም የሙገሳ ቃል ጨቅላ ለሆነው ልባቸው ቀኑን በሙሉ የጸሐይ ጮራን ይፈነጥቃል፡፡ {2SM 438.3}Amh2SM 438.3

    ልጆች በልጅነታቸው ከእናታቸው ማግኘት ያለባቸው የመጀመሪያው ትምህርት የአካል ጤናን የሚመለከት መሆን አለበት፡፡ እንዲመገቡት መፈቀድ ያለበት ምግብ ጤንነታቸው በጥሩ ሁኔታ እንዲጠበቅ ማድረግ የሚችል ቀላል ምግብ መሆን አለበት፡፡ ይህ ምግብ መወሰድ ያለበት በተወሰነ ጊዜ ሆኖ በቀን ከሶስት ጊዜ በላይ መሆን የለበትም፡፡ በቀን ሶስት ጊዜ ከመመገብ ይልቅ ሁለት ጊዜ መመገብ ይሻላል፡፡ ልጆች በትክክል ስርዓትን ቢማሩ ኖሮ በማልቀስና በመነጫነጭ ምንም ነገር እንደማያገኙ ወዲያውኑ ይማሩ ነበር፡፡ ብልህ እናት ልጆቿን ስታሰለጥን የራሷን የአሁኑን ምቾት ብቻ በመመልከት ሳይሆን የልጆቹን የወደፊት መልካም ነገር በመመልከት የምታደርገውን ታደርጋለች፡፡ ይህን ስታደርግ ልጆቿ የጤና መርህን ተከትለው እንዲበሉ፣ እንዲጠጡ እና እንዲለብሱ በማድረግ የምግብ ፍላጎትን የመቆጣጠርን እና ራስን የመካድን ጠቃሚ ትምህርት ታስተምራለች፡፡ {2SM 439.1}Amh2SM 439.1

    በደንብ ሥርዓት የተማረ፣ እግዚአብሔርን የሚወድ እና የሚታዘዝ ቤተሰብ ደስተኛ ይሆናል፡፡ አባት ከእለት ተግባሩ ሲመለስ በሥራው ቦታ ያጋጠሙትን ግራ መጋባቶች ወደ ቤት አያመጣቸውም፡፡ ቤት እና የቤተሰብ ክበብ አስደሳች ባልሆኑ ግራ መጋባቶች መበላሸት የሌለበት የተቀደሰ ክበብ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡ ከቤቱ ወጥቶ ሲሄድ አዳኙንና ኃይማኖቱን እቤቱ ትቶ አልሄደም፡፡ ሁለቱም ጓደኞቹ ናቸው፡፡ የቤቱ ጣፋጭ ተጽዕኖ፣ የባለቤቱ በረከት እና የልጆቹ ፍቅር ሸክሞቹን ስለሚያቀሉለት ወደ ቤቱ የሚመለሰው ልቡ በሰላም ተሞልቶ፣ እርሱን በደስታ እንኳን ደህና መጣህ ብለው ለመቀበል እየጠበቁ ላሉት ሚስቱና ልጆቹ በደስታ የተሞሉ የማደፋፈሪያ ቃላት ይዞ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእሱና ለሚወዳቸው ቤተሰቦቹ በቀኑ ውስጥ ሳይሰለች ላደረገላቸው ጥንቃቄ ምሥጋናን ለማቅረብ በጸሎት መሰዊያ ላይ ከቤሰቡ ጋር ዝቅ በሚልበት ጊዜ የእግዚአብሔር መላእክት በክፍላቸው ውስጥ ያንዣብባሉ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ወላጆች የሚያቀርቡትን ልባዊ ጸሎት እንደ ጣፋጭ እጣን ወደ ሰማይ ይወስዳሉ፡፡ የእነዚህ ጸሎቶች መልስ የሚመጣው በረከት ይዞ ነው፡፡ {2SM 439.2}Amh2SM 439.2

    ጨጓራን የሚጎዳን የምግብ ጣዕም ብቻ መከተል ኃጢአት መሆኑን ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮ ላይ ማስረጽ አለባቸው፡፡ አካላዊ የጤና ሕጎችን በመጣስ በፈጣሪያቸው ላይ ኃጢአት እንደሚሰሩ በአእምሮአቸው ማስረጽ አለባቸው፡፡ በዚህ መልክ የተማሩ ልጆች ለመቆጣጠር ከባድ አይሆኑም፡፡ ቁጡ እና ተለዋዋጭ ለሆኑ ጸባዮች ተገዥ አይሆኑም፣ በሕይወት ለመደሰት በተሻለ ሁኔታ ይሆናሉ፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ልጆች የግብረገብ ግዴታዎችን በፍጥነትና በግልጽ ይረዳሉ፡፡ ፈቃዳቸውንና ምኞታቸውን ለወላጆች ማስገዛትን የተማሩ ልጆች በቀላሉና በፍጥነት ለእግዚአብሔር ፈቃዳቸውን ያስገዛሉ፣ በክርስቶስ መንፈስ ቁጥጥር ሥር ለመሆንም ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ብዙዎች ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ሸክም እንዲበዛባት የሚያደርጉ ብዙ ፈተናዎች ያለባቸው ምክንያት በልጅነታቸው በትክክል ስላልሰለጠኑ እና በከፍተኛ ደረጃ የራሳቸውን ባሕርይ እንዲመሰርቱ ስለተተዉ ነው፡፡ የስህተት ልምዶቻቸው እና ልዩ የሆኑ፣ ደስታ የሌለባቸው ጸባዮቻቸው እርምት አልተሰጣቸውም፡፡ ፈቃዳቸውን ለወላጆቻቸው እንዲያስገዙ አልተማሩም፡፡ በልጅነት ጊዜ ያገኙት ስልጠና በመላው ኃይማኖታዊ ልምምዳቸው ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል፡፡ ቁጥጥር አልተደረገባቸውም፡፡ ሥነ-ስርዓት ሳይማሩ አድገዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ፣ አሁን፣ በኃይማኖታዊ ልምምዳቸው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ለተሰጠው ንጹህ መርህ መገዛት ይከብዳቸዋል፡፡ ስለዚህ ወላጆች መንፈሳዊ ልምምዳቸውን በተመለከተ ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት በላያቸው እንደሚያርፍ መገንዘብ አለባቸው፡፡ {2SM 440.1}Amh2SM 440.1

    የጋብቻ ግንኙነት እግዚአብሔር ከሰጣቸው የተቀደሱ ስርዓቶች መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች በእሱ ቅዱስ ቃል በመጠበቅ በሕሊና ዳኝነት ቁጥጥር ስር ይሆናሉ፡፡ የጋብቻ ግንኙነት የሚያስገኘው እያንዳንዱ ዕድል የሚያስከትለውን ውጤት በጥንቃቄ ይመለከታሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ልጆች እንዲጠነቀቁላቸው እና ድምቀታቸው መታየት እንዲችል ስነስርዓትን በማስተማር ከባሕርያቸው ውስጥ ሸካራነትን እንዲያስወግዱ እግዚአብሔር የሰጣቸው ውድ እንቁዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል፡፡ እነዚህ ልጆች በሕይወታቸው መልካም እንዲያደርጉና በመጨረሻም ከፍ ላለው ሕይወትና ለተሻለው ዓለም ገጣሚዎች እንዲሆኑ፣ በእግዚአብሔርና በበጉ ፊት ለዘላለም እንዲያበሩ፣ ባሕርያቸውን ለመመስረት ከበድ ያሉ ግዴታዎች እንዳሉባቸው ይሰማቸዋል፡፡ How to Live, No. 2, pp. 25-48.Amh2SM 440.2

    Larger font
    Smaller font
    Copy
    Print
    Contents